የኑክሊየር ፍንዳታ ቢሆን እንዴት ማምለጥ ይቻላል የሚናገሩ ዜናዎች እየጨመሩ ነው። ለምን?!



ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ በFACEBOOK መልእክቶቼ እንደ ጻፍሁትና በመለከት ድምጽ ቁጥር 7 ላይ በበለጠ ዝርዝር ላቀርብ እንደሞከርሁት፣ በዓለም ዙሪያ የጦርነት ወሬ እጅግ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ብቻ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በአገሪቱ የመሳሪያ ሽያጭ ታሪክ (በአንድ ጊዜ ለአንድ አገር) ትልቁ የሆነውን የሶስት መቶ ሃምሳ (350) ቢሊዮን ዶላር የተራቀቁ መሳሪያዎች ሽያጭ ውል ከሳውዲ አረቢያ ጋር እንደተፈራረመች ሰምተናል። ዛሬ በሰው ዘር ላይ እያንዣበበ ያለው የጦርነት ደመና በአንድ አካባቢ፣ በአንድ አገር ወይም ክፍለ ዓለም ብቻም አይደለም። በታላላቆቹ የዓለም መንግስታት መካከል ያለው ውጥረትና አለመተማመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙ አዋቂዎችና መሪዎችም ሳይቀር ሲያስጠነቅቁ ውሎ አድሮአል። ምን ዓይነት መረጃ እንዳላቸው ባናውቅም፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ብዙ ጊዜ ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ እንደ CNN ያሉ የዜና አውታሮች ሳይቀሩ የኑክሊየር ቦምብ በአካባቢያችሁ ቢፈነዳ ለመትረፍ ይህን ወይም ያንን አድርጉ፣ አታድርጉ የሚሉ ዜናዎችንና ቅንብሮችን ማቅረብ ጀምረዋል። ለምሳሌ የCNN ድረ ገጽ ባለፈው MARCH 17 2017 ላይ ይህን የሚመለከት ዜና አቅርቦ ነበር። በሚቀጥሉት አጫጭር መልእክቶች ላይ ከነዚህ ዜናዎች አንዳንዱን አካፍላችኋለሁ። ከዚህ መልእክት ጋር ተያይዞ የሚገኘውና BUSINESS INSIDER በሚባለው የታወቀ ድረገጽ ላይ የቀረበው ዜና መሰል ሪፖርት ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የተጻፈው መኪና ላላቸውና በመኪና ለማምለጥ ለሚሞክሩ ሰዎች ቢመስልም፡ ሁሉ ሰው ሊያነበው ያስፈልጋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብሎ፣ ከአምላኩና ከሌሎችም ጋር ታርቆና ሰላሙን ይዞ የሚኖር ሰው ምንም ነገር አያስፈራውም። ክርስቲያን ሊፈራ የሚገባው ስጋን መግደል ብቻ ሳይሆን ነፍስንም በገሃነም ሊጥል የሚችለውን አንዱን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ (ዘጸዓት3፡15)  የሆነውን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። በዚህ ክፉ ዘመን ሌላ መሸሸጊያ የለም። ዓለምን ብዙ ጊዜ የሚያጠፋ የኑክሊየር መሳሪያዎች ያላቸው ታላላቆቹ አገሮችም ቢሆን የማጥፋት እንጂ የራሳቸውንም ህዝብ የማዳን አቅሙ የላቸውም። ምናልባት ታላላቆቹ ባለጸጎችና መረጃው ያላቸው አዋቂዎችና ዋና ዋና ባለስልጣኖች በምድር ውስጥ በሰሩአቸው የኑክሊየር ታዛዎች በመጠለል ወይም መሳሪያዎቹ አይመቱአቸውም ወደሚባሉ ቦታዎች ቀድመው በመሸሽ ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። እንደኔና እንደናንተ ያለው ተራው ህዝብ ግን ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ተስፋ የለውም። ይህ ነገር በእርግጥም ከተፈጠረ አዋቂዎቹ የሚሰጡትን ምክር መስማትና ከተቻለም መከተል ጥሩ ነው። ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ሳይሆን ገና ጊዜ ሳለ ከልባቸው ተስፋ የሚያደርጉትንና እምነታቸውን በሱ ላይ የሚጥሉትን የሚያድንና የሚታደግ፣ ችሎታው፣ ፍላጎቱና ፍቅሩ ያለው አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ አለ። ወደሱ የመቅረቢያው ዋነኛ መንገድ ደግሞ ልጁ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወደ እርሱ የመጠጋትና የማምለጫው ጊዜ ደግሞ ዛሬ ነው። ኢንሹራንስ የሚገዛው አደጋው ሲፈጸም ሳይሆን ቀደም ብሎ ነው። ነገም እንደ ዛሬ ይሆናል። የዚህ ዓይነት ወሬ ከዚህም በፊት ሰምተናል፣ ምንም አይሆንም እያልን ቀኑ አይለፍብን። ሰላም እንዲሆን የሁላችንም መሻትና ጸሎት ነው። ነገር ግን የነፍሳችንን ብቸኛ ኢንሱራንስ፣ ለዚያውም ምንም ክፍያ የሌለበትንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ፣ በደሙ የዋጀልንን የምስራች ወንጌል ዛሬ እንጨብጥ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አእምሮ ፖሊስ (ሮቦኮፕ) በዱባይ ስራቸውን ጀመሩ


