ያለንበት ዘመን እና በጉጉት ልንጠብቀው የሚገባን የወንጌል ተስፋ የጌታችን የኢየሱስ ዳግም ምጽዓት


ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

በዝናብና በጸሃይ፣ ከጭቃና ከአቧራ ጋር እየታገለ የሚያርስ ገበሬ ድካሙንና ውጣ ውረዱን እንዲታገስ የሚያደርገው አንድ ቀን የድካሙን ፍሬ እንደሚያጭድ ማወቁና ማመኑ ነው። በሩጫ፣ በእግር ኳስና በሌሎችም የስፖርት መስመሮች የሚሳተፉ ሰዎች ሰውነታችውን ለውድድር ብቁ ለማድረግ የሚወዱትን ምግብና እንቅልፍ ጭምር መስዋእት በማድረግ ይለማመዳሉ፣ የጨዋታዎቹን ህጎች ያጠናሉ፣ ይሰለጥናሉ፣ የሚሳተፉበትን የስፖርት መስመር ዜናዎች በቅርብ ይከታተላሉ። የግጥሚያና የውድድር ቀኖችንም በጉጉት የሚጠብቁት የማሸነፍና ሽልማት የማግኘት እድል እንዳላቸው ስለሚያምኑ ነው።  የክርስትናን ሕይወት የደስታ፣ የሰላምና የድል ሕይወት የሚያደርገው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ሰምቶና ተቀብሎ ላመነ ሰው የተሰጠው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ነው። ያ የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ የሚገለጠው ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዳግም ተመልሶ ሲመጣና የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ መንግስት ሲመሰርት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መንገድ ያስተምራል። አለበለዚያ ግን ሃዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው በዚህ ህይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮ 15፡19
የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን የክርስቶስ ወንጌል እውነተኛ መልእክት በየዘመኑ በተለያየ መንገድ እየተሸቃቀጠና እየተበረዘ በብዙዎች ዘንድ የዚህን ዓለም ገንዘብ፣ ስልጣንና ዝና ማትረፊያ መሆኑ አሳዛኝ ቢሆንም፣ የማይካድ እውነት ነው። ይህ እንደሚሆን የሚያውቀው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት ጀምሮ ደቀ መዛሙርቱ ከገንዘብና ከዚህ ዓለም ፍቅር እንዲሁም ደግሞ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባቸው ተኩላዎች እንዲጠነቀቁ አስተምሮአቸዋል። ማቴዎስ 7:15-20 እነዚያ በገበሬው እርሻ ላይ እንክርዳድን የዘሩ ሰዎች ስራ ዛሬ በእግዚአብሔር መንግሥት እርሻ (በክርስቲያኖች) መካከል ስር ሰዶ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ብለው በሰዎች የተቀመሙና የተዘጋጁ፣ ለሰው ጆሮ ለመስማት ደስ የሚያሰኙ፣ ስጋዊና ምድራዊ ምኞትን የሚቀሰቅሱ ትምህርቶችን በመከተል ሳያውቁት ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፈቀቅ እንዲሉ አድርጓቸዋል።
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሁሉ በእምነታቸው ተስፋ ላይ እንዲያተኩሩ ካስተማሩት ከጌታ ሃዋርያት አንዱና ዋነኛው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፤
“ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ
 የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።” 1ኛ ጴጥሮስ 1፡13
ከጴጥሮስ ጋር አብሮ የጌታ ሃዋርያ የነበረው ዮሐንስ ደግሞ እንዲህ ሲል የክርስቲያንን እውነተኛ ማንነትና ተስፋ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡
“ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።” 1ኛ ዮሐንስ 3፡2
