ሰማያት እየተናገሩ ናቸው!!
በፊታችን ሰኞ ኦገስት 21፣ ከ99 ዓመታት በኋላ አሜሪካን ከምእራብ እስከ ምስራቅ የሚያቋርጥ ሙሉ የጸሃይ ግርዶሽ ይሆናል። ይህ ምልክት ምናልባት በአሜሪካ ወይም በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ስላለ የትልቅ
ጥፋት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ይሆን ???
NASA ከሚባለው የአሜሪካ
የህዋ ምርምር ድርጅት በድረ ገጹና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው፣ ሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓም በሰሜን ምእራብ ከምትገኘው
ከኦሪጎን ክፍለ ሃገር እስከ ቻርልስተን ደቡብ ካሮላይና ድረስ ጸሃይ በቀን እንደምትጨልም ተገልጿል። ጸሃይ ፈጽማ በምትጨልምበት
መስመር ላይ ያሉ ብዙ ወረዳዎችና ከተማዎች ከ2 እስከ 3 ደቂቃዎች ለሚያህል ጊዜ ቀኑ ፈጽሞ እንደሚጨልምና ሌሎቹ የአሜሪካ ክፍሎችም
ደግሞ ከዚያ ላጠረ ሰዓትም ቢሆን ግርዶሹን እንደሚያዩ ይኸው የNASA መረጃ ያመለክታል።
የጸሃይና የጨረቃን ግርዶሽ
እንዲሁም ሌሎችን በሰማይ ከዋክብትና ፕላኔቶች አልፎ አልፎ የሚታዩ ምልክቶችን፣ በሰው ዘርና በዓለም መንግስታት ታሪክ የታዩ ትልልቅ
ክስተቶችን እና መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ ክስተቶች የሚናገረውን በቅርብ የሚያጠኑ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ታሪክ ጸሃፊዎች በፊታችን
ሰኞ እንደሚታየው አይነት የጸሃይ ግርዶሽ ዓይነት በዚሁ በኦገስት 21 ቀን 1914 ዓም በምስራቅ አውሮፓ ታይቶ እንደነበር ያስታውሱና፣
ያ ግርዶሽም በአውሮፓ በጥቂት አገሮች ጠብ ተጀምሮ የነበረው ጦርነት የአንደኛውን የዓለም ጦርነት መነሳት ያመለከተ እንደነበር ያስረዳሉ።
በጥቂት አገሮች መካከል በተነሳ ጠብ ከ2 ወር በፊት ተነስቶ የነበረው ግጭት ብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ወደ ጨረሰና ታላላቅ የዓለም
መንግስታትና ግዛቶችን ወዳፈራረሰው የዓለም ጦርነት መለወጡ በታሪክ የተዘገበ ነው። የአሜሪካን ግዛት ሁሉ የሚያቋርጥ ሙሉ የጸሃይ
ግርዶሽ ለመጨረሻ ጊዜ ታይቶ የነበረው በ June 8, 1918 ነበር። ጊዜው አንደኛው የዓለም ጦርነት እያበቃ የነበረበት ቢሆንም፣
ከዚያው በመቀጠል ግን በአሜሪካ ብቻ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺ ሰዎችን የገደለና በዓለም በሙሉ ደግሞ ከ ሃምሳ እስከ አንድ መቶ
ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን የፈጀ የወረርሽኝ በሽታ ተከስቶ እንደነበር ታሪክ ይዘግባል። ባለፉት ጥቂት ወራት በአሜሪካና በሰሜን
ኮሪያ መካከል ያለውን ከፍተኛ ውጥረትና የኑክሊየር ጦርነት አደጋ የሚከታተሉ ደግሞ ይህ ሰኞ ኦገስት 21 በአሜሪካ ላይ የሚከሰተው
ግርዶሽ የመጀመሪያው የኮሪያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በ May 9, 1948 በሰሜንና በደቡብ ኮሪያ መካከል አቋርጦ የሄደውን የጸሃይ ግርዶሽ ያስታውሳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር
ጸሐይን ጨረቃና ከዋክብትን የፈጠራቸው ብርሃንን እንዲሰጡ፣ ለቀንና ለወቅቶች፣ ለወራትና ለዓመታት መቁጠሪያ እንዲያገለግሉ ብቻ ሳይሆን
ለምልክት መስጫም እንደሆነ ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 1 ቁጥር 14 እስከ 19 ያስረዳል። አዳም ለእንስሳት ሁሉ ስምን እንደ ሰጠ
የሰማይ ብርሃናትን ሁሉ ስም የሰጣቸውና ስራቸውንም የመደበላቸው እግዚአብሔር ራሱ ነው። መዝሙር 147፡4 ኢዮብ 38፡31-33። ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ክፍሎችም እግዚአብሔር በየዘመናቱ
እነዚህን የሰማይ ብርሃናትን በመጠቀም ለሰው ልጆች መልእክቶችን፣ ምልክቶችንና ማስጠንቀቂያዎችን እንደ ሰጠ ይመሰክራሉ። ለምሳሌ
ያህል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የምስራቅ ጠቢባን (ሰብአ ሰገል) ያወቁት በሰማያት ላይ የተገለጠውን ምልክት በመረዳታቸው
ነው። በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ጸሃይ እንደ ጨለመች ሉቃስ 23፡44-49 ማርቆስ 15፡33 እና ማቴዎስ
