ከአስራ አምስት ሺህ የሚበልጡ የዓለማችን ሳይንቲስቶች የሰው ዘርና ምድራችን ወደ መጥፊያቸው እጅግ ተቃርበዋል በማለት አስጠነቀቁ ተባለ

“በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱ ድምጽ የተነሳ እያመነቱ ይጨነቃሉ፣ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሳ ይደክማሉ፣ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ።” ሉቃስ 21፡25-28
በተያያዘው ሪፖርት ላይ እንደምታነቡትና በትናንትናው መልእክቴም እንደ ገለጽሁት፣ ዓለማችን በብዙ ምጦች ተይዛለች የሚለው ግምገማ ከትንቢት ተከታታዮች፣ አስፈሪ ዜና ማቅረብና የሴራ ወሬን ማናፈስ ይወዳሉ ከሚባሉ ምንጮች የመጣ ሳይሆን በምድራችን ላይ ታዋቂ ናቸው የሚባሉ ከ15 ሺ በላይ ሳይንቲስቶችም የሚስማሙበት ነው። በምድር ዙሪያ ያለው የ ኦዞን ልባስ እጅግ በመሳሳቱ ምድራችን ለአደገኛ ጨረርና ጥፋት ተጋልጣለች ሲሉ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያቸውን ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ለሰው ዘር ሁሉ የጻፉት የእነዚህ ሳይንቲስቶች ህብረት ዛሬ ግን  ምድራችን ከመቼውም የበለጠ እጅግ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቃለች፣ የሰው ዘር፣ እንስሳትና በአጠቃላይም በምድራችን ላይ ያለ ህይወት በሙሉ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጦአል ይላሉ። ከ184 አገሮች የተውጣጡት እነዚህ 15384 ሳይንቲስቶች ለሰው ዘር ሁሉ የጻፉት ደብዳቤ ምድርን በጥፋት አፋፍ ላይ ጥለዋታል ከሚላቸው ነገሮች መካከል ባለፉት 25 ዓመታት የሰው ዘር ብዛት በ35 ከመቶ ማደጉ፣ ሰዎች የሚጠቀሙበት ንጹህ ውሃ መጠን 26 በመቶ መቀነሱ፣ በብክለትና በኦክስጂን እጥረት ምክንያት ህይወት ሊኖርባቸው የማይችለው የውቅያኖስና የባህር አካሎች መጠን በ75 ከመቶ ማደጉ፣ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ደን በመመንጠሩና በሌሎችም ሰው ሰራሽ ጥፋቶች የምድር አየር ንብረት ሙቀት እያሻቀበ መሄዱና፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአእዋፍ፣ አሳዎች እንዲሁም ሌሎች እንስሳት ቁጥር በ29 ከመቶ መቀነሱ ነው። የእነዚህን ሁኔታዎች አስከፊነት ለመረዳት በፉኩሺማ ጃፓን በ2014 ዓም የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀትና ሱናሚ ተከትሎ የተፈጠረው የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ አደጋ ባለፉት ስድስት ዓመታት ተኩል ወደ ፓሲፊክ ውቅያኖስና ወደ ምድር ከባቢ አየር እየለቀቀው ያለ ከፍተኛ የኑክሊየር ጨረር የፈጠረውን አደጋ ልብ ማለት ያስፈልጋል። አደጋውን ለማቆም ይህን ወይም ያንን እያደረግን ነው የሚለው ዜና በተከታታይ ቢሰማም፣ በጉዳዩ ጥልቅ እውቀትና መረጃ ያላቸው ሰዎች ግን ጥፋቱ እንደ ቀጠለና ሊቆምም እንደማይችል ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም። ከነዚህ ባለሙያዎች አንዳንዶቹ እንደሚያቀርቡት የፉኩሺማው የኑክሊየር ኃይል ማመንጫ ፍንዳታ በዓለማችን ላይ እየለቀቀው ያለው ገዳይ ጨረር በ1945 ዓም በሂሮሺማ ጃፓን ላይ አሜሪካ የጣለችው የአቶሚክ ቦምብ ከለቀቀው ጨረር በ15000 (አስራ አምስት ሺህ) እጥፍ የከፋ ነው ይላሉ። ይህ ጨረር በቀጥታ የሚገባው ወደ ውቅያኖስችና ባህሮች እንዲሁም (አነስ ባለ መጠን) ወደ ከባቢ አየር በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የባህር እንስሳት ላለፉት ስድስ ተኩል ዓመታት እያለቁ ናቸው። እነዚህ ሳይንቲስቶች ያልጠቀሷቸው፣ ነገር ግን የሰውን ዘርና ምድራችንን ጥፋት በር ላይ ያደረሱአት ሌሎችም እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ። የተፈጸመው ጥፋት ሳይበቃን ዛሬ ደግሞ ባለጸጎቹ አገሮች ምድርን ብዙ መቶ ጊዜ ደጋግሞ ሊያጠፋ የሚችል አዳዲስ መሳሪያ በመስራት እየተሽቀዳደሙ ናቸው። የዚህ ሁሉ ክፋትና ፍጥረትን እያጠፋ ያለው ዋነኛው መርዝ ግን ኃጢዓትና እርሱም ያመጣው በእግዚአብሔር ላይ ዓመጽ፣ ራስ ወዳድነት፣ ገንዘብ ወዳድነት፣ ጥላቻ፣ ከገደብ ያለፈ ምቾት ናቸው። የምድር አዋቂዎች፣ ኃይለኞችና መሪዎች አሁንም ቢሆን ያንዣበበውን አደጋ ለመለስ የሚያስችል እውቀቱም፣ ችሎታውም የላቸውም። ብዙም ቀን ውሎ ሳያድር ይህን የሳይንቲስቶችን ማስጠቀቂያና ሌሎችም አስፈሪ ዜናዎችን ተከትሎ፣ “የገጠመንን ችግር ሁሉ በራሳችን ለመፍታት ስለማንችል፣ ከሌላ ዓለም የመጡ ሌሎች ልዩ ፍጥረታት (ETs, Aliens, Martians ወዘተ) እንዲረዱን እርዳታ ጠይቀን፣ እነርሱም ስለ ተስማሙ ውል ገብተናል። መሪያችንም እገሌ ይባላል” የሚል ዜና ቢመጣ ልንደነቅ አይገባም። ምክንያቱም ይህ ሁሉ እንደሚሆንና፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ምድርን ሁሉ የሚገዛ ሃሳዊ መሲህ (ሃሰተኛው ክርስቶስ) እንደሚገለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። “በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመጸኛ ይገለጻል። ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኛ ድንቆችም በመጻም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሰራር ነው።” 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡8-10 የዚህ መልእክት ዓላማዎች ሶስት ናቸው፤ 1ኛ) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል የዘለዓለምን ህይወት ተስፋ ያላገኙ ሁሉ በወንጌሉ የምስራች እንዲያምኑ ለመጋበዝ 2) በክርስቶስ የሚያምኑ ወገኖች ሁሉ በዓለማችን ላይ እየተካሄዱ ያሉትን ትልልቅ ነገሮች በመቃኘትና በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መነጽር በመመርመር ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ራሳቸውንና ሌሎችንም እንዲያዘጋጁ ለማነቃቃት 3) ምንም እንኳን የምናየውና የምንሰማው ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢመስልም፣ ክርስቲያኖች ሁሉ ፍጥረትን ሁሉ በእጁ የያዘው እግዚአብሔር ዛሬም በዙፋኑ ላይ እንዳለና ለሰው ዘርም ሆነ ለፍጥረት ሁሉ እኛ ከምናስበው የበለጠ ተስፋና እቅድ እንዳለው በማወቅ ያለ ፍርሃትና ያለ ስጋት መኖር እንደምንችል ለማሳሰብ ነው። ዓለሙን ሁሉ እጅግ ስለወደደ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም በመላክና ስለኛ ኃጢዓት በመስቀል ላይ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን ፍቅር ገልጾአል። ያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በዘመኑ መጨረሻ ዳግም ተመልሶ ይመጣል። ይህ ሁሉ የምናየውና የምንሰማው የእርሱ ዳግም ምጽዓት የምጥ ጣር መጀመሪያ ይመስላል። ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኛችን አድርገን ያልተቀበልን ሁሉ እርሱን አምነን የመዳን ቀን ዛሬ ነው። በእርሱ ለምናምንም ደግሞ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት መዘጃጋው ሰዓት አሁን ነው። እንደ አምስቱ ሰነፎች ቆነጃጅት በሩ እንዳይዘጋብን ቶሎ እንንቃ፣ መቅረዛችንን በዘይት እንሙላና ሙሽራውን ለመቀበል እንዘጋጅ።
“በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱ ድምጽ የተነሳ እያመነቱ ይጨነቃሉ፣ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሳ ይደክማሉ፣ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ።” ሉቃስ 21፡25-28

ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

1 አስተያየት:

  1. ለታላቁ ግምገማ እና ትንታኔ እናመሰግናለን! የቴክኖሎጂ እድገት እና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ደስታን ሊያመጡ እና ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ, ልዩነቱ ትርጉም ባለው አጠቃቀም ላይ ነው.

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...