የመለከት ድምጽ ብሎግ የአማርኛን ቋንቋ በተቀዳሚነት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ለማድረስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ያገለግላል።
የሰው ልጅ ራሱን ወደሚያጠፋበት ምሳሌያዊ እኩለ ሌሊት (proverbial midnight) ለመድረስ የቀረው ጊዜ ሁለት (2) ደቂቃ ብቻ ነው ተባለ።
የሰው ልጅ ራሱን ወደሚያጠፋበት ምሳሌያዊ እኩለ ሌሊት (proverbial midnight) ለመድረስ የቀረው ጊዜ ሁለት (2) ደቂቃ ብቻ ነው ተባለ። ቃየል በቅንዓት ተነሳስቶ የገዛ ወንድሙን
ንጹህ ደም ካፈሰሰባትና የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ከሆነባት ከዚያች አሳዛኝ ቀን ጀምሮ የሰው ዘር ከጦርነትና እርስ በእርሱ በየሰበብ
አስባቡ ከመገዳደል ያረፈባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው። የዚህ የዛሬው መልእክት መነሾ ወደሆነው ርእስ መለስ ስንል የምንረዳው ነገር
ደግሞ ከጦርነቶችም ሁሉ በላይ እጅግ የከፋ የሚሆነው የኑክሊየር ጦርነት እንደሆነ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሰው ዘር ታሪክ እንደምንማረው
እጅግ ጥቂቶች ከሆኑት በስተቀር የሰው ልጅ ፈጥሮ ስራ ላይ ሳያውላቸው የቀሩ የጦር መሳሪያዎች አሉ ለማለት ያዳግታል። ባለፉት
75 የሚሆኑ ዓመታት የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ተራቅቄያለሁ ብሎ አርቅቆ ከሰራቸው እጅግ ብዙ ህዝብን ከሚፈጁ መሳሪያዎች መካከል የኑክሊየር
የጦር መሳሪያዎች በቀደምትነት የሚቀርቡት በከንቱ አይደለም። Bulletin of the Atomic Scientists በመባል የሚጠራው የባለሙያዎች
ስብስብና መድረክ ላለፉት ሰባ ዓመታት ያህል ዓለም ምን ያህል ወደ ኑክሊየር እልቂት እንደተቃረበች የሚያሳዩ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጣ
ቆይቷል። ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘው የዚህ ዓመቱ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ከ1953 ዓም (እኤአ) በኋላ ዓለም ምሳሌያዊ ወደሆነው
የ ኑክሊየር እልቂት እኩለ ሌሊት የደረሰችበት ጊዜ እንዳልነበረ ያሳያል። በባለሙያዎቹ ግምገማ መሰረት የሰው ዘር ራሱን በኑክሊየር
መሳሪያዎች ሊፈጅ ወደሚችልበት “እኩለ ሌሊት” የቀረው ጊዜ ሁለት ደቂቃ ያህል ብቻ ነው። የሶቪየት ህብረት የመጀመሪያውን የኑክሊየር
ቦምብ በፈተሸችበት በአውሮፓውያኑ 1949 ዓም ይኽው የባለሙያዎች መድረክ ለእኩለ ሌሊት የቀረው ሶስት ደቂቃዎች ናቸው በማለት አስጠንቅቆ
ነበር። በ1953 ዓም አሜሪካ በጉልበቱ ከቀደሙት የአቶሚክ ቦምቦች እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የሃይድሮጅን ቦምብ በፈተሽበት ዓመት
ደግሞ ልክ እንደ ዘንድሮው ለጥፋት የቀረው ጊዜ ሁለት ደቂቃ ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ሶቪየት ህብረትና የምስራቁ
የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት መፈራረሱን ተከትሎ፣ ኮሚኒዝም ወደቀ፣ ቀዝቃዛው ጦርነት አከተመ፣ ምድር ሁሉ ሰላም ልትሆን ነው የሚሉ
ድምጾች ባስተጋቡበት በ1991 ዓም ደግሞ እነዚህ ባለሙያዎች የኑክሊየር ጥፋቱን ሰዓት በ15 ደቂቃ ወደኋላ በመመለስ ዓለም ከኑክሊየር
ፍጅት አደጋ በብዙ መራቋን የሚያመለክት ብዙ ተስፋ የተሞላበት መልእክት አስተላልፈው ነበር። ከ16 ዓመታት በኋላ ግን ሰሜን ኮሪያ
የኑክሊየር መሳሪያን በፈተሽበት በ2007 ዓም የጥፋት ሰዓቱን በከፍተኛ ፍጥነት ወደፊት በመግፋት የጥፋት እኩለ ሌሊት የቀረው
5 ደቂቃ ብቻ ነው ብለውም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት
ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም” በማለት በ1ኛ ተሰሎንቄ 5፡3 የተናገረው ከዚህ ሁኔታ ጋርም የተያያዘ ሊሆን ይችላል። 20ኛው
መቶ ክፍለ ዘመን የከፍተኛ እልቂት ክፍለ ዘመን መሆኑ በታሪክ የተዘገበለት ነው። በ1ኛውና በ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ የስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ
ተብሎ በሚጠራው እልቂት፣ በጀርመን በተፈጸመው የአይሁዳውያን ፍጅት፣ በተለያዩት አብዮቶችና ጸረ አብዮት ጦርነቶች፣ በበሽታና በረሃብ
ያለቀው የሰው ዘር በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ይቆጠራል። የሰውን ዘር ቁጥር ለመቀነስ ተብሎ በተቀየሰው ሰፊ የጽንስ ማስወረድ ዘመቻ መሰል
እርምጃም በዓለም ዙሪያ የተፈጀው ያልተወለደ የሰው ዘር ከአንድ መቶ ሚሊዮን ይበልጣል። እነዚህ ሁሉ እጅግ የሚዘገንኑ ቢሆኑም፣
ዛሬ “መለስተኛ ነው” የሚባል የኑክሊየር ጦርነት እንኳን ቢነሳ ከሚያልቀው ህዝብ ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። ዛሬ የምናያቸውና የምንሰማቸው
አስፈሪ ነገሮች ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት የግድ ሊሆን ያለው የምጥ ጣር መጀመሪያ አካል ናቸው።
እንደ ታጨች ንጽህት ድንግል ነቅታና ተግታ ሙሽራዋን ክርስቶስን የምትጠብቀው ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ምድር ሳይታሰብ እንደምትነጠቅ
መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ያስተምራል። ዓለም አቀፋዊ ጦርነትንና እልቂትን አስመልክቶ የዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 6 ቁጥር 4 እንዲህ ይላል፤
“ሌላም ዳማ (ቀይ) ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ፣ ሰዎችም እርስ በእርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን
ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” ዛሬ ከምናውቃቸው የሰው ልጅ ከሰራቸው ሰይፎች ሁሉ መካከል እንደ ኑክሊየር ቦምብ ያለ
የከፋ መሳሪያ የለምና፣ ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ኑክሊየር እልቂት ነው ተብሎ በብዙ የትንቢት ምሁራን ይታመናል። ዛሬ በታላላቆቹ
የዓለም ኃይላት መካከል የሚደረገውን የጦርነት ፉክክር፣ ዝግጅት እና የመሳሪያ እሽቅድምድም አትኩሮ ለሚያይ ሰው ለሰው ልጅ ምንም
ተስፋ የቀረ አይመስልም። ነገር ግን ታሪክንና ፍጥረትን ሁሉ በእጁ የያዘ አምላክ በዙፋኑ ላይ አለ። እጅግ ብዙ ህዝብ በጦርነት
ሊያልቅ ቢችልም፣ የሰው ዘር በሙሉ ግን ከምድር ላይ አይጠፋም። ፍጥረቱ የሆነውን የሰውን ልጅ ስለወደደ በመስቀል ላይ ሕይወቱን
የሰጠውን የኢየሱስ የክርስቶስን ወንጌል የምስራች አምነው ለሚቀበሉ ሁሉ ታላቅና ዘላለማዊ ተስፋ አለ። የተስፋው መጀመሪያና መጨረሻ
ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ምሁራን፣ ፈላስፎች፣ ነገስታት፣ የጦርነት ባለጀብዱዎችና ባለጠጎች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች
ነን ያሉ ሁሉ ክንዳቸውን ተንተርሰው ሲቀሩ፣ የሞትን ጣር አጥፍቶ የተነሳውና የትንሳኤን ድል ያወጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
በእርግጥ ህሊናችን እና መንፈሳዊ ዓይናችን ተከፍቶ ማየት ብንችል፣ ከምንም በላይ የሚያስፈራው በዚህ ጌታ ሳናምን በመጨረሻው ቀን
ለፍርድ በፊቱ መቆማችን ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ሲመጣና የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ላይ ሲመሰርት የሰው ዘር ሁሉ ፍጹም ሰላምንና
