ሰው ሰራሽ አእምሮ የሰውን ልጅ መተካትና የሰውንም ዘር ማጥፋት የሚችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል

https://www.rt.com/viral/386512-hawking-ai-fears-humanity/

ሰው ሰራሽ አእምሮ የሰውን ልጅ መተካትና የሰውንም ዘር ማጥፋት የሚችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ተባለ
ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል፣ በተለይም ደግሞ ስለመጨረሻው ዘመን፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት፣ በዘመኑ መጨረሻ ላይ ስለሚገለጸው የእግዚአብሔር መንግስት እና ስለዘለዓለም ፍርድ የተጻፉትን ትንቢቶች ከየእለቱ ዜናዎች ጋር በማነጻጸር ብናደምጣቸው እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከፍጥረት መካከል የዋጃቸውን ሕዝቡን ወደራሱ የሚሰበስብበትና በዓመጸኛው ዓለም ላይ የሚፈርድበት ዘመን እጅግ እየተቃረበ መሆኑን እናስተውላለን። ስለዚህ ዘመን መጨረሻ ከተጻፉት ትንቢቶች አንዱ እንዲህ ይላል፤

ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፣ ከሰማይም ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን በማኅተም ዝጋው፣ አትጻፈውም የሚል ድምጽ ሰማሁ። …….. ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምስርጢር ይፈጸማል አለ። ራዕይ 10 ቁጥር 4 እና 7

ባለፉት ጥቂት ቀናት በቤጅንግ ቻይና እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፉ ተንቀሳቃሽ ኢንተርኔት ኮንፈረንስ (GMIC) ላይ ንግግር ያደረጉት እውቁ የፊዚክስና የህዋ ምርምር ሊቅ ፕሮፌሰር ስቲቨን ሆውኪንግ እንዳሉት፣ የሰው ልጅ ራሱ የፈጠረው ሰው ሰራሽ አዕምሮ (ARTIFICIAL INTELLIGENCE ወይም ባጭሩ AI) ከራሱ ከሰው ልጅ ችሎታ እኩል ወይም በላይ የሆኑ ነገሮችን ሊሰራ የሚችልበት ደረጃ ደርሷል፣ በብዙ መስመሮችም ላይ ይህ ሰው ሰራሹ አእምሮ ከሰው ልጅ ከራሱም ችሎታ በላይ የላቁ ነገሮችን ስለሚሰራ በከፍተኛ ፍጥነት የሰውን ልጅ ህልውናና በዚህ ምድር ላይ የመኖር አስፈላጊነት ከጥያቄ ውስጥ እያስገባው ነው ብለዋል። በመጨመርም፣ ይህ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ለመርዳትና ችግሮቹን ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ቢሆንም፣ እንደፈለገው እንዲሆን ከተለቀቀ ግን የሰውን ዘር ፈጽሞ ሊጎዳና ሊያጠፋም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። “ቆም ብለን ማሰብ ያለብን አሁን ነው” ያሉት እኒህ ታዋቂ ምሁር፣ ይህ ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ ደህንነትና ህልውና ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጥፋት በጣም እንደሚያሰጋቸው ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም። የርሳቸውንም ሆነ የሌሎች አዋቂዎችን ምክር የሚሰማ ወይም የሚያስተውል ይኖር ይሆን ?!!

የኮምፒውተርና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ እጅግ በመስፋፋት ዓለምን በሙሉ መሸፈን ከመጀመረባቸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ ጀምሮ እነዚህ ሰው ሰራሽ ቁሾች (HARDWARE) የመረጃ መረቦችና (NETWORKS) እና በሰው የተጻፉ የኮምፒውተር ትእዛዞች (SOFTWARE) ቅንብሮች እጅግ ከፍተኛ ወደሆነ ልእቀት በመድረስ ዛሬ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል የሰው ልጅ ብቻ ይሰራቸዋል የሚባሉ ነገሮችን በሙሉ ሊያከናውን ወደሚችልበት ደረጃ ደርሷል። በAI የሚመሩ ቁሶችና ሶፍትዌሮች ቤት ያጸዳሉ፣ መኪና ይነዳሉ፣ አውሮፕላን ያበራሉ፣ በፋብሪካዎች ውስጥ እቃዎችን ይሰራሉ፣ ይገጣጥማሉ፣ ትልልቅ ፋብሪካዎችን፣ የኃይል ማመንጫዎችን፣ የውሃና የፍሳሽ አገልግሎት መሳሪያዎችን ይቆጣጠራሉ፣ በራዳርና ሌሎች የተለያዩ መሳሪያዎች ድምጾችን በመስማት፣ ምስሎችን በማየት፣ ሽታዎችንና ጣእሞችን በመለየት መረጃን ይሰበስባሉ፣ ከተራ የጦር መሳሪያዎች እስከ ኑክሊየር ሚሳኤሎች ድረስ የመቆጣጠርና ሲፈቀድላቸውም ኢላማ የመለየትና የመተኮስ እንዲሁም ከጠላት የተተኮሱ መሳሪያዎችን የመለየትና የመምታት ችሎታ አላቸው። በሆስፒታል ቀዶ ጥገና የማድረግ፣ ወደ ህዋ የሚመጥቁ መንኮራኩሮችን የመምራት፣ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስና የኢንሹራንስ እንዲሁም የላቁ የምህንድስናና ሳይንሳዊ ቀመሮችንና ስሌቶችን የማከናወን፣ የምርት ጥራትን የመቆጣጠርና ሌሎችም የላቁ ስራዎችን የመስራት ችሎታ አላቸው።

