የዓለም ከባቢ አየር እጅግ እየታወከ ያለው ለምን ይሆን?

የዓለም ከባቢ አየር እጅግ እየታወከ ያለው ለምን ይሆን?
ላለፉት ስምንት ቀናት ብዙ የዓለም ክፍሎችን ሲለበልብ የሰነበተው ከፍተኛ ሙቀት G& ተብሎ በሚጠራው የባለጸጋ  አገሮች ክለብ አባል በሆነችው ካናዳ፣ ኬቤክ ተብሎ በሚጠራው ክፍለ ሃገር ብቻ 33 ሰዎች ከሙቀቱ የተነሳ ሞተዋል። እድሜያቸው ከ53 እስከ 80 ድረስ ከሆኑት ከነዚህ ሰዎች መካከል አስራ ስምንቱ ሞንትሪያል በምትባለው ትልቅ ከተማ ባሉ አፓርታማዎች ኑዋሪ ሲሆኑ ቤታቸው የአየር ማቀዝቀዣ እንደሌለው ተጠቅሷል። ከዚህ በፊት በሰሜናዊው ክፍለ ዓለም፣ በተለይም ደግሞ እንደ ካናዳ ባሉ ለሰሜን ዋልታ ቅርብ በሆኑ አገሮች እንደዚህ ብዙ ቀናት የቆየ ከፍተኛ ሙቀት ታይቶ እንደማይታወቅ የአየር ጠባይ ተመራማሪዎች ገልጸዋል። ይህ ከፍተኛ ሙቀት በሩሲያ ግዛት ባለው በሳይቤሪያ፣ በሰሜናዊው ምስራቅ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በአየርላንድና በስኮትላንድ የታየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ወደ ምእራባዊው አሜሪካ ግዛት እየታየ እንደሆነ ተዘግቧል። ኦሃዮ በሚባለው የአሜሪካ ክፍለ ሃገር ባለ አንድ አውራ ጎዳና (I77) ላይ ከሙቀቱ የተነሳ መንገዱ የተሰራበት አስፋልት እንደተነሳ አንዳንድ ምንጮች ዘግበዋል።  ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘው ጽሁፍና በውስጡ ካሉት ፎቶዎች አንዱ እንደሚያሳየው አብዛኛው የምድር ክፍል በከፍተኛና  ያልተለመደ ሙቀት ውስጥ መሆኑን ያሳያል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል መሰበክ ከሁለት ሺህ ያህል ዓመታት በፊት የተጀመረው የጸጋና የምህረት ዘመን እያበቃ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ሲቃረብ በሰማይና በምድር ብዙ ምልክቶች እንደሚሆኑ ብሉይና ሐዲስ ኪዳን በሰፊው ያስተምራል። ይህን ለመረዳት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የተገለጸውን እውነት በጥንቃቄ ማጥናት፣ እንዲሁ ደግሞ በምድር፣ በከባቢ አየርና በሰማይም ሁሉ እየተካሄደ ያለውን ነገር የሚያሳዩ ዜናዎችን በማስተዋል ማጤን ያስፈልጋል። በዚህ ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳን ስንት የምድር መናወጦች፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች፣ ያልተመለዱና ብዙ ህዝብ የፈጁ የአየር ንብረት መዛባቶች ተፈጸሙ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የቴሌቪዝንና የኢንተርኔት ዜና ከመብዛቱ የተነሳ ብዙዎቻችን እኛን በቀጥታ የነካንና የጎዳን ካልሆነ በቀር እንኳንስ የዓመቱንና ከሶስት ቀን በፊት እንኳን በዜና የሰማነውን አናስታውስም። ገፋ ቢል "ወይ ጉድ፣ ይገርማል፣ ደግሞ ምን ሊመጣ ይሆን" ብለን እናልፈዋለን። ይህ ሰሞኑን በብዙ የዓለም ክፍሎች ተከስቶ ያለው ቃጠሎ፣ እንኳን በታላቁ የመከራ ዘመን ይከሰታል ተብሎ በዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 16 ቁጥር 8-9 ላይ ከተጻፈው ጋር አይወዳደርም፣ እኔም የሰሞኑ ክስተት የዚያ ትንቢት ፍጻሜ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ምናልባት እግዚአብሔር ይህን የፈቀደው በአመጻቸውና በትእቢታቸው ልባቸው እጅግ ወደ ሰማይ የደረሱትን እንደ ካናዳ ያሉ አገሮች ወደ ንስሐ ልባቸውን እንዲመልሱ ለማሳሰብ ይሆን? የራዕይ 16ቱ ቃል እንዲህ ይላል "አራተኛውም ጽዋውን በጸሃይ ላይ አፈሰሰ፣ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፣ በእነዚህም መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፣ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት መቃረብ የሚያሳዩ የምጥ ጣር ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ብዙ ዘመን ቢሆንም ምልክቶቹ መደጋገምና፣ መወሳሰብና መፋጠን ሊያነቃን ይገባል። እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች የጌታ መምጣት በድንገት ሊሆንብን አይገባም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ልብሳችን ቆሽሾ፣ ከጸጋው ርቀንና መንፈሳዊ እርቃናችንን ሆነን ጌታ እንዳይመጣ ተግተን ልንጸልይ ይገባል። ገና ኃጢዓተኞች ሳለን በልጁ አስቦ ዳግመኛ የወለደን አምላካችን ከማያምነው ዓለም ጋር እንድንጠፋ አይተወንም። ነገር ግን እኛ ደግሞ የመታዘዝ ልጆች ነንና የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ስንሰማ ልባችንን አናጠንክር። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...