በዓለማችን ላይ ይህ ሁሉ የምድር መናወጥ፣ አለመረጋጋት፣ መከራና ትርምስ ሲከሰት የዘለዓለም ሕይወት ኢንሹራንስ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ችላ ብለነው ይሆን?

በዓለማችን ላይ ይህ ሁሉ የምድር መናወጥ፣ አለመረጋጋት፣ መከራና ትርምስ ሲከሰት የዘለዓለም ሕይወት ኢንሹራንስ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ችላ ብለነው ይሆን?  https://www.rt.com/news/409633-iran-iraq-earthquake-updates/

ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 86 የሚሆኑ የምድር መናወጦች በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት ተመዝግበዋል። ከነዚህ ውስጥ ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ሰዓት ድረስ 100 በላይ ሰዎችን የገደለውና በንብረት ላይ ትልቅ አደጋን ያስከተለው በምስራቃዊው የኢራቅ ክፍልና በኢራን ድንበር አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ነው። ይህ የፈረንጆቹ ዓመት ከተጀመረ ጀምሮ ብቻ 110 በላይ የሚሆኑ ዋና ዋና መንቀጥቀጦች እንደተከሰቱ  የምድር መንቀጥቀጥን የሚያጠናውና የሚከታተለው የአሜሪካው መንግስት ቢሮ (USGS) መረጃዎች ያሳያሉ። በምድራችን ላይ ባሉት ትልልቅ ውቅያኖሶች፣ ባህሮችና ሀይቆች ውስጥ ያሉ በብዙ የሚቆጠሩ ትልልቅና ትንንሽ ፍጥረታት በየእለቱ እያለቁ መሆናቸውም በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይዘገባል። ለምሳሌ ያህል http://www.end-times-prophecy.org የተሰኘውን ድረ ገጽ መጎብኘት ዝርዝር መረጃዎችን ይሰጣል። ታላላቅ የሚባሉና በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ እንደ ከዋክብት የሚታዩ የሆሊውድ ተዋናዮች፣ ዲሬክተሮች፣ ዘፋኞችና፣ በፊልም ኢንዱስትሪው ዋና ዋና የሚባሉ ብዙ ሰዎች በታዋቂ አዋቂ ተዋናዮችና ነፍስ ባላወቁ ልጆችም ላይ ሳይቀር የገንዘብ ስልጣናቸውን በመጠቀም ሲያደርሱ የኖሩት ወሲባዊ ጥቃት ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ ቁጥር እየተጋለጠ መጥቶአል። ከላይ ለሚያዩት መልካም የሚመስለውና በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች የሚያዩአቸውን ፊልሞች፣ ቲያትሮችና የቴሌቪዝን መዝናኛዎችን የሚያመርተው ይህ ኢንዱስትሪ ጉድ በምእራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን መዘገብ እንደሚገባው ሳይዘገብ እስከ ዛሬ ታፍኖ ቢቆይም፣ እጅግ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣ ኮረዶችና ጎልማሶች በአሰሪዎቻቸውና ባለጸጎች የኢንዱስትሪው ዋናዎች የደረሰባቸውን መዋረድና በደል በአደባባይ እያወጡ ነው። የተሻለ እድል፣ ስራ፣ ገንዘብ፣ ዝናና ታዋቂነትን ታገኛላችሁ በሚል ማታለያ ከየቤተሰቦቻቸው ተታልለው ወደ የፊልሙ ኢንዱስትሪ ዋና ዋና መናኸሪያ ከተማዎች ከሄዱ በኋላ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ጠፍተው የቀሩም እጅግ ብዙ እንደሆነ ብዙ የነጻው መገናኛ ብዙኃንና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ያመለክታሉ።  የዲሞክራሲ፣ የሰላምና የብልጽግና ዋና ምሳሌ ነኝ በምትለ አሜሪካ እየተፈጸሙ ያሉት የሽብር ጥቃቶች፣ አለመረጋጋትና አምልኮ ስፍራዎችን እንኳን ሳይቀር ሰላማዊ ህዝብ የፈጁ ግድያዎች ብዙ አሜሪካውያንን እና ምእራባውያንን "ዓለም ወዴት እየሄደች ነው" በሚል ጥያቄና ፍርሃት ውስጥ ከቷል።
በነዳጅ ሃብቷ እጅግ ሃብታም የሆነችውና በንጉስ የምትመራው ሳውዲ አረቢያ የአረብ ጸደይ ተብሎ መንግስታትን ካፈራረሰው ቀውስ ብታመልጥም ዛሬ ደግሞ በተራዋ በልዑላኑ ቤተሰብ መካከል በተፈጠረ ውዝግብ ቀውስ ውስጥ እየገባች መሆኑ ደግሞ ከሰሞኑ ትልልቅ ዜናዎች አንዱ ነው። ይህ ቀውስ ደግሞ አገሪቱ ከኢራን ጋር ካላት ፉክክርና በየመን ስታካሂ  ከቆየችው ጦርነት እንዲሁን በሊባኖስ፣ በኢራቅና በሶሪያ ከታየው የኢራን ተጽእኖ መስፋፋት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አካባቢውን በሙሉ ወደ ጦርነት እሳት ሊያስገባ ይችላል በማለት ብዙ አዋቂዎች ያስጠነቅቃሉ። በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መሄዱም ብዙዎችን እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሮአል። የአሜሪካና የአጋሮቿ የምእራብ አውሮፓ አገሮች ጦር ለሩሲያ አዋሳኝ በሆኑ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች መስፈር፣ ሰሜን ኮሪያ የኑክሊየር ቦምብና ግዛቶቼን ሊመቱ የሚችሉ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች የማምረት እርምጃዋን ካላቆመች በጦርነት አፈራርሳታለሁ በማለት አሜሪካ መዛቷ እና ከፍተኛ ብዛት ያለውን ጦሯን ወደ አካባቢው ማሰማራቷ፣ የቻይናን የኤኮሚና ወታደራዊ ግስጋሴ ለመግታት በማለት አሜሪካ በደቡባዊው የቻይና ባህር አካባቢ ከቻይና ጋር የገባችው እሰጥ አገባ፣ ሶሪያንና ሊባኖስን እረዳለሁ በሚል ሰበብ ኢራን በድንበሮቼ አካባቢ ያላትን ተጽእኖ ስለጨመረች በሶሪያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ በማለት እስራኤል መዛቷ 3ኛው የዓለም ጦርነት እንዲነሳ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁኔታዎች እያባባሰ መምጣቱ ብዙዎች አዋቂዎችንና መሪዎችን እጅግ ያሳሰበ ነገር ነው። ከምድር ላይ ጠፍተው ከነበሩ ብዙ ህዝብ ከሚፈጁ ወረርሽኝ በሽታዎች መካከል አንዱ የሆነው ጥቁሩ መቅሰፍት (black plague) በማደጋስካር ብዙ ሰዎችን እየገደለ ነው፣ በፍጥነት በመሰራጨትም በዓለም ላይ ብዙ ህዝብን ሊገድል ይችላል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቆአል። ይህም ሁሉ ሳይበቃ ታዋዊ የሆኑት የፊዚክስ ፕሮፌሰር ስቲቨን ሆውኪንግ እና የእንግሊዙ ልዑል ዊሊያም የዓለም ህዝብ ቁጥር እጅግ ስለበዛ የምድርን የህይወትና የአየር ንብረት ሚዛን ያናጋል በፍጥረታትም ላይ ቀውስ ይፈጥራል እንዳሉ ተዘግቧል። ፕሮፌሰር ሆውኪንግ ከዚህም በማለፍ የሰው ዘር ከልክ በላይ በሆነ መንገድ የምድርን የኃይል ምንጮች በመጠቀም በሚቀጥሉት 600 ዓመታት ምድርን በእሳት ያቃጥላታል ሲሉ ፍርሃታቸውን ገልጸዋል። ለዚህም መድሃኒቱ የሰው ዘር ምድርን የምትመስል ሌላ ዓለም በህዋ ውስጥ ፈልጎ ወደዚያ መሄድ መጀመር ነው ሲሉ መፍትሄ ያሉትን ሰንዝረዋል።  በእስራኤል የሚገኙ ታዋቂ ራባይ (መምህር) ደግሞ የመሲሁ ማንነት በርቡ ለአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች በህልም ይገለጻል ሲሉ ተናግረዋል። እርሳቸው የሚሉ መሲህ ደግሞ ክርስቲያኖች የምንከተለው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም።
አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት መጨረሻ ሲቃረብ በምድር ላይ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ የምድር መናወጥ፣ ጦርነትና የጦርነት ወሬ፣ ህዝብ በህዝብ መንግስት ደግሞ በመንግስት ላይ መነሳት እንደሚበዛ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ሌሎችንም ብዙ ምልክቶች እንደሚከሰቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሃዋርያትና ነቢያት አመልክተዋል። ምናልባት ይህ በዘመናችን የምናየው ነገር ሁሉ በወንጌል የተገለጸው የመጨረሻው ዘመን የምጥ ጣር መጀመሪያ ይሆን?  ከሆነስ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ቤት እንዳለን አረጋግጠን ይሆን። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሰው ልጅ የዚህ ዓለም ህይወት በጊዜው ያበቃል። ሰው በክርስቶስ ቢያምንም ባያምንም ከሞት ባሻገር የዘለዓለም ህይወት አለ። በክርስቶስ የሚያምን ያን ዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ይኖራል። ክርስቶስ የሌለው ደግሞ ወደ ዘለዓለም ጨለማ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ይሄዳል። እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ስለወደደ የኃጢዓታችንን እዳ በልጁ የመስቀል ሞት ከፍሎ ሁላችንንም ወደ መንግስቱ ጋብዞናል። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛችን ለማድረግ ዛሬ ነገ አንበል። በክርስቶስ የምናምን ደግሞ እርምጃችን ከእርሱ ጋር እናስተካክል። በዓለማችን ላይ የሚካሄደውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያየው ማየት እንድንችልና ልባችንን ወደ እርሱ እንድናቀና የአብርሃም፣ የይስሃቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...