የካናዳ ሴኔት (ፓርላማ) ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በማመኑ፣ በተፈጥሮ ህሊናውና በባህሉ የማይቀበለውን ፍትወተ ስጋ መቃወምን ወንጀል የሚያደርግ ህግ አጸደቀ።

በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የምናምን ክርስቲያኖች በካናዳና በዓለም ዙሪያ እየሆኑ ያሉትን ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር መመልከት ከቻልን በእርግጥም በኖህ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውኃ የሚመስለው የመጨረሻው ዘመን ዓመጽ አንገታችን አጠገብ እየደረሰ እንዳለ እንረዳለን።

ባለፈው ሳምንት በኦንታሪዮ የልጆችን መብት መጠበቅ በሚል ሰበብ የብዙ ክርስቲያኖችንና ሌሎች ካናዳውያን ወላጆችን መብት የሚጋፋና መንግስት ተቀበሉ የሚለውን ፍልስፍና፣ ከፈጣሪ ህግ ጋር የሚቃረኑና አብዛኛው ዓለም (ኢትዮጵያ ሃገራችንም ጭምር) የማይቀበላቸውን ፍትወተ ስጋና ሰው ፈጠር “ጾታዎች” ከማይቀበሉ ወላጆች ላይ ልጆቻቸውን ለመቀማት ስለወጡ ህጎች የወጣ ዜናን አካፍዬ ነበር። የዛሬው ደግሞ ከዚያም የባሰና እጅግ የሚያስፈራ ነው። የካናዳ ሴኔት በዚህ ሳምንት በከፍተኛ ድምጽ ያሳለፈው ህግ ማንኛውም ካናዳዊ ሰው በግል ህሊናው፣ በሃይማኖቱና በባህሉ የማይቀበላቸውን ሃሳቦች በግድ ካልተቀበለ በስተቀር “የጥላቻ” ንግግር ተናግረሃል ተብሎ ወንጀለኛ እንደሚሆን የሚደነግግ ህግን አውጥቶአል። የካናዳ መንግስትና ይህን የሚደግፉት የዜና አውታሮች በሙሉ ዜና ብለው የሚነግሩን ግን ህጉ የወጣው አናሳ የሆኑ ሰዎችን መብት ለማስከበር እንደሆነ ነው። ይህ ግን በመርዙ ላይ ማርን ከመቀባት የተለየ አይደለም። ይህን ህግ ሴኔቱ አሳልፎታል። በንግስቲቱ ተወካይ ጸድቆ ህግ ሆኖ ከወጣ (ይህም የማይቀር ይመስላል) ማንኛውም ሰው በተፈጥሮአዊ ህሊናው፣ በእምነቱና፣ በባህሉ የሚያምንበትንና አብዛኛው የሰው ዘር የሚያምንበትን ነገር ጥሎ እንደ አሻንጉሊት መንግስት ያዘዘውን ነገር ብቻ ነው መናገር የሚችለው። ይህ ምን ማለት ነው? ባለፉት አስርና ሃያ ዓመታት የፈለግነውን ዓይነት ፍትወተ ስጋ መፈጸም መብታችን ስለሆነ ይከበርልን የሚሉ ወገኖችን ሰብዓዊ መብት እናስከብራለን በሚል ሽፋን ብዙ ህጎች ሲወጡ ከርመዋል። ብዙ ክርስቲያኖችም በየዋህነትና መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው በሰውነቱና በህይወቱ ላይ የፈለገውን (መንግስተ ሰማያትን ወይም ሲኦልንም ጭምር) መምረጥ ይችላል ብለው በማመን እነዚህ ሁሉ ህጎች ሲወጡ ብዙም ተቃውሞ አላሳዩም። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያንም ሃይማኖት በሰው ህይወትና በባህላችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጥበትና ከሚከበርበት አገር ስለመጣን እንዲህ ያለ ህግ እንዴት በካናዳ ሊወጣ ይችላል ብለን እናስባለን። የሚካሄደውንም ነገር መረዳት የምንፈልገው ከፖለቲካ አንጻር ይህ የሊበራሎች ነው፣ ይህ ደግሞ የኮንሰርቫቲቭ ነው እያልን ነው። ጉዳዩ ግን በየጊዜው ከሚቀያየረው ፖለቲካ በላይ ነው። መንፈሳዊ ነው። ስለ ሰው ዘር የወደፊት መቀጠል ነው። ጉዳዩ በወንድና ወንድ ወይም ሴትና ሴት መካከል ስለሚፈጸም ፍትወተ ስጋ ብቻም አይደለም።
