ሥልጣኔ፣ ቴክኖሎጂና የክርስቶስ ወንጌል
ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
አፕሪል 20፣ 2018
ከጥቂት ቀናት በፊት በምድር ላይ አንዣቦ
ስላለው ከፍተኛ የኑክሊየር ጦርነት አደጋ ከአንድ ሰው ጋር ስንነጋገር፣ ያ ሰው “አሁን ያለነው በሰለጠነ ዘመን ነው፣ በዚህ ዘመን
አገሮች ችግሮቻቸውን በመወያየት ይፈታሉ እንጂ እንዴት ይዋጋሉ? በተለይም ደግሞ የሰለጠኑትና ኃያላኑ አገሮች እንዴት እርስ በርሳቸው
ሊዋጉ ይችላሉ?” አለ። ይህ እውነት ይሆን? መልሱን ለአንባቢዎች እተዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህ እውነት እንደሆነ አይናገርም።
እኔም ከቅዱሱ መጽሐፍ ጋር መስማማትን እመርጣለሁ። እናንተስ?!
ይህ ያለንበት ዘመን የሰለጠነ፣ ካለፈው
ዘመን፣ አባት እናቶቻችን ከኖሩበት የተሻለ ነው ብለን እናምናለን። ለዚህም ከምንሰጠው ማስረጃ አብዛኛዎቹ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ
ማደግ ጋር የተያያዙ ናቸው። በአውሮፕላን ከአንድ አገር ወደ ሌላ መሄድ መቻላችን፣ በእጅ በሚያዙ ብልጥ ስልኮች (smart
phones) ለመነጋገርና ለመጻጻፍ መቻላችን፣ ኢንተርኔት
በሚባለው የመገናኛ መረብ ከቤት፣ ከመንገድ ላይ፣ ከመኪና ውስጥና ካለንበት ስፍራ ሁሉ ከሌሎች ጋር መገናኘት መቻላችን፣ ለአንዳንድ
የጤና ችግሮች መድኃኒት ማግኘታችን ወዘተ ለምሳሌ ያህል ይጠቀሳሉ። ነገር ግን፣ እኛም ሆንን የዘመኑ አዋቂዎች፣ ፈላስፎች፣ ባለስልጣኖችና
ባለ ሃብቶች እንዲሁም “ኮከብ” ነን የሚሉት ዘፋኞች፣ ተዋናዮችና ታዋቂ ሰዎች ልንመልሳቸው ከማንችል ከብዙ ጥያቄዎች፣ ልንፈታቸው
ካቃተን ብዙ ችግሮች ጋር እንኖራለን። በቀደሙት ብዙ ዘመናት የኖሩ ህዝቦችም እንዲሁ እንደ እኛ የነሱ ዘመን ከነሱ በፊት ከነበረው
የተሻለ እንደሆነ ያስቡና ይናገሩ ነበር። ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት የነበሩ የግሪክ፣ የሮም፣ የባቢሎን፣ የፋርስ፣ የግብጽ
ወዘተ ሰዎች ለምሳሌ የእነርሱ ስልጣኔ ከነሱ ከቀደሙት የተሻለ እንደሆነና ስለ ሕይወት ምስጢር እናውቃለን ብለው ያምኑ ነበር። በሐዋርያት
ዘመን የነበሩ ግሪኮች ለምሳሌ የግሪክ እውቀትና ፍልስፍና ከሌላው ዘመንና በዚያን ዘመን ከነበሩት ሌሎች አገሮች እውቀት ሁሉ የተሻለ
ነው ብለው ያስቡ ነበር። ስለዚህም ነው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ሲሰብክላቸው “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል” (የሐዋርያት ሥራ
17፤18) በማለት ያሾፉበት።
የሰው ልጅ ሁሉ በየዘመኑ ራሱን ያታልላል።
ዛሬ ከትናንት ይሻላል፣ ነገ ደግሞ ከዛሬ ወደተሻለ ደረጃ እንደርሳለን ብሎ ያስባል፣ ይሰብካል ይህንንም እውነት ለማድረግ ይሰራል፣
የማይስማሙትን ይሰድባል፣ ያስራል፣ ይገድላል። ይህ እውን መሆኑን ግን ታሪክ አያረጋግጥም። እንዲያማ ባይሆን ኖሮ ከቀደሙት ሁሉ
የሰለጠነ ነው በተባለለት በሃያኛው ክፍለ ዘመን በጦርነት ያለቀው ህዝብ ለምን ከዚያ በፊት በነበሩ ምዕተ ዓመታት ካከቀው ህዝብ
በለጠ? ለምንድ ነው ከዓመት ወደ ዓመት የሚሰሩት የሰውን ልጅ መፍጃ የጦር መሳሪያዎች ከቀደሙት እየባሱ የሚሄዱት? በእርግጥ የእኛ
