https://www.nbcnews.com/news/us-news/hawaii-ballistic-missile-threat-alert-phones-was-false-alarm-officials-n837511?utm_referrer=https%3A%2F%2Fzen.yandex.com
የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎች በድንገት በስራ ላይ
ይውሉና ብዙ ህዝብ ያልቃል የሚለው ፍርሃት በብዙ የዓለም ክፍሎች እጅግ በሰደደበት በዚህ ወቅት፣ ሃዋይ በምትባለው ጸሃያማና የፓሲፊክ
ውቅያኖስ ደሴትና የአሜሪካ ግዛት ያሉ ህዝብ የሳምንቱን መጨረሻ ቀኖቻቸውን ዛሬ ቅዳሜ የጀመሩት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ በየስልኮቻቸው
የተላከ አስፈሪ መልእክት በማንበብ ነበር። መልእክቱም የኑክሊየር ቦምብ የያዘ ሚሳኤል ወደ ሃዋይ እየመጣ አሁኑኑ መሸሸጊያ ግቡ የሚል ነበር። ምንም እንኳን ከ20 ደቂቃ በኋላ መልእክቱ በስህተት
እንደተላከ ማረጋጊያ ቢላክም እነዚያ 20 ደቂቃዎች ስንቱን ህዝብ እንዳስደነገጡና እንዳስጨነቁ መገመት ቀላል አይደለም። የኑክሊየር
ጥቃት ማስፈራሪያ ብቻ ያለመሆኑን እና በቅርቡ ሊከሰት የሚችል ነገር እንደሆነ በማመንም መሆን አለበር የአሜሪካ መንግስት የበሽታ
ቁጥጥር ድርጅት (CDC) በዚህ ወር (January 16) ለህዝብ ጤና ባለሙያዎችና ሌሎችም የህዝብ ደህንነት ለሚመለከታቸው
ባለስልጣናት በአካባቢያቸው የኑክሊየር ፍንዳታ ቢፈጸም እንዴት እልቂትንና ጉዳትን መቀነስ ይቻላል የሚል ስልጠና የሚሰጠው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት መግቢያ ያስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ ዋና ይዘቱ “ቀይ ማንቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ” መሆኑን ባለፈው መልእክቴ ላይ ገልጬ ነበር። በብዙዎች ግምት ከዋና ጸሐፊው ማስጠንቀቂያ መልእክት እጅግ አስቸኳዩ፣ አደገኛውና አስፈሪው የኑክሊየር መሳሪያዎች፣ በ1945 እኤአ አሜሪካ በጃፓን ላይ ካደረሰችው ጥፋት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ላይ ሊውሉና ብዙ ህዝብን ሊፈጁ የሚችሉባቸው ግጭቶች መብዛታቸውና መካረራቸው ነው። ይህን መሰል ዜና ስንሰማ እኔን አይመለከተኝም፣
የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ወይም የአሜሪካና የሩሲያ ጉዳይ ነው ብለን ልናጣጥለው እንችላለን። ስለዚህ ክፉ መሳሪያ አለማወቃችን ምናልባት
“እኛ ጋ አይደርስም” በሚል የተሳሳተ መደላደል ውስጥ አስገብቶንም ይሆናል። እግዚአብሔር አይበለው እንጂ ሙሉ በሙሉ የኑክሊየር
ጦርነት ቢነሳ በምድር ላይ ፍጥረት ይተርፋል ብሎ ለማመን አይቻልም። ውስን ወይም መለስተኛ የሚባል የኑክሊየር ጥቃትም ቢሆን ከተፈጸመ
የሚያልቀው የህዝብ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህን ለመረዳት ከዛሬ 73 ዓመት ያህል በፊት ሂሮሺማና ናጋሳኪ በሚባሉት የጃፓን
ከተማዎች ላይ የደረሰውን እልቂትና ጥፋት ማሰብ ብቻ በቂ ነው። በዚያን ዘመን የተጣሉት ሁለት ቦምቦች ከዛሬዎቹ ጋር ሲወዳደሩ እጅግ
ትንንሽ ነበሩ ቢባልም ከ225,000 በላይ ሰዎች አልቀዋል፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ቆስለዋል፣
ዘራቸው ጠፍቶአል። “የኑክሊየር መሳሪያዎችን ለማስወገድ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ” ወይም ICAN የሚባለው ድርጅትና ሌሎችም ምንጮች እንደሚያስረዱት በዓለማችን ላይ ካሉት 14900 ከሚሆኑ የኑክሊየር መሳሪያዎች ውስጥ 92.6 በመቶ የሚሆኑት ያሉት በአሜሪካና በሩሲያ እጅ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት በተደጋጋሚ የሚሰማው በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው የአደባባይ ፍጥጫ ይምሰል እንጂ ዋነኛው ዓለም አቀፋዊው ውጥረት በታላላቆቹ የኑክሊየር ባለቤቶች በአሜሪካና በሩሲያ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና
መካከል
መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለው ውጥረት አዲስ ባይሆንም የአሁኑን
የግጭት እሳት የለኮሰው በ2014 በሩሲያ ይደገፍ የነበረን የዩክሬንን መንግስት በአሜሪካ የሚደገፉ ቡድኖች ከመገልበጣቸው ጋር ተያይዞ ሩሲያ ድሮም ግዛቴ ነበር በማለት ክራይሚያ የሚባለውን ክልል ወደ ራሷ መቀላቀሏ ነበር። የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጣ፣
ምእራብ አውሮፓን ጨርሳ፣ ድንበሬ አጠገብ ባሉና ቀደም ሲል የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩ አገሮችም ወታደሮቿን የምታከማቸው እኔን
