የሚማሩበትን የኮሌጅ ክፍያና እዳዎቻቸውን ለመሸፈን የአሜሪካና የሌሎቹም ባለጸጎች
አገሮች ወጣቶች ሥጋቸውንና ደማቸውን ሳይቀር ለገንዘብ እየሸጡ ናቸው http://www.zerohedge.com/news/2017-12-10/plasma-pay-broke-millennials-sell-blood-just-survive
አዳጊና ድሆች ከሚባሉት አገሮች የሆንን ብዙዎቻችን ሃብታምና ባለጸጋ በሚባሉት በሰሜን
አሜሪካ፣ በምእራብ አውሮፓና በሌሎቹም አዲስ ባለጸጋ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የኢኮኖሚ ወይም የገንዘብ ችግር አለባቸው ብለን አንገምትም።
በነዚህ አገሮች የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን፣ የፊልሙ እና የሙዚቃው ኢንዱስትሪም ቢሆን ለሌላው ዓለም የሚያሳዩት በነዚህ አገሮች ያለው
ሰው ሁሉ የሞላለት፣ የተረፈውና የተሳካለት እንደሆነ ነው። ለብዙዎች የአሜሪካና የሌሎችም ባለጸጎች አገሮች ወጣቶች ግን እውነቱ
ግን ከዚህ እጅግ የራቀ ነው። ከዚህ መልእክት ጋር በተያያዘው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተውና በሌሎችም ብዙ እውነተኛ ዜናዎችን በሚያሰራጩ
ማእከላት እንደሚዘገበው ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአሜሪካና እንደ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓንና ካናዳ ያሉ “ባለጸጋ” የሚባሉ አገሮች
ወጣቶች ለኮሌጅና ለዩኒቨርሲቲ የሚያስፈልጓቸውን ክፍያዎች ለመክፈልና ሌሎች ወጭዎቻቸውንና እዳዎቻቸውን ለመሸፈን ሰውነታቸውን ለመሸጥ
በኢንተርኔት ላይ ራሳቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። ደናግል ሴቶች ልጆች ክብረ ንጽህናቸውን ለከፍተኛ ተጫራች እንደሚያቀርቡም በተደጋጋሚ
ይዘገባል። በአሜሪካ ብቻ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የተማሩና እየተማሩ ያሉ
ወጣት ሴቶች ራሳቸውን ለገበያ እንደሚያቀርቡ ይታመናል። ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መፈጠር ምክንያቱ በነዚህ ባለጸጎች አገሮች ባለፉት
አስር የሚሆኑ ዓመታት የተፈጠረው የኮኖሚ ቀውስ ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱ ሁሉ በጥቂት ሰዎች እጅ መግባቱ፣ ገደብየለሽ ራስ ወዳድነትና
ጭካኔ በህብረተሰብ መካከል መስፋፋቱ እንዲሁም ብዙው ሰው፣ ወጣቶችም ጭምር፣ አላስፈላጊ የሆነ የኑሮ እሽቅድምድምም ውስጥ መግባታቸው
ነው። የነዚህ ችግሮች ሁሉ ሥር መሰረቱ ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር መጥፋቱና ሰው ሁሉ የኑሮውን ግብ ቁሳቁስን መሰብሰብና ስጋውን
ብቻ ማስደሰት ማድረጉ ነው።
ኦክስፋም (OXFAM) የሚባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው የጥናት ዘገባ
ላይ እንደሚያሳየው በምድር ላይ ያሉ 62ቱ ከፍተኛ ባለጸጎች ሰዎች ያላቸው ሃብት 3.5 ቢሊዮን ከሚሆነው ግማሹ የምድር ህዝብ ንብረት እኩል ነው። ከ2010 እስከ 2015 ባሉት ስድስት
ዓመታት ውስጥ የነዚህ የ3.5 ቢሊዮን ሰዎች ንብረት በ41
ከመቶ ሲወድቅ፣ የ62ቱ ሰዎች ሃብት ደግሞ በ500 ቢሊዮን ዶላር በመጨመር ወደ 1.76 ትሪሊዮን ደርሶአል። ችግሩ ገንዘብ በተወሰኑ ሰዎች እጅ መሆኑ ብቻ አይደለም። ለሌሎች ስራ በሚፈጥሩ ነገሮች ላይ በመዋል ፈንታ
ጣራ ዘለል በሆኑና ሃብትን በማያፈሩ ከልክ ያለፈ የምቾትና የቅንጦት
ቁሳቁሶች ላይ ስለዋለ ለባለቤቶቹም ሆነ በሚሊዮን ለሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ፍሬን ሳያፈራ መቅረቱም ነው እንጂ። ታዲያ እነዚያ ጥቂት
ባለጸጎች ሰዎችም ቢሆን እኮ፣ የእውነተኛ ባለጸግነት ምስጢር
ቢገባቸው ኖሮ፣ በገንዘባቸው ደስ ብሎአቸውና በህዝብም መካከል በሰላም ሊኖሩ የሚችሉት የሃብታቸውን ጉልበት የሌሎችን ሸክም ለመቀነስ
ሲያውሉት፣ ለሌሎች በሮችን ሲከፍቱበትናና በድሆች ላይ እጅግ የከበደውን የድህነት ቀንበር ሲያቀልሉበት ነበር። አለበለዚያ ግን የነገው
ዓለም ተረካቢና መሪ የሆኑት ወጣቶች የሚማሩበትን የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ እዳ ለመክፈልና ለእለት ከእለት ኑሮአቸው ስጋቸውንና ደማቸውን
በገንዘብ ለመሸጥ ከተገደዱ የነገው ዓለም ምን ዓይነት ይሆን ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈው በሁለተኛው መልእክቱ በምእራፍ 3 ላይ
የመጨረሻውን ዘመን (ይህን የእኛን ዘመን) አስቸጋሪና አስጨናቂ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ገንዘብ ወዳድነት፣ ከልክ ያለፈ ራስ
ወዳድነትና የገንዘብ ፍቅር እንደሆነ እንዲህ ሲል ያስረዳል። “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።
ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትእቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመስግኑ፣
ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣
ችሉሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤”
ነቢዩ ኢሳይያስ “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች
የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም፥ አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።” ይላል። ኢሳ
52፡7 በዓለማችን ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ግን እውነቱን ክደን ሁሉ መልካም ነው ካላልን በስተቀር እውነተኛና መልካም የሆኑ
ብዙ ዜናዎችን ማግኘት እጅግ ያዳግታል። አይናችንን ወደ እግዚአብሔር ስናነሳ ግን የወንጌል የምስራች ዛሬም ለሰው ሁሉ ያበራል።
የዚህ ዓለም ሁኔታ እየከፋ ቢሄድም ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የተላከውን የወንጌልን የምስራች በመቀበልና በማመን የዘለዓለምን
ህይወትና የማያልፍን ተስፋ ማግኘት ይችላል። ዓለማችን ያለችበት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ዋና ስር መሰረቱ እኛ የሰው
ልጆች ከእውነተኛው አምላክ መራቃቸን ነው። “ኑ ወደ እግዚአብሔር
እንመለስ” ትንቢተ ሆሴዕ ምዕ 6 ቁጥር 1
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