ባለፈው ሳምንት በላክሁት መልእክት ላይ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ሰው ሰራሽ አእምሮ (Artificial Intelligence) ዛሬ በሰው ልጆች ከሚሰሩት ስራዎች ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆኑትን እንደሚወስዱ የሚናገር ዜናን አያይዤ ነበር። እነዚህ በ AI የሚወሰዱ ስራዎች ደግሞ ማሽኖች መስራት ይገባቸዋል ወይም ሊሰሩአቸው ይችላሉ ብለን የምናስባቸውን እንደ ጽዳት፣ እቃ መጫንና ማውረድ የመሳሰሉትን ብቻ ሳይሆን እኛኑ ራሳችንን የሰው ልጆችን ማስተዳደርም ሊሆን እንደሚችል ጠቆም አድርጌ ነበር። በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምታነቡት ታዲያ የተባበሩት የዓረብ ኤሚሬቶች ዋነኛዋ የንግድ ከተማ ዱባይ የመጀመሪያውን የAI ፖሊስ በስራ ላይ አሰማርታለች። በሚቀጥሉት 13 ዓመታትም ከዱባይ የፖሊስ ሃይል 25 በመቶው በነዚሁ AI ፖሊሶች (ሮቦኮፕስ) እንደሚሆን ብርጋዲዬር ጀነራል ካሊድ ናሲር አል ራዙቂ የሚባሉት የዱባይ ፖሊስ የዘመናዊ ወይም የተራቀቁ አገልግሎቶች ዲሬክተር ጀነራል ተናግረዋል። የሚቀጥለው የሮቦት ሹመት ደግሞ ምን ይሆን?! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ

ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ
ከሃያ ዓመት በፊት አብዛኛው የምድር ህዝብ በእጅ በሚያዝ ስልክ ብቻ መነጋገር፣ መጻጻፍ፣ ፎቶና ቪዲዮ ማንሳት፣ የሚፈልገውን መገብየት፣ ስለአየር ንብረት መረጃን ማግኘት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ ሙዚቃ መስማት ወዘተ ይችላል ተብሎ ቢነገር ብዙም የሚያምን ሰው አልነበረም።  ከአምስት ዓመታት በፊት ደግሞ የሰው ሰራሽ አእምሮ (ARTIFICIAL INTELLIGENCE) ሰዎች የሚሰሩትን ስራ ሁሉ ይወስዳል ቢባል ብዙው ሰው ይስቅ ነበር። አሁን ግን እዚያ ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህን የሚጠራጠር የተያያዘውን ዜና እና ሌሎችንም ብዙ መሰል ዜናዎችን ማንበብ ይችላል።
የሰው ሰራሽ አእምሮ የሚባለው በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎች የሚሰሩት ኮምፒውተሮችን የሚቆጣጠርና የሚያንቀሳቅስ ፕሮግራም ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም እየተራቀቀ ከመምጣቱ የተነሳ ብዙ ነገሮችን የመማርና የተማረውንም ስራ ላይ የማዋል ችሎታ አለው። ለምሳሌ GOOGLE የሚባለው አገልግሎት፣ FACEBOOK እና ሌሎችም በኮምፒውተርና በዓለም አቀፉ መረብ ላይ የሚሰሩ አገልግሎቶች ይህንን የሰው ሰራሽ አእምሮ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ። የኮምፒውተሮች የማስላት፣ መረጃን የማከማቸትና የማስላት ችሎታ እጅግ እየጨመረ በሄደ መጠን ይህ ቴክኖሎጂም በከፍተኛ ደረጃ እየተራቀቀ መጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለሰው ሊሰሩ አይችሉም ይባሉ ስራዎችን መስራት ጀምሮአል። ከዚያም አልፎ ሰዎች ሰዓታት፣ ቀናትና ሳምንታት ፈጅተው አንዳንዴም ከብዙ ስህተቶች ጋር ይሰሩአቸው የነበሩ ስራዎችን በጥቂት ሰከንዶች ወይም ደቂቃዎች ውስጥ በማከናወን ጊዜንና ገንዘብን እንደሚቆጥቡ በሰፊው እየተነገረ ነው። ብዙ የንግድና የመንግስት ድርጅቶችም ይህን ቴክኖሎጂ በሰፊው ለመጠቀም እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።
