መልካም የምዕራባውያን አዲስ ዓመት

መልካም የምዕራባውያን አዲስ ዓመት
የአውሮፓውያኑን የዘመን መለወጫ ለምታከብሩ ሁሉ እንኳን እግዚአብሔር በሰላም ለ2018 አደረሳችሁ። በአዲሱ ዓመት ሕይወታችሁ በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር፣ በበረከትና በስኬት የተሞላ ይሁን !! ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ አዲስ ዓመት እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር ሁሉ የገለጸውን ዘለዓለማዊና አቻ የሌለው ፍቅሩን በኑሮአችሁ ሁሉ የምትለማመዱበት ይሁንላችሁ። ይህ ያለፈው 2017 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተፈጸሙበት፣ በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የሰውን ዘር ህልውና ሊያጠፋ የሚችል የጦርነት ደመና ያንዣበበት፣ ለብዙ አሰርት ዓመታት ተደብቆ የቆየው የወደቁ መላእክትና የኔፊሊም መኖር (UFO, ET ወዘተ በሚባሉ ዘመናዊ መሰል የምስጢር ስሞችም ቢሆን) በአሜሪካ መንግስት በገሃድ የተነገረበትና ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ብዙዎች የእግዚአብሔር ቃል እውነት ወደ ጎን በመጣል የሚያጠፋ ኑፋቄን በግልጽ የተቀበሉበት ዓመት ነበር። እግዚአብሔር ግን ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፣ ይጠብቅማል። በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ማድረግ የሰብዓዊ ፍጡር ልምድ ነው። ተስፋ የሌላቸው ሰይጣንና መላእክቱ እንዲሁም ደግሞ የክርስቶስን ወንጌል እምቢ አንቀበልም ብለው ከዚህ ህይወት ያለፉ ሙታን ብቻ ናቸው። እኔ በግሌ፣ እንዲሁም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶችና የዘመኑን ሁኔታ የሚያጠኑ ክርስቲያኖች፣ 2018 ብዙ ትንቢቶች የሚፈጸሙበት ዘመን ሊሆን እንደሚችል እናምናለን። እስትንፋስ በውስጣችን እስካለ ድረስ ሁላችንም በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ተቀብለን፣ ወንጌልኑ በማመንና በመታዘዝና በኃጢዓታችን ተናዝዘን የእግዚአብሔርን ምሕረት በማግኘት ከሚመጣው ቁጣ ሁሉ ለማምለጥና ወደ ዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንችላለን። ይህ ተስፋ ግን ለዘለዓለም ክፍት ሆኖ አይቆይም። በቅዱሳን ነቢያት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያትም እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ባላወቀውና ባላሰበው ሰዓት ከተፍ ይላል። አሁንም ጭንቅላቱን ብቅ ብቅ ማድረግ እንደጀመረ የስህተትና የማታለል መንፈስ ምድርን ሁሉ እንደ ግርፍ ማጥለቅለቁ የግድ ነው። ስለዚህ ገና ቀን ሳለ ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። በአዲሱ ዓመት በዘመናት ሁሉ ሊታመን የሚችለውንና የማይናወጠውን አንዱን እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ እናድርግ። ነቢዩ ሆሴዕ እንደ ተናገረው “እንወቅ፣ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፣ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል።” ትንቢተ ሆሴዕ 6፡3 ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ ነው። እርሱ ብቻ መንገድና እውነት ሕይወትም ነው። በወልድ በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ወደ አብ መምጣት አይችልም። ማንም በምንም መንገድ አያታልለን። ሰማያትና ምድር ሲናወጡና ሲያልፉ የማያልፈው የክርስቶስ ቃል ነው። “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።” ማቴዎስ 24፡35 መልካም አዲስ ዓመት !! ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 12 ዛሬ ወጥታለች - ዋና ርዕስ "ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? " ሉቃስ 12፡56

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረባቸውና ወንጌልን በሰበከባቸው ዓመታት ሊያዳምጡት ይመጡ የነበሩትን ህዝብ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎችንም ይጠይቃቸው ነበር። የጥያቄዎቹም ዓላማ ሰሚዎቹ የሚያዩትንና የሚሰሙትን እንዲያስተውሉና በመካከላቸው የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን በማወቅ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንዲመጡ ለማድረግ ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
