በሰለጠኑና ባለጸጎች አገሮችም ህዝብ በጩቤና በቆንጨራ ሲፋጅ!


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር የሚመለስበት ዘመን መቃረቡን ከሚያመለክቱን ነገሮች ውስጥ ዘመኑ የሚያስጨንቅ መሆኑ ነው። ከሚያስጨንቁት የዚህ የመጨረሻ ዘመን ባህርያት አንዱ የጦርነትና የጦርነት ወሬ መብዛት ነው። የሚያሳዝነው ግን ለመዋጋትና ለመገዳደል አንዱ በአንዱ ላይ እየተነሳ ያለው መንግስታት ብቻ አይደሉም። አድገዋል፣ በልጽገዋል፣ ተምረዋል፣ ሰልጥነዋል ተብለው በሚነገረላቸው እንደ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ካናዳም ሳይቀር ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ወንጀል በቁጥር እየበዛ መሆኑን ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ። የመገዳደል ችግሩ ጠብመንጃና ሽጉጥ ስለሆነ መንግስታት እነዚህን ለማገድና ለመቆጣጠር ብዙ እርምጃዎችን ወስደዋል፣ እየወሰዱም ነው። እነዚህን መሳሪያዎች በአብዛኛው ተቆጣጥረዋል ከሚባሉት አገሮች አንዷ እንግሊዝ ናት። በተያያዘውና በሌሎችም ተመሳሳይ ዜናዎች እንደምናነበው፣ ከዓለም የገንዘብ ማእከሎች በዋናነት በምትጠቀሰው በለንደን ከተማ ብዙ ሰው በጩቤ፣ በቢላዋና በቆንጨራ እየተገዳደለ ነው። በፈረንጆቹ ዓመት የመጨረሻ ሁለት ወራት ብቻ በእንግሊዝ አገር በቆንጨራ የተፈጸሙት ወንጀሎች 928 ሲሆን ከነዚህም መካከል 425 የተፈጸሙት በለንደን ነው። ይህ ሁኔታ ያስፈራቸው የለንደኑ ከተማ ከንቲባም በዚሁ በያዝነው የፈረንጆቹ ወር በከተማይቱ የሚደረገውን የቢላዋ ወይም ጩቤ ዝውውር ለመቆጣጠር አዲስ መመሪያ አውጥተዋል።
ስለ ክፉ ነገሮች ያለን ሃሳብ ብዙውን ጊዜ የሚወሰነው በሚደርሰን ዜና ነው። በባለጸጎቹ አገሮቹ ባሉ የዜና ምንጮች የሚያቀርቧቸው ብዙዎቹ ዜናዎች የእነርሱ አገሮች ሰላማዊ፣ የሰለጠኑ፣ ችግሮችን ሁሉ የሚፈቱት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንደሆነ ለማሳየት ይጥራሉ። በሌላ በኩል ግን ችግር፣ ወንጀልና ጦርነት የሚገኙት ደግሞ በአዳጊዎቹና ድሆቹ አገሮች እንደሆኑ ለማሳየት አይታክቱም። በዓለማችን ላይ ያሉትን ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል ስንመዝናቸው ግን፣ ባለጸግነት፣ ትምህርት ወይም ስልጣኔ የኃጢዓትን ኃይል ወይም የሰውን ክፋት አያስወግዱም። እንዲያውም ታሪክና ዛሬም በዓይናችን የምናየው መረጃ የሚያሳየን የሰው ልጅ በሰለጠነና በቴክኖሎጂ በተራቀቀ መጠን ስልጣኔውን የሚጠቀመው የከፉና ብዙ ህዝብን የሚጨርሱ መሳሪያዎችን ለመስራትና በስራ ላይ ለማዋል መሆኑን ነው። አንድ የአገራችን የወንጌል ሰባኪ ከብዙ ዓመታት በፊት ሲናገሩ፣ “የሰው ልጅ ሰለጠነ ከማለት ይልቅ ሰየጠነ ማለቱ ይቀላል” ብለው ነበር። በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት፣ ገንዘብን መውደድ እንዲሁም ክፋትና ጭካኔ በምድር ላይ እጅግ እየበዛ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል 2ኛ ጢሞቲዎስ ምእራፍ 3 የዚህን ዘመን ባህርይ በዝርዝር ይነግረናል። ፈሪሃ እግዚአብሔር በገንዘብ ስለተተካ፣ የሰው ልጅ ከአምላኩ ይልቅ ተድላንና ገንዘብን ስለወደደ ስግብግብነት ምድርን እንደ ሰደድ እሳት እያቃጠላት ነው። በህዝብ መካከል ጭካኔ፣ በመንግስታት መካከል ጦርነት የሚሆነው እነዚህ የተጠቀሱት አመጻዎች ፍሬ ሲያፈሩ ነው። የሰውን ዘር ከዚህ ሁሉ ጥፋት ሊያድነው የሚችለው የበለጠ ገንዘብ፣ ተጨማሪ ምርት ወይም ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የወንጌል የምስራች ተሰብኮአል። እውነተኛ ሰላም፣ እረፍትና ደስታ የሚገኘው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በፍቅር በመኖር እንጂ ሃብትን በማግበስበስ ሊረካ የማይችለውን የስጋንና የከንቱ አእምሮን ምኞች በመከተል አይደለም። ይህን የተረዳው ዳዊት በመዝሙረ ዳዊት በ2ኛው ምእራፍ ላይ የምድር ነገስታትና መሪዎች በእግዚአብሔር እውነትና ስርዓት ላይ በማመጽ እንደሚነሱና በራሳቸው መንገድ የሰውን ዘር እነርሱ ራሳቸው አይተውት ወደማያውቁት ምናባዊ የብልጽግና፣ የእኩልነትና የሰላም ዓለም ለመምራት እንደሚሞክሩ አመልክቷል። በእውነትም የዚህ ሰለጠነ የሚባለው ዓለም መሪዎች ዛሬ እውነተኛ ነጻነትን፣ ሰላምንና ብልጽግናን