ሰው ሰራሽ አእምሮ ዛሬ የሚሰራው በሮቦት ውስጥ ወይም በኮምፒውተሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። ዛሬ እንደ ሰዓት፣ መነጽር፣ ልብስና ጫማ ያሉ በሰውነታችን ላይ የምንለብሳቸው ወይም የምናደርጋቸው ነገሮች፣ የምንነዳቸው መኪናዎች፣ በእጃችን የምንይዛቸው ስልኮች ማቀዝቀዣዎችና ሌሎችም ቁሶች በዚህ ቴክኖሎጂ እየተሞሉ ነው። የዛሬዎቹ የእጅ ስልኮች ተዘግተው እንኳን ሳለ የምንነጋገረውንና የምንሰማውን እያዳመጡ መረጃን ስለሚልኩ በጓዳ ጎድጓዳችን የምንነጋገረው ሳይቀር ለስለላና ለነጋዴዎች ማስታወቂያ አገልግሎት ይውላል። በሰው ሰራሽ የተሞሉት የዛሬዎቹ ሮቦቶች እንግዳ ይቀበላሉ፣ የገንዘብ ሂሳብና የባንክ ስራዎችን ይሰራሉ፣ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ስራዎች ይሰራሉ፣ በየምግብ ቤቱ ምግብ በመስራትና በማቀበል፣ ቡና በማፍላትና በማስተናገድ ያገለግላሉ፣ ፖስታና እቃ ከሻጮች ወደ ገዢዎችና ተገልጋዮች ያደርሳሉ፣ መኪና ይነዳሉ፣ አውሮፕላን ያበራሉ፣ መሳሪያ ይዘው ቤቶችን፣ ህንጻዎችንና ድርጅቶችን፣ ሰው በብዛት የሚንቀሳቀስባቸውን እንደ አውሮፕላን ማረፊያና አውቶቡስ መናኽሪያ ያሉ ስፍራዎችን እንዲሁም የጦር ሰፈሮችን ይጠብቃሉ ፣ ካስፈለገም ሊተኩሱና ሊገድሉም ይችላሉ።
ኬይ ፉ ሊ የሚባሉት የSinovation Ventures ድርጅት መስራችና የታወቁ የቻይና የቴክኖሎጂ ባለሙያ ይህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የሰዎች ልጆች ከሚሰሩአቸው ስራዎች ውስጥ ግማሹን ይወስዳሉ ሲሉ ዜናው እንደቀላል መታየት የለበትም። በዚህ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ስራ የሚነፈገው ህዝብ ብዙ ትምህርት የሌለው ወይም በልምድና በመጠነኛ ስልጠና የሚሰሩ ስራዎችን የሚሰራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡና ከፍተኛ ልምድን ያካበቱ ሰዎችም ናቸው። ታዲያ ያ ሁሉ ከስራ የሚፈናቀለው ህዝብ ምን ሰርቶ ይኖር ይሆን? ያን ያህል ህዝብ ከስራ ተፈናቅሎ የገቢ ምንጩ ከተቃወሰ ወይም ጭራሹኑ ከጠፋስ እነዚያ ይህን ቴክኖሎጂ በማሰማራት ምርትና አገልግሎታቸውን ለመሸጥ የሚፈልጉት ድርጅቶች የሚሸጡት ለማን ነው? ደግሞስ እየዋልን ስናድር ይህ ቴክኖሎጂ ለሰው አለቃ ከመሆን የሚከለክለው ነገር የለም። ዛሬ እንደ ካናዳ ባሉት በሰለጠኑት አገሮች ልጆቻችን ገና ማንበብና መጻፍ እንኳን ጠንቅቀው ሳያውቁ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ኮምፒውተር ፕሮግራም ስለማድረግ (CODING) እንዲማሩ ተደርጓል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆቻችንን በትምህርት ቤት የሚጠብቁ ሮቦቶች ቢሰማሩ ወይም የሚያስተምሩአቸው በዚህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የተሞሉ ሮቦቶችና ሌሎች ቁሶች እንደሚሆኑ ብዙም አያጠራጥርም።
ይህ ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር ቢኖረውም ለሰው ልጅ ህልውና እጅግ ያሰጋል የሚሉ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። ዋነኛው አደጋ፣ ይላሉ እነዚህ አዋቂዎች፣ ይህ ቴክኖሎጂ ያለገደብ ራሱን በራሱ ማስተማር፣ ራሱን መልሶ መፍጠርና ማባዛት ወይም ለሚሰራው ሁሉ የሰውን ፈቃድ በመጠየቅ ፈንታ ለራሱ ስልጣንን መስጠት የተማረ ወይም የለመደ እንደሆነ ነው። ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ከሄደ ደግሞ ይህ አይሆንም ሊባል አይችልም ይላሉ ብዙ ታዛቢዎች።