ከጠየቃቸው ከእነዚያ ጥያቄዎች አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 12 ቁጥር 56 ላይ ይገኛል። ይህ ጥያቄ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት ለነበሩትና ክርስቶስን ይሰሙ ለነበሩ ሰዎች እንዳስፈለገው ሁሉ በዚህ ዘመን ለምንኖር ለእኛም ያስፈልጋል። ይህ የእኛ ዘመንስ ምን ዓይነት ነው? ወዴት እያመራ ነው? ፍጻሜውስ ምን ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ልንጠይቅና በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ለነዚህ ጥያቄዎች በቅድሚያ በነቢያት፣ በጌታ በራሱና በሐዋርያት በትንቢት የተሰጡትን መልሶች ልናጤን ይገባል። ዛሬ የወጣችው የመለከት ድምጽ 12 ቁጥር ይህን ጥያቄ በአጭሩ በማንሳት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እጅግ እየተቃረበ መሆኑን ለማስረዳት ትሞክራለች። መልካም ምንባብ።
ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

የአሜሪካ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከ70 ዓመታት በላይ በከፍተኛ ደረጃ በምስጢር ተደብቆ የነበረውን ምንነታቸው የማይታወቁ የበራሪ ዲስኮች እውንነት ለመጀመሪያ ጊዜ አመነ፣ የተያያዘ መረጃንም ለመገናኛ ብዙኃን ለቀቀ።

የአሜሪካ መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከ70 ዓመታት በላይ በከፍተኛ ደረጃ በምስጢር ተደብቆ የነበረውን ምንነታቸው የማይታወቁ የበራሪ ዲስኮች እውንነት ለመጀመሪያ ጊዜ አመነ፣ የተያያዘ መረጃንም ለመገናኛ ብዙኃን ለቀቀ።

 የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ … “ ሉቃስ 8፡17-18


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እጅግ እየተቃረበ ስለመጣ የሰውን ዘር መንፈሳዊ ሕይወት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን የሚሉ ክርስቲያኖችንም ጭምር ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱ ነገሮች በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ቁጥርና ፍጥነት እየተከሰቱ ናቸው። ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመቱ በመለከት ድምጽ መጽሔት፣ በብሎግ እና በዚህ በFacebook በማስተላልፋቸው መልእክቶች በአጭሩ ላቀርብ እንደሞከርሁት አዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ተራማጅ ሃሳቦች፣ ለሰው ሁሉ የሚጠቅሙ ነገሮች በሚል ሽፋን የሰውን ልጅ በማታለልና በመሸንገል የሰው ዘር አንዱን አምላክ እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ እንዳያመልክ በተለይም ደግሞ በአንዱና ብቸኛው የሰው ዘር ሁሉ አዳኝ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳያምን የሚደረጉትና መጽሐፍ ቅዱስ ያጋለጣቸው የጨለማውን ገዥ መንፈሳዊ፣ ሃሳባዊና ቁስ አካላዊ ሴራዎች ዛሬ በአደባባይ በግልጥ መነገር ጀምረዋል።  ከነዚህም ነገሮች መካከል የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች (Flying Saucers, UFOs ወዘተ) የሚባሉት ነገሮችና እነርሱንም የሚያበሩት ፍጥረታት (Aliens, ETs, ወዘተ) ይገኙበታል። በተለይም ደግሞ በመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 4 እና 5 ላይ በነዚህ ርእሶች ላይ ሰፋ ያላ ጽሁፍ ቀርቦአል።
ከዚህ አጭር ጽሁፍ ጋር በተያያዘውና ዋሽንግተን ፖስት በሚባለው የታወቀ የአሜሪካ ጋዜጣና ሌሎችም እጅግ ብዙ የቴሌቪዝን፣ የሬድዮ እና የጋዜጣ እንዲሁም የማህበረሰባዊ መገናኛ ብዙኃን ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደ ግሩም ድንቅ ነገር በአደባባይ እየተዘገበ ያለው በቅርቡ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ከ70 ዓመታት በላይ በምስጢር ተይዞ የነበረውን “የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች” እውንነት ከላይ ከጠቀስኳቸው ከመጨረሻው ዘመን ክስተቶች አንዱ ነው። ዛሬ እንዲህ በአደባባይና በአሜሪካ መንግስት እውንነቱ መገለጥ የጀመረው የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች (UFO) ጉዳይ ባለፉት 70 ዓመታት ፍንጩ በነበራቸውና እውነቱን ለማወቅ በሚፈልጉ በብዙ ተመራማሪዎች ሲጠና የኖረ፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ መጻህፍት