ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እውነት መሆኑን የሚያሳይ የቴክኖሎጂ ግኝት

ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እውነት መሆኑን የሚያሳይ የቴክኖሎጂ ግኝት
http://www.dailymail.co.uk/sciencetech/article-4898576/Scientists-transfer-light-sound-waves-world-first.html
የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ኃይል፣ እውቀት፣ ጥበብ፣ ክብርና ግርማ ከሚያሳዩን ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው እርሱ ሁሉን ነገር መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉን ነገር የፈጠረው በአፉ ቃል መሆኑ ነው። ቃልን በመናገር ብቻ ያልነበረውን ነገር ወደ መኖር የሚያመጣ ከእርሱ ሌላ ማንም የለም። በዘፍጥረት 1፡2 ላይ እንደምናየው ጌታ አምላክ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ ምድር ባዶ እንደነበረችና፣ ጨለማም በጥልቁ ላይ እንደነበረ ተጽፎአል። ቁጥር 3 ላይ ስንደርስ ደግሞ ጌታ አምላክ ቃልን ብቻ በመናገር ብርሃንን እንደፈጠረ እናያለን። ይህ ብርሃን እኛ የሰው ልጆችና ፍጡራን ሁሉ ልናየውና ልንጠቀምበት የምንችለው ብርሃን ነው። ይህ ብርሃን የተፈጠረው በመጀመሪያው ቀን ሲሆን፣ የተፈጠረውም ከጌታ አምላክ አፍ በወጣው ቃል ኃይል ብቻ ነው። ጸሃይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ደግሞ የተፈጠሩት በአራተኛው ቀን ነው። ስለዚህ የጌታ የአምላካችን ቃል ነው ብርሃንን የፈጠረው።
ብርሃን እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ልጅ የሰራው ቴክኖሎጂ ግን ብርሃንን ገርቶ በሚገባ ሥራ ላይ ማዋል ያልቻለበት ዋነኛ ምክንያት ብርሃን እጅግ ፈጣን መሆኑ ነው። ብርሃን በአንድ ሰከንድ ውስጥ ከ 299,792 ኪሎሜትር በላይ ይሄዳል። ማለትም በአንድ ሰከንድ ውስጥ ብርሃን ምድርን ከሰባት ጊዜ በላይ ይዞራታል ማለት ነው። ታዲያ የሰው ልጅ ዛሬ የሚጠቀምባቸው እጅግ ፈጣን የሚባሉ ኮምፒውተሮች እንኳን ይህን ፍጥነት መድረስ ስለማይችሉ ብርሃንን ለመረጃ መሰብሰቢያ፣ ማጠራቀሚያ፣ ለስሌትና ለማሰራጫ ሊጠቀሙበት አልቻሉም። የዛሬዎቹ ኮምፒውተሮች የተሰሩባቸው ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች እጅግ ብዙ ኃይል የሚፈጁ፣ ከፍተኛ ሙቀት የሚያወጡና በማግኔታዊና የኤሌክትሮን ሞገድም በቀላሉ ሊታወኩ የሚችሉ በመሆናቸው አስተማማኝነታቸው ብዙ ጥያቄ አለበት።
ከዚህ መልእክት ጋር በተያያዘው ዜና ላይ እንደምናነበው፣ በአውስትራሊያ የሚገኘው የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ብርሃንን ወደ ድምጽ ለመለወጥ የሚያስችል መሳሪያ ሰርተዋል። ይህ መሳሪያ ብርሃንን ወደ ድምጽ ለአጭር ጊዜ ለውጦ ለማዘግየት መቻሉ ተዘግቦአል። የድምጽ ፍጥነት በሰከንድ 331 ሜትር ነው። ይህ ደግሞ የብርሃንን ፍጥነት 1/1000 ኛ ያህል ስለሆነ፣ አዲሱ ግኝት በሚገባ በስራ ላይ ሲውል የሰው ልጅ የብርሃንን ፍጥነት በመጠቀም አስተማማኝ ያልሆኑትን የዛሬዎቹን የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች ፎቶን በሚባሉት ትንንሽ አካላት በሚሰሩ መሳሪያዎች ሊለውጣቸው ይችላል የሚል ትልቅ ተስፋን ፈጥሮአል።
