እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን
ወደ ክርስቶስ እንደግ። ኤፌሶን 4፡15
ወደዚህ ዓለም ሥጋን ለብሶ
በመምጣት የደህንነትን የምስራች ወንጌል ያበሰረው እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳና
ወደ አብ ካረገ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ የበግ ለምድ አልብሶ የሚልካቸው ተኩላዎቹ የጌታን ህዝብ ለማመሳቀል፣ ግራ ለማጋባትና ቢቻላቸውም
ከእውነተኛው የወንጌል እምነት ለማራቅ እንደሚዘምቱ ደቀ መዛሙርቱን ደጋግሞ አስተምሮአቸው ነበር። በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 13
ከቁጥር 24 እስከ 30 የሚገኘው ምሳሌ ከነዚህ ትምህርቶች አንዱ ነው። የእርሻው ባለቤት (ኢየሱስ ክርስቶስ) እውነተኛ የህይወትን
(የስንዴውን ምሳሌ) በቀን (በገሃድ፣ በአደባባይ) በእርሻው ላይ ከዘራ በኋላ ይህንን እውነተኛ ዘር የሚመስል የውሸት ዘር (እንክርዳድ)
ደግሞ ጠላት በሌሊት (በድብቅ) በእርሻው ላይ ዘራ። አስተውሎ ለማያውቀው
ለማንኛውም ገበሬ የስንዴና የእንክርዳድ ተክል ብዙ ተመሳሳይነት ስላላቸው እርሻው ላይ በሚበቅሉበት ጊዜ አንዱን ከሌላው ለመለየት
አስቸጋሪ ነው። የእርሻው ሰራተኞች የእንክርዳዱን መዘራት ያስተዋሉት ዘሩ በበቀለና ማፍራት (ማሸት) በጀመረ ጊዜ ነበር። ይህ እስኪሆን
ድረስ ደግሞ ብዙ ቀናት አልፈዋል። የእንክርዳዱ ዘር መልካሙን የእርሻውን አፈር፣ አየርና ውሃ ከስንዴው ጋር እየተሻማ ለምልሞና
ተመሳስሎ ብዙ ሳምንትታት ቆይቷል። የፍሬ ጊዜ ሲደርስ ነው ጉዱ እየታየ የመጣው። ሰራተኞቹም የእርሻውን ባለቤት የዘራኽው መልካም
የስንዴ ዘር ብቻ አልነበረምን ብለው የጠየቁትም በእርሻው ላይ የሚታየው ፍሬ የስንዴ ብቻ እንዳልሆነ በተገነዘቡ ጊዜ ብቻ ነበር።
ታዲያ የእርሻው ባለቤት መልስም ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ደጋግሞ እንዳስተማራቸውና እንዳስጠነቀቃቸው የማያሻማ ነበር። ባለቤቱ የዘራው
ዘር እንከን የሌለው ስንዴ ሲሆን፣ እንክርዳዱን በእርሻው ላይ በሌሊት ዘርቶ የሄደው ደግሞ የእርሻውና የእርሻው ባለቤት ጠላት ነበር።
የእርሻው ባለቤት ክርስቶስ፣ እርሻው በክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች እና እንክርዳዱን የዘራው ደግሞ የሰው ዘር ጠላትና የክርስቶስ
ተቃዋሚ ዲያብሎስ መሆኑን ከምሳሌው ለመረዳት ይቻላል። የእንክርዳዱ በእርሻው ላይ መገኘትና ከስንዴው እኩል ፍሬውን እያፈራ መገኘቱ
ያስቆጣቸው የእርሻው ሰራተኞች በትክክለኛና ህጋዊ ቅንዓት ተነስተው እንክርዳዱን እንንቀል ባሉት ጊዜ ግን የእርሻው ባለቤት አልፈቀደላቸውም።
ምክንያቱም የባለቤቱ ዋነኛ ትኩረት የእያንዳንዱ የስንዴ ቅንጣት
(የጌታ ደቀ መዝሙር) ሕይወትና እንደ አቅሙም ሰላሳ፣ ስድሳ ወይም መቶ ፍሬ የማፍራቱ ሂደት እንክርዳዱን ለመንቀል በሚፈጠረው ግርግር
እንዳይተጓጎል ነው። ስንዴውም እንክርዳዱም ተጠጋግተው እግር ለእግር የቆሙት በአንዱ እርሻ ላይ፣ ምግባቸውን፣ ውሃና አየርም የሚያገኙት
ከዚያው ከአንዱ እርሻ ላይ ስለነበር ሰራተኞቹ እንክርዳዱን እንነቅላለን ሲሉ ስንዴውንም አብረው ሊመነግሉት ስለሚችሉ ነው። የእርሻው
ባለቤት ደግሞ አንድ የስንዴ ተክል እንኳን ቢሆን እንዲነቀል አይፈልግም፣ አይፈቅድምም ነበር። ስለዚህም እስከ መከር ቀን ድረስ
ተዋቸው፣ በዚያን ቀን አጫጆች የስንዴውን ነዶና እንክርዳዱን በሚገባ ይለዩታል፣ ስንዴው ወደ ጎተራው እንክርዳዱም ወደ እሳቱ ይሄዳል
ብሎ አዘዛቸው።
ጌታ ኢየሱስ ከላይ በተጻፈውና
በሌሎችም ምሳሌዎች አማካኝነት ደቀ መዛሙርቱ በዲያብሎስና ዲያብሎስ የበግ ለምድ አልብሶ ከሚልካቸው የሃሰት አስተማሪዎች ከሚፈለፍሉአቸው
