የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5

የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ?  ትምሕርት 5

ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው እነሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።” የሚለው ቃል እጅግ ብዙ መረጃዎችን የያዘ ክፍል ነው። እነዚህ “ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ” የተባለላቸው ኔፊሊምና ዘሮቻቸው ታላቅነታቸው፣ ታዋቂነታቸውና ኃያልነታቸውና ዛሬ እንደምናስበው አልነበረም። ይህን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች በሚገባ እናስተውል።

1ኛ) ኔፊሊምና ዘሮቻቸው በአካል እጅግ ትልልቅ ነበሩ። ግዙፍነታቸው በሰው ልጆች መካከል አልፎ አልፎ ከምናየውና “ትልቅ” ከምንለው የማይወዳደር ነበር። የብሉይ ኪዳን መጻህፍት ይህንን በቀጥታ ያስተምሩናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ደግሞ ጥንታዊ የሆኑና በአንዳንዶቹ የጌታ ሃዋርያት መልእክቶች ውስጥ በተዘዋዋሪ ተጠቅሰው ያሉ የጥንት መጻህፍት የነዚህ የኔፊሊምና ዘሮቻቸው ቁመት እስከ ሰላሳ ጫማ (እስከ ዘጠኝ ሜትር) እና በላይ እንደነበር ይናገራሉ። የኔፊሊም ጉዳይ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን የነበሩ አይሁድና የአካባቢው አገሮች ህዝቦች፣ በተለይም ደግሞ የጌታ ደቀመዛሙርትና አብዛኛው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የዋና ዋናዎቹ የአህዛብ መንግስታት መሪዎች ሁሉ የሚያውቁት ጉዳይ ነበር። ልብ ብለን ካስተዋልን እና ከመረመርን ይህን ነገር ጌታ ኢየሱስ ራሱም ሰይጣንን፣ አጋንንትን እና የጨለማውን መንግስት ኃይል በተመለከተ ባስተማራቸው ብዙ ትምህርቶች ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት አንዳንዴም በግልጽ ተናግሮታል። ይህንን ለመረዳት ታዲያ የትምህርቶቹን አውድ፣ ያስተማረበትን ቦታ፣ ተማሪዎቹን እና የትምህርቶቹን ዋነኛ ቁም ነገር መረዳት ያሻል። በዚህ በኛ ዘመን ደግሞ ቁመታቸው እስከ ከ 9 እስከ 15 ጫማ የሆኑ የኔፊሊም ዘሮች አጽሞች በምድር ላይ መኖራቸው ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት በብዙ ጋዜጦችና መጻህፍት እንዲሁም ፊልሞች ተዘግቧል።

መጽሐፍ ቅዱስም  ቁመታቸው እስከ 9 ክንድ (ከአምስት ሜትር በላይ) የነበሩ የኔፊሊም ዘር መኖራቸውን በማስረጃ አስደግፎ ከሚናገርባቸው ስፍራዎች አንዱ የእስራኤል ህዝብ ድል የነሱት የባሳን ንጉስ ዐግ ነበር። ይህ ሰው ርዝመቱ 9 ክንድና ስፋቱ 4 ክንድ (ማለትም 5 ሜትር ከ49 በ 2 ሜትር ከ44) በነበረ የብረት አልጋ ላይ ይተኛ እንደነበር በዘዳግም 3 ቁጥር 11 ላይ ተዘግቧል። የአልጋው ቁመትና ስፋት ብቻ ሳይሆን፣ አልጋው በዚያ ዘመን ከብረት መሰራቱም ብዙ ምስጢሮችን ያስተምረናል። አንደኛ የሰውየው ክብደት እጅግ ብዙ ነበር ማለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ ብረት ውድ ስለነበር ብዙው ነገር በነሃስ በሚሰራበት ዘመን በብረት አልጋ ላይ መተኛትም ትልቅ ክብር ነበር።
የኔፊሊም ግዙፍነት የቁመት ጉዳይ ብቻ አልነበረም። ዛሬ ለምሳሌ ቁመቱ 6 ጫማ የሆነና ወፍራም የተባለ አንድ ረጅም ሰው፣ ክብደቱ በአማካይ ቢበዛ ከ200 ኪሎ አይበልጥም። ከአራት ዓመት በፊት በአፍጋኒስታን ተራሮች ዋሻ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች የተገደለ አንድ ግዙፍ ፍጥረት (የኔፊሊም ቅሪት ተብሎ የሚገመት) ግን ክብደቱ ከ 1100 ፖውንድ በላይ ወይም 500 ኪሎ እንደነበር ተዘግቧል። ልብ እንበል ይህ ፍጥረት ቁመቱ 9 ጫማ ብቻ ነው። የባሳን ንጉስ ዐግ ግን ቁመቱ 9 ክንድ ወይም ከ 18 ጫማ  በላይ ነበር። (አንድ የመጽሃፍ ቅዱስ ጫማ 61 ሳንቲ ሜትር ወይም ከ ሁለት ጫማ በላይ ነው)። ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ክብደቱ ከ2500 ፓውንድ ወይም 1000 ኪሎ በላይ ይሆናል ማለት ነው።  ዐግ ይኖርባት የነበረችው የጥንቷ የባሳን ከተማ ዛሬ TELL ASHAREH ልትሆን እንደምትችል ተዘግቧል። በዚያች ከተማ ዛሬም ቢሆን በጥንት ዘመን የተሰራ ከፍታው 70 ጫማ የሚሆን የአፈር ክምር (ድልድል) አለ። እንደዚህ ያሉ ድልድሎችን ኔፊሊምና ዘሮቻቸው እንደ መቃብርና እቃዎቻቸውን ለመሸሸጊያ ይጠቀሙበት እንደነበር ሌሎች የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ኦሪት ዘሆልቁ 13:32 እና 33 ደግሞ አስራ ሁለቱ የእስራኤል ሰላዮች የከነዓን ምድር ከኔፊሊም ወገን በሆኑና ግዙፍ ሰዎች የተሞላ እንደነበር ዘግበዋል። የባሳንን ንጉስ ዐግን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ 22 እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሰዎች (የኔፊሊም ዘሮች) ነበሩ የኔፊሊም ዘር የነበራቸው ጎሳዎች ደግሞ ወደ 36 ይደርሳል።

