የባህር የየብስና የአየር እንስሳት በማይታወቁ ምክንያቶች በታላቅ ቁጥር እያለቁ ነው

ባለፉት ስድስት ዓመታት በምድር ሁሉ ምክንያቱ ሳይታወቅ በብዛት እያለቁ ያሉት የባህር እንስሳት ቁጥር ብዙ እጥፍ ጨምአል በታወቁ በሽታዎች በየጊዜው ከሚያልቁት ዶሮዎችና ሌሎች የየብስ እንስሳት በተጨማሪ እጅግ ብዙ የሰማይ ወፎችና ሌሎችም ፍጥረታት ባልታወቁ ምክንያቶች በታላቅ ቁጥር በየስፍራው እየሞቱ ነው። በተለይም ደግሞ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የባህር እንስሳት ማለቃቸውና ለዚህም አሳማኝ መረጃ ያለመገኘቱ ብዙዎችን እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ነው። በብዛት እንደምክንያት ሲሰጥ የከረመው የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መበከል ነው የሚል ነበር። ሰሞኑን እየወጡ ያሉ ዜናዎች ግን አንዱና ዋናው ምክንያት በ2011 በጃፓን የምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት የተቃጠለው የፉኩሺማ የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ወደ ከባቢ አየርና በተለይም ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ እየለቀቀ ያለው በጣም ከፍተኛ የጨረር መጠን መሆኑን እያመላከቱ ነው። ይህ ብክለት ከፓሲፊክ ውቅያኖስም አልፎ ወደሌሎቹ የምድር ውቅያኖሶችና ባህሮች እንደደረሰና በባህር ውስጥ እያለቁ ላሉት እንስሶች ሞትም መንስኤ ሳይሆን እንደማይቀር ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ቢናገሩም ዜናው ግን ጎልቶ አልወጣም።  በፉኩሺማው ኃይል ማመንጫ መፈንዳትም ሆነ ሌላ በማንሰማው ምክንያቶች እየተከሰተ ያለው የባህር ብክለትና የእንስሳት እልቂት ከባህር የሚገኙ ምግቦችን እየበከለ መሆኑ የማያጠራጥር ነው። ማገናኛው ከታች በተሰጠው ድረገጽ ላይ እንደምትመለከቱት እነዚህ እልቂቶች በዓለም ሁሉ እና በአማካይ በየእለቱ የሚታዩ ክስተቶች ናቸው።

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ ሲሄድ፣ በተለይም ደግሞ በታላቁ የመከራ ዘመን በምድር ላይ ከሚሆኑት እጅግ አስፈሪ ሁኔታዎች አንዱ በምድር ላይ ያሉ ዛፎችና ተክሎች ሲሶ መቃጠል፣ በባህርና በወንዞች እንዲሁም በሐይቆች እና ሌሎችም የውሃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት ሲሶ መሞት እንደሆነ የዮሐንስ ራዕይ ምዕ 8 ቁጥር 6 እስከ 11 ይናገራል። ዛሬ እየተከሰተ ያለው የባህር፣ የየብስና የአየር እንስሳት ማለቅ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ነው እያልሁ አይደለም። ነገር ግን በምድራችን ላይ እየተከሰቱ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ ዜና ስንሰማ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መመርመር ለክርስቲያን ሁሉ አስፈላጊ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በጥሞና ማንበብ መማርና ማጥናት ያስፈልጋል።