ሰው ሰራሹ አእምሮ (AI) ዛሬ የሚቆጣጠረው ኮምፒውተሮችን፣ ታብሌቶችን፣ የእጅ ስልኮችን እና በየእለቱ በግላችንና በድርጅት ወይም በጋራ የምንጠቀምባቸውን ቁሶች ብቻ አይደለም። እንደ GOOGLE, FACEBOOK, TWITTER, INSTAGRAM ያሉ እና ሌሎችም በሰፊው የምንጠቀምባቸው ሶፍትዌሮች ስራቸው ለእኛ መረጃ መስጠትና የምንፈልገውን ነገር ማፈላለግ ብቻ አይደለም። እያንዳንዳችን በተደጋጋሚ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ያጠናሉ፣ ከማን ጋር ምን እንደምንነጋገር ወይም እንደምንጻጻፍ፣ መቼ ወጥተን መቼ እንደምንገባ፣ ምን እንደምንችል፣ ምን እንደምንገዛና እንደምንሸጥ፣ ምን እንደምናምን፣ ምን እንደምንደግፍና እንደምንቃወም፣ ምን እንደምንጠላላን እንደምንወድ ሳይቀር መረጃን በመሰብሰብ እኛንና ባህርያችንን ያጠናሉ፣ አንድን ቋንቋ ወደ ሌላ ይተረጉማሉ፣ የሰውን ንግግር በማዳመጥና መልስ በመስጠት ድሮ ብዙ ሰዎች ይሰሩአቸው የነበሩ ስራዎችን በቀላሉ ያከናውናሉ። ከነዚህ ሰው ሰራሽ አእምሮዎች በስተጀርባ ያሉ ባለቤቶች ከፈለጉም እንቅስቃሴያችንና ግንኙነቶቻችንን በሙሉ እነሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የመግራትና ሲያስፈልግም እንቅስቃሴያችንን ወይም ንግግራችንን የመዝጋት ችሎታው አላቸው። ለምሳሌ፣ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የGOOGLE ና የFACEBOOK ሶፍትዌሮች የቀኝ ክንፍ ወይም CONSERVATIVE ወገኖች በምርጫው ላይ ወደፊት እየመሩ ሲገኙ የነሱን ዜናዎች ሰዎች በቀላሉ እንዳያገኙአቸውና እንዳይደግፉአቸው ወደታች በመግፋት ያፍኑአቸው እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጾአል። ስለዚህ እነ FACEBOOK እና GOOGLE ወይም ሌሎቹ ነጻ መሳይ የብዙኃን መገናኛዎች እኛ እንደምንገምተው ስራቸው በቅንነትና በነጻ ለህዝቦችና ለሰዎች ሁሉ አገልግሎት መስጠት ሳይሆን ምርጫችንን፣ ዝንባሌያችንን እና ፍላጎታችንንም ሳይቀር ለመለወጥ ችሎታው ያላቸው መሳሪያዎች ናቸው።

በእጃችን ባሉ ዘመናዊ ስልኮች፣ በየቤታችን ባሉ ቴሌቪዥኖች እና በእጃችን ላይ በምናስራቸው ሰዓቶች፣ በምግብ ማቀዝቀዣዎች፣ በመኪናዎቻችንና ሌሎችም ቁሶች ውስጥ የሚቀመጡት ሶፍትዌሮች ያለንበትን ቦታና፣ በማንኛውም ጊዜ ምን እየሰራን እንዳለ ጭምር ስለሚያውቁ፣ ችሎታው ያላቸው ሰዎችና ድርጅቶች ይህንን መረጃ በመጠቀም ሊያጠቁንና ሊጎዱንም ይችላሉ። በመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 6 (ስድስት) ላይ እንዳቀረብሁት በቀላሉ በGPS እና በሌሎችም አድራሻ ጠቋሚ መሳሪያዎች አማካይነት ያለንበት ቦታ ድረስ መጥው ሊያጠቁን የሚችሉ ነፍሳት መሰል መሳሪያዎች ከተሰሩ ውለው አድረዋል። ብዙዎች የዘመኑን ወታደራዊ ኃይላት የሚያጠኑ ባለሙያዎችም የሶስተኛው የዓለም ጦርነት የሰውን ዘር ህልውና እጅግ ያሰጋል የሚሉት ይህ ሰው ሰራሽ አእምሮ በራሱ እንዲሰራ ከተለቀቀ ሊያመጣ የሚችለውን እልቂት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እንደ ሩሲያና አሜሪካ እንዲሁም ቻይና ያሉ ታላላቆቹ አገሮች ዛሬ ሰውን በትክክል የሚለዩና ካስፈለገ መማረክ ወይም ተኩሰው መግደል የሚችሉ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ፣ የሚያዩ፣ የሚሰሙና ውሳኔ ማድረግ የሚችሉ መሳሪያዎችን በሰፊው እያመረቱ ነው። ምናልባት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ስለሚመጣው ታላቁ የመከራ ዘመን ሲናገር “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ስጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር፣ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” በማለት በማቴዎስ 24 ቁጥር 22 ላይ የተናገረው ስለዚህ ጉዳይ ይሆን ?!

