በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አሜሪካና አጋሮቿ ሶሪያን በቦምብና በሚሳኤል ሊደበድቡ እየተዘጋጁ ነው


ባለፈው ቅዳሜ ማታ፣ መጋቢት 29 (እኢአ) ጉታ በሚባለው በደማስቆ አጠገብ በሚገኝ ከተማ የሶሪያ መንግስት በሰላማዊ ህዝብ ላይ የመርዛማ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ ብዙ ሰዎችን ገድሏል የሚል ዜና ባለፈው እሁድ አፕሪል 8 በምእራቡ ዓለም ዜና አውታሮች ተሰራጭቷል። ዜናው ገና እንደተሰማና ገና በቂ መረጃም ከመገለጡ በፊት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ለዚህ ጥቃት ተጠያቂዎቹ የሶርያ መንግስትና አጋሮቹ ሩሲያና ኢራን ናቸው በማለት፣ በተለይም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያውን ፕሬዝደንት በስም በመጥቀስና በመንቀፍ መናገራቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ነው እየተባለ በሶሪያ ሲነጉድ የነበረው ጦርነት በቀላሉ ወደ ዓለም ጦርነት ሊያመራ ወደሚችልበት የማሻቀብ ደረጃ መድረሱን ያሳያል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ከየቦታው እየተሰሙ ነው።
ይህ አጭር መልእክት ከተዘጋጀበት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ሲል የአውሮፓው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ድርጅት በሚቀጥሉት 72 ሰዓታት የሰሜኑ አትላንቲክ የመከላከያ ድርጅት (አሜሪካና አጋሮቿ)  በሶሪያ ላይ የሚሳኤልና ሌሎችም የአየር ጥቃቶች ሊፈጽሙ ስለሆነ የህዝብ ማመላለሻና ሌሎችም የሲቪል አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ ከመብረራቸው በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ የጦር መርከቦች ሶሪያ ወደምትገኝበት ምስራቅ የሚዲትራኒያን ባህር እያመሩ ነው የሚሉ ብዙ ዜናዎችም ከየአቅጣጫው እየነፈሱ ነው። የሩሲያ የጦር ኃይልና መሳሪያዎች በራሷ በሶሪያና በሜዲትራኒያን ባህርም ላይ ሲገኙ፣ ቻይና ደግሞ የባህር ኃይሏ ሩሲያን ለመደገፍ ወደዚያው እንዲያመራ አዝዛለች የሚል ዜናም እየነፈሰ ነው።
በ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ የተጀመረው ይህ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰላማዊ ህዝብ ያለቀበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተሰደደበትና የተፈናቀለበት ጦርነት የአረብ ጸደይ ተብሎ ተነስቶ የነበረው በአረብ አገሮች የቆዩ መንግስታትን የመገልበጥ ስራ አካል እንደሆነ ብዙ ሲዘገብበት ቆይቷል። ከ2014 ጀምሮ ግልጽ እየሆነ የመጣ ሌላው ነገር ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ አሜሪካና አጋሮቿ እንደፈለጋቸው በየአገሩ መንግስታትን ይገለብጣሉ በማለት ስታማርር የቆየችው ሩሲያ የጦር ሰፈሮቿ ያሉባት ሶሪያ እንደ ሊቢያ፣ እንደ ኢራቅና እንደ አፍጋኒስታን እንድትፈራርስ ባለመፈለጓ የአገሩን መንግስት ለመርዳት በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ውስጥ መግባቷ ነው። ይህን ተከትሎ፣ የሶሪያ መንግስት ባይጠይቃቸውም፣ አሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ በአንድ በኩል የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ የሚዋጉ ሽምቅ ተዋጊዎችን ሲረዱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይሲስን እንዋጋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተለያዩ መልእክቶች ላስተላልፍ እንደሞከርሁት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም ላይ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነትን ይዘው የቆዩት በአሜሪካ የሚመሩት ምእራባውያኑ ኃይሎች የቀዝቃዛው ጦርነት ከበቃና ሶቪየት ሕብረት ከፈራረሰች በኋላ ተቀናቃኝ የለብንም በሚል ስሜትና ዲሞክራሲን እናስፋፋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ በብዙ አገሮች ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ከርመዋል። ይህ ያስቆጣት ሩሲያ ደግሞ የዩጎዝላቪያ መፈራረስ፣ የኢራቅ ጦርነት፣ ማቆሚያ ያጣው የአፍጋኒስታን ጦርነት፣ የሊቢያ መፈራረስና የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት የዚህ የምእራባውያኑ ማን አለብኝነት ውጤት ነው በማለት ታማርራለች። ይህ ውጥረት ስር ሲሰድ ከቆየ በኋላ በ2014 ላይ አሜሪካ ቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል የነበረችውን የዩክሬንን መንግስት የገለበጠ አብዮትን በመደገፏ፣ ሩሲያ የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ጓሮዬ እንዲጠጋ አልፈቅድም በማለት በመረረ መንገድ ተቃወመች። የምእራባውያኑ ወደ ዩክሬን መግባት በዚያው በዩክሬን በምትገኘው ክራይሚያ በምትባለው ግዛት ያለውን የባህር ኃይሏን ቦታ ለማሳጣትና ግዛቷንም ለመክበብ ነው በማለት የሰጋችው ሩሲያ በጊዜው በኑክሊየር መሳሪያ በማጥቃትም ጭምር የምእራባውያኑን ወደ ዩክሬን ለመግባት መሞከር ለማቆም ወስና እንደነበር መረጃው ያላቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህን እና ሌሎችንም በምእራባውያኑ አገሮችና በሩሲያ፣ በቻይና፣ በኢራን፣ በሶሪያና፣ በቤኔዙዌላ፣ በሰሜን ኮሪያ ወዘተ መካከል ያሉትን ውጥረቶች በተመለከተ ባለፉት ጊዜያት ሰፋ ያሉ ትንተናዎችን አቅርቤያለሁ።
አሁን በሶሪያ ላይ እያንዣበበ ያለው ሁኔታ በቀላሉ ሊያሻቅብና በታላላቆቹ አገሮች፣ ማለትም በዋናዎቹ ባለኑክሊየር መሳሪያ ባለቤቶች በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ወደሚፈጸም የቀጥታ ጦርነት ሊለወጥ እንደሚችል ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ። የዚህም ዋነኛው ምክንያት በሶሪያ የሩሲያና የኢራን ጦር መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ግጭት ለብዙ ዓመታት በምእራባውያኑና በሩሲያ፣ መካከል በየቦታው ሲገነባ የኖረው ውጥረት ሊፈነዳ መሆኑን ስለሚያመለክትም ነው። እንደ ተገመተው ይህ የሶሪያ ጦርነት አሜሪካንና አጋሮቿን ከሩሲያና አጋሮቿ ጋር በቀጥታ ወደማዋጋት ከደረሰ ምናልባት በትንቢተ ኢሳይያስ ምእራፍ 17 ላይ እና በትንቢተ ኤርምያስ 43:23 እስከ 26 ስለ ደማስቆ መደምሰስ የተጻፉት ትንቢቶች ፍጻሜ ሊሆን ይችላል በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስተማሪዎች ይጠቁማሉ። ያለንበት ዘመን የወንጌል መሰበክና የጸጋ ዘመን ማብቂያና የጌታ ኢየሱስ ዳግም ምጽዓት አጥቢያ ስለሆነ ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ መስማታችን የግድ ነው። አሁን በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ግን ከመቼውም ዘመን ይልቅ እጅግ አደገኛ ስለሆነ፣ ምናልባትም ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ምድር የኑክሊየር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚሉም ብዙ ናቸው። ምናልባትም ይህ ውጥረት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ለሚገለጸው ለሃሰተኛው መምጣት መንገድ የሚጠርግ ሊሆን ይችላል የሚሉ የትንቢት አስተማሪዎች ጥቂት አይደሉም። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...