የተጻፉበት፣ ብዙ ፊልሞች የተሰሩበት ቢሆንም፣ አሜሪካም ሆኑ ጉዳዩን በምስጢር የያዙት ታላላቆቹ አገሮች እውንነቱን በይፋ ይክዱ ስለነበር እነዚህ ነገሮች እውን ናቸው ብሎ የሚያምን ምሁር፣ ተመራማሪ ወይም በሃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጠ ሰው ሁሉ እንደ እብድ ወይም አላዋቂና የሚቃዥ ተደርጎ ይቆጠር፣ ከክብሩ ይዋረድና በአደባባይም መሳቂያ ይደረግ ነበር። በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀትና መረጃ ያላቸው ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትን የሚያጠኑ ክርስቲያኖች ታዲያ ዛሬ ብቅ ብቅ እያለ ያለው የአሜሪካ መንግስት መረጃ አሁንም ቢሆን ገና ጫፍ ጫፉ ነው ይላሉ። መረጃው ጥቂት በጥቂት ለህዝብ የሚለቀቀውም የዓለም ህዝብ ጉዳዩን እንዲለማመደው ለማድረግና ለከፍተኛውና ለመጨረሻው እውነት መገለጥ ለማዘጋጀት ነው የሚሉም ብዙ ናቸው።
በ1947 ዓም ሮዝዌል ኒው ሜክሲኮ በሚባለው ስፍራ የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች እንደተከሰከሱና እነርሱንም ሲያበሩ የነበሩ ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታት ከፊሎቹ ሞተው አስከሬናቸው፣ ከፊሎቹ ደግሞ በህይወት ተይዘው በህዝብ በማይታወቅና በከፍተኛ ምስጢር በሚጠበቁ በምድር ውስጥ ባሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ውስጥ መቀመጣቸው ብዙ የተጻፈበት ጉዳይ ነው። የአሜሪካ መንግስት ግን ይህ ነገር መሆኑን በመካድ የተከሰከሰው የአየር መመራመሪያ ባሉን ነው ማስተባበሉም በብዙዎች የታወቀ ታሪክ ነው። አንዳንድ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣናት የነበሩና ጉዳዩን በቀጥታ የሚያውቁ እንደ ሌተና ኮሎኔል ፊሊፕ ኮርሶ ያሉ ሰዎች ደግሞ የተከሰከሱትን የማይታወቁ በራሪ ዲስኮችና የሞቱትን ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታትም እንዳዩ በመጻህፍትና በሌሎችም መንገዶች ዘግበዋል። እነዚያ ከዚህ ዓለም አይደሉም የሚባሉትን በራሪ ዲስኮችና ያላቸውን ቴክኖሎጂ በመቅዳትና ከነዚያ ፍጥረታት ጋር በቅርብ በመስራት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ተመሳሳይ በራሪ ዲስኮችንና ሌሎችም መሳሪያዎችን ሰርቶ መፈተሹን ደግሞ ከ1950ዎቹ ጀምረው በስራው የተሳተፉ ወይም ጉዳዩን በቅርቡ የሚያውቁ ሰዎች መረጃውን ሲያወጡ ቆይተዋል። መቼም በዚህ ዘመን ብዙ የምንደነቀው በቴክኖሎጂ ሆነ እንጂ ጉዳዩ ግን የቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም። እነዚያ ከዚህ ዓለም አይደሉም የሚባሉትና በስውር ከአሜሪካ መንግስት የመከላከያ ተቋማት (ምናልባትም ደግሞ እንደ ሩሲያና ቻይና ካሉ ሌሎች ትልልቅ አገሮች) ጋር የሚሰሩት ፍጥረታት እነማን ናቸው? መልሱ ቀላል ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስና ዛሬ በግልጽ በብዙ መጻህፍት የተዘገቡ መረጃዎች ግን ስለነዚህ ፍጥረታት ማንነት ብዙ ፍንጮችን ይሰጡናል።
በአደባባይ እስካሁን ሲነገር የነበረውና አሁንም የምንሰማው የሰው ልጅ በሌሎች ዓለማት ላይ እንደሰው ያሉ ፍጥረታት መኖራቸውን ለማወቅ ገና ምርምር እያደረገ ነው የሚለውን ወሬ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ እንዳየነው እነዚያን የማይታወቁ በራሪ ዲስኮች የሚያበሩ  ከዚህ ዓለም ያልሆኑ ፍጥረታት መኖራቸው ግልጽ ነው። በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት ከዚህ ጋር የተያያዙ ብዙ “ዜናዎች” እና “መረጃዎች” እንደሚቀርቡ አጠራጣሪ አይደለም። ታዲያ ይህ መረጃ ለምን እስካሁን ከህዝብ ተሰወረ? እነዚህ ማንነታቸው የተደበቁ ፍጥረታት ምንድን ናቸው? ዓላማቸው ምንድን ነው? መቼና ለምን ወደዚህ ምድር መጡ ለሚሉት ጥያቄዎች እውነተኛ ወይም ቀጥተኛ መልስን ከመገናኛ ብዙሃን ወይም ጉዳዩን ከያዙት ድርጅቶች መጠበቅ የዋህነት ነው። ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ቀደም ሲል ዓለምን ሁሉ የሚያስት፣ እኔ አምላክ ነኝ የሚልና የዓለም ህዝብ ሁሉ የሚሰግድለት “የዐመጽ ሰው፣ የጥፋትም ልጅ” የሚባለው ሐሰተኛው ክርስቶስ እንደሚገለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ብዙ ትንቢታዊ ምርምሮችና ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሐሰተኛው ክርስቶስ የሚገለጸው የሰው ልጅ እስከ ዛሬ አይቶት በማያውቀው ቴክኖሎጂ ተከቦ እንደሆነ የዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 13ን ማንበብ ብቻ ብዙ ያስተምራል። የዓለም ታዳጊና አዳኝ ነኝ ብሎ የሚገለጸው