ለማጥቃት ነው የምትለዋ ሩሲያ ራሷን ለመከላከል የኑክሊየር መሳሪያዎቿን ዘመናዊ ስታደርግ ሰንብታለች። አሜሪካ ደግሞ ሩሲያ ዓለም
አቀፍ ህጎችን ጥሳለችና የማቆም ግዴታና ችሎታው አለኝ በማለትሩሲያን በሚያዋስኑ አገሮች የጦር ሰራዊትንና መሳሪያዎችን ስታከማች ሰንብታለች፣ ተደጋጋሚ
የጦር ልምምዶችንም በሩሲያ ድንበር አጠገብ ማድረጓን ቀጥላለች። ከ2014 እስከ 2016 ድረስም የአሜሪካ የስለላና የጦር ባለስልጣኖች
ሩሲያንም ራሷን ቢሆን ካስፈለገ በጦርነት ማሸነፍ እንችላለን ያሉት በስውር ሳይሆን በአሜሪካው ምክር ቤት ቀርበው ነበር። በአሜሪካና
በቻይና መካከል ያለው ውጥረት ደግሞ ከንግድና ከኤኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የአሜሪካ ኤኮኖሚ ወደታች ሲያሽቆለቁል
የቻይና ደግሞ በአስገራሚ ፍጥነት በማደጉ አሜሪካ ወደኋላ መቅረቷን በቀላሉ አልተቀበለችውም። ስለዚህ የቻይናን መስፋፋት ለመቆጣጠር
በማሰብ ከፍተኛ የጦር ኃይሏን በቻይና አካባቢ ባሉ አገሮችና ባህሮች ላይ በማሰማራት ሰበብ አስባብ ስትፈላልግ መክረሟም በሰፉው
የተዘገበበት ነው። አንዳንድ አንባቢዎች “ታዲያ ምን ይሁን?” “እኔ አንድ ሰው ነኝ? ምን ላድርግ?” እንደሚሉ አልጠራጠርም። ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጨረሻው ዘመን ሲናገር እንዲህ ያሉ ዜናዎችና ከዜናም አልፎ ጦርነቶች የግድ እንደሚሆኑ አስተምሮአል፤“ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፣ተጠበቁ አትደንግጡ፥ ዳሩ
ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፣ ራብም፣ ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ
ስፍራ ይሆናል እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” ማቴዎስ 24፡5-8“እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ዘኖች ስለ
ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።” ማቴዎስ 24፡22ጦርነቶች እጅግ ብዙ ሰውን ቢጨርሱም የዓለም መጨረሻ ግን የኑክሊየርም ሆነ ሌላ ጦርነት አይደለም።
ከዚህ የሚከፋ ትልቅ አደጋና ጥፋት አለ። ያም አደጋ የሰው ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በመቀበል የዘለዓለምን ሕይወት
ሳያገኝ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ነው። የዚህ ዓለም ሞት የስጋ ሞት ነው። ከዚያ በኋላ ግን ሰው ሁሉ በህይወቱ ዘመን ስላደረገው
መልስ ለመስጠትና ዘለዓለምን የት እንደሚያሳልፍ ለማወቅ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቆማል። ለማመን ብንፈልግም፣ ባንፈልግም ይህ
እውነት ነው። በዚህ ምድር ኑሮአችን ተጠያቂነት የግድ ከሆነ፣ በሰማያዊው ተጠያቂነት የለም የሚል ቢኖር እጅግ ከፍተኛ ስህተት ተሳስቶአል።
ከፍርድ ለማምለጥ የምንችለው ስለ ኃጢዓታችን በመስቀል ላይ የሞተውን፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳውንና በክብር ዳግም ተመልሶ በመምጣት
ይህን የተመሰቃሰለ ዓለም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጽድቶ በሰላም ሊነግስ የሚመጣውን እግዚአብሔር ወልድን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን፣ በማመን
ብቻ ነው። በትንሳኤም ቀን የሚፈርደው ይኽው ክርስቶስ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ወደ እግዚአብሔር የመድረሻ መንገድ የለም።
እውነትም መንገድም ህይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በዚህ ዓለም ከሚከሰቱ ክፉ ነገሮች ሁሉ ልናመልጥ እንችል ይሆናል። ከሞትና
በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ከመውደቅና ዘለዓለምን በሲኦል ከማሳለፍ ሊያድነን የሚችል ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዛሬ ይህን
ጌታ አምነን እንዳን። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም። ምንም ክፉ ነገር ባይሆንም ደግሞ በክርስቶስ አምነን ከእግዚአብሔር ጋር
ልንኖረው የምንችለውን የዘለዓለሙን ህይወት፣ እረፍትና ደስታ ከሞት ወዲህ ማዶ ዛሬውኑ መለማመድ መጀመሩም ይህች ዓለም ከምትሰጠው
ነገር ሁሉ የከበረ ምስጢር ነው። ጌታ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ዓይኖቻችንን በመክፈት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠውን ፍቅሩ በመቀበል
እንድናምን ይርዳን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