ከእግዚአብሔር የተላከ ምልክት አይዋሽም

ከአስራ ሁለት ቀናት በፊት “ሰማያት እየተናገሩ ናቸው” በሚል ርዕስ ሥር በኦገስት 21 በአሜሪካና በካናዳ ላይ ስለሚከሰተው ታላቅ የጸሃይ ግርዶሽ የሚናገር ዜናን በማያያዝ መልእክት አስተላልፌ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስና ታሪክ እንደሚነግረን የጸሃይና የጨረቃ ግርዶሾች እግዚአብሔር አምላከ ለህዝቦችና ለመንግስታት ሊመጣ ስለሚችል ጥፋት ከሚናገርባቸው፣ ህዝቡን ወደ ንስሃ ከሚጠራባቸውና ማስጠንቀቂያ ከሚሰጥባቸው መንገዶች አንዱ ናቸው። ባለፈው መልእክቴ ውስጥ ከአሜሪካውያን ክርስቲያኖች ወገኖቻችን ጋር በመንፈስ አንድ በመሆን ምድሪቱም ከዓመጻዋ ንስሃ እንድትገባና ወደ እግዚአብሔር እንድትመለስ እንድንጸልይ አሳስቤ ነበር።
ባለፉት ብዙ ቀናት በዜና አውታሮች እንደሰማችሁትና ከዚህ መልእክት ጋር በተያያዘው አንድ ዜና ላይ እንደምታነቡት፣ የጸሃይ ግርዶሹ ከዋለ ከአራት ቀናት በኋላ ጀምሮ ሃርቪ የተባለው ታላቅና ታሪካዊ ወጀብ ቴክሳስ ወደ ሚባለው የአሜሪካ ግዛት ገብቶ በአሜሪካ ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ዶፍ  ለአምስት ቀናት ያህል በተከታታይ በማውረድ ከፍተኛ ጥፋት እየፈጠረ ይገኛል። http://endtimeheadlines.org/2017/08/harvey-costliest-natural-disaster-u-s-history-160-billion/
ብዙ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ቤተሰቦች ተበታትነዋል ብዙዎች ቤታቸውን ትተው ተሰደዋል፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ደግሞ ከላይ፣ ከታች፣ ከፊትና ከኋላ በከፍተኛ ጎርፍና ውሃ ሙላት ተከበዋል። የሞተው፣ የቆሰለውና የት እንዳለ የማይታወቀው ሰው ቁጥር ገና በቅል አይታወቅም። ከዚህ መልእክት ጋር በተያያዘው ሪፖርት ላይ እንደምናነበው፣ ይህ ወጀብ የፈጠረው ታላቅ ውድመት ከዚህ በፊት በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል። በንብረትና በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ላይ ይህ ወጀብ ያደረሰው ውድመት በ2005 እና በ2012 ተፈጥረው የነበሩት ካትሪና እና ሳንዲ የተባሉት ሁለት ታላላቅ ወጀቦች በድምር ከፈጠሩት ውድመት እንደሚበልጥና የአሜሪካንንም የዓመት ኢኮኖሚ (GDP) በ ነጥብ ስምንት ከመቶ እንደሚጎዳው ተዘግቦአል።
ወጀብ፣ ማእበል፣ ድርቅ፣ የአየር ንብረት መዛባትና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች በየጊዜው የሚከሰቱ ናቸው ቢሉንም፣ ሁሉም ነገር የሚሆነው በአጋጣሚ ብቻ ነው የሚለው ድምዳሜ ግን እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሰዎች በቀላሉ የሚቀበሉት አይደለም። ከላይ የተጠቀሰውን ታላቅ ወጀብ ስናስብ እጅግ የሚያስገርመው ደግሞ ከዚያው ከቴክሳስ ግዛት ብዙም ሳይርቅ የሚገኘው የደቡባዊ ካሊፎርኒያ ግዛት በበኩሉ እንደ እሳት በሚያቃጥል ሙቀትና በከፍተኛ ድርቅ እየተመታ መሆኑ ነው። ሊሰማ ለሚወድ ሁሉ ጥፋት ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ደግሞና ደጋግሞ ይናገራል። በተለይም ደግሞ በከተማዎችና በአገር ላይ የሚመጣ ጥፋት እንዲሁ በአጋጣሚ የሚሆን አይደለም። ትንቢተ አሞጽ ምዕ 3 ቁ 6፣ መዝሙረ ዳዊት ምዕ 127 ቁ 1-2። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ በመጣ ቁጥርም ማእበሉና ወጀቡ ይበረታል፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ ጦርነትና ሁከት በምድር ሁሉ እየበዛ እንደሚሄድ በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24፣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 21፣ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 13 እና በሌሎችም ስፍራዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።  የኖህ ዘመንን ዝናብ በሚመስል ታሪካዊ ዝናብ ስፋቱ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ የበረሃማውን የቴክሳስን ግዛት በማጥለቅለቅና ከአሜሪካ ታላላቅ ከተሞች በአራተኛነት ደረጃ ላይ ያለችውን የሂውስተንን ከተማ ያንበረከከው ሃሪኬን ሃርቪ የፈጠረውን ጉዳት ስናስብ፣ ይህ አደጋ ከመፈጠሩ ከራት ቀናት በፊት የነበረውን የሰማያትን ማስጠንቀቂያ እናስታውስ። በዚያን ቀን ብዙ ሰዎች ግርዶሹን እንደ ማስጠንቀቂያ ከመውሰድ ይልቅ፣ ድግሶችን በማዘጋጀት አሸሸ ገዳሚ ይሉ እንደነበር በሰፊው ተዘግቧል። እኛም ለየራሳችን ከተማዎች፣ ለወገኖቻችን፣ ለያለንባቸው አገሮችም እንጸልይ። በስሙ የተጠራን ህዝቡ በፊቱ ወድቀን ንስሃ ብንገባና ከኃጢዓታችንም ሁሉ ብንመለስ እግዚአብሔር በደላቸንን ሁሉ  ይቅር እንደሚልና ያለንባቸውን ከተማዎች፣ መንደሮች፣ ማህበረሰቦችና አገሮች እንደሚፈውስ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። 2ኛ ዜና 7፡14 ሰማያትም፣ የምድር ኃይላትም እየተናገሩ ናቸው። የሚሰማ ጆሮንና የሚመለስ ልብን እግዚአብሔር ለሁላችንም ይስጠን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...