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዘመንና ይህ ቴክኖሎጂ እንደሚመጣ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ገልጾአል። የተገለጸላቸውን ነገር ለኛ ጽፈው የተውልን የጌታ ነቢያትና ሃዋርያት ይህን ቴክኖሎጂ የሚመስል ነገር በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጣና እጅግ እንደሚበዛ፣ የሰው ልጆችም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ከሚኖራቸው እምነት የተነሳ ሰይጣን ብዙው የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንደ አምላክ እንዲቀበለውና እንዲያምነው እንኳን ለማድረግ ሊጠቀምበት እንደሚችል ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 13 ቁጥር 11 እስከ 18 ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚገለጸው ሃሰተኛው ነቢይ የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንዲያምኑ ለማድረግ ሰዎች ለሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልን እንዲሰሩ እንደሚያዝና ለዚያም ምስል እስትንፋስ እንደሚሰጠው ይናገራል። እስትንፋስ የሚሰጠው የሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልም አፉን ከፍቶ በመናገር ሰዎች ሁሉ ለሃሰተኛው ክርስቶስ እንዲሰግዱ ያዝዛል፣ የማይሰግዱትንም ሁሉ ያስገድላል። ከአስር ዓመታት በፊት እንኳን ብዙ አሿፊዎች ይህን ክፍል ሲያነቡ ቅዥት ነው ወይም ደግሞ የክፉ መናፍስት ስራ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ይሉ ነበር። በእርግጥ ሃሰተኛው ክርስቶስም ሆነ ሃሰተኛው ነቢይ የሚያደርጉት ሁሉ ከጥልቁ የሚወጣ የዲያብሎስ ስራ ነው። ነገር ግን፣ ምን ያህል የጎላ ወይም እንዴት መሆኑን አናውቅም እንጂ በሰው እጅ የተሰራው ይህ ቴክኖሎጂም (ሰው ሰራሽ አእምሮ ወይም AI) በመጨረሻው ዘመን የትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢትን የሚያጠኑ ሊቃውንት ይስማማሉ። ሰው ሰራሹ አእምሮ ዛሬም ቢሆን ህይወታችንን በብዙ መንገዶች እየተቆጣጠረ እንዳለ አንዘንጋ። ቴሌቪዥኑ የምናይ የምንሰማውን ጆሮ ጠቢ፣ የእጅ ስልኩ የወጣን የገባንበትን፣ የሰማን የተነፈስነውን አሾክሿኪ፣ መኪናችን ከሰማይ ሳተላይት ጋር ተያይዞ የወጣን የገባንበትን ሁሉ የሚያሳብቅ፣ የባንክ ካርዳችን የምንበላውን የምንጠጣውንና የምንለብሰውን ሳይቀር የሚያቀብል ነው። መረጃ ፈልገን በኮምፒውተራችን GOOGLE ላይ ጉድ ጉድ ብንል ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስልካችን ያንን እቃ ግዛ፣ ይህን ፊልም እይ የሚል የሽያጭ ግብዣን ያመጣልናል። ከቤት ውስጥ አንድ ሰው መኪና ከገዛ በሚቀጥለው ቀን የጎማ ወይም ሌላ የመኪና እቃ ማስታወቂያ በራችን ድረስ ወይም ስልካችን ላይ ይመጣል። በአጋጣሚ አይደለም። ሰው ሰራሹ ቴክኖሎጂ ሳናውቀው ዙሪያችንን ከቦናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የታመንን ሁሉ  ልንፈራ አያስፈልግም። ከዚህ ሁሉ ሰው ሰራሽም ሆነ ምንጩ ከአጋንንት ከሆነ ቴክኖሎጂና አሰራር በሙሉ በምህረቱ፣ ዘለዓለማዊ ኃይሉና ፍቅሩ የከበበን አምላክ አለን። ብርሃናችን ክርስቶስ መጥቶአልና ልንነሳ የተስፋን ወንጌል ላልሰሙ ሁሉ ልናበስር ይገባል። ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ ይህን ልብ እንበል፣ በዓለም ላይ የሚካሄደውን ነገር በሙሉ በቃሉ መሰረት በመረዳት ለሌሎች ብርሃን መሆን የምንችል እኛ ብቻ ነን። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር ህዝብ ለእስራኤል እንዲህ አለ፡ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ አብሪ። እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አህዛብን ይሸፍናል፣ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፣ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አህዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገስታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።” ኢሳ 60፡1፥3። እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ በልባችን ያበራው የወንጌል ብርሃን ለሌሎችም ይብራ!!
