ያለንበት ዘመን እና በጉጉት ልንጠብቀው የሚገባን የወንጌል ተስፋ የጌታችን የኢየሱስ ዳግም ምጽዓት


ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

በዝናብና በጸሃይ፣ ከጭቃና ከአቧራ ጋር እየታገለ የሚያርስ ገበሬ ድካሙንና ውጣ ውረዱን እንዲታገስ የሚያደርገው አንድ ቀን የድካሙን ፍሬ እንደሚያጭድ ማወቁና ማመኑ ነው። በሩጫ፣ በእግር ኳስና በሌሎችም የስፖርት መስመሮች የሚሳተፉ ሰዎች ሰውነታችውን ለውድድር ብቁ ለማድረግ የሚወዱትን ምግብና እንቅልፍ ጭምር መስዋእት በማድረግ ይለማመዳሉ፣ የጨዋታዎቹን ህጎች ያጠናሉ፣ ይሰለጥናሉ፣ የሚሳተፉበትን የስፖርት መስመር ዜናዎች በቅርብ ይከታተላሉ። የግጥሚያና የውድድር ቀኖችንም በጉጉት የሚጠብቁት የማሸነፍና ሽልማት የማግኘት እድል እንዳላቸው ስለሚያምኑ ነው።  የክርስትናን ሕይወት የደስታ፣ የሰላምና የድል ሕይወት የሚያደርገው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ሰምቶና ተቀብሎ ላመነ ሰው የተሰጠው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ነው። ያ የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ የሚገለጠው ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዳግም ተመልሶ ሲመጣና የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ መንግስት ሲመሰርት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መንገድ ያስተምራል። አለበለዚያ ግን ሃዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው በዚህ ህይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮ 15፡19
የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን የክርስቶስ ወንጌል እውነተኛ መልእክት በየዘመኑ በተለያየ መንገድ እየተሸቃቀጠና እየተበረዘ በብዙዎች ዘንድ የዚህን ዓለም ገንዘብ፣ ስልጣንና ዝና ማትረፊያ መሆኑ አሳዛኝ ቢሆንም፣ የማይካድ እውነት ነው። ይህ እንደሚሆን የሚያውቀው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት ጀምሮ ደቀ መዛሙርቱ ከገንዘብና ከዚህ ዓለም ፍቅር እንዲሁም ደግሞ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባቸው ተኩላዎች እንዲጠነቀቁ አስተምሮአቸዋል። ማቴዎስ 7:15-20 እነዚያ በገበሬው እርሻ ላይ እንክርዳድን የዘሩ ሰዎች ስራ ዛሬ በእግዚአብሔር መንግሥት እርሻ (በክርስቲያኖች) መካከል ስር ሰዶ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ብለው በሰዎች የተቀመሙና የተዘጋጁ፣ ለሰው ጆሮ ለመስማት ደስ የሚያሰኙ፣ ስጋዊና ምድራዊ ምኞትን የሚቀሰቅሱ ትምህርቶችን በመከተል ሳያውቁት ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፈቀቅ እንዲሉ አድርጓቸዋል።
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሁሉ በእምነታቸው ተስፋ ላይ እንዲያተኩሩ ካስተማሩት ከጌታ ሃዋርያት አንዱና ዋነኛው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፤
“ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ
 የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።” 1ኛ ጴጥሮስ 1፡13
ከጴጥሮስ ጋር አብሮ የጌታ ሃዋርያ የነበረው ዮሐንስ ደግሞ እንዲህ ሲል የክርስቲያንን እውነተኛ ማንነትና ተስፋ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡
“ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።” 1ኛ ዮሐንስ 3፡2
የዕብራውያን ጸሃፊ ደግሞ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ተስፋ በሰማይ መሆኑን እና ያ ተስፋም የሚገለጸው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ እና ያችን በሰው እጅ ያልተሰራች ከተማ ሲገልጽ እንደሆነ እንደሚከተለው ያሳየናል፤
“እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ። በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፣ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን፤” ዕብራውያን 13፡12-14
በክርስቶስ ወንጌል የተሰጠውና ክርስቲያን ሁሉ ሊጠብቀው የሚገባው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓትና የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጥ እውን እንደሆነና የሰው ልጅ ከሚያውቀውና ከሚገምተው ሁሉ በላይ እጅግ የላቀ መሆኑን ደግሞ ሃዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ገልጾታል፤
“ዓይን ያላየችው፣ ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበው፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው፤” 1ኛ ቆሮ 2፡9
ጌታ አምላክ ይህንን ለሚወዱት ያዘጋጀውን ተስፋ በጊዜው ሊገልጸው ዝግጁ ስለሆነ በእርሱ ለሚያምኑበትና መገለጡን በመጠባበቅ ለሚኖሩ የማያሳፍራቸው መሆኑን የእብራውያን መጽሐፍ እንደሚከተለው ይነግረናል፤
“አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፣ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።” እብራውያን 11፡15-16

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ባስተላለፍኳቸው መልእክቶች በተደጋጋሚ ለአንባቢዎች ለማቅረብ እንደሞከርሁት የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የተቃረበበት ሰዓት አሁን ነው። ስለዚህም ዓለማችን በከፍተኛ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የማህበረሰብ ስነ ልቡናዊ ነውጥ ውስጥ ትገኛለች። ብዙውን ጊዜ ለውጥ ክፉ ነገር አይደለም። ዛሬ በምድር ላይ የሚታየውና ብዙዎች እድገትና ለውጥ ነው የሚሉት ግን የሰውን ዘር ወደ መልካም አቅጣጫና ፍጻሜ የሚያደርስ አለመሆኑ ገሃድ መውጣት ከመጀረ ውሎ አድሮአል። በብዙ የእምነት ድርጅቶችም ይሁን በፖለቲካና በኤኮኖሚ ተቋማት፣ በመንግስታት መዋቅሮችም ውስጥ ሆነ በየግለሰቡ የእለት ከእለት ኑሮ፣  ሃይማኖት አለኝ በሚሉ ሰዎችም ሆነ ሰልጥነናልና “አምላክ የለም” በሚሉ ዘንድ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት፣ በሃዋርያትና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመናት በፊት የተተነበየ ሁኔታ ትንቢታዊና ከፍተኛ ለውጥ ሊታይበት የሚችል ሂደት መሆኑ ቢገመትም በብዙ ሰዎች ዘንድ ግን በቂ ግንዛቤ ያገኘ አይመስልም።
