አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !


አስቸኳይ የዘለዓለም ሕይወት ጥሪ !
ውድ የፌስቡክ ባልንጀሮቼና ወገኖቼ፣ ከብዙዎቻችሁ ጋር በአካል ባንተዋወቅም፣ ባልንጀሮቼ ስለሆናችሁ በጣም ደስ ይለኛል። እናንተንም ባልንጀሮች አድርጎ ስለሰጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ሰው መሆን እጅግ አስደናቂ ነው። ምንም እንኳን የምንኖረው በተለያዩ አገሮች፣ ከተማዎች፣ ሰፈሮችና ሁኔታዎች ቢሆንም በዚህ የሩቅ መገናኛ መድረክ እንኳን ተዋውቀን ባልንጀሮች በማፍራታችን ደስ ይለናል። ባልንጀራ የሆንነው ታዲያ በአጋጣሚ አይደለም። እኛ በማናውቀው መንገድ እርስ በርስ እንድንፈላለግ፣ እንድንተዋወቅ የሚያደርግ፣ በሰማይና በምድር ሁሉን የሚገዛ ልዑል እግዚአብሔር ነው። እርሱ አጋጣሚ በሚመስሉ ነገሮች ውስጥ ሁሉ እየሰራ እንድናውቀውና ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይሻል።
ልጆች በነበርንበት ጊዜ ከባልንጀሮቻችን ጋር መጫወት ስንችል ደግሞ የምንካፈለው ነገር ሲኖረን ደስ ይለን ነበር። በዚህ በፌስቡክ ለባልንጀሮቼ ምን ላካፍላቸው ብዬ ሳስብ ለእኔ ደግሞ እጅግ ከፍተኛና አስቸኳይ ነው ብዬ የማስበው አንድ ነገር ነው። ዛሬ የምጽፍላችሁም ስለዚህ አንድ ጉዳይ ነው። ይህች የህይወት ዘመናችን ሳናስባት ቶሎ ታልፋለች። የብሉይ ኪዳኑ ጻድቅ ሰው ኢዮብ ስለ ሕይወቱ እንዲህ ብሎ ተናገረ: “ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይቸኩላል፣ ያለ ተስፋም ያልቃል” ኢዮብ 7:6።  የእናንተን ባላውቅም እኔ ግን እንደ ኢዮብ ዘመኔ እጅግ እየፈጠነ ሄዶ ማድረግ ያለብኝን ሳላደርግ እንዳያልፍብኝ አስባለሁ። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ከዚህ ምድር ስንሄድ የምኖርበት የዘላለም መኖሪያችን የት ይሆን። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህች አጭር የምድር ዘመናችን በኋላ ዘለዓለም እንዳለ ያረጋግጥልናል። ለዚህ ነው ስናስብና ስናቅድ ልክ ሺህ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ እንደሚኖር የምናስበውና የምንደክመው። የምንኖረው ሰባ፣ ሰማንያ ወይም ዘጠና ቢሆንም ፍላጎታችን፣ እቅዳችን፣ ጭንቀታችንና ጥረታችን ግን ዘላለም እንደሚኖር ሰው ነው። ምክንያቱም የተፈጠርነው ለዘለዓለም እንድንኖር ነው። ወደድንም ጠላንም፣ አመንንም አላመንንም ከሞት በኋላ የዘላለም ህይወት አለ። ጥያቄው ግን ያንን ዘላለም የምናሳልፈው የት ነው፣ እንዴት ነው የሚለው ነው። ሞት የመጣው በኋላ ሲሆን የሞት ምንጩም ኃጢዓት ነው። በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጅ ለኃጢዓት መድኃኒት የለውም። ኃያሉም፣ ደካማውም፣ ድሃውም ባለጠጋውም፣ የተማረውም ያልተማረውም፣ ሁሉ የኃጢዓት ባሪያና በሞት ፍርሃት ጥላ ስር የሚኖር ነው። በግል ህይወታችንም ሆነ በቤተሰብ፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በግለሰቦችም ሆነ በመንግስታት መካከል ላለው ችግርና ቀውስ ሁሉ ምንጩ ኃጢዓትና የኃጢዓት ፍሬዎች ናቸው።  ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ውስጥ የምናመልጥበት መንገድ አለ።
ይህ የምንኖርበት ጊዜ የመጨረሻው ዘመን ነው። የሰማይና የምድር ወይም የሰው ዘር መጨረሻ ሳይሆን የዘመን መጨረሻ ነው። ይህን የሚናገሩት እኔና የዚህ ዘመን አዋቂዎች ሳይሆኑ እግዚአብሔር አምላክ በእርግጥ የላካቸውና የቀባቸው መጽሐፍ ቅዱስንም ጽፈው ያቆዩልን ነቢያትና ሐዋርያት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።  ይህ ዘመን በአንድ በኩል የተመሰቃቀለ፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ሞትና ስቃይ የሞላበት ነው። ትምህርት፣ እውቀት፣ ስልጣኔ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ሃብት እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም ቢባልም የጦም አዳሪው፣ የህመምተኛው፣ የከፋው፣ የመረረው፣ የስደተኛው፣ ግራ የተጋባው፣ የቁስለኛው፣ ስራ ያጣውና፣ የከርታታውም ቁጥር እንደዚህ ዘመን በዝቶ አያውቅም። እኛም እያንዳንዳችን ከነዚህ በአንዱ ወይም በሌላው ተጎድተን እናዝናለን፣ እንቆዝማለን፣ አንዳንዴም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።  በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እያለቀ ያለው ዘመን ወርቃማ ዘመንም ነው፣ ምክንያቱም እኛ ልንኖርበት የምንችል ሌላ ዘመን አልተሰጠንም። ከዚህ በላይ ግን ይህን ዘመን ወርቃማ የሚያደርገው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የምስራቹን ወንጌል ሰምተንና አምነን የዘለዓለምን  ሕይወት ተስፋ ልንወርስ የምንችልበት ዘመን መሆኑ ነው። ይህ የጸጋ ዘመን የጀመረው ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት እግዚአብሔር ወልድ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንደ ሰው ሥጋን ለብሶ ወደዚህ ዓለም በመምጣት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክነቱን አሳይቶ፣ ያለ ኃጢዓት ኖሮ፣ በመጨረሻም የእኛን የኃጢዓት እዳ ለመክፈል በእኛ ምትክ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን በመነሳቱ ምክንያት ለእኛ፣ በኃጢዓታችንና በተሳሳቱ ምርጫዎቻችን ምክንያት የዘለዓለም ሞት ጥላ ላጠላብን ለሰው ልጆች የምስራቹን ወንጌል በላከ ጊዜ ነው። ዘመኑም የሚደመደመው ያ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም መንግስቱን ለመመስረት ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ነው። ያ ቀን እጅግ ተቃርቧል።
ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ሲሰበክ የቆየው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንደሚነግረን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እያንዳንዳችንን ይወደናል። በሌላ በኩል ግን ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ጻድቅ እና ፍጹም እውነተኛም ስለሆነ ኃጢዓትን ይጠላል። እኛ የሰው ልጆች ደግሞ መልካሙን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና ህይወትን የምንመኝና የምንጥር እንኳን ብንሆንም፣ ከጋራ አባታችን ከአዳምና ከእናታችን ከሔዋን ጀምሮ በኃጢዓት ውስጥ ተዘፍቀናል። “ኃጢዓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል ሐዋርያው ዮሐንስ (1ኛ ዮሐንስ 1:8)። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅሩ፣ ምህረቱና ጸጋው ከእና ኃጢአት በላይ እጅግ ታላቅ ስለሆነ፣ የእኛን በደል በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ በእኛ ፈንታ እርሱ እንዲሰቃይና በመስቀል እንዲሞት ፈቀደ። ስለኛ ኃጢዓት ሞተ እንጂ እርሱ ኃጢዓት አልነበረበትምና ሞት ሊይዘው አልቻለም። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሳኤው ኃጢዓትንም፣ ሞትንም፣ ሰይጣንንም ድል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ጥል አስወገደ። የምስራቹ ወንጌል ይህ ነው። የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ያለብን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ኃጢዓተኛ መሆናችንን አምነን የሚወደንን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን መቀበል ነው።
እባክህ ዛሬ ሃሳቤን የያዘው ይህ አይደለም፣ ይህ ነገ ይደርሳል አትበሉ። አዎን እያንዳንዳችን የየራሳችን ችግሮችና ሸክሞች አሉብን። ግን እኮ ወገኖቼ ከሁሉም የሚበልጠው የነፍሳችን ነገር ነው። የጌታችንን ትንሳኤ፣ ፋሲካን ካከበርን አንድ ሳምንት ሆነ። ከዚህም በፊት ምናልባት ይህን ወንጌል ሰምተን ችላ ብለነው ሊሆን ይችላል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ይጠራናል። ነገ አንበለው። የነፍሳችንን ነገር አናዘግይ። ሌላው ሁሉ ይደርሳል ወይም ያልፋል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ዛሬ ተቀበለው፣ ተቀበይው፣ ተቀበሉት። ብዙ ሌላ ስጦታ ቢኖረኝነና ብሰጣችሁ ደስ ባለኝ። ነገር ግን ለእኔም ሆነ ለእናንተ ታላቁ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ስጦታ ከእርሱ ጋር ልንኖርበት የምንችለው የዘለዓለም ህይወት ነው። የዚህ ሕይወት  ብቸኛው መንገድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ልናምነውና ልንቀበለው የተሰጠንም ቀን ዛሬ ነው። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

1 አስተያየት:

  1. እራስህን ለአለም ለመክፈት እና ምን አይነት ንግድ ሊያመጣ እንደሚችል ለመግለፅ ጥሩ መመሪያ ስለሰጡን እናመሰግናለን።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...