ጦርነትና የጦርነት ወሬ በዓለም ዙሪያ

http://theeconomiccollapseblog.com/archives/is-the-united-states-about-to-bomb-north-korea-the-white-house-says-the-clock-has-now-run-out

ከላይ በተያያዘው ዜና እንደምታነቡትና ከዚህም በፊት እንደ ጻፍሁት፣ ታላላቆቹ የምድር መንግስታት እጅግ  ብዙ ህዝብ ሊፈጁ የሚችሉ ጦርነቶችን ለመለኮስ እየተዘጋጁ ነው የሚሉ ዜናዎች በሰፊው ይናፈሳሉ። በ1950ዎቹ ዓመታት ተለኩሶ ብዙ ህዝብን ካጨፋጨፈና ኮሪያን ለሁለት ከከፈለ በኋላ ያለ ሰላም ውል የቆመው የሰሜንና የደቡብ ኮሪያ ጦርነት እንደገና ይፈነዳል የሚለው ፍርሃት ባለፉት 64 ዓመታት የአካባቢውን ህዝቦችና መንግስታት እንቅልፍ ሲነሳ ኖሯል። በአሜሪካ የምትደገፈዋ ደቡብ ኮሪያ ለደህንነቴ ታሰጋኛለች የምትለው ኮሚኒስቷ ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ከቻይና በምታገኘው የኤኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ ብቻ ሳትወሰን በደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና በአካባቢው የሰፈሩት የአሜሪካ ጦር ኃይሎችን ለመቋቋም ነው በሚል ሰበብ ታላቅ የጦር ሰራዊትን አሰማርታለች፣ የኑክሊየር ቦምቦችንም ሰርታለች። ባለፉት ብዙ ዓመታት እነዚህን የኑክሊየር ቦምቦች ለማሻሻልና የአሜሪካ ሰራዊት ወዳሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ የሚያደርሱ ሚሳኤሎችን ስትሰራና ስትፈትሽ ከርማለች። ይህ ደግሞ ከባላንጣዎቿ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከአሜሪካ ጋር ያለውን ውጥረት ከፍተኛ ቦታ ላይ ስላደረሰው ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሜሪካ ባለስልጣኖች “ጊዜው አልቋል” የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ በመሰንዘር በማንኛውም ጊዜ ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል አመልክተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት የኑክሊየር ቦምብ መጣል የሚችሉ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በደቡብ ኮሪያ፣ በጃፓንና በጉዋም ሰፍረው የጦርነት ልምምድ ሲያደርጉ ከርመዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች ምናልባት ይኼ ሁሉ ነጋሪት ድለቃ በዚህ ሳምንት በአሜሪካና በቻይና ፕሬዝደንቶች መካከል በሚደረገው የመጀመሪያው ጉባኤ ላይ ቻይና በደቡብ ኮሪያ ላይ ተጽእኖ እንድታደርግ ለመገፋፋት ነው ሲሉ፣ ሌሎች ግን በእርግጥም አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን በቅርቡ ታጠቃ ይሆናል ይላሉ። የሰሜን ኮሪያ የኑክሊየርና የሚሳኤል በከፍተኛ መንገድ ያሰጋኛል የምትለው ጃፓንም አሜሪካን ተገን በማድረግ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጥቃት ትፈጽም ይሆናል የሚሉ ዜናዎችም ሲናፈሱ ከርመዋል።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛት የሆነውን ክራይሚያን በጉልበት ወስዳለች፣ በምስራቅ ዩክሬን ያሉትን የሩሲያ ዝርያ ያላቸውን ህዝቦችም የመገንጠል እንቅስቃሴ ትደግፋለች፣ የሌሎችንም የምስራቅ አውሮፓን አገሮች ደህንነት ታሰጋለች በሚል ሰበብ በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲኩ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምስራቅና ሰሜን አውሮፓ በሩሲያ ድንበር ላይ ብዙ የጦር ሰራዊት፣ ታንኮች፣ መድፎች፣ የጦር አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮችና ሚሳኤሎች እንዲሁም ሌሎች መሳሪያዎችን አከማችቷል፣ ብዙ የጦርነት ልምምዶችንም አድርጓል አሁንም እያደረገ ነው። ይህንን የተገነዘበችው ሩሲያም የጦር ሰራዊቷን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ አቁማለች። እንዲሁም ደግሞ  የአሜሪካንን እና የአጋሮቿን ጥቃት ልታመክንበት የምትችላቸውን አዳዲስና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በከፍተኛ ፍጥነት እየሰራችና እየፈተሸች ሲሆን፣ በማንኛውም የሩሲያ ግዛትና ጥቅም ላይ ጥቃት ቢሰነዘር ከባለጋራዎቿ ቀድማ የኑክሊየር መሳሪያዎችን እንደምትጠቀም አስጠንቅቃለች።
በምስራቅና በደቡብ ቻይና ባህር አካባቢም በቻይናና በአሜሪካ እንዲሁም እንደ ጃፓን ባሉ የአሜሪካ አጋሮች መካከል ከፍተኛ ፍጥጫ ከተፈጠረ ውሎ አድሮአል። በቻይናና በሌላው ዓለም መካከል ለሚካሄደው ዋና የባህር ትራንስፖርት መተላከፊያ የደም ስር የሆነው የደቡብ ቻይና ባህር ብዙ ክፍሎች ከጥንትም ጀምሮ የኔ ናቸው የምትለው ቻይና እና፣ እንደፈለገኝ በፈለግሁት ቦታ የመሄድ መብት አለኝ የምትለው ቻይና ከፍተኛ የጦር ልምምዶችን በአካባቢው ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በዚያው በደቡብ ቻይና ባህር መካከል ያሉ ትንንሽ ደሴቶችን በመጠቀምን ሰው ሰራሽ ደሴቶችን በመስራት ቻይና አዳዲስ የጦር ሰፈሮችን እየመሰረተችና እያሰፋች ነው።  የአሜሪካንን አውሮፕላን እና ሚሳኤል ተሸካሚ የጦር መርከቦች ሊያጠፉ የሚችሉ አዳዲስ ሚሳኤሎችን፣ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን እና የራሷንም አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦችን በማሰማራት ላይ ያለችው ቻይና፣ ግዛቴ ነው የምትለውን እየጣሱ የሚሄዱትን የአሜሪካን የጦር አውሮፕላኖችና መርከቦች አልታገስም እያለች ስታስፈራራ ከርማለች።
ባለፉት ብዙ ዓመታት አሜሪካ በአካባቢው ካሉ አጋሮቿ ጋር በመሆን በሶሪያ ያለውን መንግስት ለመገልበጥ ተቃዋሚዎችን እና ሽምቅ ተዋጊዎችን በተዘዋዋሪና በቀጥታ ስታስታጥቅና ስትረዳ ከርማለች። ጽንፈኛ የሆነውን እስላማዊ የሽብር ድርጅት አይሲስን እንዋጋለን በሚል ሰበብ የሩሲያን መንግስት ለመጣል የሞከረችው ሙከራ ስላልተሳላካና፤ በሩሲያ፣ በኢራንና በሊባኖሱ ሂዝቦላ የሚደገፈው የሶሪያ መንግስት ከፍተኛ ወታደራዊ ድሎችን አግኝቶ የአገሩን ብዙ ክፍሎች እንደ ገና መቆጣጠር በመጀመሩ፣ የአገሩን መሪ የመምረጥ መብቱ የሶሪያ ህዝብ ነው ሲሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት የአሜሪካ ተወካይ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር። የማታ የማታ አሜሪካ ሃሳቧን ለወጠች፣ የሶሪያም ግጭት ወደ መፍትሄ ይደርስ ይሆናል ብለው ተስፋ ያደረጉ ብዙ ነበሩ። በዚህ በያዝነው ሳምንት ግን ሁኔታው ወደ ከፋ አቅጣጫ እንደገና ሊቀየር ይሆን የሚል ከፍተኛ ፍርሃት በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሮአል።   አስራ አንድ ህጻናትን ጨምሮ ከ70 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለውና በዚህ ሳምንት ኢድሊብ በሚባለው የሶሪያ ክፍለ ሃገር በምትገኝ ከተማ የተፈጸመው የመርዛማ ጭስ ጥቃት የተፈጸመው በሶሪያ መንግስት ስለሆነ አሜሪካ ዝም ብላ አታይም ብለው የአገሪቱ ፕሬዝደንት ትረምፕና ሌሎችም ባለስልጣኖቻቸው መናገራቸው ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ተስፋ አደብዝዞታል። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትርም አሜሪካንን አቋም በመደገፍ የሶሪያ መንግስት አገሪቱን የመምራት መብቱን አጥቷል ብለዋል። ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የሶሪያን መንግስትም ሆነ ሌሎችን መውቀስ ተገቢ አይደለም በማለት ሩሲያ በበኩሏ ሁኔታው ይጣራ ብላለች። አይሲስን ለመዋጋት ነው በሚል ሰበብ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከተመረጡም በኋላ ተጨማሪ ለሽምቅ ውጊያ በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ የአሜሪካ ጦር አባላት ወደ ሶሪያና ኢራቅ ሲላኩ ከርመዋል። ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ደግሞ፣ ይህ የመርዛማ ንጥረ ነገር ጥቃት ሆን ተብሎ አሜሪካ በሶሪያ ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ እንዲሁም ከሩሲያና ከኢራን ጋር ያለው ውጥረት እንዲባባስ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ትንኮሳ (FALSE FLAG ATTACK) ነው እያሉ ናቸው። ለዚህም በ2013 ተፈጽሞ የነበረውንና በተባበሩት መንግስታት ሲጣራ የመርዝ ጭስ ተጠቃሚዎቹ የሶሪያ መንግስት ሳይሆን ተቀናቃኝ ሽምቅ ተዋጊዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለከተውን ሪፖርት ይጠቅሳሉ። የዚህ ሳምንቱ የመርዝ ጭስ ጥቃት ትንኮሳ ነው ከሚሉት መካከል የአሜሪካ ከፍተኛ ምክር ቤት (SENATE) አባል የሆኑት RAND PAUL ይገኛሉ። የሶሪያን መንግስት የምትደግፈው ሩሲያ፣ ኢራንና ሂዝቦላ የሚባለው የሊባኖስ ሽምቅ ተዋጊ ድርጅት በሶሪያ ብዙ የጦር ኃይል አላቸው። ሩሲያ ደግሞ የራሷ የሆነ የጦር ሰፈር በሶሪያ አላት። ስለዚህ አሜሪካና አጋሮቿ በሶሪያ ላይ ጥቃት ቢሰነዝሩ እነዚያ የሶሪያ አጋር አገሮች ሰራዊትም፣ በተለይ ደግሞ የሩሲያ፣ ሊሞቱና ሊቆስሉ ስለሚችሉ በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት ሊፈነዳና ከፍተኛ ጦርነትን ሊለኩስ እንደሚችል ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ። በአካባቢው ያለው ሁኔታ፣ በተለይም የኢራን፣ የሂዝቦላና ሌሎች ጸረ እስራኤል ኃይሎች እንቅስቃሴ የሚያሰጋት እስራኤልም በበኩሏ ራሴን ለመከላከል ነው በሚል በሶሪያ ግዛት ላይ አልፎ አልፎ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች የዓለም አቀፉን ውጥረት አባብሶታል።
እንደዚህ ያሉ የጦርነት ዜናዎችን ስንሰማ በመኖራችን የዛሬውም የዓለም ሁኔታ ከበፊቱ የተለየ አይደለም ብለው ሁኔታውን የሚያጣጥሉ ጉዳዩን በቅርበት የማያጠኑ ወይም በትክክል ሊገነዘቡ የማይችሉ ብቻ ናቸው። በሁኔታዎቹ ላይ የቅርብ መረጃ ያላቸው ባለሙያዎችና ታዛቢዎች ግን እጅግ በአለማችን ላይ በወታደራዊ ኃይላቸው ተወዳዳሪ በሌላቸው በአሜሪካ፣ ሩሲያና ቻይና እንዲሁም ደግሞ በኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና ሌሎችም አገሮች መካከል ያለው ፍጥጫ በቀላሉ ፈንድቶ ሶሶተኛውን ሊለኮስ ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ። ከነዚህ አዋቂዎች፣ መሪዎችና ታዛቢዎች መካከል የድሮው የሩሲያ ፕሬዝደንት ሚካኤል ጎርባቾቭ፣ የካቶሊኩ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና የዓለም የኑክሊየር ባለሙያዎች ማህበር ይገኙበታል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት መዳረሱን ከሚያመለክቱን ነገሮች አንዱ ከፍተኛ የሆነ የጦርነትና የጦርነት ወሬ መብዛት ነው። ይህ ደግሞ 1ኛውና 2ኛው የዓለም ጦርነቶች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ እልቂቶች ከተካሄዱበት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በዓለም ላይ እያስተጋባ ያለ ታሪካዊ እውነት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ እነዚህ ሁሉ ሊሆኑ የግድ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ ሁሉ የዘለዓለም ህይወት ተስፋ ስላላቸው የሚያስፈራቸው የለም። 3ኛው የዓለም ጦርነት የዓለም መጨረሻ አይደለም። እጅግ ብዙ ህዝብ ግን ስለሚያልቅ ይህ እጅግ አሳዛኝና መሆን የሌለበት ነገር ነው። ስለዚህ አቅሙ ያላቸው በሙሉ እውነተኛ ሰላም እንዲገኝ መጣራቸው ተገቢና ሊደገፍም የሚገባ ነው። እያንዳንዱ በክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያንም ደግሞ የራሱ ድርሻ አለው፤ ይህም የክርስቶስን ወንጌል ላልሰሙ ሁሉ ማድረስ፣ እምነቱን በተግባር በመኖር የእግዚአብሔርን መልካምነት በፍቅርና በእውነት ማሳየት፣ የዓለም መሪዎች የሰከነ እግዚአብሔርን የሚፈራና ሰላምን የሚያስቀድም ህሊና እንዲኖራቸው መጸለይ፣ ህዝቦችን ለማጥፋት የሚጠነሰሱ ክፉ ስራዎችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መቃወምና ከዓመጽ መራቅ ናቸው። በመጨረሻው ልንገነዘበው የሚገባ እውነት ግን፣ ይህን ሁሉ ክፉ ነገር የምንሰማው የሰው ልጅ በኃጢዓት ምክንያት በመውደቁና ከአምላኩ በመራቁ ነው። የዓለም መንግስታትም ሆነ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚችለውንና የሚገባውን ያድርግ እንጂ የእውነተኛና ዘላቂ ሰላም ባለቤት ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም እንደተናገረው ዳግም ይመጣል። በክርስቶስ ለሚያምኑም እጅግ ብሩህ የሆነ የዘለዓለም ተስፋ አለ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...