የሰውን ዘር በኃጢዓት ምክንያት ከሚሆነው የዘለዓለም ሞት፣ እርሱም ሲኦል ወይም የእሳት ባህር ለማዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
በመስቀል ላይ የተቀበለውን መከራና ሞት እንዲሁም ትንሳኤውን በዓለም ሁሉ ያሉ ክርስቲያኖች በሚያስቡበት በዚህ በህማማት ሳምንት
የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲኦል የለም ብለው ማወጃቸው በካቶሊኳ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎችም የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ
ትልቅ ማእበልን ቀስቅሶአል። “እግዚአብሔር የለም” ባይ ወይም ATHEIST የሆነ የረጅም ጊዜ ወዳጃቸውና ላ ሬፑብሊካ የሚባለው
ጋዜጣ መስራች ሚስተር ኢዩጄኒዮ ስካልፋሪ ነበር እኒህ ትልቅ የሃይማኖት መሪ የሚመስሉ ሰው ይህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቃረን፣
የራሳቸውን የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሆነውን ህዝበ ክርስቲያን እምነት የሚጻረር የተሳሳተ
ትምህርት በአደባባይ የተናገሩት፣ ለዚያውም ወንጌልን ሊሰብኩለት ለሚገባ እግዚአብሔር የለም ባይ ሰው። ኢዩጄኒዮ ስካልፋሪ በበኩሉ
“እርስዎ አብዮተኛ ወይም ተራማጅ ነዎት” ብሎ የክህደትና የስህተት ትምህርታቸውን ሲያደንቅላቸው ደግሞ “ተራማጅ ወይም አብዮተኛ
መባሉ ትልቅ ክብር ነው” በማለት ነበር የተቀበሉት። ታዲያ ሲኦል ከሌለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ሞተ? ለነገሩማ እኮ እኒህ የዛሬ
አምስት ዓመት (MARCH 19 2013) በአሜሪካና በብዙ የምእራባውያን
አገሮች ድጋፍ እንዲሁም በCNN፣ በBBC በ HOLYWOOD እና በሌሎችም የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ተቋማት ጻድቅነታቸውና ዝናቸው
ተናፍሶላቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስልጣን ላይ የወጡት ሰው እንዲህ ያሉ መጽሐፍ ቅዱስንና የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ
የሚጻረሩ ነገሮች ሲናገሩ ውለው አድረዋል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉት ብዙ መሪዎችም ይህንኑ ጉዳይ እያስመለከቱ ሰውየው ቫቲካንን
እና የካቶሊክን ምእመናን ወደ ስህተት እየመሩ ነው በማለት ሲጮሁና ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን
ትንቢት የሚያጠኑ ብዙ መምህራንና በራሷ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ያሉ አንዳንድ መሪዎች አባ ፍራንሲስ ሲናገሩአቸው የከረሙት
የተሳሳቱ ትምህርቶች በአጋጣሚ የተከሰቱ ሳይሆኑ የሰውየውን ማንነትና ሊያከናውኗቸው የሚሹትን ነገሮች የሚያንጸባርቁ ናቸው ይላሉ።
አንዳንዶች ከዚህም አልፈው ምናልባት ሰውየው ዓለምን ሁሉ ሊያስትና ሊገዛ ላለው ለሃሳዊው መሲህ መንገድ ጠራጊ ወይም ጭራሹኑ በዮሐንስ
ራእይ ምእራፍ 13 ላይ የተገለጸው ሃሰተኛው ነቢይ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ጽፈዋል። የዚህ አጭር መልእክቴ ዓላም አንድና አንድ ብቻ
ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ እንደሚያስተምረው የኃጢዓት ደሞዝ የዘለዓለም ሞት ነው። የዘለዓለም ሞት ማለት ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ
በማመን የኃጢዓትን ይቅርታ ካገኙ ሰዎች በስተቀር የማያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ክብር ተለይተው በዘለዓለም ጨለማ፣ እሳቱ በማይጠፋ
ትሉ በማያንቀላፋ ሲኦል (ማርቆስ 9:48) መውደቅ ማለት ነው። እኒህ ሰው በፈቀዳቸው ስልጣን ይቀመጡ ወይም የፈቀዳቸውን ታዋቂነት
ያግኙ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ሊለውጡት አይችሉም። ስቅለት ብለን በምናከብረው በዚህ እለተ አርብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የለምን
ሁሉ የኃጢዓት እዳ ሊከፍልና ሰዎችን ሁሉ ከሲኦልና ከዘለዓለም እሳት ለማዳን በመስቀል ላይ ሞቷል፣ ሞትን ደግሞ ድል አድርጎ በሶስተኛው
ቀን ተነስቷል። የሚያምኑትን ሁሉ ወዳዘጋጀው የዘለዓለም የክብር ህይወት ይዞ ለመግባትና በማያምኑት ሁሉ ላይ ሊፈርድ ዳግም ተመልሶ
ይመጣል። ያ ዳግም ተመልሶ የሚመጣበት ጊዜ እጅግ ስለተቃረበ ነው ዛሬ እንደ አባ ፍራንሲስ ካሉ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሚባሉ በዓለም
ፊት ትልልቅ ሰዎች የክህደትን ቃል እየሰማን ያለነው። ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመጽ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ (ማለትም ዓለምን
ሁሉ በማታለል የሚገዛው ሃሰተኛው መሲህ) ሳይገለጥ የጌታ ዳግም ምጽዓት አይሆንም ተብሎ በ2ኛ ተሰሎንቄ 2 ቁጥር 3 እስከ 12
ተጽፎአል። ነቢዩ ዳንኤል በምእራፍ 7፣23 እስከ 28፣ በምእራፍ 9 ቁጥር 27 እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በማቴዎስ
ወንጌል ምእራፍ 24 በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 13 በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 17 እና ምእራፍ 21 እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 5 ቁጥር 43 ላይ ዳግም ከመምጣቱ በፊት በምድር
ላይ የሚሆኑትን ነገሮች፣ የሃሰተኞች ነቢያትና የሃሰተኞች ክርስቶሶችን መምጣት በተመለከተ በዝርዝር አስተምሮአል፣ አስጠንቅቆአልም።
ያ የዘመን መጨረሻ ይህ ያለንበት ቀን ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ስለዚህ እንንቃ፣ በመጠን እንኑር፣ ወንጌልን እንስበክ እንጂ
አንደናገጥ። በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ይመጣል፣ ያም ዘመን ቀርቦ በደጅ ነው። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የመለከት ድምጽ ብሎግ የአማርኛን ቋንቋ በተቀዳሚነት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ለማድረስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ያገለግላል።
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...
-
የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5 ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ...
-
የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ትምሕርት 6 ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ...
-
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018 አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