ዓለም በብዙ አቅጣጫዎች 3ኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስነሳ በሚችል ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች

ዓለም በብዙ አቅጣጫዎች 3ኛውን የዓለም ጦርነት ሊያስነሳ በሚችል ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች
http://endtimeheadlines.org/2017/07/rumors-war-u-s-inches-war-north-korea-millions-die/

ባለፉት ወራት ደጋግሜ እንደጻፍሁትና ከታች ከተያያዘው ሪፖርት እንደምትረዱት፣ ልንረዳው በማንችለው ፍጥነት ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ፍጅትን ሊፈጥር ወደሚችል ወደ ከፍተኛ ጦርነት እየተፋጠነች ነው። ብዙ ለመረጃዎች ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይህ ጦርነት የ3ኛው የዓለም ጦርነትና የኑክሊየር መሳሪያዎችም ስራ ላይ የሚውሉበት ሊሆን ይችላል እያሉ ያስጠነቅቃሉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ የኤኮኖሚ እቀባን አሜሪካ በሩሲያ ላይ ጥላለች። የአሜሪካው ምክር ቤት የገዛ የራሳቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት እንኳን እቀባውን እንዳስፈላጊነቱ በማስተካከል ከሩሲያ ጋር በንግግር በሚደረግ መግባባት እንዳይደርሱ እጅ እግራቸውን የሚያስር እቀባን ያሳለፉት 419 ለ3 እና 98 ለ 2 በሆነ ድምጽ ነው። ፕሬዝዳንቱም የምክር ቤቱን ውሳኔ ህግ እንዲሆን የፈረሙት ምንም ምርጫ ስለሌላቸው እንጂ እንደማይስባሙበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በአደባባይ ተናግረዋል። ታሪክን የሚያስታውስ ካለ፣ ጃፓን የአሜሪካ ግዛት የሆነውን ፐርል ሃርበርን በቦምብ የደበደበችው አላላውስ የሚል የኤኮኖሚ እቀባ በአሜሪካ ስለተደረገባት ነበርና፣ የአሁኑ የአሜሪካ ግፊትም ሩሲያ ሳትወድ ተገፍታ ወደ ጦርነት እንድትገባ ለማድረግ ነው የሚሉት የራሷ የአሜሪካ የቀድሞ ጀነራሎችና ታሪክ ታዛቢዎች ናቸው። ሩሲያም ይህን ለመበቀል ከ750 በላይ የሆኑ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ አባርራለች፣ ዲፕሎማቶቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የመዝናኛ እና የእቃ ማከማቻ ቤቶችንም ነጥቃለች።  ፍጻሜ  ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሰራዊት በብዙ የዓለም ክልሎች ግንባር ለግንባር ተፋጥጠው ለጦርነት ከፍተኛ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ አሜሪካ አዲስና እስካሁን ካሏት ሁሉ ትልቅ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን ሰርታ አሰማርታለች። ከ 3 ቀናት በፊት ቻይና የጦር ሰራዊቷ የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት በምታከብርበት ጊዜ እስከ ዛሬ ወደ አደባባይ ወጥተው ያልታዩ አስፈሪ የጦር መሳሪያዎችን አሳይታለች። ሩሲያም ዓመታዊ የባህር ኃይሏ በሚከበርበት ቀን ከ 100 በላይ የጦር መርከቦችን በማሰለፍ ኃይሏን አሳይታለች። የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩት በቦልቲክ ሪፑብሊኮችና በጆርጂያ አሜሪካና አጋሮቿ የጦር ልምምድ ሲያደርጉ ከርመዋል። በፋርሱ ባህረ ሰላጤ የአሜሪካና የኢራን የባህር ኃይሎች ከመገላመጥ አልፈው በአንድ ሳምንት ጊዜ ያህል ብቻ የአሜሪካ ጦር የኢራንን ጀልባዎች ለማስፈራራትና ለማስጠንቀቅ እንደተኮሱ ተዘግቦአል። ልብ ብሎ ለሚያዳምጠው የሚያስፈራ የጦርነት ነጋሪት በምድር እየተደለቀ ነው። ይህ እየተፈራ ያለው ጦርነት በእርግጥ ከተነሳ 3ኛው የዓለም ጦርነት እንደሚሆንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያልቁ ብዙ አዋቂዎች ያስጠነቅቃሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም የመምጫው ዘመን ሲቃረብ በምድር ላይ ጦርነትና የጦርነት ወሬ እጅግ እንደሚበዛ ተናግሮአል። ታዲያ ምን እናድርግ? ሊሆን ያለው ሁሉ ይሆናል። በተቻለን መጠን መረጃዎችን ማግኘታችንና በግላችንና ለቤተሰባችን እንዲሁም ለህብረተሰባችን ልናደርገው የምንችለው ዝግጅት ካለ በጊዜው ማድረጉ መልካም ነው። በክርስቶስ የምናምን ክርስቲያኖች ሁሉ ለሰላም እንጸልይ። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን ያልተቀበልን ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ የነፍሳችንን የዘለዓለም ኢንሹራንስ ማግኘቱ አንገብጋቢ ነው። ያ ኢንሹራንስ ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ነው። ለደህንነታችን የሚከፈለውን ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከፍሎልናል። ዛሬም ኑ እያለ የሰውን ልጆች ሁሉ ወደ ደህንነት ይጋብዛል። ጥሪውን ሳንመልስና ዛሬ ነገ ስንል ጊዜ አይለፍብን። ማንም አያታልለን። ይህችን ህይወት ጨርሰን ከዚህ ዓለም ከሄድን በኋላ ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም። የእግዚአብሔር ሰላም ይብዛላችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ። 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...