ሰማያት እየተናገሩ ናቸው!! በፊታችን ሰኞ ኦገስት 21፣ ከ99 ዓመታት በኋላ አሜሪካን ከምእራብ እስከ ምስራቅ የሚያቋርጥ ሙሉ የጸሃይ ግርዶሽ ይሆናል። ይህ ምልክት ምናልባት በአሜሪካ ወይም በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ስላለ የትልቅ ጥፋት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ይሆን ???

ሰማያት እየተናገሩ ናቸው!! በፊታችን ሰኞ ኦገስት 21፣ ከ99 ዓመታት በኋላ አሜሪካን ከምእራብ እስከ ምስራቅ የሚያቋርጥ ሙሉ የጸሃይ ግርዶሽ ይሆናል።  ይህ ምልክት ምናልባት በአሜሪካ ወይም በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ስላለ የትልቅ ጥፋት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ይሆን ???

NASA ከሚባለው የአሜሪካ የህዋ ምርምር ድርጅት በድረ ገጹና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው፣ ሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓም በሰሜን ምእራብ ከምትገኘው ከኦሪጎን ክፍለ ሃገር እስከ ቻርልስተን ደቡብ ካሮላይና ድረስ ጸሃይ በቀን እንደምትጨልም ተገልጿል። ጸሃይ ፈጽማ በምትጨልምበት መስመር ላይ ያሉ ብዙ ወረዳዎችና ከተማዎች ከ2 እስከ 3 ደቂቃዎች ለሚያህል ጊዜ ቀኑ ፈጽሞ እንደሚጨልምና ሌሎቹ የአሜሪካ ክፍሎችም ደግሞ ከዚያ ላጠረ ሰዓትም ቢሆን ግርዶሹን እንደሚያዩ ይኸው የNASA መረጃ ያመለክታል።
የጸሃይና የጨረቃን ግርዶሽ እንዲሁም ሌሎችን በሰማይ ከዋክብትና ፕላኔቶች አልፎ አልፎ የሚታዩ ምልክቶችን፣ በሰው ዘርና በዓለም መንግስታት ታሪክ የታዩ ትልልቅ ክስተቶችን እና መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ ክስተቶች የሚናገረውን በቅርብ የሚያጠኑ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ታሪክ ጸሃፊዎች በፊታችን ሰኞ እንደሚታየው አይነት የጸሃይ ግርዶሽ ዓይነት በዚሁ በኦገስት 21 ቀን 1914 ዓም በምስራቅ አውሮፓ ታይቶ እንደነበር ያስታውሱና፣ ያ ግርዶሽም በአውሮፓ በጥቂት አገሮች ጠብ ተጀምሮ የነበረው ጦርነት የአንደኛውን የዓለም ጦርነት መነሳት ያመለከተ እንደነበር ያስረዳሉ። በጥቂት አገሮች መካከል በተነሳ ጠብ ከ2 ወር በፊት ተነስቶ የነበረው ግጭት ብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ወደ ጨረሰና ታላላቅ የዓለም መንግስታትና ግዛቶችን ወዳፈራረሰው የዓለም ጦርነት መለወጡ በታሪክ የተዘገበ ነው። የአሜሪካን ግዛት ሁሉ የሚያቋርጥ ሙሉ የጸሃይ ግርዶሽ ለመጨረሻ ጊዜ ታይቶ የነበረው በ June 8, 1918 ነበር። ጊዜው አንደኛው የዓለም ጦርነት እያበቃ የነበረበት ቢሆንም፣ ከዚያው በመቀጠል ግን በአሜሪካ ብቻ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺ ሰዎችን የገደለና በዓለም በሙሉ ደግሞ ከ ሃምሳ እስከ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን የፈጀ የወረርሽኝ በሽታ ተከስቶ እንደነበር ታሪክ ይዘግባል። ባለፉት ጥቂት ወራት በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለውን ከፍተኛ ውጥረትና የኑክሊየር ጦርነት አደጋ የሚከታተሉ ደግሞ ይህ ሰኞ ኦገስት 21 በአሜሪካ ላይ የሚከሰተው ግርዶሽ የመጀመሪያው የኮሪያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በ May 9, 1948 በሰሜንና በደቡብ ኮሪያ መካከል አቋርጦ የሄደውን የጸሃይ ግርዶሽ ያስታውሳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸሐይን ጨረቃና ከዋክብትን የፈጠራቸው ብርሃንን እንዲሰጡ፣ ለቀንና ለወቅቶች፣ ለወራትና ለዓመታት መቁጠሪያ እንዲያገለግሉ ብቻ ሳይሆን ለምልክት መስጫም እንደሆነ ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 1 ቁጥር 14 እስከ 19 ያስረዳል። አዳም ለእንስሳት ሁሉ ስምን እንደ ሰጠ የሰማይ ብርሃናትን ሁሉ ስም የሰጣቸውና ስራቸውንም የመደበላቸው እግዚአብሔር ራሱ ነው። መዝሙር 147፡4 ኢዮብ 38፡31-33 ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ክፍሎችም እግዚአብሔር በየዘመናቱ እነዚህን የሰማይ ብርሃናትን በመጠቀም ለሰው ልጆች መልእክቶችን፣ ምልክቶችንና ማስጠንቀቂያዎችን እንደ ሰጠ ይመሰክራሉ። ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የምስራቅ ጠቢባን (ሰብአ ሰገል) ያወቁት በሰማያት ላይ የተገለጠውን ምልክት በመረዳታቸው ነው። በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ጸሃይ እንደ ጨለመች ሉቃስ 23፡44-49 ማርቆስ 15፡33 እና ማቴዎስ 27፡45 ይመሰክራሉ። ከዚያ ቀደም ሲልም ነቢዩ ዮናስ ለነነዌ የንስሃን መልእክት ከመስበኩ ቀደም ብሎ በነነዌ ከተማ ላይ ያለፈ የጸሃይ ግርዶሽ ተከስቶ እንደነበር በNASA ድረ ገጽ የተደገፈ መረጃን ከብዙ ምንጮች ማየት ይቻላል። የ ቡር ሳጋል ግርዶሽ (Bur Sagale) ተብሎ የሚጠራው ያ የጸሃይ ግርዶሽ በ June 15, 763 ዓመተ ዓለም ተከስቶ እንደነበር የጥንት ታሪክ መረጃዎችና NASA ያከማቻቸው ያለፉት አምስት ሺ አመታት የጸሃይና ጨረቃ ግርዶሽ መረጃ ያሳያሉ። ሌሎች ታላላቅ ጥፋቶች በምድር ላይ ከመከሰታቸው ቀድሞ በጸሃይና በጨረቃ ግርዶሽ እንዲሁም በከዋክብት በሚሰጡ ምልክቶች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አስቀድሞ የንስሃ ጥሪና ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዳግም ምጽዓቱ መቃረቡን ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ በጸሃይ፣ በጨረቃና በከዋክብትም የሚታዩ ታላላቅ ምልክቶች እንደሚሆኑ ተናግሮአል። ሉቃስ 21፡25-28
በአሜሪካ ላይ የሚከሰተው የዘንድሮው (ኦገስት 21 ሰኞ) የጸሃይ ግርዶሽ የብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎችን ሃሳብ የሳበውና ያስፈራው ደግሞ ግርዶሹ የሚከሰተው አይሁድ በየዓመቱ ለ 40 ቀን የንስሃ ጊዜን ከሚጀምሩበት የኤሉል ወር መጀመሪያ አንድ ቀን ቀድሞ መሆኑ ነው። ከብሉይ ኪዳንና ከእስራኤል ታሪክ እንደምንረዳው ሰኞ ኦገስት 21 በአይሁድ (የጥንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን አቆጣጠር) ኦቭ 30 ነው። ከማክሰኞ ኤሉል 1 ጀምሮ እስከ ማስተሰረያ ቀን (ቲሽሪ 10) ድረስ አይሁድ ሁሉ ንስሃ የሚገቡበት ቀን ነው። ይህ አርባ ቀን ሲያልቅም በሰማያት ላይ ሌላ አስገራሚ ምልክት እንደሚታይ NASA ገልጾአል። ስለዚያ ምልክት ደግሞ በሚቀጥለው መልእክቴ እገልጻለሁ። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከጥንት ጀምሮ በብዙ መንገድ በቀጥታ በተገለጸ ቃሉ፣ በህሊና፣ በተፈጥሮ ስራዎቹ፣ በሰማይ ብርሃናት በሚገለጹ ምልክቶች፣ በመላእክት፣ በነቢያት፣ በህልምና በራእይ ከገለጸ በኋላ በዘመኑ መጨረሻ ደግሞ ራሱ ልዑል አምላክ የሰውን ሥጋ ለብሶ በመምጣት በክርስቶስ ተናግሮአል። ዛሬም እየተናገረ ነው። እኛ የመስማትንና የመረዳትን ጸጋ እንለምን እንጂ እግዚአብሔር ከመናገር ዝም ብሎ አያውቅም።
በዓለም ላይ ታላቁ ኤኮኖሚና የጦር ኃይል ያላት አሜሪካ ባለፈው ዓመት በተደረገ ምርጫ ያልተጠበቁት ሰው በፕሬዝደንትነት መመረጣቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካ መመሰቃቀል፣ እንደ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ጋር ካሉ አገሮች ጋር አገሪቱ የገባችባቸውን ውጥረቶች እንዲሁም በምድሪቱ የሚታየው ማህበረሰባዊ ውጥረቶች፣ መንፈሳዊና የሞራል ውድቀት የሚያሳዝናቸው የአገሪቱ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለምድራቸው ምህረትን እንዲያደርግ የንስሃና የጸሎት ጥሪዎችን ካወጁ ውለው አድረዋል። እነዚህን ሁኔታዎችና በሰማያትም ላይ የሚከሰቱትን የዘንድሮውን የጸሃይ ግርዶሽና በሴፕቴምበር 23 የሚከሰተውን ታላቅ የሰማያት ምልክት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብዙ የአሜሪካ ክርስቲያን መሪዎች አገሪቱ በንስሃ እግዚአብሔርን እንድትፈልግ ጥሪ እያደረጉ ያሉት።  በዚህች በምድር ላይ ባለች ኃያል አገር ላይ የሚፈጠር ቀውስ በአንድም በሌላም መንገድ የማይነካው አገርና ህዝብ በምድር ላይ የለም ማለት ማጋነን አይሆንም። ስለዚህ ሁላችንም ለዚህች አገር ሰላምና ምሕረት እንጸልይ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ሪፖርት ስለ ኦገስት 21 የጸሃይ ግርዶሽና ከላይ ልገልጻቸው ስለጀመርሁት ሃሳቦች የበለጠ መረጃን ይሰጣል።