ደስታን ያያል። ስለዚያ ዘመን ነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “በአሕዛብም
መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም መካከልይበይናል፣ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ
ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” ኢሳይያስ 2፡2፥4 በዚያን ዘመን በእግዚአብሔር መንግሥት ቦታ ሊኖረን የሚችለው የተሰበከልንን
የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመቀበል ዛሬ ነፍሳችንን ለእርሱ አደራ የሰጠን እንደሆነ ብቻ ነው። በኑሮ ግርግርና ሩጫ ተዘናግተን
ወይም በምንሰማውና በምናየው ክፉ ወሬ ሁሉ ተዋክበን የነፍሳችን እና የዘለዓለም ቤታችን ጉዳይ ችላ ብለን የዘለዓለሙ በር ሳናውቀው
እንዳይዘጋብን ዛሬውኑ ወደ ጌታ አምላክ እንመለስ። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። ብንመለስ ይምረናል፣ ይቀበለናል፣ በሞቱና በትንሳኤው
ኃይል አዲስ ሰው ያደርገናል። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የኑክሊየር ጥቃት ፍርሃት መረጃውን የሚያገኙ ብዙ ህዝብን እያስጨነቀ ነው። ዛሬ በሃዋይ የተከሰተው የተሳሳተ ማስጠንቀቂያ ምሳሌ።
https://www.nbcnews.com/news/us-news/hawaii-ballistic-missile-threat-alert-phones-was-false-alarm-officials-n837511?utm_referrer=https%3A%2F%2Fzen.yandex.com
የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎች በድንገት በስራ ላይ
ይውሉና ብዙ ህዝብ ያልቃል የሚለው ፍርሃት በብዙ የዓለም ክፍሎች እጅግ በሰደደበት በዚህ ወቅት፣ ሃዋይ በምትባለው ጸሃያማና የፓሲፊክ
ውቅያኖስ ደሴትና የአሜሪካ ግዛት ያሉ ህዝብ የሳምንቱን መጨረሻ ቀኖቻቸውን ዛሬ ቅዳሜ የጀመሩት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ በየስልኮቻቸው
የተላከ አስፈሪ መልእክት በማንበብ ነበር። መልእክቱም የኑክሊየር ቦምብ የያዘ ሚሳኤል ወደ ሃዋይ እየመጣ አሁኑኑ መሸሸጊያ ግቡ የሚል ነበር። ምንም እንኳን ከ20 ደቂቃ በኋላ መልእክቱ በስህተት
እንደተላከ ማረጋጊያ ቢላክም እነዚያ 20 ደቂቃዎች ስንቱን ህዝብ እንዳስደነገጡና እንዳስጨነቁ መገመት ቀላል አይደለም። የኑክሊየር
ጥቃት ማስፈራሪያ ብቻ ያለመሆኑን እና በቅርቡ ሊከሰት የሚችል ነገር እንደሆነ በማመንም መሆን አለበር የአሜሪካ መንግስት የበሽታ
ቁጥጥር ድርጅት (CDC) በዚህ ወር (January 16) ለህዝብ ጤና ባለሙያዎችና ሌሎችም የህዝብ ደህንነት ለሚመለከታቸው
ባለስልጣናት በአካባቢያቸው የኑክሊየር ፍንዳታ ቢፈጸም እንዴት እልቂትንና ጉዳትን መቀነስ ይቻላል የሚል ስልጠና የሚሰጠው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መግቢያ ያስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ ዋና ይዘቱ “ቀይ ማንቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ” መሆኑን ባለፈው መልእክቴ ላይ ገልጬ ነበር። በብዙዎች ግምት ከዋና ጸሐፊው ማስጠንቀቂያ መልእክት እጅግ አስቸኳዩ፣ አደገኛውና አስፈሪው የኑክሊየር መሳሪያዎች፣ በ1945 እኤአ አሜሪካ በጃፓን ላይ ካደረሰችው ጥፋት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ላይ ሊውሉና ብዙ ህዝብን ሊፈጁ የሚችሉባቸው ግጭቶች መብዛታቸውና መካረራቸው ነው። ይህን መሰል ዜና ስንሰማ እኔን አይመለከተኝም፣
የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ወይም የአሜሪካና የሩሲያ ጉዳይ ነው ብለን ልናጣጥለው እንችላለን። ስለዚህ ክፉ መሳሪያ አለማወቃችን ምናልባት
“እኛ ጋ አይደርስም” በሚል የተሳሳተ መደላደል ውስጥ አስገብቶንም ይሆናል። እግዚአብሔር አይበለው እንጂ ሙሉ በሙሉ የኑክሊየር
ጦርነት ቢነሳ በምድር ላይ ፍጥረት ይተርፋል ብሎ ለማመን አይቻልም። ውስን ወይም መለስተኛ የሚባል የኑክሊየር ጥቃትም ቢሆን ከተፈጸመ
የሚያልቀው የህዝብ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህን ለመረዳት ከዛሬ 73 ዓመት ያህል በፊት ሂሮሺማና ናጋሳኪ በሚባሉት የጃፓን
ከተማዎች ላይ የደረሰውን እልቂትና ጥፋት ማሰብ ብቻ በቂ ነው። በዚያን ዘመን የተጣሉት ሁለት ቦምቦች ከዛሬዎቹ ጋር ሲወዳደሩ እጅግ
ትንንሽ ነበሩ ቢባልም ከ225,000 በላይ ሰዎች አልቀዋል፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ቆስለዋል፣
ዘራቸው ጠፍቶአል። “የኑክሊየር መሳሪያዎችን ለማስወገድ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ” ወይም ICAN የሚባለው ድርጅትና ሌሎችም ምንጮች እንደሚያስረዱት በዓለማችን ላይ ካሉት 14900 ከሚሆኑ የኑክሊየር መሳሪያዎች ውስጥ 92.6 በመቶ የሚሆኑት ያሉት በአሜሪካና በሩሲያ እጅ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት በተደጋጋሚ የሚሰማው በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው የአደባባይ ፍጥጫ ይምሰል እንጂ ዋነኛው ዓለም አቀፋዊው ውጥረት በታላላቆቹ የኑክሊየር ባለቤቶች በአሜሪካና በሩሲያ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና
መካከል
መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት አዲስ ባይሆንም የአሁኑን
የግጭት እሳት የለኮሰው በ2014 በሩሲያ ይደገፍ የነበረን የዩክሬንን መንግስት በአሜሪካ የሚደገፉ ቡድኖች ከመገልበጣቸው ጋር ተያይዞ ሩሲያ ድሮም ግዛቴ ነበር በማለት ክራይሚያ የሚባለውን ክልል ወደ ራሷ መቀላቀሏ ነበር። የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጣ፣
ምእራብ አውሮፓን ጨርሳ፣ ድንበሬ አጠገብ ባሉና ቀደም ሲል የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩ አገሮችም ወታደሮቿን የምታከማቸው እኔን
ለማጥቃት ነው የምትለዋ ሩሲያ ራሷን ለመከላከል የኑክሊየር መሳሪያዎቿን ዘመናዊ ስታደርግ ሰንብታለች። አሜሪካ ደግሞ ሩሲያ ዓለም
አቀፍ ህጎችን ጥሳለችና የማቆም ግዴታና ችሎታው አለኝ በማለትሩሲያን በሚያዋስኑ አገሮች የጦር ሰራዊትንና መሳሪያዎችን ስታከማች ሰንብታለች፣ ተደጋጋሚ
የጦር ልምምዶችንም በሩሲያ ድንበር አጠገብ ማድረጓን ቀጥላለች። ከ2014 እስከ 2016 ድረስም የአሜሪካ የስለላና የጦር ባለስልጣኖች
ሩሲያንም ራሷን ቢሆን ካስፈለገ በጦርነት ማሸነፍ እንችላለን ያሉት በስውር ሳይሆን በአሜሪካው ምክር ቤት ቀርበው ነበር። በአሜሪካና
በቻይና መካከል ያለው ውጥረት ደግሞ ከንግድና ከኤኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የአሜሪካ ኤኮኖሚ ወደታች ሲያሽቆለቁል
የቻይና ደግሞ በአስገራሚ ፍጥነት በማደጉ አሜሪካ ወደኋላ መቅረቷን በቀላሉ አልተቀበለችውም። ስለዚህ የቻይናን መስፋፋት ለመቆጣጠር
በማሰብ ከፍተኛ የጦር ኃይሏን በቻይና አካባቢ ባሉ አገሮችና ባህሮች ላይ በማሰማራት ሰበብ አስባብ ስትፈላልግ መክረሟም በሰፉው
የተዘገበበት ነው። አንዳንድ አንባቢዎች “ታዲያ ምን ይሁን?” “እኔ አንድ ሰው ነኝ? ምን ላድርግ?” እንደሚሉ አልጠራጠርም። ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጨረሻው ዘመን ሲናገር እንዲህ ያሉ ዜናዎችና ከዜናም አልፎ ጦርነቶች የግድ እንደሚሆኑ አስተምሮአል፤“ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፣ተጠበቁ አትደንግጡ፥ ዳሩ
ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፣ ራብም፣ ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ
ስፍራ ይሆናል እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” ማቴዎስ 24፡5-8“እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ዘኖች ስለ
ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” ማቴዎስ 24፡22ጦርነቶች እጅግ ብዙ ሰውን ቢጨርሱም የዓለም መጨረሻ ግን የኑክሊየርም ሆነ ሌላ ጦርነት አይደለም።
ከዚህ የሚከፋ ትልቅ አደጋና ጥፋት አለ። ያም አደጋ የሰው ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በመቀበል የዘለዓለምን ሕይወት
ሳያገኝ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ነው። የዚህ ዓለም ሞት የስጋ ሞት ነው። ከዚያ በኋላ ግን ሰው ሁሉ በህይወቱ ዘመን ስላደረገው
መልስ ለመስጠትና ዘለዓለምን የት እንደሚያሳልፍ ለማወቅ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቆማል። ለማመን ብንፈልግም፣ ባንፈልግም ይህ
እውነት ነው። በዚህ ምድር ኑሮአችን ተጠያቂነት የግድ ከሆነ፣ በሰማያዊው ተጠያቂነት የለም የሚል ቢኖር እጅግ ከፍተኛ ስህተት ተሳስቶአል።
ከፍርድ ለማምለጥ የምንችለው ስለ ኃጢዓታችን በመስቀል ላይ የሞተውን፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳውንና በክብር ዳግም ተመልሶ በመምጣት
ይህን የተመሰቃሰለ ዓለም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጽድቶ በሰላም ሊነግስ የሚመጣውን እግዚአብሔር ወልድን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን፣ በማመን
ብቻ ነው። በትንሳኤም ቀን የሚፈርደው ይኽው ክርስቶስ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ወደ እግዚአብሔር የመድረሻ መንገድ የለም።
እውነትም መንገድም ህይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዚህ ዓለም ከሚከሰቱ ክፉ ነገሮች ሁሉ ልናመልጥ እንችል ይሆናል። ከሞትና
በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ከመውደቅና ዘለዓለምን በሲኦል ከማሳለፍ ሊያድነን የሚችል ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዛሬ ይህን
ጌታ አምነን እንዳን። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም። ምንም ክፉ ነገር ባይሆንም ደግሞ በክርስቶስ አምነን ከእግዚአብሔር ጋር
ልንኖረው የምንችለውን የዘለዓለሙን ህይወት፣ እረፍትና ደስታ ከሞት ወዲህ ማዶ ዛሬውኑ መለማመድ መጀመሩም ይህች ዓለም ከምትሰጠው
ነገር ሁሉ የከበረ ምስጢር ነው። ጌታ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ዓይኖቻችንን በመክፈት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠውን ፍቅሩ በመቀበል
እንድናምን ይርዳን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለዓለም መሪዎችና ህዝቦች “ቀይ ማንቂያ” ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ።
የተባበሩት
መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለዓለም መሪዎችና ህዝቦች “ቀይ ማንቂያ” ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ። https://www.un.org/sg/en/content/sg/statement/2017-12-31/secretary-general’s-video-message-alert-world-1-january-2018-scroll