ያ የዓመጽ ሰውና የጥፋት ልጅ ደግሞ ከሰው ዘር እጅግ ከሚልቅ ስልጣኔና ከምድር ሌላ ዓለም የመጣ ነው ሊባል እንደሚችል ትንቢትን፣ ታሪክን እና ዛሬ እየተገለጸ ያለውን ክስተት በቅርብ የሚያጠኑ ክርስቲያን መሪዎች ማስተማር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ርዕስ እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ለማስረዳትም ብዙ ቦታ የሚፈጅ በመሆኑ መልእክቴን እዚሁ ጋ ለመቁረጥ እገደዳለሁ። የመልእክቴ ዋና ዓላማ ግን አንድ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጽበት ዘመን እጅብ ቅርብ ነው። ምንና እንዴት እንድንሰማ እናስተውል፣ እንጠንቀቅ። በክርስቶስ አምነን ለመዳንና በዓለም ሁሉ ላይ እንደ ጎርፍ ሊመጣ ካለው ጥፋት ልናመልጥ እንድንችል ብርሃን የሆነው የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን አለ። እናንብበው። በመለከት ድምጽ መጽሔት ቁጥር 4 እና 5 ከዚያም ደግሞ በመለከት ድምጽ ብሎግ (http://voice-of-trumpet-amharic.blogspot.ca) በዚህ ርዕስና በአጠቃላይም ስለዚህ ስላለንበት የመጨረሻው ዘመን የሚያስረዱ ብዙ ጽሁፎች ቀርበዋል። ወገኖች እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ የክርስቶስን ወንጌል ስላላመኑ በጨለማ እንዳሉት አናንቀላፋ። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን ባናውቅም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ተመልሶ ይመጣል። መብራታችን በርቶ፣ የእምነት ወገባችንን ታጥቀን ሙሽራውን ለመቀበል እንዘጋጅ። የእስራኤል አምላክ ይባርካችሁ ይጠብቃችሁም። ወንድማችሁ በፈቃዱ አድማሱ።



የሚማሩበትን የኮሌጅ ክፍያና እዳዎቻቸውን ለመሸፈን የአሜሪካና የሌሎቹም ባለጸጎች አገሮች ወጣቶች ሥጋቸውንና ደማቸውን ሳይቀር ለገንዘብ እየሸጡ ነው ተባለ።

የሚማሩበትን የኮሌጅ ክፍያና እዳዎቻቸውን ለመሸፈን የአሜሪካና የሌሎቹም ባለጸጎች አገሮች ወጣቶች ሥጋቸውንና ደማቸውን ሳይቀር ለገንዘብ እየሸጡ ናቸው http://www.zerohedge.com/news/2017-12-10/plasma-pay-broke-millennials-sell-blood-just-survive
አዳጊና ድሆች ከሚባሉት አገሮች የሆንን ብዙዎቻችን ሃብታምና ባለጸጋ በሚባሉት በሰሜን አሜሪካ፣ በምእራብ አውሮፓና በሌሎቹም አዲስ ባለጸጋ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የኢኮኖሚ ወይም የገንዘብ ችግር አለባቸው ብለን አንገምትም። በነዚህ አገሮች የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን፣ የፊልሙ እና የሙዚቃው ኢንዱስትሪም ቢሆን ለሌላው ዓለም የሚያሳዩት በነዚህ አገሮች ያለው ሰው ሁሉ የሞላለት፣ የተረፈውና የተሳካለት እንደሆነ ነው። ለብዙዎች የአሜሪካና የሌሎችም ባለጸጎች አገሮች ወጣቶች ግን እውነቱ ግን ከዚህ እጅግ የራቀ ነው። ከዚህ መልእክት ጋር በተያያዘው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተውና በሌሎችም ብዙ እውነተኛ ዜናዎችን በሚያሰራጩ ማእከላት እንደሚዘገበው ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአሜሪካና እንደ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓንና ካናዳ ያሉ “ባለጸጋ” የሚባሉ አገሮች ወጣቶች ለኮሌጅና ለዩኒቨርሲቲ የሚያስፈልጓቸውን ክፍያዎች ለመክፈልና ሌሎች ወጭዎቻቸውንና እዳዎቻቸውን ለመሸፈን ሰውነታቸውን ለመሸጥ በኢንተርኔት ላይ ራሳቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። ደናግል ሴቶች ልጆች ክብረ ንጽህናቸውን ለከፍተኛ ተጫራች እንደሚያቀርቡም በተደጋጋሚ ይዘገባል። በአሜሪካ ብቻ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የተማሩና እየተማሩ ያሉ ወጣት ሴቶች ራሳቸውን ለገበያ እንደሚያቀርቡ ይታመናል። ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መፈጠር ምክንያቱ በነዚህ ባለጸጎች አገሮች ባለፉት አስር የሚሆኑ ዓመታት የተፈጠረው የኮኖሚ ቀውስ ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱ ሁሉ በጥቂት ሰዎች እጅ መግባቱ፣ ገደብየለሽ ራስ ወዳድነትና ጭካኔ በህብረተሰብ መካከል መስፋፋቱ እንዲሁም ብዙው ሰው፣ ወጣቶችም ጭምር፣ አላስፈላጊ የሆነ የኑሮ እሽቅድምድምም ውስጥ መግባታቸው ነው። የነዚህ ችግሮች ሁሉ ሥር መሰረቱ ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር መጥፋቱና ሰው ሁሉ የኑሮውን ግብ ቁሳቁስን መሰብሰብና ስጋውን ብቻ ማስደሰት ማድረጉ ነው።