የእኔን መብት እስካልነኩ ድረስ እንደፈለጋቸው የሚለው አስተሳሰብ ብዙ ሰዎች የሚያምኑበት ነው ስንል ኖረናል። እኔም ብዙ ጊዜ እንዲህ ብያለው። ምክንያቱም ይህ አስተሳሰብ፣ ሰዎች በግል ህይወታቸው የሚፈልጉትን ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያማከለ ነው ። በየደረጃው ያሉ የካናዳና አንዳንድ የሌሎች መንግስታት ባለስልጣኖች የሚከተሉት መመሪያ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ደግሞ አብዛኛው ዓለም የሚከተለውን የተፈጥሮን ህግ ሳይሆን እነሱ ባሉበት በመንግስት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዙ ሰዎች የሚያራምዷቸውን የፖለቲካ ዓላማዎች ነው። እነዚያ ዓላማዎች ደግሞ ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን እውነቶች የሚጻረሩ ናቸው። ዲሞክራሲ ተብሎ ተመርጠናል ተብለው ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሚሰሩት ስራ ግን ህዝቡ የሚሻውን ሳይሆን ህዝቡ ራሱ በነሱ ፍልስፍናና አምላክ የለሽ የኑሮ ዘይቤ እንዲያምን ነው።  ስለዚህ የፈለግነውን ፍትወተ ስጋ ዓይነት (ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት፣ ወንድ ከሴትም ከወንድም ወዘተ) መፈጸም መብታችን ነው የሚሉ ሰዎች የመንግስትን፣ የመገናኛ ብዙኃንን፣ ዋና ዋና የግል ድርጅቶችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አመራር ስለ ያዙ ማራመድ የሚፈልጉትም ያንን የነርሱን ምርጫ ብቻ ነው። የእነርሱ መብት በህግ የተከበረ መሆኑ ብቻ በቂ ስላልሆነ ገና በእግራቸው መሄድ ከጀመሩ ህጻናት መዋያ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የእነርሱን የኑሮ ዘይቤ አልፈልግም፣ አልደግፍም ከዚያም ጋር መተባበር አልሻም እነሱ ግን የፈለጋቸው መሆን ይችላሉ የሚሉ ሰዎችን ሁሉ ሃሳባቸውን በግድ እንዲቀበሉ በአደባባይና የመንግስትንም ስልጣን በመጠቀም እያራመዱ ናቸው። ይህ በአጋጣሚ አይደለም። የእግዚአር የፍርዱ ቀን ስለደረሰ የዓለም የዓመጽ ጽዋ መሙላት ስላለበት ነው።

ብዙዎቻችን የሳትነው ትልቅ ነገር አለ። እነዚህ የፈለግነውን ዓይነት ወሲብ መፈጸም መብታችን ነው (LGBTQ) ፣ ወይም ደግሞ ወንድና ሴት፣ አቶና ወይዘሮ፣ ወይም ልጅ እከሌና ወይዘሪት መባል አንፈልግም (Transgender) የሚሉ ሰዎች ፍላጎት ሌላው ሰው እንደፈለጋቸው ብሎ እንዲተዋቸው ብቻ ሳይሆን ሌላው ህዝብ እነሱ የሚሉትን እንዲልም  ነው። ጾታችንን እንደፈለግነው እንቀይራለን፣ ስንፈልግ ወንድ፣ስንፈልግ ሴት፣ ካልፈለግን ደግሞ በአንድ ጊዜ ወንድም ሴትም፣ ወይም ምንም ጾታ የሌለን ወይም ደግሞ ያልተወሰነና በየጊዜው የሚለዋወጥ ጾታ አለን ይላሉ። ስለዚህ በአዲሱ ህግ መሰረት መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎችም አንዳንድ የእምነት መጽሃፎች ህገ ወጥ ሊሆኑ ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ይላል። የካናዳ መንግስት ይህን ህግ ሲያወጣ ታዲያ አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝና እኔ የማምነው የሰው ዘር ወንድና ሴት እንደሆነ ነው ብሎ ቢናገር ወንጀለኛ ነው ማለት ነው። ይህ ይግ ከወጣ በኋላ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በአደባባይ አንብቦ መስበክና ሰው ወንድና ሴት ብቻ ነው ማለት የጥላቻ ንግግር ስለሚሆን ወንጀል ሊሆን ነው። ይህን ህግ ያወጣው መንግስትና እኛ የዜና አውታሮች ብለው የምንሰማቸው ብዙዎቹ የቴሌቪዝን፣ የሬድዮ፣የጋዜጣ፣ የመጽሔትና የኢንተርኔት ተቋሞች ሁሉ ይህን ቢያስተባብሉ የሚሉት እውነት ነው ማለት አይደለም። ሰይጣን የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ለመለየትና ለማጥፋት የፈጠረው ትልቁ መሳሪያ እውነት የሚመስል ውሸትን ነው። ይህ እውነት የሚመስል ውሸት በመጀመሪያ ሄዋንን ከዚያም አዳምን አታልሎ ዛሬ የሰው ልጅ ወደሚገኝበት መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና ማህበረሰባዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ከተተ። ይህን እውነት የሚመስል ውሸትን የመፍጠር እኩይ መሳሪያ ዛሬ በፖለቲካውና በንግዱ እንዲሁም መንፈሳዊ በሚመስሉና በሌሎችም የህይወት ዘርፎች ውስጥ በግልጽ ይሰራል። ይሰራል ግን አናየውም። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ይህ መሳሪያ ከፈለፈላቸው ሃሳቦች አንዱ “ሰብዓዊ መብት” የሚባል ነው። ከላይ ሲመለከቱት “ሰብዓዊ መብት” መልካም ሃሳብ ይመስላል። ሰብዓዊ መብትን ሁላችንም እንወዳለን። መብታችንም እንዲከበር አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ እንከፍላለን። ችግሩ ያለው ግን “መብት” የሚለው ቃል ላይ ነው። ሰብዓዊ መብትን ለሰብዓዊ ፍጡር የሰጠው ማን ነው። ክርስቲያኖችና ሌሎችም የእምነት ሰዎች ይህን መብት ለሰው የሰጠው እግዚአብሔር ነው ብለን ስለምንቀበል ከበስተኋላው ክፉ ነገር አለ ብለን አናምንም። እግዚአብሔር የለም ወይም ደግሞ ብዙ አማልክት አሉ ብለው የሚያምኑ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን ለሰው የሚሰጠው ሰው ራሱ፣ ማለትም መንግስታትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች እንደምናምነው የእግዚአብሔርን ቃል ስለማይቀበሉ መልካምና ክፉ የሆነውን የሚወስን መንግስት፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንጂ አምላክ አይደለም ብለው ያምናሉ። በእግዚአብሔር ቃል እውነትና በተፈጥሮ ህግ ላይ የተመሰረቱት የካናዳና ሌሎች አንዳንድ መንግስታት ህጎች አንድ በአንድ እየተቀየሩ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምን እውነተኛ ክርስቲያን ሁሉ እንደ ወንጀለኛ በሚቆጠርበት፣ ወንድን ወንድ፣ ሴትን ሴት ብሎ መጥራት በህግ በተከለከለበት አገር ልንኖር የቀረን ጊዜ በቀናት፣ምናልባትን በሳምንታት ወይም ቢበዛ በጥቂት ወራት ይቆጠራሉ። እኛንም ህግ ይጠብቀናል ብለን ካመንን ሃሳባችን መልካም ቢሆንም ዘመኑ መቀየሩ ግን አልገባንም። መንግስታት በህግ ሲተዳደሩ የኖሩባቸው ዘመናትና አገሮች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትንና በህሊና የተጻፉ የተፈጥሮ ህጎችን የሚያከብሩባቸው ብቻ ነበሩ። ዛሬም ከሞላ ጎደል እንዲሁ ነው። አሁን ግን ሰልጥኗል የሚባለው፣ በተለይም ደግሞ ሰሜን አሚሪካና ምእራብ አውሮፓ የስልጣኔው መሰረት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትን ጥሎ በትልቅ ፍጥነት ዓለም ከ2ሺ ዘመን በፊት ወደነበረችበት አምልኮ ጣዖት፣ ገደብ የለሽ የፍትወተ ስጋ አስረሽ ምቺውና ክርስቲያኖችን ወደ ማሳደድ እየገባ ነው። ለራሳችንና ለቤተሰባችን እንጸልይ። ቶሎ ቶሎ ወንጌልን ላልሰሙ እናድርስ። በግል ህይወታችንም እምነታችንን ይዘን መኖር የምንችልባቸውን አማራጮች ማሰቢያው ጊዜ አሁን ነው። ከእንግዲህ በኋላ ግን እንደ ካናዳ ባሉ አንዳንድ ምእራባውያን አገሮች በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ህይወት እየኖርንና፣ በህሊናችን ያለውን እየተናገርንና ልጆቻችንን በፈሪሃ እግዚአብሔር እያሳደግን በነጻነት ለመኖር እንችላለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።  ሁሉም ሲመሰቃቀልና ሲፈራርስ እውነተኛ ክርስቲያን በሰማይ ሃገር አለው። ዳግም እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ ያለው ጌታም አይዘገይም። ተስፋ አንቆርጥም፣ ተስፋችን ግን በፍጹም ከዚህ ምድር በሆኑ ነገሮች ላይ ሊሆን አይችልም። ሰማያዊውን ተስፋ ላላወቁ ወገኖቻችን ግን የዚህን ጌታ ማዳን ቶሎ ቶሎ እንንገራቸው። ጌታ ይባርካችሁና ይጠብቃችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...