አዲሱን
የአውሮፓውያን ዓመት 2018ን መጀመር አስመልክተው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክታቸው 193 አገሮች አባል የሆኑበትና በዓለም
ላይ ሰላምንና ጸጥታን ለማስፈን በ1945 ዓም (እኤአ) የተመሰረተው ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት የቀድሞው የፖርቱጋል ጠቅላይ
ሚኒስትር አንቶኒዮ ጉቴሬስ አዲሱ ዓመት ከመቼውም ይልቅ
አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የመልእክታቸው ይዘት ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ነው፤ “ከአንድ ዓመት በፊት
ይህን ኃላፊነት ስረከብ 2017 የሰላም ዓመት እንዲሆን ማሳሰቢያን (አቤቱታን) አቅርቤ ነበር። ነገር ግን እድለ ቢስ ሆንንና የዓለማችን ሁኔታ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ወደ ፊት ሄዶ
በመሻሻል ፈንታ ወደ ኋላ ተመልሶአል። ዛሬ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ ለዓለም የማቀርበው ማሳሰቢያን ወይም አቤቱታን
ሳይሆን ማስጠንቀቂያን (ማንቂያን)፣ ቀይ ማስጠንቀቂያን ነው። በዓለም ዙሪያ ግጭቶች ስር ሰድደዋል፣ አዳዲስ አደጋዎችም ከፊት
ለፊታችን ተጋርጠውብናል። የኑክሊየር የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ጭንቀትና
ፍርሃት ሰፍኖአል። የአየር ንብረት ለውጥ ከእኛ ይልቅ እየፈጠነ ይገኛል። በሰዎች መካከል የኑሮ ልዩነት ከበፊቱ የበለጠ እየሰፋ
ይገኛል። ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን እያየን ነው። ብሔርተኝነትና ከእኛ የሚለዩ ሰዎችን የመጥላት አዝማሚያ
እያደጉ ናቸው። ይህን ዓመት (2018ን) ስንጀምር ሁላችን አንድነትን እንድንመርጥ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ዓለማችንን በእርግጥ
ሰላምና ደህንነት የሰፈነባት ማድረግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔን ማግኘት እንችላለን፣ ጥላቻን
ተቋቁመን የጋራ እሴቶቻችንን መከላከል እንችላለን። ይህን ሁሉ ለማድረግ የምንችለው ግን አብረን ስንሰራ ብቻ ነው። በዓለም
ዙሪያ ያሉ መሪዎች ሁሉ ይህን የአዲስ ዓመት ውሳኔ እንዲያደርጉ እገፋፋለሁ፡ ክፍተቶችን እናጥብብ፣ በለያዩን ነገሮች ላይ
ድልድይ እንስራ፣ ህዝቦችን በጋራ ግቦች ዙሪያ በማሰለፍ መተማመንን እንደገና እንገንባ። ልንሄድበት የሚገባን መንገድ አንድነት
ነው። ለመጻዔው ዘመናችን ወሳኝ ነውና።”
የዋና ጸሃፊው መልእክት የተጻፈው ለዓለም መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና አዋቂ ሰዎች እንዲደርስ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ረቅቆ በመሆኑ ከበስተጀርባው ያለውን የጭንቀትና የውጥረት መልእክት ብዙዎቻችን በቀላሉ ላንረዳው እንችላለን። በአጭሩ ለማስቀመጥ እኒህ ከፍተኛ የዓለም መሪ የሚነግሩን ነገር ዓለም ከመቼውም የበለጠ በከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኗን፣ እጅግ ብዙ ህዝቦችን ሊያጠፋ የሚችል የኑክሊየር ጦርነት ጥቁር ደመና ማንንዣበቡንና፣ የዓለም መሪዎችም እጅግ ከመከፋፈላቸው የተነሳ ውጥረቶችንና ግጭቶችን ለማርገብና ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማግኘት እንዳልቻሉ ነው። ዓለምን ወደ ፍጹም ጥፋት ሊከቱ የሚችሉ የጦርነት እሳቶች በየቦታው መጨስ ከመጀሩ ውሎ ማደሩን አንዘንጋ። በምስራቅና በሰሜን አውሮፓ የአሜሪካና የNATO ጦር ሰራዊትና መሳሪያ ከ2014 ጀምሮ በብዛት ጨምሮአል። በመካከለኛው ምስራቅ በሳውዲ አረቢያና