በኖህ ዘመን በነበረው ዓለም እንደሆነውና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል ላይ እንዳስተማረው ዓለም ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ተንሸራቶ እየሄደ ነው። በኖህ ዘመን ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ የጥፋትም ውኃ መጥቶ ሁሉን እስኪያጠፋ ድረስ እንዳላወቁ በዚህ ዘመንም የሰው ልጅ፣ ብዙ ክርስቲያኖችንም ጨምሮ፣ በመንፈሳዊ አዚም ስር ያለ ይመስላል። በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጡ የአጋንንት ትምህርቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው ገብተው እውነት መሬት ላይ ወድቃለች። ኃጢዓት እንደ ስልጣኔ ተደርጎ ይሰበካል፣ አመጽም በመንግስታት እንደ ህግ እየጸደቀ ነው። ብዙ ቤተ ክርስቲያን ነን በሚሉ ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚደረግ ዓመጽ ዘመናዊ ነው ተብሎ ሰዎችን ንስሃ ግቡ በማለት ፈንታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክፍሎች ዘመን ያለፈባቸው ናቸው የሚሉ ድምጾች እየበዙ ናቸው። ኃጢዓትን ኃጢዓት ነው የሚሉ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል አልተረዱትም  ተብለው ይወቀሳሉ፣ ይወገዛሉ።
ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ ጌታ ምጽዓት ስናስብ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 51 እስከ 57 ወይም በ1ኛ ተሰሎንቄ ምእራፍ 4 ከቁጥር 15 እስከ 18 እንደ ተጻፈው የእግዚአብሔር መለከት በድንገት ተነፍቶ ሙታን የሚነሱበትንና በሕይወትም ያሉ ቅዱሳን በድንገት በቅጽበተ ዓይን የሚለወጡበትን የመነጠቅን ቀንና ሰዓት ልናውቅ እንደማንችል በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ቁጥር 36 ላይ ተመልክቷል። ነገር ግን የጌታ ዳግም ምጽዓት መቃረቡን የሚያመለክቱን ብዙ ምልክቶች እንዳሉና እነዚህም ምልክቶች በአንድ ላይ፣ በተደጋጋሚና በፍጥነት መታየት ሲጀምሩ የምጥ ጣር ምልክቶች እንደሆኑ እንድናውቅና ዓይናችንን አሻቅበን ከላይ የሚመጣውን ቤዛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንጠብቅ ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ራሱ በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 21 እና በሌሎቹም ወንጌሎች ላይ ያሳስበናል። ሃዋርያትም በተደጋጋሚ ከሰበኳቸውና በሰፊው ካስተማሩባቸው ታላላቅ ርእሶች መካከል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት አንዱና ጎልቶ የሚታይ ነው።
ጌታ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ የቀደሙ ክርስቲያኖችና መሪዎች ትልልቅ መከራዎች፣ ጦርነቶች፣ ረሃብና ቸነፈር እንዲሁም የምድር መናወጥና ሌሎቹም በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ዘመን የተነገሩ ምልክቶች በተከሰቱ ጊዜ ሁሉ ጌታ ሊመጣ ነው በማለት  ሲደናገጡ ግራ ሲጋቡና ሌሎችንም ግራ ሲያጋቡ መኖራቸው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈበት ነገር ነው። እንደዚህ ባሉ ማደናገሪያዎች ግራ የተጋቡ ሰዎችና ከመጀመሪያውም ጌታ ዳግም ተመልሶ ይመጣል በሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የማያምኑ ነገር ግን ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚቆጥሩ ሰዎችም በየዘመኑ በመነሳት የራሳቸውን ሃሳቦች በትምህርተ መለኮትና ትንታኔዎች (commentary) በመጻፍ በተለይ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሃዋርያት የተገለጸውን እውነት ገለል አድርጋ በሰዎች ትምህርት እንድትመራ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ስለዚህም ዛሬ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆችና በየሴሚናሪዎቹ እንደ ተራቀቀ እውቀት የሚሰጠው ስነ መለኮት የሚባል ትምህርት በተለያዩ የግሪክና የእብራይስጥ እንዲሁም ቴክኒካዊ ሃሳቦችና ንግግሮች ተውገርግሮ የሰዎችን ሃሳብና ትንተና ከእግዚአብሔር ቃል ጎን ለጎን በማስቀመጥ እውነተኛ አገልጋዮችን በመቅረጽና በማዘጋጀት ፈንታ ግራ የተጋቡና በጥያቄ የተሞሉ አስተማሪዎችንና መሪዎችን እያፈራ ነው። ዘመናዊ ስምና ማእረግ ይሰጣቸው እንጂ ዛሬም ቢሆን በስነ መለኮት ትምህርት ስም የሚሰጡ ብዙ የተውገረገሩና የተዛቡ ትምህርቶች መሰረታቸው ከጥንት ነው። እነዚህ ጌታ ኢየሱስ ጠላት በሌሊት መጥቶ የዘራው እንክርዳድ ምሳሌ አድርጎ ካስተማራቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ትክክለኛና የስነ መለኮት ትምህርት አስፈላጊ ነው። ብዙ እውነተኛ የሆነውን ትምህርትም የሚያስተምሩ ተቋማት አሉ። ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶችን ከሚያውገረግሩ ትምህርቶች ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። የዚህ መልእክት ዓላማ ስለተዛቡ ትምህርቶች ለመግለጽ ባይሆንም፣ ከተዛቡት ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ የጌታን ዳግም ምጽዓት የሚክዱ ወይም የሚያውገረግሩ መሆናቸውን ግን ሳልጠቅስ አላልፍም። ለዚህ ነው ዛሬ ብዙው ክርስቲያን እውነተኛውንና ዘለዓለማዊውን የወንጌልን ተስፋ፣  እርሱም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓትና በክብር መንገስ፣ እንዲያውቅና እንዲረዳ ከማስተማር ይልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሚመስል የሰዎች ሃሳብና ባዶ ሃይማኖተኝነት ተይዞ ትምህርቱ፣ ሃሳቡ፣ መሻቱና ተግባሩ ሁሉ በገንዘብ፣ በምድራዊ ክብርና ብልጽግና እንዲሁም በሚያልፉት የዚህ ዓለም ነገሮች ላይ ከልክ በላይ እንዲያተኩር የተደረገው።