ዘመን ከቀደሙቱ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የላቀ ከሆነ ለምንድ ነው እንደ ስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ ካንሰር፣ የእብጠት በሽታዎች
(inflamattory diseases)፣
የአእምሮ በሽታዎች ወዘተ ከበፊቱ የበለጠ እየበዙ ያሉትና መድኃኒት ያጡት? አሉ የሚባሉት መድኃኒቶች ሁሉ ማስታገሻና ማደንዘዣ እንጂ
ፈጽሞ ህመሞቹን የማያስወግዱት ለምንድ ነው? ጠፉ የተባሉ በሽታዎች እንደገና እየተመለሱ ያሉት ለምንድ ነው። አዳዲስ በሽታ የሚያመጡ
ህዋሳት (ጀርሞች) እየበዙ ያሉትና ቀድሞ ሲያጠፉአቸው የነበሩ መድኃኒቶች ዛሬ የማይሰሩት ለምንድ ነው። በየጊዜው እየመጡ ያሉ ብዙ
ህዝብ የሚጨርሱ እንደ ዚካ ቫይረስ፣ ኢቦላና አዳዲስ የእንፍሉዌንዛ ቫይረሶችን ማስወገድ ለምን አልቻልንም?
እኛ የዛሬዎቹ ሰዎች ከትናንቶቹ የሰለጠንን
እና ከቀደሙት የምንሻል ከሆነ ለምንድ ነው ሃብትና ገንዘብ እጅግ ጥቂት በሆኑ ሰዎች እጅ ተከማችቶ፣ ባለጸጎቹ በጥጋብ የሚሆኑት
ጠፍቷቸው ያዙን ልቀቁን ሲሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና ማደሪያ በማጣት የሚጠበሱት? ስለ ሰለጠንን ከትናንቶቹ ኋላ
ቀር ሰዎች የተሻልን ከሆን ለምንድ ነው በባለጸጎቹ አገሮቹ ብዙዎቹ ትዳሮች ፈራርሰው ልጆች ወላጅ አልባ የሆኑት? ስልጣኔያችን መከናወንን
እና እርካታን ካመጣልን ለምንድ ነው እጅግ ብዙ ሰው በአልኮልና በአደገኛ እጾች ሱስ ተይዞ የሚሰቃየው። የዛሬዎቹ መንግስታት ከቀደሙት
ለህዝብ አሳቢና ለህዝብ ተጠሪ ናቸው ከተባለ ለምንድ ነው እግዚአብሔር ኃጢዓት ነው ያለውን እነርሱ ትክክል፣ ጨለማውን ብርሃን፣
ብርሃኑን ጨለማ በማለት ህዝብ የማይፈልገውን የስህተት የኑሮ ዘይቤ ሁሉ ህግ እያደረጉ በህዝብ ላይ ለመጫን የሚሞክሩት? አዎ ቴክኖሎጂና እውቀት በዝቷል። መረጃ በየቦታው ይገኛል። ሊጠቀሙበት የሚችሉት ግን የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ
ነገሮች የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች እንጂ የሰው ልጅ ወደ ተሻለ ዘመን የመሸጋገሩ ምልክቶች አይደሉም።በግልም ሆነ በቤተሰብ፣ በአገርም
ሆነ በመንግስታት ዘንድ በፍጹም እውነት እንነጋገር ካልን እውነተኛ እድገት፣ ስልጣኔ፣ የልብ ሰላም፣ የውስጥ ደስታ፣ እረፍት፣ እርካታና
ከማንኛውም ፍርሃት፣ በተለይ ደግሞ ከሞት ፍርሃት እንዲሁም ከጥላቻ ነጻ የሆነ ህይወት በውስጣችን ያለን ስንቶቻችን ነን። የትኛው
አገርና ህዝብ ነው በስልጣኔውና በቴክኖሎጂው እኩልነትን ፍትህን እና እውነተኛ ማህበረሰባዊ ሰላምን ለህዝቡ ያሰፈነው። ልብ እንበል
ታላላቆቹና ባለጸጎቹ አገሮች ናቸው እኮ በታሪክ ሁሉ ጦርነት ሲያስነሱ፣ ህዝብን ሲፈጁና ታናናሾችን ሲጨፈልቁ የኖሩት። ዛሬም ያው
ነው። በግል ህይወታችንስ ቢሆን? አንተ፣ አንቺ፣ እርስዎ ስለ ሰለጠንኩኝ፣
የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆንሁ ዛሬም ሆነ ነገ ወይም ለዘላለም፣ ምንም ይፈጠር ምን በፍጹም ረክቼ እኖራለሁ፣ ስሞት ምን እንደሚሆን
አውቃለሁና አልፈራም፣ ተስፋ አለኝ ማለት ይችላሉ? ትችላለህ? ትችያለሽ?
