ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሳይወዱት በግድ ወደ ጦርነት እየተገፉ ነው።ለምድር መሪዎች እንጸልይ።

ለምድር ታላላቅ አገሮች መሪዎች እንጸልይ። ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሳይወዱት በግድ ወደ ጦርነት እየተገፉ ይመስላል። ባለፉት አስር ቀናት ዓለም ከመቼውም በበለጠ ወደከፍተኛ ጦርነት እየተቃረበች መሆኑን ጉዳዩን በቅርቡ የሚከታተሉ ሁሉ ያስረዳሉ። አሜሪካ TRIDENT የሚባሉ የኑክሊየር ቦምብ ተሸካሚ ሚሳኤሎችን በFLORIDA አካባቢ በቅርቡ ፈተሸች። በነዚሁም ቀናት የሩሲያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ድሚትሪ ሮጎዚን የሩሲያ ዘመናዊ ሚሳኤሎች የአሜሪካንን የሚሳኤል መከላከያ በጣጥሰው ያልፋሉ ብለው ተናገሩ። የሩሲያ የስለላ መርከብ በአሜሪካ ምስራቃዊ ድንበር በባህሩ ላይ ስትሰልል መሰንበቷን በተመለከተ አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሲናገሩ “ለፖለቲካችን ጥሩ የሚሆነው ይችን የሩሲያ መርከብ ከውሃው ላይ መትቼ ማጥፋት ነው። ይህ ግን የኑክሊየር እልቂትን ያመጣል” ብለው የተናገሩትም ባለፈው ሳምንት ነው። በዚህ ባካፈልኳችሁ ዜና ላይ እንደምታዩት ደግሞ የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ 96 ከመቶ የሚሆኑት የሩሲያ የኑክሊየር ሚሳኤሎች በሙሉ ለመተኮስ ዝግጁ ናቸው የሚል ዘገባን ለሩሲያ ምክር ቤት አባላት አቅርበዋል። የእነዚህ ዜናዎች ለዓለም ሁሉ መለቀቅ ዓላማው ዜናውን ለተራው ህዝብ ለማድረስ ሳይሆን፣ ባላንጣዎቻቸውን ለማስጠንቀቅ ነው። አሜሪካና አጋሮቿም በሩሲያ ድንበር እጅግ ቀርበው በሚገኙ የኖርዌክ፣ የፖላንድ፣ የላትቪያ፣ የሊትዌኒያ እና የኢስቶኒያ ከተሞች እንዲሁም ደብሞ በሮማኒያ፣ በቡልጋሪያና ሌሎችም የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ከባድ የጦር መሳሪያዎችንና በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን እያሰፈረች ነው። ምእራባውያኑ ከቻይና፣ ከሰሜን ኮሪያና ከኢራን ጋር የገቡበት ውጥረትም በጣም እየከረረ መጥቷል። ባላፈው ሳምንት አሜሪካ የጦር አውሮፕላን እና ሚሳኤል ተሸካሚ መርከቦችን በደቡብ ቻይና ባህር እና በቀይ ባህር በሚገኘው በባብ ኤል መንደብ አካባቢ በማሰማራት ለጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል። ባለፈው እንደጻፍሁት፣ አይበለው እንጂ ጦርነት በተለይ በሩሲያና በአሜሪካ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና መካከል ከተነሳ የሰው ልጅ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው እልቂት ሊፈጠር እንደሚችል አያጠራጥርም። ከኢራንና ከሰሜን ኮሪያ ጋርም አሜሪካና አጋሮቿ ጦርነትን ቢያስነሱ የሚፈጠረው ጥፋት ትንሽ አይሆንም።
ከጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን እቅድ በቅርብ የተማረው ሃዋርያው ጴጥሮስ በ2ኛው መልእክቱ ምእራፍ 3 ቁጥር 10 ላይ እንዲህ ይላል: “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል። በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” 2ኛ ጴጥሮስ 3:10 ምናልባት ይህ በዘመናችን ያለውን የኑክሊየር ፍጥጫና ሊፈጠር ያለውን ጥፋት ያመለክት ይሆን? እያሉ የሚጠይቁ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራን ብዙ ናቸው። በእርግጥ ጌታ አምላክ ሰማይንና ምድርን ለማቃጠል የሰዎች የኑክሊየር የጦር መሳሪያ አያስፈልገውም። ነገር ግን የሰው ልጅም ራሱንና ይችን ዓለም ለማጥፋት አቆብቁቦ ባለበት በዚህ ሰዓት ይህን ማሰቡ ከአድማሱ ውጭ አይደለም።
ሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ላይ ሳለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መልአኩን ልኮ ከገለጠለት ብዙ ነገሮች አንዱ የአራቱ ፈረሶች መለቀቅ ነው። የመጀመሪያውን ነጭ ፈረስ ተከትሎ የሚመጣው ሁለተኛው ፈረስ መልኩ ዳማ (ቀይ) ሲሆን በእርሱም ላይ የተቀመጠው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድ እና ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ የማድረግ ስልጣንና ታላቅ ሰይፍ የተሰጠው ነው። በዚህ በቀዩ ፈረስ ላይም ሆነ በሌሎቹ በሶስቱ ፈረሶች ላይ የሚቀመጡት