ለሰው ዘር ሊያግናጽፍ የሚችለውን ብቸኛውን የፈጣሪን የፍቅርና የእውነት ስርዓት ህጎች በማፈራረስና በመሻር ላይ ናቸው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስና መንግስቱን እስኪመሰርት ድረስ ይህ የምናየው ጥፋት እየቀጠለና እየባሰ ይሄዳል እንጂ አይቆምም። የሰው ዘር ዋናው ችግሩ ኃጢዓት ብቸኛ መፍትሔው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ለዚህ ነው ዳዊት በዚያው በ2ኛው ምእራፍ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ለምድር ነገስታትና መሪዎች ሁሉ የተናገረው፡
 “አሁንም እናንት ነገሥታት ልብ አድርጉ፣ እናንት የምድር ፈራጆችም ተገሰጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሳጹን ተቀበሉ፣ ጌታ እንዳይቆጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ። መዝሙር 2፡10-12
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል። ይህ እውነት ለግለሰቦችም፣ ለመንግስታትም፣ ለተማሩም ላልተማሩም፣ ለሰለጠኑም፣ ላልሰለጠኑም እውነት ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !


አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !
ውድ የፌስቡክ ባልንጀሮቼና ወገኖቼ፣ ከብዙዎቻችሁ ጋር በአካል ባንተዋወቅም፣ ባልንጀሮቼ ስለሆናችሁ በጣም ደስ ይለኛል። እናንተንም ባልንጀሮች አድርጎ ስለሰጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ሰው መሆን እጅግ አስደናቂ ነው። ምንም እንኳን የምንኖረው በተለያዩ አገሮች፣ ከተማዎች፣ ሰፈሮችና ሁኔታዎች ቢሆንም በዚህ የሩቅ መገናኛ መድረክ እንኳን ተዋውቀን ባልንጀሮች በማፍራታችን ደስ ይለናል። ባልንጀራ የሆንነው ታዲያ በአጋጣሚ አይደለም። እኛ በማናውቀው መንገድ እርስ በርስ እንድንፈላለግ፣ እንድንተዋወቅ የሚያደርግ፣ በሰማይና በምድር ሁሉን የሚገዛ ልዑል እግዚአብሔር ነው። እርሱ አጋጣሚ በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ ሁሉ እየሰራ እንድናውቀውና ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይሻል።
ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከባልንጀሮቻችን ጋር መጫወት ስንችል ደግሞ የምንካፈለው ነገር ሲኖረን ደስ ይለን ነበር። በዚህ በፌስቡክ ለባልንጀሮቼ ምን ላካፍላቸው ብዬ ሳስብ ለእኔ ደግሞ እጅግ ከፍተኛና አስቸኳይ ነው ብዬ የማስበው አንድ ነገር ነው። ዛሬ የምጽፍላችሁም ስለዚህ አንድ ጉዳይ ነው። ይህች የህይወት ዘመናችን ሳናስባት ቶሎ ታልፋለች። የብሉይ ኪዳኑ ጻድቅ ሰው ኢዮብ ስለ ሕይወቱ እንዲህ ብሎ ተናገረ: “ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይቸኩላል፣ ያለ ተስፋም ያልቃል” ኢዮብ 7:6።  የእናንተን ባላውቅም እኔ ግን እንደ ኢዮብ ዘመኔ እጅግ እየፈጠነ ሄዶ ማድረግ ያለብኝን ሳላደርግ እንዳያልፍብኝ አስባለሁ። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ከዚህ ምድር ስንሄድ የምኖርበት የዘላለም መኖሪያችን የት ይሆን። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህች አጭር የምድር ዘመናችን በኋላ ዘለዓለም እንዳለ ያረጋግጥልናል። ለዚህ ነው ስናስብና ስናቅድ ልክ ሺህ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ እንደሚኖር የምናስበውና የምንደክመው። የምንኖረው ሰባ፣ ሰማንያ ወይም ዘጠና ቢሆንም ፍላጎታችን፣ እቅዳችን፣ ጭንቀታችንና ጥረታችን ግን ዘላለም እንደሚኖር ሰው ነው። ምክንያቱም የተፈጠርነው ለዘለዓለም እንድንኖር ነው። ወደድንም ጠላንም፣ አመንንም አላመንንም ከሞት በኋላ የዘላለም ህይወት አለ። ጥያቄው ግን ያንን ዘላለም የምናሳልፈው የት ነው፣ እንዴት ነው የሚለው ነው። ሞት የመጣው በኋላ ሲሆን የሞት ምንጩም ኃጢዓት ነው። በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጅ ለኃጢዓት መድኃኒት የለውም። ኃያሉም፣ ደካማውም፣ ድሃውም ባለጠጋውም፣ የተማረውም ያልተማረውም፣ ሁሉ የኃጢዓት ባሪያና በሞት ፍርሃት ጥላ ስር የሚኖር ነው። በግል ህይወታችንም ሆነ በቤተሰብ፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በግለሰቦችም ሆነ በመንግስታት መካከል ላለው ችግርና ቀውስ ሁሉ ምንጩ ኃጢዓትና የኃጢዓት ፍሬዎች ናቸው።  ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ውስጥ የምናመልጥበት መንገድ አለ።
