መልካም የምዕራባውያን አዲስ ዓመት

መልካም የምዕራባውያን አዲስ ዓመት
የአውሮፓውያኑን የዘመን መለወጫ ለምታከብሩ ሁሉ እንኳን እግዚአብሔር በሰላም ለ2018 አደረሳችሁ። በአዲሱ ዓመት ሕይወታችሁ በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር፣ በበረከትና በስኬት የተሞላ ይሁን !! ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ አዲስ ዓመት እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር ሁሉ የገለጸውን ዘለዓለማዊና አቻ የሌለው ፍቅሩን በኑሮአችሁ ሁሉ የምትለማመዱበት ይሁንላችሁ። ይህ ያለፈው 2017 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተፈጸሙበት፣ በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የሰውን ዘር ህልውና ሊያጠፋ የሚችል የጦርነት ደመና ያንዣበበት፣ ለብዙ አሰርት ዓመታት ተደብቆ የቆየው የወደቁ መላእክትና የኔፊሊም መኖር (UFO, ET ወዘተ በሚባሉ ዘመናዊ መሰል የምስጢር ስሞችም ቢሆን) በአሜሪካ መንግስት በገሃድ የተነገረበትና ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ብዙዎች የእግዚአብሔር ቃል እውነት ወደ ጎን በመጣል የሚያጠፋ ኑፋቄን በግልጽ የተቀበሉበት ዓመት ነበር። እግዚአብሔር ግን ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፣ ይጠብቅማል። በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ማድረግ የሰብዓዊ ፍጡር ልምድ ነው። ተስፋ የሌላቸው ሰይጣንና መላእክቱ እንዲሁም ደግሞ የክርስቶስን ወንጌል እምቢ አንቀበልም ብለው ከዚህ ህይወት ያለፉ ሙታን ብቻ ናቸው። እኔ በግሌ፣ እንዲሁም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶችና የዘመኑን ሁኔታ የሚያጠኑ ክርስቲያኖች፣ 2018 ብዙ ትንቢቶች የሚፈጸሙበት ዘመን ሊሆን እንደሚችል እናምናለን። እስትንፋስ በውስጣችን እስካለ ድረስ ሁላችንም በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ተቀብለን፣ ወንጌልኑ በማመንና በመታዘዝና በኃጢዓታችን ተናዝዘን የእግዚአብሔርን ምሕረት በማግኘት ከሚመጣው ቁጣ ሁሉ ለማምለጥና ወደ ዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንችላለን። ይህ ተስፋ ግን ለዘለዓለም ክፍት ሆኖ አይቆይም። በቅዱሳን ነቢያት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያትም እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ባላወቀውና ባላሰበው ሰዓት ከተፍ ይላል። አሁንም ጭንቅላቱን ብቅ ብቅ ማድረግ እንደጀመረ የስህተትና የማታለል መንፈስ ምድርን ሁሉ እንደ ግርፍ ማጥለቅለቁ የግድ ነው። ስለዚህ ገና ቀን ሳለ ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። በአዲሱ ዓመት በዘመናት ሁሉ ሊታመን የሚችለውንና የማይናወጠውን አንዱን እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ እናድርግ። ነቢዩ ሆሴዕ እንደ ተናገረው “እንወቅ፣ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፣ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል።” ትንቢተ ሆሴዕ 6፡3 ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ ነው። እርሱ ብቻ መንገድና እውነት ሕይወትም ነው። በወልድ በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ወደ አብ መምጣት አይችልም። ማንም በምንም መንገድ አያታልለን። ሰማያትና ምድር ሲናወጡና ሲያልፉ የማያልፈው የክርስቶስ ቃል ነው። “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።” ማቴዎስ 24፡35 መልካም አዲስ ዓመት !! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...