ምን ዓይነት ፍጥረታት እንደሆኑ ባይነገረንም፣ የእግዚአብሔርን ቁጣ በምድር ላይ የሚገልጡ፣ ትእዛዝ ሲሰጣቸው የሚሰሙና ያንንም ትዕዛዝ በትክክልና በፍጥነት የሚያስፈጽሙ እንደሆኑ እናነባለን። የሶስተኛው ቀይ ፈረስና በሱ ላይ ያለው ተቀማጭ ተልእኮ እጅግ የሚያስፈራ ነው። ብዙ የስነመለኮት አስተማሪዎች እነዚህ አራት ፈረሶች የሚለቀቁት ክርስቲያኖች ከምድር ላይ ከተነጠቁ በኋላ ነው ብለው ያስተምራሉ። እነዚሁ ምሁራንና አስተማሪዎች፣  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበሉ ክርስቲያኖች በምድር ላይ እያሉ በዮሐንስ ራእይ ላይ የተጻፉት ብዙዎቹ ትንቢቶች  (እነዚህን አራቱን ፈረሶችንም ጨምሮ) አይፈጸሙም ይላሉ። የትንቢት አፈጻጸም ቅደም ተከተል ይህ ነው ወይም ነው ብሎ መናገር ብዙ ጥንቃቄና የጌታን ፍርሃት የሚጠይቅ ስለሆነ ይህኛው ወገን ትክክል ነው ያኛው ትክክል አይደለም ማለት አያሻም። ነገር ግን በዓይናችን የምናየውና የምንሰማው ነገር ሁሉ የትንቢትን ፍጻሜ የሚመስል ከሆነ፣ በእርግጥ ትንቢት ሊፈጸም ነው ወይ ወይስ አይደለም ብሎ የእግዚአብሔርን ቃል መመርመር፣ በእውነተኛ ጸሎትና በተሰበረ ልብ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ አስፈላጊ ነው። ከእስራኤልና ታሪክ እንደምንማረው ተምረናል፣ አውቀነዋል፣ የኛ ዶክትሪን ብቻ ትክክል ነው ያሉት የእስራኤል የሃይማኖት መሪዎች በራሳቸ እውቀትና አስተያየት፣ እንዲሁም በቤተ መቅደስ ሥርዓታቸውና በሥልጣናቸው ላይ ከመመካታቸው የተነሳ እግዚአብሔር ወልድ ራሱ በመካከላቸው ሲመላለስ ሊያዩት አልቻሉም። ከጌታ ደቀመዛሙርት ብዙዎች ጌታ ኢየሱስ ስለኢየሩሳሌም መፍረስና ስለእስራኤል መበተን በተለይ በሉቃስ 21 ቁጥር 20 እስከ 24 የተናገረውን ስላስተዋሉና ስለታዘዙ 70 ዓም በኢየሩሳሌም ከሆነው ፍጅት አምልጠዋል፣ ለእኛም የደረሰውን ወንጌልን በስደት ምድራቸው ሰብከዋል። ሌሎች ግን ያንን የጌታን ማስጠንቀቂያ እምቢ ስላሉ በቤተ መቅደሱና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ በሆነው ጥፋትና ፍጅት ሞተዋል። በዚያ 0070 ዓም በኢየሩሳሌም ስለሆነው ፍጅት የሚያስረዱ ምሳሌዎችን እንዳላካፍላችሁ ቦታ ያጥረኛል። ባለፉት አራት ዓመታት፣ ማለትም 2013 ጀምሮ በምድር ላይ የዓመጽ መንፈስ እንደ ታላቅ ማዕበል ተነ ይህ ዓመጽ ብዙ መልኮች አሉት። አንደኛውና ዋነኛው በእግዚአብሔር ቃል ላይና እግዚአብሔር በደነገገው የተፈጥሮ ሥርዓት እንዲሁም ሞራላዊ ገደቦች ላይ የተነሳ ዓመጽ ነው። ሌላው ደግሞ ሰላማዊ፣ የበለጸጉና ያደጉ ናቸው በሚባሉት አገሮችና ህዝቦችም ዘንድ ሳይቀር ህዝቦች በህዝቦች ላይ እና መንግስታት በመንግስታት ላይ መነሳሳታቸው ነው። ቀዝቃዛው ጦርነት አበቃ፣ ሰላም ሆነ ከተባለባቸው ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረው አለም አቀፋዊ መረጋጋት በድንገት ወደ ቀውስ የገባ ቢመስልም የተዘናጋነው እኛ ነን እንጂ በበምስራቅና በምእራብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ሰላም የእውነት አልነበረም። ያለንበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ነው። ለምድር መሪዎች ሁሉ እንጸልይ። በተለይም ደግሞ የክርስቲያን አገሮች ናቸው ለሚባሉት ለአሜሪካና አጋሮቿ እና ለሩሲያ መሪዎች በተጨማሪም ደግሞ የጦርነት ከበሮን እየደለቁ ላሉት የሌሎቹ መንግስታት መሪዎች ወደልባቸው መለስ ብለው ሰብዓዊነታቸውን እንዲያስቡ፣ በየቢሮዎቻቸውና በየምሽጎቻቸው ሆነው ወደጥፋት የሚገፋፉአቸውን የክፉ መካሪዎች እምቢ እንዲሉና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሥልጣን ተላልፈው ሊያጠፉት የማይችሉትን የጦርነት እሳት እንዳይለኩሱ መጸለይ የእኛ ተግባርና ግዴታ ነው። የመንግስታትን ልብ እንደ ቦይ ውሃ መምራት የሚችለው አምላክና የምድር ሁሉ ጌታ እኛው የምናመልከው የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ፣ እነዚህን የምድር ታላላቅ መንግስታት መሪዎችንም ጨምሮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ለዘለለም እንዲኖሩና ይህን ምድርንም በአግባቡ እንዲንከባከቡ ነው። የተጻፈው ሁሉ ሊፈጸም የግድ ነው። እኛ ግን ጌታ ራሱ እንዳደረገው ከማማለድ ወደ ኋላ ልንል አይገባም። ጌታ ይባርካችሁ፣ ይጠብቃችሁም። ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ። 96% Russian nuclear ballistic missiles ready to be used at any moment


