የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን
ናቸው? ትምሕርት 6
ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓቱ መቃረቡን ሊያሳዩን እንዲችሉ
ከሰጣቸው ምልክቶች አንዱን “የኖህ ዘመን እንደነበረ እንዲሁ ይሆናል” የሚለውን ባጭሩ ተመልክተናል። የነዚህ ትምህርቶች ዓላማ እያንዳንዱ
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምንም ሆነ የማያምን ሰው የእግዚአብሔር ልጅ፥ እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከድንግል
ማርያም የተወለደው፣ በመስቀል ላይ የሞተው፣ በሶስተኛው ቀን የተነሳው፣ በአርባኛውም ቀን አርጎ በአብ ቀኝ የተቀመጠው በእርግጥም
የአማልክት አምላክ፣ የነገስታት ንጉስና የጌቶችም ሁሉ ጌት መሆኑን፣
ተመልሶም እንደሚመጣ፣ በኃጥዓንና በጻድቃን ላይ እንደሚፈርድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት በአንድ ትንሽ ማስረጃ
ለማቅረብ ነው።
እግዚአብሔር ወልድ የኛን የሰዎችን ሥጋ ለብሶ የመጣበት ዓላማ እኛን በኃጢዓታችን
የጠፋነውን ሰዎች ከዘለዓለም ሞት ለማዳን ነው። ኃጢዓት ደግሞ ሥርና መሰረት አለው። በእርግጥ እያንዳንዱ ሰው መልካምንና ክፉን
የመለየት እንዲሁም ደግሞ ጽድቅንና ኩነኔን ለመምረጥ ከፈጣሪ የተሰጠ ችሎታ ቢኖረውም፣ ኃጢዓትን ወደዚህ ዓለም ያገባው በልዑል አምላክ
ዙፋን ዙሪያ እንዲያገለግሉ ከተፈጠሩት ሰማያዊ ፍጡራን (በተለምዶ መላእክት ከምንላቸው) አንዱ ሉሲፈር የሚባለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ
ሰማያዊ ፍጡራን ብዙ ዓይነት እንደሆኑ ያስተምራል።፤ ለምሳሌ ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ሊቃነ መላእክት፣ አለቆች፣ ሥልጣናት፣ ገዢዎች፣ መላዕክት ወዘተ። ሰይጣን፣ ዲያብሎስ፣ የቀደመው እባብና
ዘንዶ ወዘተ በመባል በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራው ሉሲፈር (በእብራይስጥ
רשָׁ֑חַ ןבֶּ ללֵ֣הֵי ወይም ሂሌል ቤን ሻኻር ወይም በአማርኛ
የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ተብሎ በኢሳይያስ 14:12 ላይ የተጠቀሰው) የልዑል እግዚአብሔርን ዙፋን
ከሚጋርዱት ኪሩቤል አንዱ ነበር ሕዝቅኤል 28:14። የተሰጠው ታላቅ ውበት፣ ክብር፣ ግርማና የአገልግሎት ስፍራ አልበቃ ብሎት የልዑል አምላክን
ቦታ የተመኘ ይህ ፍጥረት በትእቢቱ ምክንያት የልዑል አምላክ ዙፋን ካላበት ሰማይ ክብሩን እና ቦታውን ተገፍፎ በተጣለ ጊዜ ከሱ
ጋር በዓመጽ የተባበሩ ሌሎች እጅግ ብዙ የሰማይ ፍጥረታትም አብረውት
ተጥለዋል። ከዚህ ከክብሩ መጣል ጋር በተያያዘ ቅንዓትና ቁጣ ተነሳስቶ
ነው ይህ ክፉ ጠላት በልዑል አምሳል የተፈጠረውን ሰውም የውድቀቱ ተካፋይ እንዲሆን በማታለል ወደ ኃጢዓት እንዲገባ ያደረገው። ታዲያ
ዕባቡ (ሰይጣን) በኤደን ገነት የጀመረውን ሰውን የማሳሳትና የማጥፋት ሥራ በኤድን ገነት አላቆመም። ቃየን በወንድሙ ላይ ተነሳስቶ
