የኑክሊየር ፍንዳታ ቢሆን እንዴት ማምለጥ ይቻላል የሚናገሩ ዜናዎች እየጨመሩ ነው። ለምን?!



ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ በFACEBOOK መልእክቶቼ እንደ ጻፍሁትና በመለከት ድምጽ ቁጥር 7 ላይ በበለጠ ዝርዝር ላቀርብ እንደሞከርሁት፣ በዓለም ዙሪያ የጦርነት ወሬ እጅግ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ብቻ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በአገሪቱ የመሳሪያ ሽያጭ ታሪክ (በአንድ ጊዜ ለአንድ አገር) ትልቁ የሆነውን የሶስት መቶ ሃምሳ (350) ቢሊዮን ዶላር የተራቀቁ መሳሪያዎች ሽያጭ ውል ከሳውዲ አረቢያ ጋር እንደተፈራረመች ሰምተናል። ዛሬ በሰው ዘር ላይ እያንዣበበ ያለው የጦርነት ደመና በአንድ አካባቢ፣ በአንድ አገር ወይም ክፍለ ዓለም ብቻም አይደለም። በታላላቆቹ የዓለም መንግስታት መካከል ያለው ውጥረትና አለመተማመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙ አዋቂዎችና መሪዎችም ሳይቀር ሲያስጠነቅቁ ውሎ አድሮአል። ምን ዓይነት መረጃ እንዳላቸው ባናውቅም፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ብዙ ጊዜ ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ እንደ CNN ያሉ የዜና አውታሮች ሳይቀሩ የኑክሊየር ቦምብ በአካባቢያችሁ ቢፈነዳ ለመትረፍ ይህን ወይም ያንን አድርጉ፣ አታድርጉ የሚሉ ዜናዎችንና ቅንብሮችን ማቅረብ ጀምረዋል። ለምሳሌ የCNN ድረ ገጽ ባለፈው MARCH 17 2017 ላይ ይህን የሚመለከት ዜና አቅርቦ ነበር። በሚቀጥሉት አጫጭር መልእክቶች ላይ ከነዚህ ዜናዎች አንዳንዱን አካፍላችኋለሁ። ከዚህ መልእክት ጋር ተያይዞ የሚገኘውና BUSINESS INSIDER በሚባለው የታወቀ ድረገጽ ላይ የቀረበው ዜና መሰል ሪፖርት ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የተጻፈው መኪና ላላቸውና በመኪና ለማምለጥ ለሚሞክሩ ሰዎች ቢመስልም፡ ሁሉ ሰው ሊያነበው ያስፈልጋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብሎ፣ ከአምላኩና ከሌሎችም ጋር ታርቆና ሰላሙን ይዞ የሚኖር ሰው ምንም ነገር አያስፈራውም። ክርስቲያን ሊፈራ የሚገባው ስጋን መግደል ብቻ ሳይሆን ነፍስንም በገሃነም ሊጥል የሚችለውን አንዱን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ (ዘጸዓት3፡15)  የሆነውን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። በዚህ ክፉ ዘመን ሌላ መሸሸጊያ የለም። ዓለምን ብዙ ጊዜ የሚያጠፋ የኑክሊየር መሳሪያዎች ያላቸው ታላላቆቹ አገሮችም ቢሆን የማጥፋት እንጂ የራሳቸውንም ህዝብ የማዳን አቅሙ የላቸውም። ምናልባት ታላላቆቹ ባለጸጎችና መረጃው ያላቸው አዋቂዎችና ዋና ዋና ባለስልጣኖች በምድር ውስጥ በሰሩአቸው የኑክሊየር ታዛዎች በመጠለል ወይም መሳሪያዎቹ አይመቱአቸውም ወደሚባሉ ቦታዎች ቀድመው በመሸሽ ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። እንደኔና እንደናንተ ያለው ተራው ህዝብ ግን ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ተስፋ የለውም። ይህ ነገር በእርግጥም ከተፈጠረ አዋቂዎቹ የሚሰጡትን ምክር መስማትና ከተቻለም መከተል ጥሩ ነው። ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ሳይሆን ገና ጊዜ ሳለ ከልባቸው ተስፋ የሚያደርጉትንና እምነታቸውን በሱ ላይ የሚጥሉትን የሚያድንና የሚታደግ፣ ችሎታው፣ ፍላጎቱና ፍቅሩ ያለው አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ አለ። ወደሱ የመቅረቢያው ዋነኛ መንገድ ደግሞ ልጁ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወደ እርሱ የመጠጋትና የማምለጫው ጊዜ ደግሞ ዛሬ ነው። ኢንሹራንስ የሚገዛው አደጋው ሲፈጸም ሳይሆን ቀደም ብሎ ነው። ነገም እንደ ዛሬ ይሆናል። የዚህ ዓይነት ወሬ ከዚህም በፊት ሰምተናል፣ ምንም አይሆንም እያልን ቀኑ አይለፍብን። ሰላም እንዲሆን የሁላችንም መሻትና ጸሎት ነው። ነገር ግን የነፍሳችንን ብቸኛ ኢንሱራንስ፣ ለዚያውም ምንም ክፍያ የሌለበትንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ፣ በደሙ የዋጀልንን የምስራች ወንጌል ዛሬ እንጨብጥ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አእምሮ ፖሊስ (ሮቦኮፕ) በዱባይ ስራቸውን ጀመሩ