አምስተኛው የዓለም መንግስት ጉባኤ በዱባይ መካሄዱን ሰምታችሁ ይሆን? የበዓል ቤተ ጣዖት መግቢያ በር ቅጂ በዱባይ እንደተተከለስ አንብባችኋል ወይ?

በዚህ ባለፈው ሳምንት አምስተኛው የዓለም መንግስት ጉባኤ በዱባይ መካሄዱን ሰምታችሁ ይሆን? ከ1800 ዓመታት በፊት በፓልማይራ ሶሪያ ተሰርቶ የነበረውና በISIS የፈረሰው የበዓል ቤተ ጣዖት ቅጂ በ3D ማተሚያ ተሰርቶ በለንደን፣ በኒውዮርክ እና አሁን ደግሞ በዱባይ እንደተተከለስ አንብባችኋል ወይ?

“የዓለም መንግስት” ጉባኤ ማለት የምታውቁት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ አይደለም። ይህ ጉባኤ እንደሚካሄድ በዜና በሰፊው የሚዘገብ አይደለም። ከFEBRUARY 12 እስከ 14 የተካሄደው ይህ “የዓለም መንግስስት” ጉባኤ ግን ትንሽ ስብሰባ አይደለም። አራት ሺ (4000) የሚሆኑ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ የመንግስታት ባለስልጣኖች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋና ዲሬክተርም የተሳተፉበት ነው። ይህ ከ2013 ጀምሮ በዱባይ እየተካሄደ ያለ ታላቅ ስብሰባ ከመጀመሪያው ዓመት ስብሰባው ተካፋዮች አንዱ የጊዜው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ነበሩ። ታዲያ እንዲህ ያለ ታላቅ ጉባኤ እየተካሄደ ሳለ የተበላ የተተፋው ሁሉ ዜና ተብሎ በሚቀርብበት በምእራቡ ዓለም እንኳን እንደ ታላቅ ዜና አይቀርብም።  ለዚህም ነው ብዙ የታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜን የሚከታተሉ ምሁራን ይህ “የዓለም መንግስት” ወይም “WORLD GOVERNMENT” የተባለው የቱ ነው? መቼ ነው የተመሰረተው? ማን መሰረተው? የተባበሩት መንግስታት እያለ ይህ ለምን አስፈለገ? ወይም ደግሞ ምናልባት በመጨረሻው ዘመን ይገለጣል የተባለው በሃሰተኛው ክርስቶስ ስር የሚመራው አንድ የዓለም መንግስት ጥንስስ ይሆን ወይ እያሉ ጥያቄዎችንና መላምቶችን እየሰነዘሩ ያሉት? በዚህ ዓመቱ አምስተኛ ስብሰባው ላይ ከ130 የዓለም አገሮች የተውጣጡ መሪዎች የተገኙበት ይህ ጉባኤ በምድራችን ላይ ያሉ ዋና ዋና የሚባሉ እንደ “የዓለም የኢኮኖሚ መድረክ WORLD ECONOMIC FORUM” ያሉ እና ሌሎችም ትልልቅ ድርጅቶች የተሳተፉበት ነው? ብዙ የትንቢት ፍጻሜን የሚከታተሉ ምሁራንን ከሚከነክነው ነገሮች አንዱ ደግሞ የሚከተለው ነው። ቁመቱ 20 ጫማ የሚሆን ከ1800 ዓመታት በፊት በፓልማይራ ሶሪያ ተሰርቶ የነበረውና ISIS ያፈረሱት የበዓል ቤተ ጣዖት መግቢያ ታላቅ በር (ARCH) በ3D ማተሚያ የተሰራ ምስል በ2016 ዓም ተሰርቶ በለንደንና በኒውዮርክ በአደባባይ ቆሞ ነበር። አሁን ደግሞ ይህ በር የዓለም መንግስት ጉባኤ በሚካሄድበት በዱባይ ተተክሎ ሰንብቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን በዓል የሚባለው ጣዖት በብዙ ስሞች በየአገሩ ይጠራ እንጂ ከጥፋት ውሃ በኋላ በባቢሎን ተመስርቶ የነበረው አንድ የዓለም መንግስት ገዢና አምላክ ተብሎ የሚመለክ ነበር። ይህ አምላክ በሮም አፖሎ፣ በግሪክ ዙስ፣ በግብጽ አይሲስና በሌሎችም አገሮች የተለያዩ ስሞችን ይዞ እስከዛሬም ድረስ በስውር የሚመለክ ነው። በተለምዶ እንደሚነገረን ጣዖት ድንጋይና ብረት ሳይሆን ከበስተጀርባው እጅግ ኃይለኛ የሆኑ የወደቁ መላእክትና የአጋንንት መናፍስትን የሚወክል ነው። በዓል የሚባለው መንፈስ ደግሞ በመጨረሻው ዘመን ከጥልቁ እንደሚወጣ በዮሃንስ ራእይ የተነገረለት የሃሰተኛው ክርስቶስ መንፈስ እንደሆነ ብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት አስተማሪዎች ይስማሙበታል። ታዲያ ይህ የፈረሰው የፓልማይራው የበዓል ቤተ ጣዖት መግቢያ በር ቅጂ ለምንድ ነው እንደገና በ2016 ዓም የተሰራውና በዓለም ዋና ዋና ከተማዎች ሁሉ በአደባባይ ሊተከልና ሊታይ የተፈለገው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለምንድ ነው ይህ አምስተኛው የዓለም መንግስት ጉባኤ በሚካሄድበት በዱባይ ከተማ የተተከለው። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ታዲያ ይህ የዓለም መንግስት ጉባኤ የተባለው ምናልባት በመጨረሻው ዘመን ይመጣል የተባለው በሃሰተኛው ክርስቶስ የሚመራው አንድ የዓለም መንግስት ጥንስስ ይሆን ወይ እያሉ ብዙዎች እንዲጠይቁ ያነሳሳው። የተያያዙትን ዜናዎች የኢንተርኔት ማገናኛዎች (LINKS) ከዚህ ቀጥሎ ልኬያቸዋለሁና አንብቡአቸው። መጽሃፍ ቅዱሳችንን፣ በተለይም የዚህን ዘመን መልክ የሚያስረዱንን ትንቢቶች ቀረብ ብለን እናጥና። በዓለም ላይ እየተካሄዱ ያሉትን ትንቢት ነክ ዜናዎች ከልብ እናስተውል።የጌታ መምጣት እየተቃረበ ሲሄድ ዓለም ሁሉ በትልቅ ስህተት ውስጥ እንደሚገባ ተጽፎአል። በክርስቶስ የምናምን ሁሉ ግን መጽሐፍ ቅዱስን በእጃችን ይዘን እና፣ የእግዚአብሔር መንፈስም ወደእውነት ሁሉ ሊመራን ዝግጁ ሆኖ ሳለ ዓለም በሚሳሳትበት ስህተት መሳሳት የለብንም። ጌታ እግዚአብሔር ክርስቶስን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ ይስጠን።  ለበለጠ መረጃ የሚከተሉትን ማገናኛዎች በመከተል አንብቡ። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ አንድ የዓለም መንግስት ጉባኤ በዱባይ ተካሄደ፣ የበዓል ቤተ ጣዖት መግቢያ በር በዱባይ ተተከለ