የዛሬው መልእክቴ ትኩረት ኤሌክትሮኒክስ፣ ፎቶንስ ወይም አዲሱ የቴክኖሎጂ እርምጃ አይደለም። የሰው ልጅ በምርምሩ ብርሃንን ዝግ አድርጎ ወደ ድምጽ በመቀየር ብርሃን መረጃን እንዲሸከምና ስራን እንዲሰራ ማድረጉ ለሁለት ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይመሰክራል። 1ኛ) እግዚአብሔር ቃልን በመናገር ብቻ ብርሃንንና ዓለምን በሙሉ መፍጠሩ (ድምጽን ወደ ብርሃን፣ ቁስ አካላትና ሌሎችም የኃይል መልኮች መለወጡ) እውን መሆኑን፣  2ኛ) መጽሐፍ ቅዱስ የማይሳሳትና እንከን የሌለበት የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን። የእግዚአብሔር ቃል፣ ድምጽ፣ ብርሃንን ስለ ፈጠረው ነው የሰው ልጅ ብርሃንን ወደ ድምጽ በመለወጥ ዝግ ሊያደርገው የቻለው። ስለዚህ በአንድ መልኩ የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያደረጉት የእግዚአብሔርን ሥራ ወደ ኋላ ገልብጠው መቅዳት ነው ማለት  ይቻላል።  በኃጢዓት መታለልና በዲያብሎስ ሽንገላ መንፈሱ የታወረው የሰው ዘር እንደሚገባ አላስተዋለውም እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ገና የሰው ዘር መርምሮ ያልደረሰባቸውንና ሊደርስባቸው የማይችሉ ታላላቅ ምስጢሮችን ያዘለ ነው።
በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ “እግዚአብሔርም ብርሃን ይሁን አለ” ተብሎ የተጻፈው ቃል እውነት ከሆነ ሌላውም የመጽሐፍ ቅዱስ  በሙሉ እውነት ነው ማለት ነው። እነዚያ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ እኛ የሰው ልጆች በበደላችንና በኃጢዓታችን ፈጽመን እንደ ጠፋንና በራሳችንም ጥረት ከዘለዓለም ሞት ልንድን እንደማንችል በግልጽ ይነግረናል። (ገላትያ 2፡16)  ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ታላቅ ፍቅሩ የተነሳ፣ አንድ ልጁን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመላክ፣ እርሱ በመስቀል ላይ ተሰቃይቶ በመሞቱና በመነሳቱ በደሙ የገዛልንን ጽድቅ አምነን እና ተቀብለን የዘለዓለምን ሕይወት እንድናገኝ የምስራቹ ወንጌል ይነግረናል። ይህ ያለንበት በዓመጽ የተሞላ ዓለም ደግሞ ከክፋት ወደ ክፋት እየባሰ በመሄዱና በዚህም መንገድ ለዘላለም መቀጠል ስለማይችል ጌታ አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣ፣ በሕያዋንና በሙታን ላይ እንደሚፈርድና የዘለዓለም መንግስቱን እንደሚመሰርት ብሉይም ሆኑ አዲስ ኪዳን ያስተምሩናል። በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 22 ቁጥር 12 እና 13 ላይ እንዲህ ተጽፎአል፡ “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ፣ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ኦሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።”  ልንሰራው የሚገባ ዋነኛው ስራ ሊያድነን የመጣውን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል ማመን ነው። “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሰራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው። “ ዮሐንስ 6፡28-29 ስለዚህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውና እኛንም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማመን ነውና፣ ይህን ታላቅ ሥራ ዛሬ ነገ ሳንል እንፈጽም። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፣ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ዮሐንስ 3፡18

ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...