እውነት መሳይ የሃሰት ትምህርቶች እንዲጠነቀቁ ካስተማራቸው ከ30 ዓመታት ያህል በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎቹም የጌታ ሃዋርያት
በዚሁ ርእስ ላይ ምእመናንን ሲያስተምሩ እንመለከታለን። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ምእራፍ 4 ላይ የኤፌሶን ከተማ
ክርስቲያኖች በዙሪያቸው እየነጎደ ከነበረው የተለያዩ የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ነፋስ እንዲጠነቀቁ ያስተማራቸው በሚከተሉት
ቃላት ነው፤
“እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፣ በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም
እየተንሳፈፍን ሕጻናት መሆን ወደፊት አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ
ክርስቶስ እንደግ። ከእርሱም (ከክርስቶስ) የተነሳ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሰራ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና
እየተያያዘ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።” ኤፌሶን 4፡14-16
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ
የሚያምኑ ቅዱሳንን ከእውነተኛው የወንጌል መንገድ ለማሳት፣ በክርስቶስ ያላመኑት ደግሞ እውነቱን እንዳያውቁና እንዳይድኑ ለማገድ
ጠላት ዲያብሎስ ከሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች ሁሉ እጅግ አደገኞቹ ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተመሳስለው የሚፈጠሩ የሃሰት ትምህርቶች
(doctrines)
ናቸው። እነዚህን የሃሰት ትምህርቶች የሚያስተምሩ ሰዎች ክርስቲያን ይመስላሉ፣ እንደ
ክርስቲያን ያወራሉ፣ በእግዚአብሔር ቃልና በእግዚአብሔር መንፈስ ሊለዩአቸው የማይችሉ አዳዲስ ክርስቲያኖችንና ገና የወንጌልን እውነት
ያልተቀበሉ ሰዎችን የመሳብና የማስከተል ችሎታም አላቸው። ስለ እግዚአብሔር ያወራሉ። ነገር ግን፣ እነሱ እናምነዋለን የሚሉት እግዚአብሔር
በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት የሚያምኑ ክርስቲያኖች የሚከተሉት የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር አይደለም። ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ነገር ግን እነሱ እንከተለዋለን የሚሉት ክርስቶስ
በመለኮትነት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነውን፣ የነበረውን፣ ያለውንና የሚመጣውን፣ እኛን ለማዳን ከድንግል ማርያም ስጋን
ለብሶ የተወለደውን፣ ከኃጢዓት ፍጹም ነጻ የሆነ ሕይወትን በምድር ላይ ከተመላለሰ በኋላ የኃጢዓታችንን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ
የሞተውን፣ የተቀበረውን፣ በሶስተኛው ቀን ከሞት የተነሳውን፣ በክብር ያረገውንና በአብ ቀኝ የተቀመጠውን፣ ዛሬ ስለ እኛ የሚማልደውን፣
እንደገና በክብርና በአካል ተመልሶ የሚመጣውን፣ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደውን እግዚአብሔር ወልድን አይደለም። ስለ መንፈስ
ቅዱስም ሲናገሩ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮትነቱ እኩል የሆነውን፣ በክርስቶስ የሚያምኑትን ወደ እውነት ሁሉ የሚመራውን፣ ዓለምን
ስለ ኃጢዓት ስለ ጽድቅና ስለፍርድ የሚወቅሰውን የራሱ ባህርይና ሰውነት ያለውን መንፈስ ቅዱስን አይደለም።