በመጨረሻው ዘመን የብዙው የሰው ዘር ባህርይ ገንዘብንና ምቾትን እንዲሁም ተድላን ከእግዚአብሔር ይልቅ መውደድ እንደሚሆን በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት በ2ኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ 3 እና በ1ኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ 3 የተገለጸውም እውነት ፈጽሞ የተረሳ ይመስላል።  ይህም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል እንዳስተማረውና ሃዋርያው ጴጥሮስም እንደጻፈው በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ከጌታ ዳግም ምጽዓት ምልክቶች አንዱ ነው። ዛሬ በተደጋጋሚ ሲሰበክና እንደ ትምህርትም ሲሰጥ እንደሚሰማውና በተግባርም እንደሚታየው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖና ተቀብሎ የዳነ ብዙ ክርስቲያን የእድገት ምልክት መቀደስ፣ መታዘዝ፣ በመስዋእትነት ሕይወት መኖርና መንፈሳዊ ፍሬን ማፍራት መሆኑ ቀርቶ በዚህ ዓለም ቁሳቁስ፣ ገንዘብ፣ ብልጽግና እና የኑሮ እሽቅድምድም የተተበተበ ነው።
ጌታ እግዚአብሔር ለልጆቹ መልካም አምላክ ነው። እንኳን በልጁ ደም ለዋጃቸው ልጆቹ ይቅርና ለክፉዎችና ለማያመስግኑትም ሁሉ ጸሃዩን ያወጣል፣ ዝናቡንም ያዘንባል። የሰማይ አእዋፍን ይመግባል፣ የምድር አበቦችንም ያለብሳል። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ እውነትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በግልጽ ያስተማረው እውነት ነው። ነገር ግን በክርስቶስ ዳግም ተወልደናል የምንል ሁሉ ከሁሉም በላይ ልንሻውና ልንናፍቀው የሚገባን ታላቁ ነገር በወንጌል የተሰጠው ተስፋ፣ እርሱም የእግዚአብሔር መንግስት በክብር መምጣት ነው። የዚያ የእግዚአብሔር መንግስት ቁንጮ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፣ ክርስቲያን ሁሉ የእርሱን በክብር ዳግም መገለጽ እንዲጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መረጃዎችን፣ ትንቢቶችን፣  ምልክቶችን እና ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት ያስተምረናል። በመጨረሻው ዘመን የጌታ መምጣት መዳረሱን ከሚያሳዩን ምልክቶች አንዱ ብዙ ሰዎች፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንዶችንም ጨምሮ፣ የጌታን ዳግም መምጣት ችላ ማለት ብሎም አለማመንና አለመቀበል እንዲሁም በዚህ ሃሳብ ላይ ማፌዝ እንደሚሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎአል። ለምሳሌ ሃዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፤
በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞች የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፣ እነርሱም የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። 2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-7
ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በምድር ላይ የሚካሄደውን ነገር አተኩረን ብንመለከት ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ እየተፈጸመ ያለው የእግዚአብሔር ክህደት፣ ዓመጽ፣ ኃጢዓትና ክፉን መውደድ በፍጥነት ስር እየሰደደ ይገኛል። የምድር መናወጥ፣ ጎርፍ፣ የምድር መሰንጠቅና መደርመስ፣ እሳተ ገሞራ (በመጽሐፍ ቅዱስ ደምና እሳት፣ ጢስና ጭጋግ ተብሎ የተጠቀሰ)፣ ጦርነትና ከፍተኛ የሆነ የጦርነት ዝግጅት፣ የህዝብ ፈጂ በሽታዎች መብዛት፣ የኢኮኖሚና የገንዘብ ስርዓት መናጋት በምድር ሁሉ እየተስፋፋ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰላምና ብልጽግና ነው እየተባለ አብረው ሲነግዱና ሲገባበዙ የኖሩት ታላላቆቹ የምድር አገሮች እነ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ አገሮች፣ ጃፓን፣ ሩሲያና ቻይና፣ ብራዚል፣ ወዘተ ዛሬ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ውዝግብና ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። የነዳጅ ዋጋ ወደ ላይ እጅግ ማሻቀብ፣ የአሜሪካው ዶላር እየተገለለ በቻይናው ገንዘብ በሬንሚምቢ (ዩዋን) በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በሰፊው መተካቱ፣ አሜሪካ ከባላጋራዎቿ ጋር ብቻ ሳይሆን ወዳጆቿ ከሚባሉትም ጋር አንጃ ግራንጃ ውስጥ መዘፈቋና የተከተለው ግራ መጋባትና ፍጥጫ ብዙ የምድር መሪዎችንና ታዛቢዎችን እያስጨነቀ ይገኛል።
በአሜሪካና በአጋሮቿ በሩሲያ ላይ የሚደረገው መጋበዝና እቀባዎች፣ በምስራቃዊ ዩክሬን ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በሩሲያ፣ በአሜሪካና በአጋሮቿ መካከል ያለው ውጥረት፣ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና እስራኤልና ሌሎችም አጋሮቻቸው በአንድ በኩል፣  የሶሪያ መንግስት፣ ኢራንና  ሩሲያ ደግሞ በሌላው ተሰልፈው የሚሻኮቱበት አደገኛ ሁኔታ፣ ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በየጥቂት ወራቱ የሚያደርጉት የጦርነት ልምምድና ለሰሜን ኮሪያ የሚያሳዩት ማስፈራሪያ፣ በደቡብ የቻይና ባህርና በታይዋን ደሴት ምክንያት በአሜሪካና በቻይና መካከል ያለው ውጥረት ሁሉ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት ሊለኩሱ የሚችሉ ሁኔታዎች መሆናቸውን አዋቂዎች ይናገራሉ። ከአሜሪካና አጋሮቿ እንዲሁም ከሩሲያ ጋር የተፈረመውን የኢራን የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎች ምርምር የሚያግድ ስምምነት አሜሪካ አልቀበለውም በማለቷ የተፈጠረው ውጥረት ላለፉት ሶስት ዓመታት የነበረውን አንጻራዊ ሰላም አዛብቶ መካከለኛውን ምስራቅ ሊወጣ በማይቻልበት የጦርነት አዘቅት ውስጥ ያስገባዋል የሚሉም ብዙ ናቸው። የአሜሪካው ምክር ቤትም በኢራን ላይ ሊደረግ ስለሚችል ጥቃትና ስለሚከተለው ጦርነት እየተነጋገረ መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ናቸው። ባለፉት ሁለት በማይሞሉ ወራት ውስጥ ደግሞ በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ውጥረት ከአደገኘነት አምልጧል፣ ጦርነትም ሊቀር ነው የሚሉ ተስፋዎች ከተናፈሱ በኋላ ሁኔታው እንደገና ወደ መባባስ ውስጥ ገብቷል፣ በአሜሪካው ፕሬዝደንትና በሰሜን ኮሪያው መሪ መካከል ሊደረግ የነበረው የድርድር ስብሰባም ተሰርዞ የጦርነት ደመና እንደገና እያንዣበበ ነው።
