
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018
አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ
ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም የሚለውን ቃል የተናገረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።
በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 3 ላይ እንደምናነበው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጥልቅ መንፈሳዊ ምስጢር ያዘለ ትምህርት የሰጠው ኒቆዲሞ ለሚባል ሰው ነበር። ኒቆዲሞስ በእስራኤል ህዝብ መካከል በከፍተኛ የሃይማኖትና
የህዝብ አመራር ደረጃ ላይ የነበረ፣ የላቀ ትምህርትን የተማረ፣ በሃይማኖታዊነቱ የተመሰከረለት፣ በምድራዊ በባለጸግነቱም የከበረ፣
በህዝብና በመሪዎችም መካከል ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ሰው ነበር። የአይሁድን እምነትና የህዝቡን ማህበረሰባዊ ህይወት በበላይነት
ይመራ የነበረውና ሳንሄድሪን ተብሎ የሚጠራው ጉባኤ አባል የነበረው ኒቆዲሞስ እንደ ሌሎቹ የጉባኤው አባላት፣ ካህነትና ሊቃውንት
ሁሉ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምረው ነገር ተስቦ ነበር አንድ ቀን በምሽት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር
ተልኮ የመጣ መሆኑን እንደሚያምንና በእጁም የሚሰሩት ድንቆች ከእግዚአብሔር በመሆናቸው ኢየሱስ የሚያደርገውንና የሚያስተምረውን እንደሚቀበልና
እንደሚስማማበት ለኢየሱስ ሊያረጋግጥለት ነበር ወደዚያ የመጣው። ምንም
ያህል የተማረ፣ በህዝብ መካከል መልካም የከበረ፣ ስልጣንና ተጽእኖ ያለው እንዲሁም ደግሞ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ድንቅ ስራዎች
መልካም አስተሳሰብና አድናቆት ያለው ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በሚገባ ለማወቅና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት
ግን ዳግም መወለድ ነበረበት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እጥር ምጥን ባለ መንገድ እንዲህ ሲል ነበር የነገረው፡
“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን
መንግሥት ሊያይ አይችልም።” ዮሐ 3፡3
በእድሜው ለገፋ፣ በሃይማኖታዊ ኑሮው ነቀፌታ
የለብኝም ብሎ ለሚያስብ፣ በህብረተሰብ መካከል ለተከበረና በምድራዊ ኑሮውም ቢሆን በብልጽግና ለታደለ ሰው የኢየሱስ ንግግር ግራ
የሚያጋባ ነበር። ይህንንም ከኒቆዲሞስ መልስ ለማየት እንችላለን። “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ
ማህጸን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? ” ዮሐ 3፡4 በማለት ነበር ኒዞዲሞስ የጠየቀው። የኒቆዲሞስን ግራ መጋባት ያየው ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ ግን ለኒቆዲሞስ ግራ መጋባት ምንጩ የሰማው የወንጌል እውነት ሳይሆን እንደ ማንኛችንም ሰዎች በበደሉና በኃጢዓቱ የሞተና
ከእግዚአብሔር ሕይወት የተለየ መሆኑ ነበር። ስለ ኃጢዓት በተደጋጋሚ የምንሰማው አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ስለ ፈጸሙት በደል
ነው። እውነቱ ግን እኛ እያንዳንዳችን በበደላችን እና በኃጢዓታችን ምክንያት ሙታን መሆናችን ነው። ኒቆዲሞስ የሃይማኖታዊው ጉባኤ
አመራር አካል የሆነበትና በሙሴ አማካይነት ህግ የተሰጣቸው ህዝቡ እስራኤላውያንም ሆኑ በምድራዊ ዘራችን የአብርሃም ልጆች ያልሆንን
አህዛብ ሁላችን በኃጢዓት ውስጥ ወድቀናል፣ ፈጽመን ጠፍተናል፣ መንፈሳዊ ማንነታችን ሞቶ ከእግዚአብሔር ተለይተናል። ሃይማኖተኛና
መንፈሳዊ ነገሮችን የምናውቅ ልንሆን እንችላለን። ልንጾም ልንጸልይና ብዙ ግብረ ሰናዮችን ልናደርግ እንችላለን። በህዝብና በመሪዎች
መካከል የከበረ ስፍራ ሊኖረን፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም መልካም አስተሳሰብና አድናቆት ሊኖረን ይችላል። ከነዚህም ሁሉ አልፈን
ለቤተ ክርስቲያንና ለወንጌል አገልግሎት የገንዘብና የሞራል ድጋፍም ልናደርግ እንዲሁም በመንፈሳዊ ፕሮግራሞች ልንሳተፍ እንችላለን።
በዚህ ምድር ህይወታችንም የተማርንና የተሟላልን (የተባረክን) ልንሆን እንችላለን። እነዚህ ሁሉ እያሉንም ታዲያ ኃጢዓት ምን ያህል