2ኛ) ኔፊሊምና ዘሮቻቸው ይህንን ያህል ግዙፍ ከሆኑ ምን አይነትና ምን ያህል ምግብ እንደሚበሉም መገመት ያስፈልጋል። ያንን የምግብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የምድርን ተክሎች እና እንስሳትን ያለአገባብ በማዳቀልና በመበከል ተግባሮች ላይ በመሰማራት የእግዚአብሔርን ፍጥረት ማበላሸትና ማጥፋት ይዘው እንደነበር የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎችም የታሪክ መረጃዎች ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ አስራ ሁለቱ የእስራኤል ሰላዮች ምድሩን ሰልለው ሲመለሱ ከኤሽኮል ሸለቆ አንድ የወይን ዘለላ ቆርጠው ለናሙና አምጥተው ነበር። ይህ ቆርጠው ይዘው የመጡት የወይን ዘለላ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በመሎጊያ (ሽመል) ላይ ተደርጎ በሁለት ሰዎች ትከሻ መካከል ተንጠልጥል መምጣት ነበረበት። ማለትም ቢያንስ ይህ አንድ ዘለላ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ድረስ ሊህን ይችላል ማለት ነው። ፍጥረታትን ከመበከልም አልፈው እነዚህ ፍጥረታት እጅግ የሚዘገንነው ሰውንና የራሳቸውን ዘር የመብላት ልማድ እንደነበራቸው የሚገልጽ ታሪክ አለ።






ባለፉት ስድሳና ሰባ ዓመታት ከምድር ላይ ረሃብንና በሽታዎችን እናጠፋለን በሚል ሰበብ የሚካሄዱት ተክሎችን፣ እንስሳትንና የሰውንም ዘር ሳይቀር ያለ አገባብ ለመቀየር የሚካሄዱት ስራዎች ምናልባት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት እንደገና ምድር ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለማመጽ የመነሳሳቷ ምልክቶች ይሆኑ ?! ከልክ ያለፈ በማዳበሪያ፣ በሆርሞንና በተለያዩ ሰው ሰራሽ መርዛማ ንጥረ ነገሮች የተበከሉ ምግቦች እንዲሁም ደግሞ አዋቂ ነን የሚሉት የዘራቸውን መሰረት የለወጧቸው ተክሎችና እንስሳት (Genetically Modified Organisms ወይም GMOs) በሰው ዘር ህይወትና ጤንነት ላይ እያመጡት ያለው ጣጣ ገና ካሁኑ እጅግ ብዙ ሆኗል። በእኛ ዘመንም እንኳን የምንጠቀምባቸው ድንቅ የተባሉ መርዞች የምድርን ንብ መፍጀታቸውና ይህም ለምድር ሁሉ አስጊ መሆኑ ዜና ከሆነ ውሎ አድሮአል። በሽታን ይከላከላሉ ተብለው በክትባት ውስጥ የሚጨመሩ እንደ ሜርኩሪ ያሉ ከባድ ብረቶች፣ ንጥረ ነገሮችና ቅመሞች እጅግ ብዙ ህዝብን ለካንሰርና ለሌሎችም በሽታ እያጋለጡ መሆናቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው።