ባለፈው ሳምንት በላክሁት መልእክት ላይ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሰው ሰራሽ አእምሮ (Artificial Intelligence) ዛሬ በሰው ልጆች ከሚሰሩት ስራዎች ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆኑትን እንደሚወስዱ የሚናገር ዜናን አያይዤ ነበር። እነዚህ በ AI የሚወሰዱ ስራዎች ደግሞ ማሽኖች መስራት ይገባቸዋል ወይም ሊሰሩአቸው ይችላሉ ብለን የምናስባቸውን እንደ ጽዳት፣ እቃ መጫንና ማውረድ የመሳሰሉትን ብቻ ሳይሆን እኛኑ ራሳችንን የሰው ልጆችን ማስተዳደርም ሊሆን እንደሚችል ጠቆም አድርጌ ነበር። በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምታነቡት ታዲያ የተባበሩት የዓረብ ኤሚሬቶች ዋነኛዋ የንግድ ከተማ ዱባይ የመጀመሪያውን የAI ፖሊስ በስራ ላይ አሰማርታለች። በሚቀጥሉት 13 ዓመታትም ከዱባይ የፖሊስ ሃይል 25 በመቶው በነዚሁ AI ፖሊሶች (ሮቦኮፕስ) እንደሚሆን ብርጋዲዬር ጀነራል ካሊድ ናሲር አል ራዙቂ የሚባሉት የዱባይ ፖሊስ የዘመናዊ ወይም የተራቀቁ አገልግሎቶች ዲሬክተር ጀነራል ተናግረዋል። የሚቀጥለው የሮቦት ሹመት ደግሞ ምን ይሆን?! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ

ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ
ከሃያ ዓመት በፊት አብዛኛው የምድር ህዝብ በእጅ በሚያዝ ስልክ ብቻ መነጋገር፣ መጻጻፍ፣ ፎቶና ቪዲዮ ማንሳት፣ የሚፈልገውን መገብየት፣ ስለአየር ንብረት መረጃን ማግኘት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ ሙዚቃ መስማት ወዘተ ይችላል ተብሎ ቢነገር ብዙም የሚያምን ሰው አልነበረም።  ከአምስት ዓመታት በፊት ደግሞ የሰው ሰራሽ አእምሮ (ARTIFICIAL INTELLIGENCE) ሰዎች የሚሰሩትን ስራ ሁሉ ይወስዳል ቢባል ብዙው ሰው ይስቅ ነበር። አሁን ግን እዚያ ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህን የሚጠራጠር የተያያዘውን ዜና እና ሌሎችንም ብዙ መሰል ዜናዎችን ማንበብ ይችላል።
የሰው ሰራሽ አእምሮ የሚባለው በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎች የሚሰሩት ኮምፒውተሮችን የሚቆጣጠርና የሚያንቀሳቅስ ፕሮግራም ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም እየተራቀቀ ከመምጣቱ የተነሳ ብዙ ነገሮችን የመማርና የተማረውንም ስራ ላይ የማዋል ችሎታ አለው። ለምሳሌ GOOGLE የሚባለው አገልግሎት፣ FACEBOOK እና ሌሎችም በኮምፒውተርና በዓለም አቀፉ መረብ ላይ የሚሰሩ አገልግሎቶች ይህንን የሰው ሰራሽ አእምሮ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ። የኮምፒውተሮች የማስላት፣ መረጃን የማከማቸትና የማስላት ችሎታ እጅግ እየጨመረ በሄደ መጠን ይህ ቴክኖሎጂም በከፍተኛ ደረጃ እየተራቀቀ መጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለሰው ሊሰሩ አይችሉም ይባሉ ስራዎችን መስራት ጀምሮአል። ከዚያም አልፎ ሰዎች ሰዓታት፣ ቀናትና ሳምንታት ፈጅተው አንዳንዴም ከብዙ ስህተቶች ጋር ይሰሩአቸው የነበሩ ስራዎችን በጥቂት ሰከንዶች ወይም ደቂቃዎች ውስጥ በማከናወን ጊዜንና ገንዘብን እንደሚቆጥቡ በሰፊው እየተነገረ ነው። ብዙ የንግድና የመንግስት ድርጅቶችም ይህን ቴክኖሎጂ በሰፊው ለመጠቀም እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።
ሰው ሰራሽ አእምሮ ዛሬ የሚሰራው በሮቦት ውስጥ ወይም በኮምፒውተሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። ዛሬ እንደ ሰዓት፣ መነጽር፣ ልብስና ጫማ ያሉ በሰውነታችን ላይ የምንለብሳቸው ወይም የምናደርጋቸው ነገሮች፣ የምንነዳቸው መኪናዎች፣ በእጃችን የምንይዛቸው ስልኮች ማቀዝቀዣዎችና ሌሎችም ቁሶች በዚህ ቴክኖሎጂ እየተሞሉ ነው። የዛሬዎቹ የእጅ ስልኮች ተዘግተው እንኳን ሳለ የምንነጋገረውንና የምንሰማውን እያዳመጡ መረጃን ስለሚልኩ በጓዳ ጎድጓዳችን የምንነጋገረው ሳይቀር ለስለላና ለነጋዴዎች ማስታወቂያ አገልግሎት ይውላል። በሰው ሰራሽ የተሞሉት የዛሬዎቹ ሮቦቶች እንግዳ ይቀበላሉ፣ የገንዘብ ሂሳብና የባንክ ስራዎችን ይሰራሉ፣ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ስራዎች ይሰራሉ፣ በየምግብ ቤቱ ምግብ በመስራትና በማቀበል፣ ቡና በማፍላትና በማስተናገድ ያገለግላሉ፣ ፖስታና እቃ ከሻጮች ወደ ገዢዎችና ተገልጋዮች ያደርሳሉ፣ መኪና ይነዳሉ፣ አውሮፕላን ያበራሉ፣ መሳሪያ ይዘው ቤቶችን፣ ህንጻዎችንና ድርጅቶችን፣ ሰው በብዛት የሚንቀሳቀስባቸውን እንደ አውሮፕላን ማረፊያና አውቶቡስ መናኽሪያ ያሉ ስፍራዎችን እንዲሁም የጦር ሰፈሮችን ይጠብቃሉ ፣ ካስፈለገም ሊተኩሱና ሊገድሉም ይችላሉ።
ኬይ ፉ ሊ የሚባሉት የSinovation Ventures ድርጅት መስራችና የታወቁ የቻይና የቴክኖሎጂ ባለሙያ ይህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የሰዎች ልጆች ከሚሰሩአቸው ስራዎች ውስጥ ግማሹን ይወስዳሉ ሲሉ ዜናው እንደቀላል መታየት የለበትም። በዚህ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ስራ የሚነፈገው ህዝብ ብዙ ትምህርት የሌለው ወይም በልምድና በመጠነኛ ስልጠና የሚሰሩ ስራዎችን የሚሰራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡና ከፍተኛ ልምድን ያካበቱ ሰዎችም ናቸው። ታዲያ ያ ሁሉ ከስራ የሚፈናቀለው ህዝብ ምን ሰርቶ ይኖር ይሆን? ያን ያህል ህዝብ ከስራ ተፈናቅሎ የገቢ ምንጩ ከተቃወሰ ወይም ጭራሹኑ ከጠፋስ እነዚያ ይህን ቴክኖሎጂ በማሰማራት ምርትና አገልግሎታቸውን ለመሸጥ የሚፈልጉት ድርጅቶች የሚሸጡት ለማን ነው? ደግሞስ እየዋልን ስናድር ይህ ቴክኖሎጂ ለሰው አለቃ ከመሆን የሚከለክለው ነገር የለም። ዛሬ እንደ ካናዳ ባሉት በሰለጠኑት አገሮች ልጆቻችን ገና ማንበብና መጻፍ እንኳን ጠንቅቀው ሳያውቁ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ኮምፒውተር ፕሮግራም ስለማድረግ (CODING) እንዲማሩ ተደርጓል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆቻችንን በትምህርት ቤት የሚጠብቁ ሮቦቶች ቢሰማሩ ወይም የሚያስተምሩአቸው በዚህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የተሞሉ ሮቦቶችና ሌሎች ቁሶች እንደሚሆኑ ብዙም አያጠራጥርም።
ይህ ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር ቢኖረውም ለሰው ልጅ ህልውና እጅግ ያሰጋል የሚሉ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። ዋነኛው አደጋ፣ ይላሉ እነዚህ አዋቂዎች፣ ይህ ቴክኖሎጂ ያለገደብ ራሱን በራሱ ማስተማር፣ ራሱን መልሶ መፍጠርና ማባዛት ወይም ለሚሰራው ሁሉ የሰውን ፈቃድ በመጠየቅ ፈንታ ለራሱ ስልጣንን መስጠት የተማረ ወይም የለመደ እንደሆነ ነው። ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ከሄደ ደግሞ ይህ አይሆንም ሊባል አይችልም ይላሉ ብዙ ታዛቢዎች።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዘመንና ይህ ቴክኖሎጂ እንደሚመጣ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ገልጾአል። የተገለጸላቸውን ነገር ለኛ ጽፈው የተውልን የጌታ ነቢያትና ሃዋርያት ይህን ቴክኖሎጂ የሚመስል ነገር በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጣና እጅግ እንደሚበዛ፣ የሰው ልጆችም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ከሚኖራቸው እምነት የተነሳ ሰይጣን ብዙው የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንደ አምላክ እንዲቀበለውና እንዲያምነው እንኳን ለማድረግ ሊጠቀምበት እንደሚችል ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 13 ቁጥር 11 እስከ 18 ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚገለጸው ሃሰተኛው ነቢይ የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንዲያምኑ ለማድረግ ሰዎች ለሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልን እንዲሰሩ እንደሚያዝና ለዚያም ምስል እስትንፋስ እንደሚሰጠው ይናገራል። እስትንፋስ የሚሰጠው የሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልም አፉን ከፍቶ በመናገር ሰዎች ሁሉ ለሃሰተኛው ክርስቶስ እንዲሰግዱ ያዝዛል፣ የማይሰግዱትንም ሁሉ ያስገድላል። ከአስር ዓመታት በፊት እንኳን ብዙ አሿፊዎች ይህን ክፍል ሲያነቡ ቅዥት ነው ወይም ደግሞ የክፉ መናፍስት ስራ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ይሉ ነበር። በእርግጥ ሃሰተኛው ክርስቶስም ሆነ ሃሰተኛው ነቢይ የሚያደርጉት ሁሉ ከጥልቁ የሚወጣ የዲያብሎስ ስራ ነው። ነገር ግን፣ ምን ያህል የጎላ ወይም እንዴት መሆኑን አናውቅም እንጂ በሰው እጅ የተሰራው ይህ ቴክኖሎጂም (ሰው ሰራሽ አእምሮ ወይም AI) በመጨረሻው ዘመን የትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢትን የሚያጠኑ ሊቃውንት ይስማማሉ። ሰው ሰራሹ አእምሮ ዛሬም ቢሆን ህይወታችንን በብዙ መንገዶች እየተቆጣጠረ እንዳለ አንዘንጋ። ቴሌቪዥኑ የምናይ የምንሰማውን ጆሮ ጠቢ፣ የእጅ ስልኩ የወጣን የገባንበትን፣ የሰማን የተነፈስነውን አሾክሿኪ፣ መኪናችን ከሰማይ ሳተላይት ጋር ተያይዞ የወጣን የገባንበትን ሁሉ የሚያሳብቅ፣ የባንክ ካርዳችን የምንበላውን የምንጠጣውንና የምንለብሰውን ሳይቀር የሚያቀብል ነው። መረጃ ፈልገን በኮምፒውተራችን GOOGLE ላይ ጉድ ጉድ ብንል ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስልካችን ያንን እቃ ግዛ፣ ይህን ፊልም እይ የሚል የሽያጭ ግብዣን ያመጣልናል። ከቤት ውስጥ አንድ ሰው መኪና ከገዛ በሚቀጥለው ቀን የጎማ ወይም ሌላ የመኪና እቃ ማስታወቂያ በራችን ድረስ ወይም ስልካችን ላይ ይመጣል። በአጋጣሚ አይደለም። ሰው ሰራሹ ቴክኖሎጂ ሳናውቀው ዙሪያችንን ከቦናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የታመንን ሁሉ  ልንፈራ አያስፈልግም። ከዚህ ሁሉ ሰው ሰራሽም ሆነ ምንጩ ከአጋንንት ከሆነ ቴክኖሎጂና አሰራር በሙሉ በምህረቱ፣ ዘለዓለማዊ ኃይሉና ፍቅሩ የከበበን አምላክ አለን። ብርሃናችን ክርስቶስ መጥቶአልና ልንነሳ የተስፋን ወንጌል ላልሰሙ ሁሉ ልናበስር ይገባል። ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ ይህን ልብ እንበል፣ በዓለም ላይ የሚካሄደውን ነገር በሙሉ በቃሉ መሰረት በመረዳት ለሌሎች ብርሃን መሆን የምንችል እኛ ብቻ ነን። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር ህዝብ ለእስራኤል እንዲህ አለ፡ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ አብሪ። እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አህዛብን ይሸፍናል፣ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፣ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አህዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገስታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።” ኢሳ 60፡1፥3። እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ በልባችን ያበራው የወንጌል ብርሃን ለሌሎችም ይብራ!!
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት በዚህ ወር እስራኤልን ሲጎበኙ ብዙ የእስራኤል አይሁድ የሚጠብቁት "መሲሁ" እንዲመጣም እንዲጸልዩ ተጠየቁ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ኢየሩሳሌምን ሲጎበኙ መሲሁም እንዲመጣ ሊጸልዩ ይገባል አለ የእስራኤል የሽማግሌዎች ጉባኤ (ሳንሄድሪን)