ኦክስፋም (OXFAM) የሚባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው የጥናት ዘገባ ላይ እንደሚያሳየው በምድር ላይ ያሉ 62ቱ ከፍተኛ ባለጸጎች ሰዎች ያላቸው ሃብት 3.5 ቢሊዮን ከሚሆነው ግማሹ የምድር ህዝብ ንብረት እኩል ነው። ከ2010 እስከ 2015 ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የነዚህ የ3.5 ቢሊዮን ሰዎች ንብረት በ41 ከመቶ ሲወድቅ፣ የ62ቱ ሰዎች ሃብት ደግሞ በ500 ቢሊዮን ዶላር በመጨመር ወደ 1.76 ትሪሊዮን ደርሶአል። ችግሩ ገንዘብ በተወሰኑ ሰዎች  እጅ መሆኑ ብቻ አይደለም። ለሌሎች ስራ በሚፈጥሩ ነገሮች ላይ በመዋል ፈንታ ጣራ ዘለል በሆኑና ሃብትን በማያፈሩ ከልክ ያለፈ የምቾትና  የቅንጦት ቁሳቁሶች ላይ ስለዋለ ለባለቤቶቹም ሆነ በሚሊዮን ለሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ፍሬን ሳያፈራ መቅረቱም ነው እንጂ። ታዲያ እነዚያ ጥቂት ባለጸጎች ሰዎችም ቢሆን እኮ፣ የእውነተኛ ባለጸግነት ምስጢር ቢገባቸው ኖሮ፣ በገንዘባቸው ደስ ብሎአቸውና በህዝብም መካከል በሰላም ሊኖሩ የሚችሉት የሃብታቸውን ጉልበት የሌሎችን ሸክም ለመቀነስ ሲያውሉት፣ ለሌሎች በሮችን ሲከፍቱበትናና በድሆች ላይ እጅግ የከበደውን የድህነት ቀንበር ሲያቀልሉበት ነበር። አለበለዚያ ግን የነገው ዓለም ተረካቢና መሪ የሆኑት ወጣቶች የሚማሩበትን የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ እዳ ለመክፈልና ለእለት ከእለት ኑሮአቸው ስጋቸውንና ደማቸውን በገንዘብ ለመሸጥ ከተገደዱ የነገው ዓለም ምን ዓይነት ይሆን ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው?  ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈው በሁለተኛው መልእክቱ በምእራፍ 3 ላይ የመጨረሻውን ዘመን (ይህን የእኛን ዘመን) አስቸጋሪና አስጨናቂ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ገንዘብ ወዳድነት፣ ከልክ ያለፈ ራስ ወዳድነትና የገንዘብ ፍቅር እንደሆነ እንዲህ ሲል ያስረዳል።  “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትእቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመስግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችሉሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤”
ነቢዩ ኢሳይያስ “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም፥ አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።” ይላል። ኢሳ 52፡7 በዓለማችን ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ግን እውነቱን ክደን ሁሉ መልካም ነው ካላልን በስተቀር እውነተኛና መልካም የሆኑ ብዙ ዜናዎችን ማግኘት እጅግ ያዳግታል። አይናችንን ወደ እግዚአብሔር ስናነሳ ግን የወንጌል የምስራች ዛሬም ለሰው ሁሉ ያበራል። የዚህ ዓለም ሁኔታ እየከፋ ቢሄድም ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የተላከውን የወንጌልን የምስራች በመቀበልና በማመን የዘለዓለምን ህይወትና የማያልፍን ተስፋ ማግኘት ይችላል። ዓለማችን ያለችበት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ዋና ስር መሰረቱ እኛ የሰው ልጆች ከእውነተኛው አምላክ መራቃቸን ነው። “ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ” ትንቢተ ሆሴዕ ምዕ 6 ቁጥር 1

ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ

ሌላ ሊሳት የማይችል የትንቢት ፍጻሜ፤ "በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፣ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቆስላሉ፣ የምድርም አህዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።" ዘካርያስ 12፡3

ሌላ ሊሳት የማይችል የትንቢት ፍጻሜ፤ "በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፣ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቆስላሉ፣ የምድርም አህዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።" ዘካርያስ 12፡3 http://www.foxnews.com/politics/2017/12/06/trump-officially-recognizes-jerusalem-as-israels-capital-orders-us-embassy-move.html
