እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ ኤፌሶን 5፡1

እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ  ኤፌሶን 5፡1
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ (አፕሪል 25፣ 2018)
“መወለድ ቋንቋ ነው” የሚለውን አባባል ዛሬ ምን ያህል እንደምናውቀው ወይም እንደምንጠቀምበት አላውቅም። አንዳንዶቻችን ድሮ ብለን በምንጠራው ዘመን ግን አባባሉ ጥልቅና ጠንካራ መልእክቶች ነበሩት። ለምሳሌ ያህል በዚያ በድሮው ዘመን አንድ ሰው ማንነቱን ለሌሎች ለመግለጽና ለማሳየት፣ ተቀባይነትን፣ ወይም ክብርን ለማግኘት ከሚያቀርባቸው መረጃዎች መካከል አንዱና ዋነኛው “የእገሌና የእገሌ ልጅ ነኝ” ማለት ነበር። ያ ሰው የጠቀሳቸውን እገሌና እገሌን የሚያውቁ፣ ነገር ግን በጠቃሹ ባህርይ ላይ ጥርጣሬ ወይም ጥያቄ ያላቸው ሰዎች ታዲያ “መወለድ ቋንቋ ነው” በማለት ያ ሰው መልካም ስም ያለው ቤተሰብ ተወላጅ ቢሆንም  የእርሱ ባህርይ ግን ከወላጆቹ ወይም ከቤተሰቦቹ ማንነት ጋር እኩል ቦታ ወይም ክብር ሊሰጠው የሚችል አለመሆኑን ያመለክቱ ነበር። የማንነትና የመልካም ባህርይ መረጃ ከሚያስፈልጉባቸው ነገሮች አንዱ ጋብቻ ነበር። በዚያን ዘመን አንድ ወጣት አንዲትን ኮረዳ ለማግባት ለማጨት ሽማግሌዎች ወደ ልጅቱ ቤተሰብ ከመላካቸው በፊት የእርሱ ቤተሰብ ልጅቷ የማን ልጅ ናት ብለው ይጠይቃሉ፣ ያጠያይቃሉ። ጉምጉምታውን የሰሙ የልጅቷ ቤተሰብም እንዲሁ ሊያጭ የሚፈልገው ሰው የማን ልጅ ነው ብለው በዘመድ አዝማድ፣ በቅርብ ባልንጀሮችና በዘመድ አዝማድ ያጠያይቃሉ። የጨዋ ቤተሰብ ልጅ ናት፣ የጥሩ ቤተሰብ ልጅ ነው የተባለ እንደሆነ ወደ መተጫጨትና ወደ ጋብቻ ከሚያመራው መንገድ ላይ አንድ እንቅፋት ተነሳ ማለት ነው። ይህ ብቻ ግን በቂ አልነበረም። የልጁና የልጅቷ ማንነት፣ በተለይም ደግሞ እንደ ታማኝነት፣ ታታሪነት፣ ትጉነትና ተግባቢነት ያሉ ባህርዮቻቸው፣ ሙያ እናና ኃላፊነትን የመሸከም ችሎታም በሁለቱ ቤተሰቦችና በሽማግሌዎች እንዲሁም በዘመድ አዝማድና በቅርብ ባልንጀሮች ይመዘኑ ነበር። የዘላቂ ትዳርን መሰረት ጠንካራ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የሁለቱ ተጋቢዎች ማንነት ማእከላዊ ስፍራን የሚይዙ ናቸው። የተጋቢዎቹን ማንነት ከሚቀርጹት ነገሮች መካከል ደግሞ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰቦች ማንነት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይታመን ነበር። ሌላው የሰርግ ዝግጅትና ሂደት፣ ጥሎሹ፣ ድግሱ፣ ስጦታው፣ የደስታ መግለጫው ወዘተ የጋብቻውን መመስረት የሚያሳምሩና የሚደግፉ ቢሆኑም  መሰረታዊ ናቸው ለማለት አይቻልም። የዚህ አጭር መልእክት ትኩረት የአማርኛ አባባሎችን ለማስተዋወቅ ወይም የጥንቱን ባህላዊ የመተጫጨትና የጋብቻ ስርዓት ዘወር ብሎ ለማየትና ለመገምገም ሳይሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመንን ክርስቲያኖች ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትና ከክርስቶስ ጋር በክብር ለመኖር መዋጀታችንን በተመለከተ ከላይ የተገለጸውን አባባል ተመርኩዞ አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን ለማመላከት ነው።
በመንፈሳዊ ሕይወት እያደግን ስንሄድ የደስታችን ምንጭ ምን መሆኑን እንገነዘባለን። መሰረታዊ እውነቶችን በአግባቡ እየተረዳን ስንመጣ ሙሉ በሙሉ ልንገልጸው የማንችለውን የዘለዓለም ሕይወት፣ ደስታና ሰላም የሰጠንን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንናፍቃለን። ከነዚህ መሰረታዊ እውነቶች መካከል አንዱ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኙ ሁሉ የክርስቶስ አካል የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ብልቶች መሆናቸው ነው። አዲስ ኪዳን ስለዚህ ሲናገር፤ “እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ” ይላል (1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12:27) ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆና እንድትገኝ ለክርስቶስ ታጭታለች። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እንደዚህ ይገልጸዋል፤ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፣ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፣” 2ኛ ቆሮ 11፡2 ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በላከው መልእክት ደግሞ፡ “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት፣ ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ይላል (ኤፌሶን 5፡27)።
ልዑል እግዚአብሔር በክቡር ልጁ ደም የዋጃት የቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቶስ አካል፣ ብልቶች ከሆንን እና ጌታ አምላክ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት፣ ንጽህት እና ነውር የሌለባት እንድትሆን ካዘዘ፤ እኛም እያንዳንዳችን በቃሉና በመንፈሱ በመታጠብ ልንቀደስና ለእርሱም ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ልንሰራ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ሰው በሰራው መቅደስ አይኖርም። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ጌታ እግዚአብሔር ማደሪያውን ሊያደርግ የፈለገው በህዝቡ መካከል ነው። በብሉይ ኪዳን የምናያቸው በምድረ በዳ የነበረው የመገናኛው ድንኳንም ሆነ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ አገልግሎት ጌታ አምላክንና ሕዝቡን የማገናኛ ስፍራ መሆን ብቻ ነበር። ለዚህም ነው የቃል ኪዳኑ ታቦት የነበረበትን ያን ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የሚጠራው። የመገናኛው ድንኳን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ ማህበር በአምላካቸው ፊት የሚገኙበት ስፍራ ነበር። ቤተ መቅደሱን ቅዱስ የሚያደርገው ስፍራው በጌታ አምላክ መገኘት ስር መሆኑ ነበር። በቤተ መቅደስ ከመገኘት ባሻገር ደግሞ እያንዳንዱ እስራኤላዊና በመካከላቸውም የሚኖር መጻተኛ ሁሉ በልቡና በቤቱ እግዚአብሔርን ማምለክና ማክበር ነበረበት። ክግብጽ ባርነት ጌታ ነጻ ያወጣቸውና የራሳቸው የሆነ ምድር የሰጣቸው ምክንያት በነጻነት ከእርሱ ጋር እንዲኖሩበት ነበር። የበረከቱ ምንጭ የከነዓን ምድር በምድር ካሉ ሌሎች ስፍራዎች ሁሉ የተለየና ያማረ መሆኑ ሳይሆን፣ ጌታ አምላክ ራሱ የሚጎበኘው ምድር መሆኑ ነበር። ዛሬ በአዲስ ኪዳን ዘመን ያለን ክርስቲያኖችም እንዲሁ በገዛ ራሱ ደሙ የዋጀንን እና የዘለዓለምን ሕይወት የሰጠንን ጌታ የምናመልከው በቤተ ክርስቲያንና በህብረት ብቻ ሳይሆን በግላችን፣ በአእምሮአችን፣ በሰውነታችን፣ በስሜታችንና በማንነታችን ሁሉ ነው። ፈርጀ ብዙ በሆነው በግል ኑሮአችን እንዲሁም በቤተሰባችን እና በግንኙነቶቻችን ሁሉ መካከል እርሱን ማክበርና ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ መትጋት እንዳለብን እንዲህ ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል ያዝዘናልም፤
        “ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኩስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ
 አሁን አቅርቡ።” ሮሜ 6፡19
“እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፣እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፣ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲህ አድርጉ፣ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፣ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገስፁ፣ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፣ እግዚአብሔርን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።”  ቆላስይስ 3፡12-17
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ስንቀበል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእግዚአብሔር ዳግም ተወልደናል፣ ስለዚህ አዲስ ፍጥረቶች ነን። ኃጢዓት ካመጣብን የዘለዓለም ሞት ድነናል፣ ስለዚህም በክርስቶስ ጽድቅ ምክንያት ጻድቃን ሆነናል። በዓመጻችን ምክንያት ተጣልተነውና ተለይተነው ከነበረው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ደም ታርቀናል፣ ስለዚህም የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይገዛን ከነበረውና ዛሬም የማያምነውን ዓለም ከሚገዛው ከጨለማው ገዥ ከዲያብሎስ፣ ከጭፍሮቹና ከአጋንንት ስልጣን ነጻ ወጥተን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር መንግሥት ፈልሰናል፣ በጨለማው ገዥና  በሥርዓቱም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጥቶናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲገለጽ እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር እንድንገለጥና አብረነው በሕይወት እንድንነግስ ታጭተናል። እነዚህን እውነቶች ሁሉ እንዳንረሳ፣ እንዳንደክምና እንዳንታክት፣ ወደ እውነት ሁሉ እንዲመራንና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገልንን እና ያስተማረንን የሚያስታውሰንን መንፈስ ቅዱስን እንደ ርስታችን መያዣ ተቀብለናል (ዮሐ 1፡12-13 ዮሐንስ 3፡16-18 ሮሜ 5፡1-2 ሮሜ 6፡6 2ኛ ቆሮ 5፡17 ቆላስይስ 1፡13-14 ሉቃስ 10፡19-20) በዚህ ሁሉ እውነት ለተከበብን ክርስቲያኖች ነው ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ” የሚለን። ልጆች በብዙ መንገድ ወላጆቻቸውን እንደሚመስሉ ሁሉ እኛም በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዳግም የተወለድን ክርስቲያኖች ዳግም የወለደንን እግዚአብሔርን እንድንመስል ይጠበቅብናል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎአል፡
“እናንተ ስለነገርኋችሁ ቃል ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፣ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፣ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ....ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።” ዮሐንስ ወንጌል 15፡3-8
ስለ ወደደንና ስላዳነን የምንወደውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ክርስቲያኖች ሁሉ እንፈልጋለን። እንዴት ደስ እንደምናሰኘው ግን ብዙ ጥያቄዎችና ግራ መጋባት ሊኖርብን ይችላል።በእርግጥ ጌታ አምላካችንን ደስ የምናሰኝባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጡልን ብዙ መንገዶች ቢኖሩም እነዚያ ነገሮች ሁሉ በሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎች ተጠቃልለዋል። እነዚያ ሁለት ምሰሶዎች ደግሞ በብሉይ ኪዳን በሙሴ በኩል ተገልጠው በአዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው ናቸው፤ 1ኛ) እግዚአብሔርን አምላካችንን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹምም ነፍሳችን፣ በፍጹምም ኃይላችን መውደድ (ዘዳግም 6፡4-9) እና 2ኛ) ባልንጀራችንን (ሌላውን ሰው ሁሉ) እንደ ራሳችን መውደድ (ዘሌዋውያን 19፡18) ናቸው (ማቴዎስ 22፡37) ።
የዚህ የዛሬው መልእክት ትኩረት የመጀመሪያው ትዕዛዝ ነው። እግዚአብሔር አምላካችንን በእርግጥ የምንወደው ከሆነ በማንኛውም ስፍራ፣ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ እንከተለዋለን፣ እንታዘዘዋለን፣ ደስ የሚያሰኘውንም ለማወቅና ለማድረግ እንተጋለን። ጌታን የምንከተለው ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ፣ ከክርስቲያኖች ጋር ህብረት ስናደርግ፣ ለሌሎች ሰዎች ስንመሰክር፣ ስንሰብክና ስናስተምር ብቻ ሳይሆን ለብቻችንም ስንሆን፣ በቤታችን ውስጥ፣ በስራ ቦታችን፣ በመንገድ ላይ፣ በሰዎች መካከል፣ በሃሳቦቻችንና በምርጫዎቻችን ሁሉ ውስጥ ሊሆን ይገባል። እንደ ፍቅር ጠንካራ ነገር የለም። እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእኛ የገለጠው ፍቅር ደግሞ የፍቅሮች ሁሉ ቁንጮና መሰረት ነው። አንዳንዶቻችን “ታዲያ እንዴት ይሆን ለጌታ ያለኝን ፍቅር ልገልጽ የምችለው” ብለን ልናስብ እንችላለን። እንድንከተለውና ደቀ መዛሙርቱ እንድንሆን የጠራን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደምንከተለውም በግልጽ አስተምሮአል። ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርትም ከጌታ የተማሩትን መሰረት በማድረግ ስለዚሁ በብዙ መንገድ አስተምረውናል።
በቆላስይስ መልእክት ላይ ከተጻፈውና ከላይ ከተጠቀሰው ክፍል እንደምንመለከተው ለእግዚአብሔር የሚታዘዙና እርሱን ደስ በሚያሰኝ ሕይወት ለመኖር የሚሹ ሁሉ ሊከታተሏቸው፣ ሊያደርጓቸውና ሊሆኗቸው ከሚገቡት ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ለናሙና ያህል  እንመልከት፡
1)    ልንቀደስና በቅድስና ልንኖር ያስፈልጋል። መቀደስ ማለት በአንድ በኩል በዓለም ካለውና ለእግዚአብሔር ተገቢውን ቦታ ከማይሰጥ ከንቱና የኃጢአት የኑሮ ዘይቤ መለየትና መሸሽ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አምላካችንን ለማወቅ፣ ሃሳቡን ለመረዳትና ለመታዘዝ እንድንችል ወደ እርሱ መቅረብ ማለት ነው። ተቀደሱ ብሎ ያዘዘን አምላክ የሚቀድሰንም እርሱ ራሱ መሆኑን አስተምሮናል። “ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፣ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።” 1ኛ ጴጥሮስ 1፡15-17 “እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ነኝ” ዘሌዋውያን 20፡8
2)   አንዱ ክርስቲያን ከሌላው ክርስቲያን ጋርም ሆነ ገና ጌታን ካላወቁ ሰዎች ጋር በሚኖሩት ግንኙነቶች ሁሉ በተቻለው መጠን በምሕረት፣ በርኅራኄ፣ በቸርነት፣ በትሕትና፣ በየዋህነትና፣ በትዕግሥት ሊኖር ያስፈልጋል። አለመግባባትን የሚፈጥሩ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ በእኛ በኩል በተቻለን ሁሉ መጣር፣ ከተፈጠሩ ደግሞ የምንሰጠው ምላሽ፣ አስተያየትም ሆነ ነቀፌታ፣ የማንስማማውንም ሰው ቢሆን በክርስቲያንነቱ ወይም በሰውነቱ የሚያክብር፣ በጸጋና በትህትና የተሞላ መሆን አለበት። እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፡
“የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፣ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱ ኃጢዓት አላደረገም፥ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” 1ኛ ጴጥሮስ 2፡21-23
3)   እግዚአብሔር አምላካችንን በትክክል ልናውቀው የምንችለው ቃሉን ስናነብ፣ ስናጠና፣ ስናሰላስል፣ ስንረዳውና ስንታዘዘው ነው። ጌታ መንፈስ ቅዱስም በግልና በህብረት በሕይወታችን በሙላት ሊሰራና በሰማያዊ ነገሮች ሁሉ ፍሬያማ ሊያደርገን የሚችለው የእግዚአብሔርን ቃል በየጊዜውና በሰፊው ስንመገብ ነው። ስለዚህ በግላችን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት ያስፈልገናል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በሕብረት የሚደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ትምህርቶች ወይም ስብከቶች አስፈላጊ ቢሆኑም ለብቻቸው ግን በቂ አይደሉም። በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንደሚገባን ለማደግና ፍሬያማ ክርስቲያን ለመኖን ከፈለግን በቂ ጊዜ ሰጥተን ቃሉን ማንበብና ማጥናት የግድ አስፈላጊ ነው። ቪዲዮ ማየት፣ በኢንተርኔት የሚቀርቡ መልእክቶችን መስማትና በሌሎች ክርስቲያኖች የተጻፉ መጻህፍትን ማንበብ ሁሉ ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ግን እኛ ራሳችን በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንን እና ማጥናታችንን ሊተኩ አይገባም። ንጉስ ዳዊት “አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።” ይላል (መዝሙር 118፤11 ) ጌታ ኢየሱስ ራሱ ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል ላይ እንዲህ ሲል ለአይሁድ መሪዎች ተናገረ፡ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።” ማቴዎስ 22፡29
4)   በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን የእግዚአብሔር ሰላም በልባችን ውስጥ እንዲገዛ ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ አመራር ዝግጁ ማድረግና እርሱን ማዳመጥ ያስፈልጋል። ይህን ልናደርግ የምንችለው ከአምላካችን ጋር የምንሆንበትን ጊዜ ወስነን ስናመሰግን፣ ስናመልክና ስንጸልይ ለሌሎችም ስናማልድ ነው። ጌታ አምላክ ከልጆቹ ጋር መነጋገር ይናፍቃል። በክርስቶስ በማመን ዳግም የተወለደ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ የመጸለይ፣ በነጻነት የማምለክና እርሱን የማክበር መብትና ልዩ እድል አለው። አምላካችን ልደን ስንፈልገው፣ ወደ እርሱም ቀርበን በምስጋና በተሞላ ልብ ደስታችንንም ሆነ ሸክማችንን በጸሎትና በዝማሬ በፊቱ ስናቀርብ ደስ ይለዋል። እንዴት ማምለክና መጸለይ እንደምንችል ባይገባን እንኳን ፈቃዳችንን ለእርሱ ካስገዛን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ይረዳናል በእኛም ውስጥ ሆኖ ይቃትትልናል፣ ለሌሎችም ይማልዳል። “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፣ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።” ሮሜ 8፡26-27
ዓይን ያላየውንና ጆሮ ያልሰማውን ወደ ሰውም ሃሳብ ሊገባ የማይችለውን ድንቅ የሆነ የዘለዓለም ክብር አዘጋጅቶ በገዛ ራሱ ፈቃድና ጽድቅ በክርስቶስ ዳግም የወለደንን አምላካችንን ለመምሰል መናፈቅ በእውነት ዳግም የተወለደ ክርስቲያን ሁሉ ባህርይ ነውና ቃሉ እንደሚያዝዘን እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን እንምሰል፣ እርሱን እንከተል።

ሥልጣኔ፣ ቴክኖሎጂና የክርስቶስ ወንጌል


ሥልጣኔ፣ ቴክኖሎጂና የክርስቶስ ወንጌል
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
አፕሪል 20፣ 2018

ከጥቂት ቀናት በፊት በምድር ላይ አንዣቦ ስላለው ከፍተኛ የኑክሊየር ጦርነት አደጋ ከአንድ ሰው ጋር ስንነጋገር፣ ያ ሰው “አሁን ያለነው በሰለጠነ ዘመን ነው፣ በዚህ ዘመን አገሮች ችግሮቻቸውን በመወያየት ይፈታሉ እንጂ እንዴት ይዋጋሉ? በተለይም ደግሞ የሰለጠኑትና ኃያላኑ አገሮች እንዴት እርስ በርሳቸው ሊዋጉ ይችላሉ?” አለ። ይህ እውነት ይሆን? መልሱን ለአንባቢዎች እተዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህ እውነት እንደሆነ አይናገርም። እኔም ከቅዱሱ መጽሐፍ ጋር መስማማትን እመርጣለሁ። እናንተስ?!
ይህ ያለንበት ዘመን የሰለጠነ፣ ካለፈው ዘመን፣ አባት እናቶቻችን ከኖሩበት የተሻለ ነው ብለን እናምናለን። ለዚህም ከምንሰጠው ማስረጃ አብዛኛዎቹ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ማደግ ጋር የተያያዙ ናቸው። በአውሮፕላን ከአንድ አገር ወደ ሌላ መሄድ መቻላችን፣ በእጅ በሚያዙ ብልጥ ስልኮች (smart phones) ለመነጋገርና ለመጻጻፍ መቻላችን፣ ኢንተርኔት በሚባለው የመገናኛ መረብ ከቤት፣ ከመንገድ ላይ፣ ከመኪና ውስጥና ካለንበት ስፍራ ሁሉ ከሌሎች ጋር መገናኘት መቻላችን፣ ለአንዳንድ የጤና ችግሮች መድኃኒት ማግኘታችን ወዘተ ለምሳሌ ያህል ይጠቀሳሉ። ነገር ግን፣ እኛም ሆንን የዘመኑ አዋቂዎች፣ ፈላስፎች፣ ባለስልጣኖችና ባለ ሃብቶች እንዲሁም “ኮከብ” ነን የሚሉት ዘፋኞች፣ ተዋናዮችና ታዋቂ ሰዎች ልንመልሳቸው ከማንችል ከብዙ ጥያቄዎች፣ ልንፈታቸው ካቃተን ብዙ ችግሮች ጋር እንኖራለን። በቀደሙት ብዙ ዘመናት የኖሩ ህዝቦችም እንዲሁ እንደ እኛ የነሱ ዘመን ከነሱ በፊት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ ያስቡና ይናገሩ ነበር። ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት የነበሩ የግሪክ፣ የሮም፣ የባቢሎን፣ የፋርስ፣ የግብጽ ወዘተ ሰዎች ለምሳሌ የእነርሱ ስልጣኔ ከነሱ ከቀደሙት የተሻለ እንደሆነና ስለ ሕይወት ምስጢር እናውቃለን ብለው ያምኑ ነበር። በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ግሪኮች ለምሳሌ የግሪክ እውቀትና ፍልስፍና ከሌላው ዘመንና በዚያን ዘመን ከነበሩት ሌሎች አገሮች እውቀት ሁሉ የተሻለ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ስለዚህም ነው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ሲሰብክላቸው “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል” (የሐዋርያት ሥራ 17፤18) በማለት ያሾፉበት።
የሰው ልጅ ሁሉ በየዘመኑ ራሱን ያታልላል። ዛሬ ከትናንት ይሻላል፣ ነገ ደግሞ ከዛሬ ወደተሻለ ደረጃ እንደርሳለን ብሎ ያስባል፣ ይሰብካል ይህንንም እውነት ለማድረግ ይሰራል፣ የማይስማሙትን ይሰድባል፣ ያስራል፣ ይገድላል። ይህ እውን መሆኑን ግን ታሪክ አያረጋግጥም። እንዲያማ ባይሆን ኖሮ ከቀደሙት ሁሉ የሰለጠነ ነው በተባለለት በሃያኛው ክፍለ ዘመን በጦርነት ያለቀው ህዝብ ለምን ከዚያ በፊት በነበሩ ምዕተ ዓመታት ካከቀው ህዝብ በለጠ? ለምንድ ነው ከዓመት ወደ ዓመት የሚሰሩት የሰውን ልጅ መፍጃ የጦር መሳሪያዎች ከቀደሙት እየባሱ የሚሄዱት? በእርግጥ የእኛ ዘመን ከቀደሙቱ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የላቀ ከሆነ ለምንድ ነው እንደ ስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ ካንሰር፣ የእብጠት በሽታዎች (inflamattory diseases)፣ የአእምሮ በሽታዎች ወዘተ ከበፊቱ የበለጠ እየበዙ ያሉትና መድኃኒት ያጡት? አሉ የሚባሉት መድኃኒቶች ሁሉ ማስታገሻና ማደንዘዣ እንጂ ፈጽሞ ህመሞቹን የማያስወግዱት ለምንድ ነው? ጠፉ የተባሉ በሽታዎች እንደገና እየተመለሱ ያሉት ለምንድ ነው። አዳዲስ በሽታ የሚያመጡ ህዋሳት (ጀርሞች) እየበዙ ያሉትና ቀድሞ ሲያጠፉአቸው የነበሩ መድኃኒቶች ዛሬ የማይሰሩት ለምንድ ነው። በየጊዜው እየመጡ ያሉ ብዙ ህዝብ የሚጨርሱ እንደ ዚካ ቫይረስ፣ ኢቦላና አዳዲስ የእንፍሉዌንዛ ቫይረሶችን ማስወገድ ለምን  አልቻልንም?
እኛ የዛሬዎቹ ሰዎች ከትናንቶቹ የሰለጠንን እና ከቀደሙት የምንሻል ከሆነ ለምንድ ነው ሃብትና ገንዘብ እጅግ ጥቂት በሆኑ ሰዎች እጅ ተከማችቶ፣ ባለጸጎቹ በጥጋብ የሚሆኑት ጠፍቷቸው ያዙን ልቀቁን ሲሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና ማደሪያ በማጣት የሚጠበሱት? ስለ ሰለጠንን ከትናንቶቹ ኋላ ቀር ሰዎች የተሻልን ከሆን ለምንድ ነው በባለጸጎቹ አገሮቹ ብዙዎቹ ትዳሮች ፈራርሰው ልጆች ወላጅ አልባ የሆኑት? ስልጣኔያችን መከናወንን እና እርካታን ካመጣልን ለምንድ ነው እጅግ ብዙ ሰው በአልኮልና በአደገኛ እጾች ሱስ ተይዞ የሚሰቃየው። የዛሬዎቹ መንግስታት ከቀደሙት ለህዝብ አሳቢና ለህዝብ ተጠሪ ናቸው ከተባለ ለምንድ ነው እግዚአብሔር ኃጢዓት ነው ያለውን እነርሱ ትክክል፣ ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑን ጨለማ በማለት ህዝብ የማይፈልገውን የስህተት የኑሮ ዘይቤ ሁሉ ህግ እያደረጉ በህዝብ ላይ ለመጫን የሚሞክሩት?  አዎ ቴክኖሎጂና እውቀት በዝቷል።  መረጃ በየቦታው ይገኛል። ሊጠቀሙበት የሚችሉት ግን የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ ነገሮች የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች እንጂ የሰው ልጅ ወደ ተሻለ ዘመን የመሸጋገሩ ምልክቶች አይደሉም።በግልም ሆነ በቤተሰብ፣ በአገርም ሆነ በመንግስታት ዘንድ በፍጹም እውነት እንነጋገር ካልን እውነተኛ እድገት፣ ስልጣኔ፣ የልብ ሰላም፣ የውስጥ ደስታ፣ እረፍት፣ እርካታና ከማንኛውም ፍርሃት፣ በተለይ ደግሞ ከሞት ፍርሃት እንዲሁም ከጥላቻ ነጻ የሆነ ህይወት በውስጣችን ያለን ስንቶቻችን ነን። የትኛው አገርና ህዝብ ነው በስልጣኔውና በቴክኖሎጂው እኩልነትን ፍትህን እና እውነተኛ ማህበረሰባዊ ሰላምን ለህዝቡ ያሰፈነው። ልብ እንበል ታላላቆቹና ባለጸጎቹ አገሮች ናቸው እኮ በታሪክ ሁሉ ጦርነት ሲያስነሱ፣ ህዝብን ሲፈጁና ታናናሾችን ሲጨፈልቁ የኖሩት። ዛሬም ያው ነው። በግል ህይወታችንስ ቢሆን?  አንተ፣ አንቺ፣ እርስዎ ስለ ሰለጠንኩኝ፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆንሁ ዛሬም ሆነ ነገ ወይም ለዘላለም፣ ምንም ይፈጠር ምን በፍጹም ረክቼ እኖራለሁ፣ ስሞት ምን እንደሚሆን አውቃለሁና አልፈራም፣ ተስፋ አለኝ ማለት ይችላሉ? ትችላለህ? ትችያለሽ?
ስለ ስልጣኔያችንና መራቀቃችን የምናስበውና የምናምነው እውነት ከሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ያለማወላዳት ለራሳችን ልንመልሳቸው የሚገባ ጥያቄዎች ናቸው። ለህዝብ፣ ለባልንጀራ፣ ለባል፣ለሚስት፣ ለአለቃ፣ ለበታች፣ ለጎረቤት፣ ለሃኪም፣ ለልጅ፣ ለፍቅረኛ መዋሸት እንችላለን። በቴሌቪዥን፣ በፊልም፣ በመጻህፍት ብዙ መናገር ይቻላል። ለራሳችን ግን፣ ለውስጣችን መዋሸት ከባድ ነው። ህሊናችን ይከሰናል። በየቁሳቁሱና በየግሳንግሱ ልንሸነግላትና ዝም ልናሰኛት ብንሞክርም ነፍሳችን በውስጣችን ትጮሃለች። ፍጹም ሰላም፣ ፍጹም እርካታ፣ ፍጹም እረፍትና ደስታ ልናገኝ የምንችለው ወደዚህ ዓለም ለምን እንደመጣን፣ እንዴትና በማን እንደተፈጠርን፣ ወደፊት ምን እንደምንሆን ስናውቅ ነው። እነዚህን ነገሮች ልናውቅና ልንረዳ የምንችለው ሁሉን ያደረገውን ልዑል እግዚአብሔርን ስናውቅ ብቻ ነው። እርሱን ማወቅ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ የምንችለው ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። እውነትና መንገድ ህይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የለም የሚሉትን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሰነፍ ናቸው ይላቸዋል። ምክንያቱም መጠየቅና ማወቅ የሚገባቸውን ለማወቅ ስላልፈለጉና ታካች ስለሆኑ ነው። እውነተኛ መርማሪ፣ ምሁር፣ ባለጸጋ፣ ኃያል ሰው መጀመሪያውንና መጨረሻውን ለማወቅ የሚተጋ፣ የሚመረምር ሰው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ለዚህ ነው፡
“ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሰራው መቅደስ አይኖርም፣ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳችን የራቀ አይደለም። የሐዋርያት ሥራ 17፡24-27
እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርነው እንደ እንስሳ ምግብ ልንበላ፣ መጠጥ ልንጠጣ፣ ፍትወተ ስጋ እንድንፈጽም፣ ስራ እንድንሰራ፣ ገንዘብ እንድንሰበስብ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስንራወጥ እንድንኖር ወይም ሌሎች ከነዚህ ጋር ተመሳሳይና ተያያዥ የሆኑ ስጋችንን እና አእምሮአችንን ለጊዜው ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን እንድናደርግ። ይህማ ቢሆን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ችሎታውና ገንዘቡ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ባለ ፍጹም ደስታ በሆኑ ነበር። ዛሬ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ ስር የሰደዱ በሽታዎች፣ ሽብርና ድንጋጤ ያለው ድሃ በሆኑና ያልተማሩ ህዝቦች በሚኖሩባቸው አገሮች ብቻ ሳይሆን እጅግ ሃብታም፣ የተማሩና ኃያላን በሚባሉ አገሮችም ጭምር ነው። ምክንያቱ ግልጽ ነው። የሰው ልጅ እውነተኛ ሰላምን፣ እረፍትን፣ እርካታንና መከናወንን የሚያገኘው በዚህ ምድር ላይ ባሉትና በሚያደርጋቸው ነገሮች ብቻ አይደለም። ምግብም፣ መጠጥም፣ በአገባቡና በስርዓቱ የሆነ ፍትወተ ስጋም፣ ገንዘብም፣ መዝናናትም የየራሳቸው ቦታ አላቸው። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢሟሉም የሰው ልጅ ሙሉ ህይወትን አያገኝም። እነዚህ የስጋዊ ማንነታችን ፍላጎቶች ናቸው። እኛ የሰው ልጆች ግን በጊዜና በቦታ በተወሰነ አካል ውስጥ የምንኖር በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ነፍስና መንፈስ ያለን ልዩና ክቡር ፍጥረት ነን። ቢገባንና ብንቀበለው የእግዚአብሔር ፍጥረት ብቻ ሳንሆን ልጆቹም ነን። ይህን ክቡር ምስጢር ስለ ናቅንና እምቢ ስላልን፣ የራሳችንን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ ስላመጽንና ከሚወደን አምላካችን ወደን ስለምንሸሽ በሞት ጥላ ውስጥ እንኖራለን። የተፈጠርነው ከልዑል አምላክ ጋር በክብር እንድንነግስ፣ እርሱን በመታዘዝ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድንኖር ነበር። አወይ አለማወቃችን! አወይ እምቢተኛነታችንና ድንቁርናችን! እጅግ ክቡር ሆነን ሳለ በሚጠፉና ጌዜያዊ ስሜቶቻቸው እንደሚነዱ እንስሶች ሆንን? ሳናውቀውም ጠፊ ፍላጎቶቻችንን በመከተል ወደ ዘላለም ሞትና ጨለማ እንሄዳለን።
ዛሬ ልጅም ሆን ወጣት፣ ጎልማሳም ሆን አዛውንት በዚህች ህይወት የምንኖረው ሰባ፣ ሰማንያ፣ ምናልባት እድለኞች ከሆን ዘጠና ዓመት ነው። ከዚያ የሚያልፉ እጅግ ጥቂት ናቸው። ከነዚህ ዓመታትም ውስጥ እንደፈለገን ሮጠን፣ ተጫውተን፣ የፈለግነውን እያደረግን መኖር የምንችልባቸው ጥቂት ዓመታት ናቸው። ልንሰማው አንፈልግም እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ሳንወድ በግድ ሞት የሚባለው ነገር ይመጣና ከዚህ ዓለም እንሄዳለን። ወዴት ይሆን የምንሄደው? ወደ መቃብር ነውና በዚያ ሁሉም ያከትማል ልንል እንችላለን። ስትሞት፣ ስትሞች፣ ሲሞቱ ሁሉም ነገር የሚያበቃ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ? ምን ማስረጃ አለሽ? ምን ማስረጃ አለዎት?  ምንስ ያህል እርግጠኛ ነህ? ነሽ? ነዎች? ምናልባት ተሳስተህ ወይም ሰዎች አሳስተውህ ከሆነስ ዘለዓለም የሚያህልን ነገር በግምት ልትገባበት እንዴት ትደፍራለህ? አንሳሳት! ሞት የዚህ ህይወት ምእራፍ አንድ መዝጊያ እንጂ የእኛነታችን ፍጻሜ አይደለም። ሥጋችን ቢሞትም ነፍሳችንና መንፈሳችን አይሞቱም። ሞት ሲመጣ የምንፈራው፣ የምንጨነቀውና የምናዝነው በዚህ ዓለም የደከምንበትን ሁሉ ጥለነው ስለምንሄድ ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላ የምንሄድበትን ስለማናውቅ ነው። ከሞት በኋላ ሃኪም፣ መድኃኒት፣ ገንዘብና ባንክ የለም። ከሞት በኋላ የፍትህ ጥያቄ፣ ሰብዓዊ መብት፣ መንግስት ወይም የሃይማኖት መሪ የለም። ከሞት በኋላ እኛ ዛሬ የምናውቀው ምግብ፣ መጠጥ፣ ፍትወተ ስጋ፣ ባልንጀራ፣ መዝናኛ፣ መጓጓዣ ወይም ቴክኖሎጂም የለም። ከሞት በኋላ እግዚአብሔርን አላምንም የሚል ምሁር፣ ፈላስፋ፣ ጀግና፣ ከሃዲ፣ ባለጠጋ፣ ባለስልጣን ወይም ተራ ሰው የለም። በዚህም ህይወት ሆነ ከሞት በኋላ በሰዎች መካከል ያለውና እውነተኛ ፋይዳ ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው፣ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር በታረቁትና የምስራቹን ወንጌል እምቢ ብለው በሚኖሩት መካከል ያለው ልዩነት ነው።
የመጨረሻው ዘመን ባህሪ ነውና ዛሬ በብዙዎች ዘንድ እምነት ተብሎ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ስም ሲሰበክ የምንሰማው የዚሁኑ የሚያልፈውን ዓለም ገንዘብ ስለማግኘት፣ ቁሳቁስ ስለመሰብሰብ፣ በጊዜያዊ ተድላ ራስን ስለ መኮርኮር፣ የስጋን ምኞት ስለማሟላት ነው። ይህ የሰማያዊውን የክርስቶስን ወንጌል ምስጢር አለማወቅ ነው። መልካምን ነገር መፈለግና ለማግኘት መጣር መልካም ነው። እግዚአብሔር በዚህ ምድርም ሆነ በዘለዓለም ደስ እንዲለን ይሻል። ነገር ግን አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በኃጢዓት ውስጥ የወደቅን ስለሆንን፣ ዓለምም በሙሉ በኃጢዓት ምክንያት የጠፋ ስለሆነ በምድራዊ ነገሮች የምናገኘው ደስታ፣ ሰላም፣ እርካታና መከናወን የተወሰነ፣ ኃላፊና ጠፊ ነው። በከበረውና በተዋረደው፣ በዘለዓለማዊውና በጊዜያዊው ነገር መካከል መለየት ጥበብ ብቻ ሳይሆን የሞትና የህይወት ጉዳይም ነው። ዛሬ እንደ በረከት የሚሰበከው ገንዘብ፣ ዝና፣ ውበት፣ ስልጣን፣ ደስታና መከናወን እግዚአብሔርን የማያውቁና የማያምኑ አህዛብም የሚፈልጉት፣ ብዙዎች ያገኙአቸውና ጥለዋቸውም የሄዱ ነገሮች ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ከእርሱ ጋር ወደማይጠፋው የዘለዓለም መንግስትና ክብር እንድንገባ፣ ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው። ስለዚህ እንደ ህጻናት በዚህ ምድር አሻንጉሊቶችና የመዝናኛ ኮልኮሌዎች ተታልለን የከበረው የዘለዓለም ሕይወትን የማግኘት እድል አይለፍብን። በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመናችን እና አምላካችንን ለማክበር ከሚያስችሉት እውቀቶች በተረፈ ዛሬ የያዝነው እውቀት ሁሉ መቃብርን አይሻገርም። ገንዘባችን፣ ስልጣናችን፣ ዝናችን፣ ጉልበታችን፣ የባልንጀሮቻችንም ብዛት ምናልባት አስከሬናችንን እስከ መቃብር ድረስ አጅበው ሊሄዱ ይችላሉ እንጂ ከእኛ ጋር የሞትን ወንዝ አይሻገሩም።
አንተስ ወንድሜ ከየትኛው ወገን ነህ? አንቺስ እህቴ? እርስዎስ? ራሳችንን ስናታልልና የማይሞላውን የዚህ ዓለም አቁማዳ ልንሞላ ስንባዝን የዘለዓለሙ እድል አይለፍብን። ነፍሳችን በውስጣችን ያለችበትን ሁኔታ ታውቃለች፣ አምላኳን ትናፍቃለች፣ ወደ እርሱ ለመድረስ ትጓጓለች። በመጀመሪያ የነፍሳችንን ጥያቄ እንመልስ። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ህይወት ተስፋችንን እንያዝ። ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ ይደርሳል። ባይደርስም፣ በዚህ ዓለም ያለው ኑሮአችን ባይሳካም፣ እንዳሰብነው ባይከናወንም የቀረው ጊዜ አጭር ነውና ያልፋል።  መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱም በኋላ ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ የብዙዎችን ኃጢዓት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢዓት ይታይላቸዋል።” ዕብራውያን 9፡27-28 ዛሬ ነገ ሳንል ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለን እንዳን። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። ነገ በዚህ ምድር ላይ የአንተ፣ የአንቺ፣ የእርስዎ፣ የእኔ ለመሆኑ ዋስትና የለም።