ስለ ስልጣኔያችንና መራቀቃችን የምናስበውና
የምናምነው እውነት ከሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ያለማወላዳት ለራሳችን ልንመልሳቸው የሚገባ ጥያቄዎች ናቸው። ለህዝብ፣ ለባልንጀራ፣ ለባል፣ለሚስት፣
ለአለቃ፣ ለበታች፣ ለጎረቤት፣ ለሃኪም፣ ለልጅ፣ ለፍቅረኛ መዋሸት እንችላለን። በቴሌቪዥን፣ በፊልም፣ በመጻህፍት ብዙ መናገር ይቻላል።
ለራሳችን ግን፣ ለውስጣችን መዋሸት ከባድ ነው። ህሊናችን ይከሰናል። በየቁሳቁሱና በየግሳንግሱ ልንሸነግላትና ዝም ልናሰኛት ብንሞክርም
ነፍሳችን በውስጣችን ትጮሃለች። ፍጹም ሰላም፣ ፍጹም እርካታ፣ ፍጹም እረፍትና ደስታ ልናገኝ የምንችለው ወደዚህ ዓለም ለምን እንደመጣን፣
እንዴትና በማን እንደተፈጠርን፣ ወደፊት ምን እንደምንሆን ስናውቅ ነው። እነዚህን ነገሮች ልናውቅና ልንረዳ የምንችለው ሁሉን ያደረገውን
ልዑል እግዚአብሔርን ስናውቅ ብቻ ነው። እርሱን ማወቅ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ የምንችለው ደግሞ በጌታ
በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። እውነትና መንገድ ህይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የለም የሚሉትን ሰዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ሰነፍ ናቸው ይላቸዋል። ምክንያቱም መጠየቅና ማወቅ የሚገባቸውን ለማወቅ ስላልፈለጉና ታካች ስለሆኑ ነው። እውነተኛ
መርማሪ፣ ምሁር፣ ባለጸጋ፣ ኃያል ሰው መጀመሪያውንና መጨረሻውን ለማወቅ የሚተጋ፣ የሚመረምር ሰው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው
እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ለዚህ ነው፡
“ዓለሙንና
በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሰራው መቅደስ አይኖርም፣ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን
ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ
የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳችን የራቀ አይደለም።” የሐዋርያት ሥራ 17፡24-27
እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርነው እንደ እንስሳ
ምግብ ልንበላ፣ መጠጥ ልንጠጣ፣ ፍትወተ ስጋ እንድንፈጽም፣ ስራ እንድንሰራ፣ ገንዘብ እንድንሰበስብ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስንራወጥ
እንድንኖር ወይም ሌሎች ከነዚህ ጋር ተመሳሳይና ተያያዥ የሆኑ ስጋችንን እና አእምሮአችንን ለጊዜው ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን እንድናደርግ።
ይህማ ቢሆን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ችሎታውና ገንዘቡ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ባለ ፍጹም ደስታ በሆኑ ነበር። ዛሬ ጭንቀት፣
ፍርሃት፣ ስር የሰደዱ በሽታዎች፣ ሽብርና ድንጋጤ ያለው ድሃ በሆኑና ያልተማሩ ህዝቦች በሚኖሩባቸው አገሮች ብቻ ሳይሆን እጅግ ሃብታም፣
የተማሩና ኃያላን በሚባሉ አገሮችም ጭምር ነው። ምክንያቱ ግልጽ ነው። የሰው ልጅ እውነተኛ ሰላምን፣ እረፍትን፣ እርካታንና መከናወንን
የሚያገኘው በዚህ ምድር ላይ ባሉትና በሚያደርጋቸው ነገሮች ብቻ አይደለም። ምግብም፣ መጠጥም፣ በአገባቡና በስርዓቱ የሆነ ፍትወተ
ስጋም፣ ገንዘብም፣ መዝናናትም የየራሳቸው ቦታ አላቸው። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢሟሉም የሰው ልጅ ሙሉ ህይወትን አያገኝም።
እነዚህ የስጋዊ ማንነታችን ፍላጎቶች ናቸው። እኛ የሰው ልጆች ግን በጊዜና በቦታ በተወሰነ አካል ውስጥ የምንኖር በእግዚአብሔር
አምሳል የተፈጠርን ነፍስና መንፈስ ያለን ልዩና ክቡር ፍጥረት ነን። ቢገባንና ብንቀበለው የእግዚአብሔር ፍጥረት ብቻ ሳንሆን ልጆቹም
ነን። ይህን ክቡር ምስጢር ስለ ናቅንና እምቢ ስላልን፣ የራሳችንን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ ስላመጽንና ከሚወደን አምላካችን ወደን ስለምንሸሽ
በሞት ጥላ ውስጥ እንኖራለን። የተፈጠርነው ከልዑል አምላክ ጋር በክብር እንድንነግስ፣ እርሱን በመታዘዝ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድንኖር
ነበር። አወይ አለማወቃችን! አወይ እምቢተኛነታችንና ድንቁርናችን! እጅግ ክቡር ሆነን ሳለ በሚጠፉና ጌዜያዊ ስሜቶቻቸው እንደሚነዱ
እንስሶች ሆንን? ሳናውቀውም ጠፊ ፍላጎቶቻችንን በመከተል ወደ ዘላለም ሞትና ጨለማ እንሄዳለን።
ዛሬ ልጅም ሆን ወጣት፣ ጎልማሳም ሆን አዛውንት
በዚህች ህይወት የምንኖረው ሰባ፣ ሰማንያ፣ ምናልባት እድለኞች ከሆን ዘጠና ዓመት ነው። ከዚያ የሚያልፉ እጅግ ጥቂት ናቸው። ከነዚህ
ዓመታትም ውስጥ እንደፈለገን ሮጠን፣ ተጫውተን፣ የፈለግነውን እያደረግን መኖር የምንችልባቸው ጥቂት ዓመታት ናቸው። ልንሰማው አንፈልግም
እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ሳንወድ በግድ ሞት የሚባለው ነገር ይመጣና ከዚህ ዓለም እንሄዳለን። ወዴት ይሆን የምንሄደው? ወደ መቃብር
ነውና በዚያ ሁሉም ያከትማል ልንል እንችላለን። ስትሞት፣ ስትሞች፣ ሲሞቱ ሁሉም ነገር የሚያበቃ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ? ምን
ማስረጃ አለሽ? ምን ማስረጃ አለዎት? ምንስ ያህል እርግጠኛ ነህ?
ነሽ? ነዎች? ምናልባት ተሳስተህ ወይም ሰዎች አሳስተውህ ከሆነስ ዘለዓለም የሚያህልን ነገር በግምት ልትገባበት እንዴት ትደፍራለህ?
አንሳሳት! ሞት የዚህ ህይወት ምእራፍ አንድ መዝጊያ እንጂ የእኛነታችን ፍጻሜ አይደለም። ሥጋችን ቢሞትም ነፍሳችንና መንፈሳችን
አይሞቱም። ሞት ሲመጣ የምንፈራው፣ የምንጨነቀውና የምናዝነው በዚህ ዓለም የደከምንበትን ሁሉ ጥለነው ስለምንሄድ ብቻ ሳይሆን ከሞት
በኋላ የምንሄድበትን ስለማናውቅ ነው። ከሞት በኋላ ሃኪም፣ መድኃኒት፣ ገንዘብና ባንክ የለም። ከሞት በኋላ የፍትህ ጥያቄ፣ ሰብዓዊ
መብት፣ መንግስት ወይም የሃይማኖት መሪ የለም። ከሞት በኋላ እኛ ዛሬ የምናውቀው ምግብ፣ መጠጥ፣ ፍትወተ ስጋ፣ ባልንጀራ፣ መዝናኛ፣
መጓጓዣ ወይም ቴክኖሎጂም የለም። ከሞት በኋላ እግዚአብሔርን አላምንም የሚል ምሁር፣ ፈላስፋ፣ ጀግና፣ ከሃዲ፣ ባለጠጋ፣ ባለስልጣን
ወይም ተራ ሰው የለም። በዚህም ህይወት ሆነ ከሞት በኋላ በሰዎች መካከል ያለውና እውነተኛ ፋይዳ ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው፣
እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር በታረቁትና የምስራቹን ወንጌል እምቢ ብለው በሚኖሩት መካከል ያለው
ልዩነት ነው።