ከሁለት ሺህ ዓመታት መፈራረስ በኋላ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንዋን አሜሪካ መቀበሏና ኤምባሲዋንም በዚሁ በያዝነው ወርና እስራኤል እንደገና በተመሰረችበት 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ በዚያው በኢየሩሳሌም መክፈቷ በብዙ አይሁዶችና እስራኤልን በሚደግፉ መካከል እንደ ትልቅ የትንቢት ፍጻሜ ቢታይም፣ በዚህ የተከፉት የእስላሞች አገሮችና ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ይህን ይቃወማሉ፣ ለመቀልበስም ይሞክራሉ። በኢየሩሳሌም የነበረውን የጥንቱን የአይሁድ ቤተ መቅደስ ለመስራት የሚታገሉ ድርጅቶች ደግሞ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ከሆነች ቤተ መቅደሱንም መስራት አለብን በማለት ግፊት እያደረጉ ሲሆን፣ በዚሁ ሳምንት ድሮ ቤተ መቅደስ ነበረበት በሚባለው ቦታ ላይ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ቆሞ ያለውን የእስላሞች መስጊድ አስወግዶ አዲስ ቤተ መቅደስ የሚያሳይ ካርታ በኢየሩሳሌም ላሉት ለአሜሪካው አምባሳደር መሰጠቱና በዜና መዘገቡ ደግሞ አንዳንዶችን ሲያስደነግጥ ሌሎችን ደግሞ አስገርሟል።
ብዙ የአይሁድ እምነት ተከታዮችና ደጋፊዎቻቸው የዛሬው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን በመቀበላቸው ከፍተኛ ትንቢታዊ ነገር ሰርተዋል ብለው ስለሚያምኑ፣ ቤተ መቅደሱም አሁን እንዲሰራ ድጋፍ እየጠየቁ ናቸው። የአሜሪካውን ፕሬዝደንት ምስል ከጥንቱ የፋርስ ንጉስ ቂሮስ ጋር የታዘ የቤተ መቅደስ ሳንቲም አትመው በገበያ ላይ አውለዋል። የሳንቲሙም ሽያጭ ለቤተ መቅደሱ መስሪያ ይሆናል ተብሏል። የጥንቱ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ከተሰራ ደግሞ የእስራኤል መሲህ (ማሺያክ) እንደሚመጣ የሚያምኑ አይሁድ ብዙ ናቸው። ይህ የቤተ መቅደሱ መሰራት ደጋፊዎች ይመጣል የሚሉት መሲህ ግን ክርስቲያኖች ዳግም ተመልሶ ይመጣል የሚሉትን የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም።
የዛሬዎቹ ብዙዎች አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሁ እንደሆነ አያምኑም። ቀረብ ብለን የጌታን ትምህርትና የሃዋርያትን መልእክቶች እንዲሁም ነቢያት ስለመጨረሻው ዘመን የተናገሯቸውን ትንቢቶች ካስተዋልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ከመምጣቱ ቀደም ሲል፣ መሲህ ነኝ የሚለው የዓመጽ ሰውና የጥፋት ልጅ (በተለምዶ ሃሰተኛው ክርስቶስ የሚባለው) ይገለጽ ዘንድ የግድ ነው።  ያ የዓመጽ ሰው አዲስ በሚሰራው ቤተ መቅደስ በአንዱ በኩል የጥፋትን ርኩሰት እንደሚያቆምበት ነቢዩ ዳንኤል በግልጽ ተናግሮአል፣ በአዲስ ኪዳንም ሃዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ሰው ተናግሮአል (2ኛ ተሰሎንቄ 2፡3-12) ታዲያ፣ ምናልባት ቤተ መቅደሱን ለመስራት እየተሯሯጡ ያሉት  አይሁድና ደጋፊዎቻቸው ሳያውቁ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ያንን ዓለምን ሁሉ የሚያስተውን የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ ተብሎ የተጠራውን ሃሰተኛውን ክርስቶስን ይሆን? ሰዎች ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመን እምቢ ካሉ በራሱ ስም የሚመጣውን ሃሳዊውን መሲህ ማመናቸው የግድ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ የጌታ ዳግም ምጽዓት እጅግ ተቃርቧል ማለት ነው። ምክንያቱም ያ ሃሰተኛው ክርስቶስ ለ42 ወራት ምድርን ካሳተና ብዙ ህዝብ ካለቀ በኋላ ይህን በራእይ አውሬው የተባለውን እና አጋሩን ያንን ሃሰተኛውን ነቢይ  ወደ እሳት ባህር የሚጥለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ያ የሚሆነው ደግሞ ጌታ በክብር ከሰማይ ተመልሶ ሲመጣ ነው። 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡8 እና ራዕይ 19፡20-21 እንዲሁም ዳንኤል 9;27 እና 12፡7-12
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በተናጥል ሲታዩ “ይህማ ምን አዲስ ነገር ነው ” ወይም ደግሞ “ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ምን አገናኘው” የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች ናቸው ተብለው የሚጠሩት ከላይ የጠቀስኳቸው ብቻም አይደሉም። ስለ ቴክኖሎጂ አስፈሪ ልዕቀት፣ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለመቀየርና ለማሻሻል እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጋር ለማደባለቅ የሚያደርጉት እሽቅድምድም፣ በሰማያት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ምልክቶችና ኤሊየንስ ናቸው የሚሏቸውንና የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች ስለሚባሉት የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ወደ አደባባይ እያወጣቸው ያሉ መረጃዎችን ወዘተ ሁሉ ብጽፍ ለማንበብ ያደክማል።
በእርግጥም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በአንድ ጊዜ ወይም በሌላ በምድር ላይ ሲታዩ የቆዩ ነገሮች ናቸው። ነገር ግን የዛሬዎቹ ክስተቶች ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ ጌታን ዳግም ምጽዓት ከተጻፉት ትንቢቶች ጋር በቅርበት በማነጻጸር ሲመዘኑ የክስተቶቹ ብዛት፣ የመከሰታቸው ፍጥነትና ተያያዥነት እንዲሁም መወሳሰብና አስጨናቂ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ቀልብን እየሳበ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ከሚያጠኑ የክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የሃይማኖት፣ የታሪክና የፖለቲካ ታዛቢዎችና ተንታኞችም ነው። ብዙ የእስልምና ድርጅቶች፣ የሂንዱይዝም፣ ኔው ኤጅ፣ የቡድሂዝም ወዘተ መሪዎችም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፍጥረት፣ በተለይም ይህች ምድርና የሰው ዘር፣  ከፍተኛ የታሪክ ለውጥ ሊፈጸም በደረሰበት ዘመን ላይ እንዳሉ ይናገራሉ።
እንንቃ፣ የእግዚአብሔር ቃል ስለዚህ ዘመን የሚናገረውን፣ ቀረብ ብለን እንመልከተው፣ ደጋግመን እናንብበው እናጥናው። መረዳታችን በየትኛውም ደረጃ ላይ ይሁን በየትኛው ጌታ አምላካችንን በእውነትና በመንፈስ ለማምለክ፣ ለመታዘዝ፣ እርሱንና በምሳሌው የፈጠረውን ጎረቤታችንን ለመውደድና የወንጌሉን የምስራች ላልሰሙ ሁሉ ለማድረስ እንትጋ። ማራናታ፣ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና።1ኛ ቆሮ 16፡22


በእስራኤልና በኢራን መካከል ጦርነት ተጀምሮአል፣ ሊባባስና ሊስፋፋ ይችላል ተብሎ ይፈራል


ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ, May 10, 2018