አተኩሮ ለተመለከተው የሰው ሰራሽ አእምሮ (artificial intelligence ወይም AI) ችሎታና በሱም የሚንቀሳቀሱ የሰላምና የጦርነት መሳሪያዎች፣ ስለሚያስፈራው ስለእግዚአብሔር ቀን በጻፈው በነቢዩ በኢዩኤል ትንቢት  (ምእራፍ 2 ቁጥር 1 እስከ 11) ላይ  የተገለጹትን ነገሮች የሚመስል ባህርይ አላቸው። የኢዩኤል ትንቢት አንዱ ክፍል እንዲህ ይላል፤

“ከፊታቸው አህዛብ ይንቀጠቀጣሉ፣ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል። እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ሰልፈኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፣ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፣ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም፣ አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፉም፣ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፣ በሰልፉ መካከል ያልፋሉ፣ እነርሱም አይቆስሉም። በከተማም ያኮበኩባሉ፣ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፣ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፣ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ።” ኢዩኤል 2፤6፥9

ሰው ሰራሹን አእምሮ በተመለከተ መረዳት የሚገባን መንፈሳዊ ነገርም አለ። የሰው ዘር ጠላት የሆነው ዲያብሎስ፣ ተከታዮቹ የወደቁት መላእክትና አጋንንት ግዑዝ በሆኑ ሃውልቶችና ጣዖታት ውስጥ በመሆን የሰው ልጆች ለዘመናት እንዲሰግዱላቸው ካደረጉ፣ በሰው ሰራሽ አእምሮ በሚመሩ ነገሮች ውስጥ በመሆን የሰውን ልጅ ከማታለልና ሰው በእጅ የተሰራውን እንዲያመልክ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ምናልባትም በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 13 ቁጥር ላይ የተጻፈው “የአውሬው ምስል” የዓለም ህዝብ ሁሉ ሃሰተኛው ክርስቶስ ከሞት ተነሳ ብሎ እንዲያምን የሚከወን በሰው ሰራሽ አእምሮ የሚመራ ቅርጽ ወይም ሰው መሳይ አካል ሊሆን እንደሚችል ብዙ የትንቢት ምሁራንና ቴክኖሎጂውን በቅርብ የሚያጠኑ አዋቂዎች ይገምታሉ?!

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለና ጌታን በመታዘዝ የሚመላለስ ክርስቲያን ሁሉ ከላይ የተጠቀሰውንና ሌሎችንም መሰል ዜናዎች ሲሰማ የጌታ ቀን እንደተቃረበ በማወቅ ራሱን ማዘጋጀት እንጂ መፍራት ወይም መታወክ አያስፈልገውም። የእግዚአብሔርን ፍቅርና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የተደረገውን የወንጌል ግብዣ ገና ያልተቀበለ ማንኛውም ሰው ደግሞ ኃጢዓተኝነቱን በመገንዘብና እግዚአብሔርም በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምክንያት ይቅር እንደሚለው በማመን ኢየሱስ ክርስቶስን የመቀበያው ቀን ዛሬ ነው። መቼ እንደሚሆን ቀኑን እና ሰዓቱን ባናውቅም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ የሚመጣበት ቀን እጅግ እየተቃረበ ነው። በዚያን ቀን ለንስሃ ቦታ የለም። ያ ቀን የፍርድና እግዚአብሔር ስንዴውን ከእንክርዳድ የሚለይበት ቀን ነው። የንስሃ ቀን ዛሬ ነው። እግዚአብሔር እርሱን የምንፈራበትና በንስሃ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደሱ የምንመለስበትን ልብ ይስጠን።
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።



ከፍተኛ የጦርነትና የህዝብ እልቂት ደመና በምድር ላይ እያንዣበበ ነው። ለራሳችን፣ ለመሪዎችና ላልዳኑ ሰዎች ሁሉ እንጸልይ!!

http://endtimeheadlines.org/2017/04/developing-us-preparing-evacuate-230000-americans-south-korea/

ከፍተኛ የጦርነትና የህዝብ እልቂት ደመና በምድር ላይ እያንዣበበ ነው። ለራሳችን፣ ለመሪዎችና ላልዳኑ ሰዎች ሁሉ እንጸልይ!!

