ኔት ፍሊክስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና ሰው ሆኖ ወደ ምድር (አሜሪካ) መጣ የሚል ምናባዊ ፊልም/የቴሌቪዝን ፕሮግራም ሊያስተላልፍ ነው

https://christianjournal.net/news/netflix-host-tv-show-reincarnated-american-jesus/


ዙሪያችን በዜና፣ በምስሎችና በብዙ ድምጾች የተሞላ ነው። ልባችንን ወደ ብዙ አቅጣጫ የሚስቡ፣ ተስፋችንን የሚገነቡ ወይም ያለንን ለመንጠቅና ግራ ለመጋባት የሚቃጣቸው ብዙ ዜናዎችን በየቀኑ እንሰማለን። አንዳንዱ ዜና እንደ ነፋስ ውልብ ብሎ ሲያልፍ ሌላው ደግሞ በግልና በጋራ ህይወታችን ላይ ብዙ ተጽእኖን፣ ብሎም ለውጥን ሊያመጣ ይችላል።
ኔት ፍሊክስ የሚባለው በኢንተርኔት ቪዲዮና የፊልም የሚያከፋፍል ድርጅት ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ ሰው በኩል ሆኖ በአሜሪካ ተገለጠ የሚል የቪዲዮ ፕሮግራምን ማስተላለፍ እንደሚጀምር የተያያዘው ዜና ያሳያል። መቼም ብዙ ሚሊዮ  ዶላር ወጭ የሚወጣባቸው እንደዚህ ያሉ ፊልሞችና የቴሌቪዝን ፕሮግራሞች የሚመጡት በድንገት ሳይሆን ታቅደውና ብዙ ተደክሞባቸው ነው። ከበስተጀርባቸውም ዓላማ መኖሩን ለመረዳት አዳጋች አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚያምኑ ክርስቲያኖች በምድር ሁሉ በሚሰደብበትና በሚንጓጠጡበት በዚህ ዘመን፣ ከክርስቲያን መሰረቷ ተላቅቃ ማንነቷን ለማግኘት በብዙ ውጥረት ውስጥ በምትንገላታው አሜሪካ የሚገኝ ይህ የመዝናኛ ድርጅት (ኔት ፍሊክስ) ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገና ሰው ሆኖ መጣ ( ለዚያውም አሜሪካዊ ወጣት፣ ) የሚል የቪዲዮና የቴሌቪዝን ፕሮግራም ለማሰራጨት ማዘጋጀቱ ለምን ይሆን። ባለፉት ሁለት የሚሆኑ ዓመታት በአሜሪካ የሚታየው የፖለቲካ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ትግልና ውጣ ውረድ ያሰለቻቸው ብዙ ሰዎች ከዚህ የሚያወጣቸው የመሲህ ምስል ስለሚናፍቁ ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ። ብዙ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ቅኝቶችም ይህን ያረጋግጣሉ።
ከዜናዎች ሁሉ የሚበልጠውና ዘላቂ የሆነው ዜና “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የሚለው የወንጌል የምስራች ነው። (ዮሐንስ 3፡16)። ይህ ከሰማይ የመጣ ዜና ብቻ ነው ለሰው ዘርና ለፍጥረት ሁሉ ዘለዓለማዊ ተስፋን የሚሰጠው። ከዚሁ ጋር የተያያዘውና የዚህ የእግዚአብሔር የፍቅር ወንጌል ተስፋ ፍጻሜ ደግሞ የተስፋው ባለቤት የሆነው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዳግም ተመልሶ መምጣት ነው።
ዘመኑ ቀርቦአል፣ መሲሁ በቅርብ ራሱን ለእኛ ይገልጻል የሚሉ አይሁድ በኢየሩሳሌም 3ኛውን ቤተ መቅደስ ለመስራት እየተሯሯጡ ናቸው። ባለፈው ግንቦር ወር ላይ አሜሪካ ኤምባዊዋን ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ማዞርዋ ለዚህ ለቤተ መቅደሱ መሰራት ድጋፍ ይሰጣል ብለው የሚያምኑም አይሁድ ጥቂት አይደሉም። ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የተሰበከው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለዓለም ሁሉ የእግዚአብሔርን ጸጋና ምህረት አሳይቶ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነፍሳት ድነዋል። የዓለም ታሪክና ገጽታ በወንጌል ተለውጦ ብዙው የሰው ዘር ከዲያብሎስ ግዛት ስር በመላቀቅ፣ መንፈሳዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ ነጻነትን ከመቼውም የሰው ዘር ዘመን በተሻለ እያየ የመጣበት ጊዜ ቢኖር እነዚህ እያለፉ ያሉት ሁለት ሺህ ዓመታት ነበሩ። ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ እንዳለው “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፣ በዓለም ነበረ፣ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም” ተብሎ የተጻፈው ቃልም እየተፈጸመ ያለው በዚሁ ዘመን ነው። ምክንያቱም የጌታ አምላክ ቃል ኪዳን ተቀባይ የሆነው የአብርሃም ልጆች አይሁድም ይሁን አህዛብ ከሰማይ የመጣውን የእግዚአብሔርን ወንጌል ቃል ወደ ጎን ጥለው በአሳሳቹ በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንደገና በእልሃቸው እየገቡ ናቸው።
ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ወንጌልን ሰምተው ያመኑትና ዛሬ ግን ወንጌሉን ወደ ኋላ በመጣል ዛሬ ብዙ የአውሮፓ ህዝቦች በጥንት ዘመናት አባቶቻቸው ሲከተሉአቸው የቆዩትን ባእድ አማልክት (አጋንንትን) ለመከተል እንደገና ተነስተዋል። በጀርመን፣ በዴንማርክ፣ በስኮትላንድና በአይስላንድ ጥንት ሲመለኩ ለነበሩት የአጋንንት አማልክት ቤተ ጣዖታትን ለመስራት ሰልጥነዋል የሚባሉት የነዚህ አገሮች ሰዎች ቁጭ ብድግ እያሉ ናቸው። በአይስላንድ፣ በጀርመን፣ በዴንማርክና በስኮትላንድ ቶር እና ኦዲን ተብለው ለሚጠሩ የባእድ አማልክ ቤተ ጣዖት የመስራቱ ሂደት መጀመሩን የተለያዩ የዜና ምንጮች እየዘገቡ ነው። በኖህ፣ በሰዶምና በገሞራ ዘመን ምድርን ያጠፋው የሰው ዘር ርኩሰት ዛሬ “ዘመናዊ” ካባ ተሰፍቶለት “ስልጣኔ”፣ “ነጻነት”፣ “እኩልነት” ፣ “ብልጽግና” እየተባለ ምድርን እንደ ጎርፍ እያጥለቀለቀ ነው።
እንደ ባለ አእምሮ ልብ ብሎ ላየውና ላስተዋለው ሰው ከሁሉ በላይ የሚያስገርመው ግን የክርስቲያን አገር ይባሉ የነበሩ ብዙዎቹ አገሮች የተገለጸውን የኢየሱስ ክርስቶስን የጸጋ ወንጌል እምቢ በማለት ከመካከላቸው አውጥተውት ሳለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ በራሳቸው ፍላጎትና መልክ የቀረጹትን “ኢየሱስ” ወደ ዓለም ለማምጣት መሞከራቸው ነው። ይህ በኔት ፍሊክስ ሊቀርብ የተዘጋጀውና “እንደገና ወደ ዓለም የመጣሁት ኢየሱስ” ነኝ ባዩ የቴሌቪዝን ገጸ ባህርይ የሚያመለክተን የሰው ልጅ ዛሬም ቢሆን አዳኝን መፈለጉ ነው። ይህን ሃሳብ እነርሱ ፈጥረው ያመጡት ይምሰላቸው እንጂ፣  አምላክ አስቀድሞ በሃዋርያት አፍ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፡ “በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመጽ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል።” እንደ ካቶሊክ፣ ፕረስቢቴሪያን፣ አንግሊካን፣ ሉተራን ወዘተ ያሉ ትልልቅ አብያተ ክርስቲያን ትልልቅ መሪዎች ኃጢዓትንና የሚያጠፉ የኑፋቄ ትምህርቶችን በአደባባይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ባስገቡበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ኔት ፍሊክስ ያሉ የገንዘብ ደላላዎች ርኩሰትን የማይጸየፍ፣ ኃጢአትን የማይቃወም የምድር መሲህ ለዓለም በመዝናኛ መልክ ለማስተዋወቅ ቢሞክሩ ልንገረም አይገባም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ከመገለጹ በፊት እነዚህ ሰዎች እንዳሰቡትና እንደተመኙት የዓመጽ ልጅ፣ የጥፋት ሰው የሆነው ሃሳዊው መሲህ (ሃሰተኛው ክርስቶስ) ለአይሁድ እንደ ፍላጎታቸው፣ ጣዖት ለሚያመልኩ እንደ ምኞታቸው፣ አምላክ የለም ለሚሉ እንደ ትምክህታቸው፣ ክርስቲያን ነን የሚል ካባ ለብሰው በዓመጽ ለሚኖሩም እንደ መሻታቸው ይገለጥላቸዋል። ምድር እጅግ አሰቃቂና አስፈሪ በሆነው በታላቁ የመከራ ዘመን ውስጥ የምታልፈው በዚህ በሃሳዊው መሲህ አገዛዝ ስር ነው። ለዚህ ነው ምድር ሁሉ “መሲህ” “መሲህ”፣ “ማህዲ”፣ “ሞሺያክ” በሚል የወሬ ትኩሳት የተያዘችው። ስለዚህ ነው እነ ኔት ፍሊክስና ሌሎችም የቴሌቪዝንና የመዝናኛ ድርጅቶች “የዓለም አዳኝ” የሚሉአቸውን የሃሰት መሲሆች ሊያስተዋውቁ ቁጭ ብድግ እያሉ ያሉት።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ጻፈው “እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም።” 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡4 ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የጌታ ዳግም ምጽዓት እንደ ተቃረበ በማሰብ ወደ አምላካችን በእውነትና በመንፈስ እንጠጋ። በእጃችን ያለው ቃሉ ስለዚ ዘመን የሚነግረንን በጥሞና እናጥና፣ እንመርምር። ቃሉ የተጻፈው የዘመን መጨረሻ የደረሰብንን እኛል ሊመራን፣ ሊመክረንና ሊገስጸን ነውና  ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ለቃሉ ልባችንን እንክፈት፣ በጸሎት እንትጋ፣ እርስ በርሳችን እንተያይ፣ ዓይናችንን ወደ ሰማይ አሻቅበን በምስጋና፣ በጸሎትና በውዳሴ በማንሳት ከላይ የሚመጣውን ብቸኛውን አዳኛችንን እና አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠብቅ።

የዓለም ከባቢ አየር እጅግ እየታወከ ያለው ለምን ይሆን?

የዓለም ከባቢ አየር እጅግ እየታወከ ያለው ለምን ይሆን?
ላለፉት ስምንት ቀናት ብዙ የዓለም ክፍሎችን ሲለበልብ የሰነበተው ከፍተኛ ሙቀት G& ተብሎ በሚጠራው የባለጸጋ  አገሮች ክለብ አባል በሆነችው ካናዳ፣ ኬቤክ ተብሎ በሚጠራው ክፍለ ሃገር ብቻ 33 ሰዎች ከሙቀቱ የተነሳ ሞተዋል። እድሜያቸው ከ53 እስከ 80 ድረስ ከሆኑት ከነዚህ ሰዎች መካከል አስራ ስምንቱ ሞንትሪያል በምትባለው ትልቅ ከተማ ባሉ አፓርታማዎች ኑዋሪ ሲሆኑ ቤታቸው የአየር ማቀዝቀዣ እንደሌለው ተጠቅሷል። ከዚህ በፊት በሰሜናዊው ክፍለ ዓለም፣ በተለይም ደግሞ እንደ ካናዳ ባሉ ለሰሜን ዋልታ ቅርብ በሆኑ አገሮች እንደዚህ ብዙ ቀናት የቆየ ከፍተኛ ሙቀት ታይቶ እንደማይታወቅ የአየር ጠባይ ተመራማሪዎች ገልጸዋል። ይህ ከፍተኛ ሙቀት በሩሲያ ግዛት ባለው በሳይቤሪያ፣ በሰሜናዊው ምስራቅ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በአየርላንድና በስኮትላንድ የታየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ወደ ምእራባዊው አሜሪካ ግዛት እየታየ እንደሆነ ተዘግቧል። ኦሃዮ በሚባለው የአሜሪካ ክፍለ ሃገር ባለ አንድ አውራ ጎዳና (I77) ላይ ከሙቀቱ የተነሳ መንገዱ የተሰራበት አስፋልት እንደተነሳ አንዳንድ ምንጮች ዘግበዋል።  ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘው ጽሁፍና በውስጡ ካሉት ፎቶዎች አንዱ እንደሚያሳየው አብዛኛው የምድር ክፍል በከፍተኛና  ያልተለመደ ሙቀት ውስጥ መሆኑን ያሳያል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል መሰበክ ከሁለት ሺህ ያህል ዓመታት በፊት የተጀመረው የጸጋና የምህረት ዘመን እያበቃ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ሲቃረብ በሰማይና በምድር ብዙ ምልክቶች እንደሚሆኑ ብሉይና ሐዲስ ኪዳን በሰፊው ያስተምራል። ይህን ለመረዳት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የተገለጸውን እውነት በጥንቃቄ ማጥናት፣ እንዲሁ ደግሞ በምድር፣ በከባቢ አየርና በሰማይም ሁሉ እየተካሄደ ያለውን ነገር የሚያሳዩ ዜናዎችን በማስተዋል ማጤን ያስፈልጋል። በዚህ ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳን ስንት የምድር መናወጦች፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች፣ ያልተመለዱና ብዙ ህዝብ የፈጁ የአየር ንብረት መዛባቶች ተፈጸሙ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የቴሌቪዝንና የኢንተርኔት ዜና ከመብዛቱ የተነሳ ብዙዎቻችን እኛን በቀጥታ የነካንና የጎዳን ካልሆነ በቀር እንኳንስ የዓመቱንና ከሶስት ቀን በፊት እንኳን በዜና የሰማነውን አናስታውስም። ገፋ ቢል "ወይ ጉድ፣ ይገርማል፣ ደግሞ ምን ሊመጣ ይሆን" ብለን እናልፈዋለን። ይህ ሰሞኑን በብዙ የዓለም ክፍሎች ተከስቶ ያለው ቃጠሎ፣ እንኳን በታላቁ የመከራ ዘመን ይከሰታል ተብሎ በዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 16 ቁጥር 8-9 ላይ ከተጻፈው ጋር አይወዳደርም፣ እኔም የሰሞኑ ክስተት የዚያ ትንቢት ፍጻሜ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ምናልባት እግዚአብሔር ይህን የፈቀደው በአመጻቸውና በትእቢታቸው ልባቸው እጅግ ወደ ሰማይ የደረሱትን እንደ ካናዳ ያሉ አገሮች ወደ ንስሐ ልባቸውን እንዲመልሱ ለማሳሰብ ይሆን? የራዕይ 16ቱ ቃል እንዲህ ይላል "አራተኛውም ጽዋውን በጸሃይ ላይ አፈሰሰ፣ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፣ በእነዚህም መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፣ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት መቃረብ የሚያሳዩ የምጥ ጣር ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ብዙ ዘመን ቢሆንም ምልክቶቹ መደጋገምና፣ መወሳሰብና መፋጠን ሊያነቃን ይገባል። እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች የጌታ መምጣት በድንገት ሊሆንብን አይገባም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ልብሳችን ቆሽሾ፣ ከጸጋው ርቀንና መንፈሳዊ እርቃናችንን ሆነን ጌታ እንዳይመጣ ተግተን ልንጸልይ ይገባል። ገና ኃጢዓተኞች ሳለን በልጁ አስቦ ዳግመኛ የወለደን አምላካችን ከማያምነው ዓለም ጋር እንድንጠፋ አይተወንም። ነገር ግን እኛ ደግሞ የመታዘዝ ልጆች ነንና የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ስንሰማ ልባችንን አናጠንክር። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...