እውነተኛው መሲህ፣ የዓለምን ሁሉ ኃጢዓት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ፣ የእስራኤልና የአህዛብ ሁሉ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ተገልጿል። ህግና ነቢያት የተናገሩትንና የተነበዩትን በሙሉ ፈጽሞ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ በአባቱ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። በተያያዘው ጽሁፍ ላይ እንደምንመለከተው ግን እጅግ ብዙ የአብርሃም ዘር የሆኑ አይሁድ መሲሁ ገና አሁን ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያልተረዳ ክርስቲያን ይህን ዜና ሲሰማ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከተነገሩት ትንቢቶች ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ ስለሆነ ምናልባት አይሁድ ሊመጣ ነው የሚሉት የተሰቀለውን፣ የሞተውንና ከሞትም በድል የተነሳውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን አይሁድ አሁን ገና መሲሁ ሊመጣ ነው የሚሉት ክርስቲያኖች የሚያምኑትን ኢየሱስ ክርስቶስን አይደለም። በእነርሱ እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ መሲህ አይደለም። በፍጹም አይቀበሉትም አያምኑትምም። የሚጠብቁትም የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት ሳይሆን የ”መሲሁን” የመጀመሪያ መምጣት ነው። ለእስራኤል ሰላምና መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው ተከፍተው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማየትና ማመን እንዲችሉ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ልንጸልይ ያስፈልጋል።
ዛሬ አይሁድ የሚጠብቁት መሲህ (በእብራይስጥ መሺያክ) እስራኤልን ከጠላቶቿ የሚታደግ ታላቅ መሪ ነው ብለው የሚያስቡትን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በሚገባ ባልተረዱበት፣ ከሞቱና ከትንሳኤው በፊት በነበረው ጊዜ የጌታ ሃዋርያትም እምነት ይህን ይመስል እንደነበር ከወንጌሎች እንረዳለን። ስለዚህ ዛሬ ብዙ አይሁድ በሚያምኑት ነገር ልንገረም አይገባም። ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 5 ቁጥር 43 ላይ “እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ” ብሎ ነበር። ስለዚህ እነሱ መሲህ ነው የሚሉትን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መሲህ ሊቀበሉ የግድ ነው ማለት ነው። እዚህ ጋ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ። እነዚህ ያለንባቸው ቀናት ካላስተዋልን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች የሚከሰቱበትና የሚናፈሱበት ጊዜ ነው። ክርስቲያኖች የዘመኑ መጨረሻ ቀርቦአልና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ። ብዙ እስላሞችም መሃዲው የሚገለጽበት ዘመን ነው ይላሉ። ሌሎች ብዙ እምነቶችም ሊመጣ ነው ብለው የሚጠብቁት “ታላቅ” መሪ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ቀደም ብሎ በምድር ላይ ስለሚመጣና ዓለምን ሁሉ ስለሚያስት አንድ “የዓመጽ ሰው” ወይም “የጥፋት ልጅ” ይናገራል። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በበጉ መጽሃፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉት በምድር የሚኖሩ ሁሉ የሚሰግዱለት ይህ “ሰው” ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፣ ብዙዎችን ያጠፋል ብዙዎችም ይከተሉታል።