ባለፈው አጭር መልእክት ላይ እንደ ጻፉሁት፣ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነው ብለው ደቀ መዛሙርቱ በጠየቁት ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰጣቸው ምልክቶች አንዱ ዘመኑ ሲደርስ ምድር ሁሉ በጦርነትና በጦርነት ወሬ መሞላቷ ነው። ከመቼውም ዘመን ይልቅ ዛሬ ምድራችን እጅግ አስከፊ በሆነ የጦርነት ስጋት ውስጥ ወድቃለች። ጥቁር የጦርነትና የከፍተኛ እልቂት ደመና በብዙ የምድር ክፍሎች አንዣቧል። በምድር ኃያል ናት የምትባለው አሜሪካና መሪዎቿ፣ እንደ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያና ጃፓን ያሉ አጋሮቿም ሆኑ በሌላው ወገን ያሉት እንደ ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሶሪያና ሌሎችም ባላንጣዎቻቸው አንዴ ከተጀመረ ወደ ኋላ ሊመለስ በማይችል የጦር ሰበቃ ውስጥ ገብተዋል። እንደ ቀላል ነገርና ጨዋታ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንና አጋሮቿን በኑክሊየር ቦምብ አጠፋለሁ በማለት በተደጋጋሚ እየፎከረች ነው። ሁኔታው ያሰጋት አሜሪካም አሉ የተባሉ አውሮፕላን ተሸካሚና የጦር መርከቦችን፣ የኑክሊየር ሚሳኤል ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን (SUBMARINES)፣ የኑክሊየር ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን እና በልዩ መንገድ የሰለጠኑ ወታደሮቿን በኮሪያው ባህረ ሰላጤ፣ በጃፓን፣ በአውስትራሊያና ሌሎችም የጦር ሰፈሮቿ በትልቅ ፍጥነት ማከማቸቷን ቀጥላለች። ይህንን ከባድና አስጊ እድገት “ምንም አይደለም” ከዚህም በፊት ጦርነቶች ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ እያሉ ለማንኳሰስ የሚሞክሩ ካሉ የአደጋውን ከባድነት ገና ያልተረዱ ናቸው። ሰሜን ኮሪያ ያለ የሌለ መሳሪያዎቿን አውጥታ የተኩስና የጦርነት ልምምዶችን እያደረገች ነው። አሜሪካ የቦምቦች ሁሉ እናት ያለችውን ከኑክሊየር ቦምብ በታች የመጨረሻ ከፍተኛ ሃይል ያለውን ቦምብ በአፍጋኒስታን በማፈንዳትና በሶሪያ ላይ ቶማ ሆክ የተባሉ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ሰሜን ኮሪያንና አጋሯ እንደሆነች በሰፊት የሚታመነውን ቻይናን ለማስፈራራት ሞክረው ነበር። ይህም አልበቃ ስላላት ደግሞ MINUTEMAN 3 የተባለውን ኑክሊየር ቦምብ ተሸካሚ የሩቅ ጥቃት ሚሳኤል APRIL 25፣2017 ላይ በመተኮስ ከ 6400 ኪሎሜትር በላይ ከሄደ በኋላ በፓሲፊክ ውቅያኖስ እንዲወድቅ በማድረግ በሰሜን ኮሪያንና በአጋሯ ቻይና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ለማድረግ ሞክራለች። ቆሟል ተብሎ ባለፉት ጥቂት ሲነገርለት የነበረው የአፍጋኒስታን ጦርነት እንደ ገና አገርሽቶ ብዙ ህዝብ እያለቀ ነው። በዚያ ለሚዋጉት ታሊባን ደግሞ ሩሲያ መሳሪያ ታቀብላለች የሚሉ ዜናዎች የሚናፈሱት ሩሲያን ለመተንኮስ ነው የሚሉ ታዛቢዎችም ብዙ ናቸው። የጦርነትና እልቂት ደመና በሰሜንና በምስራቅ አውሮፓም (በተለይም በዩክሬን፣ በክራይሚያና የቦልቲክ ሪፐብሊኮች በሚባሉት) ካንዣበበ ውሎ አድሮአል። በአሜሪካና በሩሲያ፣ በአሜሪካና በቻይና፣ በአሜሪካና በኢራን እንዲሁም በሌሎች አገሮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ከተፈጠረ ውሎ አድሮአል።


አሁን ዓለምን ያሰጋው የኑክሊየር ጦርነት ከዚህ በፊት ምድር አይታው የማታውቀውን የህዝብና የእንስሳት እልቂት ከማምጣቱም በላይ ብዙውን የምድርን አካልና ስርዓት ስለሚመርዝና ስለሚያጠፋ ዛሬ የምናውቃት ዓለም ገጽታ ሊቀየር ይችላል። የኑክሊየር ቦምብን የጥፋት ጉልበት በቅርቡ የሚያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና ሌሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች ምናልባት ጌታችን “ያ ቀንስ ባያጥር ስጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር” ያለው ምናልባት በምድር ላይ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ሊከሰት የሚችለውን የኑክሊየር ጦርነትና የህዝብ እልቂት በተመለከተ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ። የኑክሊየር አደጋ ለማንዣበቡ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ። ከነዚህ አንዱ የአሜሪካ መንግስት በነዚህ ቀናት እያደረገ ያለው በኑክሊየር ጦርነት ጊዜ እርዳታ የመስጠት ልምምድ፣ ጃፓን ህዝቧ የኑክሊየር ጥቃት ቢፈጸም ዜጎቿ ራሳቸውን እንዴት ሊከላከሉ እንደሚችሉ እያሰለጠነችና የተለያዩ ቁሶች እንዲገዙ ማበረታታቷ ምሳሌዎች ናቸው።  የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጡ ትንቢቶች ምድር በከፍተኛ የጦርነት እልቂት እንደምትጎዳ በግልጽና በተደጋጋሚ ያስረዳሉ። ከነዚህም ትንቢቶች ብዙዎቹ በዮሐንስ ራዕይና በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ይገኛሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኒቱ አድርጎ የተቀበለና ለጌታ በመታዘዝ የሚላለስ ክርስቲያን ሁሉ የሚያስፈራው ምንም ነገር የለም። ጦርነትና የጦርነት ወሬ በሰፊው ዓለምን ሁሉ ማናወጥ የጌታችን ዳግም ምጽዓት ለመቃረቡ ምልክት ሊሆን ስለሚችል እኛ ክርስቲያኖች ሁላችን ለምድር መሪዎች፣ በነዚያ አገሮች ለሚኖሩ ክርስቲያኖችና ጌታን ሳያውቁ ሊሞቱ ስለሚችሉ ሰዎች ሁሉ መጸለይ ያስፈልገናል። በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በምትወጣው የመለከት ድምጽ (ቁጥር 7) ላይ ይህንን በተመለከተ ሰፋ ያሉ መረጃዎች፣ ትንተናዎችና ትምህርቶች ይቀርባሉ። በግልም ሆነ በህብረት ለመሪዎችና ለተራውም ህዝብ በሙሉ እንጸልይ። ጌታ ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ጦርነትና የጦርነት ወሬ በዓለም ዙሪያ

http://theeconomiccollapseblog.com/archives/is-the-united-states-about-to-bomb-north-korea-the-white-house-says-the-clock-has-now-run-out

