ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር የሚመለስበት
ዘመን መቃረቡን ከሚያመለክቱን ነገሮች ውስጥ ዘመኑ የሚያስጨንቅ መሆኑ ነው። ከሚያስጨንቁት የዚህ የመጨረሻ ዘመን ባህርያት አንዱ
የጦርነትና የጦርነት ወሬ መብዛት ነው። የሚያሳዝነው ግን ለመዋጋትና ለመገዳደል አንዱ በአንዱ ላይ እየተነሳ ያለው መንግስታት ብቻ
አይደሉም። አድገዋል፣ በልጽገዋል፣ ተምረዋል፣ ሰልጥነዋል ተብለው በሚነገረላቸው እንደ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ካናዳም ሳይቀር
ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ወንጀል በቁጥር እየበዛ መሆኑን ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ። የመገዳደል ችግሩ ጠብመንጃና ሽጉጥ ስለሆነ መንግስታት
እነዚህን ለማገድና ለመቆጣጠር ብዙ እርምጃዎችን ወስደዋል፣ እየወሰዱም ነው። እነዚህን መሳሪያዎች በአብዛኛው ተቆጣጥረዋል ከሚባሉት
አገሮች አንዷ እንግሊዝ ናት። በተያያዘውና በሌሎችም ተመሳሳይ ዜናዎች እንደምናነበው፣ ከዓለም የገንዘብ ማእከሎች በዋናነት በምትጠቀሰው
በለንደን ከተማ ብዙ ሰው በጩቤ፣ በቢላዋና በቆንጨራ እየተገዳደለ ነው። በፈረንጆቹ ዓመት የመጨረሻ ሁለት ወራት ብቻ በእንግሊዝ
አገር በቆንጨራ የተፈጸሙት ወንጀሎች 928 ሲሆን ከነዚህም መካከል 425 የተፈጸሙት በለንደን ነው። ይህ ሁኔታ ያስፈራቸው የለንደኑ
ከተማ ከንቲባም በዚሁ በያዝነው የፈረንጆቹ ወር በከተማይቱ የሚደረገውን የቢላዋ ወይም ጩቤ ዝውውር ለመቆጣጠር አዲስ መመሪያ አውጥተዋል።
ስለ ክፉ ነገሮች ያለን ሃሳብ ብዙውን ጊዜ
የሚወሰነው በሚደርሰን ዜና ነው። በባለጸጎቹ አገሮቹ ባሉ የዜና ምንጮች የሚያቀርቧቸው ብዙዎቹ ዜናዎች የእነርሱ አገሮች ሰላማዊ፣
የሰለጠኑ፣ ችግሮችን ሁሉ የሚፈቱት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንደሆነ ለማሳየት ይጥራሉ። በሌላ በኩል ግን ችግር፣ ወንጀልና ጦርነት
የሚገኙት ደግሞ በአዳጊዎቹና ድሆቹ አገሮች እንደሆኑ ለማሳየት አይታክቱም። በዓለማችን ላይ ያሉትን ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል ስንመዝናቸው
ግን፣ ባለጸግነት፣ ትምህርት ወይም ስልጣኔ የኃጢዓትን ኃይል ወይም የሰውን ክፋት አያስወግዱም። እንዲያውም ታሪክና ዛሬም በዓይናችን
የምናየው መረጃ የሚያሳየን የሰው ልጅ በሰለጠነና በቴክኖሎጂ በተራቀቀ መጠን ስልጣኔውን የሚጠቀመው የከፉና ብዙ ህዝብን የሚጨርሱ
መሳሪያዎችን ለመስራትና በስራ ላይ ለማዋል መሆኑን ነው። አንድ የአገራችን የወንጌል ሰባኪ ከብዙ ዓመታት በፊት ሲናገሩ፣ “የሰው
ልጅ ሰለጠነ ከማለት ይልቅ ሰየጠነ ማለቱ ይቀላል” ብለው ነበር። በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት፣ ገንዘብን መውደድ
እንዲሁም ክፋትና ጭካኔ በምድር ላይ እጅግ እየበዛ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል 2ኛ ጢሞቲዎስ ምእራፍ 3
የዚህን ዘመን ባህርይ በዝርዝር ይነግረናል። ፈሪሃ እግዚአብሔር በገንዘብ ስለተተካ፣ የሰው ልጅ ከአምላኩ ይልቅ ተድላንና ገንዘብን
ስለወደደ ስግብግብነት ምድርን እንደ ሰደድ እሳት እያቃጠላት ነው። በህዝብ መካከል ጭካኔ፣ በመንግስታት መካከል ጦርነት የሚሆነው
እነዚህ የተጠቀሱት አመጻዎች ፍሬ ሲያፈሩ ነው። የሰውን ዘር ከዚህ ሁሉ ጥፋት ሊያድነው የሚችለው የበለጠ ገንዘብ፣ ተጨማሪ ምርት
ወይም ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የወንጌል የምስራች ተሰብኮአል። እውነተኛ
ሰላም፣ እረፍትና ደስታ የሚገኘው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በፍቅር በመኖር እንጂ ሃብትን በማግበስበስ
ሊረካ የማይችለውን የስጋንና የከንቱ አእምሮን ምኞች በመከተል አይደለም። ይህን የተረዳው ዳዊት በመዝሙረ ዳዊት በ2ኛው ምእራፍ
ላይ የምድር ነገስታትና መሪዎች በእግዚአብሔር እውነትና ስርዓት ላይ በማመጽ እንደሚነሱና በራሳቸው መንገድ የሰውን ዘር እነርሱ
ራሳቸው አይተውት ወደማያውቁት ምናባዊ የብልጽግና፣ የእኩልነትና የሰላም ዓለም ለመምራት እንደሚሞክሩ አመልክቷል። በእውነትም የዚህ
ሰለጠነ የሚባለው ዓለም መሪዎች ዛሬ እውነተኛ ነጻነትን፣ ሰላምንና ብልጽግናን ለሰው ዘር ሊያግናጽፍ የሚችለውን ብቸኛውን የፈጣሪን
የፍቅርና የእውነት ስርዓት ህጎች በማፈራረስና በመሻር ላይ ናቸው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስና መንግስቱን
እስኪመሰርት ድረስ ይህ የምናየው ጥፋት እየቀጠለና እየባሰ ይሄዳል እንጂ አይቆምም። የሰው ዘር ዋናው ችግሩ ኃጢዓት ብቸኛ መፍትሔው
ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ለዚህ ነው ዳዊት በዚያው በ2ኛው ምእራፍ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ለምድር ነገስታትና መሪዎች
ሁሉ የተናገረው፡
“አሁንም እናንት ነገሥታት ልብ አድርጉ፣ እናንት የምድር ፈራጆችም ተገሰጹ።
ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሳጹን ተቀበሉ፣ ጌታ እንዳይቆጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ።” መዝሙር 2፡10-12
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል። ይህ እውነት
ለግለሰቦችም፣ ለመንግስታትም፣ ለተማሩም ላልተማሩም፣ ለሰለጠኑም፣ ላልሰለጠኑም እውነት ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