ታዲያ በዚህ ዜና ላይ እንደምንመለከተው የአሜሪካው ፕሬዝደንት እንዲመጣ መጸለይ ይገባቸዋል የተባለው መሲህ የቱ ይሆን የሚለው ጥያቄ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት ተመራማሪዎችን ብዙም ግራ የሚያጋባ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ካልተቀበሉና ሌላ መሲህ እንዲመጣ የሚጸልዩ ከሆነ ያ የሚጠበቀው ሌላው “መሲህ” መጽሐፍ ቅዱስ የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ የሚለው ወይም በተለምዶ ሃሳዊው መሲህ የሚባለው ሰው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው በሚለው ሃሳብ ላይ ብዙ የትንቢት ምሁራን ይስማማሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ በእርግጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ ነው ማለት ነው። እንንቃ! በመጠን እንኑር! መጽሐፍ ቅዱሳችንን እናንንብብ፣ እናጥና! እንጸልይ። በመቅረዛችን ዘይት የመሙያው ጊዜ ሳናውቀው እያለፈብን እንዳይሆንና ጌታችን ሲመጣ በሩ እንዳይዘጋብን አንዘናጋ። እግዚአብሔር መልካም ነው። ነገር ግን ይህ የጸጋ ዘመን ደግሞ ለዘላለም አይቆይም። በማናስብበት ጊዜ እንደሚመጣ ጌታ ደጋግሞ ነግሮናል። እንንቃ! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የመለከት ድምጽ መጽሔር ቁጥር 7

የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 7 ዛሬ ወጥቷል። ከታች የተሰጠውን ማገኛና በመጫን ማንበብ ይቻላል። እንዲሁም ደግሞ ከFACEBOOK የVoice of Trumpet group እና ገጽ ላይ download በማድረግ ማንበት ይቻላል። ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ በFACEBOOK እና በመለከት ድምጽ ብሎግ ለማቅረብ እንደሞከርሁት፣ ጦርነትና የጦርነት ወሬ የየእለት ዜና ከሆነ ውሎ ቢያድርም፣ የዓለም ሁኔታ እየተሻሻለ ሳይሆን ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየባሰ ነው የሚሄደው። ቁጥር 7 በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ መረጃዎችን፣ ትምህርቶችን እና ሃሳቦችን ይዛ ቀርባለች። እያንዳንዱ አንባቢ ቢያንስ አንድ መልእክት፣ መታነጽና መጽናናት እንዲያገኝባት የልቤ መሻትና ጸሎቴ ነው። አንብባችሁ ላልደረሳቸውም በማድረስ እንድትረዱኝ በትህትና እጠይቃለሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የመለከት ድምጽ ቁጥር 7
አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን ታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። (መዝሙረ ዳዊት ምዕ 46። እግዚአብሔር መልካም ነው በመከራም ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ትንቢተ ናሆም 1፤7 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፣ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። (ምሳሌ 21፤31) http://www.express.co.uk/life-style/life/797877/world-war-3-bomb-shelter-locations