ከላይ በተያያዘው ዜና እንደምታነቡትና ከዚህም በፊት እንደ ጻፍሁት፣ ታላላቆቹ የምድር መንግስታት እጅግ  ብዙ ህዝብ ሊፈጁ የሚችሉ ጦርነቶችን ለመለኮስ እየተዘጋጁ ነው የሚሉ ዜናዎች በሰፊው ይናፈሳሉ። በ1950ዎቹ ዓመታት ተለኩሶ ብዙ ህዝብን ካጨፋጨፈና ኮሪያን ለሁለት ከከፈለ በኋላ ያለ ሰላም ውል የቆመው የሰሜንና የደቡብ ኮሪያ ጦርነት እንደገና ይፈነዳል የሚለው ፍርሃት ባለፉት 64 ዓመታት የአካባቢውን ህዝቦችና መንግስታት እንቅልፍ ሲነሳ ኖሯል። በአሜሪካ የምትደገፈዋ ደቡብ ኮሪያ ለደህንነቴ ታሰጋኛለች የምትለው ኮሚኒስቷ ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ከቻይና በምታገኘው የኤኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ ብቻ ሳትወሰን በደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና በአካባቢው የሰፈሩት የአሜሪካ ጦር ኃይሎችን ለመቋቋም ነው በሚል ሰበብ ታላቅ የጦር ሰራዊትን አሰማርታለች፣ የኑክሊየር ቦምቦችንም ሰርታለች። ባለፉት ብዙ ዓመታት እነዚህን የኑክሊየር ቦምቦች ለማሻሻልና የአሜሪካ ሰራዊት ወዳሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ የሚያደርሱ ሚሳኤሎችን ስትሰራና ስትፈትሽ ከርማለች። ይህ ደግሞ ከባላንጣዎቿ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከአሜሪካ ጋር ያለውን ውጥረት ከፍተኛ ቦታ ላይ ስላደረሰው ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሜሪካ ባለስልጣኖች “ጊዜው አልቋል” የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ በመሰንዘር በማንኛውም ጊዜ ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል አመልክተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት የኑክሊየር ቦምብ መጣል የሚችሉ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በደቡብ ኮሪያ፣ በጃፓንና በጉዋም ሰፍረው የጦርነት ልምምድ ሲያደርጉ ከርመዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች ምናልባት ይኼ ሁሉ ነጋሪት ድለቃ በዚህ ሳምንት በአሜሪካና በቻይና ፕሬዝደንቶች መካከል በሚደረገው የመጀመሪያው ጉባኤ ላይ ቻይና በደቡብ ኮሪያ ላይ ተጽእኖ እንድታደርግ ለመገፋፋት ነው ሲሉ፣ ሌሎች ግን በእርግጥም አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን በቅርቡ ታጠቃ ይሆናል ይላሉ። የሰሜን ኮሪያ የኑክሊየርና የሚሳኤል በከፍተኛ መንገድ ያሰጋኛል የምትለው ጃፓንም አሜሪካን ተገን በማድረግ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጥቃት ትፈጽም ይሆናል የሚሉ ዜናዎችም ሲናፈሱ ከርመዋል።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛት የሆነውን ክራይሚያን በጉልበት ወስዳለች፣ በምስራቅ ዩክሬን ያሉትን የሩሲያ ዝርያ ያላቸውን ህዝቦችም የመገንጠል እንቅስቃሴ ትደግፋለች፣ የሌሎችንም የምስራቅ አውሮፓን አገሮች ደህንነት ታሰጋለች በሚል ሰበብ በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲኩ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምስራቅና ሰሜን አውሮፓ በሩሲያ ድንበር ላይ ብዙ የጦር ሰራዊት፣ ታንኮች፣ መድፎች፣ የጦር አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮችና ሚሳኤሎች እንዲሁም ሌሎች መሳሪያዎችን አከማችቷል፣ ብዙ የጦርነት ልምምዶችንም አድርጓል አሁንም እያደረገ ነው። ይህንን የተገነዘበችው ሩሲያም የጦር ሰራዊቷን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ አቁማለች። እንዲሁም ደግሞ  የአሜሪካንን እና የአጋሮቿን ጥቃት ልታመክንበት የምትችላቸውን አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በከፍተኛ ፍጥነት እየሰራችና እየፈተሸች ሲሆን፣ በማንኛውም የሩሲያ ግዛትና ጥቅም ላይ ጥቃት ቢሰነዘር ከባለጋራዎቿ ቀድማ የኑክሊየር መሳሪያዎችን እንደምትጠቀም አስጠንቅቃለች።