በኢራን መካከል ያለው መፋጠጥ ከፍተኛ ነው። በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን እንዲሁም በሚደግፉአቸው የአረብና እስላማዊ አገሮች መካከል ያለው ውጥረት እጅግ ተባብሶአል። ይህ ውጥረት በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በኢራቅ፣ በካታር፣ በባህሬን፣ በቱርክና በሌሎችም አገሮች የውስጥና የውጭ ጉዳዮችም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድር አካባቢው በቀላሉ ወደ ጦርነት እሳት ሊገባ ይችላል። በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ አሜሪካ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ያላት ስትራቴጂያዊ ትግል አካል መሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው። ብዙዎች እንደ ቀላል እንደሚያወሩት በነዚህ ከላይ በተጠቀሱትና ሌሎችም ግጭቶች ምክንያት ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ ሊያልቅ የሚችለውን ህዝብ ለመገመት አዳጋች ነው። ዛሬ በምድር ላይ ካሉት ከ15 ሺ በላይ የኑክሊየር መሳሪዎች መካከል 100 የሚሆኑት ብቻ እንኳን በኮሪያ አካባቢ በስራ ላይ ቢውሉ ምድር ወደ ከፍተኛ ጥፋት ውስጥ እንደምትገባ የዚህን መሳሪያ አጥፊነት የሚያውቁ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
በዚህ በ2018
መጀመሪያ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እጅግ አደገኛ መሆኑን በዚህ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ያመለከቱትና ማስጠንቀቂያን የሰጡት
እኒህ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ብቻ አይደሉም። ብዙ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት የሮማዋ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
ሊቀጳጳስ የሆኑት ፍራንሲስም በበኩላቸው እጅግ አስፈሪ የሆነ ምልክትን በመጠቀም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያን አስተላልፈዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ አሜሪካ ናጋሳኪ በምትባለው የጃፓን ከተማ ላይ በጣለችው የኑክሊየር ብሞብ የሞተ አንድ
ህጻንና የህጻኑን አስከሬን በጀርባው ላይ ያዘለ ወንድሙን ፎቶ የያዘና “የጦርነት ፍሬ” የሚል የእርሳቸው ጽሁፍና ፊርማቸው
ያለበትን ካርድ በመልቀቅ በ2018 እጅግ የከፋ እልቂት በምድር ላይ ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በዚሁ ባለፈው ዓመት የመጨረሻ
ቀን ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ጦር ጥምር መሪዎች ሊቀመንበር የነበሩት ጀነራል ማይክ መለን በቴሌቪዝን ቀርበው ሲናገሩ “በእኔ
አስተያየት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ከሰሜን ኮሪያ ጋርና በዚያ አካባቢ ወደ ኑክሊየር ጦርነት የምንገባበት ጊዜ በጣም
ቀርቦአል” ብለው መናገራቸው በእርግጥም እጅግ ብዙ ህዝብን የሚፈጅና ዓለምን ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊዘፍቅ የሚችል
አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ያሳያል። የጀነራሉ የትዊተር መልእክት የሚከተለው ነበር፡ Former Joint Chiefs chair Adm. Mike Mullen to @MarthaRaddatz: "We're actually closer, in my view, to a nuclear war
with North Korea and in that region than we've ever been."
