የመለከት ድምጽ ብሎግ የአማርኛን ቋንቋ በተቀዳሚነት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ለማድረስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ያገለግላል።
የሰው ልጅ ራሱን ወደሚያጠፋበት ምሳሌያዊ እኩለ ሌሊት (proverbial midnight) ለመድረስ የቀረው ጊዜ ሁለት (2) ደቂቃ ብቻ ነው ተባለ።
የሰው ልጅ ራሱን ወደሚያጠፋበት ምሳሌያዊ እኩለ ሌሊት (proverbial midnight) ለመድረስ የቀረው ጊዜ ሁለት (2) ደቂቃ ብቻ ነው ተባለ። ቃየል በቅንዓት ተነሳስቶ የገዛ ወንድሙን
ንጹህ ደም ካፈሰሰባትና የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ከሆነባት ከዚያች አሳዛኝ ቀን ጀምሮ የሰው ዘር ከጦርነትና እርስ በእርሱ በየሰበብ
አስባቡ ከመገዳደል ያረፈባቸው ቀናት ጥቂት ናቸው። የዚህ የዛሬው መልእክት መነሾ ወደሆነው ርእስ መለስ ስንል የምንረዳው ነገር
ደግሞ ከጦርነቶችም ሁሉ በላይ እጅግ የከፋ የሚሆነው የኑክሊየር ጦርነት እንደሆነ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሰው ዘር ታሪክ እንደምንማረው
እጅግ ጥቂቶች ከሆኑት በስተቀር የሰው ልጅ ፈጥሮ ስራ ላይ ሳያውላቸው የቀሩ የጦር መሳሪያዎች አሉ ለማለት ያዳግታል። ባለፉት
75 የሚሆኑ ዓመታት የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ተራቅቄያለሁ ብሎ አርቅቆ ከሰራቸው እጅግ ብዙ ህዝብን ከሚፈጁ መሳሪያዎች መካከል የኑክሊየር
የጦር መሳሪያዎች በቀደምትነት የሚቀርቡት በከንቱ አይደለም። Bulletin of the Atomic Scientists በመባል የሚጠራው የባለሙያዎች
ስብስብና መድረክ ላለፉት ሰባ ዓመታት ያህል ዓለም ምን ያህል ወደ ኑክሊየር እልቂት እንደተቃረበች የሚያሳዩ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጣ
ቆይቷል። ከዚህ መልእክት ጋር የተያያዘው የዚህ ዓመቱ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ከ1953 ዓም (እኤአ) በኋላ ዓለም ምሳሌያዊ ወደሆነው
የ ኑክሊየር እልቂት እኩለ ሌሊት የደረሰችበት ጊዜ እንዳልነበረ ያሳያል። በባለሙያዎቹ ግምገማ መሰረት የሰው ዘር ራሱን በኑክሊየር
መሳሪያዎች ሊፈጅ ወደሚችልበት “እኩለ ሌሊት” የቀረው ጊዜ ሁለት ደቂቃ ያህል ብቻ ነው። የሶቪየት ህብረት የመጀመሪያውን የኑክሊየር
ቦምብ በፈተሸችበት በአውሮፓውያኑ 1949 ዓም ይኽው የባለሙያዎች መድረክ ለእኩለ ሌሊት የቀረው ሶስት ደቂቃዎች ናቸው በማለት አስጠንቅቆ
ነበር። በ1953 ዓም አሜሪካ በጉልበቱ ከቀደሙት የአቶሚክ ቦምቦች እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የሃይድሮጅን ቦምብ በፈተሽበት ዓመት
ደግሞ ልክ እንደ ዘንድሮው ለጥፋት የቀረው ጊዜ ሁለት ደቂቃ ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ሶቪየት ህብረትና የምስራቁ
የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት መፈራረሱን ተከትሎ፣ ኮሚኒዝም ወደቀ፣ ቀዝቃዛው ጦርነት አከተመ፣ ምድር ሁሉ ሰላም ልትሆን ነው የሚሉ
ድምጾች ባስተጋቡበት በ1991 ዓም ደግሞ እነዚህ ባለሙያዎች የኑክሊየር ጥፋቱን ሰዓት በ15 ደቂቃ ወደኋላ በመመለስ ዓለም ከኑክሊየር
ፍጅት አደጋ በብዙ መራቋን የሚያመለክት ብዙ ተስፋ የተሞላበት መልእክት አስተላልፈው ነበር። ከ16 ዓመታት በኋላ ግን ሰሜን ኮሪያ
የኑክሊየር መሳሪያን በፈተሽበት በ2007 ዓም የጥፋት ሰዓቱን በከፍተኛ ፍጥነት ወደፊት በመግፋት የጥፋት እኩለ ሌሊት የቀረው
5 ደቂቃ ብቻ ነው ብለውም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት
ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም” በማለት በ1ኛ ተሰሎንቄ 5፡3 የተናገረው ከዚህ ሁኔታ ጋርም የተያያዘ ሊሆን ይችላል። 20ኛው
መቶ ክፍለ ዘመን የከፍተኛ እልቂት ክፍለ ዘመን መሆኑ በታሪክ የተዘገበለት ነው። በ1ኛውና በ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ የስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ
ተብሎ በሚጠራው እልቂት፣ በጀርመን በተፈጸመው የአይሁዳውያን ፍጅት፣ በተለያዩት አብዮቶችና ጸረ አብዮት ጦርነቶች፣ በበሽታና በረሃብ
ያለቀው የሰው ዘር በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ይቆጠራል። የሰውን ዘር ቁጥር ለመቀነስ ተብሎ በተቀየሰው ሰፊ የጽንስ ማስወረድ ዘመቻ መሰል
እርምጃም በዓለም ዙሪያ የተፈጀው ያልተወለደ የሰው ዘር ከአንድ መቶ ሚሊዮን ይበልጣል። እነዚህ ሁሉ እጅግ የሚዘገንኑ ቢሆኑም፣