ይህ የምንኖርበት ጊዜ የመጨረሻው ዘመን ነው። የሰማይና የምድር ወይም የሰው ዘር መጨረሻ ሳይሆን የዘመን መጨረሻ ነው። ይህን የሚናገሩት እኔና የዚህ ዘመን አዋቂዎች ሳይሆኑ እግዚአብሔር አምላክ በእርግጥ የላካቸውና የቀባቸው መጽሐፍ ቅዱስንም ጽፈው ያቆዩልን ነቢያትና ሐዋርያት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።  ይህ ዘመን በአንድ በኩል የተመሰቃቀለ፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ሞትና ስቃይ የሞላበት ነው። ትምህርት፣ እውቀት፣ ስልጣኔ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ሃብት እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም ቢባልም የጦም አዳሪው፣ የህመምተኛው፣ የከፋው፣ የመረረው፣ የስደተኛው፣ ግራ የተጋባው፣ የቁስለኛው፣ ስራ ያጣውና፣ የከርታታውም ቁጥር እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም። እኛም እያንዳንዳችን ከነዚህ በአንዱ ወይም በሌላው ተጎድተን እናዝናለን፣ እንቆዝማለን፣ አንዳንዴም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።  በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እያለቀ ያለው ዘመን ወርቃማ ዘመንም ነው፣ ምክንያቱም እኛ ልንኖርበት የምንችል ሌላ ዘመን አልተሰጠንም። ከዚህ በላይ ግን ይህን ዘመን ወርቃማ የሚያደርገው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የምስራቹን ወንጌል ሰምተንና አምነን የዘለዓለምን  ሕይወት ተስፋ ልንወርስ የምንችልበት ዘመን መሆኑ ነው። ይህ የጸጋ ዘመን የጀመረው ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንደ ሰው ሥጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም በመምጣት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክነቱን አሳይቶ፣ ያለ ኃጢዓት ኖሮ፣ በመጨረሻም የእኛን የኃጢዓት እዳ ለመክፈል በእኛ ምትክ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን በመነሳቱ ምክንያት ለእኛ፣ በኃጢዓታችንና በተሳሳቱ ምርጫዎቻችን ምክንያት የዘለዓለም ሞት ጥላ ላጠላብን ለሰው ልጆች የምስራቹን ወንጌል በላከ ጊዜ ነው። ዘመኑም የሚደመደመው ያ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም መንግስቱን ለመመስረት ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ነው። ያ ቀን እጅግ ተቃርቧል።
ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ሲሰበክ የቆየው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንደሚነግረን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እያንዳንዳችንን ይወደናል። በሌላ በኩል ግን ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ጻድቅ እና ፍጹም እውነተኛም ስለሆነ ኃጢዓትን ይጠላል። እኛ የሰው ልጆች ደግሞ መልካሙን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና ህይወትን የምንመኝና የምንጥር እንኳን ብንሆንም፣ ከጋራ አባታችን ከአዳምና ከእናታችን ከሔዋን ጀምሮ በኃጢዓት ውስጥ ተዘፍቀናል። “ኃጢዓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል ሐዋርያው ዮሐንስ (1ኛ ዮሐንስ 1:8)። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅሩ፣ ምህረቱና ጸጋው ከእና ኃጢአት በላይ እጅግ ታላቅ ስለሆነ፣ የእኛን በደል በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ በእኛ ፈንታ እርሱ እንዲሰቃይና በመስቀል እንዲሞት ፈቀደ። ስለኛ ኃጢዓት ሞተ እንጂ እርሱ ኃጢዓት አልነበረበትምና ሞት ሊይዘው አልቻለም። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሳኤው ኃጢዓትንም፣ ሞትንም፣ ሰይጣንንም ድል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ጥል አስወገደ። የምስራቹ ወንጌል ይህ ነው። የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ያለብን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ኃጢዓተኛ መሆናችንን አምነን የሚወደንን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን መቀበል ነው።
እባክህ ዛሬ ሃሳቤን የያዘው ይህ አይደለም፣ ይህ ነገ ይደርሳል አትበሉ። አዎን እያንዳንዳችን የየራሳችን ችግሮችና ሸክሞች አሉብን። ግን እኮ ወገኖቼ ከሁሉም የሚበልጠው የነፍሳችን ነገር ነው። የጌታችንን ትንሳኤ፣ ፋሲካን ካከበርን አንድ ሳምንት ሆነ። ከዚህም በፊት ምናልባት ይህን ወንጌል ሰምተን ችላ ብለነው ሊሆን ይችላል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ይጠራናል። ነገ አንበለው። የነፍሳችንን ነገር አናዘግይ። ሌላው ሁሉ ይደርሳል ወይም ያልፋል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ዛሬ ተቀበለው፣ ተቀበይው፣ ተቀበሉት። ብዙ ሌላ ስጦታ ቢኖረኝነና ብሰጣችሁ ደስ ባለኝ። ነገር ግን ለእኔም ሆነ ለእናንተ ታላቁ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ስጦታ ከእርሱ ጋር ልንኖርበት የምንችለው የዘለዓለም ህይወት ነው። የዚህ ሕይወት  ብቸኛው መንገድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ልናምነውና ልንቀበለው የተሰጠንም ቀን ዛሬ ነው። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

በሶሪያ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተባለው ጦርነት ዘገየ እንጂ የቀረ አይመስልም


ባለፉት ሶስት ቀናት በብዙ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሲናፈስ የቆየውና በዚህ ድረ ገጽም ላይ የተዘገበበት አሜሪካና አጋሮቿ ከሩሲያ ጋር በሶሪያ ላይ ሊዋጉ ነው የሚለው ዜና ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) በተናፈሱት አንዳንድ ዜናዎች መልኩን የቀየረ ይመስላል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሐሙስ እለት በትዊተር በላኩት መልእክት፣ “ሶሪያን የምንመታው ቶሎም፣ ቀስ ብሎም ሊሆን ይችላል” በማለት ከአንድ ቀን በፊት የዜና ምንጮችን ሁሉ ኡኡ ካሰኘውና ሩሲያን በማስፈራራት “አዳዲስ፣ የተራቀቁና ቆንጆ ሚሳኤሎች እየመጡ ነውና ተዘጋጅ” ብለው ከላኩት መልእክት ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ይመስላል። የአውሮፓ የአየር ትራፊክና ደህንነትን የሚቆጣጠረው ድርጅትም በ72 ሰዓታት ውስጥ ጦርነት ሊነሳ ይችላል በማለት የሲቪል አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢ በረራ ከማድረጋቸው በፊት ሁኔታውን እንዲያጤኑ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። አንዳንድ አየር መንገዶችም በዚህ ምክንያት ወደ ሶሪያ፣ ሊባኖስ አካባቢው የሚሄዱ በረራዎችን እንደሰረዙ የዜና ምንጮች አመልክተዋል።ይሁን እንጂ በሶርያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በአሜሪካ በሚመራው የምእራባውያን ህብረት እና በሩሲያ፣ በሶሪያና አጋሮቿ መካከል ያለው ውጥረት ምንም መፍትሔ አላገኘም። የጦርነት አደጋው ለጊዜው ጋብ ያለ ይምሰል እንጂ ዓለማችን አሁንም በድንገት አሻቅቦ ወደ አጥፊ የኑክሊየር እልቂት ሊያስገባ ከሚችለው የጦርነት ገደል አፋፍ ላይ ገና አልተመለሰችም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት  ሶሪያን በሚሳኤልና በቦምብ ለመደብደብ እስካሁን ትእዛዝ ያልሰጡት የአገራቸውን የሶሪያ ስትራቴጂ አስመልክቶ በአሜሪካው ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ካውንስል ውስጥ ባሉት ከፍተኛ ባለስልጣኖች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ዘግበዋል። የራሳቸው የፕሬዝደንቱ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስም ሐሙስ እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ይህንኑ አመልክተዋል። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከአሜሪካ ጋር በማበር በሶሪያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እንዲያስችላቸው የመንግስታቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) ሰብስበው ለውሳኔያቸው ድጋፍ እንዳገኙ ተመልክቷል። ከዚህም አንድ ቀን ቀደም ብለው የአገራቸው የባህር ኃይል ወደ ሶሪያ እንዲያቀና ትእዛዝ መስጠታቸው በብዙ ምንጮች ተዘግቧል። ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ሶሪያን ለመምታት በቅድሚያ ዝግጁነቷን ያሳየችው የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ማክሮን ደግሞ በበኩላቸው ሲናገሩ፣ ባለፈው ቅዳሜ በሰላማዊ ህዝቦች ላይ ተፈጽሟል የተባለው የመርዛማ ንጥረ ነገር ጥቃት የተፈጸመው በሶሪያ መንግስት ለመሆኑ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለታቸው ተዘግቧል። የሶሪያ መንግስትና ሩሲያ በበኩላቸው የተባለው ጥቃት እንኳንስ በሶሪያ መንግስት ሊፈጸም ይቅርና ጭራሹኑ ያልተከሰተ፣ አሜሪካ በምትደግፋቸው ሽብርተኞች በተዘጋጀና በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ የውሸት ቪዲዮ የተፈጠረ ወሬ ነው ሲሉ እያስተባበሉ ናቸው። እነዚህ የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በአሜሪካና አጋሮቿ ድጋፍ የተመሰረቱ ድርጅቶች ከዚህም ቀደም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የመርዛማ ጭስ ጥቃቶችን በመፈጸምና ያልተፈጸመውም ተፈጸመ የሚሉ ዜናዎችን በማናፈስ አሜሪካ የሶሪያን መንግስት በቀጥታ እንድትወጋ መሞከራቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረውና ሩሲያንና አሜሪካን በቀጥታ በማጋጨት አሻቅቦ ወደ ኑክሊየር ውድመት ሊያመራ ይችላል የሚባለው ሁኔታ ምንጩ በሶሪያ ውስጥ የተከሰተ የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ በብዙ የምእራባውያን መንግስታትና የዜና ምንጮች ይቅረብ እንጂ፣ ዋነኛው ጠብ በአሜሪካና በምእራባውያን አገሮች ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ዓለም አቀፋዊ የኃይል ፉክክር ነው። በሶሪያ የተፈጠረው ጦርነት መነሾውም አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉና የማትፈልጋቸውን መንግስታት ለመገልበጥ ስታደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬ መሆኑን ለሁኔታው ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ደግሞ ሶሪያ ሁለት የሩሲያ የጦር ሰፈሮች ያሉባት የመካከለኛው ምስራቅ አገር መሆኗ ነው። ከሩሲያ ጋር የሚተባበረውን መንግስት በመገልበጥ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ በዚያ አካባቢ የእግር መርገጫ እንዳይኖራት ለማድረግና ለማዳከም መጣራቸው ለመረዳት አዳጋች አይደለም። በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄፍሪ ሳክስ ለምሳሌ፣ ሐሙስ አፕሪል 12 ላይ CNBC በሚባለው የአሜሪካ ቴሌቪዝን መረብ ላይ ቀርበው ሲናገሩ ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረው ዓለም አቀፍ ውጥረት ምንጩ የአገራቸው የስለላ ድርጅት ከሳውዲ አረቢያ ጋር በመተባበር ከብዙ ዓመታት በፊት የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በስውር ያደረገውና የከሸፈበት ሙከራ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ይህ ዛሬ በሶሪያ ሰበብ በዓለም ላይ አንዣቦ የሚገኘው ከፍተኛ የጦርነት አደጋ በ1962 እኤአ በሩሲያና በሶቪየት ህብረት በኩባ ላይ ተፈጥሮ ከነበረው አደጋ ጋር የሚቀራረብ እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎችን የፖለቲካ ታዛቢዎች ያመለክታሉ። ራሳቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንትም በዚሁ ሳምንት በትዊተር በላኩት መልእክት ላይ አገራቸው ዛሬ ከሩሲያ ጋር ያላት መጥፎ ግንኙነት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን እንኳን ከነበረው የከፋ እንደሆነ አመልክተዋል። ስለዚህ ወገኖች፣ አሜሪካንና ሩሲያን ወደ ኑክሊየር ጦርነት ሊያስገባ የሚችለው ውጥረት እንደተባለው በሶስት ቀን ውስጥ አይፈንዳ እንጂ መፍትሔን አላገኘም።  