በሰለጠኑና ባለጸጎች አገሮችም ህዝብ በጩቤና በቆንጨራ ሲፋጅ!


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር የሚመለስበት ዘመን መቃረቡን ከሚያመለክቱን ነገሮች ውስጥ ዘመኑ የሚያስጨንቅ መሆኑ ነው። ከሚያስጨንቁት የዚህ የመጨረሻ ዘመን ባህርያት አንዱ የጦርነትና የጦርነት ወሬ መብዛት ነው። የሚያሳዝነው ግን ለመዋጋትና ለመገዳደል አንዱ በአንዱ ላይ እየተነሳ ያለው መንግስታት ብቻ አይደሉም። አድገዋል፣ በልጽገዋል፣ ተምረዋል፣ ሰልጥነዋል ተብለው በሚነገረላቸው እንደ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ካናዳም ሳይቀር ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ወንጀል በቁጥር እየበዛ መሆኑን ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ። የመገዳደል ችግሩ ጠብመንጃና ሽጉጥ ስለሆነ መንግስታት እነዚህን ለማገድና ለመቆጣጠር ብዙ እርምጃዎችን ወስደዋል፣ እየወሰዱም ነው። እነዚህን መሳሪያዎች በአብዛኛው ተቆጣጥረዋል ከሚባሉት አገሮች አንዷ እንግሊዝ ናት። በተያያዘውና በሌሎችም ተመሳሳይ ዜናዎች እንደምናነበው፣ ከዓለም የገንዘብ ማእከሎች በዋናነት በምትጠቀሰው በለንደን ከተማ ብዙ ሰው በጩቤ፣ በቢላዋና በቆንጨራ እየተገዳደለ ነው። በፈረንጆቹ ዓመት የመጨረሻ ሁለት ወራት ብቻ በእንግሊዝ አገር በቆንጨራ የተፈጸሙት ወንጀሎች 928 ሲሆን ከነዚህም መካከል 425 የተፈጸሙት በለንደን ነው። ይህ ሁኔታ ያስፈራቸው የለንደኑ ከተማ ከንቲባም በዚሁ በያዝነው የፈረንጆቹ ወር በከተማይቱ የሚደረገውን የቢላዋ ወይም ጩቤ ዝውውር ለመቆጣጠር አዲስ መመሪያ አውጥተዋል።
ስለ ክፉ ነገሮች ያለን ሃሳብ ብዙውን ጊዜ የሚወሰነው በሚደርሰን ዜና ነው። በባለጸጎቹ አገሮቹ ባሉ የዜና ምንጮች የሚያቀርቧቸው ብዙዎቹ ዜናዎች የእነርሱ አገሮች ሰላማዊ፣ የሰለጠኑ፣ ችግሮችን ሁሉ የሚፈቱት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንደሆነ ለማሳየት ይጥራሉ። በሌላ በኩል ግን ችግር፣ ወንጀልና ጦርነት የሚገኙት ደግሞ በአዳጊዎቹና ድሆቹ አገሮች እንደሆኑ ለማሳየት አይታክቱም። በዓለማችን ላይ ያሉትን ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል ስንመዝናቸው ግን፣ ባለጸግነት፣ ትምህርት ወይም ስልጣኔ የኃጢዓትን ኃይል ወይም የሰውን ክፋት አያስወግዱም። እንዲያውም ታሪክና ዛሬም በዓይናችን የምናየው መረጃ የሚያሳየን የሰው ልጅ በሰለጠነና በቴክኖሎጂ በተራቀቀ መጠን ስልጣኔውን የሚጠቀመው የከፉና ብዙ ህዝብን የሚጨርሱ መሳሪያዎችን ለመስራትና በስራ ላይ ለማዋል መሆኑን ነው። አንድ የአገራችን የወንጌል ሰባኪ ከብዙ ዓመታት በፊት ሲናገሩ፣ “የሰው ልጅ ሰለጠነ ከማለት ይልቅ ሰየጠነ ማለቱ ይቀላል” ብለው ነበር። በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት፣ ገንዘብን መውደድ እንዲሁም ክፋትና ጭካኔ በምድር ላይ እጅግ እየበዛ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል 2ኛ ጢሞቲዎስ ምእራፍ 3 የዚህን ዘመን ባህርይ በዝርዝር ይነግረናል። ፈሪሃ እግዚአብሔር በገንዘብ ስለተተካ፣ የሰው ልጅ ከአምላኩ ይልቅ ተድላንና ገንዘብን ስለወደደ ስግብግብነት ምድርን እንደ ሰደድ እሳት እያቃጠላት ነው። በህዝብ መካከል ጭካኔ፣ በመንግስታት መካከል ጦርነት የሚሆነው እነዚህ የተጠቀሱት አመጻዎች ፍሬ ሲያፈሩ ነው። የሰውን ዘር ከዚህ ሁሉ ጥፋት ሊያድነው የሚችለው የበለጠ ገንዘብ፣ ተጨማሪ ምርት ወይም ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የወንጌል የምስራች ተሰብኮአል። እውነተኛ ሰላም፣ እረፍትና ደስታ የሚገኘው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በፍቅር በመኖር እንጂ ሃብትን በማግበስበስ ሊረካ የማይችለውን የስጋንና የከንቱ አእምሮን ምኞች በመከተል አይደለም። ይህን የተረዳው ዳዊት በመዝሙረ ዳዊት በ2ኛው ምእራፍ ላይ የምድር ነገስታትና መሪዎች በእግዚአብሔር እውነትና ስርዓት ላይ በማመጽ እንደሚነሱና በራሳቸው መንገድ የሰውን ዘር እነርሱ ራሳቸው አይተውት ወደማያውቁት ምናባዊ የብልጽግና፣ የእኩልነትና የሰላም ዓለም ለመምራት እንደሚሞክሩ አመልክቷል። በእውነትም የዚህ ሰለጠነ የሚባለው ዓለም መሪዎች ዛሬ እውነተኛ ነጻነትን፣ ሰላምንና ብልጽግናን ለሰው ዘር ሊያግናጽፍ የሚችለውን ብቸኛውን የፈጣሪን የፍቅርና የእውነት ስርዓት ህጎች በማፈራረስና በመሻር ላይ ናቸው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስና መንግስቱን እስኪመሰርት ድረስ ይህ የምናየው ጥፋት እየቀጠለና እየባሰ ይሄዳል እንጂ አይቆምም። የሰው ዘር ዋናው ችግሩ ኃጢዓት ብቸኛ መፍትሔው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ለዚህ ነው ዳዊት በዚያው በ2ኛው ምእራፍ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ለምድር ነገስታትና መሪዎች ሁሉ የተናገረው፡
 “አሁንም እናንት ነገሥታት ልብ አድርጉ፣ እናንት የምድር ፈራጆችም ተገሰጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሳጹን ተቀበሉ፣ ጌታ እንዳይቆጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ። መዝሙር 2፡10-12
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል። ይህ እውነት ለግለሰቦችም፣ ለመንግስታትም፣ ለተማሩም ላልተማሩም፣ ለሰለጠኑም፣ ላልሰለጠኑም እውነት ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !


አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !
ውድ የፌስቡክ ባልንጀሮቼና ወገኖቼ፣ ከብዙዎቻችሁ ጋር በአካል ባንተዋወቅም፣ ባልንጀሮቼ ስለሆናችሁ በጣም ደስ ይለኛል። እናንተንም ባልንጀሮች አድርጎ ስለሰጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ሰው መሆን እጅግ አስደናቂ ነው። ምንም እንኳን የምንኖረው በተለያዩ አገሮች፣ ከተማዎች፣ ሰፈሮችና ሁኔታዎች ቢሆንም በዚህ የሩቅ መገናኛ መድረክ እንኳን ተዋውቀን ባልንጀሮች በማፍራታችን ደስ ይለናል። ባልንጀራ የሆንነው ታዲያ በአጋጣሚ አይደለም። እኛ በማናውቀው መንገድ እርስ በርስ እንድንፈላለግ፣ እንድንተዋወቅ የሚያደርግ፣ በሰማይና በምድር ሁሉን የሚገዛ ልዑል እግዚአብሔር ነው። እርሱ አጋጣሚ በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ ሁሉ እየሰራ እንድናውቀውና ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይሻል።
ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከባልንጀሮቻችን ጋር መጫወት ስንችል ደግሞ የምንካፈለው ነገር ሲኖረን ደስ ይለን ነበር። በዚህ በፌስቡክ ለባልንጀሮቼ ምን ላካፍላቸው ብዬ ሳስብ ለእኔ ደግሞ እጅግ ከፍተኛና አስቸኳይ ነው ብዬ የማስበው አንድ ነገር ነው። ዛሬ የምጽፍላችሁም ስለዚህ አንድ ጉዳይ ነው። ይህች የህይወት ዘመናችን ሳናስባት ቶሎ ታልፋለች። የብሉይ ኪዳኑ ጻድቅ ሰው ኢዮብ ስለ ሕይወቱ እንዲህ ብሎ ተናገረ: “ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይቸኩላል፣ ያለ ተስፋም ያልቃል” ኢዮብ 7:6።  የእናንተን ባላውቅም እኔ ግን እንደ ኢዮብ ዘመኔ እጅግ እየፈጠነ ሄዶ ማድረግ ያለብኝን ሳላደርግ እንዳያልፍብኝ አስባለሁ። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ከዚህ ምድር ስንሄድ የምኖርበት የዘላለም መኖሪያችን የት ይሆን። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህች አጭር የምድር ዘመናችን በኋላ ዘለዓለም እንዳለ ያረጋግጥልናል። ለዚህ ነው ስናስብና ስናቅድ ልክ ሺህ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ እንደሚኖር የምናስበውና የምንደክመው። የምንኖረው ሰባ፣ ሰማንያ ወይም ዘጠና ቢሆንም ፍላጎታችን፣ እቅዳችን፣ ጭንቀታችንና ጥረታችን ግን ዘላለም እንደሚኖር ሰው ነው። ምክንያቱም የተፈጠርነው ለዘለዓለም እንድንኖር ነው። ወደድንም ጠላንም፣ አመንንም አላመንንም ከሞት በኋላ የዘላለም ህይወት አለ። ጥያቄው ግን ያንን ዘላለም የምናሳልፈው የት ነው፣ እንዴት ነው የሚለው ነው። ሞት የመጣው በኋላ ሲሆን የሞት ምንጩም ኃጢዓት ነው። በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጅ ለኃጢዓት መድኃኒት የለውም። ኃያሉም፣ ደካማውም፣ ድሃውም ባለጠጋውም፣ የተማረውም ያልተማረውም፣ ሁሉ የኃጢዓት ባሪያና በሞት ፍርሃት ጥላ ስር የሚኖር ነው። በግል ህይወታችንም ሆነ በቤተሰብ፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በግለሰቦችም ሆነ በመንግስታት መካከል ላለው ችግርና ቀውስ ሁሉ ምንጩ ኃጢዓትና የኃጢዓት ፍሬዎች ናቸው።  ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ውስጥ የምናመልጥበት መንገድ አለ።
ይህ የምንኖርበት ጊዜ የመጨረሻው ዘመን ነው። የሰማይና የምድር ወይም የሰው ዘር መጨረሻ ሳይሆን የዘመን መጨረሻ ነው። ይህን የሚናገሩት እኔና የዚህ ዘመን አዋቂዎች ሳይሆኑ እግዚአብሔር አምላክ በእርግጥ የላካቸውና የቀባቸው መጽሐፍ ቅዱስንም ጽፈው ያቆዩልን ነቢያትና ሐዋርያት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።  ይህ ዘመን በአንድ በኩል የተመሰቃቀለ፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ሞትና ስቃይ የሞላበት ነው። ትምህርት፣ እውቀት፣ ስልጣኔ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ሃብት እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም ቢባልም የጦም አዳሪው፣ የህመምተኛው፣ የከፋው፣ የመረረው፣ የስደተኛው፣ ግራ የተጋባው፣ የቁስለኛው፣ ስራ ያጣውና፣ የከርታታውም ቁጥር እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም። እኛም እያንዳንዳችን ከነዚህ በአንዱ ወይም በሌላው ተጎድተን እናዝናለን፣ እንቆዝማለን፣ አንዳንዴም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።  በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እያለቀ ያለው ዘመን ወርቃማ ዘመንም ነው፣ ምክንያቱም እኛ ልንኖርበት የምንችል ሌላ ዘመን አልተሰጠንም። ከዚህ በላይ ግን ይህን ዘመን ወርቃማ የሚያደርገው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የምስራቹን ወንጌል ሰምተንና አምነን የዘለዓለምን  ሕይወት ተስፋ ልንወርስ የምንችልበት ዘመን መሆኑ ነው። ይህ የጸጋ ዘመን የጀመረው ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንደ ሰው ሥጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም በመምጣት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክነቱን አሳይቶ፣ ያለ ኃጢዓት ኖሮ፣ በመጨረሻም የእኛን የኃጢዓት እዳ ለመክፈል በእኛ ምትክ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን በመነሳቱ ምክንያት ለእኛ፣ በኃጢዓታችንና በተሳሳቱ ምርጫዎቻችን ምክንያት የዘለዓለም ሞት ጥላ ላጠላብን ለሰው ልጆች የምስራቹን ወንጌል በላከ ጊዜ ነው። ዘመኑም የሚደመደመው ያ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም መንግስቱን ለመመስረት ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ነው። ያ ቀን እጅግ ተቃርቧል።
ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ሲሰበክ የቆየው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንደሚነግረን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እያንዳንዳችንን ይወደናል። በሌላ በኩል ግን ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ጻድቅ እና ፍጹም እውነተኛም ስለሆነ ኃጢዓትን ይጠላል። እኛ የሰው ልጆች ደግሞ መልካሙን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና ህይወትን የምንመኝና የምንጥር እንኳን ብንሆንም፣ ከጋራ አባታችን ከአዳምና ከእናታችን ከሔዋን ጀምሮ በኃጢዓት ውስጥ ተዘፍቀናል። “ኃጢዓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል ሐዋርያው ዮሐንስ (1ኛ ዮሐንስ 1:8)። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅሩ፣ ምህረቱና ጸጋው ከእና ኃጢአት በላይ እጅግ ታላቅ ስለሆነ፣ የእኛን በደል በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ በእኛ ፈንታ እርሱ እንዲሰቃይና በመስቀል እንዲሞት ፈቀደ። ስለኛ ኃጢዓት ሞተ እንጂ እርሱ ኃጢዓት አልነበረበትምና ሞት ሊይዘው አልቻለም። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሳኤው ኃጢዓትንም፣ ሞትንም፣ ሰይጣንንም ድል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ጥል አስወገደ። የምስራቹ ወንጌል ይህ ነው። የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ያለብን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ኃጢዓተኛ መሆናችንን አምነን የሚወደንን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን መቀበል ነው።
እባክህ ዛሬ ሃሳቤን የያዘው ይህ አይደለም፣ ይህ ነገ ይደርሳል አትበሉ። አዎን እያንዳንዳችን የየራሳችን ችግሮችና ሸክሞች አሉብን። ግን እኮ ወገኖቼ ከሁሉም የሚበልጠው የነፍሳችን ነገር ነው። የጌታችንን ትንሳኤ፣ ፋሲካን ካከበርን አንድ ሳምንት ሆነ። ከዚህም በፊት ምናልባት ይህን ወንጌል ሰምተን ችላ ብለነው ሊሆን ይችላል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ይጠራናል። ነገ አንበለው። የነፍሳችንን ነገር አናዘግይ። ሌላው ሁሉ ይደርሳል ወይም ያልፋል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ዛሬ ተቀበለው፣ ተቀበይው፣ ተቀበሉት። ብዙ ሌላ ስጦታ ቢኖረኝነና ብሰጣችሁ ደስ ባለኝ። ነገር ግን ለእኔም ሆነ ለእናንተ ታላቁ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ስጦታ ከእርሱ ጋር ልንኖርበት የምንችለው የዘለዓለም ህይወት ነው። የዚህ ሕይወት  ብቸኛው መንገድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ልናምነውና ልንቀበለው የተሰጠንም ቀን ዛሬ ነው። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

በሶሪያ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተባለው ጦርነት ዘገየ እንጂ የቀረ አይመስልም