በምስራቅና በደቡብ ቻይና ባህር አካባቢም በቻይናና በአሜሪካ እንዲሁም እንደ ጃፓን ባሉ የአሜሪካ አጋሮች መካከል ከፍተኛ ፍጥጫ ከተፈጠረ ውሎ አድሮአል። በቻይናና በሌላው ዓለም መካከል ለሚካሄደው ዋና የባህር ትራንስፖርት መተላከፊያ የደም ስር የሆነው የደቡብ ቻይና ባህር ብዙ ክፍሎች ከጥንትም ጀምሮ የኔ ናቸው የምትለው ቻይና እና፣ እንደፈለገኝ በፈለግሁት ቦታ የመሄድ መብት አለኝ የምትለው ቻይና ከፍተኛ የጦር ልምምዶችን በአካባቢው ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በዚያው በደቡብ ቻይና ባህር መካከል ያሉ ትንንሽ ደሴቶችን በመጠቀምን ሰው ሰራሽ ደሴቶችን በመስራት ቻይና አዳዲስ የጦር ሰፈሮችን እየመሰረተችና እያሰፋች ነው።  የአሜሪካንን አውሮፕላን እና ሚሳኤል ተሸካሚ የጦር መርከቦች ሊያጠፉ የሚችሉ አዳዲስ ሚሳኤሎችን፣ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን እና የራሷንም አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦችን በማሰማራት ላይ ያለችው ቻይና፣ ግዛቴ ነው የምትለውን እየጣሱ የሚሄዱትን የአሜሪካን የጦር አውሮፕላኖችና መርከቦች አልታገስም እያለች ስታስፈራራ ከርማለች።
ባለፉት ብዙ ዓመታት አሜሪካ በአካባቢው ካሉ አጋሮቿ ጋር በመሆን በሶሪያ ያለውን መንግስት ለመገልበጥ ተቃዋሚዎችን እና ሽምቅ ተዋጊዎችን በተዘዋዋሪና በቀጥታ ስታስታጥቅና ስትረዳ ከርማለች። ጽንፈኛ የሆነውን እስላማዊ የሽብር ድርጅት አይሲስን እንዋጋለን በሚል ሰበብ የሩሲያን መንግስት ለመጣል የሞከረችው ሙከራ ስላልተሳላካና፤ በሩሲያ፣ በኢራንና በሊባኖሱ ሂዝቦላ የሚደገፈው የሶሪያ መንግስት ከፍተኛ ወታደራዊ ድሎችን አግኝቶ የአገሩን ብዙ ክፍሎች እንደ ገና መቆጣጠር በመጀመሩ፣ የአገሩን መሪ የመምረጥ መብቱ የሶሪያ ህዝብ ነው ሲሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት የአሜሪካ ተወካይ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር። የማታ የማታ አሜሪካ ሃሳቧን ለወጠች፣ የሶሪያም ግጭት ወደ መፍትሄ ይደርስ ይሆናል ብለው ተስፋ ያደረጉ ብዙ ነበሩ። በዚህ በያዝነው ሳምንት ግን ሁኔታው ወደ ከፋ አቅጣጫ እንደገና ሊቀየር ይሆን የሚል ከፍተኛ ፍርሃት በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሮአል።   አስራ አንድ ህጻናትን ጨምሮ ከ70 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለውና በዚህ ሳምንት ኢድሊብ በሚባለው የሶሪያ ክፍለ ሃገር በምትገኝ ከተማ የተፈጸመው የመርዛማ ጭስ ጥቃት የተፈጸመው በሶሪያ መንግስት ስለሆነ አሜሪካ ዝም ብላ አታይም ብለው የአገሪቱ ፕሬዝደንት ትረምፕና ሌሎችም ባለስልጣኖቻቸው መናገራቸው ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ተስፋ አደብዝዞታል። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትርም አሜሪካንን አቋም በመደገፍ የሶሪያ መንግስት አገሪቱን የመምራት መብቱን አጥቷል ብለዋል። ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የሶሪያን መንግስትም ሆነ ሌሎችን መውቀስ ተገቢ አይደለም በማለት ሩሲያ በበኩሏ ሁኔታው ይጣራ ብላለች። አይሲስን ለመዋጋት ነው በሚል ሰበብ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከተመረጡም በኋላ ተጨማሪ ለሽምቅ ውጊያ በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ የአሜሪካ ጦር አባላት ወደ ሶሪያና ኢራቅ ሲላኩ ከርመዋል። ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ደግሞ፣ ይህ የመርዛማ ንጥረ ነገር ጥቃት ሆን ተብሎ አሜሪካ በሶሪያ ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ እንዲሁም ከሩሲያና ከኢራን ጋር ያለው ውጥረት እንዲባባስ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ትንኮሳ (FALSE FLAG ATTACK) ነው እያሉ ናቸው። ለዚህም በ2013 ተፈጽሞ የነበረውንና በተባበሩት መንግስታት ሲጣራ የመርዝ ጭስ ተጠቃሚዎቹ የሶሪያ መንግስት ሳይሆን ተቀናቃኝ ሽምቅ ተዋጊዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለከተውን ሪፖርት ይጠቅሳሉ። የዚህ ሳምንቱ የመርዝ ጭስ ጥቃት ትንኮሳ ነው ከሚሉት መካከል የአሜሪካ ከፍተኛ ምክር ቤት (SENATE) አባል