ሌላ ሊሳት የማይችል የትንቢት ፍጻሜ፤ "በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፣ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቆስላሉ፣ የምድርም አህዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።" ዘካርያስ 12፡3 http://www.foxnews.com/politics/2017/12/06/trump-officially-recognizes-jerusalem-as-israels-capital-orders-us-embassy-move.html
ያለንበት ወቅት እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት ትንቢቶች የሚፈጸሙበት መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ አያዳግትም። እያለፈ እያለፈ የሚከሰቱ አንዳንድ እውነታዎች ግን ከሌሎቹ የበለጠ የትንቢት ፍጻሜ ምን ያህል እውን እንደሆነ ያሳያሉ። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1917 ዓም የታላቋ ብሪታንያ መንግስት በዘመኑ ፓለስታይን ተብሎ በሚጠራውና በኦቶማን ቱርክ ግዛት ስር በነበረው ምድር አይሁድ የራሳቸው የሆነ አገር መገንባቱን ትደግፋለች በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አርተር ጀምስ ባልፉር ለዘመኑ የእንግሊዝ አይሁዳውያን መሪ ሎርድ ዎልተር ሮትቻይልድ የጻፉት ደብዳቤ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ተበታትነው የነበሩት አይሁዳውያን ወደጥንታዊ አገራቸው በመመለስ እስራኤል የምትባለው አገር እንደገና በምድር ካርታ ላይ ብቅ እንድትል በር ከፋች መሆኑ በሰፊው የተዘገበበት ነው። የዚያ ደብዳቤ 100ኛ ዓመት ባለፈው ወር ነበር በብዙ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች ታስቦ የዋለው። በብዙ ነቢያት በተደጋጋሚ የተነገረውና በ1917 ጭላንጭል የታየበት የአይሁድ ህዝብ እንደገና መሰብሰብ ታዲያ በ1948 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ተፈጽሞ እስራኤል እንደገና ብቅ አለች። አይሁዳውያን ከምድሪቱ ላይ በተለያየ ጊዜ ተነቅለው ወደ ስደት የሄዱት በጥንቱ የሶርያ ግዛት፣ በግሪኮች እና በሮማውያን ወረራዎች እንደሆነ ታሪክ በዝርዝር ቢዘግበውም ዛሬ ብዙ ታሪክ እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ግን በመጽሐፍ ቅዱስና በጥንት ታሪክም የተመሰከረለትን እውነት ለመቀበል አይፈልጉም። ብዙዎቹ እንዲያውም አይሁዳውያን ዛሬ እስራኤል ተብላ በምትጠራው ምድር ላይ ኖረውም አያውቁም በማለት ይክዳሉ። አገሩ ፓለስታይን ህዝቦቹም ፍልስጥኤማውያን ብቻ ናቸው እያሉም በሰፊው ይናገራሉ። እስራኤል እንደ አገር እንደገና ካቆጠቆጠችበት ከ1948 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ነው። እስራኤል እንደ አገር መኖር የለባትም ሲሉ የነበሩና በጦርነትም ሊያጠፉአት ወግተዋት የነበሩ ግብጽና ዮርዳኖስ ከእርሷ ጋር የሰላም ውል ቢፈራረሙም ሌሎች እጅግ ብዙ መንግስታት ግን አሁንም የእስራኤል እንደ አገር መኖር አይዋጥላቸውም። ይህ በዚሁ እንዳለ፣ እኤአ በ1967 ዓም እናጠፋታለን ብለው የተነሱ ብዙ አገሮች በወረሯት ጊዜ ነበር የእስራኤል ጦር የጥንት ዋና ከተማዋ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ የገባው። በ 70 ዓም የፈረሰው የእስራኤል ቤተ መቅደስ በነበረበት ስፍራ ላይ ሮማውያን የአምላካቸውን የጁፒተርን ቤተ ጣዖት አኑረው ከቆዩ በኋላ እስልምና በተስፋፋበት ዘመን ደግሞ ሁለተኛው ኡመር በሚባለው ከሊፍ ተጀምሮ በ705 ዓም የተሰራው አል አቅሳ የተባለው መስጊድና the Dome of the Rock የሚባለው ህንጻ ስላሉባት ኢየሩሳሌም የእስልምና እምነት ሶስተኛዋ ቅድስት ቦታ ናት የሚለው ስያሜ ባለፉት ምዕተ ዓመታት ታዋቂነትን አግኝቶአል። ስለዚህም የዘመኑ ታላቅ አገር አሜሪካም ብትሆን ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በማለት ከመቀበል እስካሁን ታቅባ ከቆየች በኋላ የእስራኤል ጦር ወደ ከተማይቱ በገባ በ50ኛው ዓመት ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በማለት አሜሪካ ማወጇ አጋጣሚ አይደለም። 