እግዚአብሔር ይጠብቃችሁና ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ሰዎች ሁሉ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እንዲዘጋጁ አሳሰቡ።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ሰዎች ሁሉ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እንዲዘጋጁ አሳሰቡ።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የምስራቹ ወንጌል ከመንግሥታት ቁንጮዎች እስከ ተራው ሰው ድረስ በአንድም በሌላም መንገድ እየደረሰ ነው። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዘለዓለም ሕይወትን ገና ያላገኙትን ሁሉ በፍቅር ወንጌሉ ለመጋበዝና፣ በእርሱ ያመኑት ሁሉ ደግሞ የዳግም ምጽዓቱ ተስፋ መቃረቡን በማወቅና በማመን እንዲበረታቱ እግዚአብሔር ትንንሾችንም ትልልቆችንም ሰዎች እየተጠቀመ ነው። በአገራቸው በናይጄሪያ የፕሬዝደንትነት አገልግሎት ጊዜአቸውን ሲጨርሱ የመንግስትን ሥልጣንን በሰላም ለሚቀጥለው መሪ በማስረከባቸው እንደ መልካም መሪ ምሳሌ ከሚጠቀሱት የአፍሪካ መሪዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞው ጀነራል ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የምድር ነገስታት ሁሉ ንጉስ፣ የጌቶቹም ሁሉ ጌታ የሆነው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት መድረሱን መናገራቸው ብዙ ሰባኪዎች አስተማሪዎች የሚናገሩት ቢሆንም፣ በህዝቧ ብዛት በአፍሪካ አንደኛ የሆነችው የዚህ አገር ፕሬዝደንት የነበሩት እኒህ ሰው ይህን እውነት በአደባባይ መናገራቸው ለብዙ ሰዎች ምስክርነት ነው።

እስከ ጥቂት አሰርት ዓመታት ድረስ የክርስትና እምነት ዋና ምሰሶዎች ነን ሲሉ የነበሩት የምእራቡ ዓለም አብያተ ክርስቲያንና መንግስታት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጥለውና ወንጌልን ረስተው ወደ ባዕድ አምልኮ እየገቡ ባለበትና ሰለጠነ የሚባለው ዓለም ብዙ ህዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሰብዓዊ ህሊናን ጥሎ ለሰዶምና ለገሞራ እንኳን ያልበጀ የዓመጽ የኑሮ ዘይቤን እንደ ጌጥ እያንጠለጠለ ያዙኝ ልቀቁኝ በሚልበት በዚህ ዘመን፣ እግዚአብሔር ድሃና ያልተማረ ተብሎ በባለጸጋው ዓለም ወደታች ይታይ ከነበረው ከአፍሪካ የወንጌልን እውነት ለዓለም ሁሉ ሲልክ ማየቱ እጅግ አስደናቂ የፈጣሪ ስራ ነው። በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ይመጣል። ቀኑንና ሰዓቱን አናውቅም፣ ለማንኛውም ግን ማንም ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ እግዚአብሔር መድረስ አይችልምና ንስሃ ገብቶ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበያው ሰዓት ዛሬ ነው። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 9 ዛሬ ወጥቶአል


ምላስ መብልን እንደሚቀምስ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን? ኢዮብ 12፡11