የጦር መርከቦች፣ ሰራዊትና መሳሪያዎች ወደ ቦታው እየተንቀሳቀሱ ነው፣ ብዙዎችም በአካባቢው ተፋጥጠዋል። በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ተወካይ የሆኑት ቫሲሊ ኔቤንዚያ ሐሙስ አፕሪል 12 ላይ ሲናገሩ፣ የሩሲያ ጦር በሶሪያ ስላለና ከዋሽንግተን የሚነፍሱት ወሬዎችም አስጊ በመሆናቸው ምክንያት እንደተባለው አሜሪካ ሶሪያን ከደበደበች አገራቸውና አሜሪካ በቀጥታ ሊዋጉ የሚችሉበትን አደገኛ ሁኔታ መኖሩን አልሸሸጉም። ምናልባትም ሰላማዊ መፍትሔ ይገኝ ይሆናል በማለት እኒሁ የሩሲያው ተወካይ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አርብ አፕሪል 13 ላይ እንደገና እንዲሰበሰብ ጠይቃለች። የድርጅቱ ዋና ጸሃፊም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ሪፖርት ያቀርባሉ ሲል ዋሽንግተን ፖስት የተባለው ጋዜጣ ምንጮች አመልክተዋል። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አሜሪካና አጋሮቿ ሶሪያን በቦምብና በሚሳኤል ሊደበድቡ እየተዘጋጁ ነው


ባለፈው ቅዳሜ ማታ፣ መጋቢት 29 (እኢአ) ጉታ በሚባለው በደማስቆ አጠገብ በሚገኝ ከተማ የሶሪያ መንግስት በሰላማዊ ህዝብ ላይ የመርዛማ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ ብዙ ሰዎችን ገድሏል የሚል ዜና ባለፈው እሁድ አፕሪል 8 በምእራቡ ዓለም ዜና አውታሮች ተሰራጭቷል። ዜናው ገና እንደተሰማና ገና በቂ መረጃም ከመገለጡ በፊት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ለዚህ ጥቃት ተጠያቂዎቹ የሶርያ መንግስትና አጋሮቹ ሩሲያና ኢራን ናቸው በማለት፣ በተለይም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያውን ፕሬዝደንት በስም በመጥቀስና በመንቀፍ መናገራቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ነው እየተባለ በሶሪያ ሲነጉድ የነበረው ጦርነት በቀላሉ ወደ ዓለም ጦርነት ሊያመራ ወደሚችልበት የማሻቀብ ደረጃ መድረሱን ያሳያል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ከየቦታው እየተሰሙ ነው።
ይህ አጭር መልእክት ከተዘጋጀበት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ሲል የአውሮፓው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ድርጅት በሚቀጥሉት 72 ሰዓታት የሰሜኑ አትላንቲክ የመከላከያ ድርጅት (አሜሪካና አጋሮቿ)  በሶሪያ ላይ የሚሳኤልና ሌሎችም የአየር ጥቃቶች ሊፈጽሙ ስለሆነ የህዝብ ማመላለሻና ሌሎችም የሲቪል አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ ከመብረራቸው በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ የጦር መርከቦች ሶሪያ ወደምትገኝበት ምስራቅ የሚዲትራኒያን ባህር እያመሩ ነው የሚሉ ብዙ ዜናዎችም ከየአቅጣጫው እየነፈሱ ነው። የሩሲያ የጦር ኃይልና መሳሪያዎች በራሷ በሶሪያና በሜዲትራኒያን ባህርም ላይ ሲገኙ፣ ቻይና ደግሞ የባህር ኃይሏ ሩሲያን ለመደገፍ ወደዚያው እንዲያመራ አዝዛለች የሚል ዜናም እየነፈሰ ነው።
