ሰው ሰራሹ የጉግል ኦውቶኤምኤል ናስ ኔት የተባለውን የራሱን ልጅ ፈጠረ (ወይም ወለደ) ተባለ። https://www.dailystar.co.uk/news/latest-news/664713/google-artificial-intelligence-ai-child-NASNet-AutoML
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማና ክብር ከመገለጡ በፊት በምድር ላይ ታላቅ
የመከራ ዘመን እንደሚሆን በነቢያት፣ በራሱ በጌታችን እና በሃዋርያትም ደጋግሞ ተነግሮአል። በዚያ በታላቁ የመከራ ጊዜ በምድር ላይ
ከሚከሰቱት እጅግ አስፈሪ ነገሮች አንዱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የሰውን ልጅ እርስ በርሱ የሚያፋጁ ጦርነቶች በየቦታው
መነሳታቸው ነው። ባለፉት ብዙ ሺህ ዓመታት የሰው ልጅ ከፈጠራቸው የእልቂት መሳሪያዎች ሁሉ የኑክሊየር ቦምብ እጅግ አስከፊው፣ ምድርንና
ፍጥረትን ሁሉ የሚያወድም መሆኑ ብዙ ይነገራል። በ1945 ዓም ነሃሴ ወር ላይ ሂሮሺማና ናጋሳኪ በሚባሉት ሁለት የጃፓን ከተማዎች
ላይ የተጣሉት የአቶሚክ ቦምቦች የፈጠሩትን ውድመት ያየ፣ ወይም ያነበበ ሰው ይህ መሳሪያ በእርግጥ ምን ያህል አስከፊ መሆኑን ያስተውላል።
እጅግ የሚያስፈራው ግን እነዚያ በጃፓን ላይ የተጣሉት ቦምቦች ከዛሬዎቹ ዘመናዊ ተርሞ ኑክሊየር ቦምቦች ጋር ሲነጻጸሩ ምናልባት
በሽጉጥ እና በመድፍ ወይም በታንክ መካከል ካለው ልዩነትም የበለጠ ልዩነት ያላቸው መሆኑ ነው። የኑክሊየር ቦምብ እጅግ አስከፊ
ቢሆንም፣ የሚቆጣጠሩት ሰዎች እስከሆኑ ድረስ፣ ትንሽም ቢሆን አርፈን በሰላም መተኛት እንችላለን። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ
ፍጥነት እያደገ የመጣውና የሰውን የመማር፣ የማወቅ፣ የማስላት፣ የመወሰንና የማስታወስ ችሎታ በብዙ እጥፍ ይበልጣል የተባለለት አርቲፊሻል
ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አእምሮ) የሚባለው ቴክኖሎጂ ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ልጅ ከሰራቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ አስፈሪና አጥፊ
ሊሆን እንደሚችል ፈሪሃ እግዚአብሔር እንኳን የሌላቸው ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው። ይህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ
ያለው ችሎታ ብዙ ህዝብን የሚፈጅ የጦር መሳሪያ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎችንም ለመግደልና ለመፍጀት በራሱ ውሳኔ ማድረግ መቻሉ ነው።
ያ ውሳኔ ደግሞ ርህራኄ እና ጸጸት የሌለበት ስለሆነ በዚህ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ስር የሚካሄድ ጦርነት ያለምንም ስህተት በሚሊዮን የሚቆጠሩ
ህዝቦችን በአንድ ጊዜ ይፈጃል የሚለው ፍርሃትና ስጋት ታላላቅ የዓለም መሪዎችንም እረፍት የነሳ ጉዳይ ነው። በእጅ የምንይዛቸው
ስልኮች፣ በየመንገዱና በየሱቁ የተተከሉ ካሜራዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ መኪናዎችና የቤት እቃዎችም ሳይቀር ፎቶና ቪዲዮ የማንሳት ብቻ
ሳይሆን የሰውን ፊት፣ የእጅ አሻራና ድምጽን የመለየት፣ ያለንበትን ቦታ የማወቅና ያለ ፈቃዳችን ለሌሎች ማስተላለፍ ችሎታ ከተሰጣቸው
ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ታዲያ ከነዚህ መሳሪያዎች የሚሰበሰበውን መረጃ በኢንተርኔት አማካይነት በመጠቀም
የፈለገውን ሰው፣ የሰዎች ስብስብ ወይም ህዝብ አብራሪ በሌላቸው ትንንሽ አውሮፕላኖችና ሌሎችም መሳሪያዎች የማጥፋት ችሎታ አለው።
ዳርፓ (DARPA) የሚባለው የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስቴር የምስጢር ፕሮጀክቶች መስሪያ ቤት፣ እንዲሁም ሌሎች የቻይና፣ የሩሲያና
ሌሎችም በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ የተራቀቁ አገሮች ድርጅቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመሩ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት በእሽቅድምድም
ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን በቅርቡ በአንድ የሩሲያ የተማሪዎች ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ
የሚሰሩ ሰው ሰራሽ ወታደሮችና ቴክኖሎጂዎች ከኑክሊየር ቦምብ ይልቅ ለሰው ዘር ህልውና እጅግ አስጊ እንደሆኑ ተናግረዋል። የእውቀት
ሁሉ ባለቤት የሆነው ልዑል እግዚአብሔር ይህን እኛ ዛሬ የምናየውንና የምንሰማውን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስለሚያውቅ ነው ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት የሰውን ዘር ከምድረ ገጽ ፈጽሞ ሊያጠፉ
የሚችሉ ታላላቅ ጦርነቶች እንደሚከሰቱ በነቢያት፣ በልጁ በክርስቶስና በሐዋርያት አማካይነት አስቀድሞ የነገረንና ያስጠነቀቀን። ለዚህም
ነው ተግተን እንድንጸልይና መዳናችንን በትልቅ ፍርሃትና ጥንቃቄ እንድንይዝ አዲስ ኪዳን የሚያስተምረን። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁጥር 21 እና 22 ላይ ስለዚህ ቀን ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎአል፤ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም
ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፣ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት
ሰዎች ያጥራሉ።” በክርስቶስ በማመን የወንጌሉን ተስፋ የተቀበለ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር
የተመረጠ ስለሆነ ሊፈራና ሊደነግጥ አይገባውም። ምክንያቱም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፡ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ
ጥላ ውስጥ ያድራል።” መዝሙር 90(91)፡1 “አምላካችን መጠጊያችንና
ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” መዝሙር
45(46) ቁ1 እና 2። ነገር ግን በክርስቶስ አምነው ላልዳኑ ሰዎች የንስሃው በር የሚዘጋበት ቀን በየእለቱ እያጠረ ነው። ስለዚህ
የራሳችንን መዳን በማሰብ እግዚአብሔርን ስናመሰግን፣ አምላካችን ለነዚያ ላልዳኑ ወገኖቻችን ያለውን ፍቅር ለመናገርና ለመመስከር
ያለን ጊዜም እያጠረ እንደሚሄድ እናስብ። ዘማሪው “ነፍሴ ወዳምላኳ፣ ስጋም ወዳፈሩ ሳይመለስ፣ ቶሎ ቶሎ ብዬ ስራዬን ልጨርስ” ብሎ
እንደዘመረው ለራሳችን እንጸልይ፣ ለሌሎች እናማልድ፣ ላልዳኑት እንመስክር። ጌታም በነገር ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ
ከእኛ ጋር ነው። ጌታ ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