ማንነታችንን እንዳጠፋው አልተረዳን እንዲሁም ደግሞ ብቸኛውን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን ዳግም አልተወለድን ይሆናል።
ሁላችንም የሰው ልጆች፣ ከአዳም እስከኔና እስካንተ፣ ከሄዋን እስከ አንቺ ድረስ፣ በኃጢዓት ምክንያት የጠፋን፣ የሞትን፣ ለዘላለም
ከእግዚአብሔር የተለየየን መሆናችንን ለማወቅ የሚከተሉትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማየቱ ብቻ በቂ ነው፤
1)
ከርኩስ ነገር ንጹሕን
ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም። ኢዮብ 14፡4
2)
እነሆ በዓመጻ ተጸነስሁ
እናቴም በኃጢዓት ወለደችኝ መዝሙር 50(51)፡5
3)
ልዩነት የለምና ሁሉም
ኃጢዓትን ሰርተዋልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።
ሮሜ 3፡23-24
4)
ኢየሱስም መለሰ እንዲህ
ሲል፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢዓት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢዓት ባሪያ ነው። ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፣ ልጁ ለዘላለም
ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።
ዮሐንስ 8፡34᎒5
5)
በበደላችሁና በኃጢዓታችሁ
ሙታን ነበራችሁ፣ በእነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሰራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር
ላይ ስልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ የሥጋችንንና የልቡናችንን
ፈቃድ እያደረግን በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን። እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌሶን 2፡1-3
6)
ኃጢዓት የለብንም ብንል
ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐ 1፡8
ስለዚህ ለኒቆዲሞስ ጌታ እንዳስተማረው በኢየሱስ
ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በቀር ማንኛውም ሰው በኃጢዓት ምክንያት መንፈሱ የሞተ ነው። ከእግዚአብሔር ለዘላለም ተለይቷል።
የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም። በዚህ ዓለምና በሰዎች ፊት የተማረም ሊሆን ይችላል። ሃይማኖተኛና ግብረ ሰናይ ፈጻሚ
ሊሆን ይችላል። ሃይማኖቴ ክርስቲያን ወይም እርሱ ልክ ነው ብሎ የሚያምነው ሌላ እምነትም ሊሆን ይችላል። በሃይማኖቱና መልካም ምግባሩ
ምክንያት ተሾሞ በአገርና በህዝብ መካከል ስልጣን ሊኖረው ይችላል። እንዲሁም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ወንጌል እንዲሁም
ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ቤተ ክርስቲያን መልካም አሳብ ያለውና እነዚህንም በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የሚረዳ ሊሆን ይችላል።
ከነዚህም ሁሉ አልፎ የእምነት መሪም ሊሆን ይችላል። ዳግም ካልተወለደ ግን እነዚህ ሁሉ ምንም ፋይዳ ስለሌላቸው የእግዚአብሔርን
መንግሥት ሊያይ አይችልም።
ኃጢዓትን ማድረግ ማለት መሳሳትና እግዚአብሔርን
መበደል ብቻ አይደለም። ኃጢዓት ዓመጽ ነው፣ በፈጠረንና በሚወደን አምላክ ላይ ማመጽ፣ በቅዱስ ስራው ላይ ማመጽ፣ ለእኛ ባለው ዘለዓለማዊ
እቅድ ላይ ማመጽ ነው። ኃጢዓት እግዚአብሔር የሰጠንን ፈቃዳችንን እና ነጻነታችንን ነጥቆ ለራሱ ፈቃድ ያስገዛናል። የኃጢዓት ውጤቱ
ሞት ነው። ሮሜ 6፡23 አዳምና ሔዋን እንዳያደርጉ የታዘዙትን ጥሰው ኃጢዓት ባደረጉ ጊዜ ወዲያውኑ ነበር በእነርሱ ላይ የነበረው
የእግዚአብሔር ጸጋ፣ ግርማና ክብር የተገፈፈው። ወዲያውኑ ነበር ራቁትነት የተሰማቸው። ምንም እንኳን በስጋ በዚህ ምድር ላይ መኖራቸው
ቢቀጥልም፣ ከጌታ አምላክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት፣ በኤድን ገነት የነበራቸው የክብር ሕይወት ግን ሊገምቱት በማይችሉት መንገድ
ነበር የተለወጠው። ከፈጣሪ ተለዩ፣ ከኤድን ገነት ተባረሩ ወደዚያም እንዳይገቡ መንገዱ በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍና በኪሩቤል