ዛሬ “መለስተኛ ነው” የሚባል የኑክሊየር ጦርነት እንኳን ቢነሳ ከሚያልቀው ህዝብ ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። ዛሬ የምናያቸውና የምንሰማቸው
አስፈሪ ነገሮች ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት የግድ ሊሆን ያለው የምጥ ጣር መጀመሪያ አካል ናቸው።
እንደ ታጨች ንጽህት ድንግል ነቅታና ተግታ ሙሽራዋን ክርስቶስን የምትጠብቀው ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ምድር ሳይታሰብ እንደምትነጠቅ
መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ያስተምራል። ዓለም አቀፋዊ ጦርነትንና እልቂትን አስመልክቶ የዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 6 ቁጥር 4 እንዲህ ይላል፤
“ሌላም ዳማ (ቀይ) ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ፣ ሰዎችም እርስ በእርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን
ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” ዛሬ ከምናውቃቸው የሰው ልጅ ከሰራቸው ሰይፎች ሁሉ መካከል እንደ ኑክሊየር ቦምብ ያለ
የከፋ መሳሪያ የለምና፣ ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ኑክሊየር እልቂት ነው ተብሎ በብዙ የትንቢት ምሁራን ይታመናል። ዛሬ በታላላቆቹ
የዓለም ኃይላት መካከል የሚደረገውን የጦርነት ፉክክር፣ ዝግጅት እና የመሳሪያ እሽቅድምድም አትኩሮ ለሚያይ ሰው ለሰው ልጅ ምንም
ተስፋ የቀረ አይመስልም። ነገር ግን ታሪክንና ፍጥረትን ሁሉ በእጁ የያዘ አምላክ በዙፋኑ ላይ አለ። እጅግ ብዙ ህዝብ በጦርነት
ሊያልቅ ቢችልም፣ የሰው ዘር በሙሉ ግን ከምድር ላይ አይጠፋም። ፍጥረቱ የሆነውን የሰውን ልጅ ስለወደደ በመስቀል ላይ ሕይወቱን
የሰጠውን የኢየሱስ የክርስቶስን ወንጌል የምስራች አምነው ለሚቀበሉ ሁሉ ታላቅና ዘላለማዊ ተስፋ አለ። የተስፋው መጀመሪያና መጨረሻ
ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ምሁራን፣ ፈላስፎች፣ ነገስታት፣ የጦርነት ባለጀብዱዎችና ባለጠጎች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች
ነን ያሉ ሁሉ ክንዳቸውን ተንተርሰው ሲቀሩ፣ የሞትን ጣር አጥፍቶ የተነሳውና የትንሳኤን ድል ያወጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
በእርግጥ ህሊናችን እና መንፈሳዊ ዓይናችን ተከፍቶ ማየት ብንችል፣ ከምንም በላይ የሚያስፈራው በዚህ ጌታ ሳናምን በመጨረሻው ቀን
ለፍርድ በፊቱ መቆማችን ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ሲመጣና የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ላይ ሲመሰርት የሰው ዘር ሁሉ ፍጹም ሰላምንና
ደስታን ያያል። ስለዚያ ዘመን ነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “በአሕዛብም
መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም መካከልይበይናል፣ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ
ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” ኢሳይያስ 2፡2፥4 በዚያን ዘመን በእግዚአብሔር መንግሥት ቦታ ሊኖረን የሚችለው የተሰበከልንን
የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመቀበል ዛሬ ነፍሳችንን ለእርሱ አደራ የሰጠን እንደሆነ ብቻ ነው። በኑሮ ግርግርና ሩጫ ተዘናግተን
ወይም በምንሰማውና በምናየው ክፉ ወሬ ሁሉ ተዋክበን የነፍሳችን እና የዘለዓለም ቤታችን ጉዳይ ችላ ብለን የዘለዓለሙ በር ሳናውቀው
እንዳይዘጋብን ዛሬውኑ ወደ ጌታ አምላክ እንመለስ። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። ብንመለስ ይምረናል፣ ይቀበለናል፣ በሞቱና በትንሳኤው
ኃይል አዲስ ሰው ያደርገናል። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...
-
የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5 ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ...
-
የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ትምሕርት 6 ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ...
-
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018 አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