እነዚህ ታላላቅ የዓለም መሪዎችና በጉዳዩ የቅርብ እውቀት
ያላቸው ሰዎች ከሚናገሩት በተጨማሪ ብዙ የእግዚአብሔርን ፊት ከልብ የሚፈልጉና ለአገሮቻቸው የሚጸልዩ ክርስቲያኖችና አገልጋዮች
ይህ አስፈሪ ዜና እውን ሊሆን እንደሚችል በሕልም፣ በራዕይና በሌላም ሰማያዊ መገለጥ ሰማያዊ ማስጠንቀቂያን እንደተቀበሉ ሲናገሩ
ውለው አድረዋል። ከመገለጾች ሁሉ በላይ የሆነውና የጸናው የእግዚአብሔር ቃል መፅሐፍ ቅዱስ ደግሞ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ
ምጽዓት ሲቃረብ፣ እግዚአብሔር ባይገታቸው፣ የሰውን ዘር ሁሉ ሊያጠፉ የሚችሉ ጦርነቶች እንደሚከሰቱ ይናገራል። ብዙ ሰዎች፣
የክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲያኖችም ጭምር ይህን ዓይነት መልእክት ስናነብ “ታዲያ ምን ይሁን?” “እኔ ምንም አቅም
የለኝም፣ ምን ማድረግ እችላለሁ?” ልንል እንደምንችል ከዚህ ቀደም በላክኋቸው መልእክቶች ላይ ከተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች
እገነዘባለሁ። ወገኖቼ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎችም ምንም እንኳን መሪዎች ቢሆኑና ስልጣንም ቢኖራቸው እንደኛው “አንድ”
ሰው ናቸው። ዛሬ በምድር ላይ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መንፈሳዊ ጦርነት አካል ነው። ስለዚህ
ክርስቲያን በኤፌሶን መልእክት ምእራፍ 6 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን እቃ ጦር በመልበስ በእውነተኛ የወንጌል መታዘዝ፣
በጾምና በጸሎት ለምድር መሪዎችና መንፈሳዊ ግራ ቀኛቸውን ለማያውቁ ህዝብ ሁሉ ልንጸልይ ይገባል። በእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም
የተነገረው ትንቢት ሁሉ ይፈጸማል። ነገር ግን በሁሉም ላይ ስልጣን ያለውን የፍቅርና የሰላም አባት የሆነውን እግዚአብሔርን
ከልባችን ስንፈልገው ይራራ ይሆናል። የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ እስኪመለስና በምድር እስኪነግስ ድረስ ጥፋትና ጦርነት
እንደታወጀ ነቢዩ ዳንኤል ከሰማይ ሰምቶ በምዕራፍ 9 ቁጥር 26 እና በሌሎች ስፍራዎችም ጽፎአል። ሌሎች ነቢያትና ሐዋርያትም
እንዲሁ። ይህ የዘመን መጨረሻ የደረሰብን እኛ ደግሞ ቃሉ እንደሚያዝዘን ለመሪዎች በመጸለይና የወንጌሉን ፍቅር በመመስከር
እንዲሁም በያለንበት ልናደርገው የምንችለውን መልካም ነገር ሁሉ በማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር
ተመልሶ ይመጣል። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
ልጥፎች (Atom)
ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...
-
የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5 ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ...
-
የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ትምሕርት 6 ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ...
-
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018 አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ...