ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ, May 10, 2018
ባለፉት 14 ወራት ብዙ አገሮች ለጦርነት
በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ፣ በተለያዩ የዓለም ክልሎች ከፍተኛ ግጭቶች ሊነሱ እንደሚችሉ እነዚህም ግጭቶች ተባብሰው ወደ ከፍተኛ ጦርነት
በመለወጥ ብዙ ህዝብን ሊያጠፉ እንደሚችሉ አመልክቼ ነበር። በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምትመለከቱት በእስራኤልና በኢራን መካከል
ጦርነት ተጀምሮአል። ዜናው እንደሚያሳየው ሳይሆን ጦርነቱ የጀመረው ከሁለት ሳምንት ያህል በፊት እስራኤል በሶርያ ውስጥ በሚገኝ
አንድ የኢራን የመሳሪያ ማከማቻ ነው ባለችው ስፍራ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ ነው። በዚያ ድብደባ ብዙ ወታደሮች የሞቱባት
ኢራን በጊዜው እንደምትበቀል ካስታወቀች በኋላ በዚህ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የእስራኤል መሪዎች ኢራን እስራኤልን ለማጥቃት እየተዘጋጀች
ናትና በቅድሚያ እርምጃ መውሰድ አለብን ሲሉ ከቆዩ በኋላ ረቡት ሌሊት (ሜይ 9 ለ10 አጥቢያ) በሶሪያ ግዛት ያሉ የኢራን ጦር
ያለባቸውን ስፍራዎችና የራሷን የሶሪያንም የአየር መከላከያና ሌሎች ወታደራዊ ማእከሎችን ስትደበድብ አድራለች። እስራኤል ይህን ድብደባ
ከማድረጓ በፊትም ቀኑ ላይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሲያ በየዓመቱ በምታደርገው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የድል በዓል ሰልፍ
ላይ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ተሰልፈው እንደ ዋሉና አገራቸው በሶሪያ ላይ ጥቃት በምትፈጽምበት ጊዜ በሶሪያ ያለው የሩሲያ ጦር ዝም
እንዲል የሩሲያውን ፕሬዝደንት ሲያግባቡ እንደዋሉ በዜና አውታሮች ተዘግቧል።
ይህ አሁን በእስራኤልና በኢራን እንዲሁም
በሶሪያ መካከል የተጀመረው ጦርነት መካከለኛውን ምስራቅና ዓለምንም በሙሉ ወደ ከፍተኛ የጦርነት እሳት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል እንደሆነ
እጅግ ብዙ የመንግስታት ባለስልጣኖች፣ የጦርና የስለላ ባለሙያዎች በሰፊው ቢያመለክቱም የምእራባውያኑ የዜና ምንጮች ግን ስለ ሁኔታው
በሰፊው አለመዘገባቸው ግልጽ ነው። የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት የሚያመለክቱ ትንቢቶችን በቅርብ በሚያጠኑ የመጽሐፍ
ቅዱስ ምሁራንና ተመራማሪዎች ዘንድ ግን ይህ ጦርነትና በዓለምም ዙሪያ የሚደረጉት ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅቶች ትንቢታዊ መሆናቸው
በሰፊው ይታመንበታል። ይህ ያለንበት ወር፣ ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል አገራቸው ፈራርሳና በምድርም ላይ እንደ ጨው ተበትነው የነበሩት
አይሁድ ከየአገሩ ተሰብስበው እስራኤል የምትባለው አገር እንደገና በምድር ካርታ ላይ የታየችበት 70ኛ ዓመት የሚከበርበት ነው።
የዛሬ 70 ዓመት በሜይ 14 ቀን ነበር እስራኤል እንደገና አገር ሆና የተመሰረተችው። የእስራኤል እንደገና እንደ አገር መመስረት
በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስቀድሞ የተነገረ ለመሆኑ የሚከሉትን አንዳንድ ትንቢቶች መመልከት ብቻ ይበቃል።
አሞጽ
9:14᎐5 ከክርስቶስ ልደት በፊት በ750 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ሕዝቅኤል
4፡3-6 ፣ 34፡13 ፣ 37፡10-14 ፣ 37፡21-22
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ593 እስከ 571 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ኢሳይያስ
66፡7-8
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ701 እስከ 681 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ኤርምያስ
16፡14-15፣ 31፡10 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ626 እስከ 586 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
በፊታችን ሰኞ ሜይ 14 እስራኤል እንደገና
የተመሰረተችበትን 70ኛ ዓመት ታከብራለች። የሰው እድሜ ሰባ ቢበዛ ሰማንያ ነው ተብሎ የተጻፈውን (መዝሙር 90፡10) እና ጌታ
ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያት ስለ መጨረሻው ዘመን ያስተማሯቸውን ትምህርቶች በማነጻጸር ይህ ሰባኛው የእስራኤል እንደገና መመስረት
መታሰቢያ ወቅት ምናልባት ገና ያልተፈጸሙት የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች የሚከናወኑበት ወቅት ይሆን? ዛሬ በመስታወት በድንግዝግዝ
እንደምናይ ነንና የትኛው ትንቢት በየትኛው ቀን ሊፈጸም እንደሚችል በእርግጠኝነት የሚያውቀው ጌታ አምላካችን ብቻ ነው። ነገር ግን