የዕብራውያን ጸሃፊ ደግሞ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ተስፋ በሰማይ መሆኑን እና ያ ተስፋም የሚገለጸው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ እና ያችን በሰው እጅ ያልተሰራች ከተማ ሲገልጽ እንደሆነ እንደሚከተለው ያሳየናል፤
“እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ። በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፣ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን፤” ዕብራውያን 13፡12-14
በክርስቶስ ወንጌል የተሰጠውና ክርስቲያን ሁሉ ሊጠብቀው የሚገባው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓትና የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጥ እውን እንደሆነና የሰው ልጅ ከሚያውቀውና ከሚገምተው ሁሉ በላይ እጅግ የላቀ መሆኑን ደግሞ ሃዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ገልጾታል፤
“ዓይን ያላየችው፣ ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበው፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤” 1ኛ ቆሮ 2፡9
ጌታ አምላክ ይህንን ለሚወዱት ያዘጋጀውን ተስፋ በጊዜው ሊገልጸው ዝግጁ ስለሆነ በእርሱ ለሚያምኑበትና መገለጡን በመጠባበቅ ለሚኖሩ የማያሳፍራቸው መሆኑን የእብራውያን መጽሐፍ እንደሚከተለው ይነግረናል፤
“አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፣ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።” እብራውያን 11፡15-16

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ባስተላለፍኳቸው መልእክቶች በተደጋጋሚ ለአንባቢዎች ለማቅረብ እንደሞከርሁት የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የተቃረበበት ሰዓት አሁን ነው። ስለዚህም ዓለማችን በከፍተኛ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የማህበረሰብ ስነ ልቡናዊ ነውጥ ውስጥ ትገኛለች። ብዙውን ጊዜ ለውጥ ክፉ ነገር አይደለም። ዛሬ በምድር ላይ የሚታየውና ብዙዎች እድገትና ለውጥ ነው የሚሉት ግን የሰውን ዘር ወደ መልካም አቅጣጫና ፍጻሜ የሚያደርስ አለመሆኑ ገሃድ መውጣት ከመጀረ ውሎ አድሮአል። በብዙ የእምነት ድርጅቶችም ይሁን በፖለቲካና በኤኮኖሚ ተቋማት፣ በመንግስታት መዋቅሮችም ውስጥ ሆነ በየግለሰቡ የእለት ከእለት ኑሮ፣  ሃይማኖት አለኝ በሚሉ ሰዎችም ሆነ ሰልጥነናልና “አምላክ የለም” በሚሉ ዘንድ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት፣ በሃዋርያትና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመናት በፊት የተተነበየ ሁኔታ ትንቢታዊና ከፍተኛ ለውጥ ሊታይበት የሚችል ሂደት መሆኑ ቢገመትም በብዙ ሰዎች ዘንድ ግን በቂ ግንዛቤ ያገኘ አይመስልም።
በኖህ ዘመን በነበረው ዓለም እንደሆነውና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል ላይ እንዳስተማረው ዓለም ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ተንሸራቶ እየሄደ ነው። በኖህ ዘመን ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ የጥፋትም ውኃ መጥቶ ሁሉን እስኪያጠፋ ድረስ እንዳላወቁ በዚህ ዘመንም የሰው ልጅ፣ ብዙ ክርስቲያኖችንም ጨምሮ፣ በመንፈሳዊ አዚም ስር ያለ ይመስላል። በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጡ የአጋንንት ትምህርቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው ገብተው