ንጹሁን ወንድሙን አቤልን ንዲገድለው ያነሳሳው ሰይጣን ነበር። ጌታ ኢየሱስም ሊገድሉት የሚፈልጉትን የአይሁድ መሪዎችን እናንተ የአባታችሁን
(የሰይጣንን) ፈቃድ ልትፈጽሙ ትሻላችሁ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነውና ያለበት አንዱ ምክንያትም ይኽው ነው።
ሰይጣን በኤደን ገነት የጀመረውን እግዚአብሔርን የመቃወምና የሰውን ዘር የማጥፋት ሥራውን በኖህ
ዘመንም ቀጥሎአል። ለዚህ ነው የሱ ተከታዮች የሆኑ የወደቁ መላእክት የተመደበላቸውን የሰማያዊ ፍጥረታት ክልል በመጣስ ወደ ምድር
ወርደው ያለ አግባብ የሰውን ሴቶች ልጆች በመውሰድና የተከለከለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸም ኔፊሊምን የወለዱት። እነዚህ ኦሪት
ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “የእግዚአብሔር ልጆች“ የሚላቸው መላዕክት ስማቸው ማን እንደነበርና ቁጥራቸውም ስንት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ
አይናገርም። ሌሎች አዋልድ ተብለው የሚቆጠሩ መጻህፍት ግን ቁጥራቸውን፣ ስማቸውን፣ የመሪዎቻቸውን ስሞች፣ ወደ ምድር የወረዱበትን
ስፍራ፣ በምድር ላይ ያደረሱትን በደልና ጥፋት እንዲሁም ፍጻሜያቸውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ይሰጣሉ። ከእነዚህም መጻህፍት
ሶስቱ መጽሐፈ ሄኖክ፣ የያሻር መጽሐፍና የኢዮቤልዩ መጽሐፍ የሚባሉት ናቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎችም ጥቂት
አብያተ ክርስትያናት መጽሐፈ ሄኖክን የመጽሐፍ ቅዱስ አካል አድርገው ይቀበሉታል። የያሻር መጽሐፍ ደግሞ በግልጽና በውስጠ ታዋቂነትም
በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፤ ለምሳሌ በኢያሱ 10:13፣ 2ኛ ሳሙኤል 1:18 እና 2ኛ ጢሞቲዎስ
3:8። በፊት በቀረቡት ትምህርቶች ላይ እንዳቀረብኩት፣ የጌታ ኢየሱስ ደቀመዛሙርትና ሐዋርያት እንዲሁም ከነሱ በኋላ የመጡት ቅዱሳን፣ የእነዚህን መጻህፍት መልእክት ማወቅ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹን መረጃዎቻቸውንም
በቀጥታና በተዘዋዋሪ በአዲስ ኪዳን መልእክቶቻቸው ውስጥ ጠቅሰዋቸዋል። ለምሳሌ 2ኛ ጢሞቲዎስ 3:8 ፤ 2ኛ ጴጥሮስ 2፤4 ፤ የይሁዳ
መልዕክት ቁጥር 14 እና 15። የኔፊሊምን ታሪክና ማንነት ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በቂ ነው። የነዚህንም መጻህፍት መረጃ እንደ
እግዚአብሔር ቃል አድርገን መውሰድ አንችልም።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አዋልድ ተብለው የሚጠሩ መጻህፍት ከጥፋት ውኃ በፊት ወደ ምድር የወረዱት
የወደቁት መላዕክት ሁለት መቶ ያህል እንደነበሩ፣ የወረዱበት ስፍራም በአርዲስ የተራሮች ሰንሰለት ውስጥ የሚገኘው ሄርሞን (በአማርኛ
አርሞንኤም) የሚባለው እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ተራራ ዛሬ በእስራኤል፣ በሊባኖስ፣ በዮርዳኖስና በሶሪያ ድንበር አካባቢ ይገኛል።