ያለንበት ወቅት እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት ትንቢቶች የሚፈጸሙበት መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ አያዳግትም።  እያለፈ እያለፈ የሚከሰቱ አንዳንድ እውነታዎች ግን ከሌሎቹ የበለጠ የትንቢት ፍጻሜ ምን ያህል እውን እንደሆነ ያሳያሉ። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1917 ዓም የታላቋ ብሪታንያ መንግስት በዘመኑ ፓለስታይን ተብሎ በሚጠራውና በኦቶማን ቱርክ ግዛት ስር በነበረው ምድር አይሁድ የራሳቸው የሆነ አገር መገንባቱን ትደግፋለች በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አርተር ጀምስ ባልፉር ለዘመኑ የእንግሊዝ አይሁዳውያን መሪ ሎርድ ዎልተር ሮትቻይልድ የጻፉት ደብዳቤ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ተበታትነው የነበሩት አይሁዳውያን ወደጥንታዊ አገራቸው በመመለስ  እስራኤል የምትባለው አገር እንደገና በምድር ካርታ ላይ ብቅ እንድትል በር ከፋች መሆኑ በሰፊው የተዘገበበት ነው። የዚያ ደብዳቤ 100ኛ ዓመት ባለፈው ወር ነበር በብዙ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች ታስቦ የዋለው።  በብዙ ነቢያት በተደጋጋሚ የተነገረውና በ1917 ጭላንጭል የታየበት የአይሁድ ህዝብ እንደገና መሰብሰብ ታዲያ በ1948 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ተፈጽሞ እስራኤል እንደገና ብቅ አለች። አይሁዳውያን ከምድሪቱ ላይ በተለያየ ጊዜ ተነቅለው ወደ ስደት የሄዱት በጥንቱ የሶርያ ግዛት፣ በግሪኮች እና በሮማውያን ወረራዎች እንደሆነ ታሪክ በዝርዝር ቢዘግበውም ዛሬ ብዙ ታሪክ እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ግን በመጽሐፍ ቅዱስና በጥንት ታሪክም የተመሰከረለትን እውነት ለመቀበል አይፈልጉም። ብዙዎቹ እንዲያውም አይሁዳውያን ዛሬ እስራኤል ተብላ በምትጠራው ምድር ላይ ኖረውም አያውቁም በማለት ይክዳሉ። አገሩ ፓለስታይን ህዝቦቹም ፍልስጥኤማውያን ብቻ ናቸው እያሉም በሰፊው ይናገራሉ። እስራኤል እንደ አገር እንደገና ካቆጠቆጠችበት ከ1948 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ነው። እስራኤል እንደ አገር መኖር የለባትም ሲሉ የነበሩና በጦርነትም ሊያጠፉአት ወግተዋት የነበሩ ግብጽና ዮርዳኖስ ከእርሷ ጋር የሰላም ውል ቢፈራረሙም ሌሎች እጅግ ብዙ መንግስታት ግን አሁንም የእስራኤል እንደ አገር መኖር አይዋጥላቸውም። ይህ በዚሁ እንዳለ፣ እኤአ በ1967 ዓም እናጠፋታለን ብለው የተነሱ ብዙ አገሮች በወረሯት ጊዜ ነበር የእስራኤል ጦር የጥንት ዋና ከተማዋ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ የገባው። በ 70 ዓም የፈረሰው የእስራኤል ቤተ መቅደስ በነበረበት ስፍራ ላይ ሮማውያን የአምላካቸውን የጁፒተርን ቤተ ጣዖት አኑረው ከቆዩ በኋላ እስልምና በተስፋፋበት ዘመን ደግሞ ሁለተኛው ኡመር በሚባለው ከሊፍ ተጀምሮ በ705 ዓም የተሰራው አል አቅሳ የተባለው መስጊድና the Dome of the Rock የሚባለው ህንጻ ስላሉባት ኢየሩሳሌም የእስልምና እምነት ሶስተኛዋ ቅድስት ቦታ ናት የሚለው ስያሜ ባለፉት ምዕተ ዓመታት ታዋቂነትን አግኝቶአል።  ስለዚህም የዘመኑ ታላቅ አገር አሜሪካም ብትሆን ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በማለት ከመቀበል እስካሁን ታቅባ ከቆየች በኋላ የእስራኤል ጦር ወደ ከተማይቱ በገባ በ50ኛው ዓመት ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በማለት አሜሪካ ማወጇ አጋጣሚ አይደለም። 50 ዓመት አንድ ኢዮቤልዩ ነው። ከ1917 እስከ 1967 አንድ ኢዮቤልዩ ሲሆን ከ1967 እስከ 2017 ደግሞ ሁለተኛ ኢዮቤልዩ ነው። እስራኤል እንደገና አገር ሆና ከተመሰረተችም በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ላይ 70 (ሰባ) ዓመት ይሆናል። የሰው እድሜ ሰባ ወይም ሰማንያ ከዚያም ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው ተብሎ ተጽፎአል። (መዝሙር 90፡10) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራንና የፍጻሜው ተከታታይ አጥኝዎች ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" ማቴ 24፡34 በማለት የተናገረው በ1948 እስራኤል እንደገና ስትመሰረት የተወለደው ወይም የነበረው ትውልድ የዘመኑን መጨረሻ፣ ምናልባትም የሃሰተኛውን ክርስቶስ መገለጥ ወይም የጌታን ዳግም ምጽዓት ያያል ለማለት ሊሆን ይችላል ብለው ያስተምራሉ። ጌታ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር ማንም እንደማያውቅ ተጽፎአል። ነገር ግን ያለንበት ዘመን ወደ ጌታ መምጣት ከመቼውም የበለጠ  እጅግ የቀረብንበት ጊዜ ነው። በመጀመሪያው ላይ እንደተጠቀሰው፣ ጌታ አምላክ በነቢዩ ዘካርያስ በኩል ሲናገር በመጨረሻው ዘመን የምድር አህዛብና መንግቶቻቸው በኢየሩሳሌም ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እንደሚሞክሩ ቢሆንም እንደሚጎዱ አስጠንቅቆአል። ይህ የሆነበት ምክንያትም ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር የራሱ ከተማ ስለሆነች ነው። ጌታ አምላክ የማደሪያስ መቅደሱን በህዝቡ በእስራኤል መካከል በማድረግ የተገኘባት፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ወደ ዓለም መጥቶ የተሰቀለባት፣ የሞተባትና የተነሳባት ከተማ በዘመኑም መጨረሻ የእግዚአብሔር መንግስት ራስ የሆነው ንጉሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግስባት ዋናዋ ከተማ ስለሆነች ነው። አህዛብ ቢነሱም፣ መንግስታት ቢቃወሙም፣ ሰይጣን አህዛብን ሁሉ በዚህች ከተማ ምክንያት ለማፋጀት ቢነሳሳም የእግዚአብሔር ሃሳብ ግን በሰዓቱ ይፈጸማል። ከዚያ በፊት ግን ለ7 ዓመት የሚገዛው ሃሰተኛው ክርስቶስ ይገለጣል። ለመጀመሪያዎቹ ሶስት ተኩል ዓመታት የውሸት ሰላም በማድረግና በማታለል ይገዛል፣ በዚህችው ኢየሩሳሌም አይሁድ እንደገና በሚሰሩት ቤተ መቅደስ እንደ ጥንቱ መስዋእት ማቅረብ ይጀምራሉ። በሰባቱ ዓመት እኩሌታ ላይ ግን ሃሰተኛው የመስዋእት ስርዓቱን ያቆምና የራሱን ምስል በቤተ መቅደሱ በመትከል አይሁድም ሆነ አህዛብ እንዲያመልኩት ግድ ይላቸዋል። ዳንኤል 9፡27 ዳንኤል 12፡7-12 ። ያ ጊዜ ታላቁ የመከራ ሰዓት ወይም በነቢዩ በኤርምያስ የያእቆብ የመከራ ዘመን የተባለው ይሆናል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በምን ቅደም ተከተል ወይም መቼ እንደሚፈጸሙ ባናውቅም በዜና ላይ ዛሬ የሰማነው ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንዋን አሜሪካ መቀበሏና ከካቶሊኩ ዋና መሪ ጀምሮ ብዙ አገሮች ይህን መቃወማቸው አጋጣሚ አይደለም። የእስራኤል ጦርም በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ የሚያመለክተው የጦርነት መነሳት አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ይህን ሁሉ በዙፋኑ ሆኖ የሚያከናውነው አምላክ ጌታ እግዚአብሔር የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሁሉ አንድም ሳይቀር ይፈጸማል፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ይመጣል፣ ይህ ዓለምና የመንግስታት ስልጣን ሁሉ የክርስቶስ ይሆናል። በዚያም ዘለዓለማዊ መንግስት ስፍራ ያላቸው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዳኑ ብቻ ናቸው። እውነትም መንገድም ሕይወትም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ሰው ሰራሹ የጉግል ኦውቶኤምኤል ናስ ኔት የተባለውን የራሱን ልጅ ፈጠረ (ወይም ወለደ) ተባለ። https://www.dailystar.co.uk/news/latest-news/664713/google-artificial-intelligence-ai-child-NASNet-AutoML

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማና ክብር ከመገለጡ በፊት በምድር ላይ ታላቅ የመከራ ዘመን እንደሚሆን በነቢያት፣ በራሱ በጌታችን እና በሃዋርያትም ደጋግሞ ተነግሮአል። በዚያ በታላቁ የመከራ ጊዜ በምድር ላይ ከሚከሰቱት እጅግ አስፈሪ ነገሮች አንዱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የሰውን ልጅ እርስ በርሱ የሚያፋጁ ጦርነቶች በየቦታው መነሳታቸው ነው። ባለፉት ብዙ ሺህ ዓመታት የሰው ልጅ ከፈጠራቸው የእልቂት መሳሪያዎች ሁሉ የኑክሊየር ቦምብ እጅግ አስከፊው፣ ምድርንና ፍጥረትን ሁሉ የሚያወድም መሆኑ ብዙ ይነገራል። በ1945 ዓም ነሃሴ ወር ላይ ሂሮሺማና ናጋሳኪ በሚባሉት ሁለት የጃፓን ከተማዎች ላይ የተጣሉት የአቶሚክ ቦምቦች የፈጠሩትን ውድመት ያየ፣ ወይም ያነበበ ሰው ይህ መሳሪያ በእርግጥ ምን ያህል አስከፊ መሆኑን ያስተውላል። እጅግ የሚያስፈራው ግን እነዚያ በጃፓን ላይ የተጣሉት ቦምቦች ከዛሬዎቹ ዘመናዊ ተርሞ ኑክሊየር ቦምቦች ጋር ሲነጻጸሩ ምናልባት በሽጉጥ እና በመድፍ ወይም በታንክ መካከል ካለው ልዩነትም የበለጠ ልዩነት ያላቸው መሆኑ ነው። የኑክሊየር ቦምብ እጅግ አስከፊ ቢሆንም፣ የሚቆጣጠሩት ሰዎች እስከሆኑ ድረስ፣ ትንሽም ቢሆን አርፈን በሰላም መተኛት እንችላለን። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውና የሰውን የመማር፣ የማወቅ፣ የማስላት፣ የመወሰንና የማስታወስ ችሎታ በብዙ እጥፍ ይበልጣል የተባለለት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አእምሮ) የሚባለው ቴክኖሎጂ ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ልጅ ከሰራቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ አስፈሪና አጥፊ ሊሆን እንደሚችል ፈሪሃ እግዚአብሔር እንኳን የሌላቸው ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው። ይህ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ያለው ችሎታ ብዙ ህዝብን የሚፈጅ የጦር መሳሪያ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎችንም ለመግደልና ለመፍጀት በራሱ ውሳኔ ማድረግ መቻሉ ነው። ያ ውሳኔ ደግሞ ርህራኄ እና ጸጸት የሌለበት ስለሆነ በዚህ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ስር የሚካሄድ ጦርነት ያለምንም ስህተት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን በአንድ ጊዜ ይፈጃል የሚለው ፍርሃትና ስጋት ታላላቅ የዓለም መሪዎችንም እረፍት የነሳ ጉዳይ ነው። በእጅ የምንይዛቸው ስልኮች፣ በየመንገዱና በየሱቁ የተተከሉ ካሜራዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ መኪናዎችና የቤት እቃዎችም ሳይቀር ፎቶና ቪዲዮ የማንሳት ብቻ ሳይሆን የሰውን ፊት፣ የእጅ አሻራና ድምጽን የመለየት፣ ያለንበትን ቦታ የማወቅና ያለ ፈቃዳችን ለሌሎች ማስተላለፍ ችሎታ ከተሰጣቸው ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ታዲያ ከነዚህ መሳሪያዎች የሚሰበሰበውን መረጃ በኢንተርኔት አማካይነት በመጠቀም የፈለገውን ሰው፣ የሰዎች ስብስብ ወይም ህዝብ አብራሪ በሌላቸው ትንንሽ አውሮፕላኖችና ሌሎችም መሳሪያዎች የማጥፋት ችሎታ አለው። ዳርፓ (DARPA) የሚባለው የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስቴር የምስጢር ፕሮጀክቶች መስሪያ ቤት፣ እንዲሁም ሌሎች የቻይና፣ የሩሲያና ሌሎችም በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ የተራቀቁ አገሮች ድርጅቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመሩ የጦር መሳሪያዎችን በመስራት በእሽቅድምድም ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን በቅርቡ በአንድ የሩሲያ የተማሪዎች ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚሰሩ ሰው ሰራሽ ወታደሮችና ቴክኖሎጂዎች ከኑክሊየር ቦምብ ይልቅ ለሰው ዘር ህልውና እጅግ አስጊ እንደሆኑ ተናግረዋል። የእውቀት ሁሉ ባለቤት የሆነው ልዑል እግዚአብሔር ይህን እኛ ዛሬ የምናየውንና የምንሰማውን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስለሚያውቅ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት የሰውን ዘር  ከምድረ ገጽ ፈጽሞ ሊያጠፉ የሚችሉ ታላላቅ ጦርነቶች እንደሚከሰቱ በነቢያት፣ በልጁ በክርስቶስና በሐዋርያት አማካይነት አስቀድሞ የነገረንና ያስጠነቀቀን። ለዚህም ነው ተግተን እንድንጸልይና መዳናችንን በትልቅ ፍርሃትና ጥንቃቄ እንድንይዝ አዲስ ኪዳን የሚያስተምረን።   በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁጥር 21 እና 22 ላይ ስለዚህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎአል፤  “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፣ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።”  በክርስቶስ በማመን የወንጌሉን ተስፋ የተቀበለ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር የተመረጠ ስለሆነ ሊፈራና ሊደነግጥ አይገባውም። ምክንያቱም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፡ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።” መዝሙር 90(91)፡1  “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” መዝሙር 45(46) ቁ1 እና 2። ነገር ግን በክርስቶስ አምነው ላልዳኑ ሰዎች የንስሃው በር የሚዘጋበት ቀን በየእለቱ እያጠረ ነው። ስለዚህ የራሳችንን መዳን በማሰብ እግዚአብሔርን ስናመሰግን፣ አምላካችን ለነዚያ ላልዳኑ ወገኖቻችን ያለውን ፍቅር ለመናገርና ለመመስከር ያለን ጊዜም እያጠረ እንደሚሄድ እናስብ። ዘማሪው “ነፍሴ ወዳምላኳ፣ ስጋም ወዳፈሩ ሳይመለስ፣ ቶሎ ቶሎ ብዬ ስራዬን ልጨርስ” ብሎ እንደዘመረው ለራሳችን እንጸልይ፣ ለሌሎች እናማልድ፣ ላልዳኑት እንመስክር። ጌታም በነገር ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው። ጌታ ይባርካችሁ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...