የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለዓለም መሪዎችና ህዝቦች “ቀይ ማንቂያ” ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለዓለም መሪዎችና ህዝቦች “ቀይ ማንቂያ” ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ። https://www.un.org/sg/en/content/sg/statement/2017-12-31/secretary-general’s-video-message-alert-world-1-january-2018-scroll
አዲሱን የአውሮፓውያን ዓመት 2018ን መጀመር አስመልክተው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክታቸው 193 አገሮች አባል የሆኑበትና በዓለም ላይ ሰላምንና ጸጥታን ለማስፈን በ1945 ዓም (እኤአ) የተመሰረተው ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት የቀድሞው የፖርቱጋል ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ጉቴሬስ አዲሱ ዓመት ከመቼውም ይልቅ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የመልእክታቸው ይዘት ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ነው፤ “ከአንድ ዓመት በፊት ይህን ኃላፊነት ስረከብ 2017 የሰላም ዓመት እንዲሆን ማሳሰቢያን (አቤቱታን) አቅርቤ ነበር። ነገር ግን እድለ ቢስ ሆንንና የዓለማችን ሁኔታ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ወደ ፊት ሄዶ በመሻሻል ፈንታ ወደ ኋላ ተመልሶአል። ዛሬ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ ለዓለም የማቀርበው ማሳሰቢያን ወይም አቤቱታን ሳይሆን ማስጠንቀቂያን (ማንቂያን)፣ ቀይ ማስጠንቀቂያን ነው። በዓለም ዙሪያ ግጭቶች ስር ሰድደዋል፣ አዳዲስ አደጋዎችም ከፊት ለፊታችን ተጋርጠውብናል። የኑክሊየር የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሃት ሰፍኖአል። የአየር ንብረት ለውጥ ከእኛ ይልቅ እየፈጠነ ይገኛል። በሰዎች መካከል የኑሮ ልዩነት ከበፊቱ የበለጠ እየሰፋ ይገኛል። ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን እያየን ነው። ብሔርተኝነትና ከእኛ የሚለዩ ሰዎችን የመጥላት አዝማሚያ እያደጉ ናቸው። ይህን ዓመት (2018ን) ስንጀምር ሁላችን አንድነትን እንድንመርጥ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ዓለማችንን በእርግጥ ሰላምና ደህንነት የሰፈነባት ማድረግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ለግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔን ማግኘት እንችላለን፣ ጥላቻን ተቋቁመን የጋራ እሴቶቻችንን መከላከል እንችላለን። ይህን ሁሉ ለማድረግ የምንችለው ግን አብረን ስንሰራ ብቻ ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ መሪዎች ሁሉ ይህን የአዲስ ዓመት ውሳኔ እንዲያደርጉ እገፋፋለሁ፡ ክፍተቶችን እናጥብብ፣ በለያዩን ነገሮች ላይ ድልድይ እንስራ፣ ህዝቦችን በጋራ ግቦች ዙሪያ በማሰለፍ መተማመንን እንደገና እንገንባ። ልንሄድበት የሚገባን መንገድ አንድነት ነው። ለመጻዔው ዘመናችን ወሳኝ ነውና።”

የዋና ጸሃፊው መልእክት የተጻፈው ለዓለም መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና አዋቂ ሰዎች እንዲደርስ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ረቅቆ በመሆኑ ከበስተጀርባው ያለውን የጭንቀትና የውጥረት መልእክት ብዙዎቻችን በቀላሉ ላንረዳው እንችላለን። በአጭሩ ለማስቀመጥ እኒህ ከፍተኛ የዓለም መሪ የሚነግሩን ነገር ዓለም ከመቼውም የበለጠ በከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኗን፣ እጅግ ብዙ ህዝቦችን ሊያጠፋ የሚችል የኑክሊየር ጦርነት ጥቁር ደመና ማንንዣበቡንና፣ የዓለም መሪዎችም እጅግ ከመከፋፈላቸው የተነሳ ውጥረቶችንና ግጭቶችን ለማርገብና ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማግኘት እንዳልቻሉ ነው። ዓለምን ወደ ፍጹም ጥፋት ሊከቱ የሚችሉ የጦርነት እሳቶች በየቦታው መጨስ ከመጀሩ ውሎ ማደሩን አንዘንጋ። በምስራቅና በሰሜን አውሮፓ የአሜሪካና NATO ጦር ሰራዊትና መሳሪያ 2014 ጀምሮ በብዛት ጨምሮአል። በመካከለኛው ምስራቅ በሳውዲ አረቢያና በኢራን መካከል ያለው መፋጠጥ ከፍተኛ ነው። በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን እንዲሁም በሚደግፉአቸው የአረብና እስላማዊ አገሮች መካከል ያለው ውጥረት እጅግ ተባብሶአል። ይህ ውጥረት በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በኢራቅ፣ በካታር፣ በባህሬን፣ በቱርክና በሌሎችም አገሮች  የውስጥና የውጭ ጉዳዮችም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድር አካባቢው በቀላሉ ወደ ጦርነት እሳት ሊገባ ይችላል። በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ አሜሪካ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ያላት ስትራቴጂያዊ ትግል አካል መሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው። ብዙዎች እንደ ቀላል እንደሚያወሩት በነዚህ ከላይ በተጠቀሱትና ሌሎችም ግጭቶች ምክንያት ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ ሊያልቅ የሚችለውን ህዝብ ለመገመት አዳጋች ነው። ዛሬ በምድር ላይ ካሉት 15 በላይ የኑክሊየር መሳሪዎች መካከል 100 የሚሆኑት ብቻ እንኳን በኮሪያ አካባቢ በስራ ላይ ቢውሉ ምድር ወደ ከፍተኛ ጥፋት ውስጥ እንደምትገባ የዚህን መሳሪያ አጥፊነት የሚያውቁ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

