ባለፉት ሶስት ቀናት በብዙ የዓለም መገናኛ
ብዙኃን ሲናፈስ የቆየውና በዚህ ድረ ገጽም ላይ የተዘገበበት አሜሪካና አጋሮቿ ከሩሲያ ጋር በሶሪያ ላይ ሊዋጉ ነው የሚለው ዜና
ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) በተናፈሱት አንዳንድ ዜናዎች መልኩን የቀየረ ይመስላል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሐሙስ እለት በትዊተር
በላኩት መልእክት፣ “ሶሪያን የምንመታው ቶሎም፣ ቀስ ብሎም ሊሆን ይችላል” በማለት ከአንድ ቀን በፊት የዜና ምንጮችን ሁሉ ኡኡ
ካሰኘውና ሩሲያን በማስፈራራት “አዳዲስ፣ የተራቀቁና ቆንጆ ሚሳኤሎች እየመጡ ነውና ተዘጋጅ” ብለው ከላኩት መልእክት ወደ ኋላ ያፈገፈጉ
ይመስላል። የአውሮፓ የአየር ትራፊክና ደህንነትን የሚቆጣጠረው ድርጅትም በ72 ሰዓታት ውስጥ ጦርነት ሊነሳ ይችላል በማለት የሲቪል
አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢ በረራ ከማድረጋቸው በፊት ሁኔታውን እንዲያጤኑ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። አንዳንድ አየር
መንገዶችም በዚህ ምክንያት ወደ ሶሪያ፣ ሊባኖስ አካባቢው የሚሄዱ በረራዎችን እንደሰረዙ የዜና ምንጮች አመልክተዋል።ይሁን እንጂ
በሶርያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በአሜሪካ በሚመራው የምእራባውያን ህብረት እና በሩሲያ፣ በሶሪያና አጋሮቿ መካከል ያለው ውጥረት
ምንም መፍትሔ አላገኘም። የጦርነት አደጋው ለጊዜው ጋብ ያለ ይምሰል እንጂ ዓለማችን አሁንም በድንገት አሻቅቦ ወደ አጥፊ የኑክሊየር
እልቂት ሊያስገባ ከሚችለው የጦርነት ገደል አፋፍ ላይ ገና አልተመለሰችም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሶሪያን በሚሳኤልና በቦምብ ለመደብደብ እስካሁን ትእዛዝ ያልሰጡት የአገራቸውን
የሶሪያ ስትራቴጂ አስመልክቶ በአሜሪካው ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ካውንስል ውስጥ ባሉት ከፍተኛ ባለስልጣኖች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች
መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ዘግበዋል። የራሳቸው የፕሬዝደንቱ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስም ሐሙስ እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ
ላይ ይህንኑ አመልክተዋል። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከአሜሪካ ጋር በማበር በሶሪያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እንዲያስችላቸው
የመንግስታቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) ሰብስበው ለውሳኔያቸው ድጋፍ እንዳገኙ ተመልክቷል። ከዚህም
አንድ ቀን ቀደም ብለው የአገራቸው የባህር ኃይል ወደ ሶሪያ እንዲያቀና ትእዛዝ መስጠታቸው በብዙ ምንጮች ተዘግቧል። ከአሜሪካ ጋር
በመተባበር ሶሪያን ለመምታት በቅድሚያ ዝግጁነቷን ያሳየችው የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ማክሮን ደግሞ በበኩላቸው ሲናገሩ፣ ባለፈው ቅዳሜ
በሰላማዊ ህዝቦች ላይ ተፈጽሟል የተባለው የመርዛማ ንጥረ ነገር ጥቃት የተፈጸመው በሶሪያ መንግስት ለመሆኑ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለታቸው
ተዘግቧል። የሶሪያ መንግስትና ሩሲያ በበኩላቸው የተባለው ጥቃት እንኳንስ በሶሪያ መንግስት ሊፈጸም ይቅርና ጭራሹኑ ያልተከሰተ፣
አሜሪካ በምትደግፋቸው ሽብርተኞች በተዘጋጀና በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ የውሸት ቪዲዮ የተፈጠረ ወሬ ነው ሲሉ እያስተባበሉ ናቸው።
እነዚህ የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በአሜሪካና አጋሮቿ ድጋፍ የተመሰረቱ ድርጅቶች ከዚህም ቀደም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የመርዛማ