የመጨረሻው ዘመን ባህሪ ነውና ዛሬ በብዙዎች
ዘንድ እምነት ተብሎ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ስም ሲሰበክ የምንሰማው የዚሁኑ የሚያልፈውን ዓለም ገንዘብ ስለማግኘት፣ ቁሳቁስ
ስለመሰብሰብ፣ በጊዜያዊ ተድላ ራስን ስለ መኮርኮር፣ የስጋን ምኞት ስለማሟላት ነው። ይህ የሰማያዊውን የክርስቶስን ወንጌል ምስጢር
አለማወቅ ነው። መልካምን ነገር መፈለግና ለማግኘት መጣር መልካም ነው። እግዚአብሔር በዚህ ምድርም ሆነ በዘለዓለም ደስ እንዲለን
ይሻል። ነገር ግን አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በኃጢዓት ውስጥ የወደቅን ስለሆንን፣ ዓለምም በሙሉ
በኃጢዓት ምክንያት የጠፋ ስለሆነ በምድራዊ ነገሮች የምናገኘው ደስታ፣ ሰላም፣ እርካታና መከናወን የተወሰነ፣ ኃላፊና ጠፊ ነው።
በከበረውና በተዋረደው፣ በዘለዓለማዊውና በጊዜያዊው ነገር መካከል መለየት ጥበብ ብቻ ሳይሆን የሞትና የህይወት ጉዳይም ነው። ዛሬ
እንደ በረከት የሚሰበከው ገንዘብ፣ ዝና፣ ውበት፣ ስልጣን፣ ደስታና መከናወን እግዚአብሔርን የማያውቁና የማያምኑ አህዛብም የሚፈልጉት፣
ብዙዎች ያገኙአቸውና ጥለዋቸውም የሄዱ ነገሮች ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ከእርሱ ጋር ወደማይጠፋው
የዘለዓለም መንግስትና ክብር እንድንገባ፣ ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው። ስለዚህ እንደ ህጻናት በዚህ ምድር አሻንጉሊቶችና
የመዝናኛ ኮልኮሌዎች ተታልለን የከበረው የዘለዓለም ሕይወትን የማግኘት እድል አይለፍብን። በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመናችን እና አምላካችንን
ለማክበር ከሚያስችሉት እውቀቶች በተረፈ ዛሬ የያዝነው እውቀት ሁሉ መቃብርን አይሻገርም። ገንዘባችን፣ ስልጣናችን፣ ዝናችን፣ ጉልበታችን፣
የባልንጀሮቻችንም ብዛት ምናልባት አስከሬናችንን እስከ መቃብር ድረስ አጅበው ሊሄዱ ይችላሉ እንጂ ከእኛ ጋር የሞትን ወንዝ አይሻገሩም።
አንተስ ወንድሜ ከየትኛው ወገን ነህ? አንቺስ
እህቴ? እርስዎስ? ራሳችንን ስናታልልና የማይሞላውን የዚህ ዓለም አቁማዳ ልንሞላ ስንባዝን የዘለዓለሙ እድል አይለፍብን። ነፍሳችን
በውስጣችን ያለችበትን ሁኔታ ታውቃለች፣ አምላኳን ትናፍቃለች፣ ወደ እርሱ ለመድረስ ትጓጓለች። በመጀመሪያ የነፍሳችንን ጥያቄ እንመልስ።
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ህይወት ተስፋችንን እንያዝ። ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ ይደርሳል። ባይደርስም፣ በዚህ
ዓለም ያለው ኑሮአችን ባይሳካም፣ እንዳሰብነው ባይከናወንም የቀረው ጊዜ አጭር ነውና ያልፋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱም በኋላ ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ
የብዙዎችን ኃጢዓት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢዓት ይታይላቸዋል።” ዕብራውያን
9፡27-28 ዛሬ ነገ ሳንል ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን
ተቀብለን እንዳን። የመዳን ቀን ዛሬ ነው። ነገ በዚህ ምድር ላይ የአንተ፣ የአንቺ፣ የእርስዎ፣ የእኔ ለመሆኑ ዋስትና የለም።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