የአካባቢው ስምም ዛሬ የጎላን ኮረብታማ ስፍራ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በእስራኤል፣ በሊባኖስና በሶሪያ መካከል ላለው መሬትን የተመለከተ
ያለመግባባት ዋና መንስኤ ነው። እኩይ ተግባራቸውን መፈጸም ከመጀመራቸው በፊት እነዚያ የወደቁት መላእክት በተራራው ላይ ስለ ተማማሉበት፣
ስሙንም ሂርሞን ያሉት እነሱ ናቸው ብሎ መጽሐፈ ሔኖክ ይናገራል። የብሉይ ኪዳንን ታሪክ ብንመለከት ደግሞ ይህ አካባቢ የባሳን ንጉስ
ዐግ የተባለው ከኔፊሊም ወገን የቀረ የመጨረሻው ግዙፍ ፍጥረታት ቅሪት ይገዛቸው የነበሩ 60 የኔፊሊም ዘሮች (ራፋይም) ከተማዎች
የነበሩበት አካባቢ ነው። ዘዳግም 2 ቁጥር 8 እስከ 17 አንብቡ። በአዲስ ኪዳን ዘመን በዚህ ተራራ ላይና ከስሩ በምትገኘው በፊልጶስ
ቂሳርያ ከተማ አጠገብ ጌታ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላትና በተራራው ላይ ክብሩን መግለጹ ሰይጣንና እነዚያ ዓመጸኞች መላእክት የሰሩትን
ስራ ለማፍረስ መምጣቱን የሚያመላክቱ ነበሩ። ማቴዎስ 16:13 እስከ 28 እና ማቴዎስ ም 17 ከቁጥር 1 እስከ 21ን አንብቡ።
የዲያብሎስን ስራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጸ ተብሎ በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈው ቃል ዲያብሎስ ምን ያህል በተወሳሰበና
በረቀቀ መንገድ የሰውን ዘር ለመበከልና ለማጥፋት እንደጣረና ዛሬም እንደሚጥር የሚያሳይ ጥልቅ መረዳትን የሚጠይቅ ቃል እንጂ ሰይጣን
በኤደን ገነት ያደረገውን አንድ ክስተት ብቻ የሚመለከት አይደለም።
ብዙዎቻችን ስለመላእክት ያለን አስተሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ አይደለም። የብዙዎቻችን
ሃሳብ እንዲያውም ከሰዓሊዎች ፈጠራ ወይም ከፊልሞች ወይም ከአፈታሪክ የተወሰደ ነው። መላእክት ክንፍ ያላቸው፣ በብርሃን ተከበው በአየር ላይ የሚንሳፈፉ የዋህና ምንም ክፉም
ሆነ በጎ የማይሰሩ ትንንሽ ህጻናት እንደሆኑ የምንገምት ብዙ ነን። በመሰረቱ በአማርኛ መልአክ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
ለተጠቀሱት ብዙ ዓይነት ሰማያዊ ፍጥረታት ሁሉ በድምር የተሰጠ ስም ነው። የዚህ ቃል የዕብራይስጡ እኩያ מַלְאַךְ (መላአክ) ወይም የግሪኩ ἄγγελόν (አንኼሎስ) የሚለው ነው። የነዚህ የእብራይስጥ እና የግሪክ ቃላት ዋና ሃሳብ መልእክተኛ ማለት
ሲሆን መልእክትን ከእግዚአብሔር ላመጡ (ለሚያመጡ) የሰማይ ፍጥረታት ሁሉ ያገለግላል። ዋነኛ የአገልግሎት መደባቸው መልእክትን ማምጣት
ያልሆነ ሌሎች ብዙ ሰማያዊ ፍጥረታት እንዳሉ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ኪሩቤል (የጌታን ዙፋን የሚጋርዱ)፣ ሱራፌል
(የጌታን ቅድስና ሊትና ቀን ሳያቋርጡ የሚያውጁ)፣ ስልጣናት (በባህር፣ በውኃ፣ በእሳት፣ በነፋሳት ላይ ሥልጣን ያላቸው)፣ ኃይላት፣
ገዢዎች (የተለያዩ አገሮችንና ህዝቦችን የሚገዙ ፥ ለምሳሌ ገብርኤል ወደ ዳንኤል እንዳይደርስ የተዋጋው የፋርስ መንግስት አለቃ)