ላለፉት 18 ወራት ከምእራቡ ዓለም፣ በተለይም ከአሜሪካ፣ የሚመነጩትን ዜናዎች የሚያዳምጥ ሰው “የውሸት ዜና” ወይም “Fake News” የሚለውን ስም ሳይሰማ አይቀርም። እነዚህ “የውሸት ዜናዎች” የሚፈጠሩትና የሚሰራጩት ደግሞ ታላላቅ በሚባሉትና ብዙ ቢሊዮን ዶላር ገቢና ወጭ ባላቸው እጅግ ብዙ ህዝብ በሚያዳምጣቸው እንደ CNN, ABC, CNBC እና MSNBC ያሉ የዜና አውታሮች ነው። “የውሸት ዜናዎች” ተብለው የሚሰራጩት ዜናዎች ደግሞ ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉትን የአሜሪካውን መሪ በማይወዱ፣ እንዳይመረጡ ሲጥሩ በነበሩ፣ ዛሬም የሰውየውን በስልጣን ላይ መቀመጥ ስለሚጠሉ በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ ከቦታቸው ለማውረድ ቆርጠው በተነሱ ከመገናኛ ብዙኃን በስተጀርባ ባሉ ታላላቅና ባለጸጋ ሰዎች ነው።
ይህን መረጃ እዚህ ጋ ያቀረብኩበት ምክንያት ስለ አሜሪካ የፖለቲካ ሁኔታ መረጃ ለመስጠት ሳይሆን “የውሸት ዜና” የሚባለውን ሃሳብ ስመለከት፣ ጽንሰ ሃሳቡ አዲስ እንዳልሆነና መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ በእግዚአብሔር ስም ስለሚሰራጩ የሃሰት ትንቢቶች፣ ትምህርቶችና ምክር መስለው ስለሚሰራጩ ክፉና አጥፊ የሃሰት መረጃዎች መናገሩን ሳስተውል ነው። በኤድን ገነት ለሔዋን በእባቡ የቀረበላት ድንቅ የሚመስል ዜና የውሸት ዜና ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታዲያ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በነቢያቱ፣ በሐዋርያትና በሌሎችም ቅዱሳን ሰዎች ከሚገልጸው እውነት ጋር የሚመሳሰሉ ሃሳቦችን፣ትንቢቶችን እና ትምህርቶችን  ጠላት ዲያብሎስ በየጊዜው በሰዎች መካከል ያሰራጫል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃሰት ነቢያት ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ደግሞ እንዲሁ ከሃዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ የሃሰት አስተማሪዎችና የስህተት ትምህርቶች እንደተሰራጩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እግዚአብሔር ዘመናትን በሙሉ በቅድሚያ ስለሚያውቅ፣ ያለፉትንና ያሉትን የሃሰት ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚከሰቱትን አስቀድሞ አይቶ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ህዝቡ ከነዚያ ትምህርቶች እንዲጠነቀቁ እውነቱን በብሉይና በሃዲስ ኪዳን መጻህፍት አስቀምጦልናል።

ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈሳዊ የሚመስሉ የሃሰት ትምህርቶችን ከእውነቱ መለየት የምንችለው በመጀመሪያ እውነቱን ሁሉ የሚያስተምረንን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ስናውቅ ነው። እውነቱን ጠንቅቀን ካላወቅንና እምነታችን በአለቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መመስረቱን ካላረጋገጥን በየጊዜው በሚነሱ የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች መወሰዳችን የግድ ነው። የስንዴን ዘር ወይም ተክል አይቶ የማያውቅ ሰው ስንዴውን ከእንክርዳዱ ሊለይ አይችልም። የእውነት መለኪያው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ አንድን ትምህርት ወይም አስተማሪ የሚከተሉት ሰዎች ብዛትና የሃሳቡ ዘመናዊ ወይም መንፈሳዊ መምሰል አይደለም። እውነት፣ መንገድና ህይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስንዴውን ከእንክርዳዱ እንዴት ልንለይ እንደምንችል፣ በተለይም ደግሞ በዚህ ዘመን በሰፊው እየተናፈሰ ያለውን “የብልጽግና ወንጌል” የሚባለውን ትምህርት ከእውነተኛው ወንጌል መለየት እንድንችል የሚረዱንን አንዳንድ ሃሳቦችን የያዘችው የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 9 ዛሬ ወጥታለች። ባለፉት ብዙ ወራት ጥቂት ሲቀርብ የቆየው የዶ/ር ዘመድኩን ተሻለ የህይወት ምስክርነት ክፍል ስድስትም በዚሁ እትም ቀርቦአል። የመጽሔቱን PDF ቅጂ በነጻ በመቅዳት (ዳውንሎድ በማድረግ) እንድታነቡና ለሌሎችም እንድታካፍሉ በትህትና እጋብዛችኋለሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ዓለም በብዙ አቅጣጫዎች 3ኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስነሳ በሚችል ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች

ዓለም በብዙ አቅጣጫዎች 3ኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስነሳ በሚችል ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች
http://endtimeheadlines.org/2017/07/rumors-war-u-s-inches-war-north-korea-millions-die/

ባለፉት ወራት ደጋግሜ እንደጻፍሁትና ከታች ከተያያዘው ሪፖርት እንደምትረዱት፣ ልንረዳው በማንችለው ፍጥነት ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ፍጅትን ሊፈጥር ወደሚችል ወደ ከፍተኛ ጦርነት እየተፋጠነች ነው። ብዙ ለመረጃዎች ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይህ ጦርነት የ3ኛው የዓለም ጦርነትና የኑክሊየር መሳሪያዎችም ስራ ላይ የሚውሉበት ሊሆን ይችላል እያሉ ያስጠነቅቃሉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ የኤኮኖሚ እቀባን አሜሪካ በሩሲያ ላይ ጥላለች። የአሜሪካው ምክር ቤት የገዛ የራሳቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት እንኳን እቀባውን እንዳስፈላጊነቱ በማስተካከል ከሩሲያ ጋር በንግግር በሚደረግ መግባባት እንዳይደርሱ እጅ እግራቸውን የሚያስር እቀባን ያሳለፉት 419 ለ3 እና 98 ለ 2 በሆነ ድምጽ ነው። ፕሬዝዳንቱም የምክር ቤቱን ውሳኔ ህግ እንዲሆን የፈረሙት ምንም ምርጫ ስለሌላቸው እንጂ እንደማይስባሙበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በአደባባይ ተናግረዋል። ታሪክን የሚያስታውስ ካለ፣ ጃፓን የአሜሪካ ግዛት የሆነውን ፐርል ሃርበርን በቦምብ የደበደበችው አላላውስ የሚል የኤኮኖሚ እቀባ በአሜሪካ ስለተደረገባት ነበርና፣ የአሁኑ የአሜሪካ ግፊትም ሩሲያ ሳትወድ ተገፍታ ወደ ጦርነት እንድትገባ ለማድረግ ነው የሚሉት የራሷ የአሜሪካ የቀድሞ ጀነራሎችና ታሪክ ታዛቢዎች ናቸው። ሩሲያም ይህን ለመበቀል ከ750 በላይ የሆኑ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ አባርራለች፣ ዲፕሎማቶቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የመዝናኛ እና የእቃ ማከማቻ ቤቶችንም ነጥቃለች።  ፍጻሜ  ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሰራዊት በብዙ የዓለም ክልሎች ግንባር ለግንባር ተፋጥጠው ለጦርነት ከፍተኛ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ አሜሪካ አዲስና እስካሁን ካሏት ሁሉ ትልቅ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን ሰርታ አሰማርታለች። ከ 3 ቀናት በፊት ቻይና የጦር ሰራዊቷ የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት በምታከብርበት ጊዜ እስከ ዛሬ ወደ አደባባይ ወጥተው ያልታዩ አስፈሪ የጦር መሳሪያዎችን አሳይታለች። ሩሲያም ዓመታዊ የባህር ኃይሏ በሚከበርበት ቀን ከ 100 በላይ የጦር መርከቦችን በማሰለፍ ኃይሏን አሳይታለች። የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩት በቦልቲክ ሪፑብሊኮችና በጆርጂያ አሜሪካና አጋሮቿ የጦር ልምምድ ሲያደርጉ ከርመዋል። በፋርሱ ባህረ ሰላጤ የአሜሪካና የኢራን የባህር ኃይሎች ከመገላመጥ አልፈው በአንድ ሳምንት ጊዜ ያህል ብቻ የአሜሪካ ጦር የኢራንን ጀልባዎች ለማስፈራራትና ለማስጠንቀቅ እንደተኮሱ ተዘግቦአል። ልብ ብሎ ለሚያዳምጠው የሚያስፈራ የጦርነት ነጋሪት በምድር እየተደለቀ ነው። ይህ እየተፈራ ያለው ጦርነት በእርግጥ ከተነሳ 3ኛው የዓለም ጦርነት እንደሚሆንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያልቁ ብዙ አዋቂዎች ያስጠነቅቃሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም የመምጫው ዘመን ሲቃረብ በምድር ላይ ጦርነትና የጦርነት ወሬ እጅግ እንደሚበዛ ተናግሮአል። ታዲያ ምን እናድርግ? ሊሆን ያለው ሁሉ ይሆናል። በተቻለን መጠን መረጃዎችን ማግኘታችንና በግላችንና ለቤተሰባችን እንዲሁም ለህብረተሰባችን ልናደርገው የምንችለው ዝግጅት ካለ በጊዜው ማድረጉ መልካም ነው። በክርስቶስ የምናምን ክርስቲያኖች ሁሉ ለሰላም እንጸልይ። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን ያልተቀበልን ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ የነፍሳችንን የዘለዓለም ኢንሹራንስ ማግኘቱ አንገብጋቢ ነው። ያ ኢንሹራንስ ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ነው። ለደህንነታችን የሚከፈለውን ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከፍሎልናል። ዛሬም ኑ እያለ የሰውን ልጆች ሁሉ ወደ ደህንነት ይጋብዛል። ጥሪውን ሳንመልስና ዛሬ ነገ ስንል ጊዜ አይለፍብን። ማንም አያታልለን። ይህችን ህይወት ጨርሰን ከዚህ ዓለም ከሄድን በኋላ ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም። የእግዚአብሔር ሰላም ይብዛላችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ። 