ሰው ሰራሽ አእምሮ የሰውን ልጅ መተካትና የሰውንም ዘር ማጥፋት የሚችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል

https://www.rt.com/viral/386512-hawking-ai-fears-humanity/

ሰው ሰራሽ አእምሮ የሰውን ልጅ መተካትና የሰውንም ዘር ማጥፋት የሚችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ተባለ
ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል፣ በተለይም ደግሞ ስለመጨረሻው ዘመን፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት፣ በዘመኑ መጨረሻ ላይ ስለሚገለጸው የእግዚአብሔር መንግስት እና ስለዘለዓለም ፍርድ የተጻፉትን ትንቢቶች ከየእለቱ ዜናዎች ጋር በማነጻጸር ብናደምጣቸው እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከፍጥረት መካከል የዋጃቸውን ሕዝቡን ወደራሱ የሚሰበስብበትና በዓመጸኛው ዓለም ላይ የሚፈርድበት ዘመን እጅግ እየተቃረበ መሆኑን እናስተውላለን። ስለዚህ ዘመን መጨረሻ ከተጻፉት ትንቢቶች አንዱ እንዲህ ይላል፤

ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፣ ከሰማይም ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን በማኅተም ዝጋው፣ አትጻፈውም የሚል ድምጽ ሰማሁ። …….. ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምስርጢር ይፈጸማል አለ። ራዕይ 10 ቁጥር 4 እና 7

ባለፉት ጥቂት ቀናት በቤጅንግ ቻይና እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፉ ተንቀሳቃሽ ኢንተርኔት ኮንፈረንስ (GMIC) ላይ ንግግር ያደረጉት እውቁ የፊዚክስና የህዋ ምርምር ሊቅ ፕሮፌሰር ስቲቨን ሆውኪንግ እንዳሉት፣ የሰው ልጅ ራሱ የፈጠረው ሰው ሰራሽ አዕምሮ (ARTIFICIAL INTELLIGENCE ወይም ባጭሩ AI) ከራሱ ከሰው ልጅ ችሎታ እኩል ወይም በላይ የሆኑ ነገሮችን ሊሰራ የሚችልበት ደረጃ ደርሷል፣ በብዙ መስመሮችም ላይ ይህ ሰው ሰራሹ አእምሮ ከሰው ልጅ ከራሱም ችሎታ በላይ የላቁ ነገሮችን ስለሚሰራ በከፍተኛ ፍጥነት የሰውን ልጅ ህልውናና በዚህ ምድር ላይ የመኖር አስፈላጊነት ከጥያቄ ውስጥ እያስገባው ነው ብለዋል። በመጨመርም፣ ይህ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ለመርዳትና ችግሮቹን ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ቢሆንም፣ እንደፈለገው እንዲሆን ከተለቀቀ ግን የሰውን ዘር ፈጽሞ ሊጎዳና ሊያጠፋም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። “ቆም ብለን ማሰብ ያለብን አሁን ነው” ያሉት እኒህ ታዋቂ ምሁር፣ ይህ ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ ደህንነትና ህልውና ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጥፋት በጣም እንደሚያሰጋቸው ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም። የርሳቸውንም ሆነ የሌሎች አዋቂዎችን ምክር የሚሰማ ወይም የሚያስተውል ይኖር ይሆን ?!!

የኮምፒውተርና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ እጅግ በመስፋፋት ዓለምን በሙሉ መሸፈን ከመጀመረባቸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ ጀምሮ እነዚህ ሰው ሰራሽ ቁሾች (HARDWARE) የመረጃ መረቦችና (NETWORKS) እና በሰው የተጻፉ የኮምፒውተር ትእዛዞች (SOFTWARE) ቅንብሮች እጅግ ከፍተኛ ወደሆነ ልእቀት በመድረስ ዛሬ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል የሰው ልጅ ብቻ ይሰራቸዋል የሚባሉ ነገሮችን በሙሉ ሊያከናውን ወደሚችልበት ደረጃ ደርሷል። በAI የሚመሩ ቁሶችና ሶፍትዌሮች ቤት ያጸዳሉ፣ መኪና ይነዳሉ፣ አውሮፕላን ያበራሉ፣ በፋብሪካዎች ውስጥ እቃዎችን ይሰራሉ፣ ይገጣጥማሉ፣ ትልልቅ ፋብሪካዎችን፣ የኃይል ማመንጫዎችን፣ የውሃና የፍሳሽ አገልግሎት መሳሪያዎችን ይቆጣጠራሉ፣ በራዳርና ሌሎች የተለያዩ መሳሪያዎች ድምጾችን በመስማት፣ ምስሎችን በማየት፣ ሽታዎችንና ጣእሞችን በመለየት መረጃን ይሰበስባሉ፣ ከተራ የጦር መሳሪያዎች እስከ ኑክሊየር ሚሳኤሎች ድረስ የመቆጣጠርና ሲፈቀድላቸውም ኢላማ የመለየትና የመተኮስ እንዲሁም ከጠላት የተተኮሱ መሳሪያዎችን የመለየትና የመምታት ችሎታ አላቸው። በሆስፒታል ቀዶ ጥገና የማድረግ፣ ወደ ህዋ የሚመጥቁ መንኮራኩሮችን የመምራት፣ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስና የኢንሹራንስ እንዲሁም የላቁ የምህንድስናና ሳይንሳዊ ቀመሮችንና ስሌቶችን የማከናወን፣ የምርት ጥራትን የመቆጣጠርና ሌሎችም የላቁ ስራዎችን የመስራት ችሎታ አላቸው።

ሰው ሰራሹ አእምሮ (AI) ዛሬ የሚቆጣጠረው ኮምፒውተሮችን፣ ታብሌቶችን፣ የእጅ ስልኮችን እና በየእለቱ በግላችንና በድርጅት ወይም በጋራ የምንጠቀምባቸውን ቁሶች ብቻ አይደለም። እንደ GOOGLE, FACEBOOK, TWITTER, INSTAGRAM ያሉ እና ሌሎችም በሰፊው የምንጠቀምባቸው ሶፍትዌሮች ስራቸው ለእኛ መረጃ መስጠትና የምንፈልገውን ነገር ማፈላለግ ብቻ አይደለም። እያንዳንዳችን በተደጋጋሚ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ያጠናሉ፣ ከማን ጋር ምን እንደምንነጋገር ወይም እንደምንጻጻፍ፣ መቼ ወጥተን መቼ እንደምንገባ፣ ምን እንደምንችል፣ ምን እንደምንገዛና እንደምንሸጥ፣ ምን እንደምናምን፣ ምን እንደምንደግፍና እንደምንቃወም፣ ምን እንደምንጠላላን እንደምንወድ ሳይቀር መረጃን በመሰብሰብ እኛንና ባህርያችንን ያጠናሉ፣ አንድን ቋንቋ ወደ ሌላ ይተረጉማሉ፣ የሰውን ንግግር በማዳመጥና መልስ በመስጠት ድሮ ብዙ ሰዎች ይሰሩአቸው የነበሩ ስራዎችን በቀላሉ ያከናውናሉ። ከነዚህ ሰው ሰራሽ አእምሮዎች በስተጀርባ ያሉ ባለቤቶች ከፈለጉም እንቅስቃሴያችንና ግንኙነቶቻችንን በሙሉ እነሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የመግራትና ሲያስፈልግም እንቅስቃሴያችንን ወይም ንግግራችንን የመዝጋት ችሎታው አላቸው። ለምሳሌ፣ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የGOOGLE ና የFACEBOOK ሶፍትዌሮች የቀኝ ክንፍ ወይም CONSERVATIVE ወገኖች በምርጫው ላይ ወደፊት እየመሩ ሲገኙ የነሱን ዜናዎች ሰዎች በቀላሉ እንዳያገኙአቸውና እንዳይደግፉአቸው ወደታች በመግፋት ያፍኑአቸው እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጾአል። ስለዚህ እነ FACEBOOK እና GOOGLE ወይም ሌሎቹ ነጻ መሳይ የብዙኃን መገናኛዎች እኛ እንደምንገምተው ስራቸው በቅንነትና በነጻ ለህዝቦችና ለሰዎች ሁሉ አገልግሎት መስጠት ሳይሆን ምርጫችንን፣ ዝንባሌያችንን እና ፍላጎታችንንም ሳይቀር ለመለወጥ ችሎታው ያላቸው መሳሪያዎች ናቸው።