ስለ ሐሰት ትምህርቶች ስናጠና
ማስተዋል የሚገባን አንድ ትልቅ ቁም ነገርም አለ። ሆን ተብለው የተፈጠሩ የለየላቸው የሐሰት ትምህርቶች አሉ። እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች
ሰዎች እውነተኛውን እግዚአብሔርን፣ በተለይም ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳያውቁና አምነው እንዳይድኑ የተፈጠሩ ናቸው። በሌላው
ወገን ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት እናምናለን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ እንቀበላለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል
በሚገባ ካለመማራቸውና በትክክል ካለመረዳታቸው የተነሳ በተሳሳተ መንገድ የሚያስተምሩአቸው ትምህርቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ
ሰባኪዎችና አስተማሪዎች አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ በምድራዊ ገንዘብም ሃብታም ይሆናል፣ አይታመምም፣ አይቸገርም ይላሉ። ከዚህም
በማለፍ አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ ካመነ በኋላ በዚህ ዓለም ገንዘብ ድሃ ቢሆን፣ ቢታመምና ቢቸገር ወይም ፈውስንና ተአምራትን
ባይለማመድ ይህ የሆነበት የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ስላላወቀና በትክክል ስላላመነ ነው ብለው ያስተምራሉ። እንዲህ ያሉ ትምህርቶች
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በከፊል ብቻ ያካተቱና የቃሉ መሰረት የሌላቸው ናቸው። እንደዚህ ያሉ ትምህርቶች ብዙ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የተገኘውን የዘለዓለም ሕይወት በመቀበል ፈንታ በምድራዊ ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታሉ፣ በአስተማሪዎቹ
የሚነገሩአቸው ነገሮችም በሙሉ ሊፈጸሙ የማይችሉ ስለሆኑ ብዙዎችን ያሰናክላሉ። በቅንነት፣ እውነቱ ሳይገባቸው የተሳሳተ ነገርን የሚያስተምሩ
ሰዎች አንድ ቀን እውነቱ ሲገለጽላቸው በንስሐ ሊመለሱ ይችላሉ። እውነቱን
በሚገባ ከተረዱና የተሳሳተ ትምህርታቸው የሚፈጥረውን መሰናክል ከተረዱ በኋላ በእልህ የተሳሳተ ትምህርታቸውን ማስተማር ከቀጠሉ ግን
ዓመጻ ነውና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፍርድ ያጋልጣሉ።
የሃሰት ትምህርቶች ብዙ
ዓይነት ናቸው። ትምህርቶቻቸውና ፍልስናዎቻቸውም ብዙና የተወሳሰቡ ስለሆኑ እንዲህ ባለ አጭር መልእክት ለመግለጽ ያስቸግራል። የሚቀጥለው
የመለከት ድምጽ መጽሔት በዚህ ርእስ ላይ ሰፋ ያለ ትምህርትን ይዞ ይቀርባል። ለአሁኑ ያህል ግን የነዚህን የሐሰት ትምህርቶች ዋና
ዋና ባህርያት ለመለየት የሚያስችሉንን አንዳንድ ነጥቦች ብቻ በአጭሩ እንመልከት፤
1) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። አስተማሪዎቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን የሚሉት ክርስቲያኖችን
በቀላሉ ለማጥመድ እንዲቻላቸውና በዓለም ሁሉ የተሰበከውን የእውነትን ወንጌል መደገፊያ በማድረግ የሃሰት ትምህርቶቻቸውን ለማስተማር እንዲመቻቸው ብቻ ነው 2ኛ ጴጥሮስ 3፡16-17
2) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከተጻፉት ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻህፍት ሌላ (ተጨማሪ) በሃሰተኛ ሰዎች የተጻፉ
የሃሰት ትምህርቶችን የያዙ መጻህፍትን ይከተላሉ። 1ኛ ጢሞቲ 4፡1
3) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተቀመጠውን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት (ሥላሴ) ይክዳሉ
ማቴዎስ 28፡19-20 1ኛ ዮሐ 2፡23
4) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የሰውን ሥጋ ለብሶ ከድንግል ማርያም
መወለዱን ይክዳሉ 1ኛ ዮሐ 4፡3
5) አንዳንድ የሐሰት ትምህርቶች ኢየሱስ ክርስቶስን እናምናለን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱንና ሰው ሆኖ የሰውን አካል ለብሶ
በዚህ ምድር ላይ መመላለሱን እንቀበላለን ቢሉም ከአብና ከወልድ እኩል የሆነውን መለኮታዊ ባህርዩን ግን ይክዳሉ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡1
1ኛ ዮሐ 4፡3
6) ኢየሱስ ክርስቶስን እናምናለን የሚሉ ብዙ የሃሰት ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በስጋ መሞቱን፣ በሶስተኛው
ቀን በስጋ ከሞት መነሳቱን፣ ከአርባ ቀንም በኋላ በአካል ወደ ሰማይ ማረጉንና፣ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ መቀመጡን ይክዳሉ 2ኛ ጢሞቲ
3፡5 2ኛ ጴጥሮስ 2፡1
7) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የሰው ልጅ ሁሉ ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር
ጸጋ ብቻ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢዓታችን መሞቱን በማመን መሆኑን ይክዳሉ ገላትያ 5፡4
8) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ሞትና ፍርድ ሊያድን የሚችለው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ
መሆኑን ባይክዱም፣ በተግባር ግን ከእግዚአብሔር አብ፣ ከወልድና ከመንፈስ
ቅዱስ (ከሥላሴ) በተጨማሪ ፍጡራን የሆኑ መላእክትና ቅዱሳንም ሰውን ከኃጢዓትና ከዘለዓለም ፍርድ ያድናሉ ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉ
ቆላስይስ 2፡18-19
9) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጻድቃንና በኃጥዓን ላይ ለመፍረድ በክብር፣ በአካል ዳግም ተመልሶ መምጣቱን
ይክዳሉ፣ ወይም ያውገረግራሉ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡4
10) ብዙ የሐሰት ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ፍቅር ከእግዚአብሔር እውነትና ቅዱስነት በመነጠል፣ “ዋናው እምነትና ፍቅር ነው”
ይላሉ። ቀጥለውም ሰው የሚድነው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ፣ በጸጋ ስለሆነ ካመነ በኋላ እንደፈለገው በኃጢዓት መመላለስ ይችላል
ብለው ያስተምራሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ ይወዳል፣ ነገር ግን ኃጢአትንና ዓመጽን
ሁሉ ደግሞ ይጠላል። ያ ባይሆንማ ኖሮ ጌታ ኢየሱስ የኃጢዓታችንን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ መሞት ባላስፈለገውም ነበር። ኢየሱስ
ክርስቶስን የሚያምን ሰው የኃጢዓት ባሪያ ሆኖ ሊኖር አይችልም። ኃጢዓትን የሚያደርግ የኃጢዓት ባሪያ ነውና። የይሁዳ መልእክት ቁጥር
4 ዕብራውያን 10፡26-31 ዮሐ 8፡34