50 ዓመት አንድ ኢዮቤልዩ ነው። ከ1917 እስከ 1967 አንድ ኢዮቤልዩ ሲሆን ከ1967 እስከ 2017 ደግሞ ሁለተኛ ኢዮቤልዩ ነው። እስራኤል እንደገና አገር ሆና ከተመሰረተችም በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ላይ 70 (ሰባ) ዓመት ይሆናል። የሰው እድሜ ሰባ ወይም ሰማንያ ከዚያም ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው ተብሎ ተጽፎአል። (መዝሙር 90፡10) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራንና የፍጻሜው ተከታታይ አጥኝዎች ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" ማቴ 24፡34 በማለት የተናገረው በ1948 እስራኤል እንደገና ስትመሰረት የተወለደው ወይም የነበረው ትውልድ የዘመኑን መጨረሻ፣ ምናልባትም የሃሰተኛውን ክርስቶስ መገለጥ ወይም የጌታን ዳግም ምጽዓት ያያል ለማለት ሊሆን ይችላል ብለው ያስተምራሉ። ጌታ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር ማንም እንደማያውቅ ተጽፎአል። ነገር ግን ያለንበት ዘመን ወደ ጌታ መምጣት ከመቼውም የበለጠ እጅግ የቀረብንበት ጊዜ ነው። በመጀመሪያው ላይ እንደተጠቀሰው፣ ጌታ አምላክ በነቢዩ ዘካርያስ በኩል ሲናገር በመጨረሻው ዘመን የምድር አህዛብና መንግቶቻቸው በኢየሩሳሌም ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እንደሚሞክሩ ቢሆንም እንደሚጎዱ አስጠንቅቆአል። ይህ የሆነበት ምክንያትም ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር የራሱ ከተማ ስለሆነች ነው። ጌታ አምላክ የማደሪያስ መቅደሱን በህዝቡ በእስራኤል መካከል በማድረግ የተገኘባት፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ወደ ዓለም መጥቶ የተሰቀለባት፣ የሞተባትና የተነሳባት ከተማ በዘመኑም መጨረሻ የእግዚአብሔር መንግስት ራስ የሆነው ንጉሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግስባት ዋናዋ ከተማ ስለሆነች ነው። አህዛብ ቢነሱም፣ መንግስታት ቢቃወሙም፣ ሰይጣን አህዛብን ሁሉ በዚህች ከተማ ምክንያት ለማፋጀት ቢነሳሳም የእግዚአብሔር ሃሳብ ግን በሰዓቱ ይፈጸማል። ከዚያ በፊት ግን ለ7 ዓመት የሚገዛው ሃሰተኛው ክርስቶስ ይገለጣል። ለመጀመሪያዎቹ ሶስት ተኩል ዓመታት የውሸት ሰላም በማድረግና በማታለል ይገዛል፣ በዚህችው ኢየሩሳሌም አይሁድ እንደገና በሚሰሩት ቤተ መቅደስ እንደ ጥንቱ መስዋእት ማቅረብ ይጀምራሉ። በሰባቱ ዓመት እኩሌታ ላይ ግን ሃሰተኛው የመስዋእት ስርዓቱን ያቆምና የራሱን ምስል በቤተ መቅደሱ በመትከል አይሁድም ሆነ አህዛብ እንዲያመልኩት ግድ ይላቸዋል። ዳንኤል 9፡27 ዳንኤል 12፡7-12 ። ያ ጊዜ ታላቁ የመከራ ሰዓት ወይም በነቢዩ በኤርምያስ የያእቆብ የመከራ ዘመን የተባለው ይሆናል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በምን ቅደም ተከተል ወይም መቼ እንደሚፈጸሙ ባናውቅም በዜና ላይ ዛሬ የሰማነው ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንዋን አሜሪካ መቀበሏና ከካቶሊኩ ዋና መሪ ጀምሮ ብዙ አገሮች ይህን መቃወማቸው አጋጣሚ አይደለም። የእስራኤል ጦርም በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ የሚያመለክተው የጦርነት መነሳት አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ይህን ሁሉ በዙፋኑ ሆኖ የሚያከናውነው አምላክ ጌታ እግዚአብሔር የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሁሉ አንድም ሳይቀር ይፈጸማል፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ይመጣል፣ ይህ ዓለምና የመንግስታት ስልጣን ሁሉ የክርስቶስ ይሆናል። በዚያም ዘለዓለማዊ መንግስት ስፍራ ያላቸው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዳኑ ብቻ ናቸው። እውነትም መንገድም ሕይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የመለከት ድምጽ ብሎግ የአማርኛን ቋንቋ በተቀዳሚነት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ለማድረስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ያገለግላል።
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...
-
የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5 ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ...
-
የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ትምሕርት 6 ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ...
-
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018 አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