በእጃችን ባሉ ዘመናዊ ስልኮች፣ በየቤታችን ባሉ ቴሌቪዥኖች እና በእጃችን ላይ በምናስራቸው ሰዓቶች፣ በምግብ ማቀዝቀዣዎች፣ በመኪናዎቻችንና ሌሎችም ቁሶች ውስጥ የሚቀመጡት ሶፍትዌሮች ያለንበትን ቦታና፣ በማንኛውም ጊዜ ምን እየሰራን እንዳለ ጭምር ስለሚያውቁ፣ ችሎታው ያላቸው ሰዎችና ድርጅቶች ይህንን መረጃ በመጠቀም ሊያጠቁንና ሊጎዱንም ይችላሉ። በመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 6 (ስድስት) ላይ እንዳቀረብሁት በቀላሉ በGPS እና በሌሎችም አድራሻ ጠቋሚ መሳሪያዎች አማካይነት ያለንበት ቦታ ድረስ መጥው ሊያጠቁን የሚችሉ ነፍሳት መሰል መሳሪያዎች ከተሰሩ ውለው አድረዋል። ብዙዎች የዘመኑን ወታደራዊ ኃይላት የሚያጠኑ ባለሙያዎችም የሶስተኛው የዓለም ጦርነት የሰውን ዘር ህልውና እጅግ ያሰጋል የሚሉት ይህ ሰው ሰራሽ አእምሮ በራሱ እንዲሰራ ከተለቀቀ ሊያመጣ የሚችለውን እልቂት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እንደ ሩሲያና አሜሪካ እንዲሁም ቻይና ያሉ ታላላቆቹ አገሮች ዛሬ ሰውን በትክክል የሚለዩና ካስፈለገ መማረክ ወይም ተኩሰው መግደል የሚችሉ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ፣ የሚያዩ፣ የሚሰሙና ውሳኔ ማድረግ የሚችሉ መሳሪያዎችን በሰፊው እያመረቱ ነው። ምናልባት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ስለሚመጣው ታላቁ የመከራ ዘመን ሲናገር “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ስጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር፣ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” በማለት በማቴዎስ 24 ቁጥር 22 ላይ የተናገረው ስለዚህ ጉዳይ ይሆን ?!

አተኩሮ ለተመለከተው የሰው ሰራሽ አእምሮ (artificial intelligence ወይም AI) ችሎታና በሱም የሚንቀሳቀሱ የሰላምና የጦርነት መሳሪያዎች፣ ስለሚያስፈራው ስለእግዚአብሔር ቀን በጻፈው በነቢዩ በኢዩኤል ትንቢት  (ምእራፍ 2 ቁጥር 1 እስከ 11) ላይ  የተገለጹትን ነገሮች የሚመስል ባህርይ አላቸው። የኢዩኤል ትንቢት አንዱ ክፍል እንዲህ ይላል፤

“ከፊታቸው አህዛብ ይንቀጠቀጣሉ፣ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል። እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ሰልፈኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፣ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፣ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም፣ አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፉም፣ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፣ በሰልፉ መካከል ያልፋሉ፣ እነርሱም አይቆስሉም። በከተማም ያኮበኩባሉ፣ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፣ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፣ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ።” ኢዩኤል 2፤6፥9

ሰው ሰራሹን አእምሮ በተመለከተ መረዳት የሚገባን መንፈሳዊ ነገርም አለ። የሰው ዘር ጠላት የሆነው ዲያብሎስ፣ ተከታዮቹ የወደቁት መላእክትና አጋንንት ግዑዝ በሆኑ ሃውልቶችና ጣዖታት ውስጥ በመሆን የሰው ልጆች ለዘመናት እንዲሰግዱላቸው ካደረጉ፣ በሰው ሰራሽ አእምሮ በሚመሩ ነገሮች ውስጥ በመሆን የሰውን ልጅ ከማታለልና ሰው በእጅ የተሰራውን እንዲያመልክ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ምናልባትም በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 13 ቁጥር ላይ የተጻፈው “የአውሬው ምስል” የዓለም ህዝብ ሁሉ ሃሰተኛው ክርስቶስ ከሞት ተነሳ ብሎ እንዲያምን የሚከወን በሰው ሰራሽ አእምሮ የሚመራ ቅርጽ ወይም ሰው መሳይ አካል ሊሆን እንደሚችል ብዙ የትንቢት ምሁራንና ቴክኖሎጂውን በቅርብ የሚያጠኑ አዋቂዎች ይገምታሉ?!

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለና ጌታን በመታዘዝ የሚመላለስ ክርስቲያን ሁሉ ከላይ የተጠቀሰውንና ሌሎችንም መሰል ዜናዎች ሲሰማ የጌታ ቀን እንደተቃረበ በማወቅ ራሱን ማዘጋጀት እንጂ መፍራት ወይም መታወክ አያስፈልገውም። የእግዚአብሔርን ፍቅርና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የተደረገውን የወንጌል ግብዣ ገና ያልተቀበለ ማንኛውም ሰው ደግሞ ኃጢዓተኝነቱን በመገንዘብና እግዚአብሔርም በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምክንያት ይቅር እንደሚለው በማመን ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበያው ቀን ዛሬ ነው። መቼ እንደሚሆን ቀኑን እና ሰዓቱን ባናውቅም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ የሚመጣበት ቀን እጅግ እየተቃረበ ነው። በዚያን ቀን ለንስሃ ቦታ የለም። ያ ቀን የፍርድና እግዚአብሔር ስንዴውን ከእንክርዳድ የሚለይበት ቀን ነው። የንስሃ ቀን ዛሬ ነው። እግዚአብሔር እርሱን የምንፈራበትና በንስሃ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደሱ የምንመለስበትን ልብ ይስጠን።
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።



ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...