ባለፉት ጥቂት ወራት በዚህ በFACEBOOK መልእክቶቼ እንደ ጻፍሁትና በመለከት ድምጽ
ቁጥር 7 ላይ በበለጠ ዝርዝር ላቀርብ እንደሞከርሁት፣ በዓለም ዙሪያ የጦርነት ወሬ እጅግ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ብቻ
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት በአገሪቱ የመሳሪያ ሽያጭ ታሪክ (በአንድ ጊዜ ለአንድ አገር) ትልቁ የሆነውን የሶስት መቶ ሃምሳ
(350) ቢሊዮን ዶላር የተራቀቁ መሳሪያዎች ሽያጭ ውል ከሳውዲ አረቢያ ጋር እንደተፈራረመች ሰምተናል። ዛሬ በሰው ዘር ላይ እያንዣበበ
ያለው የጦርነት ደመና በአንድ አካባቢ፣ በአንድ አገር ወይም ክፍለ ዓለም ብቻም አይደለም። በታላላቆቹ የዓለም መንግስታት መካከል
ያለው ውጥረትና አለመተማመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙ አዋቂዎችና መሪዎችም ሳይቀር ሲያስጠነቅቁ ውሎ አድሮአል። ምን ዓይነት
መረጃ እንዳላቸው ባናውቅም፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ብዙ ጊዜ ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ እንደ CNN ያሉ የዜና አውታሮች ሳይቀሩ
የኑክሊየር ቦምብ በአካባቢያችሁ ቢፈነዳ ለመትረፍ ይህን ወይም ያንን አድርጉ፣ አታድርጉ የሚሉ ዜናዎችንና ቅንብሮችን ማቅረብ ጀምረዋል።
ለምሳሌ የCNN ድረ ገጽ ባለፈው MARCH 17 2017 ላይ ይህን የሚመለከት ዜና አቅርቦ ነበር። በሚቀጥሉት አጫጭር መልእክቶች
ላይ ከነዚህ ዜናዎች አንዳንዱን አካፍላችኋለሁ። ከዚህ መልእክት ጋር ተያይዞ የሚገኘውና BUSINESS INSIDER በሚባለው የታወቀ ድረገጽ ላይ የቀረበው ዜና መሰል ሪፖርት ግን ልብ
ሊባል የሚገባው ነው። የተጻፈው መኪና ላላቸውና በመኪና ለማምለጥ ለሚሞክሩ ሰዎች ቢመስልም፡ ሁሉ ሰው ሊያነበው ያስፈልጋል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብሎ፣ ከአምላኩና ከሌሎችም ጋር ታርቆና ሰላሙን ይዞ የሚኖር
ሰው ምንም ነገር አያስፈራውም። ክርስቲያን ሊፈራ የሚገባው ስጋን መግደል ብቻ ሳይሆን ነፍስንም በገሃነም ሊጥል የሚችለውን አንዱን
አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ (ዘጸዓት3፡15) የሆነውን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። በዚህ ክፉ ዘመን ሌላ መሸሸጊያ የለም። ዓለምን ብዙ ጊዜ የሚያጠፋ የኑክሊየር መሳሪያዎች ያላቸው
ታላላቆቹ አገሮችም ቢሆን የማጥፋት እንጂ የራሳቸውንም ህዝብ የማዳን አቅሙ የላቸውም። ምናልባት ታላላቆቹ ባለጸጎችና መረጃው ያላቸው
አዋቂዎችና ዋና ዋና ባለስልጣኖች በምድር ውስጥ በሰሩአቸው የኑክሊየር ታዛዎች በመጠለል ወይም መሳሪያዎቹ አይመቱአቸውም ወደሚባሉ
ቦታዎች ቀድመው በመሸሽ ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። እንደኔና እንደናንተ ያለው ተራው ህዝብ ግን ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ተስፋ የለውም።
ይህ ነገር በእርግጥም ከተፈጠረ አዋቂዎቹ የሚሰጡትን ምክር መስማትና ከተቻለም መከተል ጥሩ ነው። ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ሳይሆን
ገና ጊዜ ሳለ ከልባቸው ተስፋ የሚያደርጉትንና እምነታቸውን በሱ ላይ የሚጥሉትን የሚያድንና የሚታደግ፣ ችሎታው፣ ፍላጎቱና ፍቅሩ
ያለው አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ አለ። ወደሱ የመቅረቢያው ዋነኛ መንገድ ደግሞ ልጁ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ወደ እርሱ የመጠጋትና የማምለጫው ጊዜ ደግሞ ዛሬ ነው። ኢንሹራንስ የሚገዛው አደጋው ሲፈጸም ሳይሆን ቀደም ብሎ ነው። ነገም እንደ
ዛሬ ይሆናል። የዚህ ዓይነት ወሬ ከዚህም በፊት ሰምተናል፣ ምንም አይሆንም እያልን ቀኑ አይለፍብን። ሰላም እንዲሆን የሁላችንም
መሻትና ጸሎት ነው። ነገር ግን የነፍሳችንን ብቸኛ ኢንሱራንስ፣ ለዚያውም ምንም ክፍያ የሌለበትንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ፣
በደሙ የዋጀልንን የምስራች ወንጌል ዛሬ እንጨብጥ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