ባለፉት ሶስት ቀናት በብዙ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሲናፈስ የቆየውና በዚህ ድረ ገጽም ላይ የተዘገበበት አሜሪካና አጋሮቿ ከሩሲያ ጋር በሶሪያ ላይ ሊዋጉ ነው የሚለው ዜና ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) በተናፈሱት አንዳንድ ዜናዎች መልኩን የቀየረ ይመስላል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሐሙስ እለት በትዊተር በላኩት መልእክት፣ “ሶሪያን የምንመታው ቶሎም፣ ቀስ ብሎም ሊሆን ይችላል” በማለት ከአንድ ቀን በፊት የዜና ምንጮችን ሁሉ ኡኡ ካሰኘውና ሩሲያን በማስፈራራት “አዳዲስ፣ የተራቀቁና ቆንጆ ሚሳኤሎች እየመጡ ነውና ተዘጋጅ” ብለው ከላኩት መልእክት ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ይመስላል። የአውሮፓ የአየር ትራፊክና ደህንነትን የሚቆጣጠረው ድርጅትም በ72 ሰዓታት ውስጥ ጦርነት ሊነሳ ይችላል በማለት የሲቪል አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢ በረራ ከማድረጋቸው በፊት ሁኔታውን እንዲያጤኑ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። አንዳንድ አየር መንገዶችም በዚህ ምክንያት ወደ ሶሪያ፣ ሊባኖስ አካባቢው የሚሄዱ በረራዎችን እንደሰረዙ የዜና ምንጮች አመልክተዋል።ይሁን እንጂ በሶርያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በአሜሪካ በሚመራው የምእራባውያን ህብረት እና በሩሲያ፣ በሶሪያና አጋሮቿ መካከል ያለው ውጥረት ምንም መፍትሔ አላገኘም። የጦርነት አደጋው ለጊዜው ጋብ ያለ ይምሰል እንጂ ዓለማችን አሁንም በድንገት አሻቅቦ ወደ አጥፊ የኑክሊየር እልቂት ሊያስገባ ከሚችለው የጦርነት ገደል አፋፍ ላይ ገና አልተመለሰችም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት  ሶሪያን በሚሳኤልና በቦምብ ለመደብደብ እስካሁን ትእዛዝ ያልሰጡት የአገራቸውን የሶሪያ ስትራቴጂ አስመልክቶ በአሜሪካው ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ካውንስል ውስጥ ባሉት ከፍተኛ ባለስልጣኖች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ዘግበዋል። የራሳቸው የፕሬዝደንቱ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስም ሐሙስ እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ይህንኑ አመልክተዋል። የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከአሜሪካ ጋር በማበር በሶሪያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እንዲያስችላቸው የመንግስታቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ እለት (አፕሪል 12) ሰብስበው ለውሳኔያቸው ድጋፍ እንዳገኙ ተመልክቷል። ከዚህም አንድ ቀን ቀደም ብለው የአገራቸው የባህር ኃይል ወደ ሶሪያ እንዲያቀና ትእዛዝ መስጠታቸው በብዙ ምንጮች ተዘግቧል። ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ሶሪያን ለመምታት በቅድሚያ ዝግጁነቷን ያሳየችው የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ማክሮን ደግሞ በበኩላቸው ሲናገሩ፣ ባለፈው ቅዳሜ በሰላማዊ ህዝቦች ላይ ተፈጽሟል የተባለው የመርዛማ ንጥረ ነገር ጥቃት የተፈጸመው በሶሪያ መንግስት ለመሆኑ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለታቸው ተዘግቧል። የሶሪያ መንግስትና ሩሲያ በበኩላቸው የተባለው ጥቃት እንኳንስ በሶሪያ መንግስት ሊፈጸም ይቅርና ጭራሹኑ ያልተከሰተ፣ አሜሪካ በምትደግፋቸው ሽብርተኞች በተዘጋጀና በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ የውሸት ቪዲዮ የተፈጠረ ወሬ ነው ሲሉ እያስተባበሉ ናቸው። እነዚህ የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በአሜሪካና አጋሮቿ ድጋፍ የተመሰረቱ ድርጅቶች ከዚህም ቀደም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የመርዛማ ጭስ ጥቃቶችን በመፈጸምና ያልተፈጸመውም ተፈጸመ የሚሉ ዜናዎችን በማናፈስ አሜሪካ የሶሪያን መንግስት በቀጥታ እንድትወጋ መሞከራቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረውና ሩሲያንና አሜሪካን በቀጥታ በማጋጨት አሻቅቦ ወደ ኑክሊየር ውድመት ሊያመራ ይችላል የሚባለው ሁኔታ ምንጩ በሶሪያ ውስጥ የተከሰተ የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ በብዙ የምእራባውያን መንግስታትና የዜና ምንጮች ይቅረብ እንጂ፣ ዋነኛው ጠብ በአሜሪካና በምእራባውያን አገሮች ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ዓለም አቀፋዊ የኃይል ፉክክር ነው። በሶሪያ የተፈጠረው ጦርነት መነሾውም አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉና የማትፈልጋቸውን መንግስታት ለመገልበጥ ስታደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬ መሆኑን ለሁኔታው ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ደግሞ ሶሪያ ሁለት የሩሲያ የጦር ሰፈሮች ያሉባት የመካከለኛው ምስራቅ አገር መሆኗ ነው። ከሩሲያ ጋር የሚተባበረውን መንግስት በመገልበጥ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ በዚያ አካባቢ የእግር መርገጫ እንዳይኖራት ለማድረግና ለማዳከም መጣራቸው ለመረዳት አዳጋች አይደለም። በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄፍሪ ሳክስ ለምሳሌ፣ ሐሙስ አፕሪል 12 ላይ CNBC በሚባለው የአሜሪካ ቴሌቪዝን መረብ ላይ ቀርበው ሲናገሩ ዛሬ በሶሪያ ላይ የተፈጠረው ዓለም አቀፍ ውጥረት ምንጩ የአገራቸው የስለላ ድርጅት ከሳውዲ አረቢያ ጋር በመተባበር ከብዙ ዓመታት በፊት የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ በስውር ያደረገውና የከሸፈበት ሙከራ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ይህ ዛሬ በሶሪያ ሰበብ በዓለም ላይ አንዣቦ የሚገኘው ከፍተኛ የጦርነት አደጋ በ1962 እኤአ በሩሲያና በሶቪየት ህብረት በኩባ ላይ ተፈጥሮ ከነበረው አደጋ ጋር የሚቀራረብ እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎችን የፖለቲካ ታዛቢዎች ያመለክታሉ። ራሳቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንትም በዚሁ ሳምንት በትዊተር በላኩት መልእክት ላይ አገራቸው ዛሬ ከሩሲያ ጋር ያላት መጥፎ ግንኙነት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን እንኳን ከነበረው የከፋ እንደሆነ አመልክተዋል። ስለዚህ ወገኖች፣ አሜሪካንና ሩሲያን ወደ ኑክሊየር ጦርነት ሊያስገባ የሚችለው ውጥረት እንደተባለው በሶስት ቀን ውስጥ አይፈንዳ እንጂ መፍትሔን አላገኘም።  የጦር መርከቦች፣ ሰራዊትና መሳሪያዎች ወደ ቦታው እየተንቀሳቀሱ ነው፣ ብዙዎችም በአካባቢው ተፋጥጠዋል። በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ተወካይ የሆኑት ቫሲሊ ኔቤንዚያ ሐሙስ አፕሪል 12 ላይ ሲናገሩ፣ የሩሲያ ጦር በሶሪያ ስላለና ከዋሽንግተን የሚነፍሱት ወሬዎችም አስጊ በመሆናቸው ምክንያት እንደተባለው አሜሪካ ሶሪያን ከደበደበች አገራቸውና አሜሪካ በቀጥታ ሊዋጉ የሚችሉበትን አደገኛ ሁኔታ መኖሩን አልሸሸጉም። ምናልባትም ሰላማዊ መፍትሔ ይገኝ ይሆናል በማለት እኒሁ የሩሲያው ተወካይ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አርብ አፕሪል 13 ላይ እንደገና እንዲሰበሰብ ጠይቃለች። የድርጅቱ ዋና ጸሃፊም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ሪፖርት ያቀርባሉ ሲል ዋሽንግተን ፖስት የተባለው ጋዜጣ ምንጮች አመልክተዋል። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አሜሪካና አጋሮቿ ሶሪያን በቦምብና በሚሳኤል ሊደበድቡ እየተዘጋጁ ነው