27፡45 ይመሰክራሉ። ከዚያ ቀደም ሲልም ነቢዩ ዮናስ ለነነዌ የንስሃን መልእክት ከመስበኩ ቀደም ብሎ በነነዌ ከተማ ላይ ያለፈ
የጸሃይ ግርዶሽ ተከስቶ እንደነበር በNASA ድረ ገጽ የተደገፈ መረጃን ከብዙ ምንጮች ማየት ይቻላል። የ ቡር ሳጋል ግርዶሽ
(Bur
Sagale) ተብሎ የሚጠራው ያ የጸሃይ ግርዶሽ በ June 15, 763 ዓመተ
ዓለም ተከስቶ እንደነበር የጥንት ታሪክ መረጃዎችና NASA ያከማቻቸው ያለፉት አምስት ሺ አመታት የጸሃይና ጨረቃ ግርዶሽ መረጃ
ያሳያሉ። ሌሎች ታላላቅ ጥፋቶች በምድር ላይ ከመከሰታቸው ቀድሞ በጸሃይና
በጨረቃ ግርዶሽ እንዲሁም በከዋክብት በሚሰጡ ምልክቶች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አስቀድሞ የንስሃ ጥሪና ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም
መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዳግም ምጽዓቱ መቃረቡን ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ በጸሃይ፣ በጨረቃና በከዋክብትም
የሚታዩ ታላላቅ ምልክቶች እንደሚሆኑ ተናግሮአል። ሉቃስ 21፡25-28
በአሜሪካ ላይ የሚከሰተው
የዘንድሮው (ኦገስት 21 ሰኞ) የጸሃይ ግርዶሽ የብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎችን ሃሳብ የሳበውና ያስፈራው ደግሞ ግርዶሹ የሚከሰተው
አይሁድ በየዓመቱ ለ 40 ቀን የንስሃ ጊዜን ከሚጀምሩበት የኤሉል ወር መጀመሪያ አንድ ቀን ቀድሞ መሆኑ ነው። ከብሉይ ኪዳንና ከእስራኤል
ታሪክ እንደምንረዳው ሰኞ ኦገስት 21 በአይሁድ (የጥንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን አቆጣጠር) ኦቭ 30 ነው። ከማክሰኞ ኤሉል 1 ጀምሮ
እስከ ማስተሰረያ ቀን (ቲሽሪ 10) ድረስ አይሁድ ሁሉ ንስሃ የሚገቡበት ቀን ነው። ይህ አርባ ቀን ሲያልቅም በሰማያት ላይ ሌላ
አስገራሚ ምልክት እንደሚታይ NASA ገልጾአል። ስለዚያ ምልክት ደግሞ በሚቀጥለው መልእክቴ እገልጻለሁ። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች
ከጥንት ጀምሮ በብዙ መንገድ በቀጥታ በተገለጸ ቃሉ፣ በህሊና፣ በተፈጥሮ ስራዎቹ፣ በሰማይ ብርሃናት በሚገለጹ ምልክቶች፣ በመላእክት፣
በነቢያት፣ በህልምና በራእይ ከገለጸ በኋላ በዘመኑ መጨረሻ ደግሞ ራሱ ልዑል አምላክ የሰውን ሥጋ ለብሶ በመምጣት በክርስቶስ ተናግሮአል።
ዛሬም እየተናገረ ነው። እኛ የመስማትንና የመረዳትን ጸጋ እንለምን እንጂ እግዚአብሔር ከመናገር ዝም ብሎ አያውቅም።
በዓለም ላይ ታላቁ ኤኮኖሚና
የጦር ኃይል ያላት አሜሪካ ባለፈው ዓመት በተደረገ ምርጫ ያልተጠበቁት ሰው በፕሬዝደንትነት መመረጣቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ
የሚታየውን የፖለቲካ መመሰቃቀል፣ እንደ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ጋር ካሉ አገሮች ጋር አገሪቱ የገባችባቸውን ውጥረቶች
እንዲሁም በምድሪቱ የሚታየው ማህበረሰባዊ ውጥረቶች፣ መንፈሳዊና የሞራል ውድቀት የሚያሳዝናቸው የአገሪቱ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር
ለምድራቸው ምህረትን እንዲያደርግ የንስሃና የጸሎት ጥሪዎችን ካወጁ ውለው አድረዋል። እነዚህን ሁኔታዎችና በሰማያትም ላይ የሚከሰቱትን
የዘንድሮውን የጸሃይ ግርዶሽና በሴፕቴምበር 23 የሚከሰተውን ታላቅ የሰማያት ምልክት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብዙ የአሜሪካ
ክርስቲያን መሪዎች አገሪቱ በንስሃ እግዚአብሔርን እንድትፈልግ ጥሪ እያደረጉ ያሉት። በዚህች በምድር ላይ ባለች ኃያል አገር ላይ የሚፈጠር ቀውስ በአንድም በሌላም
መንገድ የማይነካው አገርና ህዝብ በምድር ላይ የለም ማለት ማጋነን አይሆንም። ስለዚህ ሁላችንም ለዚህች አገር ሰላምና ምሕረት እንጸልይ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ሪፖርት ስለ ኦገስት 21 የጸሃይ ግርዶሽና ከላይ ልገልጻቸው ስለጀመርሁት ሃሳቦች የበለጠ መረጃን ይሰጣል።
እግዚአብሔር ይጠብቃችሁና
ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