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት በዚህ ወር እስራኤልን ሲጎበኙ ብዙ የእስራኤል አይሁድ የሚጠብቁት "መሲሁ" እንዲመጣም እንዲጸልዩ ተጠየቁ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ኢየሩሳሌምን ሲጎበኙ መሲሁም እንዲመጣ ሊጸልዩ ይገባል አለ የእስራኤል የሽማግሌዎች ጉባኤ (ሳንሄድሪን)

እውነተኛው መሲህ፣ የዓለምን ሁሉ ኃጢዓት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ፣ የእስራኤልና የአህዛብ ሁሉ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ተገልጿል። ህግና ነቢያት የተናገሩትንና የተነበዩትን በሙሉ ፈጽሞ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ በአባቱ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። በተያያዘው ጽሁፍ ላይ እንደምንመለከተው ግን እጅግ ብዙ የአብርሃም ዘር የሆኑ አይሁድ መሲሁ ገና አሁን ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያልተረዳ ክርስቲያን ይህን ዜና ሲሰማ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከተነገሩት ትንቢቶች ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ ስለሆነ ምናልባት አይሁድ ሊመጣ ነው የሚሉት የተሰቀለውን፣ የሞተውንና ከሞትም በድል የተነሳውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን አይሁድ አሁን ገና መሲሁ ሊመጣ ነው የሚሉት ክርስቲያኖች የሚያምኑትን ኢየሱስ ክርስቶስን አይደለም። በእነርሱ እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ መሲህ አይደለም። በፍጹም አይቀበሉትም አያምኑትምም። የሚጠብቁትም የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት ሳይሆን የ”መሲሁን” የመጀመሪያ መምጣት ነው። ለእስራኤል ሰላምና መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው ተከፍተው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማየትና ማመን እንዲችሉ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ልንጸልይ ያስፈልጋል።
ዛሬ አይሁድ የሚጠብቁት መሲህ (በእብራይስጥ መሺያክ) እስራኤልን ከጠላቶቿ የሚታደግ ታላቅ መሪ ነው ብለው የሚያስቡትን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በሚገባ ባልተረዱበት፣ ከሞቱና ከትንሳኤው በፊት በነበረው ጊዜ የጌታ ሃዋርያትም እምነት ይህን ይመስል እንደነበር ከወንጌሎች እንረዳለን። ስለዚህ ዛሬ ብዙ አይሁድ በሚያምኑት ነገር ልንገረም አይገባም። ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 5 ቁጥር 43 ላይ “እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ” ብሎ ነበር። ስለዚህ እነሱ መሲህ ነው የሚሉትን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መሲህ ሊቀበሉ የግድ ነው ማለት ነው። እዚህ ጋ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ። እነዚህ ያለንባቸው ቀናት ካላስተዋልን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች የሚከሰቱበትና የሚናፈሱበት ጊዜ ነው። ክርስቲያኖች የዘመኑ መጨረሻ ቀርቦአልና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ። ብዙ እስላሞችም መሃዲው የሚገለጽበት ዘመን ነው ይላሉ። ሌሎች ብዙ እምነቶችም ሊመጣ ነው ብለው የሚጠብቁት “ታላቅ” መሪ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ቀደም ብሎ በምድር ላይ ስለሚመጣና ዓለምን ሁሉ ስለሚያስት አንድ “የዓመጽ ሰው” ወይም “የጥፋት ልጅ” ይናገራል። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በበጉ መጽሃፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉት በምድር የሚኖሩ ሁሉ የሚሰግዱለት ይህ “ሰው” ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፣ ብዙዎችን ያጠፋል ብዙዎችም ይከተሉታል።