እውነት መሬት ላይ ወድቃለች። ኃጢዓት እንደ ስልጣኔ ተደርጎ ይሰበካል፣ አመጽም በመንግስታት እንደ ህግ እየጸደቀ ነው። ብዙ ቤተ ክርስቲያን ነን በሚሉ ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚደረግ ዓመጽ ዘመናዊ ነው ተብሎ ሰዎችን ንስሃ ግቡ በማለት ፈንታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክፍሎች ዘመን ያለፈባቸው ናቸው የሚሉ ድምጾች እየበዙ ናቸው። ኃጢዓትን ኃጢዓት ነው የሚሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል አልተረዱትም  ተብለው ይወቀሳሉ፣ ይወገዛሉ።
ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ ጌታ ምጽዓት ስናስብ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 51 እስከ 57 ወይም በ1ኛ ተሰሎንቄ ምእራፍ 4 ከቁጥር 15 እስከ 18 እንደ ተጻፈው የእግዚአብሔር መለከት በድንገት ተነፍቶ ሙታን የሚነሱበትንና በሕይወትም ያሉ ቅዱሳን በድንገት በቅጽበተ ዓይን የሚለወጡበትን የመነጠቅን ቀንና ሰዓት ልናውቅ እንደማንችል በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ቁጥር 36 ላይ ተመልክቷል። ነገር ግን የጌታ ዳግም ምጽዓት መቃረቡን የሚያመለክቱን ብዙ ምልክቶች እንዳሉና እነዚህም ምልክቶች በአንድ ላይ፣ በተደጋጋሚና በፍጥነት መታየት ሲጀምሩ የምጥ ጣር ምልክቶች እንደሆኑ እንድናውቅና ዓይናችንን አሻቅበን ከላይ የሚመጣውን ቤዛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንጠብቅ ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ራሱ በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 21 እና በሌሎቹም ወንጌሎች ላይ ያሳስበናል። ሃዋርያትም በተደጋጋሚ ከሰበኳቸውና በሰፊው ካስተማሩባቸው ታላላቅ ርእሶች መካከል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት አንዱና ጎልቶ የሚታይ ነው።
ጌታ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ የቀደሙ ክርስቲያኖችና መሪዎች ትልልቅ መከራዎች፣ ጦርነቶች፣ ረሃብና ቸነፈር እንዲሁም የምድር መናወጥና ሌሎቹም በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ዘመን የተነገሩ ምልክቶች በተከሰቱ ጊዜ ሁሉ ጌታ ሊመጣ ነው በማለት  ሲደናገጡ ግራ ሲጋቡና ሌሎችንም ግራ ሲያጋቡ መኖራቸው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈበት ነገር ነው። እንደዚህ ባሉ ማደናገሪያዎች ግራ የተጋቡ ሰዎችና ከመጀመሪያውም ጌታ ዳግም ተመልሶ ይመጣል በሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የማያምኑ ነገር ግን ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚቆጥሩ ሰዎችም በየዘመኑ በመነሳት የራሳቸውን ሃሳቦች በትምህርተ መለኮትና ትንታኔዎች (commentary) በመጻፍ በተለይ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሃዋርያት የተገለጸውን እውነት ገለል አድርጋ በሰዎች ትምህርት እንድትመራ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ስለዚህም ዛሬ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆችና በየሴሚናሪዎቹ እንደ ተራቀቀ እውቀት የሚሰጠው ስነ መለኮት የሚባል ትምህርት በተለያዩ የግሪክና የእብራይስጥ እንዲሁም ቴክኒካዊ ሃሳቦችና ንግግሮች ተውገርግሮ የሰዎችን ሃሳብና ትንተና ከእግዚአብሔር ቃል ጎን ለጎን በማስቀመጥ እውነተኛ አገልጋዮችን በመቅረጽና በማዘጋጀት ፈንታ ግራ የተጋቡና በጥያቄ የተሞሉ አስተማሪዎችንና መሪዎችን እያፈራ ነው። ዘመናዊ ስምና ማእረግ ይሰጣቸው እንጂ ዛሬም ቢሆን በስነ መለኮት ትምህርት ስም የሚሰጡ ብዙ የተውገረገሩና የተዛቡ ትምህርቶች መሰረታቸው ከጥንት ነው። እነዚህ ጌታ ኢየሱስ ጠላት በሌሊት መጥቶ የዘራው እንክርዳድ ምሳሌ አድርጎ ካስተማራቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ትክክለኛና የስነ መለኮት ትምህርት አስፈላጊ ነው። ብዙ እውነተኛ የሆነውን ትምህርትም የሚያስተምሩ ተቋማት አሉ። ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶችን ከሚያውገረግሩ ትምህርቶች ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። የዚህ መልእክት ዓላማ ስለተዛቡ ትምህርቶች ለመግለጽ ባይሆንም፣ ከተዛቡት ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ የጌታን ዳግም ምጽዓት የሚክዱ ወይም የሚያውገረግሩ መሆናቸውን ግን ሳልጠቅስ አላልፍም። ለዚህ ነው ዛሬ ብዙው ክርስቲያን እውነተኛውንና ዘለዓለማዊውን የወንጌልን ተስፋ፣  እርሱም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓትና በክብር መንገስ፣ እንዲያውቅና እንዲረዳ ከማስተማር ይልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሚመስል የሰዎች ሃሳብና ባዶ ሃይማኖተኝነት ተይዞ ትምህርቱ፣ ሃሳቡ፣ መሻቱና ተግባሩ ሁሉ በገንዘብ፣ በምድራዊ ክብርና ብልጽግና እንዲሁም በሚያልፉት የዚህ ዓለም ነገሮች ላይ ከልክ በላይ እንዲያተኩር የተደረገው።
በመጨረሻው ዘመን የብዙው የሰው ዘር ባህርይ ገንዘብንና ምቾትን እንዲሁም ተድላን ከእግዚአብሔር ይልቅ መውደድ እንደሚሆን በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት በ2ኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ 3 እና በ1ኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ 3 የተገለጸውም እውነት ፈጽሞ የተረሳ ይመስላል።  ይህም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል እንዳስተማረውና ሃዋርያው ጴጥሮስም እንደጻፈው በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ከጌታ ዳግም ምጽዓት ምልክቶች አንዱ ነው። ዛሬ በተደጋጋሚ ሲሰበክና እንደ ትምህርትም ሲሰጥ እንደሚሰማውና በተግባርም እንደሚታየው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖና ተቀብሎ የዳነ ብዙ ክርስቲያን የእድገት ምልክት መቀደስ፣ መታዘዝ፣ በመስዋእትነት ሕይወት መኖርና መንፈሳዊ ፍሬን ማፍራት መሆኑ ቀርቶ በዚህ ዓለም ቁሳቁስ፣ ገንዘብ፣ ብልጽግና እና የኑሮ እሽቅድምድም የተተበተበ ነው።
ጌታ እግዚአብሔር ለልጆቹ መልካም አምላክ ነው። እንኳን በልጁ ደም ለዋጃቸው ልጆቹ ይቅርና ለክፉዎችና ለማያመስግኑትም ሁሉ ጸሃዩን ያወጣል፣ ዝናቡንም ያዘንባል። የሰማይ አእዋፍን ይመግባል፣ የምድር አበቦችንም ያለብሳል። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ እውነትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በግልጽ ያስተማረው እውነት ነው። ነገር ግን በክርስቶስ ዳግም ተወልደናል የምንል ሁሉ ከሁሉም በላይ ልንሻውና ልንናፍቀው የሚገባን ታላቁ ነገር በወንጌል የተሰጠው ተስፋ፣ እርሱም የእግዚአብሔር መንግስት በክብር መምጣት ነው። የዚያ የእግዚአብሔር መንግስት ቁንጮ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፣ ክርስቲያን ሁሉ የእርሱን በክብር ዳግም መገለጽ እንዲጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መረጃዎችን፣ ትንቢቶችን፣  ምልክቶችን እና ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት ያስተምረናል። በመጨረሻው ዘመን የጌታ መምጣት መዳረሱን ከሚያሳዩን ምልክቶች አንዱ ብዙ ሰዎች፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንዶችንም ጨምሮ፣ የጌታን ዳግም መምጣት ችላ ማለት ብሎም አለማመንና አለመቀበል እንዲሁም በዚህ ሃሳብ ላይ ማፌዝ እንደሚሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎአል። ለምሳሌ ሃዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፤
በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞች የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፣ እነርሱም የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። 2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-7
ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በምድር ላይ የሚካሄደውን ነገር አተኩረን ብንመለከት ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ እየተፈጸመ ያለው የእግዚአብሔር ክህደት፣ ዓመጽ፣ ኃጢዓትና ክፉን መውደድ በፍጥነት ስር እየሰደደ ይገኛል። የምድር መናወጥ፣ ጎርፍ፣ የምድር መሰንጠቅና መደርመስ፣ እሳተ ገሞራ (በመጽሐፍ ቅዱስ ደምና እሳት፣ ጢስና ጭጋግ ተብሎ የተጠቀሰ)፣ ጦርነትና ከፍተኛ የሆነ የጦርነት ዝግጅት፣ የህዝብ ፈጂ በሽታዎች መብዛት፣ የኢኮኖሚና የገንዘብ ስርዓት መናጋት በምድር ሁሉ እየተስፋፋ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰላምና ብልጽግና ነው እየተባለ አብረው ሲነግዱና ሲገባበዙ የኖሩት ታላላቆቹ የምድር አገሮች እነ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ አገሮች፣ ጃፓን፣ ሩሲያና ቻይና፣ ብራዚል፣ ወዘተ ዛሬ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ውዝግብና ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። የነዳጅ ዋጋ ወደ ላይ እጅግ ማሻቀብ፣ የአሜሪካው ዶላር እየተገለለ በቻይናው ገንዘብ በሬንሚምቢ (ዩዋን) በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በሰፊው መተካቱ፣ አሜሪካ ከባላጋራዎቿ ጋር ብቻ ሳይሆን ወዳጆቿ ከሚባሉትም ጋር አንጃ ግራንጃ ውስጥ መዘፈቋና የተከተለው ግራ መጋባትና ፍጥጫ ብዙ የምድር መሪዎችንና ታዛቢዎችን እያስጨነቀ ይገኛል።
በአሜሪካና በአጋሮቿ በሩሲያ ላይ የሚደረገው መጋበዝና እቀባዎች፣ በምስራቃዊ ዩክሬን ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በሩሲያ፣ በአሜሪካና በአጋሮቿ መካከል ያለው ውጥረት፣ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና እስራኤልና ሌሎችም አጋሮቻቸው በአንድ በኩል፣  የሶሪያ መንግስት፣ ኢራንና  ሩሲያ ደግሞ በሌላው ተሰልፈው የሚሻኮቱበት አደገኛ ሁኔታ፣ ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በየጥቂት ወራቱ የሚያደርጉት የጦርነት ልምምድና ለሰሜን ኮሪያ የሚያሳዩት ማስፈራሪያ፣ በደቡብ የቻይና ባህርና በታይዋን ደሴት ምክንያት በአሜሪካና በቻይና መካከል ያለው ውጥረት ሁሉ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት ሊለኩሱ የሚችሉ ሁኔታዎች መሆናቸውን አዋቂዎች ይናገራሉ። ከአሜሪካና አጋሮቿ እንዲሁም ከሩሲያ ጋር የተፈረመውን የኢራን የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎች ምርምር የሚያግድ ስምምነት አሜሪካ አልቀበለውም በማለቷ የተፈጠረው ውጥረት ላለፉት ሶስት ዓመታት የነበረውን አንጻራዊ ሰላም አዛብቶ መካከለኛውን ምስራቅ ሊወጣ በማይቻልበት የጦርነት አዘቅት ውስጥ ያስገባዋል የሚሉም ብዙ ናቸው። የአሜሪካው ምክር ቤትም በኢራን ላይ ሊደረግ ስለሚችል ጥቃትና ስለሚከተለው ጦርነት እየተነጋገረ መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ናቸው። ባለፉት ሁለት በማይሞሉ ወራት ውስጥ ደግሞ በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ውጥረት ከአደገኘነት አምልጧል፣ ጦርነትም ሊቀር ነው የሚሉ ተስፋዎች ከተናፈሱ በኋላ ሁኔታው እንደገና ወደ መባባስ ውስጥ ገብቷል፣ በአሜሪካው ፕሬዝደንትና በሰሜን ኮሪያው መሪ መካከል ሊደረግ የነበረው የድርድር ስብሰባም ተሰርዞ የጦርነት ደመና እንደገና እያንዣበበ ነው።
ከሁለት ሺህ ዓመታት መፈራረስ በኋላ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንዋን አሜሪካ መቀበሏና ኤምባሲዋንም በዚሁ በያዝነው ወርና እስራኤል እንደገና በተመሰረችበት 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ በዚያው በኢየሩሳሌም መክፈቷ በብዙ አይሁዶችና እስራኤልን በሚደግፉ መካከል እንደ ትልቅ የትንቢት ፍጻሜ ቢታይም፣ በዚህ የተከፉት የእስላሞች አገሮችና ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ይህን ይቃወማሉ፣ ለመቀልበስም ይሞክራሉ። በኢየሩሳሌም የነበረውን የጥንቱን የአይሁድ ቤተ መቅደስ ለመስራት የሚታገሉ ድርጅቶች ደግሞ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ከሆነች ቤተ መቅደሱንም መስራት አለብን በማለት ግፊት እያደረጉ ሲሆን፣ በዚሁ ሳምንት ድሮ ቤተ መቅደስ ነበረበት በሚባለው ቦታ ላይ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ቆሞ ያለውን የእስላሞች መስጊድ አስወግዶ አዲስ ቤተ መቅደስ የሚያሳይ ካርታ በኢየሩሳሌም ላሉት ለአሜሪካው አምባሳደር መሰጠቱና በዜና መዘገቡ ደግሞ አንዳንዶችን ሲያስደነግጥ ሌሎችን ደግሞ አስገርሟል።
ብዙ የአይሁድ እምነት ተከታዮችና ደጋፊዎቻቸው የዛሬው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን በመቀበላቸው ከፍተኛ ትንቢታዊ ነገር ሰርተዋል ብለው ስለሚያምኑ፣ ቤተ መቅደሱም አሁን እንዲሰራ ድጋፍ እየጠየቁ ናቸው። የአሜሪካውን ፕሬዝደንት ምስል ከጥንቱ የፋርስ ንጉስ ቂሮስ ጋር የታዘ የቤተ መቅደስ ሳንቲም አትመው በገበያ ላይ አውለዋል። የሳንቲሙም ሽያጭ ለቤተ መቅደሱ መስሪያ ይሆናል ተብሏል። የጥንቱ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ከተሰራ ደግሞ የእስራኤል መሲህ (ማሺያክ) እንደሚመጣ የሚያምኑ አይሁድ ብዙ ናቸው። ይህ የቤተ መቅደሱ መሰራት ደጋፊዎች ይመጣል የሚሉት መሲህ ግን ክርስቲያኖች ዳግም ተመልሶ ይመጣል የሚሉትን የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም።
የዛሬዎቹ ብዙዎች አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሁ እንደሆነ አያምኑም። ቀረብ ብለን የጌታን ትምህርትና የሃዋርያትን መልእክቶች እንዲሁም ነቢያት ስለመጨረሻው ዘመን የተናገሯቸውን ትንቢቶች ካስተዋልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ከመምጣቱ ቀደም ሲል፣ መሲህ ነኝ የሚለው የዓመጽ ሰውና የጥፋት ልጅ (በተለምዶ ሃሰተኛው ክርስቶስ የሚባለው) ይገለጽ ዘንድ የግድ ነው።  