ባለፉት 14 ወራት ብዙ አገሮች ለጦርነት በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ፣ በተለያዩ የዓለም ክልሎች ከፍተኛ ግጭቶች ሊነሱ እንደሚችሉ እነዚህም ግጭቶች ተባብሰው ወደ ከፍተኛ ጦርነት በመለወጥ ብዙ ህዝብን ሊያጠፉ እንደሚችሉ አመልክቼ ነበር። በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምትመለከቱት በእስራኤልና በኢራን መካከል ጦርነት ተጀምሮአል። ዜናው እንደሚያሳየው ሳይሆን ጦርነቱ የጀመረው ከሁለት ሳምንት ያህል በፊት እስራኤል በሶርያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የኢራን የመሳሪያ ማከማቻ ነው ባለችው ስፍራ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ ነው። በዚያ ድብደባ ብዙ ወታደሮች የሞቱባት ኢራን በጊዜው እንደምትበቀል ካስታወቀች በኋላ በዚህ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የእስራኤል መሪዎች ኢራን እስራኤልን ለማጥቃት እየተዘጋጀች ናትና በቅድሚያ እርምጃ መውሰድ አለብን ሲሉ ከቆዩ በኋላ ረቡት ሌሊት (ሜይ 9 ለ10 አጥቢያ) በሶሪያ ግዛት ያሉ የኢራን ጦር ያለባቸውን ስፍራዎችና የራሷን የሶሪያንም የአየር መከላከያና ሌሎች ወታደራዊ ማእከሎችን ስትደበድብ አድራለች። እስራኤል ይህን ድብደባ ከማድረጓ በፊትም ቀኑ ላይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሲያ በየዓመቱ በምታደርገው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የድል በዓል ሰልፍ ላይ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ተሰልፈው እንደ ዋሉና አገራቸው በሶሪያ ላይ ጥቃት በምትፈጽምበት ጊዜ በሶሪያ ያለው የሩሲያ ጦር ዝም እንዲል የሩሲያውን ፕሬዝደንት ሲያግባቡ እንደዋሉ በዜና አውታሮች ተዘግቧል።
ይህ አሁን በእስራኤልና በኢራን እንዲሁም በሶሪያ መካከል የተጀመረው ጦርነት መካከለኛውን ምስራቅና ዓለምንም በሙሉ ወደ ከፍተኛ የጦርነት እሳት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል እንደሆነ እጅግ ብዙ የመንግስታት ባለስልጣኖች፣ የጦርና የስለላ ባለሙያዎች በሰፊው ቢያመለክቱም የምእራባውያኑ የዜና ምንጮች ግን ስለ ሁኔታው በሰፊው አለመዘገባቸው ግልጽ ነው። የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት የሚያመለክቱ ትንቢቶችን በቅርብ በሚያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና ተመራማሪዎች ዘንድ ግን ይህ ጦርነትና በዓለምም ዙሪያ የሚደረጉት ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅቶች ትንቢታዊ መሆናቸው በሰፊው ይታመንበታል። ይህ ያለንበት ወር፣ ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል አገራቸው ፈራርሳና በምድርም ላይ እንደ ጨው ተበትነው የነበሩት አይሁድ ከየአገሩ ተሰብስበው እስራኤል የምትባለው አገር እንደገና በምድር ካርታ ላይ የታየችበት 70ኛ ዓመት የሚከበርበት ነው። የዛሬ 70 ዓመት በሜይ 14 ቀን ነበር እስራኤል እንደገና አገር ሆና የተመሰረተችው። የእስራኤል እንደገና እንደ አገር መመስረት በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስቀድሞ የተነገረ ለመሆኑ የሚከሉትን አንዳንድ ትንቢቶች መመልከት ብቻ ይበቃል።
አሞጽ 9:14᎐5  ከክርስቶስ ልደት በፊት በ750 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ሕዝቅኤል 4፡3-6 ፣ 34፡13 ፣ 37፡10-14 ፣ 37፡21-22 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ593 እስከ 571 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ኢሳይያስ 66፡7-8 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ701 እስከ 681 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
ኤርምያስ 16፡14-15፣ 31፡10 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ626 እስከ 586 ዓመተ ዓለም የተጻፈ
በፊታችን ሰኞ ሜይ 14 እስራኤል እንደገና የተመሰረተችበትን 70ኛ ዓመት ታከብራለች። የሰው እድሜ ሰባ ቢበዛ ሰማንያ ነው ተብሎ የተጻፈውን (መዝሙር 90፡10) እና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያት ስለ መጨረሻው ዘመን ያስተማሯቸውን ትምህርቶች በማነጻጸር ይህ ሰባኛው የእስራኤል እንደገና መመስረት መታሰቢያ ወቅት ምናልባት ገና ያልተፈጸሙት የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች የሚከናወኑበት ወቅት ይሆን? ዛሬ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነንና የትኛው ትንቢት በየትኛው ቀን ሊፈጸም እንደሚችል በእርግጠኝነት የሚያውቀው ጌታ አምላካችን ብቻ ነው። ነገር ግን በዙሪያችን የሚታዩትን የማያሻሙ ምልክቶች ረጋ ብሎ በማጥናትና፣ በማነጻጸር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቤተ ክርስቲያንና በእስራኤልም ረጅም ታሪክ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ከቃሉና ከዘመናችን ክስተቶች ጋር በማነጻጸር ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን መሆኑን እና የጌታችን የኢየሱስ  ክርስቶስ ዳግም ምጽዓትም እንደ ተቃረበ እናውቃለን።
ዛሬ በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ከፍተኛ ውጥረት እና በዚህም ምክንያት በታላላቆቹ አገሮች መካከል ስላለው ውዝግብ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት በእስራኤልና በአካባቢዋ እንዲሁም በምድር ዙሪያ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ጦርነቶችም የተጻፉ ብዙ ትንቢቶች አሉ። የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፤
        የጎግና የማጎግ ጦርነት ፣ ሕዝቅኤል ምእራፍ 38 እና 39
        እስራኤልን ከምድር ላይ ፈጽሞ ለማጥፋት በጎረቤቶቿና በወዳጆቻቸው በእስራኤል ላይ የሚደረግ ጦርነት ፣ መዝሙር ምእራፍ 83
        በዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 6፣ 8 እና 9 ላይ ላይ የተገለጸው (የተገለሱት) አስፈሪና፣ የኑክሊየር የሚመስል፣ የዓለም ጦርነቶች።