የእንግሊዝ መንግስት መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና መተርጎም አለበት፣ የመጽሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና የእሁድ የመጽሃፍ ቅዱስ ትምህርቶችም ሳይቀሩ ሰዶማዊነት ትክክል መሆኑን ማስተማር አለባቸው የሚል ሪፖርት አወጣ።

የእንግሊዝ መንግስት መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና መተርጎም አለበት፣ የመጽሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና የእሁድ የመጽሃፍ ቅዱስ ትምህርቶችም ሳይቀሩ ሰዶማዊነት ትክክል መሆኑን ማስተማር አለባቸው የሚል ሪፖርት አወጣ። ዜናውን ከዚህ ማገናኛ ማግኘት ይቻላል። http://www.wnd.com/2017/07/u-k-govt-demands-queer-theology-in-seminaries/
ዊልተን ፓርክ የሚባለው የእንግሊዝ መንግስት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሴሚናሪዎች ሰዶማዊነትን የሚያስረዱና የሚደግፉ ትምህርቶችን እንዲያዘጋጁ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱም እንደገና እንዲተረጎምና ሰዶማዊነትን የሚቃወሙ ክፍሎች ውስጥ ያሉት ሃሳቦች መከለስ አለባቸው የሚል ሪፖርት አወጣ። በምእራብ አውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በሌሎችም ሰለጠኑ በሚባሉ አገሮች ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከመዳከማቸው የተነሳ ሰዶማዊነትን ወይም ሌሎች ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎችን ስለማይቃወሙ፣ የሪፖርቱ ትኩረት የክርስትና እምነት ጠንካራ በሆነባቸው በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካና ሌሎችም መጽሃፍ ቅዱሳዊ እምነት ጠንካራ በሆነባቸው አገሮች ላይ ነው።  ወገኖች፣ በትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ 7 ቁጥር 25 ላይ ሃሰተኛው ክርስቶስ ጌታ አምላክ የደነገጋቸውን ህግጋትንና ዘመናትን ይለውጣል ተብሎ የተጻፈው መፈጸም ከጀመረ ውሎ አድሮአል። ምናልባት የጌታ መምጣት በጣም ሩቅ የሚመስለን ካለን ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ እንዳያልፍብን ቶሎ እንንቃ። ከላይ የተጠቀሰውን ሪፖርት ለማንበብ የሚፈልግ ሰው ሪፖርቱን ከሚከተለው ድረ ገጽ ማገናኛ (link) ማግኘት ይችላል። https://www.wiltonpark.org.uk/wp-content/uploads/WP1488-Report.pdf


እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ። ኤፌሶን 4፡15

እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ። ኤፌሶን 4፡15
ወደዚህ ዓለም ሥጋን ለብሶ በመምጣት የደህንነትን የምስራች ወንጌል ያበሰረው እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳና ወደ አብ ካረገ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ የበግ ለምድ አልብሶ የሚልካቸው ተኩላዎቹ የጌታን ህዝብ ለማመሳቀል፣ ግራ ለማጋባትና ቢቻላቸውም ከእውነተኛው የወንጌል እምነት ለማራቅ እንደሚዘምቱ ደቀ መዛሙርቱን ደጋግሞ አስተምሮአቸው ነበር። በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 13 ከቁጥር 24 እስከ 30 የሚገኘው ምሳሌ ከነዚህ ትምህርቶች አንዱ ነው። የእርሻው ባለቤት (ኢየሱስ ክርስቶስ) እውነተኛ የህይወትን (የስንዴውን ምሳሌ) በቀን (በገሃድ፣ በአደባባይ) በእርሻው ላይ ከዘራ በኋላ ይህንን እውነተኛ ዘር የሚመስል የውሸት ዘር (እንክርዳድ) ደግሞ ጠላት በሌሊት (በድብቅ) በእርሻው ላይ ዘራ።  አስተውሎ ለማያውቀው ለማንኛውም ገበሬ የስንዴና የእንክርዳድ ተክል ብዙ ተመሳሳይነት ስላላቸው እርሻው ላይ በሚበቅሉበት ጊዜ አንዱን ከሌላው ለመለየት አስቸጋሪ ነው። የእርሻው ሰራተኞች የእንክርዳዱን መዘራት ያስተዋሉት ዘሩ በበቀለና ማፍራት (ማሸት) በጀመረ ጊዜ ነበር። ይህ እስኪሆን ድረስ ደግሞ ብዙ ቀናት አልፈዋል። የእንክርዳዱ ዘር መልካሙን የእርሻውን አፈር፣ አየርና ውሃ ከስንዴው ጋር እየተሻማ ለምልሞና ተመሳስሎ ብዙ ሳምንትታት ቆይቷል። የፍሬ ጊዜ ሲደርስ ነው ጉዱ እየታየ የመጣው። ሰራተኞቹም የእርሻውን ባለቤት የዘራኽው መልካም የስንዴ ዘር ብቻ አልነበረምን ብለው የጠየቁትም በእርሻው ላይ የሚታየው ፍሬ የስንዴ ብቻ እንዳልሆነ በተገነዘቡ ጊዜ ብቻ ነበር። ታዲያ የእርሻው ባለቤት መልስም ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ደጋግሞ እንዳስተማራቸውና እንዳስጠነቀቃቸው የማያሻማ ነበር። ባለቤቱ የዘራው ዘር እንከን የሌለው ስንዴ ሲሆን፣ እንክርዳዱን በእርሻው ላይ በሌሊት ዘርቶ የሄደው ደግሞ የእርሻውና የእርሻው ባለቤት ጠላት ነበር። የእርሻው ባለቤት ክርስቶስ፣ እርሻው በክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች እና እንክርዳዱን የዘራው ደግሞ የሰው ዘር ጠላትና የክርስቶስ ተቃዋሚ ዲያብሎስ መሆኑን ከምሳሌው ለመረዳት ይቻላል። የእንክርዳዱ በእርሻው ላይ መገኘትና ከስንዴው እኩል ፍሬውን እያፈራ መገኘቱ ያስቆጣቸው የእርሻው ሰራተኞች በትክክለኛና ህጋዊ ቅንዓት ተነስተው እንክርዳዱን እንንቀል ባሉት ጊዜ ግን የእርሻው ባለቤት አልፈቀደላቸውም። ምክንያቱም የባለቤቱ ዋነኛ ትኩረት የእያንዳንዱ የስንዴ  ቅንጣት (የጌታ ደቀ መዝሙር) ሕይወትና እንደ አቅሙም ሰላሳ፣ ስድሳ ወይም መቶ ፍሬ የማፍራቱ ሂደት እንክርዳዱን ለመንቀል በሚፈጠረው ግርግር እንዳይተጓጎል ነው። ስንዴውም እንክርዳዱም ተጠጋግተው እግር ለእግር የቆሙት በአንዱ እርሻ ላይ፣ ምግባቸውን፣ ውሃና አየርም የሚያገኙት ከዚያው ከአንዱ እርሻ ላይ ስለነበር ሰራተኞቹ እንክርዳዱን እንነቅላለን ሲሉ ስንዴውንም አብረው ሊመነግሉት ስለሚችሉ ነው። የእርሻው ባለቤት ደግሞ አንድ የስንዴ ተክል እንኳን ቢሆን እንዲነቀል አይፈልግም፣ አይፈቅድምም ነበር። ስለዚህም እስከ መከር ቀን ድረስ ተዋቸው፣ በዚያን ቀን አጫጆች የስንዴውን ነዶና እንክርዳዱን በሚገባ ይለዩታል፣ ስንዴው ወደ ጎተራው እንክርዳዱም ወደ እሳቱ ይሄዳል ብሎ አዘዛቸው።
ጌታ ኢየሱስ ከላይ በተጻፈውና በሌሎችም ምሳሌዎች አማካኝነት ደቀ መዛሙርቱ በዲያብሎስና ዲያብሎስ የበግ ለምድ አልብሶ ከሚልካቸው የሃሰት አስተማሪዎች ከሚፈለፍሉአቸው እውነት መሳይ የሃሰት ትምህርቶች እንዲጠነቀቁ ካስተማራቸው ከ30 ዓመታት ያህል በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎቹም የጌታ ሃዋርያት በዚሁ ርእስ ላይ ምእመናንን ሲያስተምሩ እንመለከታለን። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ምእራፍ 4 ላይ የኤፌሶን ከተማ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው እየነጎደ ከነበረው የተለያዩ የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ነፋስ እንዲጠነቀቁ ያስተማራቸው በሚከተሉት ቃላት ነው፤
“እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፣ በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕጻናት መሆን ወደፊት አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ። ከእርሱም (ከክርስቶስ) የተነሳ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሰራ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።” ኤፌሶን 4፡14-16
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ቅዱሳንን ከእውነተኛው የወንጌል መንገድ ለማሳት፣ በክርስቶስ ያላመኑት ደግሞ እውነቱን እንዳያውቁና እንዳይድኑ ለማገድ ጠላት ዲያብሎስ ከሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች ሁሉ እጅግ አደገኞቹ ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተመሳስለው የሚፈጠሩ የሃሰት ትምህርቶች (doctrines) ናቸው። እነዚህን የሃሰት ትምህርቶች የሚያስተምሩ ሰዎች ክርስቲያን ይመስላሉ፣ እንደ ክርስቲያን ያወራሉ፣ በእግዚአብሔር ቃልና በእግዚአብሔር መንፈስ ሊለዩአቸው የማይችሉ አዳዲስ ክርስቲያኖችንና ገና የወንጌልን እውነት ያልተቀበሉ ሰዎችን የመሳብና የማስከተል ችሎታም አላቸው። ስለ እግዚአብሔር ያወራሉ። ነገር ግን፣ እነሱ እናምነዋለን የሚሉት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት የሚያምኑ ክርስቲያኖች የሚከተሉት የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር አይደለም። ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ነገር ግን እነሱ እንከተለዋለን የሚሉት ክርስቶስ በመለኮትነት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነውን፣ የነበረውን፣ ያለውንና የሚመጣውን፣ እኛን ለማዳን ከድንግል ማርያም ስጋን ለብሶ የተወለደውን፣ ከኃጢዓት ፍጹም ነጻ የሆነ ሕይወትን በምድር ላይ ከተመላለሰ በኋላ የኃጢዓታችንን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ የሞተውን፣ የተቀበረውን፣ በሶስተኛው ቀን ከሞት የተነሳውን፣ በክብር ያረገውንና በአብ ቀኝ የተቀመጠውን፣ ዛሬ ስለ እኛ የሚማልደውን፣ እንደገና በክብርና በአካል ተመልሶ የሚመጣውን፣ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደውን እግዚአብሔር ወልድን አይደለም። ስለ መንፈስ ቅዱስም ሲናገሩ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮትነቱ እኩል የሆነውን፣ በክርስቶስ የሚያምኑትን ወደ እውነት ሁሉ የሚመራውን፣ ዓለምን ስለ ኃጢዓት ስለ ጽድቅና ስለፍርድ የሚወቅሰውን የራሱ ባህርይና ሰውነት ያለውን መንፈስ ቅዱስን አይደለም።  
ስለ ሐሰት ትምህርቶች ስናጠና ማስተዋል የሚገባን አንድ ትልቅ ቁም ነገርም አለ። ሆን ተብለው የተፈጠሩ የለየላቸው የሐሰት ትምህርቶች አሉ። እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ሰዎች እውነተኛውን እግዚአብሔርን፣ በተለይም ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳያውቁና አምነው እንዳይድኑ የተፈጠሩ ናቸው። በሌላው ወገን ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት እናምናለን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ እንቀበላለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ካለመማራቸውና በትክክል ካለመረዳታቸው የተነሳ በተሳሳተ መንገድ የሚያስተምሩአቸው ትምህርቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ በምድራዊ ገንዘብም ሃብታም ይሆናል፣ አይታመምም፣ አይቸገርም ይላሉ። ከዚህም በማለፍ አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ ካመነ በኋላ በዚህ ዓለም ገንዘብ ድሃ ቢሆን፣ ቢታመምና ቢቸገር ወይም ፈውስንና ተአምራትን ባይለማመድ ይህ የሆነበት የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ስላላወቀና በትክክል ስላላመነ ነው ብለው ያስተምራሉ። እንዲህ ያሉ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በከፊል ብቻ ያካተቱና የቃሉ መሰረት የሌላቸው ናቸው። እንደዚህ ያሉ ትምህርቶች ብዙ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የተገኘውን የዘለዓለም ሕይወት በመቀበል ፈንታ በምድራዊ ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታሉ፣ በአስተማሪዎቹ የሚነገሩአቸው ነገሮችም በሙሉ ሊፈጸሙ የማይችሉ ስለሆኑ ብዙዎችን ያሰናክላሉ። በቅንነት፣ እውነቱ ሳይገባቸው የተሳሳተ ነገርን የሚያስተምሩ ሰዎች  አንድ ቀን እውነቱ ሲገለጽላቸው በንስሐ ሊመለሱ ይችላሉ። እውነቱን በሚገባ ከተረዱና የተሳሳተ ትምህርታቸው የሚፈጥረውን መሰናክል ከተረዱ በኋላ በእልህ የተሳሳተ ትምህርታቸውን ማስተማር ከቀጠሉ ግን ዓመጻ ነውና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፍርድ ያጋልጣሉ።