በዙሪያችን የሚታዩትን የማያሻሙ ምልክቶች ረጋ ብሎ በማጥናትና፣ በማነጻጸር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቤተ ክርስቲያንና በእስራኤልም ረጅም
ታሪክ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ከቃሉና ከዘመናችን ክስተቶች ጋር በማነጻጸር ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን መሆኑን እና የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓትም እንደ ተቃረበ እናውቃለን።
ዛሬ በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ከፍተኛ
ውጥረት እና በዚህም ምክንያት በታላላቆቹ አገሮች መካከል ስላለው ውዝግብ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት
በእስራኤልና በአካባቢዋ እንዲሁም በምድር ዙሪያ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ጦርነቶችም የተጻፉ ብዙ ትንቢቶች አሉ። የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ
ናቸው፤
የጎግና የማጎግ ጦርነት ፣ ሕዝቅኤል ምእራፍ 38 እና 39
እስራኤልን ከምድር ላይ ፈጽሞ ለማጥፋት በጎረቤቶቿና በወዳጆቻቸው በእስራኤል ላይ የሚደረግ ጦርነት
፣ መዝሙር ምእራፍ 83
በዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 6፣ 8 እና 9 ላይ ላይ የተገለጸው (የተገለሱት) አስፈሪና፣ የኑክሊየር የሚመስል፣
የዓለም ጦርነቶች።
ይህ ዛሬ የተነሳው ጦርነት አጭር ግጭት
ይሁን ወይስ ሊቀጥልና ሊስፋፋ የሚችል መሆኑን ለጊዜው ባናውቅም፣ በምድር ላይ ካለው ከፍተኛ ውጥረትና እንደ ሩሲያ፣ ቻይና እና
አሜሪካ እያደረጓቸው ካሉ ነገሮች አንጻር ሲመዘን ግን ሁኔታው የሚባባስና ስር የሚሰድ ነው የሚለው አስተያየት ይመዝናል። ጦርነት
አንድ ውጊያ ወይም የቦምብና የሚሳኤል ድብደባ ሳይሆን፣ በሰላም ካልተፈታ በስተቀር፣ እየተባባሰ ሊሄድ የሚችል መሆኑን ብዙ ታዛቢዎች
ይስማሙበታል። በእስራኤልና በኢራን መካከል በሶሪያ ምድር ውስጥ እስካሁን ከተደረጉት ውጊያዎች በስተጀርባ በቀላሉ ልናያቸው ወይም
ልንረዳቸው የማንችል ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉ። ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ የጦር ሰፈሮች አሏት የሶሪያንም መንግስት ትደግፋለች። የኢራን
ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎችም በሶሪያ ጋባዥነት በአገሪቱ ውስጥ የጦር ሰፈሮችን መስርተዋል። እስራኤልና ጎረቤቷ ዮርዳኖስ እንዲሁም
ብዙ የአረብ አገሮች ደግሞ በአሜሪካ የሚደገፉ ሲሆኑ ከእርሷም ጋር የጸጥታ ስምምነቶች ስላሏቸው። ስለዚህ፣ ምናልባት በእስራኤልና
በኢራን መካከል የተጀመረው ውጊያ ከተስፋፋና በጊዜው መልስ ካልተገኘለት እነ ሩሲያንና አሜሪካንንም ወደ ማይፈለግ ግጭት ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል ተብሎ ይፈራል።
ከሮማው ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ በብዙ አዋቂዎች፣
ተመራማሪዎችና ባለ የቅርብ መረጃ ያላቸው ባለ ስልጣናት ይነሳል ወይም ተነስቷል እየተባለ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰፊው የሚነገርለትን
የሶስተኛውን የዓለም ጦርነት አስፈሪ የሚያደርገው የሰው ልጅ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ፈጽሞ ሊያጠፋ የሚችልበት የጦርነት ቴክኖሎጂ
እድገት ላይ መድረሱ ነው። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ ስጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር (ማቴዎስ 24፡22) ብሎ ጌታ ኢየሱስ
የተናገረለት በዚህ በመጨረሻው ዘመን ተሰርተው በስራ ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎች በእርግጥም እጅግ የሚያስፈሩ ናቸው። ይሁን እንጂ
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዘላለም ሕይወትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊፈሩና ሊደነግጡ አይገባም። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ
ዳግም ምጽዓት ሲቃረብ ስለ ጦርነትና የጦርነት ወሬ መስማቱ የግድ ነው። የእኛ መልስ መፍራትና መደንገጥ ሳይሆን በመንፈስና በአእምሮ
እንዲሁም ደግሞ ሲቻለን ተግባራዊና አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን እንዲሁም በዙሪያችን ካሉ ወገኖች ሁሉ ጋር በመተባበር
መዘጋጀት ነው። ከሁሉም በላይ በጌታ በራሱ የተሰጠንን የደህንነትን ወንጌል የምስራች ላልሰሙ ሁሉ ማድረስና ለጌታ ቀን ዝግጁ ሆነን
እንድንገኝ በመንፈሳዊ ህይወታችን መትጋት ያስፈልገናል። መዝሙረኛው ዳዊት እንዳለው፣ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን
ታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝሙር 46፡1)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