ይህ ዛሬ የተነሳው ጦርነት አጭር ግጭት ይሁን ወይስ ሊቀጥልና ሊስፋፋ የሚችል መሆኑን ለጊዜው ባናውቅም፣ በምድር ላይ ካለው ከፍተኛ ውጥረትና እንደ ሩሲያ፣ ቻይና እና አሜሪካ እያደረጓቸው ካሉ ነገሮች አንጻር ሲመዘን ግን ሁኔታው የሚባባስና ስር የሚሰድ ነው የሚለው አስተያየት ይመዝናል። ጦርነት አንድ ውጊያ ወይም የቦምብና የሚሳኤል ድብደባ ሳይሆን፣ በሰላም ካልተፈታ በስተቀር፣ እየተባባሰ ሊሄድ የሚችል መሆኑን ብዙ ታዛቢዎች ይስማሙበታል። በእስራኤልና በኢራን መካከል በሶሪያ ምድር ውስጥ እስካሁን ከተደረጉት ውጊያዎች በስተጀርባ በቀላሉ ልናያቸው ወይም ልንረዳቸው የማንችል ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉ። ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ የጦር ሰፈሮች አሏት የሶሪያንም መንግስት ትደግፋለች። የኢራን ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎችም በሶሪያ ጋባዥነት በአገሪቱ ውስጥ የጦር ሰፈሮችን መስርተዋል። እስራኤልና ጎረቤቷ ዮርዳኖስ እንዲሁም ብዙ የአረብ አገሮች ደግሞ በአሜሪካ የሚደገፉ ሲሆኑ ከእርሷም ጋር የጸጥታ ስምምነቶች ስላሏቸው። ስለዚህ፣ ምናልባት በእስራኤልና በኢራን መካከል የተጀመረው ውጊያ ከተስፋፋና በጊዜው መልስ ካልተገኘለት እነ ሩሲያንና አሜሪካንንም ወደ ማይፈለግ  ግጭት ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል ተብሎ ይፈራል።
ከሮማው ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ በብዙ አዋቂዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለ የቅርብ መረጃ ያላቸው ባለ ስልጣናት ይነሳል ወይም ተነስቷል እየተባለ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰፊው የሚነገርለትን የሶስተኛውን የዓለም ጦርነት አስፈሪ የሚያደርገው የሰው ልጅ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ፈጽሞ ሊያጠፋ የሚችልበት የጦርነት ቴክኖሎጂ እድገት ላይ መድረሱ ነው። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩ ኖሮ ስጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር (ማቴዎስ 24፡22) ብሎ ጌታ ኢየሱስ የተናገረለት በዚህ በመጨረሻው ዘመን ተሰርተው በስራ ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎች በእርግጥም እጅግ የሚያስፈሩ ናቸው። ይሁን እንጂ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዘላለም ሕይወትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊፈሩና ሊደነግጡ አይገባም። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ሲቃረብ ስለ ጦርነትና የጦርነት ወሬ መስማቱ የግድ ነው። የእኛ መልስ መፍራትና መደንገጥ ሳይሆን በመንፈስና በአእምሮ እንዲሁም ደግሞ ሲቻለን ተግባራዊና አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን እንዲሁም በዙሪያችን ካሉ ወገኖች ሁሉ ጋር በመተባበር መዘጋጀት ነው። ከሁሉም በላይ በጌታ በራሱ የተሰጠንን የደህንነትን ወንጌል የምስራች ላልሰሙ ሁሉ ማድረስና ለጌታ ቀን ዝግጁ ሆነን እንድንገኝ በመንፈሳዊ ህይወታችን መትጋት ያስፈልገናል። መዝሙረኛው ዳዊት እንዳለው፣ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን ታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝሙር 46፡1)



በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው?



በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018

አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም የሚለውን ቃል የተናገረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 3 ላይ እንደምናነበው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጥልቅ መንፈሳዊ ምስጢር ያዘለ ትምህርት የሰጠው ኒቆዲሞ  ለሚባል ሰው ነበር። ኒቆዲሞስ በእስራኤል ህዝብ መካከል በከፍተኛ የሃይማኖትና የህዝብ አመራር ደረጃ ላይ የነበረ፣ የላቀ ትምህርትን የተማረ፣ በሃይማኖታዊነቱ የተመሰከረለት፣ በምድራዊ በባለጸግነቱም የከበረ፣ በህዝብና በመሪዎችም መካከል ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ሰው ነበር። የአይሁድን እምነትና የህዝቡን ማህበረሰባዊ ህይወት በበላይነት ይመራ የነበረውና ሳንሄድሪን ተብሎ የሚጠራው ጉባኤ አባል የነበረው ኒቆዲሞስ እንደ ሌሎቹ የጉባኤው አባላት፣ ካህነትና ሊቃውንት ሁሉ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምረው ነገር ተስቦ ነበር አንድ ቀን በምሽት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ መሆኑን እንደሚያምንና በእጁም የሚሰሩት ድንቆች ከእግዚአብሔር በመሆናቸው ኢየሱስ የሚያደርገውንና የሚያስተምረውን እንደሚቀበልና እንደሚስማማበት ለኢየሱስ ሊያረጋግጥለት ነበር ወደዚያ የመጣው።  ምንም ያህል የተማረ፣ በህዝብ መካከል መልካም የከበረ፣ ስልጣንና ተጽእኖ ያለው እንዲሁም ደግሞ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ድንቅ ስራዎች መልካም አስተሳሰብና አድናቆት ያለው ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በሚገባ ለማወቅና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ግን ዳግም መወለድ ነበረበት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እጥር ምጥን ባለ መንገድ እንዲህ ሲል ነበር የነገረው፡
 “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።” ዮሐ 3፡3
በእድሜው ለገፋ፣ በሃይማኖታዊ ኑሮው ነቀፌታ የለብኝም ብሎ ለሚያስብ፣ በህብረተሰብ መካከል ለተከበረና በምድራዊ ኑሮውም ቢሆን በብልጽግና ለታደለ ሰው የኢየሱስ ንግግር ግራ የሚያጋባ ነበር። ይህንንም ከኒቆዲሞስ መልስ ለማየት እንችላለን። “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማህጸን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? ” ዮሐ 3፡4 በማለት ነበር ኒዞዲሞስ የጠየቀው። የኒቆዲሞስን ግራ መጋባት ያየው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለኒቆዲሞስ ግራ መጋባት ምንጩ የሰማው የወንጌል እውነት ሳይሆን እንደ ማንኛችንም ሰዎች በበደሉና በኃጢዓቱ የሞተና ከእግዚአብሔር ሕይወት የተለየ መሆኑ ነበር። ስለ ኃጢዓት በተደጋጋሚ የምንሰማው አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ስለ ፈጸሙት በደል ነው። እውነቱ ግን እኛ እያንዳንዳችን በበደላችን እና በኃጢዓታችን ምክንያት ሙታን መሆናችን ነው። ኒቆዲሞስ የሃይማኖታዊው ጉባኤ አመራር አካል የሆነበትና በሙሴ አማካይነት ህግ የተሰጣቸው ህዝቡ እስራኤላውያንም ሆኑ በምድራዊ ዘራችን የአብርሃም ልጆች ያልሆንን አህዛብ ሁላችን በኃጢዓት ውስጥ ወድቀናል፣ ፈጽመን ጠፍተናል፣ መንፈሳዊ ማንነታችን ሞቶ ከእግዚአብሔር ተለይተናል። ሃይማኖተኛና መንፈሳዊ ነገሮችን የምናውቅ ልንሆን እንችላለን። ልንጾም ልንጸልይና ብዙ ግብረ ሰናዮችን ልናደርግ እንችላለን። በህዝብና በመሪዎች መካከል የከበረ ስፍራ ሊኖረን፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም መልካም አስተሳሰብና አድናቆት ሊኖረን ይችላል። ከነዚህም ሁሉ አልፈን ለቤተ ክርስቲያንና ለወንጌል አገልግሎት የገንዘብና የሞራል ድጋፍም ልናደርግ እንዲሁም በመንፈሳዊ ፕሮግራሞች ልንሳተፍ እንችላለን። በዚህ ምድር ህይወታችንም የተማርንና የተሟላልን (የተባረክን) ልንሆን እንችላለን። እነዚህ ሁሉ እያሉንም ታዲያ ኃጢዓት ምን ያህል ማንነታችንን እንዳጠፋው አልተረዳን እንዲሁም ደግሞ ብቸኛውን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን ዳግም አልተወለድን ይሆናል። ሁላችንም የሰው ልጆች፣ ከአዳም እስከኔና እስካንተ፣ ከሄዋን እስከ አንቺ ድረስ፣ በኃጢዓት ምክንያት የጠፋን፣ የሞትን፣ ለዘላለም ከእግዚአብሔር የተለየየን መሆናችንን ለማወቅ የሚከተሉትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማየቱ ብቻ በቂ ነው፤
1)     ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም። ኢዮብ 14፡4
2)    እነሆ በዓመጻ ተጸነስሁ እናቴም በኃጢዓት ወለደችኝ መዝሙር 50(51)፡5
3)   ልዩነት የለምና ሁሉም ኃጢዓትን ሰርተዋልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። ሮሜ 3፡23-24
4)   ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢዓት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢዓት ባሪያ ነው። ባሪያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፣ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።
ዮሐንስ 8፡34᎒5
5)   በበደላችሁና በኃጢዓታችሁ ሙታን ነበራችሁ፣ በእነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሰራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ስልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን። እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌሶን 2፡1-3
6)   ኃጢዓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐ 1፡8
ስለዚህ ለኒቆዲሞስ ጌታ እንዳስተማረው በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በቀር ማንኛውም ሰው በኃጢዓት ምክንያት መንፈሱ የሞተ ነው። ከእግዚአብሔር ለዘላለም ተለይቷል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም። በዚህ ዓለምና በሰዎች ፊት የተማረም ሊሆን ይችላል። ሃይማኖተኛና ግብረ ሰናይ ፈጻሚ ሊሆን ይችላል። ሃይማኖቴ ክርስቲያን ወይም እርሱ ልክ ነው ብሎ የሚያምነው ሌላ እምነትም ሊሆን ይችላል። በሃይማኖቱና መልካም ምግባሩ ምክንያት ተሾሞ በአገርና በህዝብ መካከል ስልጣን ሊኖረው ይችላል። እንዲሁም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ወንጌል እንዲሁም ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ቤተ ክርስቲያን መልካም አሳብ ያለውና እነዚህንም በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የሚረዳ ሊሆን ይችላል። ከነዚህም ሁሉ አልፎ የእምነት መሪም ሊሆን ይችላል። ዳግም ካልተወለደ ግን እነዚህ ሁሉ ምንም ፋይዳ ስለሌላቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።
ኃጢዓትን ማድረግ ማለት መሳሳትና እግዚአብሔርን መበደል ብቻ አይደለም። ኃጢዓት ዓመጽ ነው፣ በፈጠረንና በሚወደን አምላክ ላይ ማመጽ፣ በቅዱስ ስራው ላይ ማመጽ፣ ለእኛ ባለው ዘለዓለማዊ እቅድ ላይ ማመጽ ነው። ኃጢዓት እግዚአብሔር የሰጠንን ፈቃዳችንን እና ነጻነታችንን ነጥቆ ለራሱ ፈቃድ ያስገዛናል። የኃጢዓት ውጤቱ ሞት ነው። ሮሜ 6፡23 አዳምና ሔዋን እንዳያደርጉ የታዘዙትን ጥሰው ኃጢዓት ባደረጉ ጊዜ ወዲያውኑ ነበር በእነርሱ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ጸጋ፣ ግርማና ክብር የተገፈፈው። ወዲያውኑ ነበር ራቁትነት የተሰማቸው። ምንም እንኳን በስጋ በዚህ ምድር ላይ መኖራቸው ቢቀጥልም፣ ከጌታ አምላክ ጋር የነበራቸው ግንኙነት፣ በኤድን ገነት የነበራቸው የክብር ሕይወት ግን ሊገምቱት በማይችሉት መንገድ ነበር የተለወጠው። ከፈጣሪ ተለዩ፣ ከኤድን ገነት ተባረሩ ወደዚያም እንዳይገቡ መንገዱ በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍና በኪሩቤል ተዘጋ። (ዘፍረት 3፡24) በምድር ላይ ባሉ በእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረው የሰው ልጅ እንጀራን የሚበላው በላቡ ወዝ እንዲሆን ተፈረደበት። ሊታመን የሚገባውን አምላክ እምቢ ብሎ የሰይጣንን ቃል ስላመነ ዛሬ በክርስቶስ የማያምኑ ሁሉ የሚተዳደሩት የዚህ ዓለም ገዥ በሆነው በዲያብሎስና በእርሱ በሚመሩ በወደቁ መላእክት ስር ነው። የሁሉ የበላይና ገዢ እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን በሰው ዓመጽ ምክንያት፣ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የክርስቶስ ያልሆነው ዓለም ሁሉ የሚተዳደረው በጨለማው ገዥ ስር ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን በመነሳቱ የኃጢዓት ዋጋ ተከፍሏል። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በማያወላዳ መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ገልጿል፣ እያንዳንዳችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን ከእርሱ ጋር የምንታረቅበትን መንገድ ጠርጓል። ይህን የወንጌልን የምስራች ሰምቶ የሚቀበል ሁሉ ከልዑል እግዚአብሔር በመንፈስ ዳግም ይወለዳል፣ በዲያብሎስ ከሚመራው የጨለማው ዓለም ወደ ዘለዓለማዊው የክርስቶስ መንግስት ይፈልሳል። ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ የመዳን መንገድ የለም። ብዙ ሃይማኖቶች፣ ብዙ ባህሎች፣ ብዙ ስርዓቶች አሉ፣ ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት የሚወሰደው መንገድ ግን የሚያልፈው የግድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው። በክርስቶስ ዳግም የተወለደ ሰው የዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ ነው፤ በዚህ ዓለም ይኖራል እንጂ ከሚጠፋው ከዚህ ዓለም አይደለም። ስለዚህም ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች በዚህ የጨለማው ዓለም ገዥና በተከታዮቹ ይጠላሉ። እነዚህ እውነቶች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይገልጻቸዋል፤
