የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 9 ዛሬ ወጥቶአል


ምላስ መብልን እንደሚቀምስ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን? ኢዮብ 12፡11

ላለፉት 18 ወራት ከምእራቡ ዓለም፣ በተለይም ከአሜሪካ፣ የሚመነጩትን ዜናዎች የሚያዳምጥ ሰው “የውሸት ዜና” ወይም “Fake News” የሚለውን ስም ሳይሰማ አይቀርም። እነዚህ “የውሸት ዜናዎች” የሚፈጠሩትና የሚሰራጩት ደግሞ ታላላቅ በሚባሉትና ብዙ ቢሊዮን ዶላር ገቢና ወጭ ባላቸው እጅግ ብዙ ህዝብ በሚያዳምጣቸው እንደ CNN, ABC, CNBC እና MSNBC ያሉ የዜና አውታሮች ነው። “የውሸት ዜናዎች” ተብለው የሚሰራጩት ዜናዎች ደግሞ ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉትን የአሜሪካውን መሪ በማይወዱ፣ እንዳይመረጡ ሲጥሩ በነበሩ፣ ዛሬም የሰውየውን በስልጣን ላይ መቀመጥ ስለሚጠሉ በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ ከቦታቸው ለማውረድ ቆርጠው በተነሱ ከመገናኛ ብዙኃን በስተጀርባ ባሉ ታላላቅና ባለጸጋ ሰዎች ነው።
ይህን መረጃ እዚህ ጋ ያቀረብኩበት ምክንያት ስለ አሜሪካ የፖለቲካ ሁኔታ መረጃ ለመስጠት ሳይሆን “የውሸት ዜና” የሚባለውን ሃሳብ ስመለከት፣ ጽንሰ ሃሳቡ አዲስ እንዳልሆነና መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ በእግዚአብሔር ስም ስለሚሰራጩ የሃሰት ትንቢቶች፣ ትምህርቶችና ምክር መስለው ስለሚሰራጩ ክፉና አጥፊ የሃሰት መረጃዎች መናገሩን ሳስተውል ነው። በኤድን ገነት ለሔዋን በእባቡ የቀረበላት ድንቅ የሚመስል ዜና የውሸት ዜና ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታዲያ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በነቢያቱ፣ በሐዋርያትና በሌሎችም ቅዱሳን ሰዎች ከሚገልጸው እውነት ጋር የሚመሳሰሉ ሃሳቦችን፣ትንቢቶችን እና ትምህርቶችን  ጠላት ዲያብሎስ በየጊዜው በሰዎች መካከል ያሰራጫል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃሰት ነቢያት ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ደግሞ እንዲሁ ከሃዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ የሃሰት አስተማሪዎችና የስህተት ትምህርቶች እንደተሰራጩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እግዚአብሔር ዘመናትን በሙሉ በቅድሚያ ስለሚያውቅ፣ ያለፉትንና ያሉትን የሃሰት ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚከሰቱትን አስቀድሞ አይቶ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ህዝቡ ከነዚያ ትምህርቶች እንዲጠነቀቁ እውነቱን በብሉይና በሃዲስ ኪዳን መጻህፍት አስቀምጦልናል።

ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈሳዊ የሚመስሉ የሃሰት ትምህርቶችን ከእውነቱ መለየት የምንችለው በመጀመሪያ እውነቱን ሁሉ የሚያስተምረንን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ስናውቅ ነው። እውነቱን ጠንቅቀን ካላወቅንና እምነታችን በአለቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መመስረቱን ካላረጋገጥን በየጊዜው በሚነሱ የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች መወሰዳችን የግድ ነው። የስንዴን ዘር ወይም ተክል አይቶ የማያውቅ ሰው ስንዴውን ከእንክርዳዱ ሊለይ አይችልም። የእውነት መለኪያው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ አንድን ትምህርት ወይም አስተማሪ የሚከተሉት ሰዎች ብዛትና የሃሳቡ ዘመናዊ ወይም መንፈሳዊ መምሰል አይደለም። እውነት፣ መንገድና ህይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስንዴውን ከእንክርዳዱ እንዴት ልንለይ እንደምንችል፣ በተለይም ደግሞ በዚህ ዘመን በሰፊው እየተናፈሰ ያለውን “የብልጽግና ወንጌል” የሚባለውን ትምህርት ከእውነተኛው ወንጌል መለየት እንድንችል የሚረዱንን አንዳንድ ሃሳቦችን የያዘችው የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 9 ዛሬ ወጥታለች። ባለፉት ብዙ ወራት ጥቂት ሲቀርብ የቆየው የዶ/ር ዘመድኩን ተሻለ የህይወት ምስክርነት ክፍል ስድስትም በዚሁ እትም ቀርቦአል። የመጽሔቱን PDF ቅጂ በነጻ በመቅዳት (ዳውንሎድ በማድረግ) እንድታነቡና ለሌሎችም እንድታካፍሉ በትህትና እጋብዛችኋለሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...