ተዘጋ። (ዘፍረት 3፡24) በምድር ላይ ባሉ በእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረው የሰው ልጅ እንጀራን የሚበላው
በላቡ ወዝ እንዲሆን ተፈረደበት። ሊታመን የሚገባውን አምላክ እምቢ ብሎ የሰይጣንን ቃል ስላመነ ዛሬ በክርስቶስ የማያምኑ ሁሉ የሚተዳደሩት
የዚህ ዓለም ገዥ በሆነው በዲያብሎስና በእርሱ በሚመሩ በወደቁ መላእክት ስር ነው። የሁሉ የበላይና ገዢ እግዚአብሔር ነው። ነገር
ግን በሰው ዓመጽ ምክንያት፣ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የክርስቶስ ያልሆነው ዓለም ሁሉ የሚተዳደረው በጨለማው
ገዥ ስር ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን በመነሳቱ የኃጢዓት ዋጋ ተከፍሏል። እግዚአብሔር ለሰው
ልጅ ያለውን ፍቅር በማያወላዳ መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ገልጿል፣ እያንዳንዳችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን ከእርሱ ጋር
የምንታረቅበትን መንገድ ጠርጓል። ይህን የወንጌልን የምስራች ሰምቶ የሚቀበል ሁሉ ከልዑል እግዚአብሔር በመንፈስ ዳግም ይወለዳል፣
በዲያብሎስ ከሚመራው የጨለማው ዓለም ወደ ዘለዓለማዊው የክርስቶስ መንግስት ይፈልሳል። ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ የመዳን
መንገድ የለም። ብዙ ሃይማኖቶች፣ ብዙ ባህሎች፣ ብዙ ስርዓቶች አሉ፣ ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት የሚወሰደው መንገድ ግን የሚያልፈው
የግድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው። በክርስቶስ ዳግም የተወለደ ሰው የዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ ነው፤ በዚህ
ዓለም ይኖራል እንጂ ከሚጠፋው ከዚህ ዓለም አይደለም። ስለዚህም ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች በዚህ የጨለማው ዓለም ገዥና በተከታዮቹ
ይጠላሉ። እነዚህ እውነቶች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይገልጻቸዋል፤
1)
በእርሱ የሚያምን ሁሉ
የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ
እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፣ በማያምን ግን በአንዱ
በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ዮሐንስ 3፡16-18
2)
እርሱ ከጨለማ ስልጣን
አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢዓትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
3)
የእርሱ ወደሆነው መጣ፣
የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው፣ እነርሱም
ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከስጋ ፈቃድ፣ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ዮሐንስ 1፡11-13
4)
ለፍጥረቱ የበኩራት
ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ያዕቆብ 1፡18
5)
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ
ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፣ አሮጌው ነገር አልፎአል፣ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮ 5፡17
6)
ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች
ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው ቃልህንም ጠብቀዋል። ዮሐንስ 17፡6
7)
እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፣
እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። ዮሐ
17፡14-15
8)
ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ
በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፣ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ
ከዓለም ስላይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው ደቀ መዝሙርም ከመምህሩ አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ።