ብዙ ሰው ዜና እሰማለሁ በአካባቢዬና እና በዓለም ዙሪያ ሰለሚሆኑት ነገሮችም ሁሉ መረጃ አገኛለሁ ብሎ ያምናል።  እስከቅርብ ዓመታት ድረስ ብዙዎቻችን ደግሞ ዜና ሰማን ብለን የምናስበው ቴሌቪዥን በማየት ወይም ሬድዮ በመስማት፣ ጋዜጦችን በማንበብ ነበር። ዘመኑ ያመጣው ኢንተርኔት ተጨማሪ የዜና ምንጮችን ቢፈጥርም እውነቱን ከውሸቱ፣ ፕሮፓጋንዳውን ከመረጃው መለየት እጅግ አስቸጋሪ ነው። የታወቁ ናቸው፣ ትልልቅ ናቸው ብለን የምናምናቸው የዜና ምንጮችም ቢሆን ዜና ብለው የሚያቀርቡልን ባለቤቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንድናምነው የሚፈልጉትን እንጂ ልናውቀው የሚገባውን አይደለም። በተለይ ደግሞ የቴሌቪዥን ዜና ከመዝናኛ ተለይቶ በማይታይበት በምዕራቡ ዓለም ያሉ ብዙ የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች የሚያተኩሩት ተመልካችና ሰሚን በመሳብ የሚያገኙትን ትርፍ እና የባለቤቶቻቸውን ዓላማዎች በማራመድ ላይ ያተኮሩ ስለሆኑ በዓለማችን ላይ በእርግጥ ስለሚሆኑት ነገሮች ሁሉ መረጃን አይሰጡንም። ይህም አዲስ አይደለም። ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቶ ሳለ ይህ በፍጥረተ ዓለም ሁሉ ዋና ዜና መሆን የነበረበት ተአምር በኢየሩሳሌም ከተማና በእስራኤል እንኳን ርዕሰ ዜና  አልነበረም። በዚያ ፈንታ "የዚያን ሮማውያን የገደሉትን የገሊላውን መሲህ ነኝ ባይ አስከሬን ደቀመዛሙርቱ ከመቃብር ሰረቁት" የሚል ወሬን ነበር የቤተመቅደሱ አለቆች ጉቦ በመክፈል ያስወሩት።  ስለዚህ ሃሰተኛው ክርስቶስም በምድር ላይ ሲገለጽ “ሃሰተኛው ክርስቶስ ተገለጸ” የሚል ዜና ለመስማት ተስፋ አናድርግ። ይልቁንም ልንሰማ የምንችለው “ዓለማችንን ካለችበት ቀውስ ሁሉ ለማውጣት የሚረዳን ታላቅ መሪ መጣልን” የሚል ዜና ነው።

ስለዚህ በምድር ላይ የሚከሰቱት ታላላቅ ነገሮች ያላቸውን መንፈሳዊ ዋጋ በሚገባ መረዳትና መገምገም የምንችለው በመጀመሪያ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ከዘለዓለም ጨለማ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ስንሸጋገር ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መንፈሳዊ ምግባችን ማድረግ ያስፈልጋል። በቃሉ የተማርነው ከህይወታችን ጋር ተዋህዶ የነገሮችን ዘለዓለማዊ ፍጻሜ ማስተዋል እንድንችል ደግሞ መጸለይና ለተረዳነው እውነት በመታዘዝ መኖር ያስፈልጋል። በጎም ይሁን ክፉ በምንሰማውን ዜና እንዳንታወክ ልባችንን እንጠብቅ። መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም መጨረሻ የሚለው የክፉውን የዓለም ስርዓት ፍጻሜ ነው።  እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ሃሳቡም በክርስቶስ ለተጠሩ ግን ያ የዓለም ፍጻሜ የተባለው የነገስታት ንጉስና የጌቶች ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ሊነግስ እንደሆነ የሚያሳይ የምጥ ጣር ምልክት ነው። ዜናን ስንሰማ እንደ ክርስቲያን እንስማ። የምናየውንና የምንሰማውን በስሜታችን ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እውነት እንፈትነው። በጎ ከሆነ እግዚአብሔርን እናመስግን። ክፉ ዜና ከሆነ ደግሞ የየትኛው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ በመመርመር ለመረዳት እንሞክር። በሁሉም ደግሞ እግዚአብሔርን እናክብር እንጂ በክርስቶስ ከቆምንበት ከመንፈሳዊ ስፍራችን አንናወጥ። http://www.end-times-prophecy.org/animal-deaths-birds-fish-end-times.html

3 አስተያየቶች:

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...