ታዲያ በዚህ ዜና ላይ እንደምንመለከተው የአሜሪካው ፕሬዝደንት እንዲመጣ መጸለይ ይገባቸዋል የተባለው መሲህ የቱ ይሆን የሚለው ጥያቄ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት ተመራማሪዎችን ብዙም ግራ የሚያጋባ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ካልተቀበሉና ሌላ መሲህ እንዲመጣ የሚጸልዩ ከሆነ ያ የሚጠበቀው ሌላው “መሲህ” መጽሐፍ ቅዱስ የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ የሚለው ወይም በተለምዶ ሃሳዊው መሲህ የሚባለው ሰው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው በሚለው ሃሳብ ላይ ብዙ የትንቢት ምሁራን ይስማማሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ በእርግጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ ነው ማለት ነው። እንንቃ! በመጠን እንኑር! መጽሐፍ ቅዱሳችንን እናንንብብ፣ እናጥና! እንጸልይ። በመቅረዛችን ዘይት የመሙያው ጊዜ ሳናውቀው እያለፈብን እንዳይሆንና ጌታችን ሲመጣ በሩ እንዳይዘጋብን አንዘናጋ። እግዚአብሔር መልካም ነው። ነገር ግን ይህ የጸጋ ዘመን ደግሞ ለዘላለም አይቆይም። በማናስብበት ጊዜ እንደሚመጣ ጌታ ደጋግሞ ነግሮናል። እንንቃ! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

የመለከት ድምጽ መጽሔር ቁጥር 7

የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 7 ዛሬ ወጥቷል። ከታች የተሰጠውን ማገኛና በመጫን ማንበብ ይቻላል። እንዲሁም ደግሞ ከFACEBOOK የVoice of Trumpet group እና ገጽ ላይ download በማድረግ ማንበት ይቻላል። ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ በFACEBOOK እና በመለከት ድምጽ ብሎግ ለማቅረብ እንደሞከርሁት፣ ጦርነትና የጦርነት ወሬ የየእለት ዜና ከሆነ ውሎ ቢያድርም፣ የዓለም ሁኔታ እየተሻሻለ ሳይሆን ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየባሰ ነው የሚሄደው። ቁጥር 7 በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ መረጃዎችን፣ ትምህርቶችን እና ሃሳቦችን ይዛ ቀርባለች። እያንዳንዱ አንባቢ ቢያንስ አንድ መልእክት፣ መታነጽና መጽናናት እንዲያገኝባት የልቤ መሻትና ጸሎቴ ነው። አንብባችሁ ላልደረሳቸውም በማድረስ እንድትረዱኝ በትህትና እጠይቃለሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
የመለከት ድምጽ ቁጥር 7
አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን ታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። (መዝሙረ ዳዊት ምዕ 46። እግዚአብሔር መልካም ነው በመከራም ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ትንቢተ ናሆም 1፤7 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፣ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። (ምሳሌ 21፤31) http://www.express.co.uk/life-style/life/797877/world-war-3-bomb-shelter-locations

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...