በ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ የተጀመረው ይህ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰላማዊ ህዝብ ያለቀበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተሰደደበትና የተፈናቀለበት ጦርነት የአረብ ጸደይ ተብሎ ተነስቶ የነበረው በአረብ አገሮች የቆዩ መንግስታትን የመገልበጥ ስራ አካል እንደሆነ ብዙ ሲዘገብበት ቆይቷል። ከ2014 ጀምሮ ግልጽ እየሆነ የመጣ ሌላው ነገር ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ አሜሪካና አጋሮቿ እንደፈለጋቸው በየአገሩ መንግስታትን ይገለብጣሉ በማለት ስታማርር የቆየችው ሩሲያ የጦር ሰፈሮቿ ያሉባት ሶሪያ እንደ ሊቢያ፣ እንደ ኢራቅና እንደ አፍጋኒስታን እንድትፈራርስ ባለመፈለጓ የአገሩን መንግስት ለመርዳት በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ውስጥ መግባቷ ነው። ይህን ተከትሎ፣ የሶሪያ መንግስት ባይጠይቃቸውም፣ አሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ በአንድ በኩል የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ የሚዋጉ ሽምቅ ተዋጊዎችን ሲረዱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይሲስን እንዋጋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተለያዩ መልእክቶች ላስተላልፍ እንደሞከርሁት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም ላይ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነትን ይዘው የቆዩት በአሜሪካ የሚመሩት ምእራባውያኑ ኃይሎች የቀዝቃዛው ጦርነት ከበቃና ሶቪየት ሕብረት ከፈራረሰች በኋላ ተቀናቃኝ የለብንም በሚል ስሜትና ዲሞክራሲን እናስፋፋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ በብዙ አገሮች ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ከርመዋል። ይህ ያስቆጣት ሩሲያ ደግሞ የዩጎዝላቪያ መፈራረስ፣ የኢራቅ ጦርነት፣ ማቆሚያ ያጣው የአፍጋኒስታን ጦርነት፣ የሊቢያ መፈራረስና የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት የዚህ የምእራባውያኑ ማን አለብኝነት ውጤት ነው በማለት ታማርራለች። ይህ ውጥረት ስር ሲሰድ ከቆየ በኋላ በ2014 ላይ አሜሪካ ቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል የነበረችውን የዩክሬንን መንግስት የገለበጠ አብዮትን በመደገፏ፣ ሩሲያ የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ጓሮዬ እንዲጠጋ አልፈቅድም በማለት በመረረ መንገድ ተቃወመች። የምእራባውያኑ ወደ ዩክሬን መግባት በዚያው በዩክሬን በምትገኘው ክራይሚያ በምትባለው ግዛት ያለውን የባህር ኃይሏን ቦታ ለማሳጣትና ግዛቷንም ለመክበብ ነው በማለት የሰጋችው ሩሲያ በጊዜው በኑክሊየር መሳሪያ በማጥቃትም ጭምር የምእራባውያኑን ወደ ዩክሬን ለመግባት መሞከር ለማቆም ወስና እንደነበር መረጃው ያላቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህን እና ሌሎችንም በምእራባውያኑ አገሮችና በሩሲያ፣ በቻይና፣ በኢራን፣ በሶሪያና፣ በቤኔዙዌላ፣ በሰሜን ኮሪያ ወዘተ መካከል ያሉትን ውጥረቶች በተመለከተ ባለፉት ጊዜያት ሰፋ ያሉ ትንተናዎችን አቅርቤያለሁ።
አሁን በሶሪያ ላይ እያንዣበበ ያለው ሁኔታ በቀላሉ ሊያሻቅብና በታላላቆቹ አገሮች፣ ማለትም በዋናዎቹ ባለኑክሊየር መሳሪያ ባለቤቶች በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ወደሚፈጸም የቀጥታ ጦርነት ሊለወጥ እንደሚችል ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ። የዚህም ዋነኛው ምክንያት በሶሪያ የሩሲያና የኢራን ጦር መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ግጭት ለብዙ ዓመታት በምእራባውያኑና በሩሲያ፣ መካከል በየቦታው ሲገነባ የኖረው ውጥረት ሊፈነዳ መሆኑን ስለሚያመለክትም ነው። እንደ ተገመተው ይህ የሶሪያ ጦርነት አሜሪካንና አጋሮቿን ከሩሲያና አጋሮቿ ጋር በቀጥታ ወደማዋጋት ከደረሰ ምናልባት በትንቢተ ኢሳይያስ ምእራፍ 17 ላይ እና በትንቢተ ኤርምያስ 43:23 እስከ 26 ስለ ደማስቆ መደምሰስ የተጻፉት ትንቢቶች ፍጻሜ ሊሆን ይችላል በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስተማሪዎች ይጠቁማሉ። ያለንበት ዘመን የወንጌል መሰበክና የጸጋ ዘመን ማብቂያና የጌታ ኢየሱስ ዳግም ምጽዓት አጥቢያ ስለሆነ ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ መስማታችን የግድ ነው። አሁን በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ግን ከመቼውም ዘመን ይልቅ እጅግ አደገኛ ስለሆነ፣ ምናልባትም ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ምድር የኑክሊየር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚሉም ብዙ ናቸው። ምናልባትም ይህ ውጥረት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ለሚገለጸው ለሃሰተኛው መምጣት መንገድ የሚጠርግ ሊሆን ይችላል የሚሉ የትንቢት አስተማሪዎች ጥቂት አይደሉም። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የመለከት ድምጽ ድረ ገጽ በከፊል በስራ ላይ ዋለ

የመለከት ድምጽ ድረ ገጽ በከፊል በስራ ላይ ዋለውድ ወገኖቼ፣ ምናልባት እንደ ሰማችሁት እንደዚህ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች እስካሁን በነጻ የሚሰጡት አገልግሎት በዚሁ መንገድ ላይቀጥል ይችላል። ስለዚህም የመለከት ድምጽ አገልግሎትም የራሱ የሆነ ድረ ገጽ ስላስፈለገው ባለፉት ብዙ ወራት ሲታቀድና ሲገነባ ከቆየ በኋላ አሁን በከፊል በስራ ላይ ውሏል። ይህ ድረ ገጽ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት የሚመለከቱ መልእክቶች፣ ዜናዎችና ትንተናዎችን፣ ትምህርታዊ ጽሁፎች፣ መንፈሳዊ መዝሙሮችና ቪዲዮ የሚቀርቡበት ይሆናል። ድረ ገጹ አሁንም በግንባታ ላይ ስላለ ከላይ ከተጠቀሱት አንዳንዶቹ ይዘቶች ገና በስራ ላይ አልዋሉም። ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የቀረቡ ጽሁፎችን፣ የመለከት ድምጽ መጽሔት ያለፉ እትሞችን እና ትንቢት ነክ ዜናዎችን በድረ ገጹ ላይ አቅርበናል። እንዲሁም ከዚህ በፊት በገበያ ላይ ያልዋሉ ከ20 የሚበልጡ በዚህ አገልግሎት ፕሬዝደንት የተደረሱና የተዘጋጁ መዝሙሮችን በማዳመጥ ጌታን እንድታመልኩት፣ እንድትጽናኑና እንድትበረታቱ ተጋብዛችኋል። አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጅታችን ስላልተጠናቀቀ ለጊዜው እንድትታገሱን እንጠይቃለን። የድረ ገጹ አድራሻ: http://www.voiceoftrumpet.org (የመለከት ድምጽ አገልግሎት) ነው።

የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ስልጣን በመጋፋት አየሩን ለመለወጥ እየጣረ ነው

የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ስልጣን በመጋፋት አየሩን ለመለወጥ እየጣረ ነው
ታላላቆቹና ባለጸጎቹ አገሮች የምድርን አየር እንደፈለጉት በመለዋወጥ ሲያሻቸው ዝናብ፣ ሲፈልጉ ማእበል፣ ሳይፈልጉ ደግሞ ድርቅ የሚያስነሱበት ቴክኖሎጂ አላቸው የሚለው ዜና አዲስ አይደለም። የአሜሪካ መንግስት ምክር ቤት በሰፊው ተወያይቶበት ችላ ብሎ የተወው ነገር ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰው አሁንም ይህ መረጃ የለውም ብዙው ደግሞ እውነት ነው ብሎ ለመቀበል አይፈልግም። ሰው የእግዚአብሔርን ስልጣን በዚህና በሌሎች መስመሮችም መጋፋት ከጀመረ ውሎ ቢያድርም የዚህ ዓይነቱ ስራ የመጨረሻ ውጤቱ ጥፋት ነው።  ስለ ቴክኖሎጂውና ስለ ሰው ድፍረት ጥርጥሩ አሁንም ላለን ሰዎች የተያያዘው ዜና ይህ በምእራቡ ዓለም የተጀመረው አየርን የመለወጥና ሰው ሰራሽ ዝናብ የማዝነብ ስራ ዛሬ ደግሞ ወደ በቻይና እንደ ተስፋፋ ያመለክታል። አስተያየት ከመስጠት በፊት የተያያዘውን ዜና በጥሞና አንብቡት።

በጣሊያን ዛሬም የሚገኘው ጌታ የተከፈነበት ነው የሚባለው የቱሪኑ የተልባ እግር ልብስ ታሪክና የክርስቶስ አካል ይህን ይመስል ነበር ተብሎ የተሰራው ቅርጽ

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት፣ በአካል በምድር የነበረበትን ሁኔታ፣ መሰቀሉን፣ መሞቱንና ትንሳኤውን በተመለከተ ታሪካዊ፣ የአርኪዎሎጂና ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ ዛሬም በጣሊያን ያለው የቱሪኑ የከፈን ጨርቅ ታሪክ የሚያስደንቅ ነው። ይህን ማገናኛ በመጫን መረጃውን አንብቡ። በጣሊያን ዛሬም የሚገኘው ጌታ የተከፈነበት ነው የሚባለው የቱሪኑ የተልባ እግር ልብስ ታሪክና የክርስቶስ አካል ይህን ይመስል ነበር ተብሎ የተሰራው ቅርጽ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...