1)     በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፣ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ዮሐንስ 3፡16-18
2)    እርሱ ከጨለማ ስልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢዓትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
3)   የእርሱ ወደሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው፣ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከስጋ ፈቃድ፣ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ዮሐንስ 1፡11-13
4)   ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ያዕቆብ 1፡18
5)   ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፣ አሮጌው ነገር አልፎአል፣ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮ 5፡17
6)   ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው ቃልህንም ጠብቀዋል። ዮሐንስ 17፡6
7)    እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፣ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። ዮሐ 17፡14-15
8)   ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፣ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስላይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው ደቀ መዝሙርም ከመምህሩ አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። ዮሐ 15፡18-19
አንድ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲቀበል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእግዚአብሔር ዳግም ይወለዳል። ሰው ዳግም በሚወለድበት ጊዜ ቀድሞ ይኖርበት የነበረውን የኃጢዓትና የባርነት ህይወት ስለሚጠላውና በኃጢዓቱም ስለሚጸጸት ንስሃ ይገባል፣ በበደሉ ያዝናል፣ ይተክዛል፣ ከዚያም በኋላ አምላኩን ለማፍቀርና ለመታዘዝ ልቡን ያዘጋጃል። ይህ ንስሃ ይባላል። ያለ ንስሃ ዳግም ልደት የለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብሎ የሚያምን ሰው ከዲያብሎስ መንግስት ስር አምልጦ ወደሚያስደንቀው ወደ ክርስቶስ መንግስት ይፈልሳል፣ አዲስ ፍጥረት፣ ሰማያዊ ዜጋ ይሆናል። በአዲሱ ህይወት ውስጥ ለማደግ ደግሞ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ መኖር፣ አዲሱን ማንነቱን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ምግብ፣ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል፣ መመገብ፤ ከአምላኩ ጋር በጸሎት፣ በምስጋና፣ በመዝሙርና በአምልኮ እንዲሁም እንደርሱ ዳግም ከተወለዱ ሰዎች ጋር ህብረትን በማድረግ በአምላኩ ዘለዓለማዊ ቤተሰብ ውስጥ ያድጋል። በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው ልክ ፍጥረታዊ ህጻን እንደሚያድግ በመንፈሳዊ ህይወቱ ያድጋል፣ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ የሆኑ እውነቶችን በማወቅ ይጎለምሳል፣ መንፈሳዊ ፍሬን በእግዚአብሔር መንግስት ያፈራል። ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ልክ አዲስ ህጻን ወተትን ለማግኘት እንደሚፈልግና እንደሚያለቅስ የእግዚአብሔርን ቃል ለመመገብ ይናፍቃል፣ በራሱም ቢሆን ለመማር ጥረት ያደርጋል። ይህ ከዳግም ልደት ምልክቶች አንዱ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን እውነት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ “ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ህጻናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” 1ኛ ጴጥሮስ 2፡3
ታዲያ ወንድሜ፣ እህቴ አንተስ? አንቺስ? እርስዎስ? በኢየሱስ ክርስቶስ አምነህ ዳግም ተወልደሃል? ተወልደሻል? ተወልደዋል?  አዲስ ፍጥረት ሆነሃል? ሆነሻል? ሆነዋል? በክርስቶስ ዳግም ያልተወለዱ ሁሉ የዚህ ዓለም ህይወት ሲያበቃ ወደ ዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግስት አይገቡም። መጨረሻቸው የእግዚአብሔር ፍርድና ለዘላለም ከፈጣሪ ተለይቶ እሳቱ በማይጠፋ፣ ትሉ በማያንቀላፋ በእሳት ባህር ይሆናል። ዳግም ስለ መወለድህ፣ ስለ መወለድሽ፣ ስለ መወለድዎ እርግጠኛ ካልሆን፣ ካልሆንሽ፣ ካልሆኑ ዛሬውኑ ንስሐ ግቡ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉ። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ አምላክ ነው። የኃጢዓታችንን ዋጋ በሙሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍሏል፣ እርሱን ከተቀበልንም በኋላ ከኃጢዓት ባርነት ነጻ የሆነ ህይወት ለመኖር የሚያስችለንን መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል። ይህን ህይወት ጨርሰን ሳንሄድ ክርስቶስን ልንቀበል ያስፈልጋል። ከሞት በኋላ ንስሃ መግባትና ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበል ተስፋ የለም። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈው:
“ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ የብዙዎችን ኃጢዓት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢዓት ይታይላቸዋል።” ዕብራውያን 9፡27
ስለዚህ ሰበብ አንፈልግ። ዛሬ ነገ ስንል የምስራቹ ወንጌል አይለፈን!

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...