እውነተኛው መሲህ፣ የዓለምን ሁሉ ኃጢዓት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ፣ የእስራኤልና
የአህዛብ ሁሉ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ተገልጿል። ህግና ነቢያት የተናገሩትንና የተነበዩትን በሙሉ ፈጽሞ
ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ በአባቱ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። በተያያዘው ጽሁፍ ላይ እንደምንመለከተው ግን እጅግ ብዙ የአብርሃም
ዘር የሆኑ አይሁድ መሲሁ ገና አሁን ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያልተረዳ ክርስቲያን ይህን ዜና ሲሰማ
ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከተነገሩት ትንቢቶች ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ ስለሆነ ምናልባት አይሁድ ሊመጣ ነው የሚሉት
የተሰቀለውን፣ የሞተውንና ከሞትም በድል የተነሳውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን አይሁድ አሁን ገና መሲሁ
ሊመጣ ነው የሚሉት ክርስቲያኖች የሚያምኑትን ኢየሱስ ክርስቶስን አይደለም። በእነርሱ እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ መሲህ አይደለም።
በፍጹም አይቀበሉትም አያምኑትምም። የሚጠብቁትም የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት ሳይሆን የ”መሲሁን” የመጀመሪያ መምጣት ነው።
ለእስራኤል ሰላምና መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው ተከፍተው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማየትና ማመን እንዲችሉ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ልንጸልይ
ያስፈልጋል።
ዛሬ አይሁድ የሚጠብቁት መሲህ (በእብራይስጥ መሺያክ) እስራኤልን ከጠላቶቿ የሚታደግ
ታላቅ መሪ ነው ብለው የሚያስቡትን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በሚገባ ባልተረዱበት፣ ከሞቱና ከትንሳኤው በፊት በነበረው
ጊዜ የጌታ ሃዋርያትም እምነት ይህን ይመስል እንደነበር ከወንጌሎች እንረዳለን። ስለዚህ ዛሬ ብዙ አይሁድ በሚያምኑት ነገር ልንገረም
አይገባም። ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 5 ቁጥር 43 ላይ “እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም ሌላው በራሱ
ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ” ብሎ ነበር። ስለዚህ እነሱ መሲህ ነው የሚሉትን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መሲህ ሊቀበሉ የግድ
ነው ማለት ነው። እዚህ ጋ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ። እነዚህ ያለንባቸው ቀናት ካላስተዋልን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች
የሚከሰቱበትና የሚናፈሱበት ጊዜ ነው። ክርስቲያኖች የዘመኑ መጨረሻ ቀርቦአልና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመጣ ነው ብለው ይጠብቃሉ።
ብዙ እስላሞችም መሃዲው የሚገለጽበት ዘመን ነው ይላሉ። ሌሎች ብዙ እምነቶችም ሊመጣ ነው ብለው የሚጠብቁት “ታላቅ” መሪ አላቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ቀደም ብሎ በምድር ላይ ስለሚመጣና ዓለምን ሁሉ ስለሚያስት
አንድ “የዓመጽ ሰው” ወይም “የጥፋት ልጅ” ይናገራል። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በበጉ መጽሃፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉት
በምድር የሚኖሩ ሁሉ የሚሰግዱለት ይህ “ሰው” ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፣ ብዙዎችን ያጠፋል ብዙዎችም ይከተሉታል።
ታዲያ በዚህ ዜና ላይ እንደምንመለከተው የአሜሪካው ፕሬዝደንት እንዲመጣ መጸለይ ይገባቸዋል
የተባለው መሲህ የቱ ይሆን የሚለው ጥያቄ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት ተመራማሪዎችን ብዙም ግራ የሚያጋባ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን
ካልተቀበሉና ሌላ መሲህ እንዲመጣ የሚጸልዩ ከሆነ ያ የሚጠበቀው ሌላው “መሲህ” መጽሐፍ ቅዱስ የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ የሚለው
ወይም በተለምዶ ሃሳዊው መሲህ የሚባለው ሰው ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው በሚለው ሃሳብ ላይ ብዙ የትንቢት ምሁራን ይስማማሉ። ይህ
ከሆነ ደግሞ በእርግጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እየተቃረበ ነው ማለት ነው። እንንቃ! በመጠን እንኑር! መጽሐፍ
ቅዱሳችንን እናንንብብ፣ እናጥና! እንጸልይ። በመቅረዛችን ዘይት የመሙያው ጊዜ ሳናውቀው እያለፈብን እንዳይሆንና ጌታችን ሲመጣ በሩ
እንዳይዘጋብን አንዘናጋ። እግዚአብሔር መልካም ነው። ነገር ግን ይህ የጸጋ ዘመን ደግሞ ለዘላለም አይቆይም። በማናስብበት ጊዜ እንደሚመጣ
ጌታ ደጋግሞ ነግሮናል። እንንቃ! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