ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው።
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊኖርበት፣ ሊያውቀው፣ ሊመራመረውና ሊያደርገው የሚገባውን ነገር በተመለከተ ድንበርን አብጅቶለት ሳለ፣ የሰው ልጅ ግን በማን አለብኝነትና በሰይጣን ሽንገላ ስቶ የማያውቀውን፣ የማይረዳውንና ወደ ኋላ ለመመለስ የማይችለውን ጥፋት እያጠፋ ነው። "እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ" ያለውን የእባቡን የሃሰት ምክር ሙሉ በሙሉ መቀበሉን በተግባር እያሳየ ነው። ጌታ አምላክ በኖህ ዘመን የነበረውን ዓለም በውኃ ያጠፋው የዘመኑ ሰው እንደዛሬው ሁሉ በማን አለብኝነትና በዓመጽ ስለ ተሞላ ነበር። ይህ መልእክቴ ስለ ግል ኃጢአትና ዓመጽ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በዓለማችን ዙሪያ ያለውን የአየር ንብረት ቀውስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ብቻ እንይ። በሰፊው ለሚታየው ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ቀውስ በዜና የሚነገረን የፕላኔቷ መሞቅ ወይም ደግሞ እንደ ኤልኒኖ፣ እንደ ኤልኒኛ ያሉ በየጊዜው በባህር ላይ የሚፈጠሩ ክስተቶች እንደ ሆኑ ነው። ከዚህ በፊት እንደ ጻፍሁት ሁኔታውን ቀረብ ብለን ብንመረምር ግን የዓለማችን ታላላቅና ሃብታም አገሮች ጠላቶቻቸውን ሊያጠቁ የሚችሉበት የአየር ንብረትን ማቃወሻ ቴክኖሎጂ እንዳላቸው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዊሊያም ኮኽን እንኳን በአፕሪል 28፣ 1997 በግልጽ ተናግረዋል። ሪፖርቱንም ከሚከተለው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል። (http://archive.defense.gov/Transcripts/Transcript.aspx?TranscriptID=674)
እነዚህ ኃያላን አገሮች አንዱ ሌላውን ለማጥቃት ከሚያደርጉት የመሳሪያ እሽቅድምድም መካከል የምድርን ማግኔታዊ ኃይል የሚቀይሩ መሳሪያዎችን በመጠቀም ሰው ሰራሽ የምድር መንቀጥቀጥን እና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታንም ሊያስነሱ የሚችሉ መሳሪያዎችን ሰርተውና ፈትሸው በስራ ላይ አውለዋል። ሌሎች የግል ድርጅቶችም፣ በተለይ በአሜሪካ፣ እነዚህን ቴክኖሎጂዎችና ስራቸውን ለገበያ እንደሚያቀርቡ ግልጽ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ሁለት የግል ድርጅቶች ድረ ገጾች መጎብኘት ይቻላል።
http://weathermodification.com እና http://www.nawmc.org

ስለ ዳግም ምጽዓቱ በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰጣቸው ምልክቶች መካከል የምድር መናወጥ፣ ረሃብና ቸነፈር ይገኛሉ። ጌታ አምላክ ለሰው ልጅና ለፍጥረቱ ካለው ቸርነትና በጎነት የተነሳ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ጸሃዩን እንደሚያወጣ፣ ለኃጢዓተኞችና ለጻድቃን ዝናቡን እንደሚያዘንብ ጌታ ኢየሱስ አስተምሮናል። ታዲያ ይህ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ላይ እጅግ እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ቀውስ፣ (ጎርፍ፣ ያለወክቱ የሚከሰት ከልክ ያለፈ ሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ በረዶ፣ )የባህርና የሰማይ እንስሳት በከፍተኛ ቁጥር ማለቅ፣ የበሽታ መብዛት የምድር መናወጥ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ ረሃብ፣ ቸነፈር ከየት ነው የሚመጣው?
አንዱ አገር ሌላውን ለማጥቃትና ለማሸነፍ፣ካልሆነም ደግሞ አቅም ለመንሳት የሚደረገው ዓለም አቀፍ የጦር ኃይል እሽቅድምድም፣ ገንዘብ የማይበቃቸው ስግብግብ ኮርፖሬሽኖች የአገሮችንና የህዝቦችን ሃብት ለማግበስበስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከእነዚህ ጥፋቶች መካከል ብዙዎቹን እየፈጠሩ መሆናቸው ዛሬ በማስረጃ የተረጋገጠ ነው።
እግዚአብሔር ዛሬም ቸር ነው፣ ምህረቱና በጎነቱም አልተለወጠም። ጌታ ህዝቦችን ወደ ንስሃ ለመመለስ የተለያዩ ቅጣቶችን በየጊዜው እንደሚልክ ይነግረናል። ዛሬ በዘመናችን እየሆነ ያለው ሁሉ ግን የዚህ ቅጣት አካል ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ አወቅሁ ብሎ በትእቢት የሚያደርገው ከንቱ የሆነ የኃያልነት መፍጨርጨር ውጤትም ነው። ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም ተመሳሳይ መረጃዎችን በማንበብና በመመርመር በእርግጥም ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን አካል መሆኑን እያንዳንዳችን ለራሳችን እንረዳ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዳግም ተመልሶ ይመጣል። ይህ ዛሬ የምናየው ቀውስ ሁሉ ከመንገድ ላይ ተወግዶ ጌታ አምላክ ከህዝቡ ጋር ለዘላለም ይነግሳል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...