ዓለም ለትልቅ ጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል፣ ክፍል 2

ዓለም ለከፍተኛ ጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል 
ክፍል 2 (ከክፍል 1 የቀጠለ - ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የድረ ገጽ ማገናኛ በመጫን የተያያዘውን ዜና ተመልከቱ)

ይህ ያስቆጣቸው ምእራባውያኑም ሩሲያን G8 ከሚባለው ቡድን ውስጥ በማስወጣትና የተለያዩ የኢኮኖሚ እቀባዎችን በሩሲያ ላይ በመጣል ተበቀሉ። በዩክሬን የተፈጠረው ቀውስ በአገሪቱ በስተምስራቅና በስተደቡብ ምስራቅ ያሉ እና የሩሲያ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች የሚበዙባቸው ክልሎችም ተስፋፋ። ከነዚህም ክልሎች ሁለቱ ከልሎች ከማእከላዊው የዩክሬን መንግስት ለመገንጠል እና ወደሩሲያ ለመደባለቅ ያደረጉት እንቅስቃሴ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተለውጦ ብዙ ሺ ህዝብ አልቆአል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ተሰደዋል። ምእራባውያኑም ይህንን ጦርነት የምትደግፈው ሩሲያ ናት በማለት ይከሳሉ። ሩሲያ እነዚህን ለመገንጠል የሚፈልጉ ክልሎች ወደራሷ ግዛት ለማስገባት ፍላጎት እንደሌላት ብትገልጽም፣ በነዚያ ክልሎች ያሉትን ሩሲያዊ ዝርያ ያላቸውን ህዝቦች መደገፍዋን ግን አትደብቅም። ይህ ሁኔታ እየተካረረ መጥቶ ዛሬ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ ሌሎችንም የምስራቅ አውሮፓ አገሮችን ልትወርና የአውሮፓን ሰላም ልታናጋ ትችላለች በሚል ሰበብ ብዙ ሰራዊትን እና የጦር መሳሪያዎችን በሩሲያ ድንበር አጠገብ ወዳሉ አገሮች እያሰፈሩ ነው። ባለፉት ስምንት ወራት አሜሪካና አጋሮቿ ከ2500 በላይ ታንኮችን እና ከ100 በላይ የጦር ሄሊኮፕተሮችን እንዲሁም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ላትቪያ፣ ሊትዌኒያ፣ ኢስቶኒና፣ ፖላንድ እና ሌሎችም አገሮች አስገብተዋል። የሩሲያን ስትራቴጂካዊ የኑክሊየር ሚሳኤሎች ሊያመክን እና የሩሲያንም ግዛት ለምእራባውያን ሚሳኤሎች ሊያጋልጥ የሚችል የራዳር ጣቢያ  አሜሪካ በቡልጋሪያ የከፈተችው ባለፈው ዓመት ነበር። ሩሲያም በበኩሏ የጦር ሰራዊቷን በማስፋፋት፣ እንደገና በማዋቀርና በአዳዲስ የጦር መሳሪያዎች በማስታጠቅ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረች ውሎ አድሮአል። በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በአሜሪካና በሶቪየት ህብረት መካከል ተደርገው የነበሩ ስምምነቶች ሁለቱ አገሮች የኑክሊየር መሳሪያዎቻቸውን በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀንሱ አስችለዋቸው ነበር። ዛሬ ግን ከነዚያ ስምምነቶች አንዳንዶቹ ስለፈረሱ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን የመስራቱ እሽቅድምድም ተጧጡፏል። ታዲያ ይህ ሁሉ ወዴት ነው የሚያመራው የሚለውን ለመመለስ እጅግ አዳጋች ባይሆንም፣ በጉዳዩ ላይ የቅርብ እውቀቱ ያላቸውን መስማቱ ደግሞ እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በዓለም ላይ ያለው የሰላም ቀውስ በሩሲያና በምእራባውያን መካከል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ አገሮችንም የሚነካካ ጉዳይ ነው። በደቡብ ኮሪያ የሰፈረው የአሜሪካ ጦርና ጃፓን ያሰጉኛል ብላ ኑክሊየር ቦምቦችን እና ሚሳኤሎችን እየሰራችና እየፈተሸች ያለቸው ሰሜን ኮሪያ፣ የምእራባውያንን እና በሳውዲ አረቢያ የሚመራውን የሱኒ እስላሞች ኃይል ለመቋቋም ወታደራዊ ኃይሏን በከፍተኛ ደረጃ እየገነባች ያለችው ኢራን፣ በደቡብ ቻይና ባህር፣ በጃፓን፣ በኮሪያ ባህረ ገብ መሬት፣ በጃፓን እና በሌሎችም የእስያ ክፍሎች ቻይና በወታደራዊ ኃይል ያለልክ ያለፈ እንዳትስፋፋ ለመግታት አሜሪካ የምታደርገውን ጥረት ለመቋቋም ቻይና ራስዋ በከፍተኛ ፍጥነት እያደረገችው ያለው የጦር መሳሪያ ማምረት፣ የጦር ሰፈሮችን የመስራትና ወታደሮቿን የማሰልጠን ተግባር፣ ሺያ እስልምናን ከምትከተለው ከኢራንና በሷም ከሚደገፉ በየመን ካሉ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በየመን ግልጽ ጦርነት ውስጥ የገባችው ሳውዲ አረቢያና ሌሎችም ትልልቅ የጦር ኃይል ያላቸው አገሮችም በከፍተኛ ፍጥነትና ወጭ ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው።

