የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች እውነተኛ ናቸው፣ በእርግጥ አሉ ተባለ።
(የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች እውን ናቸው፣ በእርግጥ አሉ ተባለ)
“የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና።” ማቴዎስ 10፡26 ሉቃስ 8፡17
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በሚቃረብበት ጊዜ ብዙ አስፈሪና አስደንጋጭ ምልክቶች በምድርና በሰማይ እንደሚታዩ መፅሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ከነዚህም ምልክቶች አንዱ በኖህ ዘመን እንደሆነው (ዘፍጥረት ምእራፍ 6) በጥልቁ የታሰሩት አጋንንት መልካቸውንና መልእክታቸውን መልካም ወደሚመስል ማታለያ ለውጠው ለሰው ልጅ ቴክኖሎጂን እንሰጥሃለን፣ ችግሮችህን ሁሉ እንፈታልሃለን፣ በምድር ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዓለማትም ላይ ለመኖር እንድትችል እንረዳሃለን በማለት በተለይ ባለፉት ሰባ በምድር ላይ የሃሰተኛውን ክርስቶስን መገለጥ ለማመቻቸት የሚሰሩት ምስጢራዊ የዓመጽ ስራ ነው። ባለፉት ሰባ የሚሆኑ ዓመታት ዓለም በቴክኖሎጂ እጅግ ተራቀቀች፣ በሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመታት ደግሞ ቴክኖሎጂ ከሰው ችሎታም በላይ ስለሚሆን፣ የሰው ልጅ አካል (ሰውነት) ራሱ ከቴክኖሎጂ ጋር በቀጥታ በመያያዝ ካልተሻሻለ በቀር በምድር ላይ መኖር አይችልም የሚሉ የTranshumanism ወንጌል ሰባኪዎች ብዙ ናቸው። ባለፉት 40 ዓመታት እንደ ከፍተኛ ምስጢር ተይዘው ከቆዩት ነገሮች መካከል የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች (UFOs) የሚባሉትና በእነርሱም ውስጥ ሲበሩ በብዙ ሰዎች የታዩና በፎቶ እንዲሁም በቪዲዮ የተቀረጹ የሰው ምሳሌ ያላቸው፣ ግን እንደ ሰው በአፋቸው የማይናገሩ ኤሊየንስ፣ ወይም ኤክስትራ ቴሬስትሪያልስ የሚባሉ ልዩ ፍጥረታት ናቸው። በአንድ በኩል የምእራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን እነዚህ በራሪ ዲስኮችና ልዩ ፍጥረታት የሉም፣ ቅዥት ነው እያሉ ሲያስተባብሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፊልም ኢንዱስትሪው የሰው ዘር የእነዚህን ፍጥረታት መኖር ቀስ በቀስ እንዲቀበለው ለማድረግ በመዝናኛ መልኩ ብዙ ፊልሞችን እየሰሩ ሲለቁ ሰንብተዋል። Star Wars የሚባለው ተከታታይ ፊልም ከብዙዎቹ ከነዚህ ፊልሞች አንዱ ነው።
ሰሞኑን ግን ከፊልምና ከቴሊቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች አልፈው፣ እነዚህ በራሪ ዲስኮችና ልዩ ፍጥረታት እውን ናቸው የሚሉ መረጃዎች በአደባባይ እየወጡ ናቸው። ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘው ዜና አንድና ዋና ምሳሌ ነው። ባለፈው ሳምንት Tom DeLonge በተባለው ታዋቂ ዘፋኝና የፊልም ባለሙያና ከፍተኛ የአሜሪካ መንግስት የመለካከያና የስለላ ድርጅት ሰራተኞች በነበሩ ሰዎች የተቋቋመው “tothestars.media” የሚባል ድርጅት እነዚህን በራሪ ዲስኮችና ከሌሎች ዓለማት የሚመጡ ፍጥረታት ናቸው የሚባሉትን በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት እስከ ዛሬ ድረስ አፍኖ አቆይቶአቸው የነበሩ ብዙ መረጃዎችን በመዝናኛ፣ በትምህርትና፣ በምርምርና በመረጃ መልክ ለህዝብ ይፋ እንደሚያወጣ ተገልጾአል። የነዚህ መረጃዎች ይፋ መውጣት ደግሞ በሰው ልጅ ሃይማኖቶች፣ አስተሳሰብና እውቀት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ፣ ለውጥና ቀውስ እንደሚያመጣ ከወዲሁ ተመልክቶአል። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት ቅዱሳን መላእክት፣ የሰው ዘር፣ እንስሳትና እጽዋት እንደሆኑ ይነግረናል። በሌላ አለማት ላይ ሌሎች ሰው መሰል ፍጥረታትን እግዚአብሔር እንደ ፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ዓመጸኛ መላእክትና ከነሱም አንዳንዶቹ ዘራቸውን ከሰው ዘር ጋር አደባልቀው የወለዱአቸው ኔፊሊም፣ ጊቦሪም፣ ራፋይም፣ ኤሚማውያን፣ ዘምዙማውያን ወዘተ የሚበሉ እኩያን ፍጥረታት እንደነበሩ በብሉይም በሃዲስ ኪዳንም በብዙ ስፍራ ተገልጾአል። እነዚህም በኋላ አጋንንት እንደሆኑና ከነሱም የተወሰኑቱ በጥልቁ እንደ ታሰሩና ሃሳዊው መሲህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት ከጥልቁ ወጥቶ የሰውን ዘር እንደሚያስት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን።
በሚቀጥሉት ወራትና ጥቂት ዓመታት ምድርን ሊያጥለቀልቅ ያለውና አዲስ ግኝት ተብሎ እንደ ዜናና መዝናኛ ሊቀርብ የተዘጋጀው የማይታወቁ በራሪ ዲስኮችና በነሱም የሚንቀሳቀሱት ልዩ ፍጥረታት (ኤሊየንስ፣ ኤክስትራ ቴሬስትሪያልስ) ዜና ከጌታ ዳግም ምጽዓት በፊት የምድርን ህዝብ ለማሳትና የክርስቶስን ወንጌል እውነት ለማጣጣልና ቢቻላቸውም ለመሻር ከሚለቀቁት ሃሰቶች አንዱ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራንና በጉዳዩ ላይ የረጅም ጊዜ ጥናት ያካሄዱ እውነተኛ የክርስቲያን መሪዎች ያስጠነቅቃሉ። በጥልቁ ውስጥ ታስረው ከቆዩ በኋላ ዘመኑ ሲደርስ ተፈትተው ምድርን ሁሉ ለማሳት የሚመጡትን አጋንንት እና የነሱ መሪ የሆነውን አባዶንን (አፖልዮንን) ከሌላ ዓለም የመጡ ከሰው የተሻሉ ፍጥረታት አድርጎ የሚቀርበው እውቀትና መሻሻል መሳይ ማታለያ ብዙዎችን ማሳሳቱ የማይቀር እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ቢጻፍም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ሁሉ ግን የጌታ ቀን እንደ ሌባ ይደርስባቸው ዘንድ በጨለማ አይደሉምና በሚመጡት ወራት የሚናፈሱትን ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተራቀቁ የሚመስሉ ዜናዎችን በጥንቃቄ ማጤን ያስፈልጋል።
በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰበከውን የመዳን ወንጌል ተቀብሎ ዳግም በመወለድ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀ ክርስቲያን ሁሉ የሚያስፈራው አንዳችም ነገር የለም። ነገር ግን ተግተን ልንጸልይና መጽሐፍ ቅዱሳችንን በቅርብ በማጥናት በምድር ላይ የሚካሄደውን ነገር ሁሉ ከቃሉ አንጻር መረዳት ያስፈልገናል። ሐዋርያት የነበሩበትን የመጀመሪያውን ምዕተ ዓመት እንደ “መጨረሻው ቀን” ከቆጠሩት እኛ ከሁለት ሺ ዓመታት በኋላ በምድር ላይ ያለን ክርስቲያኖችማ ምን ያህል መጨረሻው ላይ እንሆን? እንንቃ፣ በመጠን እንኑር፣ ሙሽራው መጥቶ ተኝተን እንዳያገኘን እንጸልይ፣ ወንጌልን እስንበክ፣ የክርስቶስን መንጋ እናስተምር፣ ለጌታ ቀን ራሳችንን እናዘጋጅ። ጌታ ይባርካችሁና ይጠብቃችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች እውን ናቸው፣ በእርግጥ አሉ ተባለ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...