የሆኑት RAND PAUL ይገኛሉ። የሶሪያን መንግስት የምትደግፈው ሩሲያ፣ ኢራንና ሂዝቦላ የሚባለው የሊባኖስ ሽምቅ ተዋጊ ድርጅት በሶሪያ ብዙ የጦር ኃይል አላቸው። ሩሲያ ደግሞ የራሷ የሆነ የጦር ሰፈር በሶሪያ አላት። ስለዚህ አሜሪካና አጋሮቿ በሶሪያ ላይ ጥቃት ቢሰነዝሩ እነዚያ የሶሪያ አጋር አገሮች ሰራዊትም፣ በተለይ ደግሞ የሩሲያ፣ ሊሞቱና ሊቆስሉ ስለሚችሉ በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት ሊፈነዳና ከፍተኛ ጦርነትን ሊለኩስ እንደሚችል ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ። በአካባቢው ያለው ሁኔታ፣ በተለይም የኢራን፣ የሂዝቦላና ሌሎች ጸረ እስራኤል ኃይሎች እንቅስቃሴ የሚያሰጋት እስራኤልም በበኩሏ ራሴን ለመከላከል ነው በሚል በሶሪያ ግዛት ላይ አልፎ አልፎ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች የዓለም አቀፉን ውጥረት አባብሶታል።
እንደዚህ ያሉ የጦርነት ዜናዎችን ስንሰማ በመኖራችን የዛሬውም የዓለም ሁኔታ ከበፊቱ የተለየ አይደለም ብለው ሁኔታውን የሚያጣጥሉ ጉዳዩን በቅርበት የማያጠኑ ወይም በትክክል ሊገነዘቡ የማይችሉ ብቻ ናቸው። በሁኔታዎቹ ላይ የቅርብ መረጃ ያላቸው ባለሙያዎችና ታዛቢዎች ግን እጅግ በአለማችን ላይ በወታደራዊ ኃይላቸው ተወዳዳሪ በሌላቸው በአሜሪካ፣ ሩሲያና ቻይና እንዲሁም ደግሞ በኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና ሌሎችም አገሮች መካከል ያለው ፍጥጫ በቀላሉ ፈንድቶ ሶሶተኛውን ሊለኮስ ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ። ከነዚህ አዋቂዎች፣ መሪዎችና ታዛቢዎች መካከል የድሮው የሩሲያ ፕሬዝደንት ሚካኤል ጎርባቾቭ፣ የካቶሊኩ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና የዓለም የኑክሊየር ባለሙያዎች ማህበር ይገኙበታል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት መዳረሱን ከሚያመለክቱን ነገሮች አንዱ ከፍተኛ የሆነ የጦርነትና የጦርነት ወሬ መብዛት ነው። ይህ ደግሞ 1ኛውና 2ኛው የዓለም ጦርነቶች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ እልቂቶች ከተካሄዱበት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በዓለም ላይ እያስተጋባ ያለ ታሪካዊ እውነት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ እነዚህ ሁሉ ሊሆኑ የግድ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ ሁሉ የዘለዓለም ህይወት ተስፋ ስላላቸው የሚያስፈራቸው የለም። 3ኛው የዓለም ጦርነት የዓለም መጨረሻ አይደለም። እጅግ ብዙ ህዝብ ግን ስለሚያልቅ ይህ እጅግ አሳዛኝና መሆን የሌለበት ነገር ነው። ስለዚህ አቅሙ ያላቸው በሙሉ እውነተኛ ሰላም እንዲገኝ መጣራቸው ተገቢና ሊደገፍም የሚገባ ነው። እያንዳንዱ በክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያንም ደግሞ የራሱ ድርሻ አለው፤ ይህም የክርስቶስን ወንጌል ላልሰሙ ሁሉ ማድረስ፣ እምነቱን በተግባር በመኖር የእግዚአብሔርን መልካምነት በፍቅርና በእውነት ማሳየት፣ የዓለም መሪዎች የሰከነ እግዚአብሔርን የሚፈራና ሰላምን የሚያስቀድም ህሊና እንዲኖራቸው መጸለይ፣ ህዝቦችን ለማጥፋት የሚጠነሰሱ ክፉ ስራዎችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መቃወምና ከዓመጽ መራቅ ናቸው። በመጨረሻው ልንገነዘበው የሚገባ እውነት ግን፣ ይህን ሁሉ ክፉ ነገር የምንሰማው የሰው ልጅ በኃጢዓት ምክንያት በመውደቁና ከአምላኩ በመራቁ ነው። የዓለም መንግስታትም ሆነ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚችለውንና የሚገባውን ያድርግ እንጂ የእውነተኛና ዘላቂ ሰላም ባለቤት ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም እንደተናገረው ዳግም ይመጣል። በክርስቶስ ለሚያምኑም እጅግ ብሩህ የሆነ የዘለዓለም ተስፋ አለ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የሰውን ልጅ ጭንቅላትና ሰውነት ከኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጋር በቀጥታ በማያያዝ የማሻሻል ስራ እየተጧጧፈ ነው።