ጦርነትና የጦርነት ወሬ የጌታን ዳግም ምጽዓት መቃረብ ከሚያመለከቱት ነገሮች አንዱ መሆኑን በማቴውስ ምዕ 24 እና በሉቃስ 21 ላይ እናነባለን። እነዚህም ከምጥ ጣር መጀመሪያዎች አንዱ እንጂ ብቸኛ አመላካች አይደሉም። በየትኛውም ዘመን ቢሆን ጦርነት አጥፊና አሰቃቂ መሆኑ የታወቀ ነው። በዚህ ዘመን፣ በተለይም ደግሞ በታላላቆቹ የዓለም መንግስታት በአሜሪካ፣ በሩሲያ፣ በቻይና እና በተባባሪዎቻቸው መካከል የሚነሱ ጦርነቶች በሰው ዘር ላይ ሊያመጡት የሚችሉት ጥፋት ግን እጅግ ከባድና ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “እነዚያ ቀኖች ባያጥሩስ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር” ካለ፣ ሊሆን የሚችለውን ጥፋት የሰው ቋንቋ ሊገልጸው አይችልም። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ ለመንግስታት እና በየደረጃው ላሉ መሪዎች ሁሉ መጸለይ ያስፈልገናል። የተጻፈው ሁሉ የሚፈጸም ቢሆንም ይኼ ያለንበትና የወንጌል ጸጋ ለሰዎች ሁሉ እንዲሰበክ እግዚአብሔር የሰጠን ዘመን ከመዘጋቱ በፊት ኃላፊነታችንን ወንጌልን በመስበክ፣ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በቅድስና እና በፍቅር በመኖርና ለሌሎች የእግዚአብሔርን ፍቅር በማሳየት ልንወጣ ይገባናል። የሰላም አምላክ ልባችንን ለዚህ ያነሳሳ። ከ2500 በላይ የአሜሪካ ታንኮችና፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና መድፎች አውሮፓ ገቡ 
ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ

ዓለም ለትልቅ ጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል _ክፍል አንድ

ክፍል አንድ

 (ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ የተሰጠውን የድረገጽ ማገናኛ በመጫን የተያያዘውን ዜና አንብቡ)

ከ2012 መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ዓለማችን ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ገብታ ወደማታውቅበት ከፍተኛ የጦርነት አደጋ ውስጥ ገብታለች። ብዙዎቻችሁ እንደምታስታውሱት በ2014 እኤአ በዩክሬን የነበረው በህዝብ የተመረጠ መንግስት  በምእራባውያን (በተለይም አሜሪካ) ግፊትና እነሱም ለተቃዋሚዎች በሰጡት ድጋፍ ምክንያት ተገለበጠ። በዚያኑ አካባቢ ነበር የአረብ ስፕሪንግ ስም የተሰጠውና ለብዙ ዘመናት በስልጣን ላይ የቆዩ የተለያዩ የዓረብ አገሮች መንግስታት ተራ በተራ ይገለበጡ የነበረው። ለምሳሌ የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ፣ የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ እና የቱኒሲያው ፕሬዝደንት ቤን አሊ መገልበጥ አይዘነጋም። በጊዜው በሰፊው ይናፈስ የነበረው ዜና እነዚህ የመንግስት ግልበጣዎች የአገሮቹ ህዝቦች ያመጡአቸው አብዮቶች ውጤት እንደነበር ቢሆንም ከዚያ በኋላ የወጡ ብዙ መረጃዎች ግን ያ የአረብ ስፕሪንግ ይባል የነበረው አሁንም አንዳንድ የምእራባውያን አገሮች የማይፈልጓቸውን መንግስታት ከስልጣን ለማስወገድ የወጠኑት እቅድ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይ ደግሞ በሊቢያ የተደረገው የመንግስት ግልበጣ ምእራባውያንና አጋሮቻቸው በቀጥታ የተሳተፉበት እንገነበር ግልጽ ነው። ታዲያ ያንን የአረብ ስፕሪንግ የተባለውን መንግስታትን የመገልበጥና የአገሮችን አስተዳደር በአሜሪካና በአጋሮቿ መልክ ለመቅረጽ እየተለኮሰ የነበረውን ሰደድ እሳት ወደ ዩክሬን እና ሶሪያ ለማስፋፋት በሚሞከርበት ጊዜ በታላላቆቹ የዓለም የጦር ኃይል ባለቤቶች ማለትም አሜሪካና አጋሮቿ በአንድ በኩል እና በሌሎች ታላላቅ አገሮች፣ በተለይም በሩሲያ  መካከል ብዙ ውጥረት መፈጠር ጀመረ። ሶቪየት ህብረት በፈራረሰ ጊዜ ሩሲያ እንደገና ተነስታ ምእራቡን ዓለም ልትገዳደር አትችልም የሚል እምነት አድሮባቸው የነበሩ ምእራባውያን መንግስታት ዲሞክራሲን ለማስፋፋት በሚል ሽፋን የማይፈልጓቸውን መንግስታትን የመቀያየርና አገሮችንም አፈራርሶ አዳዲሶችን የመመስረት ዓላማቸውን ቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩትና በሶቪየት ህብረት ጥላ ስር በነበሩ የምስራቅ አውሮፓና ሌሎችም ከሩሲያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ወዳላቸው አገሮች ማስፋፋት ከጀመሩ ውሎ አድሮአል። የዩጎዝላቪያ መፈራረስ፣ በተለይም ደግሞ የሰርቢያ ታሪካዊ አካል የነበረችው የኮሶቮ በምእራባውያን ግፊት መገንጠል፣ በዩክሬን እና በጆርጂያ የተደረጉ የቀለም አብዮቶች ሩሲያን እጅግ አስቆጥተዋል። እንዲሁም ደግሞ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አከተመ በተባለበት ጊዜ በሶቪየት ህብረት ሲመራ የነበረው WARSAW የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ሲፈርስ ምዕራባውያን መርተውት የነበረው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ግን በመፍረስ ፈንታ የበለጠ እየተስፋፋ እና ይባሱኑ ደግሞ ቀደም ሲል የሶቪየት ህብረት አካል እና በሶቪየት ህብረት ጥላ ስር የነበሩ አገሮችን አባል በማድረግ ግዛቱን ወደ ሩሲያ ድንበር እጅግ እያስጠጋ መጣ። ይህ ነገር ያሰጋትና ያሰለቻት ሩሲያ በሶቪየት ህብረት መፍረስ ተዳክሞ የነበረውን የጦር ኃይሏን ባልተጠበቀ ፍጥነት ዘመናዊ ካደረገችና ካጠናከረች በኋላ አሜሪካንና አጋሮቿን አሁንስ በዛ ያለች ይመስል በዩክሬን ምእራባውያን የደገፉት የመንግስት ግልበጣ ሲደረግ፣ ለረጅም ዘመናት የሩሲያ አካል የነበረውንና በሶቪየት ህብረት ዘመን ወደ ዩክሬን ተደባልቆ የነበረውን የክራይሜያን ግዛት ወደራሷ ደባለቀች። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን የዛሬዋ ዩክሬንም የሶቪየት ህብረት አካል እንደነበረች ነው። የምእራባውያኑም እቅድ ዩክሬንን ደረጃ በደረጃ የአውሮፓ የጋራ ገበያ እና የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል በማድረግና ኃይላቸውን በቀጥታ በሩሲያ ድንበር ላይ በማስፈር ሩሲያ በጥቁር ባህር ላይ ያላትን ታላቅ የጦር ኃይል በማምከን እና አገሪቱ ከጥቁር ባህር ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የምትተላለፍበትን መንገድ በራሳቸው ኃይል በመክበብ ሩሲያ በዓለም ላይ ያላትን ስትራቴጂያዊ ኃይል ለማዳከም መሆኑ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ነው። ይህ ያስቆጣት ሩሲያም ሳልቀደም ልቅደም በማለት በሶቪየት ህብረት ዘመን ከሩሲያ ግዛት ስር ተከፍሎ ወደዩክሬን ገብቶ የነበረውን የክራይሜያን ክልል ወደራሷ በመደባለቅ የምዕራባውያኑን ሙከራ አመከነች። የቀድሞ የሶቪየት ህብረት ፕሬዝዳንት የነበሩት ጎርባቼቭ ዓለም ለጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል አሉ

ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ  ክፍል 2 ከታች ይቀጥላል

ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ማቴ 24:6

            (ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ የተሰጠውን የድረ ገጽ ማገናኛ በመጫን የተያያዘውን ዜና አንብቡ)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽዓቱ መዳረስ ደቀመዛሙርቱ በጠየቁት ጊዜ ከሰጣቸው ምልክቶች አንዱ “ጦርንም እና የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው” ማቴዎስ 24:6 የሚል ነበር። ቃየል ወንድሙን አቤልን ከገደለው በኋላ የሰው ልጅ ከጦርነት ያረፈበት ረጅም ዘመን ባይኖርም የጌታ መመለስ ሲቃረብ በምድር ላይ የሚታዩት ጦርነቶች ግን እጅግ ታላላቅና ብዙ ህዝብን የሚፈጁ መሆናቸው በመጽሀፍ ቅዱስ ተገልጦአል። ያለፈው 20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን በሰው ልጅ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶችን፣ ማለትም አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶች ያየችበት ጊዜ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከአስራ ሰባት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ሲያልቅ የቆሰለው ደግሞ ከሃያ ሚሊዮን በላይ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሞተው ህዝብ ደግሞ ወደ ስድሳ (60) ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን በጦርነቱ ሳቢያ በመጣ ረሃብና በሽታ ያለቁት ደግሞ ወደ ሃያ (20) ሚሊዮን ናቸው። ይህም በጠቅላላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያለቀውን ህዝብ ቁጥር ወደ ሰማኒያ (80) ሚሊዮን ያደርሰዋል። እነዚህ ከ1914 እስከ 1918 እና ከ1939 እስከ 1945 የተካሄዱ ሁለት የዓለም ጦርነቶች የፈጁት ህዝብ ከመቶ (100) ሚሊዮን በላይ ነው ማለት ነው። በአገር ደረጃ ብናየው ደግሞ ያለቀው ህዝብ ቁጥር ዛሬ በምድር ላይ ከሚገኙት 196 አገሮችና ግዛቶች ውስጥ አናሳ የህዝብ ቁጥር ያላቸውን 71 (ሰባ አንድ) አገሮች በሙሉ የሚደመስስ ነበር ማለት ነው። እነዚህ ሁለት የዓለም ጦርነቶች ምንም ያህል ትልልቅ ቢሆኑም ታዲያ፣ ገና ሊመጡ ካላቸው ጦርነቶች ጋር ሲወዳደሩ እጅግ ትንሽ እንደሚሆኑ ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ። ዛሬ በዓለማችን ላይ ካሉት የጦር መሳሪያዎች ዓይነትና ብዛት ጋር ሲመዛዘኑ የሰው ልጅ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተዋጋባቸው መሳሪያዎች እጅግ ኋላ ቀርና ደካማ ነበሩ። በሂሮሺማ ጃፓን ላይ የተጣለው የአቶሚክ ቦምብ ጉልበቱ አስራ አምስት ሺ ኪሎ ቲኤንቲ (15KILO TON TNT) ሲሆን በናጋሳኪ ላይ የተጣለው ደግሞ ጉልበቱ ሃያ ሺ ኪሎ ቲኤንቲ (20 KILO TON) ነበር። እነዚያ ሁለት ቦምቦች በድምሩ ከ129ሺ እስከ 246 ሺ ወታደሮችና ሲቪል ህዝቦችን አሰቃቂ በሆነ መንገድ ፈጅተዋል። በሂሮሺማ ላይ የተጣለው ቦምብ ክብደቱ አራት ሺ አራት መቶ ኪሎግራም ሲሆን የናጋሳኪው ደግሞ 4670 ኪሎግራም ነበር። በዘመኑ እጅግ ታላቅ የተባሉት እነዚያ አቶሚክ ቦምቦች ጉልበት ከዛሬዎቹ ጋር ሲወዳደር ታዲያ እነዚያ የ1945ቶቹ የሚመደቡት በጣም ትንንሽ ወይም በሰው የጀርባ ቦርሳ ሊያዙ ይችላሉ ከሚባሉት ጋር ነው። ሩሲያ በቅርቡ እንደሰራችው የተዘገበው RS28 SARMAT የሚባለው የኑክሊየር ቦምብ(ሚሳኤል) ሶቪየት ህብረት ሰርታው የነበረውን RS36 SATAN የተባለውን የሚተካ ሲሆን፣ ይህ ቦምብ እንግሊዝን ወይም ፈረንሳይን የሚያህል አንድን አገር በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ የሚያጠፋ እንደሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህንን እና ከዚህ አነስ የሚሉ ከ13800 (አስራ ሶስት ሺህ ስምንት መቶ) የኑክሌየር ቦምቦች ዛሬ በአገሮች እጅ ውስጥ አሉ። ከነዚህም ውስጥ 3530 የሚሆኑት በማንኛውም ሰዓት ለመተኮስ ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ይጠብቃሉ። ሩሲያ 7000 የኑክሌየር ቦምቦች እንዳሏት ሲገመት አሜሪካ ደግሞ 6800 እንዳሏት ይዘገባል።  ከዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆኑት እነዚህ ምድርን አጥፊ መሳሪያዎች የሚገኙት በአሜሪካና በሩሲያ እጅ ነው። ሁለቱ አገሮች ብቻ በድምር 13800 ቦምቦች ሲኖሩአቸው ታናናሽ የኑክሌየር ሃይሎች የሚባሉት ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን፣ ህንድና እስራኤል ደግሞ በድምሩ 1105 ቦምቦች አሉአቸው። ሰሜን ኮሪያም ይህ መሳሪያ እንዳላት በሰፊው ይዘገባል። “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር ብሎ ጌታ በማቴዎስ 24:22 ላይ የተናገረው እነዚህና ሌሎችም ብዙ የዘመናችን አስፈሪ የጦር መሳሪያዎች የሚያመጡትን እልቂትም ሊመለከት እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትና የሳይንሱ እውቀት ያላቸው ሰዎች ያስረዳሉ። ዓለማችን በዚህ ዓይነት የፍጅት ፍጥጫ ውስጥ ሆና እያለች ነው ከ2012 ጀምሮ ብዙዎች፣ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት በቅርቡ ሊነሳ ይችላል የሚሉት። የካቶሊኩን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እንዲያውም ይህ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት አሁንም ትንሽ በትንሽ ጀምሮአል በማለት ደጋግመው ተናግረዋል። ልብ እንበል፣ ይህ የአፍ ወለምታ አይደለምና። አሜሪካና አጋሮቿ በአንድ በኩል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና ሌሎችም አገሮች ከባድ በሆነ የጦርነት ዝግጅት ውስጥ ከገቡ ዓመቶች እየተቆጠሩ ነው። ካለፈው ዓመት የክረምት ወራት (SUMMER) ጀምሮ አሜሪካ ብቻ ከ2500 በላይ ታንኮችን እና በቅርቡ ደግሞ ከ100 በላይ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ወደ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ፖላንድ እና ሶስቱ የቦልቲክ ሪፐብሊክ ወደሚባሉት አገሮች አስገብታለች። ሩሲያ በበኩሏ ሰራዊቷን በሙሉ በተጠንቀቅ ላይ በማቆም ከፍተኛ የጦርነት ልምምዶችን እያደረገች ነው። በደቡብ የቻይና ባህር አካባቢም አሜሪካና ቻይና በፍጥጫ ላይ ናቸው። ሰሜን ኮሪያም በበኩሏ የኑክሌየር ቦምቦች እና የሚሳኤል ተኩስ ልምምዶችን እያደረገች መሆኑ በየእለቱ የሚዘገብ ነው። ጦርነት በድንገት አይፈነዳም። ኃይለኞቹ የዓለም አገሮች ሁሉ ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። የሶቪየት ህብረት የመጨረሻ ፕሬዝደንት የነበሩት ሚካኤል ጎርባቾቭ በቅርቡ ይህን በማስመልከት ሲናገሩ ዓለም ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት በከፍተኛ ፍጥነት እየተዘጋጀች ነው በማለት አስጠንቅቀዋል። የዓለም ከፍተኛ የኑክሊየር ባለሙያዎች ማህበርም ዓለም በኑክሊየር ጦርነት ልትጠፋ የቀራት ሁለት ደቂቃ ነው በማለት አስጠንቅቀዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። ዳሩ ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመነ ክርስቲያን ሊፈራ አይገባውም። ማወቅ፣ መጸለይ፣ በልብ መዘጋጀትና ለሚጠፉት ወንጌልን መስበክ ግን ግዴታችን ነውና እንትጋ። በሚቀጥሉት መልእክቶቼ ላይ የበለጠ ዝርዝርን ለመስጠት እሞክራለሁ። ከ100 በላይ የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተሮች አውሮፓ ገቡ
እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ ልባችሁንም በሰላሙ ይጠብቅ። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የባህር የየብስና የአየር እንስሳት በማይታወቁ ምክንያቶች በታላቅ ቁጥር እያለቁ ነው

ባለፉት ስድስት ዓመታት በምድር ሁሉ ምክንያቱ ሳይታወቅ በብዛት እያለቁ ያሉት የባህር እንስሳት ቁጥር ብዙ እጥፍ ጨምአል በታወቁ በሽታዎች በየጊዜው ከሚያልቁት ዶሮዎችና ሌሎች የየብስ እንስሳት በተጨማሪ እጅግ ብዙ የሰማይ ወፎችና ሌሎችም ፍጥረታት ባልታወቁ ምክንያቶች በታላቅ ቁጥር በየስፍራው እየሞቱ ነው። በተለይም ደግሞ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የባህር እንስሳት ማለቃቸውና ለዚህም አሳማኝ መረጃ ያለመገኘቱ ብዙዎችን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ነው። በብዛት እንደምክንያት ሲሰጥ የከረመው የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መበከል ነው የሚል ነበር። ሰሞኑን እየወጡ ያሉ ዜናዎች ግን አንዱና ዋናው ምክንያት በ2011 በጃፓን የምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት የተቃጠለው የፉኩሺማ የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ወደ ከባቢ አየርና በተለይም ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ እየለቀቀ ያለው በጣም ከፍተኛ የጨረር መጠን መሆኑን እያመላከቱ ነው። ይህ ብክለት ከፓሲፊክ ውቅያኖስም አልፎ ወደሌሎቹ የምድር ውቅያኖሶችና ባህሮች እንደደረሰና በባህር ውስጥ እያለቁ ላሉት እንስሶች ሞትም መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀር ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ቢናገሩም ዜናው ግን ጎልቶ አልወጣም።  በፉኩሺማው ኃይል ማመንጫ መፈንዳትም ሆነ ሌላ በማንሰማው ምክንያቶች እየተከሰተ ያለው የባህር ብክለትና የእንስሳት እልቂት ከባህር የሚገኙ ምግቦችን እየበከለ መሆኑ የማያጠራጥር ነው። ማገናኛው ከታች በተሰጠው ድረገጽ ላይ እንደምትመለከቱት እነዚህ እልቂቶች በዓለም ሁሉ እና በአማካይ በየእለቱ የሚታዩ ክስተቶች ናቸው።