ወዘተ።
ሌላው መላእክትን በተመለከተ
ብዙዎቻችን የምንዘነጋው ነገር መላእክት በሁለት እንደሚከፈሉ ነው ። ሰይጣንን ተከትለው ከክብራቸው የተጣሉ መላእክት አሉ። ነገር
ግን ጌታ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉት ደግሞ ካመጹት ይልቅ በቁጥር እጅግ የሚበዙ ቅዱሳን መላእክት አሉ። የዮሐንስ ራዕይ
የወደቁት መላእክት ከጠቅላላው 1/3ኛ ብቻ እንደሆኑ በምዕራፍ 12 ቁጥር 3እና 4 ላይ ያመለክታል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ
መላእክትን በተመለከተ የተጻፉትን ነገሮች ስናነብ ስለየትኞቹ እንደሆነ መለየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ጌታ ኢየሱስ ስለጋብቻ ሲያስተምር
ሳለ፣ ከሞት የተነሱ ቅዱሳን እንደ ሰማይ መላዕክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፣ አይጋቡምም ብሎ ያስተማረው ስለ ቅዱሳን መላእክት ነው።
ጌታም አያገቡም፣ አይጋቡምም አለ እንጂ አካል የላቸውም ወይም ማግባት አይችሉም አይደለም ያለው።
ይህንን ክፍል በሚገባ ያልተረዱ
ሰዎች ታዲያ መላእክት ሰውነት የላቸውም፣ ሊያገቡ ወይም ፍትወተ ስጋ መፈጸም ስለማይችሉ ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ዘራቸውን አደባልቀው
ኔፊሊምን ሊወልዱ አይችሉም ይላሉ። በእርግጥ ቅዱሳን መላዕክት ጌታ አምላክ በመደበላቸው የክብር ስፍራ ስለሚኖሩና ስለማይሞቱም ዘራቸውን
ለመተካት ሲሉ ሚስት ማግባት ወይም ልጅ መውለድ አያስፈልጋቸውም። ስለዚህም አያገቡም፣ አይጋቡምም። ከወደቁት መላእክት አንዳንዶቹ
ግን የጌታን ስርዓት ጥሰው እንግዳ ስጋን በመከተል ዓመጻን እንዳደረጉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስተምራል።
በዘፍጥረት 3 ቁጥር 15 ላይ
ጌታ አምላክ እባቡን (ሰይጣንን) “በአንተ እና በሴቲቱ (ሔዋን)፣ በዘርህና (זַרְעֲךָ֖) በዘርዋም (זַרְעָ֑הּ) መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፣ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” ያለውን ልብ ብለን ብንመለከት እባቡ (ሰይጣን) ዘር እንዳለው የተናገረው
ጌታ እግዚአብሔር ራሱ ነው። በእብራይስጡ ዘርህ እና ዘርዋ የሚሉት ቃላት አንድ ዓይነት ዘርን ነው የሚያመለክቱት። እባቡ ማለትም
ሰይጣን ዘር እንዳለው ብቻ ሳይሆን ጌታ አምላክ የተናገረው በሴቲቱ ዘር (በክርስቶስ) እና በእባቡ ዘር (ሃሰተኛው ክርስቶስ) መካከል
ስለሚኖረው ጦርነትና ስለክርስቶስ የመስቀሉ ድልም ነው። ጌታ ኢየሱስ (ከወንድ ፈቃድ ያልተወለደው፣ በመንፈስ ቅዱስ ከሴቲቱ ዘር
የተወለደው) ጠላትን ያሸነፈው በመስቀሉ ሲሆን የእባቡን ዘር ፈጽሞ የሚቀጠቅጠውና ሁሉን ከእግሩ በታች የሚያስገዛው የእባቡ ልጅ
የሆነውን ሃሰተኛውን ክርስቶስን፣ ሃሰተኛውን ነቢይና ሰይጣንን ራሱን ወደ እሳት ባህር ሲጥል ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ በክብር ዳግመኛ ተመልሶ ሲመጣ ነው።