ጭስ ጥቃቶችን በመፈጸምና ያልተፈጸመውም ተፈጸመ የሚሉ ዜናዎችን በማናፈስ አሜሪካ የሶሪያን መንግስት በቀጥታ እንድትወጋ መሞከራቸው
ሲዘገብ ቆይቷል።
ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረውና ሩሲያንና
አሜሪካን በቀጥታ በማጋጨት አሻቅቦ ወደ ኑክሊየር ውድመት ሊያመራ ይችላል የሚባለው ሁኔታ ምንጩ በሶሪያ ውስጥ የተከሰተ የእርስ
በርስ ጦርነት ነው ተብሎ በብዙ የምእራባውያን መንግስታትና የዜና ምንጮች ይቅረብ እንጂ፣ ዋነኛው ጠብ በአሜሪካና በምእራባውያን
አገሮች ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ዓለም አቀፋዊ የኃይል ፉክክር ነው። በሶሪያ የተፈጠረው ጦርነት መነሾውም አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ
ያሉና የማትፈልጋቸውን መንግስታት ለመገልበጥ ስታደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬ መሆኑን ለሁኔታው ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች
ያስረዳሉ። ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ደግሞ ሶሪያ ሁለት የሩሲያ የጦር ሰፈሮች ያሉባት የመካከለኛው ምስራቅ አገር መሆኗ
ነው። ከሩሲያ ጋር የሚተባበረውን መንግስት በመገልበጥ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ በዚያ አካባቢ የእግር መርገጫ እንዳይኖራት ለማድረግና
ለማዳከም መጣራቸው ለመረዳት አዳጋች አይደለም። በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄፍሪ ሳክስ ለምሳሌ፣ ሐሙስ አፕሪል
12 ላይ CNBC በሚባለው የአሜሪካ ቴሌቪዝን መረብ
ላይ ቀርበው ሲናገሩ ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረው ዓለም አቀፍ ውጥረት ምንጩ የአገራቸው የስለላ ድርጅት ከሳውዲ አረቢያ ጋር በመተባበር
ከብዙ ዓመታት በፊት የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በስውር ያደረገውና የከሸፈበት ሙከራ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ይህ ዛሬ በሶሪያ ሰበብ በዓለም ላይ አንዣቦ
የሚገኘው ከፍተኛ የጦርነት አደጋ በ1962 እኤአ በሩሲያና በሶቪየት ህብረት በኩባ ላይ ተፈጥሮ ከነበረው አደጋ ጋር የሚቀራረብ
እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎችን የፖለቲካ ታዛቢዎች ያመለክታሉ። ራሳቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንትም በዚሁ ሳምንት በትዊተር በላኩት መልእክት
ላይ አገራቸው ዛሬ ከሩሲያ ጋር ያላት መጥፎ ግንኙነት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን እንኳን ከነበረው የከፋ እንደሆነ አመልክተዋል።
ስለዚህ ወገኖች፣ አሜሪካንና ሩሲያን ወደ ኑክሊየር ጦርነት ሊያስገባ የሚችለው ውጥረት እንደተባለው በሶስት ቀን ውስጥ አይፈንዳ
እንጂ መፍትሔን አላገኘም። የጦር መርከቦች፣ ሰራዊትና መሳሪያዎች
ወደ ቦታው እየተንቀሳቀሱ ነው፣ ብዙዎችም በአካባቢው ተፋጥጠዋል። በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ተወካይ የሆኑት
ቫሲሊ ኔቤንዚያ ሐሙስ አፕሪል 12 ላይ ሲናገሩ፣ የሩሲያ ጦር በሶሪያ ስላለና ከዋሽንግተን የሚነፍሱት ወሬዎችም አስጊ በመሆናቸው
ምክንያት እንደተባለው አሜሪካ ሶሪያን ከደበደበች አገራቸውና አሜሪካ በቀጥታ ሊዋጉ የሚችሉበትን አደገኛ ሁኔታ መኖሩን አልሸሸጉም።
ምናልባትም ሰላማዊ መፍትሔ ይገኝ ይሆናል በማለት እኒሁ የሩሲያው ተወካይ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አርብ
አፕሪል 13 ላይ እንደገና እንዲሰበሰብ ጠይቃለች። የድርጅቱ ዋና ጸሃፊም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ሪፖርት ያቀርባሉ ሲል ዋሽንግተን
ፖስት የተባለው ጋዜጣ ምንጮች አመልክተዋል። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