ከፍተኛ የጦርነትና የህዝብ እልቂት ደመና በምድር ላይ እያንዣበበ ነው። ለራሳችን፣ ለመሪዎችና ላልዳኑ ሰዎች ሁሉ እንጸልይ!!
ባለፈው አጭር መልእክት ላይ እንደ ጻፉሁት፣ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነው ብለው ደቀ መዛሙርቱ በጠየቁት ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰጣቸው ምልክቶች
አንዱ ዘመኑ ሲደርስ ምድር ሁሉ በጦርነትና በጦርነት ወሬ መሞላቷ ነው። ከመቼውም ዘመን ይልቅ ዛሬ ምድራችን እጅግ አስከፊ በሆነ የጦርነት ስጋት
ውስጥ ወድቃለች። ጥቁር የጦርነትና የከፍተኛ እልቂት ደመና በብዙ የምድር ክፍሎች አንዣቧል። በምድር ኃያል ናት የምትባለው አሜሪካና
መሪዎቿ፣ እንደ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያና ጃፓን ያሉ አጋሮቿም ሆኑ በሌላው ወገን ያሉት እንደ ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሶሪያና
ሌሎችም ባላንጣዎቻቸው አንዴ ከተጀመረ ወደ ኋላ ሊመለስ በማይችል የጦር ሰበቃ ውስጥ ገብተዋል። እንደ ቀላል ነገርና ጨዋታ ሰሜን
ኮሪያ አሜሪካንና አጋሮቿን በኑክሊየር ቦምብ አጠፋለሁ በማለት በተደጋጋሚ እየፎከረች ነው። ሁኔታው ያሰጋት አሜሪካም አሉ የተባሉ
አውሮፕላን ተሸካሚና የጦር መርከቦችን፣ የኑክሊየር ሚሳኤል ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን (SUBMARINES)፣ የኑክሊየር ቦምብ
ጣይ አውሮፕላኖችን እና በልዩ መንገድ የሰለጠኑ ወታደሮቿን በኮሪያው ባህረ ሰላጤ፣ በጃፓን፣ በአውስትራሊያና ሌሎችም የጦር ሰፈሮቿ
በትልቅ ፍጥነት ማከማቸቷን ቀጥላለች። ይህንን ከባድና አስጊ እድገት “ምንም አይደለም” ከዚህም በፊት ጦርነቶች ነበሩ ወደፊትም
ይኖራሉ እያሉ ለማንኳሰስ የሚሞክሩ ካሉ የአደጋውን ከባድነት ገና ያልተረዱ ናቸው። ሰሜን ኮሪያ ያለ የሌለ መሳሪያዎቿን አውጥታ
የተኩስና የጦርነት ልምምዶችን እያደረገች ነው። አሜሪካ የቦምቦች ሁሉ እናት ያለችውን ከኑክሊየር ቦምብ በታች የመጨረሻ ከፍተኛ
ሃይል ያለውን ቦምብ በአፍጋኒስታን በማፈንዳትና በሶሪያ ላይ ቶማ ሆክ የተባሉ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ሰሜን ኮሪያንና አጋሯ እንደሆነች
በሰፊት የሚታመነውን ቻይናን ለማስፈራራት ሞክረው ነበር። ይህም አልበቃ ስላላት ደግሞ MINUTEMAN 3 የተባለውን ኑክሊየር ቦምብ
ተሸካሚ የሩቅ ጥቃት ሚሳኤል APRIL 25፣2017 ላይ በመተኮስ ከ 6400 ኪሎሜትር በላይ ከሄደ በኋላ በፓሲፊክ ውቅያኖስ እንዲወድቅ
በማድረግ በሰሜን ኮሪያንና በአጋሯ ቻይና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ለማድረግ ሞክራለች። ቆሟል ተብሎ ባለፉት ጥቂት ሲነገርለት የነበረው
የአፍጋኒስታን ጦርነት እንደ ገና አገርሽቶ ብዙ ህዝብ እያለቀ ነው። በዚያ ለሚዋጉት ታሊባን ደግሞ ሩሲያ መሳሪያ ታቀብላለች የሚሉ
ዜናዎች የሚናፈሱት ሩሲያን ለመተንኮስ ነው የሚሉ ታዛቢዎችም ብዙ ናቸው። የጦርነትና እልቂት ደመና በሰሜንና በምስራቅ አውሮፓም
(በተለይም በዩክሬን፣ በክራይሚያና የቦልቲክ ሪፐብሊኮች በሚባሉት) ካንዣበበ ውሎ አድሮአል። በአሜሪካና በሩሲያ፣ በአሜሪካና በቻይና፣
በአሜሪካና በኢራን እንዲሁም በሌሎች አገሮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ከተፈጠረ ውሎ አድሮአል።
አሁን ዓለምን ያሰጋው የኑክሊየር ጦርነት ከዚህ በፊት ምድር አይታው የማታውቀውን የህዝብና የእንስሳት እልቂት ከማምጣቱም
በላይ ብዙውን የምድርን አካልና ስርዓት ስለሚመርዝና ስለሚያጠፋ ዛሬ የምናውቃት ዓለም ገጽታ ሊቀየር ይችላል። የኑክሊየር ቦምብን
የጥፋት ጉልበት በቅርቡ የሚያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና ሌሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች ምናልባት ጌታችን “ያ ቀንስ ባያጥር ስጋን
የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር” ያለው ምናልባት በምድር ላይ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ሊከሰት የሚችለውን የኑክሊየር ጦርነትና የህዝብ
እልቂት በተመለከተ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ። የኑክሊየር አደጋ ለማንዣበቡ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ። ከነዚህ አንዱ የአሜሪካ መንግስት
በነዚህ ቀናት እያደረገ ያለው በኑክሊየር ጦርነት ጊዜ እርዳታ የመስጠት ልምምድ፣ ጃፓን ህዝቧ የኑክሊየር ጥቃት ቢፈጸም ዜጎቿ ራሳቸውን
እንዴት ሊከላከሉ እንደሚችሉ እያሰለጠነችና የተለያዩ ቁሶች እንዲገዙ ማበረታታቷ ምሳሌዎች ናቸው። የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጡ ትንቢቶች ምድር
በከፍተኛ የጦርነት እልቂት እንደምትጎዳ በግልጽና በተደጋጋሚ ያስረዳሉ። ከነዚህም ትንቢቶች ብዙዎቹ በዮሐንስ ራዕይና በትንቢተ ዳንኤል
ውስጥ ይገኛሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኒቱ አድርጎ የተቀበለና ለጌታ በመታዘዝ የሚላለስ ክርስቲያን ሁሉ የሚያስፈራው ምንም
ነገር የለም። ጦርነትና የጦርነት ወሬ በሰፊው ዓለምን ሁሉ ማናወጥ የጌታችን ዳግም ምጽዓት ለመቃረቡ ምልክት ሊሆን ስለሚችል እኛ
ክርስቲያኖች ሁላችን ለምድር መሪዎች፣ በነዚያ አገሮች ለሚኖሩ ክርስቲያኖችና ጌታን ሳያውቁ ሊሞቱ ስለሚችሉ ሰዎች ሁሉ መጸለይ ያስፈልገናል።
በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በምትወጣው የመለከት ድምጽ (ቁጥር 7) ላይ ይህንን በተመለከተ ሰፋ ያሉ መረጃዎች፣ ትንተናዎችና ትምህርቶች
ይቀርባሉ። በግልም ሆነ በህብረት ለመሪዎችና ለተራውም ህዝብ በሙሉ እንጸልይ። ጌታ ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