11) የሐሰት አስተማሪዎች የሚሰሙአቸውን ሰዎች ስለራሳቸው ትልቅነት፣ እውቀት፣ ልዩ መገለጽ በመንገር ተከታዮቻቸው ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስን በማወቅ ፈንታ በነሱ (በአስተማሪዎቹና በመሪዎቹ) ማንነትና ስራ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋሉ። 2ኛ ቆሮ 4፡5 ዮሐ 3፡30
12) የሃሰት ትምህርትና አስተማሪዎች ዋነኛው መለኪያ ፍሬያቸው ነው። እንደ እግዚአብሔር ቃል መልካም ፍሬን የማያፈራ ዛፍ ሁሉ
ይቆረጣል። ማቴ 7፡15-20
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ
በክብር ዳግም መገለጽ እየተቃረበ በሄደ ቁጥር የሃሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች እየበዙና እጅግ እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ጌታ አስተምሮናል።
እነዚህ የሃሰት ትምህርቶችና አስተማሪዎቻቸው ቢቻላቸው በጌታ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡት እንኳን ለማሳት ይሞክራሉ። ነገር ግን
ጌታ ኢየሱስ “የራሴን በጎች አውቃለሁ፣ የራሴም በጎች ያውቁኛል” ዮሐ 10፡14-15 እንዳለው፣ በጌታ ወንጌል የተጠሩ፣ የተመረጡና የታመኑ ሁሉ ድል ይነሳሉ። ራዕይ 17፡14
ዛሬ በዙሪያችን እየነጎደ
ያለው የሃሰት ትምህርቶች መብዛት፣ የብዙዎች ከወንጌል እውነት በመንሸራተት ከዓለም ዓመጽ ጋር መተባበር ሊያስደነግጠን አይገባም።
ሁሉም እንደተጻፈው ይፈጸማል። የእግዚአብሔር ጸጋ በሁለት ምሰሶዎች ላይ ቆሞአል። እነዚህም ምሰሶዎች እውነትና ፍቅር ናቸው። እውነት
ያለ ፍቅር ፍርድን ብቻ ያስከትላል። ፍቅር ያለ እውነት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቅዱስነትና የማይደፈር ባህርዩን እርሱም አምላክነቱንና
ጌትነቱን ይጻረራል። ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱና በመነሳቱ ሁለቱም የጸጋ ምሰሶዎች፣ እውነትና ፍቅር ጸንተዋል። ክርስቶስ
የሁሉ ነገር ማእከል ነው። ያለ እርሱ እውነትም ሆነ ፍቅር ሊኖሩ አይችሉም። የክርስትና እምነትና የዘለዓለም ሕይወት የማይናወጥ
መሰረት ክርስቶስ ነው። የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማይ በመጣው በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ቁጭ ብለን ማንበብ፣ መማር፣
ማሰብና ማሰላሰል፣ መጸለይ፣ ሕይወታችን እና ዘመኑን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መመርመር ያስፈልገናል። የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን
መጨረሻ ላይ ነው። ትንቢት ወደ ፍጻሜው እየቸኮለ ነው። በክርስቶስ ዳግም የተወለድን ሁሉ ሊሻር የማይችለውን የእግዚአብሔርን ቃል
በየእለቱ በልባችን ልንሸሽግና ወደ እውነት ሁሉ በሚመራን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ ያስፈልጋል። የክርስቶስን የወንጌሉን ብርሃን በላያችን
ላይ በማብራት መልካምን ስራ በእኛ የጀመረው ጌታ አምላክ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ሊያጸናን የታመነና ጻድቅ ነው። በክርስቶስ
በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ እያደረግን በክብር ለሚገለጽበት ለዚያ ለታላቁ ቀን የተዘጋጀን እንድንሆን የጸጋ ሁሉ አምላክ ማስተዋልን፣
ትህትናን፣ መንፈሳዊ ረሃብንና ጥማትን እርሱንም መፈለግን በውስጣችን ይሙላ። ለእርሱ ክብር በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ለዘለዓለም
እስከ ዘለዓለም ይሁን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