 በዚህ በ2018 መጀመሪያ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እጅግ አደገኛ መሆኑን በዚህ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ያመለከቱትና ማስጠንቀቂያን የሰጡት እኒህ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ብቻ አይደሉም። ብዙ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት የሮማዋ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ የሆኑት ፍራንሲስም በበኩላቸው እጅግ አስፈሪ የሆነ ምልክትን በመጠቀም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያን አስተላልፈዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ አሜሪካ ናጋሳኪ በምትባለው የጃፓን ከተማ ላይ በጣለችው የኑክሊየር ብሞብ የሞተ አንድ ህጻንና የህጻኑን አስከሬን በጀርባው ላይ ያዘለ ወንድሙን ፎቶ የያዘና “የጦርነት ፍሬ” የሚል የእርሳቸው ጽሁፍና ፊርማቸው ያለበትን ካርድ በመልቀቅ በ2018 እጅግ የከፋ እልቂት በምድር ላይ ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በዚሁ ባለፈው ዓመት የመጨረሻ ቀን ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ጦር ጥምር መሪዎች ሊቀመንበር የነበሩት ጀነራል ማይክ መለን በቴሌቪዝን ቀርበው ሲናገሩ “በእኔ አስተያየት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ከሰሜን ኮሪያ ጋርና በዚያ አካባቢ ወደ ኑክሊየር ጦርነት የምንገባበት ጊዜ በጣም ቀርቦአል” ብለው መናገራቸው በእርግጥም እጅግ ብዙ ህዝብን የሚፈጅና ዓለምን ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሊዘፍቅ የሚችል አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ያሳያል። የጀነራሉ የትዊተር መልእክት የሚከተለው ነበር፡  Former Joint Chiefs chair Adm. Mike Mullen to @MarthaRaddatz: "We're actually closer, in my view, to a nuclear war with North Korea and in that region than we've ever been."
እነዚህ ታላላቅ የዓለም መሪዎችና በጉዳዩ የቅርብ እውቀት ያላቸው ሰዎች ከሚናገሩት በተጨማሪ ብዙ የእግዚአብሔርን ፊት ከልብ የሚፈልጉና ለአገሮቻቸው የሚጸልዩ ክርስቲያኖችና አገልጋዮች ይህ አስፈሪ ዜና እውን ሊሆን እንደሚችል በሕልም፣ በራዕይና በሌላም ሰማያዊ መገለጥ ሰማያዊ ማስጠንቀቂያን እንደተቀበሉ ሲናገሩ ውለው አድረዋል። ከመገለጾች ሁሉ በላይ የሆነውና የጸናው የእግዚአብሔር ቃል መፅሐፍ ቅዱስ ደግሞ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ምጽዓት ሲቃረብ፣ እግዚአብሔር ባይገታቸው፣ የሰውን ዘር ሁሉ ሊያጠፉ የሚችሉ ጦርነቶች እንደሚከሰቱ ይናገራል። ብዙ ሰዎች፣ የክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲያኖችም ጭምር ይህን ዓይነት መልእክት ስናነብ “ታዲያ ምን ይሁን?” “እኔ ምንም አቅም የለኝም፣ ምን ማድረግ እችላለሁ?” ልንል እንደምንችል ከዚህ ቀደም በላክኋቸው መልእክቶች ላይ ከተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች እገነዘባለሁ። ወገኖቼ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎችም ምንም እንኳን መሪዎች ቢሆኑና ስልጣንም ቢኖራቸው እንደኛው “አንድ” ሰው ናቸው። ዛሬ በምድር ላይ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መንፈሳዊ ጦርነት አካል ነው። ስለዚህ ክርስቲያን በኤፌሶን መልእክት ምእራፍ 6 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን እቃ ጦር በመልበስ በእውነተኛ የወንጌል መታዘዝ፣ በጾምና በጸሎት ለምድር መሪዎችና መንፈሳዊ ግራ ቀኛቸውን ለማያውቁ ህዝብ ሁሉ ልንጸልይ ይገባል። በእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም የተነገረው ትንቢት ሁሉ ይፈጸማል። ነገር ግን በሁሉም ላይ ስልጣን ያለውን የፍቅርና የሰላም አባት የሆነውን እግዚአብሔርን ከልባችን ስንፈልገው ይራራ ይሆናል። የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ እስኪመለስና በምድር እስኪነግስ ድረስ ጥፋትና ጦርነት እንደታወጀ ነቢዩ ዳንኤል ከሰማይ ሰምቶ በምዕራፍ 9 ቁጥር 26 እና በሌሎች ስፍራዎችም ጽፎአል። ሌሎች ነቢያትና ሐዋርያትም እንዲሁ። ይህ የዘመን መጨረሻ የደረሰብን እኛ ደግሞ ቃሉ እንደሚያዝዘን ለመሪዎች በመጸለይና የወንጌሉን ፍቅር በመመስከር እንዲሁም በያለንበት ልናደርገው የምንችለውን መልካም ነገር ሁሉ በማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተመልሶ ይመጣል። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


1 አስተያየት:

  1. በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን መካከል ስላለው ቅድመ ጦርነት ሁኔታ ጥሩ አጠቃላይ እይታ እና ትንተና እናመሰግናለን

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...