የሃሰት ትምህርቶች ብዙ ዓይነት ናቸው። ትምህርቶቻቸውና ፍልስናዎቻቸውም ብዙና የተወሳሰቡ ስለሆኑ እንዲህ ባለ አጭር መልእክት ለመግለጽ ያስቸግራል። የሚቀጥለው የመለከት ድምጽ መጽሔት በዚህ ርእስ ላይ ሰፋ ያለ ትምህርትን ይዞ ይቀርባል። ለአሁኑ ያህል ግን የነዚህን የሐሰት ትምህርቶች ዋና ዋና ባህርያት ለመለየት የሚያስችሉንን አንዳንድ ነጥቦች ብቻ በአጭሩ እንመልከት፤
1)     ብዙ የሐሰት ትምህርቶች መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። አስተማሪዎቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን የሚሉት ክርስቲያኖችን በቀላሉ ለማጥመድ እንዲቻላቸውና በዓለም ሁሉ የተሰበከውን የእውነትን ወንጌል መደገፊያ  በማድረግ የሃሰት ትምህርቶቻቸውን ለማስተማር እንዲመቻቸው ብቻ ነው  2ኛ ጴጥሮስ 3፡16-17
2)    ብዙ የሐሰት ትምህርቶች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከተጻፉት ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻህፍት ሌላ (ተጨማሪ) በሃሰተኛ ሰዎች የተጻፉ የሃሰት ትምህርቶችን የያዙ መጻህፍትን ይከተላሉ። 1ኛ ጢሞቲ 4፡1
3)   ብዙ የሐሰት ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተቀመጠውን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት (ሥላሴ) ይክዳሉ
ማቴዎስ 28፡19-20  1ኛ ዮሐ 2፡23
4)   ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የሰውን ሥጋ ለብሶ ከድንግል ማርያም መወለዱን ይክዳሉ  1ኛ ዮሐ 4፡3
5)   አንዳንድ የሐሰት ትምህርቶች ኢየሱስ ክርስቶስን እናምናለን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱንና ሰው ሆኖ የሰውን አካል ለብሶ በዚህ ምድር ላይ መመላለሱን እንቀበላለን ቢሉም ከአብና ከወልድ እኩል የሆነውን መለኮታዊ ባህርዩን ግን ይክዳሉ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡1 1ኛ ዮሐ 4፡3
6)   ኢየሱስ ክርስቶስን እናምናለን የሚሉ ብዙ የሃሰት ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በስጋ መሞቱን፣ በሶስተኛው ቀን በስጋ ከሞት መነሳቱን፣ ከአርባ ቀንም በኋላ በአካል ወደ ሰማይ ማረጉንና፣ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ መቀመጡን ይክዳሉ 2ኛ ጢሞቲ 3፡5  2ኛ ጴጥሮስ 2፡1
7)    ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የሰው ልጅ ሁሉ  ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢዓታችን መሞቱን በማመን መሆኑን ይክዳሉ  ገላትያ 5፡4
8)   ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ሞትና ፍርድ ሊያድን የሚችለው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ባይክዱም፣ በተግባር ግን ከእግዚአብሔር አብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ (ከሥላሴ) በተጨማሪ ፍጡራን የሆኑ መላእክትና ቅዱሳንም ሰውን ከኃጢዓትና ከዘለዓለም ፍርድ ያድናሉ ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉ   ቆላስይስ 2፡18-19
9)   ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጻድቃንና በኃጥዓን ላይ ለመፍረድ በክብር፣ በአካል ዳግም ተመልሶ መምጣቱን ይክዳሉ፣ ወይም ያውገረግራሉ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡4
10)  ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ፍቅር ከእግዚአብሔር እውነትና ቅዱስነት በመነጠል፣ “ዋናው እምነትና ፍቅር ነው” ይላሉ። ቀጥለውም ሰው የሚድነው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ፣ በጸጋ ስለሆነ ካመነ በኋላ እንደፈለገው በኃጢዓት መመላለስ ይችላል ብለው ያስተምራሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ግዚአብሔር ሰውን ሁሉ ይወዳል፣ ነገር ግን ኃጢአትንና ዓመጽን ሁሉ ደግሞ ይጠላል። ያ ባይሆንማ ኖሮ ጌታ ኢየሱስ የኃጢዓታችንን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ መሞት ባላስፈለገውም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምን ሰው የኃጢዓት ባሪያ ሆኖ ሊኖር አይችልም። ኃጢዓትን የሚያደርግ የኃጢዓት ባሪያ ነውና። የይሁዳ መልእክት ቁጥር 4  ዕብራውያን 10፡26-31 ዮሐ 8፡34
11)   የሐሰት አስተማሪዎች የሚሰሙአቸውን ሰዎች ስለራሳቸው ትልቅነት፣ እውቀት፣ ልዩ መገለጽ በመንገር ተከታዮቻቸው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ፈንታ በነሱ (በአስተማሪዎቹና በመሪዎቹ) ማንነትና ስራ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋሉ። 2ኛ ቆሮ 4፡5 ዮሐ 3፡30
12)  የሃሰት ትምህርትና አስተማሪዎች ዋነኛው መለኪያ ፍሬያቸው ነው። እንደ እግዚአብሔር ቃል መልካም ፍሬን የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል። ማቴ 7፡15-20
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዳግም መገለጽ እየተቃረበ በሄደ ቁጥር የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች እየበዙና እጅግ እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ጌታ አስተምሮናል። እነዚህ የሃሰት ትምህርቶችና አስተማሪዎቻቸው ቢቻላቸው በጌታ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡት እንኳን ለማሳት ይሞክራሉ። ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ “የራሴን በጎች አውቃለሁ፣ የራሴም በጎች ያውቁኛል” ዮሐ 10፡14-15 እንዳለው፣ በጌታ ወንጌል የተጠሩ፣ የተመረጡና የታመኑ ሁሉ ድል ይነሳሉ። ራዕይ 17፡14
ዛሬ በዙሪያችን እየነጎደ ያለው የሃሰት ትምህርቶች መብዛት፣ የብዙዎች ከወንጌል እውነት በመንሸራተት ከዓለም ዓመጽ ጋር መተባበር ሊያስደነግጠን አይገባም። ሁሉም እንደተጻፈው ይፈጸማል። የእግዚአብሔር ጸጋ በሁለት ምሰሶዎች ላይ ቆሞአል። እነዚህም ምሰሶዎች እውነትና ፍቅር ናቸው። እውነት ያለ ፍቅር ፍርድን ብቻ ያስከትላል። ፍቅር ያለ እውነት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቅዱስነትና የማይደፈር ባህርዩን እርሱም አምላክነቱንና ጌትነቱን ይጻረራል። ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱና በመነሳቱ ሁለቱም የጸጋ ምሰሶዎች፣ እውነትና ፍቅር ጸንተዋል። ክርስቶስ የሁሉ ነገር ማእከል ነው። ያለ እርሱ እውነትም ሆነ ፍቅር ሊኖሩ አይችሉም። የክርስትና እምነትና የዘለዓለም ሕይወት የማይናወጥ መሰረት ክርስቶስ ነው። የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማይ በመጣው በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ቁጭ ብለን ማንበብ፣ መማር፣ ማሰብና ማሰላሰል፣ መጸለይ፣ ሕይወታችን እና ዘመኑን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መመርመር ያስፈልገናል። የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። ትንቢት ወደ ፍጻሜው እየቸኮለ ነው። በክርስቶስ ዳግም የተወለድን ሁሉ ሊሻር የማይችለውን የእግዚአብሔርን ቃል በየእለቱ በልባችን ልንሸሽግና ወደ እውነት ሁሉ በሚመራን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ ያስፈልጋል። የክርስቶስን የወንጌሉን ብርሃን በላያችን ላይ በማብራት መልካምን ስራ በእኛ የጀመረው ጌታ አምላክ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ሊያጸናን የታመነና ጻድቅ ነው። በክርስቶስ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ እያደረግን በክብር ለሚገለጽበት ለዚያ ለታላቁ ቀን የተዘጋጀን እንድንሆን የጸጋ ሁሉ አምላክ ማስተዋልን፣ ትህትናን፣ መንፈሳዊ ረሃብንና ጥማትን እርሱንም መፈለግን በውስጣችን ይሙላ። ለእርሱ ክብር በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