ያ የዓመጽ ሰው አዲስ በሚሰራው ቤተ መቅደስ በአንዱ በኩል የጥፋትን ርኩሰት እንደሚያቆምበት ነቢዩ ዳንኤል በግልጽ ተናግሮአል፣ በአዲስ ኪዳንም ሃዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ሰው ተናግሮአል (2ኛ ተሰሎንቄ 2፡3-12) ታዲያ፣ ምናልባት ቤተ መቅደሱን ለመስራት እየተሯሯጡ ያሉት  አይሁድና ደጋፊዎቻቸው ሳያውቁ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ያንን ዓለምን ሁሉ የሚያስተውን የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ ተብሎ የተጠራውን ሃሰተኛውን ክርስቶስን ይሆን? ሰዎች ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመን እምቢ ካሉ በራሱ ስም የሚመጣውን ሃሳዊውን መሲህ ማመናቸው የግድ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ የጌታ ዳግም ምጽዓት እጅግ ተቃርቧል ማለት ነው። ምክንያቱም ያ ሃሰተኛው ክርስቶስ ለ42 ወራት ምድርን ካሳተና ብዙ ህዝብ ካለቀ በኋላ ይህን በራእይ አውሬው የተባለውን እና አጋሩን ያንን ሃሰተኛውን ነቢይ  ወደ እሳት ባህር የሚጥለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ያ የሚሆነው ደግሞ ጌታ በክብር ከሰማይ ተመልሶ ሲመጣ ነው። 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡8 እና ራዕይ 19፡20-21 እንዲሁም ዳንኤል 9;27 እና 12፡7-12
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በተናጥል ሲታዩ “ይህማ ምን አዲስ ነገር ነው ” ወይም ደግሞ “ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ምን አገናኘው” የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ናቸው ተብለው የሚጠሩት ከላይ የጠቀስኳቸው ብቻም አይደሉም። ስለ ቴክኖሎጂ አስፈሪ ልዕቀት፣ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለመቀየርና ለማሻሻል እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጋር ለማደባለቅ የሚያደርጉት እሽቅድምድም፣ በሰማያት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ምልክቶችና ኤሊየንስ ናቸው የሚሏቸውንና የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች ስለሚባሉት የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ወደ አደባባይ እያወጣቸው ያሉ መረጃዎችን ወዘተ ሁሉ ብጽፍ ለማንበብ ያደክማል።
በእርግጥም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በአንድ ጊዜ ወይም በሌላ በምድር ላይ ሲታዩ የቆዩ ነገሮች ናቸው። ነገር ግን የዛሬዎቹ ክስተቶች ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ ጌታን ዳግም ምጽዓት ከተጻፉት ትንቢቶች ጋር በቅርበት በማነጻጸር ሲመዘኑ የክስተቶቹ ብዛት፣ የመከሰታቸው ፍጥነትና ተያያዥነት እንዲሁም መወሳሰብና አስጨናቂ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ቀልብን እየሳበ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ከሚያጠኑ የክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የሃይማኖት፣ የታሪክና የፖለቲካ ታዛቢዎችና ተንታኞችም ነው። ብዙ የእስልምና ድርጅቶች፣ የሂንዱይዝም፣ ኔው ኤጅ፣ የቡድሂዝም ወዘተ መሪዎችም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፍጥረት፣ በተለይም ይህች ምድርና የሰው ዘር፣  ከፍተኛ የታሪክ ለውጥ ሊፈጸም በደረሰበት ዘመን ላይ እንዳሉ ይናገራሉ።
እንንቃ፣ የእግዚአብሔር ቃል ስለዚህ ዘመን የሚናገረውን፣ ቀረብ ብለን እንመልከተው፣ ደጋግመን እናንብበው እናጥናው። መረዳታችን በየትኛውም ደረጃ ላይ ይሁን በየትኛው ጌታ አምላካችንን በእውነትና በመንፈስ ለማምለክ፣ ለመታዘዝ፣ እርሱንና በምሳሌው የፈጠረውን ጎረቤታችንን ለመውደድና የወንጌሉን የምስራች ላልሰሙ ሁሉ ለማድረስ እንትጋ። ማራናታ፣ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና።1ኛ ቆሮ 16፡22


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...