ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ

ሰው ሰራሽ አእምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን የሰዎችን ስራ ይወስዳል ተባለ
ከሃያ ዓመት በፊት አብዛኛው የምድር ህዝብ በእጅ በሚያዝ ስልክ ብቻ መነጋገር፣ መጻጻፍ፣ ፎቶና ቪዲዮ ማንሳት፣ የሚፈልገውን መገብየት፣ ስለአየር ንብረት መረጃን ማግኘት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ ሙዚቃ መስማት ወዘተ ይችላል ተብሎ ቢነገር ብዙም የሚያምን ሰው አልነበረም።  ከአምስት ዓመታት በፊት ደግሞ የሰው ሰራሽ አእምሮ (ARTIFICIAL INTELLIGENCE) ሰዎች የሚሰሩትን ስራ ሁሉ ይወስዳል ቢባል ብዙው ሰው ይስቅ ነበር። አሁን ግን እዚያ ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህን የሚጠራጠር የተያያዘውን ዜና እና ሌሎችንም ብዙ መሰል ዜናዎችን ማንበብ ይችላል።
የሰው ሰራሽ አእምሮ የሚባለው በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎች የሚሰሩት ኮምፒውተሮችን የሚቆጣጠርና የሚያንቀሳቅስ ፕሮግራም ሲሆን፣ ይህ ፕሮግራም እየተራቀቀ ከመምጣቱ የተነሳ ብዙ ነገሮችን የመማርና የተማረውንም ስራ ላይ የማዋል ችሎታ አለው። ለምሳሌ GOOGLE የሚባለው አገልግሎት፣ FACEBOOK እና ሌሎችም በኮምፒውተርና በዓለም አቀፉ መረብ ላይ የሚሰሩ አገልግሎቶች ይህንን የሰው ሰራሽ አእምሮ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ። የኮምፒውተሮች የማስላት፣ መረጃን የማከማቸትና የማስላት ችሎታ እጅግ እየጨመረ በሄደ መጠን ይህ ቴክኖሎጂም በከፍተኛ ደረጃ እየተራቀቀ መጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለሰው ሊሰሩ አይችሉም ይባሉ ስራዎችን መስራት ጀምሮአል። ከዚያም አልፎ ሰዎች ሰዓታት፣ ቀናትና ሳምንታት ፈጅተው አንዳንዴም ከብዙ ስህተቶች ጋር ይሰሩአቸው የነበሩ ስራዎችን በጥቂት ሰከንዶች ወይም ደቂቃዎች ውስጥ በማከናወን ጊዜንና ገንዘብን እንደሚቆጥቡ በሰፊው እየተነገረ ነው። ብዙ የንግድና የመንግስት ድርጅቶችም ይህን ቴክኖሎጂ በሰፊው ለመጠቀም እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።
ሰው ሰራሽ አእምሮ ዛሬ የሚሰራው በሮቦት ውስጥ ወይም በኮምፒውተሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። ዛሬ እንደ ሰዓት፣ መነጽር፣ ልብስና ጫማ ያሉ በሰውነታችን ላይ የምንለብሳቸው ወይም የምናደርጋቸው ነገሮች፣ የምንነዳቸው መኪናዎች፣ በእጃችን የምንይዛቸው ስልኮች ማቀዝቀዣዎችና ሌሎችም ቁሶች በዚህ ቴክኖሎጂ እየተሞሉ ነው። የዛሬዎቹ የእጅ ስልኮች ተዘግተው እንኳን ሳለ የምንነጋገረውንና የምንሰማውን እያዳመጡ መረጃን ስለሚልኩ በጓዳ ጎድጓዳችን የምንነጋገረው ሳይቀር ለስለላና ለነጋዴዎች ማስታወቂያ አገልግሎት ይውላል። በሰው ሰራሽ የተሞሉት የዛሬዎቹ ሮቦቶች እንግዳ ይቀበላሉ፣ የገንዘብ ሂሳብና የባንክ ስራዎችን ይሰራሉ፣ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ስራዎች ይሰራሉ፣ በየምግብ ቤቱ ምግብ በመስራትና በማቀበል፣ ቡና በማፍላትና በማስተናገድ ያገለግላሉ፣ ፖስታና እቃ ከሻጮች ወደ ገዢዎችና ተገልጋዮች ያደርሳሉ፣ መኪና ይነዳሉ፣ አውሮፕላን ያበራሉ፣ መሳሪያ ይዘው ቤቶችን፣ ህንጻዎችንና ድርጅቶችን፣ ሰው በብዛት የሚንቀሳቀስባቸውን እንደ አውሮፕላን ማረፊያና አውቶቡስ መናኽሪያ ያሉ ስፍራዎችን እንዲሁም የጦር ሰፈሮችን ይጠብቃሉ ፣ ካስፈለገም ሊተኩሱና ሊገድሉም ይችላሉ።
ኬይ ፉ ሊ የሚባሉት የSinovation Ventures ድርጅት መስራችና የታወቁ የቻይና የቴክኖሎጂ ባለሙያ ይህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የሰዎች ልጆች ከሚሰሩአቸው ስራዎች ውስጥ ግማሹን ይወስዳሉ ሲሉ ዜናው እንደቀላል መታየት የለበትም። በዚህ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ስራ የሚነፈገው ህዝብ ብዙ ትምህርት የሌለው ወይም በልምድና በመጠነኛ ስልጠና የሚሰሩ ስራዎችን የሚሰራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡና ከፍተኛ ልምድን ያካበቱ ሰዎችም ናቸው። ታዲያ ያ ሁሉ ከስራ የሚፈናቀለው ህዝብ ምን ሰርቶ ይኖር ይሆን? ያን ያህል ህዝብ ከስራ ተፈናቅሎ የገቢ ምንጩ ከተቃወሰ ወይም ጭራሹኑ ከጠፋስ እነዚያ ይህን ቴክኖሎጂ በማሰማራት ምርትና አገልግሎታቸውን ለመሸጥ የሚፈልጉት ድርጅቶች የሚሸጡት ለማን ነው? ደግሞስ እየዋልን ስናድር ይህ ቴክኖሎጂ ለሰው አለቃ ከመሆን የሚከለክለው ነገር የለም። ዛሬ እንደ ካናዳ ባሉት በሰለጠኑት አገሮች ልጆቻችን ገና ማንበብና መጻፍ እንኳን ጠንቅቀው ሳያውቁ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ኮምፒውተር ፕሮግራም ስለማድረግ (CODING) እንዲማሩ ተደርጓል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆቻችንን በትምህርት ቤት የሚጠብቁ ሮቦቶች ቢሰማሩ ወይም የሚያስተምሩአቸው በዚህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የተሞሉ ሮቦቶችና ሌሎች ቁሶች እንደሚሆኑ ብዙም አያጠራጥርም።
ይህ ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር ቢኖረውም ለሰው ልጅ ህልውና እጅግ ያሰጋል የሚሉ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። ዋነኛው አደጋ፣ ይላሉ እነዚህ አዋቂዎች፣ ይህ ቴክኖሎጂ ያለገደብ ራሱን በራሱ ማስተማር፣ ራሱን መልሶ መፍጠርና ማባዛት ወይም ለሚሰራው ሁሉ የሰውን ፈቃድ በመጠየቅ ፈንታ ለራሱ ስልጣንን መስጠት የተማረ ወይም የለመደ እንደሆነ ነው። ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ከሄደ ደግሞ ይህ አይሆንም ሊባል አይችልም ይላሉ ብዙ ታዛቢዎች።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዘመንና ይህ ቴክኖሎጂ እንደሚመጣ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ገልጾአል። የተገለጸላቸውን ነገር ለኛ ጽፈው የተውልን የጌታ ነቢያትና ሃዋርያት ይህን ቴክኖሎጂ የሚመስል ነገር በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጣና እጅግ እንደሚበዛ፣ የሰው ልጆችም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ከሚኖራቸው እምነት የተነሳ ሰይጣን ብዙው የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንደ አምላክ እንዲቀበለውና እንዲያምነው እንኳን ለማድረግ ሊጠቀምበት እንደሚችል ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 13 ቁጥር 11 እስከ 18 ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚገለጸው ሃሰተኛው ነቢይ የዓለም ህዝብ ሃሰተኛውን ክርስቶስን እንዲያምኑ ለማድረግ ሰዎች ለሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልን እንዲሰሩ እንደሚያዝና ለዚያም ምስል እስትንፋስ እንደሚሰጠው ይናገራል። እስትንፋስ የሚሰጠው የሃሰተኛው ክርስቶስ ምስልም አፉን ከፍቶ በመናገር ሰዎች ሁሉ ለሃሰተኛው ክርስቶስ እንዲሰግዱ ያዝዛል፣ የማይሰግዱትንም ሁሉ ያስገድላል። ከአስር ዓመታት በፊት እንኳን ብዙ አሿፊዎች ይህን ክፍል ሲያነቡ ቅዥት ነው ወይም ደግሞ የክፉ መናፍስት ስራ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ይሉ ነበር። በእርግጥ ሃሰተኛው ክርስቶስም ሆነ ሃሰተኛው ነቢይ የሚያደርጉት ሁሉ ከጥልቁ የሚወጣ የዲያብሎስ ስራ ነው። ነገር ግን፣ ምን ያህል የጎላ ወይም እንዴት መሆኑን አናውቅም እንጂ በሰው እጅ የተሰራው ይህ ቴክኖሎጂም (ሰው ሰራሽ አእምሮ ወይም AI) በመጨረሻው ዘመን የትንቢት ፍጻሜ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢትን የሚያጠኑ ሊቃውንት ይስማማሉ። ሰው ሰራሹ አእምሮ ዛሬም ቢሆን ህይወታችንን በብዙ መንገዶች እየተቆጣጠረ እንዳለ አንዘንጋ። ቴሌቪዥኑ የምናይ የምንሰማውን ጆሮ ጠቢ፣ የእጅ ስልኩ የወጣን የገባንበትን፣ የሰማን የተነፈስነውን አሾክሿኪ፣ መኪናችን ከሰማይ ሳተላይት ጋር ተያይዞ የወጣን የገባንበትን ሁሉ የሚያሳብቅ፣ የባንክ ካርዳችን የምንበላውን የምንጠጣውንና የምንለብሰውን ሳይቀር የሚያቀብል ነው። መረጃ ፈልገን በኮምፒውተራችን GOOGLE ላይ ጉድ ጉድ ብንል ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስልካችን ያንን እቃ ግዛ፣ ይህን ፊልም እይ የሚል የሽያጭ ግብዣን ያመጣልናል። ከቤት ውስጥ አንድ ሰው መኪና ከገዛ በሚቀጥለው ቀን የጎማ ወይም ሌላ የመኪና እቃ ማስታወቂያ በራችን ድረስ ወይም ስልካችን ላይ ይመጣል። በአጋጣሚ አይደለም። ሰው ሰራሹ ቴክኖሎጂ ሳናውቀው ዙሪያችንን ከቦናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የታመንን ሁሉ  ልንፈራ አያስፈልግም። ከዚህ ሁሉ ሰው ሰራሽም ሆነ ምንጩ ከአጋንንት ከሆነ ቴክኖሎጂና አሰራር በሙሉ በምህረቱ፣ ዘለዓለማዊ ኃይሉና ፍቅሩ የከበበን አምላክ አለን። ብርሃናችን ክርስቶስ መጥቶአልና ልንነሳ የተስፋን ወንጌል ላልሰሙ ሁሉ ልናበስር ይገባል። ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ ይህን ልብ እንበል፣ በዓለም ላይ የሚካሄደውን ነገር በሙሉ በቃሉ መሰረት በመረዳት ለሌሎች ብርሃን መሆን የምንችል እኛ ብቻ ነን። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር ህዝብ ለእስራኤል እንዲህ አለ፡ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ አብሪ። እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አህዛብን ይሸፍናል፣ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፣ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አህዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገስታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።” ኢሳ 60፡1፥3። እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ በልባችን ያበራው የወንጌል ብርሃን ለሌሎችም ይብራ!!
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...