የማይገለጽ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። ማቴዎስ 10፡26 ሉቃስ 8፡17

የማይገለጽ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። ማቴዎስ 10፡26 ሉቃስ 8፡17

የሚከተለውን ማገናኛ (LINK) በመጫን የሚገርም የአርኪዎሎጂ መረጃን የሚያቀርበውን ቪዲዮ ተመልከቱ።


የዓለም ታሪክ፣ አርኪዎሎጂ፣ ፍልስፍና ወዘተ እየተባለ በዓለም ሁሉ ስንማረው የነበረው ነበር ብዙ ውሸቶች የሞሉበትና እውነተኛውን የዓለም ታሪክ የደበቀ መሆኑ እየተጋለጠ ከመጣ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። በትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ 12 በተለይም በቁጥር 4 ላይ እንደተጻፈው የዘመኑ መጨረሻና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ስለተቃረበ፣ ተሰውረው የነበሩ መረጃዎችና ታፍነው የነበሩ እውቀቶች ሁሉ ወደ አደባባይ እየወጡ ናቸው። ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘውን ቪዲዮ ስትመለከቱ የእግዚአብሔር ቃል ምን ያህል የከበረ እውነትንና ታሪኮችን ይዞ እንዳቆየልን ማስተዋል ትችላላችሁ። ቪዲዮው ላይ የሚቀርበው ሪፖርት የአርኪዎሎጂ እና የጥንት ታሪክ ጥናት ውጤት እንጂ የሃይማኖት ስብከት ስላልሆነ አቅራቢዎ የሚናገሩአቸውን ነገሮች ለመረዳት በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበውን እውነተኛውን የጥንት ዘመን ታሪክ መረዳት ያስፈልጋል።
ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 6 በምድር ላይ ኔፊሊም የሚባሉ እንደነበሩ ይነግረናል። ኔፊሊም የሚለው ቃሉ “የወደቁ” የሚል ሲሆን፣ ለነዚያ ፍጥረታት ኔፊሊም የሚለው ስም የተሰጠበት ምክንያትም በዚያው በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1ና 2 ላይ ተገልጾአል። የእግዚአብሔር ልጆች (ብነይ ኤሎሂም) ከሚባሉት ከወደቁት መላእክት አንዳንዱ በልኡል እግዚአብሔር የፍጥረት ስርዓት ላይ በማመጽ ወደ ምድር በመውረድ ከሰው ሴቶች ልጆች ጋር ዘራቸውን በማደባለቃቸው የተወለዱት ከፊል የወደቁ መላእክትና ከፊል የሰው ዘር ያላቸው ፍጥረታት ናቸው ኔፊሊም የተባሉት። እነዚህ ፍጥረታት እንደ አባቶቻቸው ሁሉ እኩያን ስለነበሩ ምድርን በዓመጽ ሞልተዋት ስለነበረ ነው ጌታ አምላክ እጅግ አዝኖና ተቆጥቶ በኖህ ዘመን የነበረውን ዓለም በጥፋት ውኃ ያጠፋው። ለሰው ልጆች የጦር መሳሪያ መስራትን፣ ጽንስን ማስወረድን፣ ያልተፈቀደ ግብረ ስጋ መፈጸምን (እንደ ሰዶማዊነት ያሉ)፣ ጥንቆላን፣ ኮከብ ቆጠራንና ሟርትን ያስተማሩ እነዚያ የኔፊሊም አባቶችና ኔፊሊም እንደነበሩ ሌሎች የታሪክና አዋልድ መጻህፍት ብዙ ማስረጃ ይሰጣሉ። ከነዚህ ከረዓይት ዓመጽና የሰው ልጆችም እነሱን ተከትለው ዘራቸውን፣ የምድር እንስሳትንና እጽዋትንም ዘር ሁሉ በመበከላቸው ነበር ጌታ አምላክ ተቆጥቶ ዓለምን በውኃ ያጠፋው።
ከጥፋት ውኃ በኋላም ደግሞ ኔፊሊም እንደገና በምድር ላይ እንደነበሩ በዚያው በዘፍጥረት 6፡4 ላይ እናነባለን። “በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፣ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው”። ብዙዎቻችን የምናነበው የ1962 ዓም የአማርኛው ትርጉምና ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች እነዚያ ኔፊሊም “በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ” ቢልም፣ ብሉይ ኪዳን በመጀመሪያ የተጻፈበት እብራይስጡ ግን ኔፊሊም ኃያላን የነበሩ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ግዙፍ ወይም ረዓይት (giants) እንደነበሩ ይናገራል። በ2000 ዓም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የተተረጎመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ትርጉምም እነዚያን ኔፊሊም “ረዓይት” ብሎ የእብራይስጡን ሃሳብ በተሻለ መንገድ ተርጉሞታል። በዚሁ ትርጉም ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አዋልድ መጻህፍት፣ በተለይም ደግሞ መጽሐፈ ሄኖክና መጽሐፈ ኩፋሌ ስለ ረዓይትና የተያያዙ ታሪኮች ተጨማሪ መረጃ ይሰጣሉ።
በባቢሎን እንዲሁም በሰዶምና ገሞራ የታየው ዓመጽና የተከተለው የእግዚአብሔር ቁጣ ከጥፋት ውኃ በኋላ እንደገና በምድር ላይ በተባዙት በኔፊሊም የተመራ ነበር። ኔፊሊም በአካል እጅግ ግዙፍ ፍጥረታት ነበሩ።  ቁመታቸው እስከ 30 ጫማና ከዚያም በላይ ይደርስ እንደነበር የሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻህፍት፣ የታሪክና የአርኪዎሎጂ መረጃዎች በምድር ሁሉ አሉ። በሙሴ መሪነት እስራኤል ያሸነፋቸው የሃሴቦን ንጉስ ሴዎንና የባሳን ንጉስ ዓግ የኔፊሊም ዝርያ ያላቸውና እንደ አምላክ ይመለኩ የነበሩ ናቸው። የእስራኤል ህዝብ ከነዓንን ከመውረሱ በፊት እንዲያጠፋቸው ታዝዞ የነበሩት የነዚሁ የኔፊሊም ዝርያ ያላቸው “ህዝቦች” ነበሩ። በእስራኤል ዘመን የነበሩት እንደ አናቃውያን፣ ዘምዙማውያን፣ ኤዊያውያንና ሌሎችም የረዓይት ዝርያዎች ከኔፊሊም የተወለዱ እንደነበሩ ኦሪት ዘሆልቁ ምዕራፍ 13 በተለይም ደግሞ ቁጥር 33 ያስረዳል። ዳዊት የገደለው ጎልያድና ዳዊት ከነገሰም በኋላ የሱ ወታደሮች የገደሉአቸው ሌሎች የጎልያድ ወንድሞችና ዝርያዎችም ከነዚያው ከኔፊሊም ዝርያዎች የቀሩ ነበሩ። በእስራኤል ዘመን የኔፊሊም ዝርያዎች ራፋይም ተብለው ይጠሩም ነበር።