3ኛ) ኔፊሊም  በአካል ግዙፍ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ልጆችም እጅግ የበለጠ እውቀት፣ ኃይልና ቴክኖሎጂም ነበራቸው። ከሰዎች ሴቶች ልጆች የወለዱአቸው አባቶቻቸው የወደቁ መላእክት ስለነበሩ ነፊሊም አማልክት ነን ብለው የሰው ልጆችን እንደባሪያ መግዛት የሚያስችሉአቸውን የተከለከሉ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎችን ሰጥተዋቸው ነበር። ልብ እንበል የነዚያ የኔፊሊምና የአባቶቻቸው ሁሉ ዋነኛ አለቃ ሰይጣን ዓላማ የጌታ የእግዚአብሔርን ቦታ መውሰድ ነበር። ይህ ስለማይሆንለት ደግሞ ጌታ አምላክ በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን የሰውን ልጆች ለመግዛትና ለማጥፋት ተነሳሳ።  ይህንን ኃይላቸውንና የላቀ እውቀታቸውን በመጠቀም ከላይ እንዳየነው የሚፈልጉትን ምግብን ለማግኘትና በክፋትም ጭምር የእንስሳትንና የተክሎችን ምንነትና ባህርይ በመቀየር (HYBRIDIZATION and GENETIC ENGINEERING) ተግባር ላይ ተሰማርተው ነበር። በነሱ አስተሳሰብ ተራ የነበረው የሌላው ህዝብ ቁጥር እንዳይበዛ ደግሞ ጽንስን ማስወረድን እና የመገዳደያ መሳሪያዎችን አሰራር ለሰዎች ያስተማሩ እነሱ እንደነበሩ የሚያስረዱ ብዙ መረጃዎች አሉ። ከነሱ ሰውነት ጋር የሚሄዱ እጅግ ታላላቅ ህንጻዎችን፣ መድረኮችን፣ መሰዊያዎችን፣ ፒራሚዶችን፣ ዋሻዎችን እና የዋሻ መንገዶችን ይሰሩ ነበር። ሰውነታቸው እጅግ ትልቅ ስለነበር ትልልቅ ድንጋዮችን መቁረጥና ማንቀሳቀስ ይችሉ ነበር። ዛሬ ካሉን ቴክኖሎጂዎችም የላቀ የምህንድስና፣ የግንባታ፣ የኃይል ምንጭና የማጓጓዣ ቴክኖሎጂ እንደነበራቸው ይታመናል። ለምሳሌ የምድርን የስበት ኃይል የሚቋቋም (ANTI GRAVITY) የማንሳፈፍ ችሎታ እንደነበራቸው ይታመናል። ለዚህ ይሆን ዛሬም በአጋንንት ሥልጣን ተሰጠን የሚሉ ሰዎች እቃዎችን የሚያንሳፍፉት? የሰላቢ መንፈስ የሚባለውስ ከዚህ ጋር የተያያዘ ይሆን? ምናልባት እነዚያ ኔፊሊም እንደገና ወደምድር መምጣት ስለጀመሩ ይሆን በብዙ ሺ ዓመታት እንኳን ያልደረስንበትን ቴክኖሎጂ በድንገትና በፍጥነት ባለፉት ከ100 በማይበልጡ አመታት ያገኘነው?? ምናልባት እነሱ እንደገና ብቅ ብቅ ማለት ስለጀመሩ ይሆን ታላላቆቹ የምድር መንግስታትና ህዝቦች ሁሉ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ለማለት ጌታ አምላክን እየተዳፈሩ ያሉት? በሚቀጥሉት ትምህርቶች ላይ ይህንን በበለጠ ዝርዝር እንመለከታለን።

4ኛ) በአፈታሪክ አማልክትና ታላላቅ የጥንት ነገስታት ተብለው እስከዛሬ ድረስ በየትምህርት ቤቱና በየዩ
ኒቨርሲቲው ታሪካቸው እንደትምህርት የሚሰጥላቸው የግሪኮቹ አይሲስና ኦሳይሪስ፣ የባቢሎኖቹ በአል፣ አስታሮትና፣ ታሙዝ፣ የግሪኮቹ አፖሎና አቴና፣ የሮማውያኑ ጁፒተርና ማርስ ወዘተ በሙሉ የኔፊሊም ዘሮች ነበሩ። በታሪክ ሲያስተምሩን ግን ስማቸው ብዙና የሰው የሚመስል የፈጸሙት ጀብዱ ግን ሰው ሊያደርገው የማይችል ነው።  ሊያሳምኑን እንደሚፈልጉት ታዲያ እነዚህ ሁሉ የሰው ሃሳብ የወለዳቸው ተረት ተረት ሳይሆኑ በርግጥም በአካል የነበሩ ፍጥረታት ናቸው። እነዚህን አማልክት ነው ዳዊት በመዝሙር 95(96) ቁጥር 5 ላይ “የአሕዛብ አማልክት አጋንንት ናቸውና እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሰራ።” የሚለው። ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መረጃ አለው። ለዚህም ነው በየዘመኑ የተነሱ አምባ ገነኖች፣ የሃሰት ሃይማኖት መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ ነቢያትን፣ ሃዋርያትን እና እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ይጥሩ የነበረው። ነገር ግን ብርሃን በጨለማ ይበራል ጨለማውም አላሸነፈውም።