http://endtimeheadlines.org/2017/04/upgraded-humans-will-become-next-billion-dollar-industry/

እግዚአብሔር የፈጠረው በቂ አይደለም፣ እርጅናንና ሞትንም እናጠፋለን የሚሉ "ደካማ" የሆነውን የሰውን ጭንቅላትና ሰውነት የማሻሻሉ ስራ መጀመሩን የሚያበስሩ ዜናዎች በተደጋጋሚ እየወጡ ነው። ይህ የተያያዘውም ከነዚሁ ዜናዎች አንዱ ነው። ምናልባት ይህ ቀልድ ወይም ብቅ ብሎ የሚጠፋ የሚመስለው ካለ፣ ታላላቆቹ የምድር ኩባንያዎች ብዙ ቢሊዮን ብር በማፍሰስ ላይ እንዳሉና ከነዚህም ቴክኖሎጂዎች የመጀመሪያዎቹ እየተሰሩና እየተፈተሹ መሆኑን ልብ ይበል። ከዚህ ዜና ጋር ተያይዞ የቀረበው HOMO DEUS የተባለውና አዲስ የወጣ መጽሐፍ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ መረጃና እውቀት ለሚፈልጉ መልካም ንባብ ነው። የሆህን ዘመን በሚመስል ዘመን እየኖርን እንዳለ እናስተውል። በኖህ ዘመን የሰው ትእቢትና ኃጢዓት ሰማይ ስለደረሰ ነበር የዚያን ጊዜው ዓለም በውኃ የጠፋው። ገንዘብ ያለው የተሻሻለ ሰው እንዲሆን ቴክኖሎጂ ሲገጠምለት፣ ብ የሌለውን ደግሞ ምን ያደርጉት ይሆን።  የፈለጉት ሁሉ ይሳካለቸዋል ማለት አይደለም። ሊፈጥሩት የሚችሉት ጥፋት ግን በቀላሉ ሊገመት አይገባም። ዚህ የምድር ባለጸጎችና አዋቂ ነን ባዮች እንደሚያስቡት ሰው በአጋጣሚ ወደዚህ ዓለም ብቅ ያለ ቁስ ሳይሆን፣ በሚወደው አምላኩ በብዙ ጥንቃቄ ውብና ድንቅ ሆኖ የተሰራ ፍጥረት ነው። ዲያብሎስ በመጀመሪያ አዳምንና ሄዋንን በማታለል ከአምላካቸው ለይቶ በኃጢዓት እንዲወድቁና ወደ ሞት እንዲገቡ ገፋፋቸው። ዛሬ ደግሞ እርጅናን ታጠፋላችሁ፣ እንደ አምላክ የሚሆን እውቀትና ችሎታ ይኖራችኋል በሚል መልኩን ቀየር አድርጎ በመጣ ስህተት ይህችንም በጌታ ምህረት የቀረችለትን የምድር ሰባና ሰማንያ ዓመት እድሜው ለማፈራረስ ጠላት ቆርጦ ተነስቷል። የገዛናቸው ኮምፒውተሮች አስር ጊዜ መብራት መጥፋታቸው፣  አንዴ ቫይረስ ያዘው፣ አንዴ HACK ተደረገ፣ አንድ ጊዜ upgrade አድርጉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ network የለም፣ እየተባልን ቁም ስቅል ማየቱ ቀረና ጭራሹኑ ብለው ብለው ፈጣሪ የሰጠንን ሰውነት ከምናምን ጋር ሊቀጣጥሉት መከጀላቸው ምን ያህል የሰው ትእቢት ከፍ እንዳለ የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ የሚሄድበትን አቅጣጫ ምን ያህል እንደሳተም የሚያስረዳ ነው። ልብ ያለው ልብ ይበለው። በመለከት ድምጽ ቁጥር 6 ላይ እንዳቀረብኩት፣ ኮቤ ጃፓን በሚገኘው የRIKEN RESEARCH INSTITUTE ባደረገው ጥናት እንደተመለከተው የሰው ጭንቅላት በአንድ ሰከንድ ውስጥ የሚሰራቸውን ስራዎች ለመስራት 82,944 የኮምፒውተር ጭንቅላቶች (processors) በአንድ ላይ ተያይዘው ለመስራት የፈጀባቸው ጊዜ 40 ደቂቃ ነበር። ለአንድ ሰከንድ የሰው ጭንቅላት ስራ ይህ ሁሉ ኮምፒውተር ከተሰለፈ፣ ራሳችን በቀን የሚያከናውነው ለማድረግማ ምን ያህል ኮምፒውተሮች ይሰለፉ ይሆን። የሰውን ጭንቅላት፣ ችሎታና የእድሜ ገደብ እናሻሽላለን በሚል ሰበብ ሊያደርጉ ያቀዱት ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ምንም ያድርጉ ምን፣ ለሰው ልጅ ከስጋዊም ሆነ ከዘለዓለማዊው ሞት የመዳኛ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እድሜን የሚሰጥ የሚያሳጥርም እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር የፈጠረው ይህ ሰውነታችን ግሩምና ድንቅ ነው። ነገር ግን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ሊሆን ያለው ሁሉ ይሆናል። እግዚአብሔር መልካም ነው። ቅኖችንና እርሱን የሚሹትን ሁሉ ለክፉ አሳልፎ አይሰጥም። ስለዚህ በእርሱ የሚያምን ሁሉ መታወክ የለበትም። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ህይወት አለው። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላላመኑ ሁሉ ደግሞ የጌታ አምላክ የፍቅር እጆች አሁንም እንደተዘረጉ ናቸው። ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሌላ የዘለዓለም ህይወት መንገድም ዋስትናም የለም። ስለዚህ ቀኑ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመምጣት ከዚህ ቀውጢ ዘመን እናምልጥ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...