ኔፊሊምና ዝርያዎቻቸው ከፊል የወደቀ መላእክትና ከፊል ሰው ስለነበሩ ከፍተኛ እውቀት ቢኖራቸውም ሃሳባቸውና ስራቸው ሁሉ ግን እኩይ ነበር። ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ስለነበራቸው። የሰውንና የእንስሳትን እንዲሁም የራሳቸውን ዘር በማደባለቅ የጌታ አምላክን ህግ በመጣስ ብዙ የሚያስፈሩና አደገኛ ፍጥረታትን እንዲወለዱ አድርገዋል። በግሪክ፣ በግብጽ፣በባቢሎን፣ በሮምና ሌሎችም የጥንት ሃይማኖቶች ይመለኩ የነበሩት ራሳቸው ኔፊሊምና እነሱ አዳቅለው የፈጠሩአቸው እኩያን ፍጥረታት ነበሩ። ዛሬ በምድር ላይ አለ ከምንለው ቴክኖሎጂ የሚተካከልና በብዙ መንገድም የሚበልጥም ቴክኖሎጂ ስለነበራቸው በምድር ሁሉ እንደ ፒራሚዶች ያሉ ግዙፍ ስራዎችን ሰርተዋል። በተያያዘው ቪዲዮ ላይ እንደምታዩትም የተራቀቀ የህዋ፣ የከዋክብትና የሌሎች ሳይንሳዊ እውቀት ፈጣሪዎች እነሱ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።  የነዚያ የረዓይት (ኔፊሊም) ዓጽሞች እንዳይገኙ እየሰበሰቡ ሲያቃጥሉና ሲደብቁ የኖሩት እንደ ቫቲካንና Smithsonian Institution ያሉ ድርጅቶች እውነቱን ለማፈን ቢጥሩም እነሱ ሊያጠፉአቸው ወይም ሊደብቁአቸው ያልቻሉ ምስጢሮች ዛሬ ወደ አደባባይ እየወጡ ነው።
ዛሬ እንደ አሸን የፈላው ቴክኖሎጂ፣ Genetic Engineering፣ የጾታ ግራ መጋባት፣ የሰዶማዊነትና ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ የተከለከሉ የረከሱ ፍትወተ ስጋ አይነቶች መስፋፋት፣ መንግስታት ከህሊና እና ከመጽሃፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚጻረሩ ህጎችን በሰፊው ማውጣታቸው፣ እየተጋነነ የመጣው የ3ኛው የዓለም ጦርነት ወሬ፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት መብዛት ወዘተ ያ የኖህ ዘመን የነበረው ሁኔታ እንደገና እየተከሰተ እንዳለ ያሳያል። ለዚህም ምክንያቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት መቃረቡ ነው። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት፣ ከፖለቲካው ጫጫታ በተጨማሪ በአሜሪካ ኮንግረስ፣ በNASA እና በመገናኛ ብዙኃንና በኢንተርኔት ብዙ ሲነገር የምንሰማው ስለ ALIENS እና Extra Terrestrials ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት እነሲያ በኖህ ዘመን፣ በባቢሎንና በከነዓን የነበሩት የኔፊሊምና የራፋይም ዘሮች እንደገና ወደምድር ግልብጥ ብለው የሚወጡበት ጊዜ ስለተቃረበ ነው። ነገር ግን፣ በመገናኛ ብዙኃን ወይም አዋቂ በሚባሉ ሰዎች እንደሚነገረን እነዚህ ፍጥረታት በሌላ ጋላክሲዎች፣ ዓለማትና ፕላኔቶችና ዓለማት የሚኖሩ “የሰለጠኑ” ALIENS ወይም  EXTRA Terrestrial ሳይሆኑ ከሌሎች ከመንፈስ ወደ አካል ከአካል ወደ መንፈስ የሚቀያየሩ የኔፊሊም ዘሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን ይህ እንደሚሆን በግልጽ ነግሮናል። በክብር ዳግም ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ስለሚሆነው ታላቁ የመከራ ጊዜ ሲናገር ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ብሎአል፡ “ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን (በዓለም ላይ ሊገለጽ ያለውን ነገር) ከመጠበቅ የተነሳ ይደክማሉ፣” ሉቃስ 21፡26 የእነዚያ የኔፊሊም ዘሮች በምድር ላይ ዛሬ በስውር ከብዙ መንግስታት ጋር እየሰሩ እንዳሉ የሚያስረዱ መረጃዎች አሉ።
የመልእክቴ ዋነኛ ሃሳብ አንድ ነው። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምንና ህይወቱን ለእግዚአብሔር ላስገዛ ሰው፣ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር ነውና መፍራት አያስፈልግም። ነገር ግን ከጌታ ከአምላካችን ጋር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መታረቃችንን እናረጋግጥ። ህይወታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያሳይ መሆኑን እንመርምር። በጌታ ያላመንን ከሆንን ደግሞ የንስሃ ቀን ዛሬ ነው። ነገ አይደለም።
ከላይ ሰለ ተነሳው ርእስና ሌሎችም የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ሰፋ ያሉ ትምህርቶችንና መረጃዎችን ከመለከት ድምጽ መጽሔትና ከመለከት ድምጽ ብሎግ ማግኘት ይቻላል። መጽሔቱንና ሌሎች መልእክቶችን ከሚከተለው ድረ ገጽ ማግኘት ይቻላል;;
http://voice-of-trumpet-amharic@blogspot.ca
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ የሚመጣበት ዘመን እጅግ ቅርብ ነው። ማራናታ !! አሜን ጌታችን ሆይ ቶ ሎ ና !

ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ። 

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...