የአሜሪካ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከ70 ዓመታት በላይ በከፍተኛ ደረጃ በምስጢር
ተደብቆ የነበረውን ምንነታቸው የማይታወቁ የበራሪ ዲስኮች እውንነት ለመጀመሪያ ጊዜ አመነ፣ የተያያዘ መረጃንም ለመገናኛ ብዙኃን
ለቀቀ።
“የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ … “ ሉቃስ 8፡17-18
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እጅግ እየተቃረበ ስለመጣ የሰውን ዘር መንፈሳዊ ሕይወት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ
እናምናለን የሚሉ ክርስቲያኖችንም ጭምር ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱ ነገሮች በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ቁጥርና ፍጥነት እየተከሰቱ
ናቸው። ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመቱ በመለከት ድምጽ መጽሔት፣ በብሎግ እና በዚህ በFacebook በማስተላልፋቸው መልእክቶች በአጭሩ ላቀርብ እንደሞከርሁት አዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ተራማጅ
ሃሳቦች፣ ለሰው ሁሉ የሚጠቅሙ ነገሮች በሚል ሽፋን የሰውን ልጅ በማታለልና በመሸንገል የሰው ዘር አንዱን አምላክ እግዚአብሔርን
በእውነትና በመንፈስ እንዳያመልክ በተለይም ደግሞ በአንዱና ብቸኛው የሰው ዘር ሁሉ አዳኝ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳያምን የሚደረጉትና
መጽሐፍ ቅዱስ ያጋለጣቸው የጨለማውን ገዥ መንፈሳዊ፣ ሃሳባዊና ቁስ አካላዊ ሴራዎች ዛሬ በአደባባይ በግልጥ መነገር ጀምረዋል። ከነዚህም ነገሮች መካከል የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች (Flying Saucers, UFOs ወዘተ) የሚባሉት ነገሮችና እነርሱንም የሚያበሩት ፍጥረታት
(Aliens, ETs, ወዘተ) ይገኙበታል። በተለይም
ደግሞ በመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 4 እና 5 ላይ በነዚህ ርእሶች ላይ ሰፋ ያላ ጽሁፍ ቀርቦአል።
ከዚህ አጭር ጽሁፍ ጋር በተያያዘውና ዋሽንግተን ፖስት በሚባለው የታወቀ የአሜሪካ ጋዜጣና ሌሎችም እጅግ ብዙ የቴሌቪዝን፣
የሬድዮ እና የጋዜጣ እንዲሁም የማህበረሰባዊ መገናኛ ብዙኃን ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደ ግሩም ድንቅ ነገር በአደባባይ እየተዘገበ
ያለው በቅርቡ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ከ70 ዓመታት በላይ በምስጢር ተይዞ የነበረውን “የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች”
እውንነት ከላይ ከጠቀስኳቸው ከመጨረሻው ዘመን ክስተቶች አንዱ ነው። ዛሬ እንዲህ በአደባባይና በአሜሪካ መንግስት እውንነቱ መገለጥ
የጀመረው የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች (UFO) ጉዳይ ባለፉት 70 ዓመታት ፍንጩ በነበራቸውና እውነቱን ለማወቅ በሚፈልጉ በብዙ ተመራማሪዎች
ሲጠና የኖረ፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ መጻህፍት የተጻፉበት፣ ብዙ ፊልሞች የተሰሩበት ቢሆንም፣ አሜሪካም ሆኑ ጉዳዩን በምስጢር የያዙት
ታላላቆቹ አገሮች እውንነቱን በይፋ ይክዱ ስለነበር እነዚህ ነገሮች እውን ናቸው ብሎ የሚያምን ምሁር፣ ተመራማሪ ወይም በሃላፊነት
ቦታ ላይ የተቀመጠ ሰው ሁሉ እንደ እብድ ወይም አላዋቂና የሚቃዥ ተደርጎ ይቆጠር፣ ከክብሩ ይዋረድና በአደባባይም መሳቂያ ይደረግ
ነበር። በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀትና መረጃ ያላቸው ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትን የሚያጠኑ ክርስቲያኖች ታዲያ
ዛሬ ብቅ ብቅ እያለ ያለው የአሜሪካ መንግስት መረጃ አሁንም ቢሆን ገና ጫፍ ጫፉ ነው ይላሉ። መረጃው ጥቂት በጥቂት ለህዝብ የሚለቀቀውም
የዓለም ህዝብ ጉዳዩን እንዲለማመደው ለማድረግና ለከፍተኛውና ለመጨረሻው እውነት መገለጥ ለማዘጋጀት ነው የሚሉም ብዙ ናቸው።
በ1947 ዓም ሮዝዌል ኒው ሜክሲኮ በሚባለው ስፍራ የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች እንደተከሰከሱና እነርሱንም ሲያበሩ የነበሩ
ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታት ከፊሎቹ ሞተው አስከሬናቸው፣ ከፊሎቹ ደግሞ በህይወት ተይዘው በህዝብ በማይታወቅና በከፍተኛ ምስጢር
በሚጠበቁ በምድር ውስጥ ባሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ውስጥ መቀመጣቸው ብዙ የተጻፈበት ጉዳይ ነው። የአሜሪካ መንግስት ግን ይህ
ነገር መሆኑን በመካድ የተከሰከሰው የአየር መመራመሪያ ባሉን ነው ማስተባበሉም በብዙዎች የታወቀ ታሪክ ነው። አንዳንድ የአሜሪካ
የመከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣናት የነበሩና ጉዳዩን በቀጥታ የሚያውቁ እንደ ሌተና ኮሎኔል ፊሊፕ ኮርሶ ያሉ ሰዎች ደግሞ የተከሰከሱትን
የማይታወቁ በራሪ ዲስኮችና የሞቱትን ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታትም እንዳዩ በመጻህፍትና በሌሎችም መንገዶች ዘግበዋል። እነዚያ
ከዚህ ዓለም አይደሉም የሚባሉትን በራሪ ዲስኮችና ያላቸውን ቴክኖሎጂ በመቅዳትና ከነዚያ ፍጥረታት ጋር በቅርብ በመስራት የአሜሪካ
መከላከያ ሚኒስቴር ተመሳሳይ በራሪ ዲስኮችንና ሌሎችም መሳሪያዎችን ሰርቶ መፈተሹን ደግሞ ከ1950ዎቹ ጀምረው በስራው የተሳተፉ
ወይም ጉዳዩን በቅርቡ የሚያውቁ ሰዎች መረጃውን ሲያወጡ ቆይተዋል። መቼም በዚህ ዘመን ብዙ የምንደነቀው በቴክኖሎጂ ሆነ እንጂ ጉዳዩ
ግን የቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም። እነዚያ ከዚህ ዓለም አይደሉም የሚባሉትና በስውር ከአሜሪካ መንግስት የመከላከያ ተቋማት (ምናልባትም
ደግሞ እንደ ሩሲያና ቻይና ካሉ ሌሎች ትልልቅ አገሮች) ጋር የሚሰሩት ፍጥረታት እነማን ናቸው? መልሱ ቀላል ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስና
ዛሬ በግልጽ በብዙ መጻህፍት የተዘገቡ መረጃዎች ግን ስለነዚህ ፍጥረታት ማንነት ብዙ ፍንጮችን ይሰጡናል።
በአደባባይ እስካሁን ሲነገር የነበረውና አሁንም የምንሰማው የሰው ልጅ በሌሎች ዓለማት ላይ እንደሰው ያሉ ፍጥረታት መኖራቸውን
ለማወቅ ገና ምርምር እያደረገ ነው የሚለውን ወሬ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ እንዳየነው እነዚያን የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች
የሚያበሩ ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታት መኖራቸው ግልጽ ነው። በሚቀጥሉት
ሳምንታትና ወራት ከዚህ ጋር የተያያዙ ብዙ “ዜናዎች” እና “መረጃዎች” እንደሚቀርቡ አጠራጣሪ አይደለም። ታዲያ ይህ መረጃ ለምን
እስካሁን ከህዝብ ተሰወረ? እነዚህ ማንነታቸው የተደበቁ ፍጥረታት ምንድን ናቸው? ዓላማቸው ምንድን ነው? መቼና ለምን ወደዚህ ምድር
መጡ ለሚሉት ጥያቄዎች እውነተኛ ወይም ቀጥተኛ መልስን ከመገናኛ ብዙሃን ወይም ጉዳዩን ከያዙት ድርጅቶች መጠበቅ የዋህነት ነው።
ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ቀደም ሲል ዓለምን ሁሉ የሚያስት፣ እኔ አምላክ ነኝ የሚልና የዓለም ህዝብ ሁሉ የሚሰግድለት
“የዐመጽ ሰው፣ የጥፋትም ልጅ” የሚባለው ሐሰተኛው ክርስቶስ እንደሚገለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ብዙ ትንቢታዊ ምርምሮችና ጥናቶች
እንደሚያመለክቱት ሐሰተኛው ክርስቶስ የሚገለጸው የሰው ልጅ እስከ ዛሬ አይቶት በማያውቀው ቴክኖሎጂ ተከቦ እንደሆነ የዮሐንስ ራዕይ
ምእራፍ 13ን ማንበብ ብቻ ብዙ ያስተምራል። የዓለም ታዳጊና አዳኝ ነኝ ብሎ የሚገለጸው ያ የዓመጽ ሰውና የጥፋት ልጅ ደግሞ ከሰው
ዘር እጅግ ከሚልቅ ስልጣኔና ከምድር ሌላ ዓለም የመጣ ነው ሊባል እንደሚችል ትንቢትን፣ ታሪክን እና ዛሬ እየተገለጸ ያለውን ክስተት
በቅርብ የሚያጠኑ ክርስቲያን መሪዎች ማስተማር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ርዕስ እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ለማስረዳትም ብዙ
ቦታ የሚፈጅ በመሆኑ መልእክቴን እዚሁ ጋ ለመቁረጥ እገደዳለሁ። የመልእክቴ ዋና ዓላማ ግን አንድ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጽበት
ዘመን እጅብ ቅርብ ነው። ምንና እንዴት እንድንሰማ እናስተውል፣ እንጠንቀቅ። በክርስቶስ አምነን ለመዳንና በዓለም ሁሉ ላይ እንደ
ጎርፍ ሊመጣ ካለው ጥፋት ልናመልጥ እንድንችል ብርሃን የሆነው የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን አለ። እናንብበው። በመለከት
ድምጽ መጽሔት ቁጥር 4 እና 5 ከዚያም ደግሞ በመለከት ድምጽ ብሎግ (http://voice-of-trumpet-amharic.blogspot.ca)
በዚህ ርዕስና በአጠቃላይም
ስለዚህ ስላለንበት የመጨረሻው ዘመን የሚያስረዱ ብዙ ጽሁፎች ቀርበዋል። ወገኖች እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ የክርስቶስን ወንጌል
ስላላመኑ በጨለማ እንዳሉት አናንቀላፋ። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን ባናውቅም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ተመልሶ ይመጣል። መብራታችን
በርቶ፣ የእምነት ወገባችንን ታጥቀን ሙሽራውን ለመቀበል እንዘጋጅ። የእስራኤል አምላክ ይባርካችሁ ይጠብቃችሁም። ወንድማችሁ በፈቃዱ
አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