ዮሐ 15፡18-19
አንድ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲቀበል
በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእግዚአብሔር ዳግም ይወለዳል። ሰው ዳግም በሚወለድበት ጊዜ ቀድሞ ይኖርበት የነበረውን የኃጢዓትና የባርነት
ህይወት ስለሚጠላውና በኃጢዓቱም ስለሚጸጸት ንስሃ ይገባል፣ በበደሉ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ከዚያም በኋላ አምላኩን ለማፍቀርና ለመታዘዝ
ልቡን ያዘጋጃል። ይህ ንስሃ ይባላል። ያለ ንስሃ ዳግም ልደት የለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብሎ የሚያምን ሰው ከዲያብሎስ መንግስት
ስር አምልጦ ወደሚያስደንቀው ወደ ክርስቶስ መንግስት ይፈልሳል፣ አዲስ ፍጥረት፣ ሰማያዊ ዜጋ ይሆናል። በአዲሱ ህይወት ውስጥ ለማደግ
ደግሞ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ መኖር፣ አዲሱን ማንነቱን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ምግብ፣ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል፣
መመገብ፤ ከአምላኩ ጋር በጸሎት፣ በምስጋና፣ በመዝሙርና በአምልኮ እንዲሁም እንደርሱ ዳግም ከተወለዱ ሰዎች ጋር ህብረትን በማድረግ
በአምላኩ ዘለዓለማዊ ቤተሰብ ውስጥ ያድጋል። በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው ልክ ፍጥረታዊ ህጻን እንደሚያድግ በመንፈሳዊ
ህይወቱ ያድጋል፣ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ የሆኑ እውነቶችን በማወቅ ይጎለምሳል፣ መንፈሳዊ ፍሬን በእግዚአብሔር መንግስት ያፈራል። ዳግም
የተወለደ ክርስቲያን ልክ አዲስ ህጻን ወተትን ለማግኘት እንደሚፈልግና እንደሚያለቅስ የእግዚአብሔርን ቃል ለመመገብ ይናፍቃል፣ በራሱም
ቢሆን ለመማር ጥረት ያደርጋል። ይህ ከዳግም ልደት ምልክቶች አንዱ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን እውነት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤
“ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ህጻናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” 1ኛ ጴጥሮስ 2፡3
ታዲያ ወንድሜ፣ እህቴ አንተስ? አንቺስ?
እርስዎስ? በኢየሱስ ክርስቶስ አምነህ ዳግም ተወልደሃል? ተወልደሻል? ተወልደዋል? አዲስ ፍጥረት ሆነሃል? ሆነሻል? ሆነዋል? በክርስቶስ ዳግም ያልተወለዱ ሁሉ
የዚህ ዓለም ህይወት ሲያበቃ ወደ ዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግስት አይገቡም። መጨረሻቸው የእግዚአብሔር ፍርድና ለዘላለም ከፈጣሪ
ተለይቶ እሳቱ በማይጠፋ፣ ትሉ በማያንቀላፋ በእሳት ባህር ይሆናል። ዳግም ስለ መወለድህ፣ ስለ መወለድሽ፣ ስለ መወለድዎ እርግጠኛ
ካልሆን፣ ካልሆንሽ፣ ካልሆኑ ዛሬውኑ ንስሐ ግቡ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉ። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ
አምላክ ነው። የኃጢዓታችንን ዋጋ በሙሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍሏል፣ እርሱን ከተቀበልንም በኋላ ከኃጢዓት ባርነት ነጻ የሆነ
ህይወት ለመኖር የሚያስችለንን መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል። ይህን ህይወት ጨርሰን ሳንሄድ ክርስቶስን ልንቀበል ያስፈልጋል። ከሞት
በኋላ ንስሃ መግባትና ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበል ተስፋ የለም። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈው:
“ለሰዎችም
አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ የብዙዎችን ኃጢዓት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ
በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢዓት ይታይላቸዋል።” ዕብራውያን 9፡27
ስለዚህ ሰበብ አንፈልግ። ዛሬ ነገ ስንል
የምስራቹ ወንጌል አይለፈን!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