ስለመላእክት ትክክለኛ መረዳት
እንዲኖረን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለነዚህ ሰማያዊ ፍጥረታት የተጻፈውን በጥንቃቄ ማጥናት ያሻል። መላእክት እንግዶች ሆነው መጥተው
እግራቸውን ታጥበዋል፣ ምግብ በልተዋል (አብርሃም፣ ማኑሄ) መስዋእት ተቀብለው በእሳት እንዲቃጠል አድርገዋል (ማኑሄ) ፣ በአካል
ተገልጸው ከሰው ጋር ታግለዋል (ያእቆብ)፣ በአካል ወደሰው ቤት እንግድነት ገብተው አደጋ ሲፈጠር በር ዘግተዋል (ሎጥ ቤት ሰዶም)፣
የሰዎችን እጅ ይዘው ከጥፋት አድነዋል (ሎጥ)፣ ወዘተ። ይህ ርዕስ
ደግሞ ራሱን የቻለ ትምህርት ይፈልጋልና አንድ ነጥብን ብቻ አቅርቤ ይህንን ትምህርት አጠናቅቃለሁ። በዘፍጥረት 6;2 ላይ “የእግዚአብሔር
ልጆች” የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያመለክተው በእግዚአብሔር
አምላክ በቀጥታ የተፈጠሩ ሕያዋን ፍጥረታትን ነው። እነዚህ ደግሞ መላእክት፣ አዳምና ሔዋን ናቸው። በአዲስ ኪዳን ላይም በክርስቶስ
ኢየሱስ የምናምንን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ብሎ የሚጠራበት ምክንያት በእምነት በክርስቶስ በኩል እንደገና በእግዚአብሔር ስለተፈጠርን
ነው። ከላይ እንዳየነው ይህ በአማርኛ “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብሎ
ከእብራይስጡ የተተረጎመው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስ ውስጥ በተጠቀሰባቸው
ቦታዎች ሁሉ የሚያመለክተው መላእክትን፣ አዳምንና ሔዋንን፣ ክርስቶስን እና በክርስቶስ ዳግም የተወለዱትን ነው። በዘፍጥረት 6 ላይ
ያለው ትርጉም ግን የወደቁትን መላእክት የሚመለከት ነው።
በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን
ጌታ እግዚአብሔር እስራኤልንና አህዛብን ለማዳን ያደረገውን ስራ ትልቅነትና የክርስቶስን የመስቀሉን ድል ምስጢር ለመረዳት የምንችለው
ሰይጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በመንፈሳዊም ሆነ በአካል የሰውን ዘር ለማጥፋት ያደረገውን እና ዛሬም እያደረገው ያለውን የእብሪት
ስራ ስንረዳ ብቻ ነው። የእስራኤል ታሪክ ፣ ትግሎች፣ ውድቀትና መነሳት፣ ከኔፊሊም ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። የኔፊሊምን ታሪክ
ካልተረዳን ብዙውን የእስራኤልን ታሪክ፣ በተለይም ደግሞ ከነዓንን መውረሳቸውን፣ የአካባቢውን ህዝቦች ጣዖታት ማምለካቸውንና በዚያም
ምክንያት በጠላቶቻቸው መመታታቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ብዙ የብሉይና የሃዲስ ታሪኮች እና ትምህርቶችን ለመረዳት የምንችለው ሰይጣን
በኤድን ገነት፣ በኖህ ዘመን፣ በባቢሎን ግንብ፣ በግብጽ ምድር በፈርዖን
ባርነት ስር እስራኤል በነበሩ ጊዜ፣ በባቢሎን ምርኮ፣ በሮማውያን፣ በግሪኮችና በሌሎችም ጠላቶቻቸው በኩል ሊያደርስባቸው የነበረውን
የጥፋት ምክንያትና ምንጮቻቸውን ስንረዳ ነው። በዚህ በእኛ ዘመንም እንኳን አይሁድን ለማጥፋት ተነስቶ የነበረው የጀርመኑ ናዚ እንቅስቃሴ