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ ሲሄድ፣ በተለይም ደግሞ በታላቁ የመከራ ዘመን በምድር ላይ ከሚሆኑት እጅግ አስፈሪ ሁኔታዎች አንዱ በምድር ላይ ያሉ ዛፎችና ተክሎች ሲሶ መቃጠል፣ በባህርና በወንዞች እንዲሁም በሐይቆች እና ሌሎችም የውሃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት ሲሶ መሞት እንደሆነ የዮሐንስ ራዕይ ምዕ 8 ቁጥር 6 እስከ 11 ይናገራል። ዛሬ እየተከሰተ ያለው የባህር፣ የየብስና የአየር እንስሳት ማለቅ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ነው እያልሁ አይደለም። ነገር ግን በምድራችን ላይ እየተከሰቱ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ ዜና ስንሰማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መመርመር ለክርስቲያን ሁሉ አስፈላጊ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በጥሞና ማንበብ መማርና ማጥናት ያስፈልጋል።


ብዙ ሰው ዜና እሰማለሁ በአካባቢዬና እና በዓለም ዙሪያ ሰለሚሆኑት ነገሮችም ሁሉ መረጃ አገኛለሁ ብሎ ያምናል።  እስከቅርብ ዓመታት ድረስ ብዙዎቻችን ደግሞ ዜና ሰማን ብለን የምናስበው ቴሌቪዥን በማየት ወይም ሬድዮ በመስማት፣ ጋዜጦችን በማንበብ ነበር። ዘመኑ ያመጣው ኢንተርኔት ተጨማሪ የዜና ምንጮችን ቢፈጥርም እውነቱን ከውሸቱ፣ ፕሮፓጋንዳውን ከመረጃው መለየት እጅግ አስቸጋሪ ነው። የታወቁ ናቸው፣ ትልልቅ ናቸው ብለን የምናምናቸው የዜና ምንጮችም ቢሆን ዜና ብለው የሚያቀርቡልን ባለቤቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንድናምነው የሚፈልጉትን እንጂ ልናውቀው የሚገባውን አይደለም። በተለይ ደግሞ የቴሌቪዥን ዜና ከመዝናኛ ተለይቶ በማይታይበት በምዕራቡ ዓለም ያሉ ብዙ የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች የሚያተኩሩት ተመልካችና ሰሚን በመሳብ የሚያገኙትን ትርፍ እና የባለቤቶቻቸውን ዓላማዎች በማራመድ ላይ ያተኮሩ ስለሆኑ በዓለማችን ላይ በእርግጥ ስለሚሆኑት ነገሮች ሁሉ መረጃን አይሰጡንም። ይህም አዲስ አይደለም። ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቶ ሳለ ይህ በፍጥረተ ዓለም ሁሉ ዋና ዜና መሆን የነበረበት ተአምር በኢየሩሳሌም ከተማና በእስራኤል እንኳን ርዕሰ ዜና  አልነበረም። በዚያ ፈንታ "የዚያን ሮማውያን የገደሉትን የገሊላውን መሲህ ነኝ ባይ አስከሬን ደቀመዛሙርቱ ከመቃብር ሰረቁት" የሚል ወሬን ነበር የቤተመቅደሱ አለቆች ጉቦ በመክፈል ያስወሩት።  ስለዚህ ሃሰተኛው ክርስቶስም በምድር ላይ ሲገለጽ “ሃሰተኛው ክርስቶስ ተገለጸ” የሚል ዜና ለመስማት ተስፋ አናድርግ። ይልቁንም ልንሰማ የምንችለው “ዓለማችንን ካለችበት ቀውስ ሁሉ ለማውጣት የሚረዳን ታላቅ መሪ መጣልን” የሚል ዜና ነው።

ስለዚህ በምድር ላይ የሚከሰቱት ታላላቅ ነገሮች ያላቸውን መንፈሳዊ ዋጋ በሚገባ መረዳትና መገምገም የምንችለው በመጀመሪያ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ከዘለዓለም ጨለማ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ስንሸጋገር ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መንፈሳዊ ምግባችን ማድረግ ያስፈልጋል። በቃሉ የተማርነው ከህይወታችን ጋር ተዋህዶ የነገሮችን ዘለዓለማዊ ፍጻሜ ማስተዋል እንድንችል ደግሞ መጸለይና ለተረዳነው እውነት በመታዘዝ መኖር ያስፈልጋል። በጎም ይሁን ክፉ በምንሰማውን ዜና እንዳንታወክ ልባችንን እንጠብቅ። መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም መጨረሻ የሚለው የክፉውን የዓለም ስርዓት ፍጻሜ ነው።  እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ሃሳቡም በክርስቶስ ለተጠሩ ግን ያ የዓለም ፍጻሜ የተባለው የነገስታት ንጉስና የጌቶች ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ሊነግስ እንደሆነ የሚያሳይ የምጥ ጣር ምልክት ነው። ዜናን ስንሰማ እንደ ክርስቲያን እንስማ። የምናየውንና የምንሰማውን በስሜታችን ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እውነት እንፈትነው። በጎ ከሆነ እግዚአብሔርን እናመስግን። ክፉ ዜና ከሆነ ደግሞ የየትኛው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ በመመርመር ለመረዳት እንሞክር። በሁሉም ደግሞ እግዚአብሔርን እናክብር እንጂ በክርስቶስ ከቆምንበት ከመንፈሳዊ ስፍራችን አንናወጥ። http://www.end-times-prophecy.org/animal-deaths-birds-fish-end-times.html

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...