ባለፈው ቅዳሜ ማታ፣ መጋቢት 29 (እኢአ) ጉታ በሚባለው በደማስቆ አጠገብ በሚገኝ ከተማ የሶሪያ መንግስት በሰላማዊ ህዝብ ላይ የመርዛማ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ ብዙ ሰዎችን ገድሏል የሚል ዜና ባለፈው እሁድ አፕሪል 8 በምእራቡ ዓለም ዜና አውታሮች ተሰራጭቷል። ዜናው ገና እንደተሰማና ገና በቂ መረጃም ከመገለጡ በፊት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ለዚህ ጥቃት ተጠያቂዎቹ የሶርያ መንግስትና አጋሮቹ ሩሲያና ኢራን ናቸው በማለት፣ በተለይም ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያውን ፕሬዝደንት በስም በመጥቀስና በመንቀፍ መናገራቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ነው እየተባለ በሶሪያ ሲነጉድ የነበረው ጦርነት በቀላሉ ወደ ዓለም ጦርነት ሊያመራ ወደሚችልበት የማሻቀብ ደረጃ መድረሱን ያሳያል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ከየቦታው እየተሰሙ ነው።
ይህ አጭር መልእክት ከተዘጋጀበት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ሲል የአውሮፓው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ድርጅት በሚቀጥሉት 72 ሰዓታት የሰሜኑ አትላንቲክ የመከላከያ ድርጅት (አሜሪካና አጋሮቿ)  በሶሪያ ላይ የሚሳኤልና ሌሎችም የአየር ጥቃቶች ሊፈጽሙ ስለሆነ የህዝብ ማመላለሻና ሌሎችም የሲቪል አውሮፕላኖች በምስራቅ ሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ ከመብረራቸው በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ የጦር መርከቦች ሶሪያ ወደምትገኝበት ምስራቅ የሚዲትራኒያን ባህር እያመሩ ነው የሚሉ ብዙ ዜናዎችም ከየአቅጣጫው እየነፈሱ ነው። የሩሲያ የጦር ኃይልና መሳሪያዎች በራሷ በሶሪያና በሜዲትራኒያን ባህርም ላይ ሲገኙ፣ ቻይና ደግሞ የባህር ኃይሏ ሩሲያን ለመደገፍ ወደዚያው እንዲያመራ አዝዛለች የሚል ዜናም እየነፈሰ ነው።
በ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ነው ተብሎ የተጀመረው ይህ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰላማዊ ህዝብ ያለቀበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የተሰደደበትና የተፈናቀለበት ጦርነት የአረብ ጸደይ ተብሎ ተነስቶ የነበረው በአረብ አገሮች የቆዩ መንግስታትን የመገልበጥ ስራ አካል እንደሆነ ብዙ ሲዘገብበት ቆይቷል። ከ2014 ጀምሮ ግልጽ እየሆነ የመጣ ሌላው ነገር ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ አሜሪካና አጋሮቿ እንደፈለጋቸው በየአገሩ መንግስታትን ይገለብጣሉ በማለት ስታማርር የቆየችው ሩሲያ የጦር ሰፈሮቿ ያሉባት ሶሪያ እንደ ሊቢያ፣ እንደ ኢራቅና እንደ አፍጋኒስታን እንድትፈራርስ ባለመፈለጓ የአገሩን መንግስት ለመርዳት በቀጥታ ወደ ጦርነቱ ውስጥ መግባቷ ነው። ይህን ተከትሎ፣ የሶሪያ መንግስት ባይጠይቃቸውም፣ አሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ በአንድ በኩል የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ የሚዋጉ ሽምቅ ተዋጊዎችን ሲረዱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይሲስን እንዋጋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተለያዩ መልእክቶች ላስተላልፍ እንደሞከርሁት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም ላይ የኤኮኖሚና ወታደራዊ የበላይነትን ይዘው የቆዩት በአሜሪካ የሚመሩት ምእራባውያኑ ኃይሎች የቀዝቃዛው ጦርነት ከበቃና ሶቪየት ሕብረት ከፈራረሰች በኋላ ተቀናቃኝ የለብንም በሚል ስሜትና ዲሞክራሲን እናስፋፋለን በሚል ሽፋን የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ በብዙ አገሮች ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ከርመዋል። ይህ ያስቆጣት ሩሲያ ደግሞ የዩጎዝላቪያ መፈራረስ፣ የኢራቅ ጦርነት፣ ማቆሚያ ያጣው የአፍጋኒስታን ጦርነት፣ የሊቢያ መፈራረስና የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት የዚህ የምእራባውያኑ ማን አለብኝነት ውጤት ነው በማለት ታማርራለች። ይህ ውጥረት ስር ሲሰድ ከቆየ በኋላ በ2014 ላይ አሜሪካ ቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል የነበረችውን የዩክሬንን መንግስት የገለበጠ አብዮትን በመደገፏ፣ ሩሲያ የሰሜኑ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ጓሮዬ እንዲጠጋ አልፈቅድም በማለት በመረረ መንገድ ተቃወመች። የምእራባውያኑ ወደ ዩክሬን መግባት በዚያው በዩክሬን በምትገኘው ክራይሚያ በምትባለው ግዛት ያለውን የባህር ኃይሏን ቦታ ለማሳጣትና ግዛቷንም ለመክበብ ነው በማለት የሰጋችው ሩሲያ በጊዜው በኑክሊየር መሳሪያ በማጥቃትም ጭምር የምእራባውያኑን ወደ ዩክሬን ለመግባት መሞከር ለማቆም ወስና እንደነበር መረጃው ያላቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህን እና ሌሎችንም በምእራባውያኑ አገሮችና በሩሲያ፣ በቻይና፣ በኢራን፣ በሶሪያና፣ በቤኔዙዌላ፣ በሰሜን ኮሪያ ወዘተ መካከል ያሉትን ውጥረቶች በተመለከተ ባለፉት ጊዜያት ሰፋ ያሉ ትንተናዎችን አቅርቤያለሁ።
አሁን በሶሪያ ላይ እያንዣበበ ያለው ሁኔታ በቀላሉ ሊያሻቅብና በታላላቆቹ አገሮች፣ ማለትም በዋናዎቹ ባለኑክሊየር መሳሪያ ባለቤቶች በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ወደሚፈጸም የቀጥታ ጦርነት ሊለወጥ እንደሚችል ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ። የዚህም ዋነኛው ምክንያት በሶሪያ የሩሲያና የኢራን ጦር መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ግጭት ለብዙ ዓመታት በምእራባውያኑና በሩሲያ፣ መካከል በየቦታው ሲገነባ የኖረው ውጥረት ሊፈነዳ መሆኑን ስለሚያመለክትም ነው። እንደ ተገመተው ይህ የሶሪያ ጦርነት አሜሪካንና አጋሮቿን ከሩሲያና አጋሮቿ ጋር በቀጥታ ወደማዋጋት ከደረሰ ምናልባት በትንቢተ ኢሳይያስ ምእራፍ 17 ላይ እና በትንቢተ ኤርምያስ 43:23 እስከ 26 ስለ ደማስቆ መደምሰስ የተጻፉት ትንቢቶች ፍጻሜ ሊሆን ይችላል በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስተማሪዎች ይጠቁማሉ። ያለንበት ዘመን የወንጌል መሰበክና የጸጋ ዘመን ማብቂያና የጌታ ኢየሱስ ዳግም ምጽዓት አጥቢያ ስለሆነ ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ መስማታችን የግድ ነው። አሁን በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ግን ከመቼውም ዘመን ይልቅ እጅግ አደገኛ ስለሆነ፣ ምናልባትም ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ምድር የኑክሊየር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚሉም ብዙ ናቸው። ምናልባትም ይህ ውጥረት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ለሚገለጸው ለሃሰተኛው መምጣት መንገድ የሚጠርግ ሊሆን ይችላል የሚሉ የትንቢት አስተማሪዎች ጥቂት አይደሉም። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የመለከት ድምጽ ድረ ገጽ በከፊል በስራ ላይ ዋለ

የመለከት ድምጽ ድረ ገጽ በከፊል በስራ ላይ ዋለውድ ወገኖቼ፣ ምናልባት እንደ ሰማችሁት እንደዚህ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች እስካሁን በነጻ የሚሰጡት አገልግሎት በዚሁ መንገድ ላይቀጥል ይችላል። ስለዚህም የመለከት ድምጽ አገልግሎትም የራሱ የሆነ ድረ ገጽ ስላስፈለገው ባለፉት ብዙ ወራት ሲታቀድና ሲገነባ ከቆየ በኋላ አሁን በከፊል በስራ ላይ ውሏል። ይህ ድረ ገጽ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት የሚመለከቱ መልእክቶች፣ ዜናዎችና ትንተናዎችን፣ ትምህርታዊ ጽሁፎች፣ መንፈሳዊ መዝሙሮችና ቪዲዮ የሚቀርቡበት ይሆናል። ድረ ገጹ አሁንም በግንባታ ላይ ስላለ ከላይ ከተጠቀሱት አንዳንዶቹ ይዘቶች ገና በስራ ላይ አልዋሉም። ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የቀረቡ ጽሁፎችን፣ የመለከት ድምጽ መጽሔት ያለፉ እትሞችን እና ትንቢት ነክ ዜናዎችን በድረ ገጹ ላይ አቅርበናል። እንዲሁም ከዚህ በፊት በገበያ ላይ ያልዋሉ ከ20 የሚበልጡ በዚህ አገልግሎት ፕሬዝደንት የተደረሱና የተዘጋጁ መዝሙሮችን በማዳመጥ ጌታን እንድታመልኩት፣ እንድትጽናኑና እንድትበረታቱ ተጋብዛችኋል። አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጅታችን ስላልተጠናቀቀ ለጊዜው እንድትታገሱን እንጠይቃለን። የድረ ገጹ አድራሻ: http://www.voiceoftrumpet.org (የመለከት ድምጽ አገልግሎት) ነው።

የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ስልጣን በመጋፋት አየሩን ለመለወጥ እየጣረ ነው

የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ስልጣን በመጋፋት አየሩን ለመለወጥ እየጣረ ነው
ታላላቆቹና ባለጸጎቹ አገሮች የምድርን አየር እንደፈለጉት በመለዋወጥ ሲያሻቸው ዝናብ፣ ሲፈልጉ ማእበል፣ ሳይፈልጉ ደግሞ ድርቅ የሚያስነሱበት ቴክኖሎጂ አላቸው የሚለው ዜና አዲስ አይደለም። የአሜሪካ መንግስት ምክር ቤት በሰፊው ተወያይቶበት ችላ ብሎ የተወው ነገር ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰው አሁንም ይህ መረጃ የለውም ብዙው ደግሞ እውነት ነው ብሎ ለመቀበል አይፈልግም። ሰው የእግዚአብሔርን ስልጣን በዚህና በሌሎች መስመሮችም መጋፋት ከጀመረ ውሎ ቢያድርም የዚህ ዓይነቱ ስራ የመጨረሻ ውጤቱ ጥፋት ነው።  ስለ ቴክኖሎጂውና ስለ ሰው ድፍረት ጥርጥሩ አሁንም ላለን ሰዎች የተያያዘው ዜና ይህ በምእራቡ ዓለም የተጀመረው አየርን የመለወጥና ሰው ሰራሽ ዝናብ የማዝነብ ስራ ዛሬ ደግሞ ወደ በቻይና እንደ ተስፋፋ ያመለክታል። አስተያየት ከመስጠት በፊት የተያያዘውን ዜና በጥሞና አንብቡት።

በጣሊያን ዛሬም የሚገኘው ጌታ የተከፈነበት ነው የሚባለው የቱሪኑ የተልባ እግር ልብስ ታሪክና የክርስቶስ አካል ይህን ይመስል ነበር ተብሎ የተሰራው ቅርጽ

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት፣ በአካል በምድር የነበረበትን ሁኔታ፣ መሰቀሉን፣ መሞቱንና ትንሳኤውን በተመለከተ ታሪካዊ፣ የአርኪዎሎጂና ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ ዛሬም በጣሊያን ያለው የቱሪኑ የከፈን ጨርቅ ታሪክ የሚያስደንቅ ነው። ይህን ማገናኛ በመጫን መረጃውን አንብቡ። በጣሊያን ዛሬም የሚገኘው ጌታ የተከፈነበት ነው የሚባለው የቱሪኑ የተልባ እግር ልብስ ታሪክና የክርስቶስ አካል ይህን ይመስል ነበር ተብሎ የተሰራው ቅርጽ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...