የሰው ዘር ዛሬ እንኳን ያልደረሰበት የሂሳብ እውቀት ከዛሬ 3700 ዓመታት በፊት በምድር እንደነበረ ማስረጃ ቀረበ

የሰው ዘር ዛሬ እንኳን ያልደረሰበት የሂሳብ እውቀት ከዛሬ 3700 ዓመታት በፊት በምድር ላይ እንደነበረ ማስረጃ ቀረበ
ከ 17ኛውና 18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በየትምህርት ቤቱና በየዩኒቨርሲቲው በሚሰጡት ትምህርቶች ውስጥ ቀስ በቀስ ስር በመስደድ የገቡት፣ በሳይንስና በእድገት ስም የአጋንንትን ትምህርት የሚያራምዱ እውቀቶች ዛሬ የሰው ልጅ ያለበት መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባው ምስቅልቅል ውስጥ ከትተውታል። ዘለዓለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረውን የፍጥረትን ታሪክ ለመሻር የተነሱት እነዚህ ትምህርቶች የጥንቱ ሰው ኋላ ቀር፣ ያልተማረ፣ ውስብስብ የሆኑ ሳይንሳዊና የቴክኖሎጂ ነገሮች የማይገቡት እንደነበረ ሲያስተምሩ ምንም እፍረት አይሰማቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት፣ እውነተኛውን የዓለም ታሪክና በየጊዜውም እያመለጡ የሚወጡትን የአርኪዎሎጂ ምርምር መረጃዎችን ቀረብ ብለን ከተከታተልን ግን፣ ዛሬ ብዙ ምሁራን እና የሰለጠንን ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሚናናፍሱት የዘገምታ ለውጥ (ወይም ኢቮሉሽን) የሚባለው በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠ የአጋንንት ትምህርት መሆኑን እንረዳለን።
የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅም የተከደነ የለም ተብሎ እንደተጻፈው እውነት ሁሉ በጊዜው በአደባባይ ይገለጻል። ከዚህ አጭር መልእክት ጋር ተያይዞ የሚገኘው ጽሁፍ እንደሚያሳየው፣ የተራቀቀ የሂሳብ እውቀት የመነጨው እስከ ዛሬ ድረስ ሲነገረን እንደኖረው ከግሪኮች፣ ከሮማውያን ወይም ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከጃፓን ወይም ከቻይናም አይደለም። 3700 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ከጥንቱ የባቢሎን ግዛት የተገኙ የሸክላ ሰሌዳዎች እንደሚያመለክቱት በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ውስብስብ የሆኑ የህንጻ ቅየሳና፣ የህዋ ምርምርን እንዲሁም ሌሎች ውስብስብ የሂሳብ ስሌቶችን በማድረግ የሚሰሩ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችላቸው እውቀት ነበራቸው የሚለው ሃሳብ በማስረጃ እየተደገፈ መጥቷል። ታዲያ ይህን ያህል የተራቀቀ እውቀት በዚያ ከጥፋት ውሃ በፊት በነበረው ዘመን ጀምሮ ከነበረ፣ እውቀቱ በምድር ሁሉ ያልተሰራጨውና አብዛኛው የምድር ህዝብ በኋላ ቀርነት ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የቆየው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ መነሳቱ የግድ ነው።
የአርኪዎሎጂ ምርምሩን የሚያካሂዱት ምሁራን ራሳቸው እንደሚያመለክቱት ደግሞ እነዚያ የጥንት ሰዎች ይህን የመሰለ የተራቀቀ የሂሳብ እውቀትን ቤተ ጣዖቶቻቸውንና ቤተ መንግስቶቻቸውን ለመስራት ይጠቀሙበት ነበር። ማለትም በዚያም ዘመን ቢሆን ብዙ ህዝቦች እውነተኛውን አምላክ ክደው ባእድ አማልክትን ያመልኩ ነበር። እነዚያ ባእድ አማልክት የግብጾቹ አይሲስና ኦሳይሪስ፣ የባቢሎኖቹ ማርዱክ፣ በአል፣ ቤል፣ አስታሮት፣ የግሪኮችና የሮማውያኑ አፖሎ፣ ሄርኩለስ፣ ዙስ፣ ዳያና፣ አርጤምስ፣ ቪነስ ወዘተ እነማን ነበሩ? ጠለቅ ያለ ጥናትን ለማድረግና ለዚያም የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ለማድረግ ዝግጁ ከሆንን፣ የጥንት ህዝቦችም ሆኑ ዛሬ በምድር ሁሉ ያሉ ባእድ አማልክት የሚያመልኩ ህዝቦች የሚሰግዱት ለድንጋይና ለእንጨት ወይም ለብረት ሃውልቶች ሳይሆን በነዚያ ሃውልቶች የተመሰሉትን በኖህ ዘመን በጥፋት ውሃ የጠፉትን ረዓይት መንፈሶች (አጋንንትን) መሆኑን ልንረዳ እንችላለን። ዛሬ በሃውልትና በተለያዩ ቁሳቁስ የሚመሰሉት አጋንንት በግሪክ፣ በሮም፣ በባቢሎን፣ በፋርስ በግብጽና ሌሎችም የጥንት ግዛቶች ሲመለኩ የነበሩት እነዚያ “በጥንቱ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን” ናቸው የሚለው ሃሳብ ዛሬ በብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ መረጃዎች እየተደገፈ የመጣ ሃሳብ ነው። ይህን ዓይነት ምርምርና እውቀት ለክርስትና ህይወታችን ምን ያደርግልናል ብለን ከጠየቅን ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚናገረው ነገር አለ ወይ ብለን መመርመሩ አስፈላጊ ነው።
ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 6፣ 7 እና 8 ስለ ኖህ ዘመንና ስለ ጥፋት ውኃ የሚያስተምረንን ረጋ ብለንና በቅርብ ካጤንነው የእግዚአብሔር ልጆች (BNAI ELOHIM) የሚባሉ የሰውን ሴቶች ልጆች በወሰዱና ልጆች በወለዱላቸው ጊዜ ኔፊሊም የሚባሉ እንደተወለዱ እንመለከታለን። እነዚያ ኔፊሊም ደግሞ በዘመኑ የታወቁ ኃያላን ነበሩ። መሰረታዊው የእብራይስጡ ትርጉም ኃያላን የሚለውን ቃል “ሃጊቦሪም” ይለዋል። ይህ ቃል ደግሞ መታወቅን፣ ወኔንና ጀግናነትን ብቻ ሳይሆን እነዚያ ፍጥረታት በአካልም ከሰዎች የተለዩ ግዙፍና ጉልበተኞች እንደነበሩም ይጠቁማል። በጣም የሚያስገርመው ነገር ደግሞ፣ ልክ እነዚህ ኔፊሊም በምድር ላይ መብዛት ሲጀምሩ ነበር የሰው ልጆች ደግሞ መንገዳቸውን በምድር ላይ ያበላሹትና የእግዚአብሔርን ታላቅ ቁጣ ያነሳሱት። እውቀት በመብዛቱ ክፋትና ዓመጽ ለምን በዛ? የእውቀት መብዛት ለዓመጽ መነሳሳትና መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጎ ነበር ወይስ ሁለቱም በአጋጣሚ ነው የተከሰቱት? እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚሰጠው እውቀትና ጥበብ ሁሉ ሰውን ወደ ጽድቅ፣ ወደ ፍቅርና ወደ እውነት እንዲሁም ወደ ዘላለም ህይወት ብቻ የሚመራ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። ስለዚህ የኖህን ዘመን ህዝብ ያጠፋው እውቀትና ስልጣኔ መሰል ስህተት ምንጩ እግዚአብሔር ሳይሆን በኤደን ገነት የመጀመሪያውን ውሸት ለሰው ልጅ ያስተማረው እባቡ ነው።
ከዚሁ ሃሳብ ጋር ተያይዞ ልብ ልንለው የሚገባ ነገርም አለ። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ በአስገራሚ ፍጥነት ከፍተኛ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ ገብቶአል። ነገር ግን በዚሁ እጅግ ሰለጠንን በምንልበት ዘመን ደግሞ የሰው ዘር በከፍተኛ ሞራላዊ ውድቀት ውስጥ ተዘፍቆአል፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እጅግ ስር ሰድዶአል። ፈሪሃ እግዚአብሔር መሬት ላይ ተጥሎአል። ወንዶች በወንዶች፣ ሴቶች በሴቶች ጋር ነውር ማድረግ እንደ ቀላል በሚቆጠርበት በዚህ ዘመን፣ ሰው ወንድ ይሁን ወይም ሴት እንኳን ለመለየት እጅብ ብዙዎች ግራ ተጋብተው ይገኛሉ። ገና ተጫውተው ያልጨረሱ ህጻናት ትልልቅ ነን በሚሉ ሰዎች እየተደፈሩ ህይዋተቸው የምድር ሲኦል እየሆነ ነው። እንደ ኖህ ዘመን እውቀትና ስልጣኔ በዝቶአል በሚባልበት ዘመን የመንፈሳዊና ሞራላዊ ውድቀት በሰው ልጅ ላይ የበዛው በአጋጣሚ ይሆን?!  ብዙ ምርምሮችና መረጃዎች ይህ በአጋጣሚ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ምናልባት እነዚያ በኖህ ዘመንና ከዚያም በኋላ በምድር ላይ ነበሩ የተባሉት ኔፊሊም ዛሬም እንደገና በስውር በምድር ላይ እየሰሩ ይሆን?!! በማርች 2017 የወጣው የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 5 (አምስት) በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ ሃሳቦችንና መረጃዎችን ይሰጣል። መጽሔቱን ከሚከተለው የመለከት ድምጽ ብሎግ አድራሻ ላይ ማግኘት ይቻላል።  http://voice-of-trumpet-amharic.blogspot.ca ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።



ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...