ከጥንቱ የኔፊሊም መፈጠር ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው ብዙ ጥናቶችና መረጃዎች ያሳያሉ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም
ከመመለሱ በፊት የአመጽ ሰው ወይም የጥፋት ልጅ የሚባለው ሃሰተኛው
ክርስቶስ እንደሚገለጥ፣ እንደገና
የተመሰረተችው እስራኤል፣ ሌሎችም አይሁድና የምድርም ህዝብ ሁሉ እንደሚሰግዱለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ይህ ጌታችን በመገለጡ
የሚሽረውና በአፉም እስትንፋስ የሚያጠፋው ዐመጸኛ ሰው መንፈስ ዛሬ በምድር ላይ በግልጽ እየሰራ ነው። ወደ አደባባይ መውጣት ብቻ
ሳይሆን ወደቤተ ክርስቲያንም ገብቶ ብዙ አብያተ ክርስቲያን ነን የሚሉ ከሰዶምና ከገሞራ ባላነሰ ዓመጽ ውስጥ ገብተዋል። እዚህ ጋር ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁሉ
እንድናስተውል ያስ ጋል። ይህ የዓመጽ ሰው የተባለው ሃሰተኛው ክርስቶስ ሲገለጽ እጅግ ብዙ የሆነው የምድር ህዝብ ሁሉ አሜን ብሎ
ነው የሚቀበለው። ብዙ ክርስቲያን ነን የሚሉ፣ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በግላቸው የማያውቁት ሰዎችም ሁሉ ይከተሉታል።
ይህን ሰው ምድር ሁሉ፣ ቤተክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎችም ጭምር፣ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችና እግዚአብሔር የለም ባዮችም እንደሚቀበሉት
በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ተጽፏል። የዚህ ነገር ምልቶችም በግልጽ በዘመናችን እየታዩ ነው። በቅርቡ ለምሳሌ ከእስራኤል የሃይማኖት
መሪዎች የሚወጡ ዜናዎች መሲሁ (ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን እነሱ የሚጠብቁት መሲህ) በቅርብ ጊዜ ራሱን ለእስራኤል ሁሉ ይገልጻል
ብለዋል። በዚህ ባለፈው ሳምንትም
የእስራኤል ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር የሆኑት Roni Alsheikh መሲሁ በቅርቡ ስለሚመጣና እሱን ለማግኘትም ሰዎች ሲሞክሩ ብዙ መጋፋትና ግርግር ሊፈጠር ስለሚችል ዝግጅቶችን እያደረግን
ነው ብለዋል። እነዚህን ዜናዎች ከዜና ምንጩ በእስራኤል ከሚገኘው https://www.breakingisraelnews.com። ድረ ገጽና ሌሎችም ብዙ ምንጮች ማረጋገጥ ትችላላችሁ።
በምንሰማው ዜና ሁሉ መታወክና መረበሽ የለብንም። ጌታ በምን ቀንና ሰዓት እንደሚመጣ አናውቅም።
ነገር ግን ዛሬ ወይም ነገ ቢመጣ በምን ዓይነት ሁኔታ ያገኘን ይሆን? እንንቃ! በመጠንም እንኑር እንጂ አናንቀላፋ። በክርስቶስ
ኢየሱስ ወደ ክብሩ የጠራን ደግሞ በጌታ ቀን ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆነን እንድንገኝ ሊያደርገን ይችላል። እና ከሰማነውና ከታዘዝን
ያደርገዋል።
አዘጋጅና
አቅራቢ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