ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነስቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፣ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 1ኛ ጴጥሮስ 4፡16

ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነስቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፣ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 1ኛ ጴጥሮስ 4፡16


በምእራቡ ዓለም የሚገኙ ብዙዎች ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያውቁት ይልቅ፣ ስለ ፊልሞች፣ ዘፋኞች፣ ተዋናዮችና ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች የሚያውቁት ይበልጣል። የብዙዎች የክርስትና እምነትም የሚወሰነው በሳምንት አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ጊዜ በጸሎት ቤት ወይም በቴሌቪዝንና በሬድዮ በሚሰሙት ላይ ነው። የቴሌቪዥን፣ ሬድዮ፣ ሲኒማ ቤት፣ ኢንተርኔትና ኮምፒውተር መምጣት ብዙ መልካም አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም፣ ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ቁጭ ብሎ ከማንበብና የወንጌልን እውነት በቀጥታ ከመረዳት ይልቅ በነዚህ መገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡትን ብቻ ቁጭ ብሎ በመመልከት መንፈሳዊ ህይወታቸውን የሚገነቡ ይመስላቸዋል። በትክክለኛ መንገድ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስተምሩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ገንቢ አገልግሎት አላቸው። ነገር ግን እያንዳንዱ ማንበብ የሚችል ክርስቲያን የሰማውን ሁሉ ከመቀበሉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እውነቱን መፈተንና መመርመር ያስፈልገዋል። አስተማሪና የቤተክርስቲያን መሪ የሆነውን ጢሞቲዎስን እንኳን ሐዋርያው ጳውሎስ “እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ”  ይለዋል። 1ኛ ጢሞቲ 4፡13  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የዘመኑን አዋቂ ነን ባዮች ሰዱቃውያንን “መጻህፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማታውቁ ትስታላችሁ” አላቸው። ማቴዎስ 22፡29-33
ከዚህ መልእክት ጋር ከተያያዘው ሪፖርት እንደምትመለከቱት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ነን የሚሉ ብዙ የአሜሪካ የውሸት አስተማሪዎችና የውሸት መጋቢዎች በግልጽ የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃወም ትምህርትን እንደ እውነት ለማስተማርና ተከታዮቻቸውም እንዲቀበሉት ለማድረግ ተስማምተው ውል ፈርመዋል። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ተብሎ በግልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ሳለ፣ ሰው ወንድና ሴት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ጾታዎችም ሊኖሩት  ይችላሉ፣ ሰው ሲፈልግ ወንድ ሲፈልግ ሴት፣ ሳይፈልግ ደግሞ ከሁለቱም የተለየ፣ ወይም ሁለቱንም ወይም ምንም ጾታ የለኝም ማለት ይችላል፣ ጋብቻ ደግሞ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ ሳይሆን ሰዎች እንደ ፈለጉት ሊያደርጉት የሚችሉ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም መቀበል አለባት የሚል ትምህርትን የሚያጸድቅ ቃል ኪዳንን ተፈራርመዋል። በዚሁ በፈረንጆቹ አመት የካናዳ መንግስትም አንድ ህጻን ሲወለድ  ወንድ ወይም ሴት ብቻ ሳይሆን ጾታው ያልተወሰነም ሊሆን ይችላል ብሎ፣ በትውልድ መረጃ እና በፓስፖርት ላይ እንኳን ወንድም ሴትም ያልሆነ የሚባል ሶስተኛ ጾታን ፈጥሮአል። ከላይ የተጠቀሱት ሃሰተኛ አስተማሪዎች ደግሞ ከዚህም አልፈው ተርፈው የነርሱን የመርገም ፍልስፍናና ትምህርት እንደ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ መገለጽ በማቅረብ፣ እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምሩትን ክርስቲያን መሪዎችና አስተማሪዎች ራእይ የሌላቸውና ኋላ ቀሮች ናቸው በማለት በግልጽ እያሳጡ ይገኛሉ።
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፍቅር የቀመሱና የእግዚአብሔርን ቃል ተረድተው ለጌታ በመታዘዝ ሕይወት የሚመላለሱ ክርስያኖች ሁሉ በዚህ ዜና ሊደነግጡ አይችሉም። ምክንያቱም ይህ የትንቢት ፍጻሜና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓቱ ስለተቃረበ የግድ ሊሆን የሚገባው ነገር ነው። ነገር ግን ማንም የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። ዛሬ የሐሰተኛው ክርስቶስ መንፈስ እንደ ድሮው በስውር ሳይሆን በግልጽ በምድር ላይ እየሰራ ነው። በ2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 2 ላይ እንደ ተጻፈው መቼ ለይቶለት እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚቀመጥ ቀኑን ባናውቅም፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው እያሉ የእግዚአብሔርን ቃልና መሰረታዊ የተፈጥሮ ህግጋትን  የሚጻረሩ ነገሮችን ክርስቲያኖች እንዲቀበሉ የሚያስተምሩ እነዚህ የሃሰተኛው ክርስቶስ መንገድ ጠራጊዎች መሆናቸው አጠራጣሪ አይደለም። ምክንያቱም ያ ዐመጸኛ የመገለጹ አንዱ ምልክት የእግዚአብሔርን ህግጋት ለመለወጥ መሞከሩ ነው። ትንቢተ ዳንኤል 7፡25።
እንንቃ ! መጽሐፍ ቅዱሳችንን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስር ሆነን እናንብብ እና እናጥና። ከእውነተኛ ክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻችን ጋር ያለንን ህብረት እናጠንክር። የምንሰማውና የምናምነው ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚስማማ መሆኑን እናረጋግጥ። እምነትና በክርስቶስ ደም የታጠበ በጎ ህሊና ካለን ከቃሉ ቃር የሚጻረረውን የሃሰትና የአጋንንት ትምህርት መለየት እንችላለን። ይህ ወቅት ግን የትእግስትና የጽናት ጊዜ ነው። በእውነተኛ ክርስቲያን ላይ ያለው ሰልፍና ጦርነት ዛሬ የሚመጣው ከሩቅ ሳይሆን በተያያዘው ሪፖርት ላ  እንደምታነቡት ክርስቲያንና መሪዎች ነን ከሚሉ ነው። እግዚአብሔር ግን ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል። ከእግዚአብሔር በክርስቶስ ዳግም የተወለደም ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ሆኖ ስለሚመሰክርለት የእግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል። ከሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ከተናገረ፣ እኛ ደግሞ የሚታየውን ሁሉ እያየንና እየሰማን በእርግጥም ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነስቶ የሚጀመርበት ጊዜ መድረሱን እናውቃለን።
ልባችን አይታወክ። ሌሊቱ ሊነጋ ሲል ጨለማው ይከብዳል እንዲሉ፣ በምድር ላይ ዓመጻው ይክበድ እንጂ፣ የነገስታት ንጉስና የጌቶች ጌታ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት ከተፍ ይላል። የዓለም መንግሥት ሥልጣንም ሁሉ የእርሱ ሊሆን ቀኑ ቅርብ ነው።  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቅንነት በሚወዱና በሚያመልኩት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ይሁን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...