5ኛ) የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ፈቃድ በመጣስና የተሰጣቸውን የክብር ስፍራ በመተው ወደ  ምድር በመውረድና ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ዘራቸውን ያደባለቁት የወደቁት መላእክት ከመውደቃቸው በፊት ስማቸው “የእግዚአብሔር ልጆች” ወይም በእብራይስጥ “הָֽאֱלֹהִים֙ בְּנֵ֤י”  (ብነይ ሃ ኤሎሂም) ነበር። ከወደቁ በኋላ ግን እነሱም ልጆቻቸውም ኔፊሊም ይባላሉ። በእብራይስጥ ኔፊሊም ማለት “የወደቁት” ማለት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስና ይሁዳ እንደ ጻፉት እነዚያ የወደቁት መላእክት ዛሬ በጨለማ ጉድጓድ ውስጥ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ታስረዋል። የመጀመሪያዎቹ የወደቁት መላእክትና በኖህ ዘመን ከነሱና ከሰው ልጆች ሴቶች የተወለዱት ልጆቻቸው ደግሞ በጥፋት ውኃ ጠፍተዋል። ከዚያም በኋላ ሌሎች የወደቁ መላእክት ይህንኑ በደል እንደገና እንደፈጸሙ ዘፍጥረት 6  እና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ያስተምሩናል። እነዚህ ግዙፍ፣ ኃያላንና እኩያን ፍጥረታት (ኔፊሊምና ዘሮቻቸው) ሙሉ በሙሉ ሰብዓዊ ፍጥረት አይደሉምና ሲሞቱ ነፍሳቸውና መንፈሳቸው ወደ ፈጣሪ (ወደ እግዚአብሔር) መመለስ አይችልም። ስለዚህ በዚሁ በምድር ላይ ይቅበዘበዛሉ። እነዚህ ናቸው አጋንንት የተባሉትና ሁል ጊዜ አካልን ለመልበስ ስለሚናፍቁ ወደ ሰዎች ውስጥ መግባት የሚፈልጉት። በወንጌል ላይ እንደምናነበው፣ ጌታ ከፈቀደላቸው እነዚህ የሞቱት የኔፊሊም መንፈሶች ወደ አሳማዎችም ውስጥ ቢሆን ለመግባት ደስተኞች ናቸው።እንስሶች ግን ሊሸከሙአቸው ስለማይችሉ ወደ  ባህርም ሆነ ወደ እሳት ገብተው ይሞታሉ። ለዚህ ነው አጋንንት ወደሰዎች ሲገቡ ሰዎች የሚታመሙት፣ እጅግ ክፉ የሆነ ነገርን የሚፈጽሙት፣ በተለያየ መንገድም ራሳቸውን ለማጥፋት የሚፈልጉት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት በርሱ ላይ ለሚያምኑ ሁሉ በነዚህ እኩይ መናፍስት ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጥቷል። በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ዳግም ለተወለዱና ለሚከተሉት ለደቀ መዛሙርቱ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤  “እንዲህም አላቸው፣ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጎዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” ሉቃስ ምዕ 10 ቁ 18፣20። ማንኛውም በዚህ ሰማያዊ ሥልጣን መኖር የሚሻ የክርስቶስ ተከታይ ሁሉ ታላቅ ኃላፊነት አለበት። ኃላፊነቱም የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቆ መረዳት፣ ለተገለጠለትም የቃሉ እውነትና ለመንፈስ ቅዱስ አመራር ሁሉ በመታዘዝና የእግዚአብሔርን ሥም በሚያከብር አካሄድ መኖር ነው።  


ኔፊሊምን ከሰዎች ሴቶች ልጆች የወለዱት እነዚያ የወደቁት መላእክት እነማን ናቸው፣ መላእክት አካል አላቸው ወይ፣ ይህንንስ ከላይ የተገለጸውንስ ማድረግ ይችላሉ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በትምህርት 6 ላይ እንመለከታለን። አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ።

1 አስተያየት:

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...